ትምህርትን ይሖዋን ለማወደስ ተጠቀሙበት
“ከራሱ የሚናገር የራሱን ክብር ይፈልጋል፤ የላከውን ክብር የሚፈልግ ግን እርሱ እውነተኛ ነው።”—ዮሐንስ 7:18
1. የትምህርት ሂደት የጀመረው መቼና እንዴት ነው?
ትምህርት መሰጠት የተጀመረው ከብዙ ብዙ ዘመናት በፊት ነው። ታላቅ መምህርና አስተማሪ የሆነው ይሖዋ አምላክ የበኩር ልጁን ከፈጠረ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የማስተማር ሂደት ተጀመረ። (ኢሳይያስ 30:20፤ ቆላስይስ 1:15) በዚህ ጊዜ ከታላቁ መምህር ትምህርት የሚቀስም አንድ ፍጡር ተገኘ! ኢየሱስ ክርስቶስ ተብሎ የሚታወቀው ይህ ልጅ የአባቱ የቅርብ ወዳጅ ሆኖ ባሳለፋቸው ኅልቆ መሳፍርት የሌላቸው ዘመናት ስለ ይሖዋ ባሕርያት፣ ስለ ይሖዋ ሥራዎችና ዓላማዎች በዋጋ ሊተመን የማይችል ውድ እውቀት ገብይቷል። ከዚያም ኢየሱስ ሰው ሆኖ በምድር ላይ በኖረበት ጊዜ “አባቴ እንዳስተማረኝ እነዚህን እናገር ዘንድ እንጂ ከራሴ አንዳች” አላደርግም ብሏል።—ዮሐንስ 8:28 ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።
2-4. (ሀ) በዮሐንስ ምዕራፍ 7 መሠረት ኢየሱስ በ32 እዘአ በዳስ በዓል ላይ በተገኘበት ጊዜ ምን ዓይነት ሁኔታዎች ነበሩ? (ለ) አይሁዳውያን በኢየሱስ የማስተማር ችሎታ የተደነቁት ለምን ነበር?
2 ታዲያ ኢየሱስ ይህን ያካበተውን ትምህርት እንዴት ተጠቀመበት? ምድራዊ አገልግሎቱን ባከናወነበት የሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል የተማረውን ለሰዎች አካፍሏል። ይህን ያደርግ የነበረው ግን ለአንድ ብቸኛ ዓላማ ነበር። ይህ ዓላማው ምን ነበር? በዮሐንስ ምዕራፍ 7 ላይ የሚገኙትን ኢየሱስ ያስተማረው ትምህርት ከየት እንደተገኘና ዓላማውም ምን እንደሆነ የገለጸባቸውን ቃላት እንመልከት።
3 እነዚህን ቃላት የተናገረበትን ሁኔታና ጊዜ እንመልከት። ኢየሱስ ከተጠመቀ ወደ ሦስት ከሚጠጉ ዓመታት በኋላ፣ በ32 እዘአ የጸደይ ወራት ነበር። አይሁዳውያን የዳስ በዓላቸውን ለማክበር በኢየሩሳሌም ተሰብስበዋል። በበዓሉ የመጀመሪያ ቀኖች ስለ ኢየሱስ ብዙ ነገር ሲወራ ሰንብቷል። በዓሉ በተጋመሰበት ጊዜ ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደሱ መጥቶ ማስተማር ጀመረ። (ዮሐንስ 7:2, 10-14) በዚህም ጊዜ እንደ ሌሎቹ ጊዜያት ታላቅ አስተማሪ መሆኑን አስመስክሯል።—ማቴዎስ 13:54፤ ሉቃስ 4:22
4 ዮሐንስ ምዕራፍ 7 ቁጥር 15 እንዲህ ይላል፦ “አይሁድም፦ ይህ ሰው ሳይማር መጻሕፍትን እንዴት ያውቃል? ብለው ይደነቁ ነበር።” አይሁዳውያን ለምን እንደተደነቁ ገብቶሃልን? ኢየሱስ በማንኛውም የአይሁድ ሃይማኖታዊ አስተማሪዎች ትምህርት ቤት ገብቶ ስለማያውቅ በእነርሱ አስተሳሰብ ያልተማረ ሰው ነበር። ኢየሱስ ግን ያለምንም ችግር ከቅዱሳን ጽሑፎች እያወጣ ማንበብ ይችል ነበር። (ሉቃስ 4:16-21) እንዲያውም ይህ የገሊላ ነዋሪ የሆነው እንጨት ጠራቢ ስለ ሙሴ ሕግ እንኳ ሊያስተምራቸው ችሏል! (ዮሐንስ 7:19-23) ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ?
