“ብርሃንም ወደ ዓለም መጣ”
“ብርሃንም ወደ ዓለም ስለመጣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለወደዱ ፍርዱ ይህ ነው።”—ዮሐንስ 3:19
1. የአምላክ ፍርድ ጉዳይ ማንኛውንም ሰው ሊያሳስበው የሚገባው ለምንድነው?
በአሁኑ ጊዜ የሚኖሩት አብዛኞቹ ሰዎች ስለ አምላክ ፍርድ እምብዛም አይጨነቁም። አንዳንድ ሰዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን አዘውትረው ከሄዱና ጎረቤቶቻቸውን የሚጎዳ ነገር ካልሠሩ አምላክ ጥሩ ፍርድ እንደሚበይንላቸው ያምናሉ። ብዙ ሰዎች ሕዝበክርስትና ስለ ሲኦል እሳትና ስለ መንጽሔ የምታስተምረው መሠረተ ትምህርት የመለኮታዊ ፍርድን አጠቃላይ ሐሳብ አቃልለው እንዲመለከቱ አድርጎአቸዋል። ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ግዴለሽነትና የሕዝበ ክርስትና ውሸት እያንዳንዱ ሰው በመጨረሻው በአምላክ የሚፈረድ የመሆኑን ቁምነገር ሊለውጥ አይችልም። (ሮሜ 14:12፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:1፤ ራእይ 20:13) በዚህ ፍርድ ላይ የተመኩ ብዙ ነገሮች አሉ። ጥሩ ፍርድ የሚያገኙት ሰዎች የአምላክን የዘላለም ሕይወት ስጦታ ሲቀበሉ ጥሩ ፍርድ የማያገኙት ደግሞ የኃጢአትን ሙሉ ደመወዝ ማለትም ሞትን ይቀበላሉ።—ሮሜ 6:23
2. ለአምላክ ፍርድ መሠረቱ ምንድነው?
2 ስለዚህ እውነተኛ ክርስቲያኖች ሁሉ የአምላክ ፍርድ ጉዳይ ያሳስባቸዋል። አምላክንም ለማስደሰት ከልባቸው ይጥራሉ። ታዲያ እርሱን ሊያስደስቱት የሚችሉት እንዴት ነው? ኢየሱስ በዮሐንስ 3:19 ላይ የዚህን መልስ ይሰጠናል። እንዲህ አለ፦ “ብርሃንም ወደ ዓለም ስለመጣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለወደዱ ፍርዱ (በዚህ ላይ የተመሠረተ ነው [አዓት]) ይህ ነው።” አዎን የአምላክ ፍርድ የሚመሠረተው ወይም የሚመካው ከጨለማ ይልቅ ብርሃንን የምንወድ በመሆናችን ላይ ነው።
“አምላክ ብርሃን ነው”
3. ጨለማው ምንድነው? ብርሃኑስ ምንድነው?
3 ብዙ ጊዜ ሰይጣን “የብርሃን መልአክ” መስሎ ቢታይም ጨለማ በመንፈሳዊ አባባል በሰይጣን ግዛት ያለውን ድንቁርናና ተስፋቢስነት ያመለክታል። (2 ቆሮንቶስ 4:4፤ 11:14፤ ኤፌሶን 6:12) በሌላ በኩል ደግሞ ብርሃን ከይሖዋ አምላክ የሚመጣውን ዕውቀትና ማስተዋል ያመለክታል። ጳውሎስ “በክርስቶስ ፊት የእግዚአብሔርን የክብሩን እውቀት ብርሃን እንዲሰጥ በልባችን ውስጥ የበራ በጨለማ ብርሃን ይብራ ያለ እግዚአብሔር ነውና” በማለት በጻፈ ጊዜ ስለዚህ ብርሃን ተናግሯል። (2 ቆሮንቶስ 4:6) መንፈሳዊ ብርሃን ከይሖዋ አምላክ ጋር የቅርብ ግንኙነት አለው። ሐዋርያው ዮሐንስ “እግዚአብሔር ብርሃን ነው” ብሎ ለመጻፍ የበቃውም በዚህ ምክንያት ነው።—1 ዮሐንስ 1:5፤ ራእይ 22:5
4. (ሀ) ይሖዋ ብርሃንን ያስገኘው እንዴት ነው? (ለ) ለብርሃን ፍቅር ልናሳይ የምንችለው በምን መንገድ ነው?
