በእውነት ላይ የተመሠረተ እምነት አሳዩ
“ያለ እምነት ደስ ማሰኘት አይቻልም። ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንደሚሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋል።”—ዕብራውያን 11:6
1, 2. የአዳም እምነት ፈተና የደረሰበት እንዴት ነበር? ከምንስ ውጤት ጋር?
እምነት አምላክ መኖሩን ከማመን የበለጠ ነገር ይጠይቃል። የመጀመሪያው ሰው አዳም ስለ ይሖዋ አምላክ ሕላዌ ምንም ጥርጣሬ አልነበረውም። አምላክ በልጁ በቃል በኩል ሳይሆን አይቀርም ከአዳም ጋር ይነጋገር ነበር። (ዮሐንስ 1:1-3፤ ቆላስይስ 1:15-17) ሆኖም አዳም ይሖዋን ባለመታዘዙና እምነት ሳያሳይ በመቅረቱ ምክንያት የዘላለም ሕይወት ተስፋውን አጥቶአል።
2 የአዳም ሚስት የይሖዋን ትዕዛዝ በጣሰች ጊዜ የወደፊት ደስታው በአደጋ ላይ የወደቀ መሰለ። እሷን የማጣቱ ሃሳብ ራሱ የመጀመሪያውን ሰው እምነት በፈተና ላይ ጣለ። አምላክ የአዳምን ደስታና ደህንነት በማያሳጣ መንገድ ችግሩን ሊፈታ ይችል ይሆንን? አዳም ተላልፎ ኃጢአት በመስራት ከሔዋን ጋር መተባበሩ እሷን ማጣቱ ደስታውን በማይነካበት መንገድ አምላክ ችግሩን የሚፈታው እንዳልመሰለው አሳይቷል። ከልቡ መለኰታዊ አመራር ከመሻት ይልቅ ችግሩን በራሱ መንገድ ለመፍታት ሞከረ። አዳም በይሖዋ እምነት ሳያሳይ በመቅረቱ በራሱና በዘሮቹ ሁሉ ላይ ሞትን አመጣ።—ሮሜ 5:12
እምነት ምንድነው?
3. መጽሐፍ ቅዱስ ለእምነት የሰጠው ፍች በአንድ መዝገበ ቃላት ከተሰጠው የሚለየው እንዴት ነው?
3 አንድ መዝገበ ቃላት የእምነትን ትርጉም ሲገልጽ “ማስረጃ በሌለው ነገር መተማመን” ማለት ነው ይላል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ሐሳብ አይደግፍም። ከዚህ ተቃራኒ የሆነ ሐሳብ በመግለጽ እምነት በሐቅ፣ በእውነታዎችና፣ እርግጠኛ ሕልውና ባላቸው ነገሮች ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ያረጋግጣል። ቅዱሳን ጽሑፎች “እምነት ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው” ይላሉ። (ዕብራውያን 11:1) እምነት ያለው ሰው አምላክ የሰጠው ተስፋ ሁሉ አስቀድሞ እንደተፈጸመ ያህል እርግጠኛ እንደሆነ ዋስትና አለው። የማይታየው እውነታ አሳማኝ ማስረጃ ያለው በመሆኑ ያልታየው ነገር የማስረጃውን ያህል እርግጠኛ ሆኖ ይታያል።
4. አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ መጽሐፍ ቅዱስ ለእምነት የሰጠውን ፍች የሚደግፈው እንዴት ነው?
