ስለ አምላክ ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው?
አንዳንዶች አምላክ ለሰው ልጆች ራሱን የመግለጥ ፍላጎት ያለው መሆኑን ይጠራጠራሉ። ፍላጎት ካለውስ ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው? በማለት ይጠይቃሉ።
በ16ኛው ክፍለ ዘመን ይኖር የነበረው የፕሮቴስታንት ተሃድሶ አራማጁ ጆን ካልቪን፣ የሰው ልጆች አምላክ ራሱን እስካልገለጠላቸው ድረስ በራሳቸው ጥረት ሊያውቁት አይችሉም የሚል ትክክለኛ መደምደሚያ ላይ ደርሶ ነበር። ይሁንና አንዳንዶች አምላክ ለሰው ልጆች ራሱን የመግለጥ ፍላጎት ያለው መሆኑን ይጠራጠራሉ። ፍላጎት ካለውስ ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው? በማለት ይጠይቃሉ።
ታላቁ ‘ፈጣሪ’ የሆነው ይሖዋ ሁሉንም ነገር የሚያከናውንበት የራሱ የሆነ ምክንያት አለው። ከዚህም በላይ “ሁሉን የሚችል አምላክ” እንደመሆኑ መጠን ዓላማው ሙሉ በሙሉ እንዲፈጸም የማድረግ ችሎታ አለው። (መክብብ 12:1፤ ዘፀአት 6:3) የአምላክ ነቢይ የሆነው አሞጽ በመንፈስ አነሳሽነት ተገፋፍቶ “በእውነት ጌታ እግዚአብሔር ምስጢሩን ለአገልጋዮቹ ለነቢያት ሳይገልጥ፣ ምንም ነገር አያደርግም” በማለት ስለጻፈ፣ አምላክ ዓላማውን ለሰው ልጆች የመግለጥ ፍላጎት እንዳለው እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ይሁንና አምላክ ዓላማውን የሚገልጠው ለአገልጋዮቹ ወይም ከልባቸው ለሚወዱት ብቻ ነው መባሉን ልብ በል። ይህም ምክንያታዊ ነው። አንተ ብትሆን ኖሮ ምስጢርህን የምትነግረው ለማን ነው? ላገኘኸው ሰው ሁሉ ነው ወይስ ለልብ ጓደኞችህ?—አሞጽ 3:7፤ ኢሳይያስ 40:13, 25, 26
ትሑት የሆኑ ሰዎች የአምላክን ጥበብና እውቀት እጅግ ያደንቃሉ። እንዲህ ማድረጋቸውም ተገቢ ነው። ይሁን እንጂ ከዚህ መለኮታዊ ጥበብና እውቀት ተጠቃሚዎች ለመሆን ከፈለግን አድናቆት ብቻውን አይበቃም። መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን አስተሳሰብ መማር ከፈለግን ትሑት ልብ ሊኖረን እንደሚገባ በአጽንኦት ሲገልጽ እንደሚከተሉት ባሉ አገላለጾች ይጠቀማል:- ‘ትእዛዜን በልብህ አኑር፤ ጆሮህን ወደ ጥበብ አቅና፤ ልብህንም ወደ ማስተዋል መልስ፤ እንዲሁም የመለየት ጥበብን ለማግኘት ተማጠን፤ ድምፅህን ከፍ አድርገህ ማስተዋልን ጥራ፤ እርሷንም እንደ ብር ፈልጋት።’—ምሳሌ 2:1-4
ይህን የመሰለውን ጥረት የሚያደርግ ትሑት ሰው በእርግጥም አምላክን ማወቅ ይችላል። በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው ይህ ጥቅስ ቀጠል አድርጎ “እግዚአብሔር ጥበብን ይሰጣልና፤ ከአንደበቱም ዕውቀትና ማስተዋል ይወጣል” በማለት ይገልጻል። አዎን፣ እውነትን ከልባቸው የሚፈልጉ ሰዎች “ጽድቅን፣ ፍትሕን፣ ሚዛናዊነትን፣ መልካሙንም መንገድ ሁሉ” መገንዘብ ይችላሉ።—ምሳሌ 2:6-9
እውነትን ለማግኘት የተደረገ ፍለጋ
ዚ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሪሊጅን እንደሚከተለው ብሏል:- “የሰው ልጅ ሕይወት እውን የሆነውንና ያልሆነውን፣ ኃያሉንና ደካማውን፣ እውነተኛውንና አታላዩን፣ ንጹሑንና የተበከለውን፣ ግልጽ የሆነውንና ያልሆነውን እንዲሁም በሁለት ጽንፎች መካከል ያለውን አንጻራዊ አመለካከት ለመለየት በሚደረግ ፍለጋ የተሞላ ነው።” ሰዎች ይህን ፍላጎታቸውን ለማሟላት ሲሉ ለብዙ ዘመናት እውነትን ሲፈልጉ ቆይተዋል። እያንዳንዱ ሰው መዝሙራዊው “የእውነት አምላክ” ብሎ የጠራውን ይሖዋን ለማግኘት እስከጣረ ድረስ ድካሙ ከንቱ ሆኖ አይቀርም።—መዝሙር 31:5