4 ይሖዋ ብርሃን እንዲታይ ያደረገው በዛሬው ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በጽሑፍ ሰፍሮ እንደልብ ተሰራጭቶ በሚገኘው ቃሉ አማካኝነት ነው። (መዝሙር 119:105፤ 2 ጴጥሮስ 1:19) ስለዚህ መዝሙራዊው “አቤቱ ሕግህን እንደምን እጅግ ወደድሁ! ቀኑን ሁሉ እሱ ትዝታዬ ነውና። ነፍሴ ምስክርህን ጠበቀች። እጅግም ወደደችው” ብሎ በጻፈ ጊዜ ለብርሃን የነበረውን እርግጠኛ ፍቅር ገልጾአል። (መዝሙር 119:97, 167) አንተስ የመዝሙራዊውን ያህል ብርሃንን ታፈቅራለህን? የአምላክን ቃል አዘውትረህ ታነባለህን? ታሰላስለዋለህን? የሚናገረውንስ በተግባር ለመተርጐም ትጥራለህን? (መዝሙር 1:1-3) ከሆነ ከይሖዋ ጥሩ ፍርድ ለማግኘት በመፈለግ ላይ ነህ ማለት ነው።
“እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ”
5. መለኮታዊው ብርሃን የሚያተኩረው በማን ላይ ነው?
5 ከይሖዋ የሚገኘው ሕይወት ሰጪ ብርሃን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያተኮረ ነው። በዮሐንስ ወንጌል መግቢያ ላይ “በእርሱ ሕይወት ነበረች። ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች። ብርሃን በጨለማ ይበራል። ጨለማም አላሸነፈውም” የሚል እናነባለን። (ዮሐንስ 1:4, 5) እውነትም ኢየሱስ ከብርሃን ጋር የተቀራረበ ኅብረት ስለነበረው “ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን” ተብሎ ተጠርቶአል። (ዮሐንስ 1:9) ኢየሱስም ራሱ “በዓለም ሳለሁ የዓለም ብርሃን ነኝ” ብሏል።—ዮሐንስ 9:5
6. አንድ ሰው ወደ ዘላለም ሕይወት የሚያመራ ጥሩ ፍርድ ለማግኘት ምን ማድረግ አለበት?
6 ስለዚህ ብርሃንን የሚያፈቅሩ ሰዎች ኢየሱስን ያፈቅሩታል፤ በእርሱም ያምናሉ። ከኢየሱስ ውጭ ሆኖ ወይም ከኢየሱስ ተለይቶ ጥሩ ፍርድ ማግኘት አይቻልም። አዎን ኢየሱስ መዳንን ወይም ደህንነትን ለመስጠት በአምላክ የተሾመ እንደመሆኑ ጥሩ ፍርድ ልናገኝ የምንችለው ተስፋችንን እርሱ ላይ በመጣል ብቻ ነው። ኢየሱስ “በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው። በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቁጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም” ብሏል። ታዲያ በኢየሱስ ማመን ምን ማለት ነው?
7. በኢየሱስ ማመን በሌላ በማን ማመንን ያመለክታል?
