ምዕራፍ 20
ትንሣኤ—ለማንና የት?
1, 2. የጥንቶቹ የአምላክ አገልጋዮች በትንሣኤ ያምኑ እንደነበር እንዴት እናውቃለን?
በየትኛውም ጊዜ የነበሩ የአምላክ አገልጋዮች በትንሣኤ አምነዋል። ኢየሱስ ሰው ሆኖ ከመወለዱ ከ2, 000 ዓመታት በፊት ይኖር ስለነበረው ስለ አብርሃም መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር [ልጁን ይስሐቅን] ከሙታን እንኳ ሊያስነሣው እንዲቻለው አስቧል” ይላል። (ዕብራውያን 11:17-19) በኋላም የአምላክ አገልጋይ የነበረው ኢዮብ “ሰው ቢሞት እንደገና ሕያው ለመሆን ይችላልን?” በማለት ጠይቋል። ኢዮብ ራሱ ላስነሣው ጥያቄ መልስ ሲሰጥ ለአምላክ “ትጠራኛለህ፤ እኔ ራሴም እመልስልሃለሁ” ብሎታል። በዚህ መንገድ በትንሣኤ ያምን እንደነበረ አሳይቷል። — ኢዮብ 14:14, 15 አዓት
2 ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ “ሙታን እንዲነሡ ግን ሙሴ ደግሞ በቁጥቋጦው ዘንድ [ይሖዋን] የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ በማለቱ አስታወቀ፤ ሁሉ ለእርሱ ሕያዋን ስለሆኑ የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም” በማለት ስለ ጉዳዩ አብራርቷል። (ሉቃስ 20:37, 38) በክርስቲያን ግሪክኛ ጽሑፎች ውስጥ “ትንሣኤ” የሚለው ቃል ከ40 ጊዜ በላይ ተጠቅሷል። በእርግጥም የሙታን ትንሣኤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከዋና ዋናዎቹ ትምህርቶች አንዱ ነው። — ዕብራውያን 6:1, 2
3. ማርታ በትንሣኤ ላይ ምን እምነት እንደነበራት ገለጸች?
3 ኢየሱስን ትወድ የነበረችው ማርታ ወንድሟ አልዓዛር በሞተ ጊዜ በትንሣኤ እንደምታምን አሳይታለች። ኢየሱስ እየመጣ መሆኑን ስትሰማ ማርታ ልትቀበለው ሮጣ ወጣች:- “ጌታ ሆይ፥ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር” አለችው። የተሰማትን ኀዘን በመመልከት ኢየሱስ “ወንድምሽ ይነሣል” በሚሉት ቃላት አጽናናት። ማርታም መልሳ:- “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንዲነሣ አውቃለሁ” አለችው። — ዮሐንስ 11:17-24
4-6. ማርታ በትንሣኤ ለማመን ምን ምክንያቶች ነበሯት?
4 ማርታ በትንሣኤ ለማመን ጠንካራ ምክንያቶች ነበሯት። ለምሳሌ ከብዙ ዓመታት በፊት የአምላክ ነቢያት የነበሩት ኤልያስና ኤልሳዕ ከአምላክ ባገኙት ኃይል እያንዳንዳቸው አንድ አንድ ልጅ ከሞት ማስነሳታቸውን ታውቃለች። (1ነገሥት 17:17-24፤ 2ነገሥት 4:32-37) እንዲሁም አንድ የሞተ ሰው ወደ ጉድጓድ ተጥሎ የሞተውን የኤልሳዕን አጥንቶች ሲነካ ከሞት መነሣቱን ታውቃለች። (2ነገሥት 13:20, 21) ሆኖም በትንሣኤ ላይ ያላትን እምነት ከሁሉም ይበልጥ ያጠነከረላት ኢየሱስ ራሱ ያስተማረውና ያደረገው ነገር ነው።
5 ኢየሱስ ከሁለት ዓመታት ከሚያንስ ጊዜ በፊት ሙታንን በማስነሣት በኩል ስለሚኖረው ድርሻ ሲናገር ምናልባት ማርታ በዚያ ተገኝታ ሊሆን ይችላል። እንዲህ አለ:- “አብ ሙታንን እንደሚያነሣ ሕይወትም እንደሚሰጣቸው፥ እንዲሁ ወልድ ደግሞ ለሚወዳቸው ሕይወትን ይሰጣቸዋል። በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ . . . ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ።” — ዮሐንስ 5:21, 28, 29
