ታላቁን መከራ በሕይወት ማለፍ
“እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው፣ልብሳቸውንም አጥበው በበጉ ደም አነጹ።”—ራእይ 7:14
1. በምድራዊው ትንሣኤ የሚነሡትን ሰዎች የሚቀበሏቸው እነማን ይሆናሉ?
በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ‘በጻድቃንና በዓመፀኞች ትንሣኤ’ ሲነሡ እንደገና ሕያው የሚሆኑት ባዶ በሆነች መሬት ላይ አይደለም። (ሥራ 24:15) ከሞት እንደ ተነሡ ውብ በሆነ መንገድ የተሻሻሉ አካባቢዎችን ይመለከታሉ፤ እንዲሁም መኖሪያ፣ ልብስና የተትረፈረፈ ምግብ ተዘጋጅቶ ይጠብቃቸዋል። እነዚህን ሁሉ ዝግጅቶች የሚያዘጋጀው ማን ነው? ምድራዊው ትንሣኤ ከመጀመሩ በፊት በአዲሱ ዓለም ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች እንዳሉ ግልጽ ነው። እነዚህ ሰዎች እነማን ናቸው? መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ ሰዎች ከመጪው ታላቅ መከራ በሕይወት የሚተርፉ እንደሆኑ ያመለክታል። አንዳንድ ታማኝ ሰዎች ታላቁን መከራ በሕይወት አልፈው ፈጽሞ ሞትን ሳይቀምሱ ለዘላለም እንደሚኖሩ የሚናገረው ትምህርት እጅግ ከሚማርኩት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች አንዱ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። ይህ ተስፋ እውነተኛ እንደሆነ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በሚገባ ተገልጿል።
እንደ ኖኅ ዘመን
2, 3. (ሀ) በኖኅ ዘመንና በእኛ ዘመን መካከል ምን ተመሳሳይነቶች አሉ? (ለ) ኖኅና ቤተሰቡ ከጥፋት ውኃ በሕይወት መትረፋቸው ምን ያመለክታል?
2 ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ 24:37–39 ላይ የኖኅን ዘመን አሁን ከምንኖርበት የመጨረሻ ቀን ጋር አነጻጽሮታል። እንዲህ አለ፦ “የኖኅ ዘመን እንደ ነበረ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና። በዚያች ወራት ከጥፋት ውኃ በፊት ኖኅ ወደ መርከብ እስከገባበት ቀን ድረስ ሲበሉና ሲጠጡ፣ ሲያገቡና ሲጋቡም እንደ ነበሩ፣ የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ እንዳላወቁ፣ የሰው ልጅ መምጣት ደግሞ እንዲሁ ይሆናል።”
3 ምድር አቀፉ የውኃ መጥለቅለቅ የአምላክን የማስጠንቀቂያ መልእክት ለማዳመጥ ፈቃደኛ ያልሆኑትን በሙሉ ጠራርጎ አጥፍቷል። ኖኅንና ቤተሰቦቹን ግን አላጠፋቸውም። ኢየሱስ እንደተናገረው እነርሱ ‘ወደ መርከብ ገብተዋል።’ ለአምላክ ያደሩ ሰዎች ስለነበሩ ይሖዋ ከጥፋት የሚድኑበትን መንገድ አዘጋጅቶላቸዋል። ሁለተኛ ጴጥሮስ 2:5, 9 “[አምላክ] ከሌሎች ሰባት ጋር ጽድቅን የሚሰብከውን ኖኅን አድኖ በኃጢአተኞች ዓለም ላይ የጥፋትን ውኃ ካወረደ፣ ጌታ እግዚአብሔርን የሚያመልኩትን ከፈተና እንዴት እንዲያድን . . . ያውቃል” የሚለው ኖኅና ቤተሰቡ ከጥፋት የተረፉበትን ሁኔታ ሲያመለክት ነው። ሰዎች በጥቅሉ የአምላክን የማስጠንቀቂያ መልእክት እንደማይሰሙ ለማመልከት ኢየሱስ የኖኅን ዘመን ከመጨረሻው ቀን ጋር አነጻጽሮታል። ይሁን እንጂ እንዲህ በማድረግ ኢየሱስ ኖኅና ቤተሰቡ ይሖዋ አምላክን ታዝዘው ወደ መርከብ እንደገቡና ከታላቁ የውኃ መጥለቅለቅ እንደተረፉ ማረጋገጫ ሰጥቷል። ኖኅና ቤተሰቡ ከጥፋት መዳናቸው የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች በዚህ ዓለም መጨረሻ ከሚመጣው ጥፋት እንደሚድኑ ያመለክታል።
የመጀመሪያው መቶ ዘመን ምሳሌ
4. ኢየሱስ በተናገራቸው ቃላት ፍጻሜ መሠረት ኢየሩሳሌምን በ70 እዘአ እንድትጠፋ ያደረጓት ክስተቶች ምን ነበሩ?