7 መጀመሪያ ነገር ኢየሱስ ራሱ “በእኔ የሚያምን በላከኝ ማመኑ ነው እንጂ በእኔ አይደለም። እኔንም የሚያይ የላከኝን ያያል። በእኔ የሚያምን ሁሉ በጨለማ እንዳይኖር እኔ ብርሃን ሆኜ ወደ ዓለም መጥቻለሁ” ብሏል። (ዮሐንስ 12:44-46) ኢየሱስን የሚያፈቅሩና በእሱም የሚያምኑ የኢየሱስ አምላክና አባት ለሆነው ለይሖዋም ጥልቅ ፍቅርና እምነት ሊኖራቸው ይገባል። (ማቴዎስ 22:37፤ ዮሐንስ 20:17) በአምልኮታቸው የኢየሱስን ስም እየተጠቀሙ ለይሖዋ የበለጠ ክብር የማይሰጡ ሁሉ ለብርሃን እውነተኛ ፍቅር አያሳዩም።—መዝሙር 22:27፤ ሮሜ 14:7, 8፤ ፊልጵስዩስ 2:10, 11
የአምላክ “ዋና ወኪል”
8. ኢየሱስ ሰው ሆኖ ከመወለዱ በፊት እንኳን ሳይቀር መለኮታዊ ብርሃን በእርሱ ላይ ያተኮረው እንዴት ነበር?
8 በኢየሱስ ማመን ማለት ኢየሱስ በይሖዋ ዓላማ ውስጥ ያለውን ድርሻ ሙሉ በሙሉ መቀበል ማለት ነው። ይህም መልአኩ ለዮሐንስ “የኢየሱስ ምስክር የትንቢት መንፈስ ነውና” ወይም እንደ አዓት “ትንቢት የሚነገረው ስለኢየሱስ ለመመስከር ነው” ሲል በተናገረው ቃል ግልጽ ሆኖአል። (ራእይ 19:10፤ ሥራ 10:43፤ 2 ቆሮንቶስ 1:20) በመለኮታዊ መንፈስ አነሣሽነት የተነገሩ ትንቢቶች ሁሉ፣ በኤደን ከተነገረው ከመጀመሪያው ትንቢት ጀምሮ ከኢየሱስና ኢየሱስ በአምላክ ዓላማዎች አፈጻጸም ውስጥ ካለው ቦታ ጋር ግንኙነት ያላቸው ናቸው። በተመሳሳይም ጳውሎስ ለገላትያ ክርስቲያኖች የሕጉ ቃል ኪዳን “ወደ ክርስቶስ የሚያመጣ ሞግዚታችን” ነበረ በማለት ነግሯቸዋል። (ገላትያ 3:24) የጥንቱ የሕግ ቃል ኪዳን ሕዝቡን ለኢየሱስ መሲሕ ሆኖ መምጣት እንዲያዘጋጅ የታቀደ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ ገና ሰው ሆኖ ከመወለዱ በፊት እንኳን ከይሖዋ የሚመጣው ብርሃን አትኩሮበት ነበር።
9. ከ33 እዘአ ጀምሮ ብርሃንን ማፍቀር ምን ነገርን ጨምሯል?
9 በ29 እዘአ ኢየሱስ ራሱን ለጥምቀት አቀረበና በመንፈስ ቅዱስ ተቀባ። ይህን በማድረጉም ተስፋ የተደረገው መሲሕ ሆነ። በ33 እዘአ ደግሞ በፍጹም ሰውነቱ ሞተ። ከዚያም በኋላ ከሙታን ተነስቶ ወደ ሰማይ አረገና ስለ ኃጢአታችን የተሠዋውን የፍጹም ሕይወቱን ዋጋ አቀረበ። (ዕብራውያን 9:11-14, 24) እነዚህ በተከታታይ የተፈጸሙ ክንውኖች ሁሉ አምላክ ከሰዎች ጋር በነበረው ግኑኝነት ረገድ ለውጥ እንዲያደርግ አስቻሉት። አሁን ኢየሱስ “የሕይወት ዋና ወኪል” “የመዳን ዋና ወኪል”፣ “የእምነታችን ራስና ፈጻሚ” ሆነ። (ሥራ 3:15፤ ዕብራውያን 2:10፤ 12:2፤ ሮሜ 3:23, 24) ከ33 እዘአ ወዲህ ብርሃንን የሚወዱ ሁሉ “መዳንም በሌላ በማንም እንደሌለና እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የሌለ” መሆኑን ተገንዝበው ተቀብለዋል።—ሥራ 4:12
10. የኢየሱስን ቃላት ማዳመጥና መታዘዝ ይህን ያህል አስፈላጊ የሆነው ለምንድነው?