6 ኢየሱስ እነዚህን ቃላት እስከተናገረበት ጊዜ ድረስ ማንንም ሰው ከሞት እንዳስነሣ የሚገልጽ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመዘገበ ታሪክ የለም። ይሁን እንጂ ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ናይን በምትባል ከተማ የአንዲት መበለት ልጅ የሆነን አንድ ወጣት አስነሣ። የዚህም ወሬ ወደ ደቡባዊ ይሁዳ ደርሶ ስለነበር ማርታ ስለዚህ ነገር እንደሰማች ምንም አያጠራጥርም። (ሉቃስ 7:11-17) በኋላም ማርታ በገሊላ ባሕር አጠገብ በኢያኢሮስ ቤት የተፈጸመውን ሰምታ መሆን አለባት። የ12 ዓመት ልጁ በጣም ታመመችና ሞተች። ሆኖም ኢየሱስ ወደ ኢያኢሮስ ቤት በመጣ ጊዜ ወደ ሞተችው ልጅ ሄደና:- “አንቺ ብላቴና ተነሽ” አላት። እርሷም ተነሥታ ቆመች! — ሉቃስ 8:40-56
7. ኢየሱስ ሙታንን ለማስነሣት እንደሚችል ለማርታ ምን ማረጋገጫ ሰጣት?
7 ያም ሆኖ ግን ማርታ ኢየሱስ ወንድሟን በዚህ ጊዜ እንደሚያስነሣላት አልጠበቀችም ነበር። “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንዲነሣ አውቃለሁ” ያለችውም በዚህ ምክንያት ነው። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ሙታንን በማስነሣቱ ሥራ የሚኖረውን ድርሻ በማርታ አእምሮ ውስጥ ለመቅረጽ እንዲህ አለ:- “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነ የሚያምንብኝ ሁሉ ለዘላለም አይሞትም።” ወዲያውም ኢየሱስን አልዓዛር ወደተቀበረበት ቦታ ወሰዱት። እርሱም “አልዓዛር ሆይ፥ ወደ ውጭ ና ብሎ ጮኸ።” ለአራት ቀን ሞቶ የነበረው አልዓዛርም ወጣ። — ዮሐንስ 11:24-26, 38-44
8. ኢየሱስ ከሞት ለመነሣቱ ምን ማረጋገጫ አለ?
8 ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ኢየሱስ ራሱ ተገደለና በመቃብር ውስጥ አኖሩት። ሆኖም እዚያ የቆየው ለሦስት ቀን ያህል ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ ይህ የሆነበትን ምክንያት እንደሚከተለው በማለት ገለጸ:- “ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው ለዚህም ነገር እኛ ሁላችን ምስክሮች ነን።” የአምላክ ልጅ ከመቃብር እንዳይወጣ የሃይማኖት መሪዎቹ ሊያግዱት አልቻሉም። (ሥራ 2:32፤ ማቴዎስ 27:62-66፤ 28:1-7) ክርስቶስ ከሞት መነሣቱ ምንም አያጠራጥርም ምክንያቱም ከዚያ በኋላ ለብዙ ደቀ መዛሙርቱ ሕያው ሆኖ ታይቷል። አንድ ጊዜ 500 ለሚሆኑት ታይቷል። (1 ቆሮንቶስ 15:3-8) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በትንሣኤ ላይ የነበራቸው እምነት በጣም ጠንካራ ከመሆኑ የተነሣ አምላክን ለማገልገል ሲባል ሞትን ለመቀበል ፈቃደኞች ነበሩ።
9. መጽሐፍ ቅዱስ የትኞቹ ዘጠኝ ሰዎች ከሞት መነሣታቸውን ይገልጻል?
9 ሙታን ሊነሡ እንደሚችሉ በሌላም ጊዜ በሐዋርያው ጴጥሮስና ጳውሎስ በኩል ተጨማሪ ማስረጃ ተሰጥቶናል። በመጀመሪያ ጴጥሮስ በኢዮጴ ከተማ የነበረችውን ዶርቃ የምትባል [ጣቢታ ተብላም ትጠራለች] ከሞት አስነሥቷል። (ሥራ 9:36-42) ከዚያም በኋላ ጳውሎስ እየተናገረ እያለ ከሦስተኛ ፎቅ መስኮት ወድቆ የሞተውን አውጤኪስ የተባለ ወጣት ጳውሎስ ከሞት አስነሥቶታል። (ሥራ 20:7-12) በእርግጥም እነዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙ ዘጠኝ ትንሣኤዎች ሙታን እንደገና ሊነሡ እንደሚችሉ የማያጠራጥር ማረጋገጫ ይሰጣሉ!