4 በተጨማሪም ኢየሱስ በዚህ ዓለም መጨረሻ ስለሚከሰቱት ሁኔታዎች ተናግሯል። በማቴዎስ 24:21, 22 ላይ እንዲህ እናነባለን፦ “በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናልና። እነዚያ ቀኖችስ ባያጥሩ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር። ነገር ግን እነዚያ ቀኖች ስለ ተመረጡት ሰዎች ያጥራሉ።” እነዚህ ቃላት የመጀመሪያ ፍጻሜያቸውን ያገኙት በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደ ዘመናችን አቆጣጠር ነው። በ66 እዘአ የኢየሩሳሌም ከተማ በሴስትየስ ጋለስ ይመራ በነበረው የሮማ ሠራዊት ተከበበች። የሮማ ሠራዊት የቤተ መቅደሱን ግድግዳ እስከ ማፍረስ ደርሶ ነበር፤ ብዙ አይሁዳውያንም እጃቸውን ለመስጠት ተዘጋጅተው ነበር። ይሁን እንጂ ሴስትየስ ጋለስ ምንም ዓይነት ግልጽ ምክንያት ሳይኖረው ድንገት ሳይታሰብ ሠራዊቱ ወደኋላው እንዲያፈገፍግ አደረገ። ክርስቲያኖች የሮማ ሠራዊት ወደኋላ መመለሱን እንደተመለከቱ ኢየሱስ ከብዙ ዓመታት በፊት የተናገራቸውን ቃላት በመታዘዝ እርምጃ ወሰዱ፦ “ኢየሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደ ቀረበ እወቁ። የዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራራዎች ይሽሹ፣ በመካከልዋም ያሉ ከእርስዋ ፈቀቅ ይበሉ፣ በገጠር ያሉም ወደ እርስዋ አይግቡ።” (ሉቃስ 21:20, 21) የተመረጡት ክርስቲያን አይሁዶች ለጥፋት የተወሰነችውን ከተማ ጥለው በመውጣታቸው ብዙም ሳይቆይ በከተማዋ ላይ ከደረሰው በጣም አሠቃቂ የሆነ ጥፋት ለመዳን ችለዋል። በ70 እዘአ የሮማ ጭፍሮች በጄኔራል ቲቶ አዝማችነት ተመልሰው መጡ። በኢየሩሳሌም ዙሪያ ከሠፈሩ በኋላ ከተማዋን ከብበው አጠፏት።
5. በ70 እዘአ በኢየሩሳሌም ላይ የደረሰው መከራ እንዲያጥር የተደረገው ከምን አንጻር ነው?