5, 6. (ሀ) ኢየሱስ የሚያስተምረውን ትምህርት ያገኘው ከየት እንደሆነ የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ባገኘው ትምህርት የተጠቀመበት እንዴት ነው?
5 በቁጥር 16 እና 17 ላይ እንደምናነበው ኢየሱስ “ትምህርቴስ ከላከኝ ነው እንጂ ከእኔ አይደለም፤ ፈቃዱን ሊያደርግ የሚወድ ቢኖር፣ እርሱ ይህ ትምህርት ከእግዚአብሔር ቢሆን ወይም እኔ ከራሴ የምናገር ብሆን ያውቃል” በማለት ገልጿል። አይሁዳውያን ኢየሱስ ከማን እንደተማረ ለማወቅ ፈልገው ነበር። እርሱም ከአምላክ የተማረ መሆኑን በግልጽ ነገራቸው።—ዮሐንስ 12:49፤ 14:10
6 ኢየሱስ ባገኘው ትምህርት እንዴት ተጠቀመበት? በዮሐንስ 7:18 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ኢየሱስ “ከራሱ የሚናገር የራሱን ክብር ይፈልጋል፤ የላከውን ክብር የሚፈልግ ግን እርሱ እውነተኛ ነው፣ በእርሱም ዓመፃ የለበትም” በማለት ተናግሯል። (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) ኢየሱስ ያገኘውን ትምህርት “በእውቀት ፍጹም የሆነውን” ይሖዋን ለማክበር መጠቀሙ ምንኛ የተገባ ነው!—ኢዮብ 37:16
7, 8. (ሀ) ባገኘነው ትምህርት እንዴት መጠቀም አለብን? (ለ) ሚዛኑን የጠበቀ ትምህርት ምን አራት መሠረታዊ ዓላማዎች አሉት?
7 ስለዚህ ከኢየሱስ በጣም አስፈላጊ የሆነ ትምህርት እናገኛለን። ያገኘነውን ትምህርት ራሳችንን ከፍ ከፍ ለማድረግ ሳይሆን ይሖዋን ለማወደስና ለማስከበር መጠቀም ይኖርብናል። ትምህርታችን ከዚህ የተሻለ ጥቅም ሊያስገኝ አይችልም። ትምህርትን ለይሖዋ ክብርና ውዳሴ ለማምጣት ልትጠቀምበት የምትችለው እንዴት ነው?
8 ማስተማር ማለት “በተለይ አንድን ችሎታ፣ ሞያ ወይም ሥራ መደበኛ የሆነ መመሪያና ቁጥጥር የታከለበት ልምምድ በመስጠት ማሠልጠን” ማለት ነው። ሚዛኑን የጠበቀ ትምህርት አራት መሠረታዊ ዓላማዎች ያሉት መሆኑንና በእነዚህ ዓላማዎች በመጠቀም እንዴት ይሖዋን ማወደስ እንደሚቻል እንመልከት። ሚዛኑን የጠበቀ ትምህርት (1) በጥሩ ሁኔታ እንድናነብ፣ (2) ግልጽ በሆነ ሁኔታ እንድንጽፍ፣ (3) በአእምሮም ሆነ በሥነ ምግባር እንድንጎለምስ እንዲሁም (4) የዕለት ተዕለት ኑሯችንን እንድናሸንፍ የሚያስችለንን ተግባራዊ ሥልጠና እንድናገኝ ሊረዳን ይገባል።
በሚገባ ማንበብን መማር
9. ጥሩ አንባቢ መሆን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
9 በአንደኛነት የተጠቀሰው በሚገባ የማንበብ ችሎታ ነው። ጥሩ አንባቢ መሆን ይህን ያህል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔድያ “ንባብ . . . የማንኛውም ትምህርት መሠረት ከመሆኑም በላይ ለዕለታዊ ኑሮ በጣም አስፈላጊ ከሆኑት ችሎታዎች አንዱ ነው። . . . ጥሩ አንባቢዎች የበለጸገና ምርታማ ኅብረተሰብ በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። ራሳቸውም ቢሆኑ ይበልጥ አመርቂ የሆነ ኑሮ ይኖራሉ” በማለት ያብራራል።
10. የአምላክን ቃል ማንበብ እርካታ የሞላበት ሕይወት እንዲኖረን የሚረዳን እንዴት ነው?