የሚነሡት እነማን ናቸው?
10, 11. (ሀ) አምላክ የትንሣኤ ዝግጅት ያደረገው ለምንድን ነው? (ለ) በሥራ 24:15 መሠረት የትኞቹ ሁለት ወገኖች ትንሣኤ ያገኛሉ?
10 በመጀመሪያ አምላክ ማንንም ሰው ከሞት የማስነሣት ዓላማ አልነበረውም፤ ምክንያቱም አዳምና ሔዋን ታማኝ ሆነው ቢቀጥሉ ኖሮ ማንም ሰው መሞት አያስፈልገውም ነበር። ነገር ግን የአዳም ኃጢአት በሁሉም ሰው ላይ አለፍጽምናንና ሞትን አመጣ። (ሮሜ 5:12) ስለዚህ ከአዳም ልጆች መካከል የሚፈልጉ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ሲል ይሖዋ ትንሣኤን አዘጋጀ። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ትንሣኤ ማግኘቱንና አለማግኘቱን የሚወስነው ምንድን ነው?
11 መጽሐፍ ቅዱስ ‘ጻድቃንም ዓመፀኞችም ይነሣሉ’ በማለት ስለ ሁኔታው ያብራራል። (ሥራ 24:15) ይህ አንዳንዶችን ያስገርማቸው ይሆናል። “ዓመፀኞችን” እንደገና ወደ ሕይወት ለምን ያመጣቸዋል?’ ብለው ይገረሙ ይሆናል። ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ በነበረበት ጊዜ የተፈጸመው ሁኔታ ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ይረዳናል።
12, 13. (ሀ) ኢየሱስ ለአንድ ወንጀለኛ ምን ብሎ ቃል ገባለት? (ለ) ኢየሱስ የተናገረላት “ገነት” የምትገኘው የት ነው?
12 እነዚህ በኢየሱስ ጎን የተሰቀሉት ሰዎች ወንጀለኞች ናቸው። አንደኛው “አንተስ ክርስቶስ አይደለህምን? ራስህንም እኛንም አድን ብሎ ሰደበው።” ሌላው ወንጀለኛ ግን በኢየሱስ አመነ። ወደ እርሱም ዘወር ብሎ “በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ አለው።” በዚያን ጊዜም ኢየሱስ “ዛሬ እውነት እልሃለሁ፣ በገነት ከእኔ ጋር ትሆናለህ” በማለት ቃል ገባለት። — ሉቃስ 23:39-43 አዓት
13 ይሁን እንጂ እዚህ ላይ ኢየሱስ:- “በገነት ከእኔ ጋር ትሆናለህ” ሲል ምን ማለቱ ነበር? ገነት የት ናት ? የዚህን መልስ ለማወቅ ‘አምላክ በመጀመሪያ የፈጠራት ገነት የት ነበረች?’ ብለን እንጠይቃለን። በምድር ላይ ነበረች፤ አይደለም እንዴ? አምላክ የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት የኤደን የአትክልት ስፍራ ተብላ በምትጠራ ውብ ገነት ውስጥ አስቀመጣቸው። ስለዚህ ይህ ድሮ ወንጀለኛ የነበረው ሰው በገነት ውስጥ እንደሚሆን ስናነብ ይህች ምድር ለመኖሪያ የምትሆን ውብ ቦታ እንደምትደረግ በአእምሮአችን ሊታየን ይገባል። “ገነት” የሚለው ቃል “የአትክልት ቦታ” ወይም “የመናፈሻ ቦታ” ማለት ነው።— ዘፍጥረት 2:8, 9
14. ኢየሱስ ቀድሞ ወንጀለኛ ከነበረው ሰው ጋር በገነት አብሮ የሚሆነው በምን መንገድ ነው?
14 እርግጥ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀድሞ ወንጀለኛ ከነበረው ሰውዬ ጋር እዚህ ምድር ላይ አይቀመጥም። ኢየሱስ በሰማይ ሆኖ በምድራዊት ገነት ላይ ንጉሥ ሆኖ ይገዛል። ስለዚህ ከዚያ ሰው ጋር የሚሆነው ከሞት ስለሚያስነሣውና ሥጋዊም ሆነ መንፈሳዊ ፍላጎቱን ስለሚያሟላለት ነው። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ወንጀለኛ የነበረን ሰው በገነት ውስጥ እንዲኖር የሚፈቅድለት ለምንድን ነው?