10 በኢየሱስ ማመን እሱ “ቃል” እና “ድንቅ መካር” መሆኑን መቀበልንም ይጨምራል። (ዮሐንስ 1:1፤ ኢሳይያስ 9:6) ኢየሱስ የሚናገረው ነገር ሁልጊዜ መለኮታዊ እውነትን ያንጸባርቃል። (ዮሐንስ 8:28፤ ራእይ 1:1, 2) እሱን ማዳመጥ የሕይወትና የሞትን ያህል ልዩነት የሚያመጣ ጉዳይ ነው። ኢየሱስ ከብበውት የነበሩትን አይሁድ እንዲህ አላቸው፦ “ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው። ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም።” (ዮሐንስ 5:24) በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ የኢየሱስን ቃል በመከተል እርምጃ የወሰዱ ሰዎች በእርግጥ ከሰይጣን ዓለም ጨለማ ድነው ወደ ሕይወት መጥተዋል። በሱ ሰማያዊ መንግሥት ተባባሪ ወራሾች የመሆን ተስፋ አግኝተው ጸድቀዋል። (ኤፌሶን 1:1፤ 2:1, 4-7) ባሁኑ ጊዜ የኢየሱስን ቃላት መታዘዝ ብዙ ሰዎች ከአርማጌዶን ተርፈው በአዲሱ ዓለም ውስጥ ወደ ፍጹም ሰብአዊ ሕይወት የመድረስ ተስፋ አግኝተው የሚጸድቁበትን መንገድ ይከፍትላቸዋል።—ራእይ 21:1-4፤ ከያዕቆብ 2:21, 25 ጋር አወዳድር
“ከሁሉ በላይ ራስ”
11. በ33 እዘአ ለኢየሱስ ምን ከፍተኛ ሥልጣን ተሰጠው?
11 ኢየሱስ ከትንሣኤው በኋላ የብርሃኑን ሌላ ክፍል ለተከታዮቹ ገልጾላቸዋል። “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ” አላቸው። (ማቴዎስ 28:18) ስለዚህ ኢየሱስ በይሖዋ ጽንፈ ዓለማዊ ድርጅት ውስጥ ወደላቀ ሥልጣን ከፍ እየተደረገ ነበር ማለት ነው። ጳውሎስ “ክርስቶስንም ከሙታን ሲያስነሣው ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው በክርስቶስ ባደረገው ሥራ የብርታቱ ጉልበት ይታያል። ሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዛለት፤ ከሁሉ በላይም ራስ እንዲሆን ለቤተ ክርስቲያን ሰጠው። እርሷም አካሉና ሁሉን በሁሉ የሚሞላ የእርሱ ሙላቱ ናት።” (ኤፌሶን 1:20-23፤ ፊልጵስዩስ 2:9-11) ከ33 እዘአ ጀምሮ ብርሃንን መውደድ ይህን የኢየሱስን እጅግ ከፍ ያለ ሥልጣን አምኖ መቀበልንም ጨምሮአል።
12. ቅቡዓን ክርስቲያኖች ገና ከመጀመሪያው ጀምሮ በደስታ የተቀበሉት ምንን ነው? ይህንስ በተግባራዊ መንገድ ያሳዩት እንዴት ነው?
