‘ከሰማይ ከወረደው እንጀራ’ ጥቅም ማግኘት
እስራኤላውያን ከግብጽ በተአምር ነፃ ከወጡ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በነፃ አውጪያቸው በይሖዋ ላይ እምነት እንደሌላቸው አሳይተዋል። ከዚህ የተነሳ ይሖዋ ለ40 ዓመታት በሲና ምድረ በዳ እንዲንከራተቱ አደረገ። በዚህ ጊዜ ሁሉ እስራኤላውያንና ከእነርሱ ጋር የወጡት መጻተኛ የሆኑ “ብዙ ድብልቅ ሕዝብ” ‘የተትረፈረፈ’ መብልና መጠጥ አግኝተዋል። (ዘጸአት 12:37, 38) መዝሙር 78:23-25 ይህ ሊሆን የቻለበትን መንገድ ይነግረናል:- “[ይሖዋ] ደመናውን ከላይ አዘዘ፣ የሰማይንም ደጆች ከፈተ፤ ይበሉም ዘንድ መናን አዘነበላቸው፣ የሰማይንም እንጀራ ሰጣቸው። የመላእክትንም እንጀራ ሰው በላ፤ ስንቅንም እስኪተርፋቸው ላከላቸው።”
ሙሴ ራሱ መና ይመገብ ስለነበር ስለዚህ ልዩ ምግብ መግለጫ ሊሰጥ ችሏል። ጠዋት “የወደቀውም ጠል ባለፈ ጊዜ፣ . . . በመሬት ላይ እንደ ደቃቅ ውርጭ ሆኖ ቅርፊት የሚመስል ደቃቅ ነገር በምድረ በዳ ታየ። የእስራኤልም ልጆች ባዩት ጊዜ . . . እርስ በርሳቸው:- ይህ ምንድር ነው? ተባባሉ” ሲል ጽፏል፤ ወይም ቃል በቃል በዕብራይስጥ “ማን ሁ?” ይህ መግለጫ እስራኤላውያን ምግቡን “መና” ብለው ለሰየሙበት ቃል ምንጭ ሊሆን ይችላል። ሙሴ እንዲህ ብሏል:- “እርሱም እንደ ድንብላል ዘር ነጭ ነው፤ ጣዕሙም እንደ ማር ቂጣ ነው።”—ዘጸአት 16:13-15, 31፣ የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ
አንዳንዶች እንደሚሉት መና በተፈጥሮ የሚገኝ ምግብ አይደለም። መናውን ለማቅረብ ከሰብዓዊ ባሕርይ ውጭ የሆነ ኃይል አስፈልጎ ነበር። ለምሳሌ ያህል የመና መገኘት በቦታ ወይም በወቅት ላይ የተመካ አልነበረም። መናውን ለነገ ካሳደሩት ይተላና መሽተት ይጀምር ነበር። ሆኖም እያንዳንዱ ቤተሰብ ከሳምንታዊው ሰንበት በፊት እጥፍ አድርጎ የሚወስደው መና ቢያድር አይበላሽም። ስለዚህ መና በማይኖርበት ቀን ማለትም በሰንበት ሊበላ ይችላል። በእርግጥም መና ተአምራዊ ዝግጅት ነበር።—ዘጸአት 16:19-30
መዝሙር 78 ላይ “መላእክት” መጠቀሳቸው ይሖዋ መናውን ለመስጠት በመላእክት ሳይጠቀም እንዳልቀረ ያሳያል። (መዝሙር 78:25) ያም ሆነ ይህ ሕዝቡ አምላክ ላሳያቸው ደግነት አመስጋኝ የሚሆኑበት በቂ ምክንያት ነበራቸው። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ከግብፅ ባርነት ላወጣቸው አምላክ አመስጋኝ ሳይሆኑ ቀርተዋል። እኛም በይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት ላይ የማናሰላስል ከሆነ የእርሱን ዝግጅቶች አቅልለን ልንመለከት አልፎ ተርፎም አድናቆት ላናሳይ እንችላለን። ስለዚህ ይሖዋ “ለትምህርታችን” እንዲሆን የእስራኤልን ነፃ መውጣትና ከዚያ በኋላ የተከናወኑትን ነገሮች መዝግቦ ስላቆየልን አመስጋኝ መሆን እንችላለን።—ሮሜ 15:4
ለእስራኤላውያን የተሰጠ ትምህርት ክርስቲያኖችን ይጠቅማል
ይሖዋ ወደ ሦስት ሚልዮን የሚጠጉ እስራኤላውያንን መና ሲመግብ ሰብዓዊ ፍላጎታቸውን ከማሟላት የበለጠ ነገር በአእምሮው ይዞ ነበር። ‘ትህትና ሊያስተምራቸውና ሊፈትናቸው’ ፈልጎ ነበር። ይህንም ያደረገው ለገዛ ጥቅማቸው ሲል ሊያነጻቸውና ሊያሠለጥናቸው በማሰብ ነው። (ዘዳግም 8:16፤ ኢሳይያስ 48:17) ለዚህ የማንጻትና የማሠልጠን ሥራ አዎንታዊ ምላሽ ቢሰጡ ኖሮ ይሖዋ ተስፋይቱ ምድር ውስጥ ሰላም፣ ብልጽግናና ደስታ በመስጠት ‘በመጨረሻ ዘመን ለእነርሱ መልካም በማድረግ’ ይደሰት ነበር።
