በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበረችው ኢየሩሳሌም—የአርኪኦሎጂ ውጤቶች ምን ይላሉ?
ኢየሩሳሌም ውስጥ በተለይ ከ1967 ወዲህ ከፍተኛ የአርኪኦሎጂ እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል። በአሁኑ ጊዜ ብዙዎቹ የቁፋሮ ቦታዎች ለሕዝብ ክፍት ናቸው። እስቲ ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹን አብረን እየጎበኘን አርኪኦሎጂ ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ጋር እንዴት እንደሚስማማ እንመልከት።
በንጉሥ ዳዊት ዘመን የነበረችው ኢየሩሳሌም
መጽሐፍ ቅዱስ የጽዮን ተራራ በማለት የሚጠራውና ጥንት የዳዊት ከተማ ተቆርቁሮበት የነበረው ቦታ ትልቅ ከተማ ከሆነችው ከዛሬዋ ኢየሩሳሌም ጋር ሲወዳደር ከቁጥር የሚገባም አይደለም። ከ1978-85 ባሉት ዓመታት በሟቹ ፕሮፌሰር ይገል ሻይሎ መሪነት በዳዊት ከተማ በተደረጉት ቁፋሮዎች ከጉብታው በስተ ምሥራቅ በደረጃ መልክ የተሠራ ግዙፍ ድንጋይ ወይም እንደ ድጋፍ ሆኖ የሚያገለግል ግንብ ተገኝቷል።
ይህ ኢያቡሳውያን (ዳዊት አካባቢውን ድል አድርጎ ከመያዙ በፊት የነበሩት ነዋሪዎች) ምሽግ ሠርተውበት የነበረው እንደ እርከን ያለ ግድግዳ ግዙፍ ቅሪት እንደሚሆን ፕሮፌሰር ሻይሎ ተናግረዋል። ሻይሎ በእነዚህ እንደ እርከን በተሠሩ ግድግዳዎች አናት ላይ ያገኙት በደረጃ መልክ የተሠራ ድንጋይ ዳዊት በኢያቡሳውያን ምሽግ ላይ እንደ አዲስ የገነባው አምባ ነው ብለዋል። በ2 ሳሙኤል 5:9 ላይ እንዲህ እናነባለን:- “ዳዊትም በአምባይቱ ውስጥ ተቀመጠ፣ የዳዊትም ከተማ ብሎ ጠራት። ዳዊትም ዙሪያዋን ከሚሎ ጀምሮ ወደ ውስጥ ቀጠራት።”
እዚሁ ግንብ አጠገብ የከተማዋ ጥንታዊ የውኃ መውረጃ በሮች ይገኛሉ፤ የዚህ የውኃ መውረጃ የተወሰነው ክፍል ከዳዊት ዘመን ጀምሮ የነበረ ይመስላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ስለ ኢየሩሳሌም የውኃ መውረጃ የሚናገሩት አንዳንድ ሐሳቦች ጥያቄ አስነስተዋል። ለምሳሌ ያህል ዳዊት አብረውት ለነበሩት “ኢያቡሳውያንንም የሚመታ በውኃ መሄጃው ይውጣ” ጠላትንም ‘ያውጣ’ ሲል ተናግሯል። (2 ሳሙኤል 5:8) ይህንን ያደረገው የዳዊት የጦር አዛዥ የነበረው ኢዮአብ ነው። ‘የውኃ መሄጃ’ ሲል ምንን ለመግለጽ ነው?
የታወቀውን የሰሊሆም የውኃ መውረጃ በተመለከተም ሌሎች ጥያቄዎች ተነሥተዋል። በንጉሥ ሕዝቅያስ መሐንዲሶች በስምንተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የተቆፈረውና በ2 ነገሥት 20:20 እንዲሁም በ2 ዜና መዋዕል 32:30 ላይ የተጠቀሰው የውኃ መውረጃ ይህ ሳይሆን አይቀርም። ይህን መተላለፊያ የቆፈሩት ሁለት ቡድኖች ከሁለት የተለያየ ጫፎች ተነሥተው እንዴት አንድ ቦታ ሊገናኙ ቻሉ? የውኃ መተላለፊያው ቀጥ ብሎ ቢሠራ ሊያጥር ሲችል ጠመዝማዛ አድርገው ለመሥራት የመረጡት ለምንድን ነው? በተለይ የተጠቀሙት በዘይት የሚሠራ መብራት መሆኑ ስለማይቀር እንዴት በቂ አየር ማግኘት ቻሉ?