ይሖዋ የሚለው ስም ቃል በቃል ሲተረጎም “ይሆናል” የሚል ትርጉም አለው። (ዘፍጥረት 2:4 የአዲስ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) የአምላክ ስም ትርጉም በፈጣሪነቱና በዓላማው ላይ ያተኮረ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ይሖዋ የሚለውን ስም ማወቅና በስሙ መጠቀም የእውነተኛው ሃይማኖት መለያ ነው። ኢየሱስም ይህን ሐቅ በማያሻማ ሁኔታ ገልጿል። እንዲያውም ተከታዮቹን አስመልክቶ ለአምላክ ባቀረበው ጸሎት ላይ የሚከተለውን ብሏል:- “እኔንም የወደድህባት ፍቅር በእነርሱ እንድትሆን እኔም በእነርሱ፣ ስምህን አስታወቅኋቸው አስታውቃቸውማለሁ።”—ዮሐንስ 17:26 የ1954 ትርጉም
በጥንት ዘመን የኖረ ዮሴፍ የተባለ አንድ ዕብራዊ ሕልም እንዲፈታ ሲጠየቅ፣ ከአምላክ ጋር ባለው ወዳጅነት በመታመን በሙሉ ልብ “የሕልም ትርጓሜ ከእግዚአብሔር የሚገኝ አይደለምን?” ሲል ተናግሯል።—ዘፍጥረት 40:8፤ 41:15, 16
ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላም የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር የአገሩ ጠቢባን ሊፈቱት ያልቻሉትን አንድ ሕልም አይቶ ነበር። በዚህ ጊዜ ነቢዩ ዳንኤል ለንጉሡ “ምስጢርን የሚገልጥ አምላክ በሰማይ አለ፤ እርሱም በሚመጡት ዘመናት የሚሆነውን ነገር ለንጉሥ ናቡከደነፆር ገልጦአል” ብሎታል።—ዳንኤል 2:28
የዮሴፍና የዳንኤል ምሳሌ፣ ይሖዋ አምላክ ጥበቡንና እውቀቱን የሚገልጠው እርሱን ለሚያገለግሉት ብቻ መሆኑን ያሳያል። እውነት ነው፣ የአምላክን ሞገስ ማግኘት ከዚህ ቀደም የነበሩንን አንዳንድ አመለካከቶች መተውን ይጠይቅብን ይሆናል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩት አይሁዶች ወደ ክርስትና ሲለወጡ ተመሳሳይ የሆነ እርምጃ መውሰድ አስፈልጓቸዋል። የአይሁድ ሥርዓት ያወጣቸውን ደንቦች እንዲያከብሩና እንዲጠብቁ ተደርገው ያደጉ በመሆኑ “ለሚመጡት መልካም ነገሮች ጥላ” የሆነውን የሙሴን ሕግ ለመፈጸም የመጣውን ኢየሱስን መሲሕ አድርገው ለመቀበል ጊዜ ወስዶባቸው ነበር። (ዕብራውያን 10:1፤ ማቴዎስ 5:17፤ ሉቃስ 24:44, 45) የሙሴ ሕግ እጅግ በላቀው ‘በክርስቶስ ሕግ’ ተተክቶ ነበር።—ገላትያ 6:2፤ ሮሜ 13:10፤ ያዕቆብ 2:8
ሁላችንም የተወለድነው ከአምላክ በራቀ ዓለም ውስጥ ነው። ከመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ባልና ሚስት በወረስነው ኃጢአት ምክንያት ስንወለድ ጀምሮ ከአምላክ ጋር ጠላትነት ነበረን፤ በዚህም የተነሳ ስለ አምላክ ዓላማዎች ትክክለኛ እውቀት የለንም። ከዚህም ባሻገር ተንኰለኛ ልብ ወርሰናል። (ኤርምያስ 17:9፤ ኤፌሶን 2:12፤ 4:18፤ ቈላስይስ 1:21) የአምላክ ወዳጅ ለመሆን የእርሱን አስተሳሰብ መኮረጅ ይኖርብናል። ይህን ማድረግ ደግሞ ቀላል አይደለም።
የሐሰት ሃይማኖት አስተሳሰቦችንና ወጎችን ማስወገድ ከባድ ሊሆን ይችላል፤ በተለይም ደግሞ ከልጅነታችን ጀምሮ በውስጣችን ሲቀረጹ ከቆዩ ይህን ማድረጉ ይበልጥ አስቸጋሪ ይሆንብናል። ይሁንና በያዝነው የስሕተት ጎዳና መቀጠላችን ጥበብ ይሆናል? በጭራሽ! ከዚህ ይልቅ አስተሳሰብን ማስተካከልና የአምላክን ሞገስ ማግኘት የጥበብ እርምጃ መሆኑ አያጠራጥርም።
