በእርግጥ አምላክን ማወቅ እንችላለን?
“እውነተኛ አምላክ የሆንኸውን አንተን . . . ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።”—ዮሐንስ 17:3
ሐዋርያው ጳውሎስ በአድናቆት ተሞልቶ “የእግዚአብሔር የጥበቡና የዕውቀቱ ባለ ጠግነት እንዴት ጥልቅ ነው!” ብሏል። ቀጠል አድርጎም “ፍርዱ አይመረመርም፤ ለመንገዱም ፈለግ የለውም!” በማለት ተናግሯል። (ሮሜ 11:33) እነዚህ ቃላት የአምላክ ጥበብና እውቀት በሰዎች ስለማይመረመር አምላክንም ሆነ ዓላማዎቹን ፈጽሞ ማወቅ አንችልም ብለን ለመደምደም ምክንያት ይሆኑናል?
ቪያ ኔጌቲቫ (negative way) የሚባለውን ሃይማኖታዊ ፍልስፍና የሚያራምዱ ሰዎች እንደሚሉት ከሆነ አምላክን ማወቅ አንችልም። ዚ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሪሊጅን ይህን ፍልስፍና አስመልክቶ እንደሚከተለው ይላል:- “አምላክ ልናውቀው ከምንችለው በላይ በጣም የላቀ ነው። . . . አምላክ ስም ሊወጣለትም ሆነ እንዲህ ነው ተብሎ ሊገለጽ አይችልም። ማንኛውም ስምም ሆነ መግለጫ ገደብ ያለው ሲሆን አምላክ ደግሞ . . . ገደብ የለውም። ከእውቀት በላይ ስለሆነ እርሱን ማወቅ አይቻልም።”a
ኒውስዊክ የተባለው መጽሔት እንደዘገበው ከሆነ እምብዛም ሃይማኖተኛ ባልሆነ ኅብረተሰብ ውስጥ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች “አንድ እውነት አለ፤ እርሱም እውነት የሚባል ነገር አለመኖሩ ነው” ወደሚለው “በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነትን እያገኘ ወዳለ አዲስ አስተሳሰብ” ያዘነበሉ ይመስላል።
ያም ሆኖ ብዙዎች የሕይወትን ዓላማ በተመለከተ ምላሽ ያላገኙ በርካታ ጥያቄዎች አሏቸው። እነዚህ ሰዎች ድህነት፣ በሽታና ዓመጽ የሚያስከትሏቸውን አሳዛኝ ችግሮች ተመልክተዋል። በመሆኑም ሕይወት አስተማማኝ አለመሆኑ ተስፋ አስቆራጭ ሆኖባቸዋል። እንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች ለጥያቄዎቻቸው መልስ ለማግኘት የሚጓጉ ቢሆኑም መልስ በማጣታቸው ሳቢያ ጥያቄዎቹ ጭራሹኑ መልስ የላቸውም ወደሚል መደምደሚያ ሊያመሩ ይችላሉ። በመሆኑም አብዛኞቹ ያሉበትን የሃይማኖት ድርጅት ለቅቀው ይወጣሉ፤ ስለ አምላክ መኖር ያላቸው እምነት ካልጠፋ ወደ እርሱ ያቀርበናል በሚሉት የራሳቸው የሆነ መንገድ መመላለስ ይጀምራሉ።
የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ጥሩ አመለካከት ያላቸውና ኢየሱስ ክርስቶስ የአምላክ ቃል አቀባይ መሆኑን የሚያምኑ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን አመለካከት ለማወቅ ጥረት ሊያደርጉ ይገባል። ምናልባት በአንድ ወቅት ኢየሱስ ስለ ሁለት ዓይነት መንገዶች የተናገረውን ታስታውስ ይሆናል። “ወደ ጥፋት የሚወስደው መንገድ ትልቅ . . . ወደ ሕይወት የሚያደርሰው ግን መንገዱ ቀጭን” እንደሆነ ተናግሯል። ኢየሱስ፣ በእነዚህ መንገዶች ላይ የሚጓዙትን ሰዎች ማንነት መለየት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ሲገልጽ “ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ” ብሏል። ፍሬያቸው ምን ዓይነት ነው? ኢየሱስ ቀጠል አድርጎ ፍሬው የሚናገሩት ነገር ሳይሆን ድርጊታቸው መሆኑን ሲገልጽ “በሰማይ ያለውን ያባቴን ፈቃድ ሳይፈጽም ‘ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤’ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማይ አይገባም” ብሏል። በአምላክ አምናለሁ ብሎ መናገር ብቻውን በቂ አይደለም። ከዚህ ይልቅ የአምላክን ፈቃድ መፈጸም ይገባል። ለዚህ ደግሞ በመጀመሪያ ደረጃ የአምላክን ፈቃድ በተመለከተ ትክክለኛ እውቀት ማግኘት አለብን ቢባል ምክንያታዊ ነው።—ማቴዎስ 7:13-23
ኢየሱስ የሰው ልጆች ስለ አምላክ ማወቅ እንደሚችሉ በግልጽ አመልክቷል። “እውነተኛ አምላክ የሆንኸውን አንተንና የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” ብሏል። (ዮሐንስ 17:3) በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው አምላክ የሚገልጠውን ጥበብና እውቀት ማግኘት እንችላለን፤ ሆኖም ይህን እውቀት ማግኘት የምንችለው ጥረት ካደረግን ብቻ ነው። ይሁን እንጂ አምላክ ይህን ለሚያደርጉ ሰዎች የዘላለም ሕይወት ስለሚሰጣቸው ድካማቸው የሚያስቆጭ አይሆንም።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ይህን መሰሉ አስተሳሰብ የምሥራቃውያን ሃይማኖት በሆኑት በሂንዱይዝም፣ በታኦይዝምና በቡድሂዝም ልማዶች ውስጥም ይገኛል።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጠባቡ መንገድ ወደ ሕይወት እንደሚያደርስ ኢየሱስ ተናግሯል