10 ንባብ በአጠቃላይ ‘ይበልጥ አመርቂ የሆነ ኑሮ እንድንኖር’ ሊረዳን የሚችል ከሆነ የአምላክን ቃል ማንበብ ምን ያህል የበለጠ ጥቅም ሊያስገኝልን ይችላል! የአምላክን ቃል ማንበብ አእምሯችንና ልባችን ተከፍቶ የአምላክን ሐሳቦችና ዓላማዎች እንድንረዳ ያስችለናል። የአምላክን ዓላማዎችና ሐሳቦች በግልጽ መረዳት ደግሞ ሕይወታችን ትርጉም ያለው እንዲሆን ያስችላል። በተጨማሪም ዕብራውያን 4:12 እንደሚለው “የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፣ የሚሠራም ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው።” የአምላክን ቃል በምናነብበትና በምናሰላስልበት ጊዜ ከመጽሐፉ ደራሲ ጋር ይበልጥ እንቀራረባለን። በሕይወታችን ውስጥ ይበልጥ እርሱን እንድናስደስት የሚያስችለንን ለውጥ እናደርጋለን። (ገላትያ 5:22, 23፤ ኤፌሶን 4:22–24) በተጨማሪም ያነበብናቸውን ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው እውነቶች ለሌሎች ለማካፈል እንገፋፋለን። ይህ ሁሉ ታላቁ መምህር ይሖዋ አምላክ እንዲወደስ ያደርጋል። በእርግጥም የማንበብ ችሎታችንን ከዚህ በበለጠ ሁኔታ እንድንጠቀምበት የሚያስችለን መንገድ አይኖርም!
11. ሚዛናዊ በሆነ የግል ጥናት ፕሮግራም ውስጥ ምን መካተት አለበት?
11 ወጣቶችም ሆንን አረጋውያን በሚገባ ማንበብን መማር ያስፈልገናል፤ ምክንያቱም ንባብ በክርስቲያናዊ ሕይወታችን ውስጥ ከፍተኛ ቦታ አለው። ዘወትር ከምናደርገው የአምላክ ቃል ንባብ በተጨማሪ ሚዛናዊ የሆነ የግል ጥናት ፕሮግራም አውጥተን ቅዱሳን ጽሑፎችን በየዕለቱ መመርመር ከተባለው ቡክሌት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ መመርመር፣ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን ማንበብ እንዲሁም ለስብሰባዎች መዘጋጀት ይኖርብናል። ክርስቲያናዊ አገልግሎታችንስ? ለሕዝብ መስበክ፣ ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራት ጥሩ የንባብ ችሎታ የሚጠይቅ እንደሆነ ግልጽ ነው።
በግልጽ ለመጻፍ መማር
12. (ሀ) በግልጽ መጻፍን መማር አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) በዘመናት ሁሉ ከተጻፉት ጽሑፎች የሚበልጠው ጽሑፍ የትኛው ነው?
12 ሁለተኛው ሚዛኑን የጠበቀ ትምህርት ዓላማ በግልጽ የመጻፍ ችሎታ እንዲኖረን መርዳት መሆን አለበት። መጻፍ ቃላችንንና ሐሳባችንን ለሌሎች ከማስተላለፉም በላይ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉ ያስችላል። ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት 40 የሚያክሉ አይሁዳውያን ወንዶች ከደንገል በተሠራ ወረቀት ወይም በብራና ላይ የቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል የሆኑትን ቃላት ጻፉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) በእርግጥም ይህ ጽሑፍ በዘመናት ሁሉ ከተጻፉት ጽሑፎች የበለጠ ነው! ይህ ቅዱስ ቃል ሳይከለስና ሳይበረዝ እስከ ዘመናችን እንዲደርስ ይሖዋ የመጻፉንና የመገልበጡን ሥራ ይመራና ይቆጣጠር እንደነበረ ግልጽ ነው። ይሖዋ ቃሉ በአፈ ታሪክ መልክ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ሳያደርግ በመጽሐፍ ተጽፎ በማቆየቱ አናመሰግነውምን?—ከዘጸአት 34:27, 28 ጋር አወዳድር።
13. እስራኤላውያን መጻፍ ይችሉ እንደነበር የሚጠቁመው ምንድን ነው?
