የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
ክርስቲያኖች ስለ ቁርባን ሊኖራቸው የሚገባው አመለካከት ምንድን ነው?
የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጆን ፖል በቅርቡ “አንድ ካቶሊክ በሥርዓተ ቁርባን ላይ የማይገኝ ከሆነ ቤተ ክርስቲያን ኃጢአተኛ አድርጋ እንደምትቆጥረው በድጋሚ ማረጋገጣቸውን” ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ መጽሔት ዘግቦ የነበረ ሲሆን ለእምነታቸው ያደሩ ካቶሊኮችም በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ። ቁርባን ምንድን ነው? ቤተ ክርስቲያንና መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ይስማማሉን?
ቲንግስ ካተሊክስ አር አስክድ አባውት በተባለው መጽሐፍ ላይ የካቶሊክ ቄስ የሆኑት ማርቲን ጄ ስኮት ቁርባንን እንደሚከተለው በማለት ገልጸውታል:- “ቁርባን ደም አልባ የሆነ የክርስቶስ ሥጋና ደም መሥዋዕት ነው። ክርስቶስ በጎልጎታ በተሰቀለበት ጊዜ ያቀረበው መሥዋዕት ደም የፈሰሰበት መሥዋዕት ነበር። በመሠረቱ ቁርባን በመስቀል ላይ ከቀረበው መሥዋዕት ጋር ተመሳሳይ ነው። ይህ ዘይቤያዊ ወይም ምሳሌያዊ ወይም ደግሞ የተጋነነ አነጋገር አይደለም።” አክለውም እንዲህ ብለዋል:- “ሥርዓተ ቁርባን የአምላክን ልጅ ወደ መሠዊያዎቻችን የሚያወርድና ለአንድ እግዚአብሔር መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርብ ነው።”
ሥርዓተ ቁርባን ቅዱስ ጽሑፋዊ ነውን?
ቅን ካቶሊኮች ሥርዓተ ቁርባን ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርት ነው ብለው ያምናሉ። ለዚህ በማስረጃነት የሚጠቅሱት በተለምዶ የመጨረሻው እራት ተብሎ በሚጠራው ወቅት ላይ ኢየሱስ የተናገራቸውን ቃላት ነው። ኢየሱስ ቂጣና ወይን ለሐዋርያቱ ካከፋፈለ በኋላ ቂጣውን እያመለከተ “ይህ ሥጋዬ ነው” ሲል ወይኑን አስመልክቶ ደግሞ “ደሜ ይህ ነው” ብሏል። (ማቴዎስ 26:26-28) ኢየሱስ እነዚህን ቃላት ሲናገር ቂጣውንና ወይኑን ወደ ራሱ ሥጋና ደም ለውጧቸዋል ብለው ካቶሊኮች ያምናሉ። ይሁን እንጂ ኒው ካተሊክ ኢንሳይክለፒዲያ (1967) እንደሚከተለው በማለት ያስጠነቅቃል:- “‘ይህ ሥጋዬ ነው’ ወይም ‘ደሜ ይህ ነው’ የሚሉትን ቃላት ቃል በቃል መውሰድ አለብን የሚል ድርቅ ያለ አቋም ሊኖረን አይገባም። ... ምክንያቱም ‘መከሩም የዓለም መጨረሻ ነው’ (ማቴ 13:39) ወይም ‘እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ’ (ዮሐ 15:1) እንደሚሉት ባሉት ሐረጎች ውስጥ የገባው [“መሆን” የሚለው ግሥ] አንድን ነገር ለማመልከት ወይም ለመወከል የገባ ነው።” በመሆኑም በማቴዎስ 26:26-28 ላይ ያለው አገላለጽ በመጨረሻው እራት ላይ ቂጣውና ወይኑ ቃል በቃል ወደ ኢየሱስ ሥጋነትና ደምነት እንደተለወጡ እንደማያሳይ ይህ ሰፊ ተቀባይነት ያለው ኢንሳይክለፒዲያ እንኳን ሳይቀር ገልጿል።