5 ጆሴፈስ የተባለው አይሁዳዊ ታሪክ ጸሐፊ 1,100,000 አይሁዳውያን እንደተገደሉና 97,000 የሚያክሉ ከእልቂቱ ተርፈው ወደ ግዞት እንደተወሰዱ ተርኳል። ኢየሱስ “የተመረጡ” በማለት የተነበየላቸው ሰዎች እነዚህ ከጥፋቱ የተረፉ ክርስቲያን ያልሆኑ አይሁዶች እንዳልነበሩ ግልጽ ነው። ኢየሱስ ስለ ዓመፀኛው የአይሁድ ብሔር ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “እነሆ፣ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል። እላችኋለሁና፣ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እስክትሉ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩኝም።” (ማቴዎስ 23:38, 39) መውጫ ቀዳዳ አጥተው በኢየሩሳሌም ከተማ የቆዩት አይሁዶች መጨረሻ ላይ የኢየሱስን መሲሕነት ተቀብለው ክርስቲያኖች እንደሆኑና የይሖዋን ሞገስ እንዳገኙ የሚያረጋግጥ ማስረጃ አይገኝም። ቢሆንም በ70 እዘአ በኢየሩሳሌም ላይ የወረደው መከራ እንዲያጥር ተደርጓል። የሮማ ጭፍራ ያደረገው የመጨረሻው ከበባ ለረዥም ጊዜ የቆየ አልነበረም። ይህም ጥቂት አይሁዳውያን፣ በሮማ ግዛት የተለያዩ ክፍሎች ተበታትነው በባርነት ለመኖር ቢሆንም፣ በሕይወት እንዲተርፉ አስችሏል።
ከጥፋት የተረፉ እጅግ ብዙ ሰዎች
6, 7. (ሀ) እስከ ዛሬ ድረስ ታይቶ በማያውቀው መከራ ወቅት የምትጠፋው ታላቅ ሃይማኖታዊ ከተማ ማን ናት? (ለ) ዮሐንስ በዚህ ዓለም ላይ የሚወርደውን መጪውን ታላቅ መከራ አስመልክቶ ምን ብሎ ተንብዮአል?
6 በ70 እዘአ በኢየሩሳሌም ላይ የደረሰው ጥፋት በእርግጥም በዚያች ሃይማኖታዊ ከተማ ላይ “ታላቅ መከራ” ያመጣ ቢሆንም እነዚህ የኢየሱስ ቃላት ዋነኛ ፍጻሜያቸውን የሚያገኙት ገና ወደፊት ነው። ከዚህችኛዋ የምትበልጠው ሃይማኖታዊ ከተማ ማለትም የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት የሆነችው ታላቂቱ ባቢሎን በተቀረው የሰይጣን የነገሮች ሥርዓት ላይ የሚወርደውን አቻ የማይገኝለትን መከራ አስከትሎ የሚመጣው ገዳይ የሆነ ታላቅ መከራ ይደርስባታል። (ማቴዎስ 24:29, 30፤ ራእይ 18:21) ሐዋርያው ዮሐንስ ኢየሩሳሌም ከጠፋች ከ26 ዓመታት በኋላ በራእይ 7:9–14 ላይ ስለዚህ ዓለም አቀፍ ታላቅ መከራ ጽፏል። እጅግ ብዙ ሰዎች ከጥፋቱ እንደሚተርፉ አመልክቷል።
7 እነዚህ “እጅግ ብዙ ሰዎች” የተባሉት ከጥፋቱ የሚተርፉ ሰዎች በሚወስዱት አንድ ዓይነት ወሳኝ እርምጃ ተለይተው ይታወቃሉ። ራእይ 7:14 እንደሚለው በሰማይ ካሉት 24 ሽማግሌዎች አንዱ ለዮሐንስ እንዲህ ብሎታል፦ “እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው፣ ልብሳቸውንም አጥበው በበጉ ደም አነጹ።” አዎን፣ እነዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች አዳኛቸው ይሖዋ መሆኑን በግልጽ ያውጃሉ። በፈሰሰው የኢየሱስ ደም ያምናሉ፤ እንዲሁም በፈጣሪያቸውና በተቀባው ንጉሥ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት የጽድቅ አቋም አላቸው።
8. በ“እጅግ ብዙ ሰዎች” እና በቀሪዎቹ የኢየሱስ ቅቡዓን ወንድሞች መካከል ምን ጥሩ ዝምድና አለ?