ቢብሊካል አርኪኦሎጂ ሪቪው የተባለው መጽሔት ለእነዚህ ጥያቄዎች ተቀባይነት ያለው መልስ ሰጥቷል። የስነ ምድር ጥናት ሊቅ የሆኑትና በዚህ ቁፋሮ ወቅት በአማካሪነት ያገለገሉት ዳን ጊል እንደሚከተለው ሲሉ እንደተናገሩ ተጠቅሷል:- “ከዳዊት ከተማ በታች ግሩም የሆነ ተፈጥሮአዊ ሸረሸር ይገኛል። ሸረሸር የሚለው ቃል የስነ ምድር ተመራማሪዎች ከምድር በታች ባለ ዓለት ውስጥ የሚሰርግና የሚፈስስ ውኃ የሚፈጥረውን ጎድጓዳ ቦታ፣ ዋሻ እንዲሁም የውኃ መውረጃ ለማመልከት የሚጠቀሙበት ቃል ነው። . . . ከዳዊት ከተማ በታች በሚገኘው የምድር ለምድር የውኃ መስመር ላይ ያደረግነው ስነ ምድራዊ ምርምር እንደሚጠቁመው በተፈጥሮአዊ መሸርሸር የተፈጠሩትን የውኃ መውረጃዎችና ጉድጓዶች ሰዎች ጥበብ በተሞላበት መንገድ አስፍተው የውኃ አገልግሎት እንዲሰጡ አድርገዋቸዋል።”
ይህም ምናልባት የሰሊሆም የውኃ መውረጃ በቁፋሮ እንዴት ሊገኝ እንደቻለ ሳይጠቁመን አይቀርም። ይህ የውኃ መተላለፊያ በኮረብታዎቹ ሥር እየተጠማዘዘ የሚያልፈውን ተፈጥሮአዊ የውኃ መተላለፊያ ተከትሎ የተሠራ ሊሆን ይችላል። ከሁለቱ ጫፍ ተነሥተው መቆፈር የጀመሩት ሁለት ቡድኖች ቀደም ሲል የነበረውን ዋሻ በመቀየር ጊዜያዊ የውኃ መተላለፊያ አበጅተው ሊሆን ይችላል። ከዚያም ውኃው ከግዮን ምንጭ ተነስቶ ወደ ሰሊሆም ኩሬ እንዲያመራ ቁልቁል አንድ መውረጃ ተቆፍሮለታል፤ ይህ የውኃ መውረጃ በከተማዋ ቅጥር ውስጥ እንዲያልፍ ተደርጎ የተሠራ ሳይሆን አይቀርም። ርዝመቱ 533 ሜትር ቢሆንም እንኳ በሁለቱ ጫፎች መካከል የነበረው የከፍታ ልዩነት 32 ሳንቲ ሜትር ብቻ ነበር። ይህ በእርግጥም ድንቅ የምኅንድስና ጥበብ ነበር።
ምሁራን የጥንቷ ከተማ በአብዛኛው ውኃ ታገኝ የነበረው ከግዮን ምንጭ እንደነበር ከተገነዘቡ ቆይተዋል። ከከተማዋ ቅጥር ውጭ ይገኝ የነበረ ቢሆንም ብዙም ሩቅ ስላልነበር አንድ የውኃ መውረጃና 11 ሜትር ጥልቀት ያለው ጉድጓድ በቁፋሮ ሊገኝ ችሏል፤ ይህም ነዋሪዎቹ ከከተማዋ መከላከያ ቅጥር ሳይወጡ ውኃ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል። ይህ የውኃ መስመር በ1867 ለመጀመሪያ ጊዜ ባገኙት በቻርለስ ዋረን ስም የዋረን ጉድጓድ ተብሎ ተሰይሟል። ይሁን እንጂ ይህ የውኃ መውረጃና ጉድጓዱ የተሠሩት መቼ ነበር? በዳዊት ዘመን ነበሩን? ኢዮአብ የተጠቀመበት የውኃ መውረጃ ይህ ነበርን? ዳን ጊል እንዲህ ሲሉ መልስ ይሰጣሉ:- “የዋረን ጉድጓድ ተፈጥሮአዊ ሽንቁር መሆን አለመሆኑን ለማወቅ ወጣ ገባ ከሆነው ግድግዳ ላይ የካልካሪየስ ቅርፊት ወስደን በካርቦን 14 መርምረነው ነበር። ምንም አልነበረውም፤ ይህ ደግሞ ቅርፊቱ ከ40,000 የሚበልጡ ዓመታት እንደቆየ የሚያሳይ በመሆኑ ጉድጓዱ በሰው የተቆፈረ ነው ለማለት ፈጽሞ እንደማይቻል የማያሻማ ማረጋገጫ ይሰጣል።”
