እውነት የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል
ምንም እንኳ ሁኔታው የሚያሳዝን ቢሆንም በጊዜያችን የሚገኙ ብዙ ሰዎች ሕይወታቸው በችግር የተሞላና ተስፋ አስቆራጭ መሆኑ ምንም አያጠያይቅም። እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ደስታ ማግኘት ይችላሉን? አንዳንዶቹ ሰዎች በሌሎች ላይ የሚያደቡ ወንጀለኞች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ወደፊት የኅብረተሰቡ ሐቀኛ አባላት ለመሆን ይችላሉን? የሁለቱም ጥያቄዎች መልስ አዎን የሚል ነው። ሰዎች ሊቀየሩ ይችላሉ። አኗኗራቸው ሊለወጥ ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህ እንዴት ሊሆን እንደሚችል ሲገልጽ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።”—ሮሜ 12:2
‘ፍጹም ስለሆነው የእግዚአብሔር ፈቃድ’ የሚገልጽ ሐሳብ መጠቀሱ ጳውሎስ እነዚህን ቃላት ከመጻፉ ከ20 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የተናገረውን ያስታውሰናል። ኢየሱስ “እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል” ብሏል። (ዮሐንስ 8:32) ኢየሱስ “እውነት” ሲል አምላክ በመንፈሱ አማካኝነት የሰጠውን መረጃ፣ በተለይም ለእኛ ሲባል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጾ የሚገኘውን ስለ አምላክ ፈቃድ የሚናገረውን መረጃ ማለቱ ነው። (ዮሐንስ 17:17) የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በእርግጥ ሰዎችን ነፃ ያወጣልን? ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ መኖር በእርግጥ የሰዎችን ሕይወት ሊቀይር ይችላልን? በእርግጥ ይችላል። ጥቂት ምሳሌዎችን ተመልከት።
ዓላማ ያለው ሕይወት
በጂብራልታር የሚኖረው ሞይሴስ ከጥቂት ጊዜ በፊት ምንም ደስታ የሌለው ሰው ነበር። እንዲህ ይላል:- “ሰካራም ነበርኩ። የማድረውም በጎዳና ላይ ነበር። ሕይወቴ እንደተበላሸ ይሰማኝ ነበር። በእያንዳንዱ ምሽት አምላክ ምሕረት እንዲያደርግልኝና በችግር የተሞላ ተጨማሪ ቀን እንዳያሳየኝ እለምነው ነበር። ለምንም ነገር የማልረባ ከሆንኩ፣ ሥራና ቤተሰብ ከሌለኝ እንዲሁም ማንም የሚረዳኝ ሰው ከሌለ ለምን ወደዚህ ዓለም እንደመጣሁ አምላክን እያለቀስሁ እጠይቅ ነበር። የእኔ መኖር ትርጉሙ ምንድን ነው?” ከዚያ በኋላ አንድ ነገር ተከሰተ።
ሞይሴስ በመቀጠል እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “የይሖዋ ምሥክር ከሆነው ከሮቤርቶ ጋር ስገናኝ አምላክ ጸሎቴን እንደሰማልኝ አወቅሁ። ሮቤርቶ መጽሐፍ ቅዱስና አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተባለ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚያስችል ጽሑፍ ሰጠኝ።a ሌሊቱን ተኝቼ በማሳልፍባት አግዳሚ ወንበር ላይ ቁጭ ብለን በየቀኑ መጽሐፍ ቅዱስን እናጠና ነበር። ከአንድ ወር በኋላ ሮቤርቶ በአቅራቢያው በሚገኝ የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ወደሚደረግ ስብሰባ ወሰደኝ። ብዙም ሳይቆይ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አመለካከቴን ሙሉ በሙሉ ለወጠው። በጎዳና ላይ ማደሬን፣ መጠጣቴንም ሆነ ማጨሴን አቆምኩ። ሕይወቴ ተቀይሯል፤ ደስተኛም ነኝ። በቅርብ ጊዜ ውስጥ ተጠምቄ ከምሥክሮቹ እንደ አንዱ በመሆን ይሖዋን እንደማገለግል ተስፋ አደርጋለሁ።”