4 በአዲሲቱ ዓለም ትርጉም “አማን” ከሚለው ግሥ የተገኘው ምክንያት አመልካች ቃል አንዳንዴ “እምነት ማሳየት” ተብሎ ተተርጉሟል። ቲኦሎጂካል ዎርድ ቡክ ኦቭ ዘ ኦልድ ቴስታመንት በተሰኘው መጽሐፍ መሠረት “ይህ ቃል የሚያስተላልፈው መሠረታዊ ሐሳብ የታመነው ነገር እርግጠኛ መሆኑን ነው። . . . ይህ ሐሳብ እምነትን እንደ አንድ የሚቻል፣ እውነት ይሆናል ተብሎ ተስፋ የሚደረግ፣ ሆኖም እርግጠኛ ያልሆነ ነገር አድርጎ ከሚወስደው ዘመናዊ አስተሳሰብ ተቃራኒ ነው።” ይኸው ጽሑፍ እንዲህ ይላል፦ “ከዚሁ ሥርወ ቃል የመጣው አሜን የሚል ቃል በአዲስ ኪዳን ውስጥ ‘እውነት፣ እውነት’ የሚል ትርጉም ተሰጥቶታል። አሜን የሚለው የእንግሊዝኛ ቃልም የተገኘው ከዚህ ቃል ነው። ኢየሱስም አንድ ነገር እርግጠኛ መሆኑን አጽንቶ ለመግለጽ በዚህ ቃል ብዙ ጊዜ ተጠቅሞአል።” (ማቴዎስ 5:18, 26, ወዘተ) በክርስቲያን ግሪክ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ “እምነት” ተብሎ የተተረጐመው ቃል በሐቅ ወይም በእውነት ላይ ጸንቶ በተመሠረተ ነገር ማመን የሚል ትርጉም አለው።
5. በዕብራውያን 11:1 ላይ “እርግጠኛ ተስፋ” ተብሎ የተተረጐመው የግሪክኛ ቃል በጥንት የንግድ ሠነዶች ላይ ያገለገለው እንዴት ነበር? ይህስ ለክርስቲያኖች ምን ቁም ነገር አለው?
5 በዕብራውያን 11:1 ላይ “እርግጠኛ ተስፋ” ተብሎ የተተረጐመው የግሪክኛ ቃል (ሃይፖስታሲስ) በጥንቱ የፓፒረስ የንግድ ሠነዶች ላይ ለወደፊቱ አንድ ንብረት ለመቀበል ዋስትና የሚሰጥን ውል ወይም ሐሳብ ለማስተላለፍ አገልግሏል። ሞልተንና ሚሊጋን የተባሉት ምሁራን “እምነት ተስፋ ለተደረጉት ነገሮች የባለቤትነት መረጃ ነው” ተብሎ እንዲተረጎም ሐሳብ አቅርበዋል። (ቮካብለሪ ኦፍ ዘ ግሪክ ቴስታመንት) በግልጽ እንደሚታየው አንድ ሰው ለአንድ ንብረት የባለቤትነት መረጃ ካለው አንድ ቀን ንብረቱን ለማግኘት ያለው ተስፋ እንደሚፈጸምለት “እርግጠኛ ተስፋ” ሊኖረው ይችላል።
6. በዕብራውያን 11:1 ላይ “የሚያስረዳ” (ወይም “አስረጂ”) ተብሎ የተተረጐመው የግሪክኛ ቃል ቁምነገር ምንድን ነው?
6 በዕብራውያን 11:1 ላይ “የሚያስረዳ” ወይም “አስረጅ” ተብሎ የተተረጐመው የግሪክኛ ቃል (ኤሌግኮስ) ሲሆን አንድን ነገር በተለይም አንድን እውነት የማይመስል ነገር ለማረጋገጥ ማስረጃ የማቅረብን ሐሳብ ያስተላልፋል። እርግጠኛ ወይም ተጨባጭ ማስረጃ ቀደም ሲል ሳይስተዋል የቀረ ነገርን ግልጽ በማድረግ እውነት መስሎ ቀድም ብሎ የነበረውን ግምታዊ አስተሳሰብ ያፈርሳል። ስለዚህ በዕብራይስጡም ሆነ በግሪክ ቅዱሳን ጽሑፎች እምነት በምንም ዓይነት መንገድ “ማስረጃ በሌለው ነገር ጽኑ እምነት ማሳደር” የሚል ትርጉም ኖሮት አያውቅም። ከዚህ ይልቅ እምነት የተመሠረተው በእውነት ላይ ነው።
በመሠረታዊ እውነቶች ላይ የተመሠረተ
7. ጳውሎስና ዳዊት የአምላክን ሕልውና የካዱትን ሰዎች የገለጿቸው እንዴት ነው?