ከሕዝቅያስ ዘመን የተገኙ ቅሪቶች
ንጉሥ ሕዝቅያስ የኖረው የአሦር መንግሥት በፊቱ ያገኘውን ሁሉ ድል እያደረገ ይገሰግስ በነበረበት ዘመን ነበር። ሕዝቅያስ በነገሠ በስድስተኛው ዓመት አሦራውያን የአሥሩ ነገድ ዋና ከተማ የነበረችውን ሰማርያን ድል አደረጉ። ከስምንት ዓመታት በኋላ (በ732 ከዘአበ) አሦራውያኑ እንደገና መጥተው ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ማስፈራራት ጀመሩ። ሁለተኛ ዜና መዋዕል 32:1-8 ሕዝቅያስ የተጠቀመውን የመከላከያ ስልት ይገልጻል። ዛሬ ከዚያ ዘመን የቀሩ የሚታዩ ማስረጃዎች ይኖራሉን?
አዎን፣ በ1969 ፕሮፌሰር ናህማን አቪጋድ ከዚያ ዘመን የቀሩ ቅርሶችን አግኝተዋል። በተደረጉት ቁፋሮዎች አማካኝነት የአንድ ግዙፍ ግንብ የተወሰነ ክፍል የተገኘ ሲሆን የመጀመሪያው 40 ሜትር ርዝመትና 7 ሜትር ስፋት አለው፤ እንዲሁም ከፍታው 8 ሜትር እንደሚሆን ተገምቷል። ከፊሉ ግምብ የቆመው በመሬት ውስጥ ባለ አለት ላይ ሲሆን ከፊሉ ደግሞ በአዳዲስ ቤቶች ፍርሥራሽ ላይ ነው። ይህንን ግንብ የገነባው ማን ነው? የተገነባውስ መቼ ነው? አርኪኦሎጂያዊ ምርምሮችን ይዞ የሚወጣ አንድ መጽሔት እንደገለጸው “አቪጋድ ግንቡ የተሠራበትን ጊዜና ዓላማ እንዲያውቁ የረዷቸው ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ናቸው።” እነዚህ ጥቅሶች እንዲህ ይነበባሉ:- “ሰውነቱንም አጸናና፣ የፈረሰውንም ቅጥር ሁሉ ጠገነ፣ በላዩም ግንብ ሠራበት፣ ከእርሱም በስተ ውጭ ሌላ ቅጥር ሠራ።” (2 ዜና መዋዕል 32:5) “ቅጥሩንም ለማጥናት ቤቶችን አፈረሳችሁ።” (ኢሳይያስ 22:10) ዛሬ ሰፊ ቅጥር በመባል የሚታወቀው የዚህ ግንብ ክፍል በጥንቷ ከተማ የአይሁዳውያን መንደር ለጎብኚዎች ክፍት ሆኗል።
ኢየሩሳሌም በዚህ ወቅት የነበራት ስፋት እስከዚያ ጊዜ ድረስ ይኖራታል ተብሎ ከሚታሰበው የበለጠ እንደሆነ የተለያዩ ቁፋሮዎች አረጋግጠዋል፤ ይህም የሆነው የሰሜኑ መንግሥት በአሦራውያን ድል ከተደረገ በኋላ በነበረው የስደተኞች ፍልሰት ምክንያት ሳይሆን አይቀርም። ፕሮፌሰር ሻይሎ እንደገመቱት የኢያቡሳውያኑ ከተማ 6 ሄክታር መሬት የሚሸፍን ነበር። በሰሎሞን ጊዜ ደግሞ ወደ 16 ሄክታር ይሸፍን ነበር። ከ300 ዓመታት በኋላ በንጉሥ ሕዝቅያስ ዘመን ዙሪያውን በቅጥር የታጠረው የከተማዋ ክልል ወደ 60 ሄክታር መሬት አድጎ ነበር።