13 በጥንት ዘመን ማንበብና መጻፍ የሚችሉት በሜሶጶጣሚያና በግብጽ እንደነበሩት ጸሐፊዎች የመሰሉ ልዩ መብት የተሰጣቸው ሰዎች ብቻ ነበሩ። እስራኤላውያን ግን ከሌሎች ሕዝቦች በተለየ ሁኔታ እያንዳንዳቸው ማንበብና መጻፍ እንዲችሉ ይበረታቱ ነበር። ዘዳግም 6:8, 9 ላይ እስራኤላውያን በበራቸው መቃን ላይ እንዲጽፉ የተሰጠው ትእዛዝ ምሳሌያዊ ቢሆንም መጻፍ ይችሉ እንደነበረ ያመለክታል። ልጆች ገና በሕፃንነታቸው ጽሕፈት ይማሩ ነበር። ከጥንቶቹ የዕብራውያን ጽሑፎች አንዱ የሆነው የጌዘር ቀን መቁጠሪያ ተማሪዎች የማስታወስ ችሎታቸውን ያዳብሩበት የነበረ ጽሑፍ እንደሆነ የሚያምኑ ምሁራን አሉ።
14, 15. የመጻፍ ችሎታን ለመጠቀም የሚያስችሉ ጠቃሚና ጤናማ የሆኑ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?
14 ታዲያ እኛ የመጻፍ ችሎታችንን ጠቃሚና ጤናማ በሆነ መንገድ ልንጠቀም የምንችለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ በጉባኤና በትልልቅ ስብሰባዎች ላይ ማስታወሻ በመጻፍ እንደሆነ የታወቀ ነው። አንድ ደብዳቤ፣ “ጥቂት ቃሎችን” ብቻ የያዘ እንኳን ቢሆን አንድን የታመመ ሰው ሊያጽናና ወይም ጥሩ መስተንግዶ ላደረገ ወንድም ወይም እህት ምስጋና ሊገልጽ ይችላል። (1 ጴጥሮስ 5:12) በጉባኤ ውስጥ የሚወደውን ሰው በሞት ያጣ ወንድም ቢኖር የምንጽፈው አጭር ደብዳቤ ወይም ካርድ ስለ እኛ ሆኖ “ሊያጽናናው” ይችላል። (1 ተሰሎንቄ 5:14) እናትዋ በካንሰር ሕመም የሞተችባት አንዲት እህት “አንድ ወዳጄ ጥሩ ደብዳቤ ጻፈችልኝ። ይህን ደብዳቤ ደግሜ፣ ደጋግሜ ስላነበብኩት በጣም ረድቶኛል” ብላለች።
15 የመጻፍ ችሎታችንን ለይሖዋ ውዳሴ ለማስገኘት ከምንጠቀምባቸው ግሩም መንገዶች አንዱ ደብዳቤ በመጻፍ ስለ መንግሥቱ መመሥከር ነው። ራቅ ባለ አካባቢ ብቻቸውን ከሚኖሩ ፍላጎት ያሳዩ አዳዲስ ሰዎች ጋር ደብዳቤ መጻጻፍ አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜ አለ። በበሽታ ምክንያት ለጊዜው ከቤት ወደ ቤት ሄዳችሁ መስበክ ሊቸግራችሁ ይችላል። በዚህ ጊዜ በአካል ቀርባችሁ የምትናገሩትን ነገር በደብዳቤ መግለጽ ትችላላችሁ።
16, 17. (ሀ) በደብዳቤ የመንግሥቱን ምሥክርነት መስጠት ዋጋ እንዳለው የትኛው ተሞክሮ ያሳያል? (ለ) ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ተሞክሮ ልትናገር ትችላለህን?