7 ሐዋርያው ጳውሎስ የፈጣሪ “የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ነገሮች ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና፣ ስለዚህም [የእውነት ተቃዋሚዎች] . . . የሚያመካኙት አጡ” ብሎ በጻፈ ጊዜ አንድ መሠረታዊ እውነት ገልጿል። (ሮሜ 1:20) አዎ፣ “ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ።” “ምድርም ከፍጥረቱ ተሞላች።” (መዝሙር 19:1፤ 104:24) ይሁን እንጂ አንድ ሰው ማስረጃውን ለመመልከትና ለማስተዋል ፈቃደኛ ካልሆነስ? መዝሙራዊው ዳዊት እንዲህ ብሏል፦ “ኃጢአተኛ ስለ እግዚአብሔር ግድ የለውም። በትዕቢቱም ‘እግዚአብሔር የለም’ ብሎ ያስባል።” (መዝሙር 10:4 እንደ 1980 እትም እንዲሁም መዝሙር 14:1) እምነት በአምላክ ሕላዌ መሠረታዊ እውነት ላይ በከፊል የተመሠረተ ነው።
8. እምነት የሚያሳዩ ሰዎች ምን ማረጋገጫና ማስተዋል ሊኖራቸው ይችላል?
8 ይሖዋ ከመኖሩም በላይ እምነት የሚጣልበት አምላክ ነው። በተስፋዎቹ ልንተማመን እንችላለን። እንዲህ ብሏል፦ “እንደተናገርሁ በእርግጥ ይሆናል፣ እንዳሰብሁም እንዲሁ ይቆማል። (ኢሳይያስ 14:24፤ 46:9, 10) እነዚህ ትርጉም አልባ የሆኑ ባዶ ቃላት አይደሉም። በአምላክ ቃል ውስጥ የተመዘገቡት በመቶ የሚቆጠሩ ትንቢቶች እንደተፈጸሙ ግልጽ ማስረጃ አለ። እምነት የሚያሳዩ ሰዎች እነዚህን መረጃዎች በመረዳት እየተፈጸሙ ያሉትን ሌሎች ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜ ማስተዋል ይችላሉ። (ኤፌሶን 1:18) ለምሳሌ ያህል እየተፋጠነ ያለውን የተቋቋመችውን መንግሥት ስብከት እንዲሁም በትንቢት የተነገረውን የእውነተኛ አምልኰ መስፋፋት ጨምሮ የኢየሱስን መገኘት “ምልክት” ፍጻሜ እየተመለከቱ ነው። (ማቴዎስ 24:3-14፤ ኢሳይያስ 2:2-4፤ 60:8, 22) በቅርቡ መንግሥታት “ሰላምና ደህንነት” ብለው እንደሚጮኹና ከዚያም ብዙ ሳይቆይ ወዲያው አምላክ “ምድርን የሚያጠፏትን እንደሚያጠፋ” ያውቃሉ። (1 ተሰሎንቄ 5:3፤ ራእይ 11:18) በትንቢታዊ እውነቶች ላይ የተመሠረተ እምነት ባለቤት መሆን በጣም ትልቅ በረከት ነው።
የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ
9. በእምነትና በመንፈስ ቅዱስ መካከል ያለው ዝምድና ምንድን ነው?
9 የእምነት መሠረት የሆነው እውነት የአምላክ መንፈስ ቅዱስ ውጤት በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል። (2 ሳሙኤል 23:2፤ ዘካርያስ 7:12፤ ማርቆስ 12:36) በመሆኑም እምነት ከአምላክ መንፈስ ቅዱስ አሠራር ተለይቶ ሊኖር አይችልም። ጳውሎስ ‘ከመንፈስ ፍሬ አንዱ እምነት ነው’ ብሎ ሊጽፍ የቻለው በዚህ ምክንያት ነው። (ገላትያ 5:22) ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎች መለኰታዊውን እውነት ንቀው ሕይወታቸውን የአምላክን መንፈስ በሚያሳዝን ሥጋዊ ምኞትና አመለካከት በክለዋል። ስለዚህ “እምነት ለሁሉም ሰው አይደለም።” ምክንያቱም እምነትን የሚያሳድጉበት ወይም የሚያዳብሩበት መሠረት የላቸውም።—2 ተሰሎንቄ 3:2፤ ገላትያ 5:16-21፤ ኤፌሶን 4:30
10, 11. አንዳንድ የቀድሞ የይሖዋ አገልጋዮች እምነት ያሳዩት እንዴት ነው?
10 ሆኖም ከአዳም ዘሮች መካከል አንዳንድ ግለሰቦች እምነት አሳይተዋል። ዕብራውያን ምዕራፍ 11፦ “በእምነት ከተመሠከረላቸው” ብዙ ስማቸው ያልተጠቀሰ የይሖዋ አገልጋዮች ጋር አቤልን፣ ሄኖክን፣ ኖህን፣ አብርሃምን፣ ሣራን፣ ይስሐቅን፣ ያዕቆብን፣ ዮሴፍን፣ ሙሴን፣ ረዐብን፣ ጌዴዎንን፣ ባርቅን፣ ሳምሶንን፣ ዮፍታሔን፣ ዳዊትንና ሳሙኤልን ይጠቅስልናል። “በእምነት” የተደረጉትን ነገሮች አስተውል። አቤል ለአምላክ መሥዋዕት ያቀረበውና ኖህም መርከቡን የሠራው በእምነት ነበር። አብርሃም “ርስት አድርጎ ሊቀበለው ወዳለው ሥፍራ ለመውጣት በእምነት ታዘዘ።” በእምነት ሙሴ “ግብጽን ተወ።”—ዕብራውያን 11:4, 7, 8, 27, 29, 39
11 በግልጽ እንደሚታየው እነዚህ የይሖዋ አገልጋዮች ሁሉ በይሖዋ መኖር ከማመን የበለጠ ነገር አድርገዋል። በሱ በማመን “ለሚፈልጉት ዋጋ የሚሰጥ” አምላክ በመሆኑ ተማምነዋል። (ዕብራውያን 11:6) በጊዜው ያገኙት የእውነት ትክክለኛ እውቀት በጣም አነስተኛ ቢሆንም በዚያው ባወቁት በመመላለስ የአምላክ መንፈስ እንዲሠሩ የመራቸውን አድርገዋል። ከአዳም ፈጽሞ የተለየ አቋም ይዘዋል። አዳም በእውነት ላይ በተመሠረተ እምነት ወይም ከመንፈስ ቅዱስ አመራር ጋር ተስማምቶ አልሠራም። አምላክ ቅዱስ መንፈሱን የሚሰጠው ለሚታዘዙት ሰዎች ብቻ ነው።—ሥራ 5:32
12. (ሀ) አቤል እምነት የነበረው በምን ነበር? ይህንስ እንዴት አሳየ? (ለ) እምነት ቢኖራቸውም የቅድመ ክርስትና የይሖዋ ምሥክሮች ምን አላገኙም?
12 ከአባቱ ከአዳም በተለየ ሁኔታ አምላካዊ ሰው የነበረው አቤል እምነት ነበረው። ከዚያ በፊት ስለተነገረው “በዘርህና በዘርዋ መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፣ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፣ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ” ስለሚለው ብቸኛ ትንቢት ከወላጆቹ ተምሮ እንደነበረ ግልጽ ነው። (ዘፍጥረት 3:15) እዚህ ላይ አምላክ ክፋትን እንደሚያጠፋና ጽድቅን መልሶ እንደሚያቋቁም ቃል ገብቷል። ይህ ትንቢት እንዴት እንደሚፈጸም አቤል አላወቀም። ይሁን እንጂ አምላክ ለሚፈልጉት ዋጋ ሰጪ ስለመሆኑ የነበረው እምነት በጣም ጠንካራ ከመሆኑ የተነሣ መሥዋዕት እንዲያቀርብ አነሳስቶታል። ስለ ትንቢቱ ብዙ ሳያስብ አልቀረም። ተስፋውን ለማስፈጸምና የሰው ልጆችን ወደ ፍጽምና ከፍ ለማድረግ ደም መፍሰስ እንደሚያስፈልግ አምኖአል። ስለዚህ አቤል የእንስሳ መሥዋዕት ማቅረቡ ተገቢ ነበር። ሆኖም አቤልና ሌሎች የቅድመ ክርስትና ዘመን የይሖዋ ምሥክሮች እምነት የነበራቸው ቢሆኑም “የተስፋቸውን ፍጻሜ አላገኙም።”—ዕብራውያን 11:39
እምነትን ፍጹም ማድረግ
13. (ሀ) አብርሃምና ዳዊት ስለተስፋው ፍጻሜ ምን አወቁ? (ለ) “እውነት በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ሆነ” ሊባል እንዴት ይችላል?
13 አምላክ ባለፉት መቶ ዘመናት በሙሉ ስለ “ሴቲቱ ዘር” የሰጠው ተስፋ እንዴት እንደሚፈጸም ተጨማሪ እውነቶችን በተከታታይ ይገልጥ ነበር። ለአብርሃም “በዘርህም የምድር አሕዛብ ራሳቸውን ይባርካሉ” ተብሎ ተነግሮት ነበር። (ዘፍጥረት 22:18) በኋላ ለንጉሥ ዳዊት ተስፋ የተገባው ዘር በሱ ንጉሣዊ መሥመር እንደሚመጣ ተነግሮት ነበር። ይህ ተስፋ የተደረገው ዘር ኢየሱስ ክርስቶስ በ29 እዘአ መጣ። (መዝሙር 89:3, 4፤ ማቴዎስ 1:1፤ 3:16, 17) “ኋለኛው አዳም” ኢየሱስ ክርስቶስ እምነት በማሳየት ረገድ ከእምነተ ቢሱ አዳም በተለየ ሁኔታ በምሳሌነት የሚጠቀስ ሆነ። (1 ቆሮንቶስ 15:45) ሕይወቱን ያሳለፈው ራሱን ሙሉ በሙሉ ለይሖዋ ወስኖ በማገልገልና ስለመሲሑ የተነገሩትን ብዙ ትንቢቶች በመፈጸም ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ ተስፋ ስለተደረገው ዘር የተነገረውን እውነት ይበልጥ ግልጽ አድርጐአል። የሙሴ ሕግ ጥላ የሆነላቸውን ነገሮች እውን አድርጐአል። (ቆላስይስ 2:16, 17) ስለዚህም “እውነት በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ” ሊባል ችሏል።—ዮሐንስ 1:17
14. ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች እምነት አዲስ መልክ እንደያዘ ያሳያቸው እንዴት ነበር?
14 እውነት በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከሆነ ወዲህ “በተስፋው” እምነት ለመጣል የሚያስችል ሠፊ መሠረት ተገኝቷል። እምነት የበለጠ ጽኑ እንዲሆን ተደርጓል። አዲስ መጠንና ስፋት አግኝቶአል። በዚህ ረገድ ጳውሎስ እንደሱው ቅቡዓን ለሆኑ ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፎአል፦ “ነገር ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ከማመን የሆነው የተስፋ ቃል ለሚያምኑ (እምነት ለሚያሳዩ) ይሰጥ ዘንድ መጽሐፍ ከኃጢአት በታች ሁሉን ዘግቶታል። እምነትም ሳይመጣ ሊገለጥ ላለው እምነት ተዘግተን ከሕግ በታች እንጠብቅ ነበር። እንደዚህ በእምነት እንጸድቅ ዘንድ ሕግ ወደ ክርስቶስ የሚያመጣ ሞግዚታችን ሆኗል። እምነት ግን መጥቷልና ከእንግዲህ ወዲህ ከሞግዚት በታች አይደለንም። በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና።”—ገላትያ 3:22-26
15. እምነት ፍጹም ሊደረግ ወይም ሊሟላ የሚችለው እንዴት ብቻ ነበር?
