የአንባቢያን ጥያቄዎች
ኢየሱስ በቃና በተደረገው የሠርግ ግብዣ ላይ እናቱን ያነጋገረበት መንገድ ለእርሷ አክብሮት እንደሌለው ወይም ደግነት እንደጎደለው ያሳያል?—ዮሐንስ 2:4
ኢየሱስ ከተጠመቀ ብዙም ሳይቆይ፣ እርሱና ደቀ መዛሙርቱ በቃና በተደረገ የሠርግ ግብዣ ላይ ተገኝተው ነበር። እናቱም እዚያው ነበረች። በድግሱ ላይ ቀርቦ የነበረው የወይን ጠጅ እያለቀ መሄዱን የተመለከተችው ማርያም ኢየሱስን “የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም” አለችው። ኢየሱስም “አንቺ ሴት፣ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም” በማለት መለሰላት።—ዮሐንስ 2:1-4 የ1954 ትርጉም
በዛሬው ጊዜ፣ አንድ ሰው እናቱን “አንቺ ሴት” ብሎ ቢጠራት እንዲሁም “ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?” ብሎ ቢመልስላት አክብሮት ማጣት እንዲያውም ስድብ እንደሆነ ተደርጎ ሊታይ ይችላል። ነገር ግን ኢየሱስን እንዲህ አድርጓል ብሎ መክሰስ በወቅቱ የነበረውን ባሕልና ቋንቋ ከግምት ውስጥ አለማስገባት ይሆናል። ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ይህን አባባል እንዴት ይጠቀሙበት እንደነበረ መረዳት በጣም ጠቃሚ ነው።
በቫይን የተዘጋጀው ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኦልድ ኤንድ ኒው ቴስታመንት ወርድስ “አንቺ ሴት” የሚለውን ሐረግ በተመለከተ “ሴቶችን ለማነጋገር የሚሠራበት ይህ ቃል፣ ተግሣጽን ወይም ሻካራ ንግግርን ከማመልከት ይልቅ ፍቅርን አሊያም አክብሮትን የሚገልጽ ነው” ብሏል። ሌሎች ምንጮችም ቢሆኑ ከዚህ ጋር የሚስማማ ሐሳብ አላቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ዚ አንከር ባይብል “ይህ አባባል ዘለፋ አሊያም አክብሮት የጎደለው አነጋገር አይደለም፤ ንግግሩ ፍቅር እንደሌለውም አያመለክትም። . . . ኢየሱስ ሁልጊዜም ሴቶችን ለመጥራት የሚጠቀምበት ጨዋነት የተንጸባረቀበት መንገድ ነው” ብሏል። ዘ ኒው ኢንተርናሽናል ዲክሽነሪ ኦቭ ኒው ቴስታመንት ቲኦሎጂ የተባለው መጽሐፍ ደግሞ፣ አባባሉ “ሰዎችን ለማነጋገር ከማገልገል ውጪ አክብሮት የጎደለው አጠራርን አያመለክትም” ብሏል። እንዲሁም በገርሃት ኪትል የተዘጋጀው ቲኦሎጂካል ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት እንደዚህ ዓይነት አነጋገር “በፍጹም አክብሮት የጎደለው ወይም ክብርን የሚነካ አይደለም” ብሏል። እንግዲያው ኢየሱስ እናቱን “አንቺ ሴት” ብሎ በመጥራቱ እንዳንጓጠጣት ወይም ደግነት በጎደለው መንገድ እንዳናገራት አድርገን መደምደም አይገባንም።—ማቴዎስ 15:28፤ ሉቃስ 13:12፤ ዮሐንስ 4:21፤ 19:26፤ 20:13, 15
“ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?” ስለሚለው አባባልስ ምን ለማለት ይቻላል? ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተደጋጋሚ ጊዜያት ተጠቅሶ የሚገኝ የአይሁዳውያን የተለመደ ዘይቤያዊ አነጋገር ነው። ለምሳሌ፣ በ2 ሳሙኤል 16:10 (የ1954 ትርጉም) ላይ አቢሳ ሳሚን እንዳይገድለው ዳዊት ሲከላከል:- “እናንተ የጽሩያ ልጆች፣ እኔ ከእናንተ ጋር ምን አለኝ? እግዚአብሔር:- ዳዊትን ስደበው ብሎ አዝዞታልና ይርገመኝ” ብሎ ተናግሯል። በተመሳሳይም በ1 ነገሥት 17:18 (የ1954 ትርጉም) ላይ በሰራፕታ የነበረችው መበለት ልጇ በሞተበት ወቅት ኤልያስን:- “የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፣ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? ኃጢአቴንስ ታሳስብ ዘንድ፣ ልጄንስ ትገድል ዘንድ ወደ እኔ መጥተሃልን?” ብላዋለች።
ከእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች መመልከት እንደሚቻለው “ከአንተ [ከአንቺ] ጋር ምን አለኝ?” የሚለውን አባባል በተደጋጋሚ ሰዎች ይጠቀሙበት እንደነበረ ማየት ይቻላል። የአነጋገር ዘይቤው ከንቀት ወይም ከትዕቢት ጋር የተያያዘ ሳይሆን በአንድ ሐሳብ ወይም ድርጊት አለመስማማትን አሊያም የተለየ አመለካከት መያዝን የሚያመለክት ነው። ታዲያ ኢየሱስ ለማርያም ስለተናገራቸው ቃላት ምን ማለት ይቻላል?