የአምላክ መመሪያ የሚተላለፍበትን መንገድ ማወቅ
የእውነትን ቃል ለመረዳትና ከቃሉ ጋር ተስማምቶ ለመኖር የሚያስችል እርዳታ ማግኘት የምንችለው ከየት ነው? አምላክ በጥንት ዘመን ይኖሩ ለነበሩት እስራኤላውያን ብሔሩን የሚመሩ ታማኝ ግለሰቦችን ሾሞላቸው ነበር። በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ የክርስቲያን ጉባኤ ራስ የሆነው ክርስቶስ እውነትን ከልባቸው የሚፈልጉ ሰዎችን ይመራቸዋል። ይህንንም የሚያደርገው ከልባቸው እውነትን የሚሹ ሰዎችን እንዲመሩና እንዲጠብቁ ኃላፊነት በሰጣቸው ታማኝ ተከታዮቹ አማካኝነት ነው። (ማቴዎስ 24:45-47፤ ቈላስይስ 1:18) ሆኖም አንድ ሰው የአምላክ መመሪያ የሚተላለፍበትን መንገድ ለይቶ ማወቅ የሚችለው እንዴት ነው?
የኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮች እርሱ በምድር ላይ ሳለ ያሳየውን ባሕርይ ለማንጸባረቅ የተቻላቸውን ያህል ይጥራሉ። ይህን መሰሉን መንፈሳዊ ባሕርይ ማዳበራቸው በክፋት እየባሰ በሚሄደው በዚህ ዓለም ውስጥ በግልጽ ተለይተው እንዲታወቁ ያደርጋቸዋል። (በገጽ 6 ላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት።) አንተ ወይም ጎረቤቶችህ በምትከተሉት ሃይማኖት ውስጥ እነዚህ ባሕርያት ሲንጸባረቁ ትመለከታለህ? ይህን ጉዳይ መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት በማድረግ መመርመሩ ጠቃሚ ነው።
አንተም መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ይህን እንድታደርግ እናበረታታሃለን። ባለፈው ዓመት በ235 አገሮችና ደሴቶች ውስጥ የሚገኙ በአማካይ ከ6,000,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት በሚያስችለው በዚህ መሰሉ ዝግጅት ተጠቃሚዎች ሆነዋል። የአምላክን ጥበብና እውቀት ማግኘት እርካታ የሚያስገኝ፣ የሚክስና ቀጣይ የሆነ ተግባር ነው። የአምላክን ጥበብና እውቀት ለማግኘት በሚደረገው በዚህ ጉዞ አንተስ ለምን ተካፋይ አትሆንም? እንዲህ በማድረግህ መቼም ቢሆን አትቆጭም። በእርግጥ አምላክን ማወቅ እንችላለን!
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአምላክን ፈቃድ የሚያደርጉ ሰዎች . . .
በፖለቲካዊ ግጭቶች ውስጥ አይሳተፉም። —ኢሳይያስ 2:4
መልካም ፍሬዎችን ያፈራሉ። —ማቴዎስ 7:13-23
በመካከላቸው እውነተኛ ፍቅር ይንጸባረቃል። —ዮሐንስ 13:35፤ 1 ዮሐንስ 4:20
አንድነት አላቸው። —ሚክያስ 2:12
በዙሪያቸው ያለው ዓለም የሚያንጸባርቀውን መጥፎ አመለካከትና ምግባር አይኮርጁም።—ዮሐንስ 17:16
ስለ እውነት ይመሰክራሉ እንዲሁም ሌሎችን ደቀ መዛሙርት ያደርጋሉ።—ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20
እርስ በርሳቸው ለመበረታታት አዘውትረው ይሰበሰባሉ።—ዕብራውያን 10:25
በዓለም ዙሪያ እንደ አንድ ሆነው አምላክን ያወድሳሉ። —ራእይ 7:9, 10
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አምላክ የሚሰጠውን እውቀት በግለሰብ፣ በቤተሰብና በጉባኤ ደረጃ ማግኘት ይቻላል