እንዴት ያለ ለውጥ ነው! ብዙውን ጊዜ ሰዎች ከእውቀት ማጣት የተነሣ ተስፋ ቢስ ይሆናሉ። ስለ አምላክ ወይም ስለ አስደናቂ ዓላማዎቹ አያውቁም። ሞይሴስ ይህን እውቀት መቅሰሙ ሕይወቱን ለመለወጥ የሚያስችል ጥንካሬና ድፍረት እንዲያገኝ አስችሎታል። የሚከተለው የመዝሙራዊው ጸሎት በሞይሴስ ሁኔታ ላይ መልስ አግኝቷል:- “ብርሃንህንና እውነትህን ላክ፤ እነርሱ ይምሩኝ፣ ወደ ቅድስናህ ተራራና ወደ ማደሪያህ ይውሰዱኝ።”—መዝሙር 43:3
በቤሊዝ የሚኖረው ዳንኤል ተመሳሳይ የሆነ ተሞክሮ አለው። ዳንኤል በጎዳና ላይ የሚያድር ሰው አልነበረም፤ ጥሩ ሥራ ነበረው። ይሁን እንጂ ለ20 ዓመታት ያህል ከአደንዛዥ ዕፅና ከአልኮል ሱስ ጋር ታግሏል፤ እንዲሁም ከሥነ ምግባር ውጪ የሆነ ሕይወት ይመራ ነበር። ዳንኤል በካቶሊክ ቤተሰብ ውስጥ ያደገ ቢሆንም ሕይወት ለእሱ ትርጉም አልነበረውም፤ የአምላክንም መኖር ተጠራጠረ። ወደ ተለያዩ ቤተ ክርስቲያኖች በመሄድ እርዳታ ለማግኘት ጥሯል። ይሁን እንጂ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱት ብዙዎቹ ጓደኞቹም ሆኑ የሚያውቃቸው አንዳንድ ቀሳውስት አደንዛዥ ዕፅንም ሆነ አልኮልን አላግባብ እንደሚጠቀሙ ተመለከተ። ይህ በእንዲህ እንዳለ ደግሞ ሚስቱ ልትፈታው በዝግጅት ላይ ነበረች።
ዳንኤል ተስፋ በመቁረጡ ሰዎች ካሉባቸው ሱሶች እንዲላቀቁ የሚያስችል ፕሮግራም ወደሚሰጥበት ወደ አንድ የሕክምና ተቋም ሄደ። ይሁንና በሕክምና ተቋሙ የሚሰጠውን ትምህርት ካጠናቀቀም በኋላ ተጨማሪ እርዳታ ካላገኘ ወደ ቀድሞ ሁኔታው እንደሚመለስ ያውቅ ነበር። ሆኖም ማግኘት ያለበት ምን ዓይነት እርዳታ ነው? ዳንኤል ከሕክምና ተቋሙ በግንቦት 1996 ከወጣ ከሁለት ቀናት በኋላ ወደ አንድ የይሖዋ ምሥክር ቀርቦ “እባክህ መጽሐፍ ቅዱስን አስጠናኝ” በማለት ለመነው። በዚህ ጥያቄ የተገረመው ይህ ወንድም ከዳንኤል ጋር በሳምንት ሁለት ቀን ለማጥናት ዝግጅት አደረገ። ዳንኤልም ወዲያውኑ ሕይወቱን ከአምላክ ፈቃድ ጋር ማስማማት ጀመረ። የቀድሞ ጓደኞቹን በመተው አደንዛዥ ዕፅንም ሆነ አልኮልን አላግባብ ከማይወስዱትና የጾታ ብልግናን ከሚጸየፉት ክርስቲያኖች ጋር ጓደኝነትን መሠረተ። በዚህ መንገድ ዳንኤል መጽሐፍ ቅዱስ የሚለው ትክክል መሆኑን ተገንዝቧል:- “ከጠቢባን ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የሰነፎች ባልንጀራ ግን ክፉ መከራን ይቀበላል።” (ምሳሌ 13:20) “በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ንጹሕ ሕሊና ማግኘት ምን ማለት እንደሆነ ተገነዘብኩ” ሲል የተናገረው ብዙም ሳይቆይ ነበር። የዳንኤል ሕይወትም ተለውጧል።
በፖርቶ ሪኮ የሚኖር አንድ ሌላ ሰው የሚያስደንቅ ለውጥ አድርጓል። ይህ ሰው ታስሮ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ብዙ ሰዎች በመግደሉ በጣም አደገኛ እንደሆነ ተደርጎ ይታይ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ይለውጠው ይሆን? አዎን። አንድ የይሖዋ ምሥክር የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔት ጥቂት ቅጂዎችን ሊሰጠው ችሎ ነበር። ሰውየው ወዲያውኑ ተጨማሪ መጽሔቶችን ለማግኘት ጠየቀ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከጀመረ በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ልቡን መንካት ሲጀምር በግልጽ የሚታይ ለውጥ አደረገ። ለውጥ ማድረጉን ከሚያሳዩት እርምጃዎች መካከል የመጀመሪያው ረዥም ፀጉሩን መስተካከሉና የተንጨባረረ ጺሙን መላጨቱ ነበር።
