የይሖዋን ፈቃድ ፈጽመዋል
ጳውሎስ የደረሰበትን መከራ በድል ተወጣ
ጳውሎስ በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ ወድቋል። እርሱና ሌሎች 275 ሰዎች የተሳፈሩበት መርከብ በሜድትራኒያን ባሕር ላይ የሚነሳ አውራቂስ የሚባለው በጣም አደገኛ ዓውሎ ነፋስ ገጥሞታል። ዓውሎ ነፋሱ ኃይለኛ ከመሆኑ የተነሳ ቀን ፀሐይን ማታ ደግሞ ከዋክብትን ማየት አልተቻለም ነበር። በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው መንገደኞቹ በሕይወት እንተርፋለን የሚል ተስፋ አልነበራቸውም። ሆኖም ጳውሎስ “ይህ መርከብ እንጂ ከእናንተ አንድ ነፍስ እንኳ አይጠፋም” ሲል አምላክ በሕልም የገለጠለትን በመንገር አጽናናቸው።—ሥራ 27:14, 20-22
ዓውሎ ነፋሱ በያዛቸው በ14ኛው ቀን መርከበኞቹ የውኃው ጥልቀት ሀያ አክናድ ብቻ መሆኑን ሲገነዘቡ ተደሰቱ።a ጥቂት ርቀት ከተጓዙ በኋላ እንደገና መለኪያ ገመድ ጣሉ። በዚህ ጊዜ ጥልቀቱ 15 አክናድ ሆኖ ተገኘ። ወደ የብስ ተቃርበዋል! ሆኖም ይህ ምሥራች የራሱ የሆነ ሊጤን የሚገባው አንድምታ አለው። መርከቡ ጥልቀት በሌለው ውኃ ላይ በጨለማ ወዲያና ወዲህ ሲንሳፈፍ ከዓለት ጋር ተላትሞ የመሰባበር አደጋ ሊያጋጥመው ይችላል። መርከበኞቹ መልሕቆቹን መጣላቸው ጥበብ ያለበት እርምጃ ነበር። ከእነርሱ መካከል አንዳንዶቹ ለመጠባበቂያ የተዘጋጀችውን ታንኳ አውርደው እንደምንም በባሕሩ ላይ ለመቅዘፍ አሰቡ።b ሆኖም ጳውሎስ ለጦር መኮንኑና ለወታደሮቹ “እነዚህ በመርከቡ ካልቆዩ እናንተ ትድኑ ዘንድ አትችሉም” ብሎ በመንገር እንዳይሄዱ አገዳቸው። መኮንኑ በጳውሎስ ሐሳብ በመስማማቱ በመርከቡ ላይ ያሉት 276 ተሳፋሪዎች በሙሉ ጎሕ እስኪቀድ ድረስ በጭንቀት ተውጠው መጠባበቅ ያዙ።—ሥራ 27:27-32
የመርከብ መሰበር አደጋ
በሚቀጥለው ቀን ጠዋት የመርከቡ ተሳፋሪዎች የአሸዋ ዳር ያለው የባሕር ሰርጥ ተመለከቱ። መርከበኞቹ እንደገና ተስፋቸው አብቦ መልሕቆቹን ፈትተው ታናሹን ሸራ ለነፋስ ከፍ አደረጉት። መርከቡ ወደ ባሕር ዳርቻው መንቀሳቀስ ሲጀምር በደስታ ስሜት እንደተንጫጩ ምንም ጥርጥር የለውም።—ሥራ 27:39, 40
ይሁን እንጂ በድንገት መርከቡ በአንድ የአሸዋ ቁልል ላይ ተተከለ። ይባስ ብሎም ኃይለኛ ማዕበል የመርከቡን ጀርባ ደጋግሞ በመምታቱ መርከቡ ይሰባበር ጀመር። ተሳፋሪዎቹ በሙሉ መርከቡን ጥለው መሄድ አለባቸው! (ሥራ 27:41) ሆኖም ይህ ችግር ይፈጥራል። ጳውሎስን ጨምሮ አብዛኞቹ ተሳፋሪዎች እስረኞች ናቸው። በሮማውያን ሕግ መሠረት ደግሞ በቁጥጥሩ ስር ያለውን እስረኛ እንዲያመልጥ ያደረገ ወታደር ለእስረኛው የታሰበውን ቅጣት መቀበል ይኖርበታል። ለምሳሌ ያህል አንድ ነፍሰ ገዳይ ቢያመልጥ ግዳጁን በአግባቡ ያልተወጣው ወታደር የራሱን ሕይወት መክፈል አለበት።
ወታደሮቹ እንዲህ ዓይነቱን መዘዝ በመፍራት ሁሉንም እስረኞች ለመግደል ወሰኑ። ሆኖም ለጳውሎስ ወዳጃዊ አመለካከት የነበረው የጦር መኮንን በጉዳዩ ጣልቃ ገባ። ዋና የሚችሉ ሁሉ ከመርከቡ በመዝለል በዋና ወደ የብስ እንዲሄዱ አዘዘ። ዋና የማይችሉት ደግሞ በሳንቃዎች ወይም በሌሎች የመርከቡ ስብርባሪዎች ላይ መንጠላጠል ነበረባቸው። በተሰበረችው መርከብ ላይ የነበሩት ተሳፋሪዎች አንድ በአንድ ወደ ባሕር ዳርቻው ወጡ። ጳውሎስ በተናገረው መሠረት አንድም ሰው አልሞተም!—ሥራ 27:42-44
በማልታ የተፈጸመ ተአምር