8 ዛሬ በሰማያዊው ንጉሥ በኢየሱስ ክርስቶስ አመራር ሥር የሚገኙ ወደ አምስት ሚልዮን የሚጠጉ የእጅግ ብዙ ሰዎች አባሎች አሉ። ለክርስቶስ ይገዛሉ፣ በምድር ላይ ከቀሩት ቅቡዓን ወንድሞቹም ጋር ተቀራርበው ይሠራሉ። እጅግ ብዙ ሰዎች ለእነዚህ ቅቡዓን ስላደረጉላቸው ነገር ሲናገር ኢየሱስ “እውነት እላችኋለሁ፣ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት” ብሏል። (ማቴዎስ 25:40) እነዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች ከራስ ወዳድነት በራቀ መንፈስ የክርስቶስን ቅቡዓን ወንድሞች ስለሚረዱ ለኢየሱስ መልካም እንዳደረጉ ተፈርዶላቸዋል። ይህም ከኢየሱስ ክርስቶስና ከይሖዋ አምላክ ጋር አስተማማኝ ዝምድና እንዲኖራቸው ይረዳቸዋል። የአምላክ ምሥክሮች በመሆን ከቅቡዓን ቀሪዎች ጋር የመተባበርና ስሙን የመሸከም መብት አግኝተዋል።—ኢሳይያስ 43:10, 11፤ ኢዩኤል 2:31, 32
ንቁ ሆኖ መጠበቅ
9, 10. (ሀ) በሰው ልጅ ፊት የጽድቅ አቋማችንን ጠብቀን ለመቆም ምን ማድረግ አለብን? (ለ) ‘ነቅተን ለመኖር’ ምን እርምጃ መውሰድ አለብን?
9 እጅግ ብዙ ሰዎች ዘወትር በሰው ልጅ ፊት ያላቸውን አቋም ሳያላሉ መጠበቅ አለባቸው። ይህም እስከ መጨረሻው ንቁ ሆኖ መጠባበቅን ይጠይቃል። ኢየሱስ እንዲህ ብሎ በተናገረ ጊዜ ይህን በግልጽ አመልክቷል፦ “ነገር ግን ልባችሁ በመጠጥ ብዛትና በስካር ስለ ትዳርም በማሰብ እንዳይከብድ፣ ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ በምድር ሁሉ ላይ በሚቀመጡ ሁሉ እንደ ወጥመድ ይደርስባቸዋልና። እንግዲህ ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ፣ በሰው ልጅም ፊት ለመቆም እንድትችሉ ስትጸልዩ ሁልጊዜ ትጉ።”—ሉቃስ 21:34–36
10 በሰው ልጅ ፊት ለመቆም እንድንችል የእርሱን ሞገስ ማግኘት ያስፈልገናል። የዚህ ዓለም አስተሳሰብ እንዲመራን ከፈቀድንለት ግን ይህን ማግኘት አንችልም። ዓለማዊ አስተሳሰብ በጣም አታላይ ስለሆነ አንድ ሰው የመንግሥቱን ጉዳዮች ለማስቀደም እስከማይችል ድረስ በሥጋዊ ተድላዎች እንዲጠመድ ወይም ስለ ኑሮ ችግሮች ብቻ እንዲያስብ ሊያደርገው ይችላል። (ማቴዎስ 6:33) እንዲህ ዓይነቱ ጎዳና አንድን ሰው በመንፈሳዊ እንዲዳከምና ለአምላክና ለሰዎች ያለውን ኃላፊነት እንዲዘነጋ ሊያደርገው ይችላል። ሊቀዘቅዝ ወይም ከባድ ኃጢአት በመሥራት ምናልባትም ንሥሐ ያለመግባት መንፈስ በማሳየት በጉባኤ ውስጥ ያለውን ቦታ ሊያጣ ይችላል። የእጅግ ብዙ ሰዎች አባል የሆነ እያንዳንዱ ግለሰብ ስለ ራሱ መጠንቀቅ አለበት። ከዚህ ለአምላክ ደንታ ከሌለው ዓለምና ከተግባሮቹ ተለይቶ መኖር አለበት።—ዮሐንስ 17:16
11. የትኞቹን ቅዱስ ጽሑፋዊ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ማዋላችን ከአርማጌዶን በሕይወት እንድንተርፍ ይረዳናል?
11 ይህንንም ለማድረግ እንድንችል ይሖዋ በቃሉ፣ በቅዱስ መንፈሱና በሚታየው ድርጅቱ አማካኝነት የሚያስፈልገንን ሁሉ ሰጥቶናል። በእነዚህ ነገሮች ሙሉ በሙሉ መጠቀም አለብን። በተጨማሪም የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ከፈለግን ጠንቃቆች መሆንና አምላክን መታዘዝ ይኖርብናል። ከዚህም በላይ መጥፎ ለሆነ ነገር ሁሉ ጠንካራ የጥላቻ ስሜት ማዳበር አለብን። መዝሙራዊው እንዲህ ብሏል፦ “በከንቱ ሸንጎ አልተቀመጥሁም፣ ከዓመፀኞችም ጋር አልገባሁም። የክፉዎችን ማኅበር ጠላሁ፣ ከዝንጉዎችም ጋር አልቀመጥም። ከኃጢአተኞች ጋር ነፍሴን፣ ከደም ሰዎችም ጋር ሕይወቴን አታጥፋ።” (መዝሙር 26:4, 5, 9) በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ ወጣቶችም ሆኑ አረጋውያን ራሳቸውን ለይሖዋ ካልወሰኑ ሰዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ገደብ ሊያበጁለት ይገባል። የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ነውር የሌለብንና የዓለም ዕድፍ ያልነካን ሆነን ለመገኘት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። (መዝሙር 26:1–5፤ ያዕቆብ 1:27፤ 4:4) እንዲህ ካደረግን ይሖዋ በአርማጌዶን ለአምላክ ደንታ ከሌለው ዓለም ጋር ጠራርጎ እንደማያጠፋን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።
አንዳንዶች ‘ለዘላለም አይሞቱም’
12, 13. (ሀ) ኢየሱስ አልዓዛርን ከማስነሳቱ በፊት ማርታ ሙሉ በሙሉ ያልተረዳቻቸውን የትኞቹን ቃላት ተናግሯል? (ለ) ኢየሱስ አንዳንዶች ‘ለዘላለም እንደማይሞቱ’ የተናገራቸው ቃላት ምን ማለት አልነበሩም?
12 ከዚህ ሥርዓት ፍጻሜ በሕይወት አልፎ የሞት ሥጋት በማይኖርበት ዓለም ለመኖር ስለመቻላችን ማሰብ በጣም ያስደስታል። ኢየሱስ ይህን ተስፋ አረጋግጦልናል። ኢየሱስ ሞቶ የነበረውን ጓደኛውን አልዓዛርን ከሞት ከማስነሣቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ለአልዓዛር እህት ለማርታ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም፤ ይህን ታምኚያለሽን? አላት።” ማርታ በትንሣኤ የምታምን ብትሆንም ኢየሱስ የተናገረውን ሙሉ በሙሉ አልተረዳችም ነበር።—ዮሐንስ 11:25, 26
13 ኢየሱስ ታማኝ ሐዋርያቱ ሳይሞቱ ለሁል ጊዜ በሥጋ እንደሚኖሩ መናገሩ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ደቀ መዛሙርቱ እንደሚሞቱ በኋላ አመልክቷል። (ዮሐንስ 21:16–23) እንዲያውም በ33 እዘአ በጰንጠቆስጤ ዕለት በመንፈስ ቅዱስ መቀባታቸው ነገሥታትና ካህናት በመሆን የሚያገኙትን ሰማያዊ ውርሻ ለመቀበል መሞት እንደነበረባቸው የሚያመለክት ነው። (ራእይ 20:4, 6) በመሆኑም ከጊዜ በኋላ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች በሙሉ ሞተዋል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ይህን ቃል የተናገረበት ዓላማ አለው። ሞትን ሳያዩ ስለ መኖር የተናገረው ቃል ይፈጸማል።
14, 15. (ሀ) ኢየሱስ አንዳንዶች ‘ለዘላለም እንደማይሞቱ’ የተናገራቸው ቃላት የሚፈጸሙት እንዴት ነው? (ለ) ይህ ዓለም ያለበት ሁኔታ ምን ይመስላል? ይሁን እንጂ ጻድቃን ምን ተስፋ አላቸው?