በመጀመሪያው ቤተ መቅደስ ዘመን የነበሩት መካነ መቃብሮች
በመጀመሪያው ቤተ መቅደስ ወቅት ማለትም ባቢሎናውያን በ607 ከዘአበ ኢየሩሳሌምን ከማጥፋታቸው በፊት የነበሩት መካነ መቃብሮችም ተጨማሪ የመረጃ ምንጭ ሆነዋል። በ1979/80 በሄኖም ሸለቆ ተዳፋት ላይ በርካታ የመቃብር ዋሻዎች በቁፋሮ በተገኙ ጊዜ በጣም አስገራሚ የምርምር ውጤቶች ታይተዋል። የአርኪኦሎጂ ምርምር የሚያካሂዱት ጋብሪየል ባርኬይ እንዲህ ብለዋል:- “በኢየሩሳሌም በተደረገው አርኪኦሎጂያዊ ምርምር ታሪክ ከመጀመሪያው ቤተ መቅደስ ዕቃ ማስቀመጫዎች መካከል እንደ አሁኑ ከነሙሉ ንብረታቸው የተገኙት በጣም ጥቂት ናቸው። እስከ አንድ ሺህ የሚደርሱ ነገሮችን በውስጡ ይዟል። በእስራኤል ውስጥ በተለይ ደግሞ በኢየሩሳሌም የተሠማሩት የአርኪኦሎጂ ተመራማሪዎች የሌት ተቀን ሕልም በጽሑፍ የሠፈረ ነገር ማግኘት ነው።” ከብር የተሠሩ ሁለት ትናንሽ ጥቅልሎች ተገኝተዋል፤ ይሁን እንጂ የያዙት ነገር ምን ነበር?
ባርኬይ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “የተዘረጋውን የብር ቁራጭ አግኝቼ በማጉያ መነፅር ስመለከተው ስስ በሆነውና በቀላሉ ሊቆረጥ በሚችለው የብር ጥቅልል ላይ ስለት ባለው መሣሪያ በጥንቃቄ የተጻፉ ፊደላት ሞልተውታል። . . . በጽሑፉ መካከል መለኮታዊው ስም ዮድ-ሄ-ዋው-ሄ በሚሉት አራት የዕብራይስጥ ፊደላት በግልጽ ተቀምጦ የሚታይ ሲሆን የተጻፈው በጥንቱ የዕብራይስጥ ሆሄያት ነው።” ባርኬይ ከዚያ በኋላ ትንሽ ቆይቶ ባሳተሙት ጽሑፍ ላይ እንዲህ በማለት ተናግረዋል:- “በጣም ያስገረመን በሁለቱም የብር ጥቅልል ቁራጮች ላይ የተቀረጸው ቃለ ቡራኬ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኘው የካህናቱ በረከት ጋር ተመሳሳይ መሆኑ ነው።” (ዘኁልቁ 6:24-26) በኢየሩሳሌም ውስጥ በተገኘ ጽሑፍ ላይ የይሖዋ ስም ሲገኝ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር።
ምሁራን እነዚህ የብር ጥቅልሎች ምን ያህል ዘመን እንዳስቆጠሩ ያወቁት እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ ከተገኙበት አርኪኦሎጂያዊ ሁኔታ በመነሣት ነበር። ከ300 የሚበልጡ የተሠሩበት ዘመን ሊታወቅ የሚችል የሸክላ ቁርጥራጮች በዕቃ ማስቀመጫው ውስጥ የተገኙ ሲሆን እነዚህም በሰባተኛውና በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የተሠሩ ናቸው። የሆሄያቱ አጻጻፍም ዘመናቸው ከሚታወቁት ከሌሎች ጽሑፎች ጋር ሲነጻጸር ይህንኑ ዘመን የሚጠቁም ሆኗል። እነዚህ ጥቅልሎች ኢየሩሳሌም በሚገኘው የእስራኤል ቤተ መዘክር ውስጥ ይገኛሉ።