ሊያውቁት የሚያስፈልገው ሌላው ዓቢይ ቁም ነገር “ሰውም ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ነገር ሁሉ በሕይወት እንዲኖር እንጂ ሰው በእንጀራ ብቻ በሕይወት እንዳይኖር” ነበር። (ዘዳግም 8:3) አምላክ መና ባይሰጣቸው ኖሮ እስራኤላውያን በረሃብ ያልቁ ነበር። ይህን ደግሞ በሚገባ ያውቃሉ። (ዘጸአት 16:3, 4) አመስጋኝ የሆኑ እስራኤላውያን ሕይወታቸው ሙሉ በሙሉ የተመካው በይሖዋ ላይ እንደሆነ በየዕለቱ ማሳሰቢያ ያገኙ ስለነበር ራሳቸውን ዝቅ አድርገዋል። የተትረፈረፈ ቁሳዊ ነገር ወዳለባት ወደ ተስፋይቱ ምድር ከገቡ በኋላ ይሖዋንም ሆነ የእርሱ ጥገኛ መሆናቸውን የመርሳት አጋጣሚያቸው ዝቅተኛ ይሆናል።
እንደ እስራኤላውያን ሁሉ ክርስቲያኖች ለሕይወት የሚያስፈልጓቸውን ቁሳዊም ሆኑ መንፈሳዊ ነገሮች ከአምላክ እንደሚጠብቁ መዘንጋት የለባቸውም። (ማቴዎስ 5:3፤ 6:31-33) ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ሰይጣን ካቀረበለት ፈተናዎች ለአንዱ መልስ ሲሰጥ በዘዳግም 8:3 የሚገኘውን የሙሴን ቃል ጠቅሶ እንዲህ ብሏል:- “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል።” (ማቴዎስ 4:4) አዎን፣ እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች በቃሉ ውስጥ የሚገኙትን የይሖዋን መግለጫዎች በማንበብ ራሳቸውን ይመግባሉ። በተጨማሪም ከአምላክ ጋር በመጓዛቸውና የመንግሥቱን ፍላጎቶች በአንደኛ ደረጃ በማስቀመጣቸው በሕይወታቸው ውስጥ የእነዚህን መግለጫዎች ጠቃሚ ውጤቶች ሲያገኙ እምነታቸው ይጠናከራል።
ምንም እንኳ እነዚህ ነገሮች የይሖዋ ፍቅራዊ አሳቢነት መግለጫዎች ቢሆኑም ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች ዘወትር በሕይወታቸው ለሚያገኟቸው ነገሮች አድናቆት ሊያጡ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል እስራኤላውያን በተአምር መና ሲሰጣቸው በመጀመሪያ ተገርመውና ተደስተው የነበረ ቢሆንም ከጊዜ በኋላ ብዙዎቹ አጉረምራሚ ሆነዋል። አክብሮት በጎደለው ሁኔታ “ሰውነታችንም ይህን ቀላል እንጀራ ተጸየፈ” ሲሉ አማርረዋል። ይህ ‘ከሕያው እግዚአብሔር መራቅ’ እንደጀመሩ የሚጠቁም አባባል ነበር። (ዘኁልቁ 11:6፤ 21:5፤ ዕብራውያን 3:12 የ1980 ትርጉም) ስለዚህ የእነርሱ ምሳሌ ‘እኛንም የዘመናት መጨረሻ የደረሰብንን ለመገሠጽ’ ሊያገለግል ይችላል።—1 ቆሮንቶስ 10:11
ለዚህ የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ትኩረት መስጠት የምንችለው እንዴት ነው? አንደኛው መንገድ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች ወይም በታማኝና ልባም ባሪያ ክፍል አማካኝነት የሚቀርቡልንን ዝግጅቶች የተለመዱና ተራ ነገሮች አድርገን ባለመመልከት ነው። (ማቴዎስ 24:45) የይሖዋን ስጦታዎች አቅልለን መመልከት ከጀመርን ወይም ለስጦታዎቹ አድናቆት ካጣን ከእርሱ ጋር ያለን ግንኙነት እየቀዘቀዘ ይሄዳል።