16 አንድ ተሞክሮ እንመልከት። ከበርካታ ዓመታት በፊት አንዲት እህት አንዲት ሴት ባልዋ እንደሞተባት ጋዜጣ ላይ አነበበች። ወዲያውም ደብዳቤ ጽፋ ስለመንግሥቱ መሠከረችላት። ምንም መልስ አላገኘችም። ከ21 ዓመት በኋላ ግን በኅዳር ወር 1994 ይህች እህት ደብዳቤ ጽፋላት ከነበረችው ሴት ልጅ የተጻፈ ደብዳቤ ደረሳት። የሴትዮዋ ልጅ እንዲህ ስትል ጻፈች፦
17 “በሚያዝያ ወር 1973 አባቴ በመሞቱ እናቴን ለማጽናናት ደብዳቤ ጽፈሽ ነበር። በዚያ ጊዜ የዘጠኝ ዓመት ልጅ ነበርኩ። እናቴ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀምራ ነበር። ቢሆንም እስከ አሁን ድረስ የይሖዋ አገልጋይ አልሆነችም። ይሁን እንጂ የእርስዋ ጥናት መጀመር ከእውነት ጋር እንድተዋወቅ አስችሎኛል። በ1988፣ ደብዳቤሽ ከደረሰን ከ15 ዓመት በኋላ መሆኑ ነው፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመርኩ። መጋቢት 9 ቀን 1990 ተጠመቅኩ። ከበርካታ ዓመታት በፊት ስለጻፍሽው ደብዳቤ በጣም አመሰግንሻለሁ። የዘራሽው ዘር በይሖዋ እርዳታ የበቀለ መሆኑን ስገልጽልሽ በጣም ደስ ይለኛል። እናቴ ደብዳቤሽን እንዳስቀምጠው ሰጥታኛለች። ከአንቺ ጋር መተዋወቅ እፈልጋለሁ። ይህ ደብዳቤ እንደሚደርስሽ ተስፋ አደርጋለሁ።” የዚህች ልጅ አድራሻና የስልክ ቁጥር የሰፈረበት ይህ ደብዳቤ ከበርካታ ዓመታት በፊት ለእናትዋ ደብዳቤ ጽፋ ለነበረችው እህት ደረሰ። ወጣትዋ እህት አሁንም ደብዳቤ እየጻፈች የመንግሥቱን መልእክት ለሰዎች ከምታካፍለው ምሥክር ስልክ ሲደወልላት እንዴት ያለ ደስታ እንደተሰማት ልትገምቱ ትችላላችሁ!
በአእምሮ፣ በሥነ ምግባርና በመንፈሳዊ መጎልመስ
18. በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመናት ወላጆች ለልጆቻቸው አእምሯዊና ሥነ ምግባራዊ ትምህርት የሚሰጡት እንዴት ነበር?
18 ሦስተኛው ዓላማ ደግሞ ሚዛኑን የጠበቀ ትምህርት በአእምሮና በሥነ ምግባር እንድናድግ ሊረዳን የሚገባ መሆኑ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመናት ከወላጆች መሠረታዊ ግዴታዎች አንዱ ለልጆቻቸው አእምሯዊና ሥነ ምግባራዊ ትምህርት መስጠት ነበር። ልጆች መጻፍና ማንበብ ብቻ ሳይሆን ከዚህ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነውንና የሕይወት እንቅስቃሴያቸውን በሙሉ የሚገዛውን የአምላክ ሕግ መማር ነበረባቸው። ስለዚህ ትምህርታቸው ስለ ሃይማኖታዊ ግዴታዎች፣ የጋብቻ ግንኙነትን ስለሚመሩበት መሠረታዊ ሥርዓት፣ ስለ ቤተሰብ ዝምድና፣ ስለ ወሲባዊ ሥነ ምግባርና ለሌሎች ሰዎች ማሟላት ስለሚኖርባቸው ግዴታ የሚገልጹ መመሪያዎችን ያጠቃልል ነበር። እንዲህ ያለው ትምህርት በአእምሮና በሥነ ምግባር ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊ ጭምር እንዲያድጉ ይረዳቸው ነበር።—ዘዳግም 6:4-9, 20, 21፤ 11:18-21
19. ልንመራባቸው የሚገቡ ከሁሉ የተሻሉ የሥነ ምግባር ሥርዓቶች የትኞቹ እንደሆኑ የሚያመለክተንና በመንፈሳዊ ለመጎልመስ የሚያስችለን ትምህርት ከየት ልናገኝ እንችላለን?