በድካም የተዝለፈለፉት መንገደኞች ማልታ በምትባል ደሴት ላይ ጥገኝነት አገኙ። ነዋሪዎቹ “ባዕድ ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝቦች” ወይም “ባርባራውያን” (በግሪክኛ ቫርቫሮስ) ናቸው።c ሆኖም የማልታ ሰዎች ጨካኞች አልነበሩም። ከዚህ ይልቅ የጳውሎስ የጉዞ ጓደኛ የሆነው ሉቃስ “የሚያስገርም ቸርነት አደረጉልን፤ ዝናብ ስለ ሆነም ስለ ብርዱም እሳት አንድደው ሁላችንን ተቀበሉን” ሲል ዘግቧል። ጳውሎስ ራሱ ከማልታ ነዋሪዎች ጋር ጭራሮ በመሰብሰብና እሳት ውስጥ በመጨመር ተባብሯል።—ሥራ 28:1-3 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ።
በድንገት አንዲት እባብ በጳውሎስ እጅ ላይ ተጠመጠመች! የደሴቲቱ ነዋሪዎች ጳውሎስ ነፍሰ ገዳይ ሳይሆን አይቀርም ብለው አሰቡ። አምላክ ኃጢአት የፈጸሙበት የሰውነት ክፍል ላይ ጉዳት በማድረስ ኃጢአተኞችን ይቀጣል የሚል አስተሳሰብ የነበራቸው ይመስላል። ሆኖም ጳውሎስ እባቡን ከእጁ አራግፎ እሳት ውስጥ ሲጨምር የአካባቢው ነዋሪዎች በጣም ተገረሙ! የዓይን ምሥክር የሆነው ሉቃስ እንደዘገበው “እነርሱም [ጳውሎስ] ሊያብጥ ወይም ወዲያው ሞቶ ሊወድቅ ነው ብለው ይጠባበቁት ነበር።” የደሴቲቱ ነዋሪዎች አስተሳሰባቸውን በመቀየር ጳውሎስ አምላክ ነው ሲሉ ተናገሩ።—ሥራ 28:3-6
ጳውሎስ ቀጣዮቹን ሦስት ወራት በማልታ ባሳለፈበት ወቅት በእንግድነት የተቀበለውን የደሴቲቱ አለቃ የፑፕልዮስን አባት እንዲሁም በበሽታ እየተሰቃዩ የነበሩ ሌሎች ሰዎችን ፈውሷል። ከዚህ በተጨማሪ ጳውሎስ የእውነትን ዘር በመዝራቱ እንግዳ ተቀባይ የሆኑት የማልታ ነዋሪዎች ከፍተኛ በረከት እንዲያገኙ አስችሏል።—ሥራ 28:7-11
ከዚህ የምናገኘው ትምህርት
ጳውሎስ አገልግሎቱን ሲያከናውን በርካታ ችግሮች ገጥመውታል። (2 ቆሮንቶስ 11:23-27) ከላይ በተጠቀሰው ዘገባ ላይ ጳውሎስ በምሥራቹ ምክንያት ታስሮ ነበር። ከዚያም ኃይለኛ ዓውሎ ነፋስና በዚያም ሳቢያ የመርከብ መሰበርን የመሳሰሉ ያልተጠበቁ ፈተናዎች አጋጥመውታል። ይህ ሁሉ ቢደርስበትም ጳውሎስ ቀናተኛ የምስራቹ ሰባኪ ለመሆን ካደረገው ቁርጥ ውሳኔ ፍንክች አላለም። ከደረሰበት ሁኔታ በመነሳት እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም መብዛትንና መጒደልን ተምሬአለሁ። ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ።”—ፊልጵስዩስ 4:12, 13
የኑሮ ችግሮች የእውነተኛው አምላክ ቀናተኛ አገልጋዮች ለመሆን ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ሊያዳክሙብን አይገባም! አንድ ያልተጠበቀ ፈተና ሲደርስብን ሸክማችንን በይሖዋ ላይ እንጥላለን። (መዝሙር 55:22) ከዚያም ይሖዋ ፈተናውን በጽናት መወጣት እንድንችል በምን መንገድ እንደሚረዳን ለማየት በትዕግሥት እንጠብቃለን። እስከዚያው ድረስ እርሱ ለእኛ እንደሚያስብ ሙሉ በሙሉ በመተማመን በታማኝነት ማገልገላችንን እንቀጥላለን። (1 ቆሮንቶስ 10:13፤ 1 ጴጥሮስ 5:7) የመጣው ቢመጣ የማያወላውል አቋም በመያዝ እንደ ጳውሎስ ሁሉ እኛም የሚደርሱብንን መከራዎች በድል መወጣት እንችላለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አንድ አክናድ አራት ክንድ ወይም 1.8 ሜትር ገደማ እንደሚጠጋ ይገመታል።
b ታንኳ፣ አንድ መርከብ በባሕር ዳርቻ መልሕቁን ሲጥል ወደ የብስ ለመውጣት የሚያገለግል ትንሽ ጀልባ ነው። በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው መርከበኞቹ እዚያው የሚቀሩትን መርከብ መንዳት የማይችሉ ሰዎች ጥለው የራሳቸውን ሕይወት ለማዳን ሙከራ ማድረጋቸው ነበር።
c በዊልፍሬድ ፈንክ የተዘጋጀው ወርድ ኦሪጂንስ እንዲህ ይላል:- “ግሪካውያን ከግሪክኛ ውጪ ያሉትን ቋንቋዎች ‘ቫርