‘ወልድ አብን ለመግለጥ ፈቃደኛ ነው’
“ከወልድና ወልድ ሊገልጥለት ከሚፈቅድለት በስተቀር አብ ማን እንደሆነ የሚያውቅ የለም።”—ሉቃስ 10:22
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
ኢየሱስ የአባቱን ማንነት ለመግለጥ ከሁሉ የተሻለ ብቃት አለው የምንለው ለምንድን ነው?
ኢየሱስ የአባቱን ማንነት ለሌሎች የገለጠው እንዴት ነው?
አብን በመግለጥ ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የምትችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
1, 2. ብዙ ሰዎች የትኛው ጥያቄ ግራ ያጋባቸዋል? ለምንስ?
‘አምላክ ማን ነው?’ የዚህ ጥያቄ መልስ ለብዙ ሰዎች እንቆቅልሽ ሆኖባቸዋል። ለምሳሌ ታዋቂ የሆኑት አብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት አምላክ ሥላሴ እንደሆነ ያምናሉ፤ ሆኖም ብዙዎቹ ይህ ትምህርት ለመረዳት አዳጋች እንደሆነ ይሰማቸዋል። ደራሲና የሃይማኖት መሪ የሆኑ አንድ ሰው ይህን አምነው በመቀበል እንዲህ ብለዋል፦ “ይህ ትምህርት ውስን የሆነው የሰው አእምሮ ሊረዳው ከሚችለው በላይ ነው። ሁኔታውን በሰብዓዊ መንገድ መግለጽ ወይም በሰውኛ መንገድ ማስረዳት የማይቻል ነው።” በሌላ በኩል ደግሞ በዝግመተ ለውጥ የሚያምኑ በርካታ ሰዎች አምላክ እንደሌለ ይሰማቸዋል። እነዚህ ሰዎች አስደናቂ የሆኑ የፍጥረት ሥራዎች የተገኙት እንዲሁ በአጋጣሚ እንደሆነ ይናገራሉ። ያም ሆኖ ቻርልስ ዳርዊን የአምላክን ሕልውና ከመካድ ይልቅ እንዲህ ብሏል፦ “እኔ እንደሚመስለኝ ይህ ጉዳይ ከሰው የመረዳት አቅም በላይ ነው ብሎ መደምደሙ ከሁሉ የተሻለ ነው።”
2 እምነታቸው ምንም ይሁን ምን ብዙ ሰዎች ከአምላክ ሕልውና ጋር በተያያዘ ብዙ ጥያቄዎች ይፈጠሩባቸዋል። ይሁንና ለጥያቄዎቻቸው አጥጋቢ ምላሽ ማግኘት ሲያቅታቸው ተስፋ ቆርጠው አምላክን ለማወቅ የሚያደርጉትን ጥረት ያቆማሉ። በእርግጥም ሰይጣን “የማያምኑትን ሰዎች አእምሮ አሳውሯል።” (2 ቆሮ. 4:4) በመሆኑም አብዛኛው የሰው ዘር፣ የአጽናፈ ዓለም ፈጣሪ ስለሆነው ስለ አብ እውነቱን አለማወቁና ግራ መጋባቱ ምንም አያስገርምም።—ኢሳ. 45:18
3. (ሀ) የፈጣሪን ማንነት የገለጠልን ማን ነው? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
3 ወጣም ወረደ ሰዎች ስለ አምላክ እውነቱን ማወቃቸው በጣም አስፈላጊ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም የሚድኑት “የይሖዋን ስም” የሚጠሩ ብቻ ናቸው። (ሮም 10:13) የአምላክን ስም መጥራት ሲባል ስሙ የሚወክለውን አካል በደንብ ማወቅ ማለት ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን አስፈላጊ እውቀት ለደቀ መዛሙርቱ ነግሯቸዋል። በሌላ አባባል የአብን ማንነት ገልጦላቸዋል። (ሉቃስ 10:22ን አንብብ።) ለመሆኑ ኢየሱስ ከማንም በተሻለ የአብን ማንነት መግለጥ ይችላል የምንለው ለምንድን ነው? ይህንን ያደረገውስ እንዴት ነው? አብን ለሌሎች በመግለጥ ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? እስቲ የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ እንመርምር።
ኢየሱስ ክርስቶስ ከማንም የተሻለ ብቃት አለው
4, 5. ኢየሱስ የአባቱን ማንነት ለመግለጥ ከሁሉ የተሻለ ብቃት አለው የምንለው ለምንድን ነው?
4 ኢየሱስ፣ የአባቱን ማንነት በመግለጥ ረገድ ከማንም የተሻለ ብቃት አለው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ‘የአምላክ አንድያ ልጅ’ ሆኖ በሰማይ ይኖር ነበር፤ በዚህ ወቅት ከእሱ በቀር ማንኛውም ሕያው ፍጡር ወደ ሕልውና አልመጣም ነበር። (ዮሐ. 1:14፤ 3:18) ይህ እንዴት ያለ ልዩ መብት ነው! ሌላ ምንም ዓይነት ፍጥረት ወደ ሕልውና ከመምጣቱ በፊት ከአብ ጋር የሚኖረው ኢየሱስ ብቻ ስለነበር አብ ለወልድ ልዩ ትኩረት ለመስጠት አስችሎታል፤ በዚህም የተነሳ ወልድ ስለ አብ ማንነትና ባሕርያት በሚገባ አውቋል። አብና ወልድ ሕልቆ መሳፍርት ለሌላቸው ዘመናት አብረው ሲኖሩ በስፋት የሐሳብ ልውውጥ አድርገው መሆን አለበት፤ ይህ ደግሞ እርስ በርስ ያላቸው ፍቅር ጥልቅ እንዲሆን አድርጓል። (ዮሐ. 5:20፤ 14:31) ወልድ ስለ አባቱ ማንነት ይህ ነው የማይባል እውቀት አካብቶ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም!—ቆላስይስ 1:15-17ን አንብብ።
5 አብ፣ ልጁ “የአምላክ ቃል” ይኸውም የእሱ ቃል አቀባይ እንዲሆን ሾሞታል። (ራእይ 19:13) በመሆኑም ኢየሱስ የአብን ማንነት ለሌሎች ለመግለጥ ከማንም የተሻለ ብቃት አለው። የወንጌል ጸሐፊ የሆነው ዮሐንስም “ቃል” የተባለው ኢየሱስን “በአባቱ እቅፍ” እንዳለ አድርጎ መግለጹ ተገቢ ነው። (ዮሐ. 1:1, 18) ዮሐንስ ይህን መግለጫ ሲጠቀም በወቅቱ በምግብ ሰዓት የነበረውን ልማድ በተዘዋዋሪ መጥቀሱ ነበር። በዚያ ዘመን በአንድ መደብ ላይ የተቀመጡ ሁለት ሰዎች አፍ ለአፍ ገጥመው የማውራት ልማድ ነበራቸው። ተጠጋግተው መቀመጣቸው በደንብ ለማውራት ያመቻቸዋል። በተመሳሳይም ወልድ “በአባቱ እቅፍ” መሆኑ ከእሱ ጋር ስለማንኛውም ጉዳይ እንዲነጋገር አስችሎታል።
6, 7. አብና ወልድ ያላቸው ወዳጅነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ የሄደው እንዴት ነው?
6 አብና ወልድ ያላቸው ወዳጅነት በጊዜ ሂደት እየተጠናከረ ሄዷል። ወልድ፣ አምላክን ‘ዕለት ዕለት ደስ ያሰኘው’ ነበር። (ምሳሌ 8:22, 23, 30, 31ን በ1954 ትርጉም አንብብ።) ሁለቱም አብረው መሥራታቸው ብሎም ወልድ የአብን ባሕርይ ለማንጸባረቅ ጥረት ማድረጉ በመካከላቸው የነበረውን ዝምድና ይበልጥ አጠናክሮታል ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ ነው። ሌሎች የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታት ወደ ሕልውና ከመጡ በኋላ ደግሞ ይሖዋ እያንዳንዱን ፍጥረት እንዴት እንደሚይዝ ተመልክቷል፤ ይህም ለአባቱ ያለው ፍቅርና አድናቆት ይበልጥ ከፍ እንዲል አድርጎ መሆን አለበት።
7 ከጊዜ በኋላ ሰይጣን የይሖዋን ሉዓላዊነት አስመልክቶ ያነሳው ግድድርም ቢሆን ይሖዋ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙት ፍቅሩን፣ ፍትሑን፣ ጥበቡንና ኃይሉን እንዴት እንደሚጠቀምባቸው ለማስተዋል የሚያስችል አጋጣሚ ለወልድ ከፍቶለታል። ይህም ወልድ ራሱ ከጊዜ በኋላ ምድራዊ አገልግሎቱን ሲያከናውን የሚያጋጥሙትን ችግሮች ለመወጣት እንዳዘጋጀው ምንም ጥርጥር የለውም።—ዮሐ. 5:19
8. የወንጌል ዘገባዎች የአብን ባሕርያት ይበልጥ ለማወቅ የሚረዱን እንዴት ነው?
8 ወልድ ከይሖዋ ጋር የተቀራረበ ዝምድና ስለነበረው ከማንም በተሻለ ስለ አብ ማንነት ዝርዝር መረጃ መስጠት ይችላል። እንግዲያው ስለ አብ ለማወቅ አንድያ ልጁ ያስተማረውንና ያደረገውን ነገር ከመመርመር የተሻለ ምን አማራጭ ሊኖር ይችላል? ለምሳሌ ያህል፣ መዝገበ ቃላት በመመልከት ብቻ “ፍቅር” የሚለውን ቃል ትርጉም ሙሉ በሙሉ መረዳት ምን ያህል ሊከብደን እንደሚችል መገመት አያዳግትም። የወንጌል ጸሐፊዎች፣ ኢየሱስ ያከናወነውን አገልግሎትና ሌሎችን የያዘበትን መንገድ አስመልክተው በዝርዝር በጻፏቸው ዘገባዎች ላይ በማሰላሰል ግን “አምላክ ፍቅር ነው” የሚለውን አባባል በጥልቀት መረዳት እንችላለን። (1 ዮሐ. 4:8, 16) የአምላክን ሌሎች ባሕርያት ለማወቅም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው፤ ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ለደቀ መዛሙርቱ የገለጠላቸውን ሌሎች የአምላክ ባሕርያት በደንብ ለማወቅም ተመሳሳይ ነገር ማድረግ ይኖርብናል።
ኢየሱስ አባቱን የገለጠው እንዴት ነው?
9. (ሀ) ኢየሱስ አብን የገለጠው በየትኞቹ ሁለት ዋና ዋና መንገዶች ነው? (ለ) ኢየሱስ የአብን ማንነት በትምህርቶቹ አማካኝነት እንዴት እንደገለጠ የሚያሳይ ምሳሌ ተናገር።
9 ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱና ወደፊት ተከታዮቹ ለሚሆኑት ሰዎች የአብን ማንነት የገለጠላቸው እንዴት ነው? ይህን ያደረገው በሁለት ዋና ዋና መንገዶች ማለትም ባስተማራቸው ትምህርቶችና ባከናወናቸው ነገሮች ነው። እስቲ በመጀመሪያ ኢየሱስ ያስተማራቸውን ነገሮች እንመልከት። ኢየሱስ ለተከታዮቹ ያስተማራቸው ትምህርቶች የአባቱን አስተሳሰብና ስሜት እንዲሁም ነገሮችን የሚያከናውንበትን መንገድ በጥልቀት እንደሚያውቅ የሚያሳዩ ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ አባቱን ብዙ በጎች ካሉትና አንዲት በግ በጠፋችበት ጊዜ ፍለጋ ከሄደ አሳቢ እረኛ ጋር አመሳስሎታል። የመንጋው ባለቤት የጠፋችውን በግ ሲያገኛት “ካልጠፉት ከዘጠና ዘጠኙ ይልቅ በእሷ ይበልጥ” እንደተደሰተ ኢየሱስ ተናግሯል። ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ሲናገር ሊያስተላልፍ የፈለገው ትምህርት ምንድን ነው? “በተመሳሳይም በሰማይ ያለው አባቴ ከእነዚህ ከታናናሾቹ መካከል አንዱም እንዲጠፋ አይፈልግም” በማለት ተናግሯል። (ማቴ. 18:12-14) ታዲያ ከዚህ ምሳሌ ስለ ይሖዋ ምን ትምህርት ማግኘት ትችላለህ? አንዳንድ ጊዜ ምንም እንደማትጠቅምና እንደተጣልክ የሚሰማህ ቢሆንም እንኳ በሰማይ ያለው አባትህ ስለ አንተ ያስባል፤ እንዲሁም ይንከባከብሃል። ይሖዋ ‘ታናናሾች’ ተብለው ከተጠሩት እንደ አንዱ አድርጎ ይቆጥርሃል።
10. ኢየሱስ በድርጊቱ አባቱን የገለጠው እንዴት ነው?
10 ኢየሱስ በድርጊቱ የአባቱን ማንነት ለደቀ መዛሙርቱ ገልጧል። በመሆኑም ሐዋርያው ፊልጶስ “አብን አሳየን” ብሎ ሲጠይቀው ኢየሱስ “እኔን ያየ አብንም አይቷል” ብሎ መናገሩ ትክክል ነው። (ዮሐ. 14:8, 9) ኢየሱስ የአባቱን ባሕርያት እንዴት እንዳንጸባረቀ የሚያሳዩ አንዳንድ ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት። ኢየሱስ በሥጋ ደዌ በሽታ የተያዘ አንድ ሰው እንዲፈውሰው ሲለምነው “መላ ሰውነቱን የሥጋ ደዌ” የወረሰው ቢሆንም ግለሰቡን በመዳሰስ “እፈልጋለሁ፣ ንጻ” አለው። ሰውየው ኢየሱስ ያደረገለትን ነገር ሲመለከት የዚህ ሁሉ ምንጭ ይሖዋ መሆኑን እንደተገነዘበ ምንም ጥርጥር የለውም። (ሉቃስ 5:12, 13) በተጨማሪም አልዓዛር በሞተበት ወቅት ኢየሱስ ‘መንፈሱ ሲታወክ፤ ውስጡም ሲረበሽ’ እንዲሁም ‘እንባውን ሲያፈስ’ ደቀ መዛሙርቱ ሲመለከቱ አባቱ ምን ያህል ሩኅሩኅ እንደሆነ ተገንዘበው መሆን አለበት። ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት እንደሚያስነሳው ቢያውቅም የአልዓዛር ቤተሰቦችና ወዳጆች የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ሲመለከት እሱም በጣም አዝኗል። (ዮሐ. 11:32-35, 40-43) አንተም ኢየሱስ ካደረጋቸው ነገሮች የአብን ምሕረት እንድታስተውል ያስቻሉህ የምትወዳቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች እንደሚኖሩ ምንም ጥያቄ የለውም።
11. (ሀ) ኢየሱስ ቤተ መቅደሱን ለማንጻት የወሰደው እርምጃ ስለ አባቱ ምን ይገልጣል? (ለ) ኢየሱስ ቤተ መቅደሱን እንዳነጻ የሚገልጸው ዘገባ የሚያጽናናን እንዴት ነው?
11 ኢየሱስ ቤተ መቅደሱን ለማንጻት የወሰደው እርምጃስ ምን የሚያስተምረን ነገር አለ? እስቲ ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናህ ለማየት ሞክር፦ ኢየሱስ የገመድ ጅራፍ አበጅቶ ከብቶችና በጎች የሚሸጡ ሰዎችን ከቤተ መቅደሱ አስወጣ። የገንዘብ ለዋጮችንም ሳንቲሞች በተነ፤ እንዲሁም ጠረጴዛዎቻቸውን ገለባበጠ። (ዮሐ. 2:13-17) ኢየሱስ የወሰደ ይህ የኃይል እርምጃ ደቀ መዛሙርቱ ንጉሥ ዳዊት “የቤትህ ቅናት በላችኝ” በማለት የተናገረውን ትንቢት እንዲያስታውሱ አድርጓቸዋል። (መዝ. 69:9) ኢየሱስ ጠንከር ያለ እርምጃ በመውሰድ ለንጹሑ አምልኮ ጥብቅና የመቆም ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው አሳይቷል። ከዚህ ዘገባ የአብን ባሕርይ ማስተዋል ትችላለህ? ይህ ዘገባ አምላክ ክፉዎችን ከምድረ ገጽ ጠራርጎ ለማጥፋት የሚያስችል ይህ ነው የማይባል ኃይል እንዳለው ብቻ ሳይሆን እንዲህ ያለውን እርምጃ ለመውሰድ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለውም ያሳያል። ኢየሱስ ለክፋት ድርጊቶች ምን ያህል ጥላቻ እንዳለው የሚገልጸው ይህ ዘገባ አብ በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ ተንሰራፍቶ የሚገኘውን ክፋት ሲመለከት ምን እንደሚሰማው ያሳያል። ይህን ማወቃችን የፍትሕ መጓደል ሲደርስብን ትልቅ ማጽናኛ ይሆነናል!
12, 13. ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ከያዘበት መንገድ ስለ ይሖዋ ምን እንማራለን?
12 አሁን ደግሞ ሌላ ምሳሌ ይኸውም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን የያዘበትን መንገድ እንመልከት። ደቀ መዛሙርቱ ከሁሉ የሚበልጠው ማን እንደሆነ በተደጋጋሚ ይከራከሩ ነበር። (ማር. 9:33-35፤ 10:43፤ ሉቃስ 9:46) ኢየሱስ ከአባቱ ጋር ረጅም ዘመን አብሮ የኖረ እንደመሆኑ መጠን ይሖዋ እንዲህ ላለው የኩራት ዝንባሌ ምን አመለካከት እንዳለው ያውቃል። (2 ሳሙ. 22:28፤ መዝ. 138:6) ከዚህም በላይ ሰይጣን ዲያብሎስ እንዲህ ዓይነቱን ዝንባሌ ሲያንጸባርቅ ተመልክቷል። ይህ ራስ ወዳድ የሆነ መንፈሳዊ ፍጡር የሥልጣን ጥመኛ ከመሆኑም በላይ ከፍ ተደርጎ የመታየት ምኞት የተጠናወተው መሆኑን አሳይቷል። በመሆኑም ኢየሱስ፣ ሥልጠና የሰጣቸው ደቀ መዛሙርቱ ሥልጣን የመፈለግ ዝንባሌ ያለቀቃቸው መሆኑን ሲመለከት ምን ያህል አዝኖ ይሆን? ሐዋርያት እንዲሆኑ በመረጣቸው ደቀ መዛሙርቱ መካከልም እንኳ ይህ ባሕርይ ይታይ ነበር! ኢየሱስ ምድራዊ ሕይወቱን እስካጠናቀቀበት ዕለት ድረስ የሥልጣን ምኞት እንደነበራቸው አሳይተዋል። (ሉቃስ 22:24-27) ያም ቢሆን ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ውሎ አድሮ የእሱን አርዓያ ተከትለው የትሕትና ባሕርይ እንደሚያዳብሩ ተስፋ በማድረግ እነሱን በደግነት መገሠጹን ቀጥሎ ነበር።—ፊልጵ. 2:5-8
13 ታዲያ ኢየሱስ የደቀ መዛሙርቱን የተሳሳተ ዝንባሌ በትዕግሥት ለማረም ጥረት ካደረገበት መንገድ የይሖዋን ማንነት ለማስተዋል ቻልክ? ኢየሱስ ካደረጋቸውና ከተናገራቸው ነገሮች በመነሳት አብ፣ ሕዝቦቹ በተደጋጋሚ ጊዜያት ስህተት ቢሠሩም እንደማይጥላቸው አስተዋልክ? ይሖዋ እንዲህ ዓይነት ባሕርያት ያሉት አምላክ መሆኑን ማወቃችን ስህተት በምንሠራበት ጊዜ ንስሐ መግባታችንን በጸሎት እንድንገልጽ አያነሳሳንም?
ወልድ በፈቃደኝነት አብን ገልጦታል
14. ኢየሱስ የአባቱን ማንነት ለመግለጥ ፈቃደኛ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?
14 አምባገነን የሆኑ በርካታ መሪዎች ሕዝቦቻቸውን በቁጥጥራቸው ሥር ለማድረግ ያመቻቸው ዘንድ አንዳንድ ጠቃሚ መረጃዎችን ከዜጎቻቸው ለመደበቅ ይሞክራሉ። ኢየሱስ ግን ከዚህ በተቃራኒ ስለ አባቱ የሚያውቀውን ነገር ለሌሎች በመንገር አብን ሙሉ በሙሉ ለመግለጥ ፈቃደኛ ነበር። (ማቴዎስ 11:27ን አንብብ።) ከዚህም በተጨማሪ ደቀ መዛሙርቱ “ስለ እውነተኛው አምላክ እውቀት” ማግኘት እንዲችሉ የማስተዋል ችሎታ ሰጥቷቸዋል። (1 ዮሐ. 5:20) ይሁንና የማስተዋል ችሎታ ሰጥቷቸዋል ሲባል ምን ማለት ነው? ደቀ መዛሙርቱ፣ ስለ አብ የሚያስተምራቸውን ትምህርቶች መረዳት እንዲችሉ ኢየሱስ አእምሯቸውን ከፍቶላቸው ነበር። አብ የሥላሴ ክፍል ነው እንደሚሉ ያሉ ለመረዳት አስቸጋሪ የሆኑ ትምህርቶችን በማስተማር የአባቱን ማንነት አልሰወረም።
15. ኢየሱስ ስለ አባቱ አንዳንድ ነገሮችን ለደቀ መዛሙርቱ ከመንገር የተቆጠበው ለምንድን ነው?
15 ኢየሱስ ስለ አባቱ የሚያውቀውን ነገር በሙሉ ለሌሎች ገልጦ ነበር? እንደዚህ አላደረገም፣ እንዲያውም የሚያውቀውን ነገር በሙሉ ባለመናገር ጥበበኛ መሆኑን አሳይቷል። (ዮሐንስ 16:12ን አንብብ።) ሁሉንም ነገር ከመናገር የተቆጠበው ለምንድን ነው? ምክንያቱም የሚያውቀውን በሙሉ ቢነግራቸው በወቅቱ ‘ሊሸከሙት አይችሉም’ ነበር። ይሁን እንጂ “ወደ እውነት ሁሉ” የሚመራቸው ‘ረዳት’ ማለትም መንፈስ ቅዱስ ሲመጣ ከፍተኛ እውቀት እንደሚገለጥላቸው ኢየሱስ ተናግሯል። (ዮሐ. 16:7, 13) ጥበበኛ የሆነ ወላጅ ልጆቹ ነገሮችን መረዳት የሚችሉበት ዕድሜ ላይ እስኪደርሱ ድረስ አንዳንድ ነገሮችን ከመንገር እንደሚቆጠብ ሁሉ ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱ ስለ አብ አንዳንድ እውነታዎችን ለመረዳት የሚያስችል ብስለት እስኪያገኙ ድረስ ጠብቋል። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ያለባቸውን የአቅም ገደብ ከግምት ውስጥ ማስገባቱ ደግ እንደነበር ያሳያል።
ሌሎች ይሖዋን እንዲያውቁት በመርዳት ኢየሱስን ምሰሉ
16, 17. አብን ለሌሎች ለመግለጥ ብቃቱ አለህ ሊባል የሚችለው እንዴት ነው?
16 አንድን ሰው በደንብ ስታውቀውና ጥሩ ጥሩ ባሕርያት እንዳሉት ስትገነዘብ ስለ እሱ ለሌሎች ሰዎች ለመናገር አትገፋፋም? ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ ስለ አባቱ ለሌሎች ይናገር ነበር። (ዮሐ. 17:25, 26) እኛስ የይሖዋን ማንነት ለሰዎች በመግለጥ ረገድ የእሱን ምሳሌ መከተል እንችላለን?
17 ከላይ እንዳየነው ኢየሱስ ስለ አባቱ ከማንም የበለጠ ጥልቅ እውቀት አለው። ያም ሆኖ ኢየሱስ የሚያውቃቸውን ነገሮች ለሌሎች ለማካፈል ፈቃደኛ ነበር፤ ሌላው ቀርቶ ተከታዮቹ ከአባቱ ማንነት ጋር የተያያዙ አንዳንድ ጥልቅ እውነቶችን መገንዘብ እንዲችሉ የማስተዋል ችሎታ ሰጥቷቸዋል። ከኢየሱስ ባገኘነው እርዳታ አማካኝነት ከሌሎች እጅግ በላቀ መንገድ በሰማይ ስለሚኖረው አባታችን ማወቅ ችለናል ቢባል አትስማማም? ኢየሱስ ባስተማራቸው ትምህርቶችና ባደረጋቸው ነገሮች አማካኝነት አባቱን ለእኛ ለመግለጥ ፈቃደኛ በመሆኑ በጣም አመስጋኞች ነን! እንዲያውም አብን በማወቃችን ኩራት ቢሰማን የሚገርም አይደለም። (ኤር. 9:24፤ 1 ቆሮ. 1:31) ወደ ይሖዋ ለመቅረብ ጥረት በማድረጋችን እሱም ወደ እኛ ቀርቧል። (ያዕ. 4:8) በመሆኑም ያገኘነውን እውቀት ለሌሎች ለማካፈል ብቃቱ አለን። ይሁንና ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
18, 19. አብን ለሌሎች መግለጥ የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው? አብራራ።
18 በአነጋገራችንም ሆነ በድርጊታችን አብን በመግለጥ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል ይኖርብናል። በመስክ አገልግሎት ላይ የምናገኛቸው ብዙ ሰዎች የአምላክን ማንነት እንደማያውቁ ማስታወሳችን ጥሩ ነው። የሐሰት ትምህርቶች ስለ አምላክ እውነቱን እንዳይረዱ ጋርደውባቸዋል። በመሆኑም ስለ አምላክ ስም፣ እሱ ለሰው ልጆች ስላለው ዓላማና ስለ ማንነቱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሌሎችን ልናስተምር እንችላለን። ከዚህም በተጨማሪ የአምላክን ማንነት ከዚህ በፊት አስተውለነው በማናውቀው መልኩ የሚገልጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን ስናገኝ ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ልንወያይባቸው እንችላለን። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ እነሱም ተጠቃሚ ይሆናሉ።
19 በምግባራችን አብን በመግለጥ ረገድስ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? ሰዎች የምናደርጋቸውን ነገሮች በመመልከት የክርስቶስን ፍቅር ማስተዋል ይችላሉ፤ ይህ ደግሞ ወደ ኢየሱስና ወደ አብ እንዲቀርቡ ያደርጋቸዋል። (ኤፌ. 5:1, 2) ሐዋርያው ጳውሎስ እሱ ‘የክርስቶስን አርዓያ እንደተከተለ ሁሉ እኛም የእሱን አርዓያ እንድንከተል’ አበረታቶናል። (1 ቆሮ. 11:1) በምግባራችን አማካኝነት ሰዎች የይሖዋን ማንነት እንዲያውቁ መርዳት እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! እንግዲያው ሁላችንም፣ አብን ለሌሎች በመግለጥ ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ መከተላችንን እንቀጥል።