15. “ዓመፀኞች” ከሞት የሚነሡት ለምንድን ነው?
15 ይህ ሰው መጥፎ ነገሮችን ማድረጉ እውነት ነው። “ዓመፀኛ” ሰው ነበር። በተጨማሪም የአምላክን ፈቃድ አያውቅም ነበር። ይሁን እንጂ ስለ አምላክ ዓላማዎች ቢያውቅ ኖሮ ወንጀለኛ ይሆን ነበርን? ሁኔታውን ለማየት ኢየሱስ ይህንን ዓመፀኛና የአምላክን ፈቃድ ሳያውቁ የሞቱ ሌሎች ብዙ ሺህ ሚልዮን ሰዎችን ከሞት ያስነሣቸዋል። ለምሳሌ ያህል ባለፉት ክፍለ ዘመናት ማንበብ የማይችሉና መጽሐፍ ቅዱስን በጭራሽ አይተው የማያውቁ ብዙ ሰዎች ሞተዋል። ይሁን እንጂ እነዚህ ከሲኦል ወይም ከሐዴስ ይነሣሉ። ከዚያም በገነቲቱ ምድር ውስጥ የአምላክን ፈቃድ ይማራሉ። ፈቃዱን በማድረግ በእውነት አምላክን እንደሚወዱት ለማረጋገጥም አጋጣሚ ይኖራቸዋል።
16. (ሀ) ከሙታን መካከል የማይነሡት እነማን ናቸው? (ለ) በነገሮች ላይ ፍርድ ለመስጠት መሞከር የማይገባን ለምንድን ነው? (ሐ) በጣም ሊያሳስበን የሚገባው ምን መሆን ይኖርበታል?
16 ይህም ሲባል ሁሉም ሰው ትንሣኤ ያገኛል ማለት አይደለም። ኢየሱስን አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ ትንሣኤ እንደማያገኝ መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል። አውቆ በሠራው ክፉ ድርጊት ምክንያት ይሁዳ ‘የጥፋት ልጅ’ ተብሎ ተጠርቷል። (ዮሐንስ 17:12) እርሱ ትንሣኤ ወደማይገኝበት ምሳሌያዊ ገሃነም ሄዷል። (ማቴዎስ 23:33) የአምላክን ፈቃድ ካወቁ በኋላ ሆነ ብለው መጥፎ ነገር የሚያደርጉ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ላይ ኃጢአት ሠርተው ሊሆን ይችላል። ደግሞም በመንፈስ ቅዱስ ላይ ኃጢአት የሚሠሩትን አምላክ ከሞት አያስነሣቸውም። (ማቴዎስ 12:32፤ ዕብራውያን 6:4-6፤ 10:26, 27) ነገር ግን ፈራጁ አምላክ ስለሆነ ባለፉት ዘመናት የነበሩት ወይም በዘመናችን ያሉት አንዳንድ ክፉ ሰዎች ይነሣሉ ወይም አይነሡም ብለን ለመናገር የምንሞክርበት ምንም ምክንያት የለንም። አምላክ እነማን በሐዴስ ውስጥ እንዳሉ እነማን ደግሞ በገሃነም ውስጥ እንዳሉ ያውቃል። በእኛ በኩል ግን አምላክ በአዲሱ ሥርዓቱ ውስጥ እንዲገቡ የሚፈልጋቸው ዓይነት ሰዎች ለመሆን የምንችለውን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል። — ሉቃስ 13:24, 29
17. የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ትንሣኤ የማያስፈልጋቸው እነማን ናቸው?
17 እንደ እውነቱ ከሆነ የዘላለም ሕይወት ከሚያገኙት መካከል ትንሣኤ የሚያስፈልጋቸው ሁሉም አይደሉም። አሁን በዚህ የነገሮች ሥርዓት ‘የመጨረሻ ቀኖች’ ውስጥ የሚኖሩ ብዙዎች የአምላክ አገልጋዮች አርማጌዶንን በሕይወት ያልፋሉ። ከዚያም የጻድቅ “አዲስ ምድር” ክፍል በመሆን መሞት በፍጹም አያስፈልጋቸውም። ኢየሱስ “ሕያው የሆነ የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም” በማለት ለማርታ የነገራት ነገር በእነርሱ ላይ ቃል በቃል ሊፈጸም ይችላል። — ዮሐንስ 11:26፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1
18. ትንሣኤ የሚያገኙት “ጻድቃን” እነማን ናቸው?