12 በግልጽ እንደሚታየው ሁሉም የሰው ዘር ወደፊት የኢየሱስን ሥልጣን አምኖ መቀበል ይኖርበታል። (ማቴዎስ 24:30፤ ራእይ 1:7) የብርሃን አፍቃሪዎች ግን ገና ከመጀመሪያው ጀምሮ ይህንን የኢየሱስን ሥልጣን አውቀውለታል። የክርስቲያን ጉባኤ ቅቡዓን አባሎች ኢየሱስን “የአካሉ ማለት የጉባኤው ራስ” መሆኑን ይቀበላሉ። (ቆላስይስ 1:18፤ ኤፌሶን 5:23) የዚያ አካል ማለትም የጉባኤው ክፍል በሆኑበት ጊዜ “ከጨለማው ሥልጣን ድነው ወደ አምላክ ፍቅር ልጅ መንግሥት ፈልሰዋል።” (ኤፌሶን 1:13) ከዚያ ወዲያ በሁሉም የሕይወታቸው ዘርፍ የኢየሱስን አመራር ከልብ ይከተላሉ። በዘመናችን “ሌሎች በጎችንም” እንዲሁ እንዲያደርጉ አስተምረዋቸዋል። (ዮሐንስ 10:16) የኢየሱስን ራስነት አምኖ መቀበል ጥሩ ፍርድ ለማግኘት የሚያስችል ቁልፍ መስፈርት ነው።
13. ኢየሱስ የመንግሥቱን ሥልጣን መጠቀም የጀመረው መቼ ነበር? በዚህ በምድር ላይስ ምን ነገር ተከተለ?
13 ኢየሱስ በ33 እዘአ ወደ ሰማይ እንዳረገ ወዲያውኑ ሥልጣኑን ሙሉ በሙሉ አልተጠቀመበትም። የክርስቲያን ጉባኤ ራስ ቢሆንም በጠቅላላው የሰው ዘር ላይ ሙሉ ሥልጣኑን የሚጠቀምበት ጊዜ እስኪደርስ ጠብቋል። (መዝሙር 110:1፤ ሥራ 2:33-35) ያ ተገቢ ጊዜ ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ በዙፋን ላይ በተቀመጠበትና የዚህ ዓለም “የመጨረሻ ቀኖች” በጀመሩበት ዓመት በ1914 መጥቷል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ቅቡአን ቀሪዎችን የመሰብሰብ ሥራ በተለይ ከ1919 ጀምሮ ሲከናወን ቆይቶ ወደማክተሚያው ተጠግቶአል። በተለይ ከ1935 ጀምሮ ኢየሱስ የሰው ዘሮችን “የተዘጋጀላቸውን መንግሥት” በሚወርሱ “በጎችና” “ወደ ዘላለም መቆረጥ” (ጥፋት) በሚሄዱ “ፍየሎች” መካከል ሲለያይ ቆይቷል።—ማቴዎስ 25:31-34, 41, 46
14. እጅግ ብዙ ሰዎች ለብርሃን ፍቅር ያሳዩት እንዴት ነው? ምንስ ውጤት ያመጣላቸዋል?
14 በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች የበጎቹ ቁጥር እየበዛ መሄዱ በጣም ያስደስታል። በሚልዮኖች የሚቆጠሩ “ከሕዝብና ከነገድ ከወገንና ከቋንቋ” የተውጣጡ እጅግ ብዙ ሰዎች በዓለም መድረክ ላይ ብቅ ብለዋል። እነዚህም በግ መሰል ሰዎች እንደ ቅቡዓን ባልንጀሮቻቸው ብርሃንን ያፈቅራሉ። “ልብሳቸውን አጥበው በበጉ ደም አንጽተዋል።” በታላቅ ድምፅም “ማዳን በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው የአምላካችንና የበጉ ነው” በማለት ይጮኻሉ። በዚህም ምክንያት እጅግ ብዙ ሰዎች በቡድን ደረጃ ይፈረድላቸዋል። የእጅግ ብዙ ሰዎች አባሎች ጨለማን የሚያፈቅሩ ሰዎች ከሚጠፉበት ከአርማጌዶን ጥፋት በመትረፍ “ከታላቁ መከራ” ይወጣሉ።—ራእይ 7:9, 10, 14
“የብርሃን ልጆች”
15. ተግባራችን ለንጉሡ ለኢየሱስ ክርስቶስ መገዛታችንን የሚያሳየው በምን መንገድ ነው?