አንድ ሰው ኢየሱስ በአንድ ወቅት እንደሚከተለው ብሎ መናገሩን ያስታውስ ይሆናል:- “ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ፤ ... ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው።” (ዮሐንስ 6:51, 54) ኢየሱስን ያዳምጡት ከነበሩት መካከል አንዳንዶቹ የተናገረውን ቃል በቃል በመውሰዳቸው ተጨንቀው ነበር። (ዮሐንስ 6:60) ይሁን እንጂ ኢየሱስ በዚያ ወቅት ሥጋውን ወደ ቂጣ ለውጦት ነበር? ብለን ልንጠይቅ እንችላለን። በጭራሽ አልለወጠውም! ምሳሌያዊ አነጋገር መጠቀሙ ነበር። ራሱን ከቂጣው ጋር ያነጻጸረበት ምክንያት በመሥዋዕቱ አማካኝነት ለሰው ልጆች ሕይወትን ስለሚሰጥ ነው። ዮሐንስ 6:35, 40 በግልጽ እንደሚያሳየው አንድ ሰው የክርስቶስን ሥጋና ደም እንደ በላና እንደጠጣ የሚቆጠረው በኢየሱስ ክርስቶስ ሲያምን ነው።
ሥርዓተ ቁርባን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዋነኛ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት በመሆኑ አንድ ሰው የቅዱሳን ጽሑፎች ድጋፍ ይኖረዋል ብሎ ይጠብቅ ይሆናል። ይሁን እንጂ የቅዱሳን ጽሑፎች ድጋፍ የለውም። ዘ ካተሊክ ኢንሳይክለፒዲያ (የ1913 እትም) የዚህን ምክንያት ሲያብራራ እንዲህ ብሏል:- “የእኛ መሠረተ ትምህርት ዋና መሠረት ... ከጥንት ዘመናት ጀምሮ በሥርዓተ ቁርባን የሚቀርበው መሥዋዕት የመማለጃ ዋጋ እንዳለው የሚገልጸው ሃይማኖታዊ ወግ ነው።” አዎን፣ የሮማ ካቶሊክ ሥርዓተ ቁርባን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሳይሆን በወግ ላይ የተመሠረተ ነው።
አንድ ወግ የቱንም ያህል በቅንነት የሚታመንበት ይሁን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚቃረን ከሆነ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አይኖረውም። ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩትን የሃይማኖት መሪዎች “ስለ ወጋችሁም የእግዚአብሔርን ቃል ሻራችሁ” ሲል ነቅፏቸዋል። (ማቴዎስ 15:6) ኢየሱስ ለአምላክ ቃል ከፍ ያለ ግምት የሰጠ በመሆኑ እስቲ የሥርዓተ ቁርባንን ትምህርት ከቅዱሳን ጽሑፎች አንጻር እንመልከተው።
ክርስቶስ መሥዋዕት ሆኖ የሚቀርበው ምን ያህል ጊዜ ነው?
የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ቁርባን በተከበረ ቁጥር ኢየሱስ እንደሚሠዋ የምታስተምር ሲሆን እንዲህ ሲባል ግን ኢየሱስ ቃል በቃል ይሞታል ማለት እንዳልሆነና መሥዋዕቱም ደም አልባ መሆኑን ትናገራለች። መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ አባባል ጋር ይስማማል? ዕብራውያን 10:12, 14 ምን እንደሚል ተመልከት:- “[ኢየሱስ] ግን ስለ ኃጢአት አንድን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ፣ አንድ ጊዜ በማቅረብ የሚቀደሱትን የዘላለም ፍጹማን አድርጎአቸዋልና።”
ይሁን እንጂ አንድ ቅን የሆነ ካቶሊክ ‘ሁላችንም ብዙ ጊዜ እንበድላለን። ታዲያ ኢየሱስ መሥዋዕቱን ደጋግሞ ማቅረብ አይኖርበትም?’ የሚል ተቃውሞ ያሰማ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው መልስ በዕብራውያን 9:25, 26 ላይ ተመዝግቦ ይገኛል:- “[ክርስቶስ] ራሱን ብዙ ጊዜ ሊያቀርብ አልገባም፤ . . . አሁን ግን በዓለም ፍጻሜ ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጦአል።” ክርስቶስ “ራሱን ብዙ ጊዜ ሊያቀርብ አልገባም” ማለቱን ልብ በል። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ 5:19 ላይ ይህ የሆነበትን ምክንያት ሲያብራራ እንዲህ ብሏል:- “በአንዱ ሰው አለመታዘዝ [በአዳም] ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደ ሆኑ፣ እንዲሁ ደግሞ በአንዱ መታዘዝ [በኢየሱስ] ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ።” የአዳም አንድ የዓመፅ ድርጊት ሁላችንንም ለሞት ዳርጎናል፤ የኢየሱስ አንድ የማዳን ተግባር ደግሞ በመሥዋዕቱ ለምናምን ሁሉ ኃጢአታችን ይቅር እንዲባልልንና ወደፊት ደግሞ የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ የሚያስችለንን መሠረት ጥሏል።
ኢየሱስ አንድ ጊዜም ይሠዋ በተደጋጋሚ ምን የሚያመጣው ለውጥ ይኖራል? ትልቁ ነገር ለኢየሱስ መሥዋዕት ዋጋ ያለን አድናቆት ነው። ይህ እስከ ዛሬ ከተሰጡት ስጦታዎች ሁሉ የሚበልጥ ስጦታ ነው፤ እጅግ ውድና ፍጹም የሆነ ወደፊትም መደገም የማያስፈልገው ስጦታ ነው።
እርግጥ የኢየሱስ መሥዋዕት ሊታወስ የሚገባው ነገር ነው። ይሁን እንጂ አንድን ክንውን በማስታወስና በመድገም መካከል ልዩነት አለ። ለምሳሌ ያህል የጋብቻቸውን ቀን የሚያከብሩ ባልና ሚስት ሥነ ሥርዓቱን ሳይደግሙ የተጋቡበትን ቀን አስበው ሊውሉ ይችላሉ። የይሖዋ ምሥክሮች በየዓመቱ የኢየሱስን ሞት አስበው ይውላሉ፤ ይህንንም የሚያደርጉት ኢየሱስ ባዘዘው መሠረት ለእሱ ‘መታሰቢያነት’ እንጂ እሱን ለመሠዋት አይደለም። (ሉቃስ 22:19) በተጨማሪም እነዚህ ክርስቲያኖች ሕይወታቸውን፣ ድርጊቶቻቸውንና እምነቶቻቸውን ቅዱሳን ጽሑፎች ከሚናገሩት ነገር ጋር በማስማማት ዓመቱን በሙሉ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ከይሖዋ አምላክ ጋር የጠበቀ ዝምድና እንዲኖራቸው ለማድረግ ይጥራሉ።
አብዛኛውን ጊዜ ይህ የአስተሳሰብ ለውጥ ማድረግን የሚጠይቅ ነው። ሆኖም ምሥክሮቹ የሰውን ወግ ሳይሆን የአምላክን ቃል በታማኝነት የሚደግፉ ከሆነ እንደሚባረኩ ስለሚያውቁ ይደሰታሉ። እንዲሁም ወደ ሁለት ሺህ ከሚጠጉ ዓመታት በፊት ለአንዴና ለሁልጊዜው በቀረበው የኢየሱስ መሥዋዕታዊ ደም ካመኑ ከማንኛውም ኃጢአት ያነጻቸዋል።—1 ዮሐንስ 1:8, 9
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በቅዱስ ጊልስ ሥርዓተ ቁርባን ሲካሄድ
[ምንጭ]
Erich Lessing/Art Resource, NY