18 ትንሣኤ የሚያገኙት “ጻድቃን” እነማን ናቸው? ከእነዚህ መካከል ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ይኖሩ የነበሩ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ይገኛሉ። ከእነዚህ ውስጥ ብዙዎቹ በዕብራውያን ምዕራፍ 11 ላይ በስም ተጠቅሰዋል። እነርሱ ወደ ሰማይ ለመሄድ ተስፋ አላደረጉም። ነገር ግን በምድር ላይ እንደገና ለመኖር ተስፋ አድርገዋል። በተጨማሪም ትንሣኤ ከሚያገኙት “ጻድቃን” መካከል በቅርብ ዓመታት የሞቱት ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ይገኛሉ። አምላክ እነርሱን ከሞት በማስነሣት በምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር የነበራቸው ተስፋ እንዲፈጸምላቸው ያደርጋል።
የሚነሡት መቼና የት ነው?
19. (ሀ) ኢየሱስ በትንሣኤ የመጀመሪያ የሆነው በምን መንገድ ነው? (ለ) ቀጥለው የሚነሡት እነማን ናቸው?
19 ኢየሱስ ክርስቶስ ‘ከሙታን ትንሣኤ የመጀመሪያው’ እንደሆነ ተነግሮለታል። (ሥራ 26:23 አዓት) ይህም ሲባል እንደገና መሞት ከማያስፈልጋቸው ውስጥ በመጀመሪያ የተነሣው እርሱ ነው ማለት ነው። በተጨማሪም መንፈሳዊ አካል በመሆን በመጀመሪያ የተነሣው እርሱ ነው። (1 ጴጥሮሰ 3:18) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው ብሎ በመግለጽ ሌሎቹም እንደሚኖሩ ይናገራል:- “እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ ክርስቶስ እንደ በኩራት ነው፥ በኋላም [በመገኘቱ] ለክርስቶስ የሆኑት ናቸው።” (1 ቆሮንቶስ 15:20-23) ስለዚህ በትንሣኤ ጊዜ አንዳንዶች ከሌሎች ቀድመው ይነሣሉ።
20. (ሀ) “ለክርስቶስ የሆኑት” እነማን ናቸው? (ለ) ምን ዓይነትስ ትንሣኤ ይኖራቸዋል?
20 “ለክርስቶስ የሆኑት” የተባሉት በመንግሥቱ ከእርሱ ጋር ለመግዛት የተመረጡት 144, 000 ታማኝ ደቀመዛሙርቱ ናቸው። እነርሱ ስለሚያገኙት ሰማያዊ ትንሣኤ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “በፊተኛው ትንሣኤ ዕድል ያለው ብፁዕና ቅዱስ ነው፤ ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ስልጣን የለውም፥ ዳሩ ግን . . . ከእርሱ ጋር ይህን ሺህ ዓመት ይነግሣሉ።” — ራዕይ 20:6፤ 14:1, 3
21. (ሀ) “የመጀመሪያው ትንሣኤ” የሚጀምረው መቼ ነው? (ለ) ለሰማያዊ ሕይወት እስካሁን እነማን እንደተነሡ አያጠራጥርም?
21 ስለዚህ ከክርስቶስ በመቀጠል ከሞት የሚነሡት 144, 000ዎቹ ናቸው። እነርሱ “በመጀመሪያው ትንሣኤ” ወይም “በፊተኛው ትንሣኤ” ይካፈላሉ። (ፊልጵስዩስ 3:11) ይህስ የሚፈጸመው መቼ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “በመገኘቱ” ጊዜ ነው ይላል። ቀደም ባሉት ምዕራፎች ላይ እንደተማርነው የክርስቶስ መገኘት የጀመረው በ1914 ነው። ስለዚህ ታማኝ ክርስቲያኖች ወደ ሰማይ ለመሄድ “የመጀመሪያ ትንሣኤ” የሚያገኙበት ቀን ጀምሯል ማለት ነው። ሐዋርያትና ሌሎች የጥንት ክርስቲያኖች በአሁኑ ጊዜ እንደተነሱና ሰማያዊ ሕይወት እንዳገኙ አያጠራጥርም። — 2 ጢሞቴዎስ 4:8
22. (ሀ) “በፊተኛው ትንሣኤ” እነማንም ጭምር ድርሻ ይኖራቸዋል? (ለ) እነርሱስ የሚነሡት መቼ ነው?