በ607 ከዘአበ በኢየሩሳሌም ላይ የደረሰው ጥፋት
በ607 ከዘአበ በኢየሩሳሌም የደረሰውን ጥፋት በሚመለከት መጽሐፍ ቅዱስ በ2 ነገሥት ምዕራፍ 25፣ በ2 ዜና መዋዕል ምዕራፍ 36 እና በኤርምያስ ምዕራፍ 39 ላይ የናቡከደነፆር ሠራዊት ከተማዋን በእሳት እንዳጋያት ይገልጻል። በቅርቡ የተደረጉ ቁፋሮዎች የዚህን ታሪካዊ ዘገባ እውነተኛነት አረጋግጠዋልን? እንደ ፕሮፌሰር ይገል ሻይሎ አባባል ከሆነ “[ባቢሎናውያን ያደረሱትን ጥፋት በሚመለከት] በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ማስረጃ የሚደግፍ ግልጽ አርኪኦሎጂያዊ ማስረጃ ተገኝቷል፤ የተለያዩት ተቋሞች ጨርሶ መውደማቸው እንዲሁም የቤቶቹ ከእንጨት የተሠሩ የተለያዩ ክፍሎች በእሳት መበላታቸው ትክክል መሆኑ ተረጋግጧል።” አክለውም “በኢየሩሳሌም ውስጥ የተካሄዱት ቁፋሮዎች በሙሉ ስለዚህ ጥፋት የሚጠቁሙ ነገሮች ተገኝቶባቸዋል” ብለዋል።
ጎብኚዎች ከ2,500 ዓመታት በፊት የደረሰውን የዚህን ጥፋት ቅሪት መመልከት ይችላሉ። የእስራኤላውያኑ ማማ፣ የተቃጠለው ቤት እንዲሁም የማኅተሙ ቤት የሚሉት ስሞች ጥበቃ የሚደረግላቸውንና ለሕዝብ ክፍት የሆኑትን የአርኪኦሎጂ ቦታዎች የሚጠቁሙ የታወቁ ስሞች ናቸው። የአርኪኦሎጂ ተመራማሪዎቹ ጄን ኤም ካሂል እና ዴቪድ ታርለር ኤንሸንት ጀሩሳሌም ሪቪልድ በተባለው መጽሐፍ ውስጥ እንዲህ በማለት ጠቅለል አድርገው ተናግረዋል:- “ባቢሎናውያን በኢየሩሳሌም ላይ ያደረሱትን ከፍተኛ ጥፋት የሚያረጋግጠው ከተቃጠለው ቤት፣ ከማኅተሙ ቤትና ከመሳሰሉት ቦታዎች ተቆፍሮ የወጣው በቃጠሎ የከሰለ ግግር ብቻ ሳይሆን በምሥራቅ በኩል ያለውን ተዳፋት ሸፍኖ የተገኘው ከፈራረሱ ሕንጻዎች የወረደው የድንጋይ ክምር ጭምር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ከተማዋ ጥፋት የሚሰጠው መግለጫ . . . የአርኪኦሎጂ ግኝቱን የሚያጠናክር ነው።”
በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ከዳዊት ዘመን አንስቶ በ607 ከዘአበ እስከጠፋችበት ጊዜ ድረስ ኢየሩሳሌም ስለነበራት ሁኔታ የሚሰጠው መግለጫ ባለፉት 25 ዓመታት ውስጥ በተደረጉት የአርኪኦሎጂ ቁፋሮዎች በብዙ መንገድ ተረጋግጧል። ይሁን እንጂ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ስለነበረችው ኢየሩሳሌምስ ምን ማለት ይቻላል?