19 ዛሬስ? ጥሩ ሰብዓዊ ትምህርት አስፈላጊ ነው። አእምሯችን እንዲዳብር ይረዳል። ይሁን እንጂ ልንመራባቸው የሚገቡ ከሁሉ የተሻሉ የሥነ ምግባር ሥርዓቶች የትኞቹ እንደሆኑ የሚያመለክተንና መንፈሳዊ እድገት እንድናገኝ የሚያስችለን ትምህርት ከየት ልናገኝ እንችላለን? በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በየትኛውም የምድር ክፍል ልናገኝ የማንችለው ቲኦክራሲያዊ ትምህርት እናገኛለን። መጽሐፍ ቅዱስንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በግላችን በማጥናትና በጉባኤና በትላልቅ ስብሰባዎች የሚሰጡትን መመሪያዎች በመቀበል ይህን የማያቋርጥና ከፍተኛ ዋጋ ያለው መለኮታዊ ትምህርት ያለምንም ክፍያ በነፃ ለማግኘት እንችላለን! ይህ መለኮታዊ ትምህርት ምን ያስተምረናል?
20. መለኮታዊ ትምህርት ምን ያስተምረናል? ምንስ ውጤቶች ያስገኛል?
20 መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ስንጀምር መጀመሪያ የምንማረው መሠረታዊ የሆኑትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርቶች ወይም “የመጀመሪያውን ትምህርት” ነው። (ዕብራውያን 6:1 የ1980 ትርጉም) ጥናታችንን እየቀጠልን ስንሄድ “ጠንካራ ምግብ” ማለትም ጥልቅ የሆኑ እውነቶችን መውሰድ እንጀምራለን። (ዕብራውያን 5:14) ከዚህም በተጨማሪ አምላክ የሚፈልግብንን እያሟላን ለመኖር የሚያስችሉንን መሠረታዊ ሥርዓቶች እንማራለን። ለምሳሌ ያህል ሥጋን ከሚያረክሱ ልማዶችና ድርጊቶች እንዴት እንደምንርቅ እንዲሁም ለባለ ሥልጣኖችና ለሌሎች ሰዎች አካልና ንብረት እንዴት አክብሮት እንደምናሳይ እንማራለን። (2 ቆሮንቶስ 7:1፤ ቲቶ 3:1, 2፤ ዕብራውያን 13:4) በተጨማሪም በሥራችን ሐቀኞችና ትጉሆች መሆን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጾታዊ ሥነ ምግባር የሚሰጠውን ትእዛዝ ማክበር ለምን አስፈላጊ እንደሆነ እንማራለን። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10፤ ኤፌሶን 4:28) እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሕይወታችን ውስጥ ሥራ ላይ በማዋል ረገድ እድገት እያሳየን ስንሄድ በመንፈሳዊ እናድጋለን፣ ከአምላክ ጋር ያለን ዝምድናም ይጠነክራል። እነዚህን እውነቶች መረዳትና እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች ጠብቆ መኖር ሕይወታችን ትርጉምና ዓላማ ያለው እንዲሆን ከማስቻሉም በላይ የዚህ መለኮታዊ ትምህርት ምንጭ ለሆነው ለይሖዋ አምላክ ክብርና ውዳሴ ያስገኛል።—1 ጴጥሮስ 2:12
የዕለት ተዕለት ኑሮን ለማሸነፍ የሚያስችል ተግባራዊ ሥልጠና
21. ልጆች በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመናት ምን ተግባራዊ ሥልጠና ያገኙ ነበር?