22 ሆኖም ከክርስቶስ ጋር በሰማይ የመግዛት ተስፋ ካላቸው መካከል ክርስቶስ ለዓይን በማይታይ ሁኔታ በተገኘበት በአሁኑ ዘመን በሕይወት የሚኖሩ ክርስቲያኖች አሉ። ቀሪዎቹ ማለትም ከ144, 000ዎቹ ውስጥ ገና በምድር ላይ የቀሩት እነርሱ ናቸው። ታዲያ ትንሣኤ የሚያገኙት መቼ ነው? እነርሱ በሞት አንቀላፍተው መቆየት አያስፈልጋቸውም፤ ነገር ግን ሲሞቱ ወዲያውኑ ይነሣሉ። መጽሐፍ ቅዱስ:- “ሁላችን አናንቀላፋም ነገር ግን የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበተ ዓይን እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋልና ሙታንም . . . ይነሣሉ” በማለት ይገልጻል። — 1 ቆሮንቶስ 15:51, 52፤ 1 ተሰሎንቄ 4:15-17
23. ወደ መንፈሳዊ ሕይወት የሚደረገውን ለውጥ መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት አድርጎ ይገልጸዋል?
23 ሆኖም ግን ይህ ሰማያዊ ሕይወት የሚያስገኝ “የመጀመሪያ ትንሣኤ” ለሰዎች ዓይን የማይታይ ነው። ይህን ትንሣኤ የሚያገኙ ሰዎች መንፈሳዊ ፍጥረታት ሆነው ሕይወት ያገኛሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ወደ መንፈሳዊ ሕይወት የሚደረገውን ለውጥ እንደሚከተለው ይገልጸዋል:- “በመበስበስ ይዘራል ባለመበስበስ ይነሣል፤ በውርደት ይዘራል በክብር ይነሣል፤ . . . ፍጥረታዊ አካል ይዘራል፥ መንፈሳዊ አካል ይነሣል።” — 1 ቆሮንቶስ 15:42-44
24. (ሀ) ‘ከመጀመሪያው ትንሣኤ’ የሚቀጥለው ትንሣኤ የትኛው ነው? (ለ) “የሚበልጥ ትንሣኤ” የተባለውስ ለምንድን ነው?
24 ይሁን እንጂ “ፊተኛው ትንሣኤ” የሚለው አገላለጽ ሌላ ትንሣኤ እንደሚቀጥል ያሳያል። ይህም ጻድቃንም ሆኑ ዓመፀኞች ገነት በምትሆነዋ ምድር ላይ ሕይወት የሚያገኙበት ትንሣኤ ነው። ይህ ከአርማጌዶን በኋላ ይከናወናል። ይህም ኤልያስና ኤልሳዕ ያስነሡአቸው ልጆች እንዲሁም በምድር ላይ ተነሥተው የነበሩ ሰዎች ካገኙት ትንሣኤ ‘የሚበልጥ ትንሣኤ’ ይሆናል። ለምን? ምክንያቱም ከአርማጌዶን በኋላ ትንሣኤ የሚያገኙት ሰዎች አምላክን ለማገልገል ከመረጡ እንደገና መሞት አያስፈልጋቸውም። — ዕብራውያን 11:35
አምላክ የሚፈጽመው ተአምር
25. (ሀ) ከሞት የሚነሣው የበፊቱ አካል የማይሆነው ለምንድን ነው? (ለ) የሚነሣው ምኑ ነው? ለሚነሡትስ ምን ይሰጣቸዋል?