14 አንደኛ ነገር ታማኝ የሆኑ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ዘላለማዊው ሞት ፈጽሞ አይደርስባቸውም። (ራእይ 20:6) በተጨማሪም የኢየሱስ ቃላት አምላክ ልክ በኖኅ ዘመን እንዳደረገው በሰው ልጆች ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ ክፋትን ከምድር ጠራርጎ የሚያጠፋበትን ጊዜ ይጠቁማሉ። በዚያ ጊዜ የአምላክን ፈቃድ ሲያደርጉ የሚገኙ ታማኝ ግለሰቦች በአምላክ የፍርድ እርምጃዎች መሞት አይኖርባቸውም። ከዚህ ይልቅ ልክ እንደ ኖኅና ቤተሰቡ በዓለም ላይ ከሚደርሰው ጥፋት በሕይወት የመትረፍ አጋጣሚ ያገኛሉ። እንዲህ ዓይነቱ ተስፋ በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ላይ የተመሠረተና በምሳሌዎች የተደገፈ ሙሉ ተአማኒነት ያለው ነው። (ከዕብራውያን 6:19ና ከ2 ጴጥሮስ 2:4–9 ጋር አወዳድር።) በቅርቡ ይህ ዓመፀኛ ሰብዓዊ ኅብረተሰብ የሚገኝበት የአሁኑ ዓለም እንደሚወድም የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ ያሳያል። ይህ ዓለም ከክፋት የማይመለስ በመሆኑ የአሁኑ ሁኔታ ሊሻሻል የሚችልበት መንገድ የለም። አምላክ በኖኅ ዘመን ስለነበረው ዓለም የተናገረው ቃል በዛሬው ጊዜ ላለው ዓለምም እውነት ሆኗል። የአብዛኛዎቹ ሰዎች ልብ በክፋት የተሞላ ነው፤ ሐሳባቸውም ሁልጊዜ ክፉ ነው።—ዘፍጥረት 6:5
15 ሰዎች አለምንም መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት ምድርን እንዲገዙ ይሖዋ ፈቅዷል። አሁን ግን የተሰጣቸው ጊዜ ተገባዷል ማለት ይቻላል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው በቅርቡ ይሖዋ በምድር ላይ የሚኖሩትን ክፉዎች በሙሉ ያጠፋል። (መዝሙር 145:20፤ ምሳሌ 2:21, 22) ይሁን እንጂ ጻድቃንን ከክፉዎች ጋር አያጠፋም። አምላክ እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ አድርጎ አያውቅም! (ከዘፍጥረት 18:22, 23, 26 ጋር አወዳድር።) በአምላካዊ ፍርሃት እርሱን በታማኝነት ለማገልገል የሚጥሩትን ሰዎች የሚያጠፋበት ምን ምክንያት አለ? ኖኅና ቤተሰቡ በዘመኑ የነበረው ክፉ ዓለም ሲወድም እንዳልጠፉ ሁሉ ታላቁ መከራ በሚጀምርበት ጊዜም በሕይወት የሚኖሩት የይሖዋ ታማኝ አምላኪዎች በፊቱ ሞገስ ማግኘታቸውና ከጥፋት ተጠብቀው ማለፋቸው ምክንያታዊ ነው። (ዘፍጥረት 7:23) መለኮታዊ ጥበቃ አግኝተው ከዚህ ዓለም ፍጻሜ በሕይወት ያልፋሉ።
16. በአዲሱ ዓለም ውስጥ ምን ዕጹብ ድንቅ የሆኑ ነገሮች ይከሰታሉ? ይህስ በሕይወት ለሚተርፉት ምን ትርጉም አለው?
16 ከዚያስ በኋላ ምን ይሆናል? በአዲሱ ዓለም ውስጥ የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት የሚያስገኛቸው ጥቅሞች ሙሉ በሙሉ ሥራ ላይ ሲውሉ የሰው ዘር ፈዋሽ በረከቶች ይዘንቡለታል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ምሳሌያዊ የሕይወት ውኃ ወንዝ ይናገራል፦ “ከበጉ ዙፋን የሚወጣውን እንደ ብርሌ የሚያንጸበርቀውን የሕይወትን ውኃ ወንዝ አሳየኝ። በወንዙም ወዲያና ወዲህ በየወሩ እያፈራ አሥራ ሁለት ፍሬ የሚሰጥ የሕይወት ዛፍ ነበረ፣ የዛፉም ቅጠሎች ለሕዝብ መፈወሻ ነበሩ።” (ራእይ 22:1, 2) ያ “መፈወሻ” አዳማዊውን ሞት ጭምር ድል የሚያደርግ መሆኑ እጅግ የሚያስደስት ነው! “ሞትን ለዘላለም ይውጣል፣ ጌታ እግዚአብሔርም ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል።” (ኢሳይያስ 25:8) በዚህ መንገድ ታላቁን መከራ በሕይወት አልፈው ወደ አዲሱ ዓለም የሚገቡ ፈጽሞ መሞት አያስፈልጋቸውም!