አምላክ ንስሐ የሚገቡና አኗኗራቸውን የሚቀይሩ ኃጢአተኞችን ይቅር እንደሚል መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ጳውሎስ “ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን? . . . ከእናንተም አንዳንዶቹ እንደ እነዚህ ነበራችሁ፤ ነገር ግን . . . ታጥባችኋል” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 11) እነዚህ ቃላትም ሆኑ በሥራ 24:15 ላይ የሚገኙት ‘ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሞት ይነሣሉ’ የሚሉት ቃላት ይህን ሰው እንዳጽናኑት ምንም ጥርጥር የለውም። እንዲህ ብሏል:- “ለሕልፈተ ሕይወት የዳረግኋቸውን ሰዎች ይቅርታ ለመጠየቅ እንድችል ሙታን በትንሣኤ ሲነሡ በዚያ ለመገኘት እፈልጋለሁ።”
አዲስ ቤተሰብ
በአርጀንቲና፣ የይሖዋ ምሥክሮች የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ የሆነው ሉዪስ አንድ ቀን አሳዛኝ የሕይወት ታሪክ ካለው ከአንድ ወጣት ጋር ይተዋወቃል። ይህ ወጣት ወላጆቹ ወልደው ስለጣሉት ያደገው በተለያዩ ተቋሞች ውስጥ ነበር። ዕድሜው 20 ዓመት ገደማ ሲሆን እናቱ የምትገኝበትን አካባቢ ስላወቀ አብሯት ለመኖር ወሰነ። ጠንክሮ በመሥራት ጠቀም ያለ ገንዘብ ካጠራቀመ በኋላ እናቱ ወደምትኖርበት ከተማ ሄደ። እናቱ ያጠራቀመው ገንዘብ እስኪሟጠጥ ድረስ አብሯት እንዲኖር አደረገች። ገንዘቡ ባለቀ ጊዜ ግን ቤቷን ለቅቆ እንዲሄድላት ጠየቀችው። ይህ የእናቱ ድርጊት ራሱን ለመግደል እንዲነሣሣ አድርጎት ነበር።
ይሁን እንጂ ሉዪስ ለዚህ ወጣት የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ሊያካፍለው ችሎ ነበር። ይህ እውነት ደግሞ “አባቴና እናቴ ትተውኛልና፣ እግዚአብሔር ግን ተቀበለኝ” የሚለውን ዋስትና የሚጨምር ነበር። (መዝሙር 27:10) ይህ ወጣት በፍጹም የማይከዳ ሰማያዊ አባት እንዳለው ሊገነዘብ ችሏል። በአሁኑ ጊዜ የአንድ አዲስ ቤተሰብ ማለትም የይሖዋ ቤተሰብ አባል በመሆኑ ደስተኛ ነው።
በዚያው አገር የሚገኝ አንድ ሌላ ሰው ለአንድ የይሖዋ ምሥክር መጠበቂያ ግንብ የተባለውን መጽሔት እንደሚወደው ይነግረዋል። ለምን? ምክንያቱም ትዳሩን ከመፍረስ አድኖለታል። ይህ ሰው አንድ ቀን ከሥራው ሲመለስ “ፍቺ” የሚል በትልቁ የተጻፈ ርዕስ ያለው አንድ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት በቆሻሻ መጣያ ቅርጫት ውስጥ ተጥሎ ያያል። ትዳሩ በችግር ውስጥ ይገኝ ስለነበርና እሱና ሚስቱ ደግሞ በሕጋዊ መንገድ ለመለያየት በዝግጅት ላይ ስለነበሩ መጽሔቱን ከወደቀበት አንስቶ ማንበብ ጀመረ። መጽሔቱን ወደ ቤቱ በመውሰድ ከሚስቱ ጋር ሆኖ አነበበው። ባልና ሚስቱ በመጽሔቱ ላይ የሚገኘውንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን ምክር በሥራ ላይ ለማዋል ጥረት አደረጉ። (ኤፌሶን 5:21–6:4) ወዲያውኑ ግንኙነታቸው ተሻሻለ። ተለያይተው ለመኖር የነበራቸውን ሐሳብ በመተው እነዚህ ባልና ሚስት በአንድነት መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ላይ ይገኛሉ።
በኡራጉዋይ የሚኖር ሉዪስ የሚባል አንድ ሌላ ሰው ምንም ደስታ አልነበረውም። የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኛ ከመሆኑም በላይ በመናፍስታዊ ድርጊቶች የሚካፈል፣ ጣዖት የሚያመልክና ያለልክ የሚጠጣ መሆኑ ሕይወቱን አመሰቃቅሎት ነበር። በመጨረሻም ሉዪስ ሙሉ በሙሉ ተስፋ በመቁረጡ በአምላክ መኖር የማያምን ሰው ሆነ። አንድ ጓደኛው ሕይወት የተገኘው እንዴት ነው? በዝግመተ ለውጥ ወይስ በፍጥረት? (የእንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ሰጠው።b ይህ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ለአጭር ጊዜ ለመገናኘት ያስችለው እንጂ ሉዪስ ብዙም ሳይቆይ ወደ መጠጥና አደንዛዥ ዕፅ ልማዱ ተመለሰ። በከፍተኛ ሐዘን ተውጦ በነበረበት ወቅት በአንድ የቆሻሻ መጣያ ጉድጓድ ውስጥ ቁጭ ብሎ ጸለየ። ትክክለኛው የአምላክ ስም ማን መሆኑን ስለተጠራጠረ “የኢየሱስ ክርስቶስ አባት” በማለት ወደ አምላክ ጸለየ።