21 አራተኛው ሚዛኑን የጠበቀ ትምህርት ዓላማ አንድ ሰው የዕለት ተዕለት ኑሮውን እንዲያሸንፍ የሚያስችለው ተግባራዊ ሥልጠና መስጠት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ይሰጥ የነበረው ትምህርት ተግባራዊ ሥልጠናዎችን ያጠቃልል ነበር። ሴት ልጆች የቤት ውስጥ ሥራዎችን ይማራሉ። የምሳሌ መጽሐፍ የመጨረሻ ምዕራፍ ይህ ትምህርት ብዙ የተለያዩ ነገሮችን እንደሚያጠቃልል ያሳያል። የቤት ውስጥ ሥራዎች በርካታና የተለያዩ መሆናቸውን ከምሳሌ መጽሐፍ የመጨረሻ ምዕራፍ መረዳት እንችላለን። ልጃገረዶች ፈትል፣ ሸማ መሥራት፣ ምግብ ማብሰል፣ ቤታቸውን ማስተዳደር፣ ንግድና ንብረት መሸጥና መግዛት መቻል ነበረባቸው። ወንዶች ልጆች ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ የአባታቸውን ሥራ፣ ግብርናም ሆነ ንግድ ወይም አንድ ዓይነት የእጅ ሞያ ይማሩ ነበር። ኢየሱስ ከአሳዳጊ አባቱ ከዮሴፍ አናጢነት ተምሯል። በመሆኑም “የጸራቢ ልጅ” መባል ብቻ ሳይሆን “ጸራቢው” ተብሎ ተጠርቷል።—ማቴዎስ 13:55፤ ማርቆስ 6:3
22, 23. (ሀ) ትምህርት ልጆችን ለምን ነገር ሊያዘጋጃቸው ይገባል? (ለ) አስፈላጊ መስሎ ስለታየን ተጨማሪ ትምህርት ለመከታተል ስንመርጥ ምን ዓይነት ዝንባሌ ሊኖረን ይገባል?
22 ዛሬም ቢሆን ሚዛናዊ የሆነ ትምህርት አንድ ቀን ቤተሰብን ለመርዳት የሚያዘጋጅ መሆን አለበት። በ1 ጢሞቴዎስ 5:8 ላይ የሚገኙት የሐዋርያው ጳውሎስ ቃላት ለቤተሰብ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ማቅረብ የተቀደሰ ተግባር እንደሆነ ያሳያሉ። ጳውሎስ “ለእርሱ ስለ ሆኑት ይልቁንም ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ ማንም ቢሆን፣ ሃይማኖትን የካደ ከማያምን ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው” በማለት ጽፏል። ስለዚህ ትምህርት ልጆች ወደፊት ለሚሸከሟቸው ኃላፊነቶች የሚያዘጋጃቸውና ጠንካራ ሠራተኞች የሆኑ የማኅበረሰቡ አባሎች የሚያደርጋቸው መሆን አለበት።
23 ዓለማዊ ትምህርትን መከታተል ያለብን እስከ ምን ደረጃ ነው? ይህ ከአገር ወደ አገር ይለያያል። ቢሆንም የሥራው ዓለም በምንኖርበት አገር ተቀባይነት ካለው አነስተኛ ትምህርት ተጨማሪ ሥልጠና የሚጠይቅ ከሆነ ልጆች ተጨማሪ ትምህርት ወይም ሥልጠና መውሰዱ የሚያስከትለውን ትርፍና ኪሳራ በማስላት ውሳኔ እንዲያደርጉ መርዳቱ የወላጆች ፋንታ ነው። ይሁን እንጂ አንድ ሰው አስፈላጊ ሆኖ ታይቶት ከፍተኛ ትምህርት ለመከታተል ሲፈልግ ዓላማው ምን መሆን ይኖርበታል? ለራሱ ክብርና ዝና ለማግኘት መሆን እንደሌለበት የታወቀ ነው። (ምሳሌ 15:25፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:17) ኢየሱስ ከተወው ምሳሌ ያገኘነው ትምህርት ትዝ ይበልህ፦ ትምህርት ይሖዋን ለማወደስ ማገልገል ይኖርበታል። ከፍተኛ ትምህርት ለመከታተል ከመረጥን ዓላማችን ይሖዋን የተቻለንን ያህል በተሟላ ሁኔታ በክርስቲያናዊ አገልግሎት ለማገልገል እንድንችል ለኑሯችን የሚበቃንን ለማግኘት መሆን ይኖርበታል።—ቆላስይስ 3:23, 24
24. ከኢየሱስ የተማርነው ፈጽሞ ልንረሳው የማይገባ ትምህርት ምንድን ነው?