ይሖዋ አስደናቂ የሆኑ አዳዲስ ነገሮችን በአንድ ጊዜ የማያዥጎደጉድብን ለእኛው ጥቅም ሲል ነው። ከዚህ ይልቅ በቃሉ ላይ ቀስ በቀስ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄድ ብርሃን እንዲፈነጥቅ ያደርጋል። (ምሳሌ 4:18) ይህ ደግሞ ሕዝቦቹ የሚማሯቸውን ነገሮች ለማዋሃድና በተግባር ለማዋል ጊዜ ይሰጣቸዋል። ኢየሱስ የመጀመሪያዎቹን ደቀ መዛሙርት ሲያስተምር የአባቱን ምሳሌ ተከትሏል። የአምላክን ቃል የገለጸላቸው “መስማት በሚችሉበት መጠን” ወይም አንዳንድ ትርጉሞች እንዳሰፈሩት “መረዳት በሚችሉበት መጠን” ነበር።—ማርቆስ 4:33፤ ከዮሐንስ 16:12 ጋር አወዳድር።
ለአምላክ ዝግጅቶች ያለህን አድናቆት አሳድግ
ኢየሱስ በሚያስተምርበት ጊዜ በመደጋገም ዘዴ ተጠቅሟል። እርግጥ አእምሯችን አንድን ነጥብ ለምሳሌ ያህል አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ወዲያውኑ ሊይዝ ይችል ይሆናል፤ ሆኖም ነጥቡን ማስተዋልና የክርስቲያናዊ ‘አዲስ ሰው’ ክፍል ማድረግ ረዘም ያለ ጊዜ ሊወስድ ይችላል። በተለይ ደግሞ ሥር የሰደደ ዓለማዊ አኗኗርና ዝንባሌ ካለን ይህ ሊከሰት የሚችል ነገር ነው። (ኤፌሶን 4:22-24) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ኩራትን በማሸነፍና ትሕትናን በማዳበር ረገድ ያጋጠማቸው ይኸው ነበር። ኢየሱስ ትሕትናን በተመለከተ በተለያዩ ወቅቶች ለእነርሱ ትምህርት መስጠት አስፈልጎት ነበር። በእያንዳንዱ አጋጣሚ ነጥቡን እንዲያገኙት ያንኑ መሠረታዊ ሐሳብ ከተለያየ አቅጣጫ ያቀረበ ሲሆን በመጨረሻም ሊገባቸው ችሏል።—ማቴዎስ 18:1-4፤ 23:11, 12፤ ሉቃስ 14:7-11፤ ዮሐንስ 13:5, 12-17
በአሁኑ ጊዜ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችና የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች በደንብ የታሰበበት የመደጋገም ዘዴ በመጠቀም ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ ይከተላሉ። ስለዚህ ይህን ነገር አምላክ ለእኛ ያለው የፍቅራዊ አሳቢነት መግለጫ አድርገን እናድንቀው እንጂ የሚሰጠንን ነገር በፍጹም መሰልቸት የለብንም። መና እንደሰለቻቸው እስራኤላውያን መሆን አንፈልግም። በእርግጥም ይሖዋ ያለማቋረጥ የሚሰጠንን ማሳሰቢያዎች ማስተዋል እንድንችል በትዕግሥት ራሳችንን ስናቀርብ በሕይወታችን ውስጥ መልካም ውጤት እናገኛለን። (2 ጴጥሮስ 3:1) እንዲህ ዓይነት የአድናቆት ዝንባሌ መያዛችን በእርግጥ በልባችንም ሆነ በአእምሯችን የአምላክን ቃል ‘እንዳስተዋልን’ ያሳያል። (ማቴዎስ 13:15, 19, 23) በዚህ ረገድ መዝሙራዊው ዳዊት ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል። ዳዊት ዛሬ እኛ የምናገኛቸውን ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ምግቦች ባያገኝም እንኳ የይሖዋ ሕግ “ከማርና ከማር ወለላም ይጣፍጣል” ሲል ገልጿል!—መዝሙር 19:10
የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝ “መና”
ኢየሱስ ለአይሁዳውያኑ “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ” ብሏቸዋል። “አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ ሞቱም፤ ሰው ከእርሱ በልቶ እንዳይሞት . . . ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ . . . እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው።” (ዮሐንስ 6:48-51) ሥጋዊ እንጀራ ወይም መና የዘላለም ሕይወት ሰጥቶ አያውቅም፤ ሊሰጥም አይችልም። ሆኖም በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ እምነት የሚያሳድሩ ሰዎች የኋላ ኋላ የዘላለም ሕይወት በረከት ያገኛሉ።—ማቴዎስ 20:28