ማርያም፣ ለኢየሱስ “የወይን ጠጅ እኮ አለቀባቸው” ብላ ስትነግረው ወይኑ እንዳለቀባቸው ማሳወቋ ብቻ ሳይሆን አንድ ነገር አድርግላቸው ማለቷ ነበር። ኢየሱስም ቢሆን በወቅቱ የተለመደውን ዘይቤያዊ አነጋገር ተጠቅሞ ማርያም በዘዴ ያቀረበችውን ጥያቄ እንደማይቀበለው ገልጿል። ከዚያም “ጊዜዬ ገና አልደረሰም” በማለት ከላይ ያለውን ሐሳብ የተናገረበትን ምክንያት ግልጽ አድርጓል።
ኢየሱስ በ29 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከተጠመቀና መሲሕ ሆኖ ከተቀባ ጀምሮ በታማኝነት መመላለስ እንደሚጠበቅበት እንዲሁም ይህ ዓይነቱ ሕይወት ከጊዜ በኋላ ወደ ሞት እንደሚመራው ከዚያም ትንሣኤ እንደሚያገኝና ክብራማ ሕይወት እንደሚቀበል በሚገባ ተገንዝቦ ነበር። ኢየሱስ ተስፋ የተደረገበት መሲሕ እንደመሆኑ መጠን እርሱን በተመለከተ የይሖዋ ፈቃድ ይህ ነበር። እርሱም “የሰው ልጅ እንዲያገለግሉት ሳይሆን፣ ለማገልገልና ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ለመስጠት መጥቶአልና” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 20:28) ኢየሱስ የመሞቻው ጊዜ እየቀረበ ሲመጣ “ሰዓቱ ደርሶአል” በማለት ይህንን ጉዳይ ግልጽ አድርጎታል። (ዮሐንስ 12:1, 23፤ 13:1) ስለዚህም ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ባቀረበው ጸሎት ላይ “አባት ሆይ፤ ጊዜው ደርሶአል፤ ልጅህ ያከብርህ ዘንድ ልጅህን አክብረው” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:1) በተጨማሪ ሕዝቡ እርሱን ለመያዝ ወደ ጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ ሲመጡ ኢየሱስ የተኙትን ሐዋርያት ከእንቅልፍ ቀስቅሶ “ሰዓቲቱ ደርሳለች፤ እነሆ፤ የሰው ልጅ ለኀጢአተኞች እጅ አልፎ ይሰጣል” በማለት ነገራቸው።—ማርቆስ 14:41
ኢየሱስ በቃና በተደረገው ሠርግ ላይ በተገኘበት ወቅት ግን መሲሕ በመሆን ገና አገልግሎቱን መጀመሩ ሲሆን ‘ጊዜውም ገና አልደረሰም’ ነበር። የእርሱ ተቀዳሚ ዓላማ የአባቱን ፈቃድ አባቱ በሚፈልገው መንገድ እንዲሁም እርሱ በመደበለት ጊዜ መፈጸም ነበር። ይህን ደግሞ ማንም እንዲያደናቅፍበት አልፈለገም። በመሆኑም ይህን ውሳኔውን ለእናቱ ጠበቅ አድርጎ የገለጸ ቢሆንም ንግግሩ አክብሮት የሌለው ወይም ደግነት የጎደለው አልነበረም። ማርያምም ብትሆን ልጇ እንዳሳፈራት ወይም እንደ ዘለፋት አልተሰማትም። ከዚህ ይልቅ ማርያም፣ ኢየሱስ የተናገረው ነገር ስለገባት በሠርጉ ላይ ለነበሩት አገልጋዮች “የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” ብላቸዋለች። ኢየሱስ፣ እናቱ ያለችውን ችላ ብሎ ከማለፍ ይልቅ ውኃውን ምርጥ ወደሆነ ወይን ጠጅ በመለወጥ መሲሕ ከሆነ በኋላ የመጀመሪያውን ተአምር ፈጸመ፤ በዚህ መንገድ፣ በአንድ በኩል የአባቱን ፈቃድ በመፈጸም በሌላ በኩል ደግሞ እናቱ ያሳሰባትን ነገር ለማቃለል እርምጃ በመውሰድ ግሩም የሆነ ሚዛናዊነት አሳይቷል።—ዮሐንስ 2:5-11
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ እናቱን ያናገራት በደግነት ቢሆንም ነጥቡን ጠበቅ አድርጎ ገልጿል