በሕይወት የመኖሩ ዓላማ ምን እንደሆነ እንዲጠቁመው አምላክን ጠየቀ። “በሚቀጥለው ቀን” አለ ሉዪስ “አንድ የማውቀው ሰው እሱ የማይፈልገውን አንድ መጽሐፍ ሰጠኝ። ርዕሱ ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል! የሚል ነበር።”c መጽሐፉ ለጥያቄው መልስ እንዲያገኝ ረዳው። ሉዪስ አምላክን እንዴት ማገልገል እንደሚገባው የሚያሳየውን ሃይማኖት ለማግኘት እንዲችል በድጋሚ ጸለየ። የበሩ ደወል ተደውሎ በሩ ሲከፈት የመጡት ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች መሆናቸው እንዴት የሚያስገርም ነበር! ሉዪስ ወዲያውኑ ከእነሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። ፈጣን እድገት አደረገ። አሁን የተጠመቀ ምሥክር በመሆኑ ተባርኳል። ንጹሕ የሆነ ሕይወት ከመምራትም አልፎ ሌሎችም ዓላማ ያለው ሕይወት እንዲኖራቸው እየረዳ ነው። “ሥጋ ሁሉ ጸሎትን ወደምትሰማ ወደ አንተ ይመጣል” የሚሉትን የመዝሙር 65:2ን ቃላት እውነት ሆነው አግኝቷቸዋል።
በፊሊፒንስ የሚኖረው አለን በተማሪዎች ንቅናቄ ላይ ይሳተፍ ነበር። “መጪው ትውልድ እኩልነትን እንዲያገኝ በወቅቱ የነበረውን መንግሥት ከሥልጣን ለማስወገድ” ዓላማ ያለው የአንድ ድርጅት አባል ነበር። ነገር ግን አንድ ቀን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ይገናኝና አምላክ ለሰው ልጆች ያለውን ዓላማ ከመጽሐፍ ቅዱስ ይማራል። ይህ ዓላማ የሚከተለውን በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ተስፋን ያካትታል:- “ገና ጥቂት ኃጢአተኛም አይኖርም . . . ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።” (መዝሙር 37:10, 11) አለን እንዲህ ብሏል:- “ንቅናቄያችን ይታገልለት የነበረው ነገር ወደፊት እንደሚፈጸም ከብዙ ጊዜ በፊት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ቃል የተገባ መሆኑን ተገነዘብኩ። እጅግ እንሻቸው የነበሩ ነገሮች በሙሉ በአምላክ መንግሥት አማካኝነት እውን ይሆናሉ።” በአሁኑ ጊዜ አለን የአምላክ መንግሥት ደጋፊ ሲሆን ሌሎች ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ላይ እምነት እንዲኖራቸው በመርዳት ላይ ይገኛል።
አዎን፣ ሰዎች የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን እውነት ሲቀበሉ ሕይወታቸው ይለወጣል። በሕይወት የሚተርፉ የሰው ዘሮች በሙሉ ሕይወታቸውን ከአምላክ ፈቃድ ጋር አስማምተው የሚኖሩበት ጊዜ በቅርቡ እንደሚመጣ የተረጋገጠ ነው። ይህ እንዴት ያለ ለውጥ ይሆናል! ከዚያ በኋላ “በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ አይጎዱም አያጠፉምም፤ ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለችና” የሚለው ትንቢት ፍጻሜውን ያገኛል።—ኢሳይያስ 11:9
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።
b ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።
c ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።