ከኢየሱስ ቤዛ ተጠቃሚ የሚሆኑ አብዛኞቹ ሰዎች በምድራዊ ገነት ላይ የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ። ከእነዚህ መካከል ከግብፅ ሲወጡ ከእስራኤላውያን ጋር ተቀላቅለው በወጡት “ብዙ ድብልቅ ሕዝብ” በሆኑ መጻተኞች የተመሰሉት “እጅግ ብዙ ሰዎች፣” ምድርን ከማንኛውም ክፋት ነፃ ከሚያደርገው ከፊታችን ካለው “ታላቅ መከራ” በሕይወት ይተርፋሉ። (ራእይ 7:9, 10, 14፤ ዘጸአት 12:38) እስራኤላውያን ራሳቸው ጥላ የሚሆኑላቸው ሰዎች ደግሞ ከዚያ የበለጠ ሽልማት ያገኛሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ እነዚህ 144,000 የሚሆኑ ሰዎች የአምላክ መንፈሳዊ እስራኤልን እንደሚያዋቅሩ ገልጿል። በሚሞቱበት ጊዜ የሚያገኙት ሽልማት ለሰማያዊ ሕይወት ከሞት መነሳት ይሆናል። (ገላትያ 6:16፤ ዕብራውያን 3:1፤ ራእይ 14:1) በዚያ ኢየሱስ በዓይነቱ ልዩ የሆነ መና ይሰጣቸዋል።
‘የተሰወረው መና’ ትርጉም
ከሞት የተነሳው ኢየሱስ “ድል ለነሣው ከተሰወረ መና እሰጠዋለሁ” ሲል ለመንፈሳዊ እስራኤል ተናግሯል። (ራእይ 2:17) ይህ ምሳሌያዊ የተሰወረ መና አምላክ ለሙሴ በተቀደሰው የቃል ኪዳን ታቦት ውስጥ እንዲያኖረው ያዘዘውን መና ያለበት የወርቅ መሶብ ያስታውሰናል። ታቦቱ የሚቀመጠው ቅዱስተ ቅዱሳኑ በሚገኝበት የድንኳኑ ክፍል ውስጥ ነበር። እዚያ ከዕይታ ውጭ ሆኖ በስውር የተቀመጠ ያህል ነበር። ለመታሰቢያነት የሚያገለግለው ይህ የመና ናሙና ታቦቱ ውስጥ ሲቀመጥ አልተበላሸም። በመሆኑም መና ብልሽት የማይደርስበትን የምግብ አቅርቦት ለማመልከት ተስማሚ ምሳሌ ሊሆን ይችላል። (ዘጸአት 16:32፤ ዕብራውያን 9:3, 4, 23, 24) ኢየሱስ ለ144,000ዎቹ የተሰወረውን መና መስጠቱ የአምላክ መንፈሳዊ ልጆች እንደመሆናቸው መጠን የማይጠፋና የማይበሰብስ ሕይወት ማግኘታቸውን ያረጋግጣል።—ዮሐንስ 6:51፤ 1 ቆሮንቶስ 15:54
መዝሙራዊው “የሕይወት ምንጭ ከአንተ [ከይሖዋ] ዘንድ ነውና” ብሏል። (መዝሙር 36:9) እውነተኛውም ሆነ ምሳሌያዊው የመና ዝግጅት ምንኛ ይህን መሠረታዊ እውነት ያጠናክራል! አምላክ ለጥንቱ እስራኤል የሰጠው መና፣ ለእኛ ሲል በኢየሱስ ሥጋ መልክ ያቀረበልን ምሳሌያዊ መና እንዲሁም በኢየሱስ አማካኝነት ለ144,000ዎቹ የሚሰጣቸው ምሳሌያዊ ስውር መና ሕይወት ማግኘታችን ሙሉ በሙሉ የተመካው በአምላክ ላይ መሆኑን ያስታውሰናል። (መዝሙር 39:5, 7) በትሕትናና በጭምትነት ዘወትር በእርሱ ላይ እንደምንመካ እናሳይ። ይሖዋ በአጸፋው ‘በመጨረሻ ዘመናችን በመልካም ይባርከናል።’—ዘዳግም 8:16
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሁሉም የሰው ልጆች የዘላለም ሕይወት ማግኘታቸው የተመካው ‘ከሰማይ በወረደው ሕያው እንጀራ’ ላይ ነው
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሁሉም ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘታችን ለይሖዋ ማሳሰቢያዎች ያለንን አድናቆት ያሳያል