24 እኛም በበኩላችን ሚዛኑን የጠበቀ ሥጋዊ ትምህርት ለማግኘት በምናደርገው ጥረት ትጉዎች እንሁን። ከዚህ በላይ ግን በይሖዋ ድርጅት ውስጥ አለማቋረጥ ከሚሰጠው የመለኮታዊ ትምህርት ፕሮግራም ሙሉ ተጠቃሚዎች ለመሆን እንጣር። በምድር ገጽ ላይ ከተመላለሱት ሰዎች ሁሉ ይበልጥ የተማረ ሰው ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ያገኘነውን ከፍተኛ ዋጋ ያለው ትምህርት አንርሳ! ትምህርት ለራሳችን ክብርና ዝና ማትረፊያ ሳይሆን ለታላቁ መምህር ለይሖዋ አምላክ ውዳሴ የሚያስገኝ መሆን ይኖርበታል!
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ኢየሱስ ያገኘውን ትምህርት የተጠቀመበት እንዴት ነው?
◻ በሚገባ ማንበብን መማር አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
◻ በመጻፍ ችሎታችን ተጠቅመን ይሖዋን ለማወደስ የምንችለው እንዴት ነው?
◻ መለኮታዊ ትምህርት በሥነ ምግባርም ሆነ በመንፈሳዊ እንድንጎለምስ የሚረዳን እንዴት ነው?
◻ ሚዛናዊ የሆነ ትምህርት ምን ተግባራዊ ሥልጠና ሊያካትት ይገባል?
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ለትምህርት ባለሙያዎች የቀረበ ተግባራዊ እርዳታ
የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በ1995/96 በተደረገው “ደስተኛ አወዳሾች” የአውራጃ ስብሰባ ላይ የይሖዋ ምሥክሮችና ትምህርት የተባለ አዲስ ብሮሹር አውጥቷል። ይህ በኅብረ ቀለማት ያሸበረቀ ባለ 32 ገጽ ብሮሹር በተለይ ለትምህርት ባለሞያዎች ታስቦ የተዘጋጀ ነው። እስካሁን ድረስ በ58 ቋንቋዎች ተተርጉሟል።
ብሮሹሩ ለትምህርት ባለሙያዎች የተዘጋጀው ለምንድን ነው? የይሖዋ ምሥክሮች ልጆች የሆኑ ተማሪዎች ያሏቸውን እምነቶች በተሻለ ሁኔታ እንዲገነዘቡ ለመርዳት ነው። ብሮሹሩ ምን ነገር ይዟል? ተጨማሪ ትምህርትን፣ የልደት በዓልንና ገናን እንዲሁም ለሰንደቅ ዓላማ ሰላምታ መስጠትን በተመለከተ ያለንን አመለካከት ግልጽና አዎንታዊ በሆነ መንገድ ያብራራል። በተጨማሪም ብሮሹሩ ልጆቻችን ከትምህርታቸው በተሻለ ሁኔታ እንዲጠቀሙ እንደምንፈልግና ልጆቻችን ስለሚሰጣቸው ትምህርት ትኩረት በመስጠት ከትምህርት ባለሙያዎች ጋር ከልብ ለመተባበር እንደምንፈልግ ለትምህርት ባለሙያዎች ማረጋገጫ ይሰጣል።
ትምህርት በተባለው ብሮሹር እንዴት መጠቀም ይቻላል? የተዘጋጀው ለትምህርት ባለሙያዎች ስለሆነ ለመምህራን፣ ለርዕሰ መምህራንና ለሌሎች የትምህርት ቤት ባለ ሥልጣኖች እንስጣቸው። እነዚህ የትምህርት ባለሙያዎች አመለካከታችንንና እምነታችንን እንዲረዱ እንዲሁም አንዳንድ ጊዜ የተለየ አቋም የመያዝ መብት እንዲሰጠን እንደምንጠይቅ እንዲገነዘቡ እንዲረዳቸው እንመኛለን። ወላጆች በግላቸው ከልጆቻቸው አስተማሪዎች ጋር ለመወያየት ቢጠቀሙበት ጥሩ ነው።
[[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በጥንቷ እስራኤል ትምህርት ከፍተኛ ቦታ ይሰጠው ነበር