25 አንድ ሰው ከሞተ በኋላ የሚነሣው ምኑ ነው? በፊት የሞተው አካል አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰማያዊ ሕይወት ትንሣኤ ሲያብራራ ይህንን አሳይቷል። (1 ቆሮንቶስ 15:35-44) በምድር ላይ ሕይወት ለማግኘት የሚነሡትም ቢሆኑ በፊት በሕይወት በነበሩበት ጊዜ የነበራቸውን አካል አያገኙም። ያ አካል ምናልባት በስብሶ ወደ አፈር ተመልሶ ይሆናል። የሞተው አካል የተገነባባቸው ንጥረ ነገሮች ከጊዜ በኋላ የሌሎች ሕያዋን ነገሮች ክፍል ሆነው ይሆናል። ስለዚህም አምላክ የሚያስነሣው ያንኑን አካል ሳይሆን የሞተውን ያንኑን ሰው ይሆናል። ወደ ሰማይ ለሚሄዱት ሰዎች አዲስ መንፈሳዊ አካል ይሰጣቸዋል። በምድር ላይ ለመኖር ትንሣኤ ለሚያገኙትም አዲስ ሥጋዊ አካል ይሰጣቸዋል። ሰውየው ከመሞቱ በፊት የሚያውቁት ሰዎች አሁንም ለይተው እንዲያውቁት አዲሱ ሥጋዊ አካሉ ፊት ከነበረው አካሉ ጋር ተመሳሳይ እንደሚሆን አያጠራጥርም።
26. (ሀ) ትንሣኤ ይህን ያህል አስደናቂ ተአምር የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) አምላክ ሞተው ያሉትን ሰዎች ለማስታወስ ያለውን ታላቅ ችሎታ ለመረዳት የሚያስችሉን ሰዎች የፈለሰፏቸው ምን ነገሮች አሉ?
26 ትንሣኤ በእርግጥ አስደናቂ ተአምር ነው። የሞተው ሰው በሕይወት ዘመኑ ውስጥ ብዙ ነገር አሳልፎና ብዙ እውቀት ገንብቶ ሊሆን ይችላል። ብዙ ትዝታዎችም ይኖሩት ይሆናል። በሕይወት ከኖሩት ከሌሎች ሰዎች ሁሉ ልዩ የሚያደርገውን ባሕርይ አዳብሯል። ሆኖም ይሖዋ አምላክ እያንዳንዱን ዝርዝር ሁኔታ ያስታውሳል። ከሞት በሚያስነሣበት ጊዜ እነዚህን ባሕርያት አሟልቶ የያዘውን ሰው መልሶ ያመጣዋል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው ወደፊት የሚነሡት ሙታን:- “ሁሉ ለእርሱ ሕያዋን” ናቸው። (ሉቃስ 20:38) የሰዎችን ድምፅና ስዕል መቅረጽና ሰውየው ከሞተ ከረጅም ጊዜ በኋላ ይህንን ድምፅና ስዕል መስማትና ማየት ተችሏል። ይሖዋ ግን ሕያው አድርጎ የሚያስታውሳቸውን ሰዎች በሙሉ መልሶ ወደ ሕያውነት ሊያመጣቸው ይችላል፤ ደግሞም በእርግጥ ያመጣቸዋል።
27. ቀጥሎ ትንሣኤን ለሚመለከቱ ለየትኞቹ ጥያቄዎች መልስ እናገኛለን?
27 መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን ከተነሡ በኋላ በገነት ውስጥ ስለሚኖረው ሕይወት ብዙ ተጨማሪ ነገር ይገልጽልናል። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ አንዳንዶቹ “ለሕይወት ትንሣኤ” ሌሎቹ ደግሞ “ለፍርድ ትንሣኤ” እንደሚነሡ ተናግሯል። (ዮሐንስ 5:29) ምን ማለቱ ነበር? ትንሣኤ የሚያገኙት “ጻድቃን” የሚገጥማቸው ሁኔታ ‘ዓመፀኞቹ’ ከሚገጥማቸው ሁኔታ የተለየ ይሆናልን? ስለ ፍርድ ቀን የምናደርገው ጥናት ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጠናል።
[በገጽ 167 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
“በትንሣኤ እንዲነሣ አውቃለሁ”
ኤልያስ የአንዲት መበለት ወንድ ልጅ አስነሥቷል
አልሳዕ አንድ ልጅ አስነሥቷል
የኤላሳዕን አጥንቶች የነካ አንድ ሰው ሕያው ሆኗል
[በገጽ 168 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ኢየሱስ ያስነሣቸው ሰዎች
የናይን መበለት ወንድ ልጅ
አልዓዛር
የኢያኢሮስ ሴት ልጅ
[በገጽ 169 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ትንሣኤ ያገኙ ሌሎች ሰዎች
ዶርቃ
ኢየሱስ ራሱ
አውጤኪስ
[በገጽ 170 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ለክፉ አድራጊው ቃል የገባለት ገነት የምትገኘው የት ነው?