በኢየሱስ ዘመን የነበረችው ኢየሩሳሌም
ምሁራን በ70 እዘአ በሮማ ሠራዊት ከደረሰው ጥፋት በፊት በኢየሱስ ዘመን የነበረችው ኢየሩሳሌም ምን ትመስል እንደነበር ጥሩ ግንዛቤ እንዲያገኙ የረዳቸው የቁፋሮ ውጤቶች፣ መጽሐፍ ቅዱስ፣ የመጀመሪያው መቶ ዘመን የአይሁድ ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስና ሌሎችም ምንጮች የሚሰጡት መግለጫ ነው። በኢየሩሳሌም ከሚገኝ አንድ ትልቅ ሆቴል በስተጀርባ ያለው ሞዴል ከአዳዲስ የቁፋሮ ግኝቶች ጋር በሚስማማ መንገድ በየጊዜው እየታደሰ ነው። የከተማዋ ዋነኛ ገጽታ ቤተ መቅደሱ የሚገኝበት ጉብታ የነበረ ሲሆን ሄሮድስ መጠኑን በሰሎሞን ዘመን ከነበረው በሁለት እጥፍ አሳድጎታል። በጥንቱ ዓለም በሰው ከተሠሩት መድረኮች ሁሉ የሚበልጥ 480 ሜትር በ280 ሜትር ስፋት ያለው ትልቅ መድረክ ነበር። አንዳንዶቹ ለግንባታ ያገለገሉት ድንጋዮች እስከ 50 ቶን ይመዝኑ የነበረ ሲሆን አንዱ እንዲያውም ወደ 400 ቶን የሚጠጋ ክብደት ነበረው። አንድ ምሁር እንዳሉት “በጥንቱ ዘመን በየትኛውም ቦታ ይህን ያህል መጠን ያለው ለግንባታ የሚያገለግል ድንጋይ አልነበረም።”
ኢየሱስ “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፣ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ” ብሎ ሲናገር ሲሰሙ አንዳንዶቹ ሰዎች መደንገጣቸው አያስገርምም። ኢየሱስ የተናገረው “ስለ ሰውነቱ ቤተ መቅደስ” ቢሆንም ግዙፍ ስለሆነው የቤተ መቅደሱ ሕንፃ የተናገረ መስሏቸው ነበር። በመሆኑም “ይህ ቤተ መቅደስ ከአርባ ስድስት ዓመት ጀምሮ ይሠራ ነበር፣ አንተስ በሦስት ቀን ታነሣዋለህን?” ሲሉ ተናግረዋል። (ዮሐንስ 2:19-21) ቤተ መቅደሱ በነበረበት ጉብታ አካባቢ በተደረጉት ቁፋሮዎች አማካኝነት ዛሬ ወደዚያ የሚሄዱ ጎብኚዎች በኢየሱስ ዘመን ከነበሩት ነገሮች መካከል የተወሰኑትን ቅጥሮችና ሌሎቹንም የምኅንድስና ሥራዎች በከፊል መመልከት የሚችሉ ሲሆን ኢየሱስ እስከ ደቡባዊው የቤተ መቅደሱ በር እንደተጓዘባቸው በሚገመቱት ደረጃዎች መጓዝ ይችላሉ።
ከቤተ መቅደሱ ጉብታ ምዕራባዊ ቅጥር ብዙም ሳይርቅ በጥንቷ ከተማ የአይሁዳውያን መንደር ውስጥ በቁፋሮ የተገኙ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የተሠሩትና በጥሩ ሁኔታ የቀድሞ መልካቸውን እንዲይዙ የተደረጉ ሁለት ቦታዎች ማለትም የተቃጠለው ቤትና የሄሮዳውያን መኖሪያዎች ይገኛሉ። የተቃጠለው ቤት ከተገኘ በኋላ የአርኪኦሎጂ ተመራማሪው ናህማን አቪጋድ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ይህ ቤት በ70 እዘአ ኢየሩሳሌም በጠፋች ጊዜ በሮማውያን እንደተቃጠለ ምንም አያጠራጥርም። በከተማዋ ውስጥ በተደረጉት ቁፋሮዎች ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተማይቱ በእሳት እንደጋየች የሚያሳዩ ግልጽና የማያሻሙ የአርኪኦሎጂ ማስረጃዎች ተገኝተዋል።”— በገጽ 12 ላይ የሚገኙትን ፎቶግራፎች ተመልከት።
