የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
“በዓለም ውስጥ ብርሃን አብሪዎች መሆን”
የይሖዋ ምሥክሮች ደም ባለመውሰዳቸው የተነሳ የተለዩ ተደርገው ከመታየታቸውም በላይ ብዙውን ጊዜ ስለ እነርሱ መጥፎ ወሬ ይነዛል። ይሁን እንጂ ይህ አቋማቸው ጠንካራ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ አለው። አምላክ ደምን በጣም ውድ አድርጎ ስለሚመለከተው ተገቢ ባልሆነ መንገድ መጠቀምን እንደሚያወግዝ መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል። (ዘፍጥረት 9:3, 4፤ ዘሌዋውያን 17:14) የይሖዋ ምሥክሮች ቅዱሳን ጽሑፎች ስለዚህ ጉዳይ ምን እንደሚሉ ባደረጉት ምርምር ‘ከደም ራቁ’ የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ዘመናዊ የሆነውን ለሕክምና ሲባል ደም የመስጠትንም ተግባር ያጠቃልላል የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል።—ሥራ 15:19, 20, 28, 29
በቅርብ ዓመታት በአንዳንድ አገሮች ውስጥ ያሉ የሕክምና ቡድን አባላትና ፍርድ ቤቶች በዚህ ጉዳይ ላይ ለይሖዋ ምሥክሮች ድጋፋቸውን እየሰጡ ነው። ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ደም የሚሰጠውን መመሪያ የምታውቅ በዴንማርክ የምትኖር አንዲት ወጣት የልጆች እናት በመኪና አደጋ ሞተች። ደም አልወስድም ብላ ስለነበር የዜና ማሰራጫዎች የይሖዋ ምሥክሮችን በተመለከተ የጥላቻ ወሬ ነዙ። ይህን ለአንድ ወር የቆየ የጥላቻ ዘመቻ የቆሰቆሱት ዶክተሮችዋ ነበሩ።
የወጣቷ ወላጆች ጉዳዩ እንዲጣራላቸው የጠየቁ ሲሆን የዴንማርክ የበሽተኞች ቅሬታ ሰሚ ኮሚሽን ሚያዝያ 1994 ውሳኔ አስተላለፈ። ውሳኔው በሽተኛዋ የሞተችው ደም አልወስድም በማለቷ ሳይሆን ተገቢውን ሕክምና ባለማግኘቷ እንደሆነ ገለጸ። ይህ ውሳኔ የተላለፈው ከሕክምና ጋር ግንኙነት ያላቸውን ሕግ ነክ ጉዳዮች የሚመለከተው ቦርድና የጤና ባለሙያዎች አጣርተው ያገኙትን ውጤት በመንተራስ ነው። ብሔራዊው የጤና ቦርድ ዴንማርክ ውስጥ ለሚገኙ የጤና ጥበቃ መሥሪያ ቤቶች በላከው ደብዳቤ ላይ የይሖዋ ምሥክሮች ደም እንደማይወስዱ ግምት ውስጥ በማስገባት ዶክተሮች በደም ፋንታ ሊሰጡ ከሚችሉት አማራጭ ሕክምናዎች በተሻለው ተጠቅምው ሊያክሟቸው እንደሚገባ ገልጿል።
ሌላው ሉኪሚያ በተባለ በሽታ የሞተው የ15 ዓመቱ የይሖዋ ምሥክር የዳን ጉዳይ ነው። ዳን ደም አልወስድም በማለት የወሰደውን ድፍረት የተሞላበት ውሳኔ ዶክተሮች አክብረውለታል። በዚህ የተነሳ የዜና ማሰራጫዎች ሰፊ ዘመቻ ያደረጉ ሲሆን በዳን ሞት ዶክተሮቹን ወቅሰዋል። ቢሆንም ብዙዎች በዚህ አሉታዊ ፕሮፓጋንዳ አልተስማሙም።
ለምሳሌ ዳን ይማርበት የነበረው ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር የቀብር ንግግሩን ለማዳመጥ በመንግሥት አዳራሹ ተገኝተው ነበር። የዜና ማሰራጫዎች ስለ ዳን አማሟት በሚያናፍሷቸው የተሳሳቱ ወሬዎች እንዳዘኑ ተናግረዋል። ርዕሰ መምህሩ የይሖዋ ምሥክር የሆነ አንድ የሥራ ባልደረባቸውን ቀርበው ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ብዙ ጥያቄዎች ከጠየቁት በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች—ከስሙ በስተጀርባ ያለው ድርጅት የተባለውን የቪዲዮ ካሴት ወሰዱ። የቪዲዮ ካሴቱ በጣም ስላስደሰታቸው በትምህርት ቤቱ ያሉት አስተማሪዎች ሁሉ እንዲያዩት ዝግጅት አደረጉ። በኋላም ተማሪዎች በጠቅላላ በየክፍላቸው ተመለከቱት።
የዴንማርክ የጤና ጥበቃ ሚንስትርም ቢሆኑ በዳን ዶክተሮች ላይ በተነዛው የተሳሳተ ወሬ አልተስማሙም። ዶክተሮቹ ብስለት ያለውን የዳንን ውሳኔና በጥሩ መሠረት ላይ የተገነባው እምነቱን በማክበር ትክክለኛ ነገር እንዳደረጉ ተናግረዋል።
የአምላክን ሕግ የሚታዘዙ በሚልዮን የሚቆጠሩ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች አሉ። በታዛዥነታቸው የተነሳ “በዓለም ውስጥ ብርሃን አብሪዎች” በመሆን ተለይተው ይታወቃሉ።—ፊልጵስዩስ 2:12, 15 አዓት