አስተማማኝ ተስፋ
17. አንዳንዶች አርማጌዶንን በሕይወት የማለፋቸውና ‘ለዘላለም ሞትን ሳያዩ የመኖራቸው’ ተስፋ ምን ያህል አስተማማኝ ነው?
17 በዚህ እጅግ አስገራሚ የሆነ ተስፋ ሙሉ ትምክህት ሊኖረን ይችላልን? አዎን፣ ፍጹም ትምክህት ሊኖረን ይችላል! ኢየሱስ ሰዎች ሞትን ሳያዩ የሚኖሩበት ጊዜ እንደሚመጣ ለማርታ ጠቁሞላታል። (ዮሐንስ 11:26) ከዚህም በላይ ኢየሱስ ለዮሐንስ ባሳየው ራእይ ምዕራፍ 7 ላይ እጅግ ብዙ ሰዎች ከታላቁ መከራ በሕይወት አልፈው እንደሚወጡ ተገልጿል። ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረውንና ስለ ኖኅ የጥፋት ውኃ የሚናገረውን ታሪክ ለማመን እንችላለንን? አለ አንዳች ጥርጥር ለማመን እንችላለን! ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ አገልጋዮቹን በፍርድ ጊዜያት እንዴት ከጥፋት እንዳዳናቸውና ታላላቅ ብሔራት እንዴት እንደወደቁ የሚገልጹ ሌሎች ታሪኮችንም ይዟል። በዚህ የመጨረሻ ቀን አምላክ ከዚህ ያነሰ ያደርጋል ተብሎ ሊጠበቅ ይገባልን? ፈጣሪ የሚሳነው ነገር ይኖራልን?—ከማቴዎስ 19:26 ጋር አወዳድር።
18. ይሖዋ በሚያመጣው ጽድቅ የሚሰፍንበት አዲስ ዓለም ውስጥ ሕይወት እንደምናገኝ እርግጠኞች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
18 በአሁኑ ጊዜ ይሖዋን በታማኝነት በማገልገል እርሱ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ዋስትና ልናገኝ እንችላለን። በሚልዮን የሚቆጠሩ ብዙ ሰዎች ደግሞ በዚህች አዲስ ዓለም የመኖር አጋጣሚ የሚያገኙት በትንሣኤ አማካኝነት ነው። ይሁን እንጂ በዚህ በእኛ ዘመን በሚልዮን የሚቆጠሩ የይሖዋ ሕዝቦች፣ አዎን፣ ማንም ሰው ሊቆጥራቸው ወይም ቁጥራቸውን ሊወስን የማይችላቸው እጅግ ብዙ ሰዎች በዓይነቱ ልዩ ከሆነ ታላቅ መከራ የማለፍ መብት ያገኛሉ። ዳግመኛም ሞትን አያዩም።
እባክህ አብራራ
◻ በኖኅ ዘመን የተከናወነው ሁኔታ ከአርማጌዶን በሕይወት መትረፍ እንደሚቻል የሚያሳይ ጥላ የሆነው እንዴት ነው?
◻ ኢየሱስ የይሖዋን ፍርዶች ለማስፈጸም ሲመጣ ጸንተን ለመቆም ምን ማድረግ አለብን?
◻ አርማጌዶንን በሕይወት ያለፉ ሰዎች ‘ለዘላለም መሞት’ አያስፈልጋቸውም ማለት የምንችለው ለምንድን ነው?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያኖች በኢየሩሳሌም ላይ ከደረሰው መከራ አምልጠዋል