ከእነዚህ ግኝቶች መካከል አንዳንዶቹ በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ ስለተከናወኑት አንዳንድ ነገሮች የሚጠቁሙ ናቸው። ሕንጻዎቹ የሚገኙት በከተማዋ የላይኛው ክፍል ሲሆን ይህ ቦታ ሊቀ ካህናቱን ጨምሮ የኢየሩሳሌም ባለጠጎች የሚኖሩበት አካባቢ ነበር። በእነዚህ ቤቶች ውስጥ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሃይማኖታዊ የመንጻት ሥርዓት የሚከናወንባቸው ገንዳዎች ነበሩ። አንድ ምሁር እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል:- “ይህን ያህል ብዙ ቁጥር ያለው የመታጠቢያ ገንዳ መገኘቱ በከተማዋ የላይኛው ክፍል የሚኖሩት ሰዎች በሁለተኛው ቤተ መቅደስ ዘመን እንደ ሃይማኖታዊ ወግ የተያዘውን የንጽሕና ሥርዓት አጥብቀው ይከተሉ እንደነበር የሚያሳይ ማስረጃ ነው። (እነዚህ ሕጎች ስለ ሚክቬህ የሚያብራሩ አሥር ምዕራፎችን በያዘው በሚሽናህ ውስጥ ተገልጸዋል።)” ይህ መረጃ ኢየሱስ እነዚህን ሃይማኖታዊ ወጎች በተመለከተ ለጻፎችና ለፈሪሳውያን የተናገረውን ሐሳብ እንድናስተውል ይረዳናል።— ማቴዎስ 15:1-20፤ ማርቆስ 7:1-15
በተጨማሪም በኢየሩሳሌም ውስጥ በጣም የሚያስገርም ብዛት ያላቸው ከድንጋይ ተወቅረው የተሠሩ ዕቃዎች ተገኝተዋል። ናህማን አቪጋድ እንዲህ ብለዋል:- “በኢየሩሳሌም በእያንዳንዱ ሰው ቤት ውስጥ ይህን ያህል በብዛት ሊገኙ የቻሉት ለምንድን ነው? መልሱ አይሁዳውያን በደነገጉት ስለ ንጽሕና የሚገልጽ ሃይማኖታዊ ወግ ማለትም ሃላካህ ውስጥ ይገኛል። ሚሽና እንደሚለው ከሆነ ከድንጋይ ተወቅረው የተሠሩ ነገሮች በቀላሉ አይረክሱም። . . . ድንጋይ በሃይማኖታዊ ወግ በተገለጸው መንገድ አይረክስም።” ይህም ኢየሱስ ወደ ወይን የለወጠው ውኃ በሸክላ በተሠሩ ዕቃዎች ውስጥ ሳይሆን ከድንጋይ ተወቅረው በተዘጋጁ ጋኖች ውስጥ የተቀመጠበትን ምክንያት እንደሚያስረዳ ታምኖበታል።— ዘሌዋውያን 11:33፤ ዮሐንስ 2:6
የእስራኤልን ቤተ መዘክር ስንጎበኝ ሁለት እንግዳ የሆኑ የአጽም ማስቀመጫዎች እናያለን። ቢብሊካል አርኪኦሎጂ ሪቪው የተባለው መጽሔት እንዲህ ይላል:- “ሰዎች በአጽም ማስቀመጫዎቹ ይጠቀሙ የነበሩት ሮማውያን በ70 እዘአ ኢየሩሳሌምን ከማጥፋታቸው በግምት ከአንድ መቶ ዓመት በፊት ነበር። . . . አስከሬኑ በመቃብር ዋሻ ግድግዳ ላይ በተቦረቦረ ቦታ ውስጥ ያርፍና ሥጋው ከፈረሰ በኋላ አጥንቱ ብቻ ሲቀር ተሰብስቦ በአጽም ማስቀመጫ ውስጥ ይከተታል፤ ይህ ብዙውን ጊዜ ካጌጠ የኖራ ድንጋይ የሚሠራ ማስቀመጫ ነው።” ዛሬ ለጎብኚዎች እይታ ሲባል በቤተ መዘክር የተቀመጡት ሁለቱ የአጽም ማስቀመጫዎች በኅዳር 1990 በአንድ የመቃብር ዋሻ ውስጥ የተገኙ ናቸው። የአርኪኦሎጂ ተመራማሪው ዝቪ ግሪንሀት እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል:- “በመቃብር ቦታው በሁለቱ የአጽም ማስቀመጫዎች ላይ የተገኘው . . . ‘ቀያፋ’ የሚለው ቃል በአርኪኦሎጂ ግኝቶች መካከል ሲታይ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ይህ ምናልባት . . . በአዲስ ኪዳን ውስጥ የተጠቀሰው የሊቀ ካህናቱ የቀያፋ የቤተሰብ መጠሪያ ሳይሆን አይቀርም . . . ኢየሱስ ወደ ሮማዊው ገዢ ወደ ጴንጤናዊው ጲላጦስ የተወሰደው በኢየሩሳሌም ከሚገኘው የቀያፋ ቤት ነበር።” አንደኛው የአጽም ማስቀመጫ ወደ 60 ዓመት የሚጠጋ ዕድሜ ያለውን የአንድ ሰው አጥንቶች የያዘ ነው። ምሁራን እነዚህ አጥንቶች የቀያፋ እንደሚሆኑ ግምታዊ ሐሳብ ሰንዝረዋል። አንድ ምሁር እነዚህ ግኝቶች በኢየሱስ ዘመን የነበሩ መሆናቸውን በመግለጽ እንዲህ ብለዋል:- “ከሌሎቹ የአጽም ማስቀመጫዎች በአንዱ ውስጥ የተገኘ አንድ ሳንቲም በሄሮድስ አግሪጳ (37-44 እዘአ) የታመመ ነበር። ሁለቱ የቀያፋ የአጽም ማስቀመጫዎች የተሠሩት በዚያ መቶ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ ሊሆን ይችላል።”
በአሪዞና ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የቅርብ ምሥራቅ አርኪኦሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑት ዊሊያም ጂ ዴቨር ኢየሩሳሌምን በሚመለከት የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል:- “ባለፉት 15 ዓመታት ውስጥ ስለዚህ ቁልፍ አርኪኦሎጂያዊ ቦታ ያገኘነው እውቀት ከዚያ በፊት በነበሩት 150 ዓመታት ውስጥ ካገኘነው እውቀት የበለጠ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።” ባለፉት አሥርተ ዓመታት ውስጥ የተከናወኑት ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው ብዙ የአርኪኦሎጂ እንቅስቃሴዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪክ ይበልጥ ግልጽ የሚያደርጉ ውጤቶችን አስገኝተዋል።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ሁለተኛው ቤተ መቅደስ በነበረበት ዘመን የኢየሩሳሌም ከተማ ምን ዓይነት መልክ እንደነበራት የሚያሳይ ሞዴል-በኢየሩሳሌም በሚገኘው የሆሊላንድ ሆቴል ግቢ ውስጥ የሚገኝ
[በገጽ 10 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ከላይ:- የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ የሚገኝበት ጉብታ የደቡብ ምዕራብ ማዕዘን
በቀኝ:- ወደ ዋረን ጉድጓድ የሚወስደው መውረጃ