15 ይሁን እንጂ የብርሃን አፍቃሪዎች ቅቡዓንም ሆኑ ሌሎች በጎች አምላክ በዙፋን ላይ ንጉሥና ዳኛ አድርጎ ላስቀመጠው ለኢየሱስ ተግባራዊ በሆነ መንገድ ሊገዙለት የሚችሉት እንዴት ነው? አንዱ መንገድ ኢየሱስ የሚቀበላቸው ዓይነት ሰዎች ለመሆን በመጣር ነው። ኢየሱስ በምድር በነበረበት ጊዜ ሰዎች ለእውነት የነበራቸውን ቅንዓት፣ ሙሉ ልባዊነት፣ ጉጉትና የመሳሰሉትን ባሕርያት በአድናቆት ተመልክቶአል። እሱ ራሱም ለእነዚህ ባሕርያት ጥሩ ምሳሌ ሆኖአል። (ማርቆስ 12:28-34, 41-44፤ ሉቃስ 10:17, 21) እንዲፈረድልን የምንፈልግ ከሆነ እነዚህን ባሕርያት ማዳበር ይኖርብናል።
16. የጨለማውን ሥራ ማስወገድ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
16 ፍጻሜው እየቀረበ ሲሄድ የሰይጣን ዓለም ጨለማ ይበልጥ ጥቅጥቅ እየሆነ ስለሚሄድ እነዚህን ባሕርያት የማዳበራችን አስፈላጊነት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አስፈላጊ ሆኖአል። (ራእይ 16:10) ስለዚህ ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች የጻፋቸው “ሌሊቱ አልፏል፤ ቀኑም ቀርቧል። እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ። በቀን እንደምንሆን በአገባብ እንመላለስ። በዘፈንና በስካር አይሁን። በዝሙትና በመዳራት አይሁን። በክርክርና በቅንዓት አይሁን” የሚሉት ቃላት ዛሬም ለእኛ በጣም ተገቢ ናቸው። (ሮሜ 13:12, 13) የዘላለም ሕይወት ከአምላክ የሚሰጠን ስጦታ ቢሆንም የእምነታችንና ለብርሃን ያለን ፍቅር እውነተኛነት በተግባራችን መገለጽ ይኖርበታል። (ያዕቆብ 2:26) ስለዚህ የምንቀበለው ፍርድ በአመዛኙ የሚመካው መልካም ሥራዎችን በመፈጸማችን ላይና ከክፉ ሥራዎች በመሸሻችን ላይ ይሆናል።
17. “ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን መልበስ” ምን ማለት ነው?
17 ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ 13:12, 13 ላይ የሰፈረውን ምክር ከሰጠ በኋላ “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት፤ ምኞቱንም እንዲፈጽም ለሥጋ አታስቡ” በማለት ይደመድማል። (ሮሜ 13:14) “ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን መልበስ” ማለት ምን ማለት ነው? ክርስቲያኖች የኢየሱስን ምሳሌነትና ጠባዩን በትክክል በመላበስ፣ ክርስቶስን ለመምሰል በመጣጣርና የእርሱን ፈለግ በቅርብ በመከታተል ሊከተሉት ይገባቸዋል ማለት ነው። ጴጥሮስ “የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን (ፈለጉን) እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሏል” ይላል።—1 ጴጥሮስ 2:21
18. እንዲፈረድልን ከፈለግን ምን መሠረታዊ ለውጦች ማድረግ ሊያስፈልግ ይችላል?
18 ይህን ለማድረግ አብዛኛውን ጊዜ አንድ ክርስቲያን በሕይወቱ ላይ መሠረታዊ ለውጦችን እንዲያደርግ ይጠይቅበታል። “ቀድሞ በጨለማ ነበራችሁና” ብሏል ጳውሎስ። “አሁን ግን በጌታ ብርሃን ናችሁ። የብርሃኑ ፍሬ በበጎነትና በጽድቅ በእውነትም ሁሉ ነውና ለጌታ ደስ የሚያሰኘውን እየመረመራችሁ እንደ ብርሃን ልጆች ተመላለሱ።” (ኤፌሶን 5:8, 9) የጨለማውን ሥራ ማድረግን ልማድ ያደረጉ ሰዎች ለውጥ ካላደረጉ በስተቀር ሊፈረድላቸው አይችልም።
“እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ”
19. አንድ ክርስቲያን በምን የተለያዩ መንገዶች ነው ብርሃንን ሊያንጸባርቅ የሚችለው?
19 በመጨረሻም ብርሃንን ማፍቀር ማለት ሌሎች ብርሃኑን ሊያዩት እንዲችሉና ወደሱም እንዲሳቡ ብርሃኑን ማንጸባረቅ ማለት ነው። “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ” ብሏል ኢየሱስ። ጨምሮም “መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ” ብሏል። (ማቴዎስ 5:14, 16) የአንድ ክርስቲያን መልካም ሥራ ማንኛውንም ዓይነት በጐነት፣ ጽድቅንና እውነትን ማሳየትን ይጨምራል። ምክንያቱም እንዲህ ዓይነቱ መልካም ጠባይ ለእውነት ጥሩ ምሥክርነት ይሰጣል። (ገላትያ 6:10፤ 1 ጴጥሮስ 3:1) በተጨማሪም የክርስቲያን መልካም ሥራ ለሌሎች ስለ እውነት መናገርን ይጨምራል። ይህም በአሁኑ ጊዜ “ለአሕዛብ ሁሉ ምሥክር እንዲሆን ይህን የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ” ለመስበክ በሚደረገው ዓለም አቀፍ ዘመቻ መካፈል ማለት ነው። እንዲሁም ፍላጎት ላሳዩት ሰዎች በትዕግሥት ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ከእነሱ ጋር ማጥናትና በምላሹም እነሱም የብርሃን ሥራዎችን እንዲያሳዩ መርዳት ማለትም ነው።—ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20
20. (ሀ) በአሁኑ ጊዜ ብርሃኑ የቱን ያህል ደምቆ በማብራት ላይ ይገኛል? (ለ) ለብርሃኑ ምላሽ የሚሰጡ ሰዎች የሚያገኙአቸው ደማቅ በረከቶች ምንድናቸው?
20 በዘመናችን ታማኝ ክርስቲያኖች የሚያደርጉት የቅንዓት የስብከት እንቅስቃሴ ምስጋና ይግባውና የምሥራቹ ከ200 በላይ በሆኑ አገሮች እየተሰማና ብርሃኑም ከምን ጊዜውም በበለጠ ሁኔታ እያበራ ነው። ኢየሱስ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ። የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም” ብሏል። (ዮሐንስ 8:12) በዚህ ተስፋ አፈጻጸም መካፈል እንዴት የሚያስደስት ነገር ነው! አሁን ሕይወታችን በጣም ስለበለጸገ ከእንግዲህ በሰይጣን ዓለም ጨለማ ውስጥ አንማቅቅም። ይሖዋ የሾመው ዳኛ እንደሚፈርድልን በጉጉት የምንጠባበቅ ስለሆንን በእርግጥም ተስፋችን አስደናቂ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 4:8) ወደ ብርሃን ከመጣን በኋላ ወደ ጨለማው ተመልሰን በመነከራችን ምክንያት የሚፈረድብን ብንሆን እንዴት የሚያሳዝን ነገር ይሆናል! በሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት ላይ እንዴት በእምነት ጸንተን እንደምንኖር እንወያያለን።
ልታብራራ ትችላለህን?
◻ ለአምላክ ፍርድ መሠረቱ ምንድነው?
◻ የአምላክን ዓላማዎች በተመለከተ ኢየሱስ ምን ዋና የሥራ ድርሻ አለው?
◻ ኢየሱስ ይሖዋ ንጉሥ አድርጎ በዙፋን ያስቀመጠው እንደመሆኑ ለእርሱ እንደምንገዛ የምናሳየው እንዴት ነው?
◻ “የብርሃን ልጆች” መሆናችንን የምናሳየው እንዴት ነው?
◻ ብርሃኑ በዚህ ዓለም ጨለማ ውስጥ ከምንጊዜውም በበለጠ ሁኔታ እያበራ ያለው በምን መንገድ ነው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በመጨረሻው ሁሉም ሰው የኢየሱስን ሥልጣን መቀበል ይኖርበታል
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለሌሎች ስናንፀባርቀው ብርሃኑን እንደምናፈቅረው እናሳያለን