15 እሥራኤላውያን አምላክ በሕጉ ቃል ኪዳን አማካኝነት ከእነርሱ ጋር በነበረው አሠራርና ግንኙነት እምነት አድርገው ነበር። አሁን ግን ይህ እምነታቸው ማሟያ አስፈለገው። እንዴት? የሕጉ ዓላማ ወደ መሲሑ ለመምራት ስለነበረ በመንፈስ በተቀባው በኢየሱስ በማመን ነው። የቅድመ ክርስትናው እምነት ፍጹም ሊሆን ወይም ሊሟላ የሚችለው በዚህ መንገድ ብቻ ነበር። ለእነዚህ የጥንት ክርስቲያኖች “የእምነታቸውን ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን” መመልከታቸው በጣም አስፈላጊ ነበር! (ዕብራውያን 12:2) ለእነርሱም ብቻ ሳይሆን ለክርስቲያኖች ሁሉ በጣም አስፈላጊ ነው።
16. መንፈስ ቅዱስ በተጠናከረ መልክ የመጣው እንዴት ነበር? ለምንስ?
16 እየጨመረ ከመጣው የመለኰታዊ እውነት እውቀትና የሱ ውጤት ከሆነው የእምነት መሟላት ወይም ፍጹም መደረግ አንጻር መንፈስ ቅዱስም እንዲሁ በተጠናከረ መንገድ መውረድ ነበረበትን? አዎ፣ በ33 እዘአ የጴንጠቆስጤ ዕለት ኢየሱስ የተናገረለት ተስፋ የተገባው ረዳት የአምላክ መንፈስ በደቀመዛሙርቱ ላይ ወረደ። (ዮሐንስ 14:26፤ ሥራ 2:1-4) በዚያን ጊዜ መንፈስ ቅዱስ እነሱን የክርስቶስ ቅቡዓን ወንድሞች በማድረግ ፈጽሞ አዲስ በሆነ መንገድ ይሠራባቸው ነበር። የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ የሆነው እምነታቸው ተጠናክሮ ነበር። ይህም በፊታቸው ለተዘረጋው ከፍተኛ ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራ አስታጠቃቸው።—ማቴዎስ 28:19, 20
17. (ሀ) ከ1914 ወዲህ እውነት የመጣውና እምነትም ፍጹም የተደረገው እንዴት ነበር? (ለ) ከ1919 ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ በሥራ ላይ ለመሆኑ ምን ማስረጃ አለን?
17 ከ1900 ዓመታት በፊት ኢየሱስ እጩ ንጉሥ ሆኖ ራሱን ባቀረበ ጊዜ እምነት መጣ። ይሁን እንጂ አሁን ደግሞ በመግዛት ላይ ያለ ሰማያዊ ንጉሥ ስለሆነ የእምነታችን መሠረት የሆነው እውነት በጣም አድጓል። ይህም እምነታችንን ፍጹም አድርጎታል። በተመሳሳይም የመንፈስ ቅዱስ አሠራር በጣም ተጠናክሮአል። ይህም በግልጽ የታየው በ1919 መንፈስ ቅዱስ የአምላክን ውስን አገልጋዮች እንደሞቱ ያህል ከነበሩበት ሁኔታ እንደገና ባነቃቃቸው ጊዜ ነበር። (ሕዝቅኤል 37:1-14፤ ራእይ 11:7-12) በዚያን ጊዜም የመንፈሳዊ ገነት መሠረት ተጣለ። ይህ መንፈሳዊ ገነት በቀጣዮቹ አሥርተ ዓመታት ይበልጥ ግልጽና ዓመት በዓመትም ይበልጥ ክብራማ እየሆነ መጥቷል። የአምላክ ቅዱስ መንፈስ በሥራ ላይ ለመሆኑ ከዚህ የበለጠ ማስረጃ ሊኖር ይችል ነበርን?
እምነታችንን መመርመር የሚኖርብን ለምንድነው?
18. በእምነት ረገድ እሥራኤላውያኑ ሰላዮች የተለያዩት እንዴት ነበር?
18 እሥራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ነፃ እንደወጡ ወዲያውኑ 12 ሰዎች የከነዓንን ምድር እንዲሰልሉ ተላኩ። ይሁን እንጂ ከእነሱ አሥሩ ይሖዋ ለእሥራኤል ምድሪቱን ለመስጠት የገባውን ቃል ለመፈጸም ያለውን ችሎታ በመጠራጠር እምነት አጡ። አስተሳሰባቸውን የሚቆጣጠረው የሚታይና ቁሳዊ ነገር ብቻ ነበር። ከአሥራ ሁለቱ ውስጥ በማየት ሳይሆን በእምነት እንደሚመላለሱ ያረጋገጡት ኢያሱና ካሌብ ብቻ ነበሩ። (ከ2 ቆሮንቶስ 5:7 ጋር አወዳድር) እምነት በማሳየታቸውም በሕይወት ተርፈው ወደ ተስፋይቱ ምድር ከሚገቡት መካከል ሊሆኑ የቻሉት እነሱ ብቻ ነበሩ።—ዘኁልቁ 13:1-33፤ 14:35-38
19. እምነትን ለመገንባት መሠረቱ ዛሬ ከምንጊዜውም የበለጠ ጥልቅ የሆነው እንዴት ነው? ሆኖም ምን ማድረግ ይኖርብናል?
19 በዛሬው ጊዜ በአምላክ የጽድቅ አዲስ ዓለም ድንበር ላይ ቆመናል። እንድንገባ ከተፈለገ እምነት ያስፈልገናል። ደስ የሚለው ነገር የዚህ እምነት መሠረት የሆነው እውነት የአሁኑን ያህል ጥልቅ ሆኖ አያውቅም። መላው መጽሐፍ ቅዱስ አለን። የኢየሱስ ክርስቶስና የሱ ቅቡዓን ተከታዮች ምሳሌ አለን። እንዲሁም በሚልዮን የሚቆጠሩ መንፈሳዊ ወንድሞችና እህቶች ድጋፍና ከዚህ በፊት ተደርጎ በማያውቅ መጠን የአምላክ መንፈስ ቅዱስ እርዳታ አለልን። ሆኖም እምነታችንን ብንመረምርና የምንችለውን ያህል ልናጠነክረው እርምጃ ብንወስድ ይበጀናል።
20. ራሳችንን የትኞቹን ጥያቄዎች መጠየቃችን ተገቢ ነው?
20 ‘ልክ ነው ይህ እውነት መሆኑን አምናለሁ’ ትል ይሆናል። ሆኖም ግን እምነትህ የቱን ያህል ጠንካራ ነው? ‘የይሖዋ መንግሥት የሰብዓዊ መንግሥታትን ያህል እውን ሆኖ ይታየኛልን? የይሖዋን የሚታይ ድርጅትና የአስተዳደር አካሉን ለይቼ አውቄያለሁን? ሙሉ ድጋፍስ እየሰጠሁት ነውን? በእምነት ዓይኔ መንግሥታት ወደ መጨረሻው የአርማጌዶን ሥፍራ እየተንቀሳቀሱ እንዳሉ እመለከታለሁን? እምነቴስ በዕብራውያን ምዕራፍ 11 ላይ ከተጠቀሱት “የምሥክሮች ታላቅ ደመና” እምነት ጋር ይመሳሰላልን?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ።—ዕብራውያን 12:1፤ ራእይ 16:14-16
21. እምነት ባለ እምነቶቹን የሚገፋፋቸው እንዴት ነው? እነሱ የሚባረኩትስ እንዴት ነው? (በገጽ 13 ላይ ካለው ሣጥን ሐሳቦችን ጨምር)
21 በእውነት ላይ የተመሠረተ እምነት ያላቸው ሰዎች ለሥራ ይንቀሳቀሳሉ። አቤል እንዳቀረበው ተቀባይነት ያገኘ መሥዋዕት የነሱም የምሥጋና መሥዋዕት አምላክን ያስደስተዋል። (ዕብራውያን 13:15, 16) ኖህ አምላክን በመታዘዝ የጽድቅ ሰባኪ እንደነበረ ሁሉ እነሱም የመንግሥቱ ሰባኪዎች በመሆን የጽድቅ መንገድን ይከተላሉ። (ዕብራውያን 11:7፤ 2 ጴጥሮስ 2:5) በእውነት ላይ የተመሠረተ እምነት ያላቸው ሰዎች እንደ አብርሃም ችግር ሲያጋጥማቸውና በጣም ፈታኝ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር ሆነውም ሳይቀር ይሖዋን ይታዘዛሉ። (ዕብራውያን 11:17-19) እምነት ያላቸው ሰዎች በጥንት ዘመን እንደነበሩት የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች ዛሬም በአፍቃሪው ሰማያዊ አባታቸው እጅግ ይባረካሉ፣ ይንከባከባቸዋልም።—ማቴዎስ 6:25-34፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:6-10
22. እምነት እንዴት ሊጠናከር ይችላል?
22 የይሖዋ አገልጋይ ከሆንክና እምነትህ በአንድ ዓይነት መንገድ እየተዳከመ እንዳለ ከተሰማህ ምን ልታደርግ ትችላለህ? የአምላክን ቃል ተግተህ በማጥናትና ልብህን የሞላውን የእውነት ውሃ አፍህ እንዲያፈልቅ በማድረግ እምነትህን አጠንክር። (ምሳሌ 18:4) እምነትህ ዘወትር ካልተጠናከረ ደካማና የማይሠራ ሊሆንብህ አልፎ ተርፎም የሞተ ሊሆን ይችላል። (1 ጢሞቴዎስ 1:19፤ ያዕቆብ 2:20, 26) እንዲህ ያለው ነገር በእምነትህ ላይ እንዳይደርስበት ቁርጥ ውሣኔ አድርግ። “አለማመኔን እርዳው” ብለህ በመጸለይም የይሖዋን እርዳታ ለምን።—ማርቆስ 9:24
መልስህ ምንድን ነው?
◻ እምነት ምንድን ነው?
◻ እምነት ከእውነትና ከመንፈስ ቅዱስ ተለይቶ ሊኖር የማይችለው ለምንድን ነው?
◻ ኢየሱስ ክርስቶስ የእምነታችን ፍጹም አድራጊ የሆነው እንዴት ነው?
◻ እምነታችን የቱን ያህል ጠንካራ መሆኑን መመርመር ያለብን ለምንድን ነው?
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
እምነት ያላቸው ሰዎች. . .
◻ ስለ ይሖዋ ይናገራሉ።—2 ቆሮንቶስ 4:13
◻ የኢየሱስን ዓይነት ሥራዎች ይሠራሉ።—ዮሐንስ 14:12
◻ ለሌሎች የመበረታታት ምንጭ ናቸው።—ሮሜ 1:8, 11, 12
◻ ዓለምን ያሸንፋሉ።—1 ዮሐንስ 5:5
◻ የሚፈሩበት ምክንያት የለም።—ኢሳይያስ 28:16
◻ ለዘላለማዊ ሕይወት የተዘጋጁ ናቸው።—ዮሐንስ 3:16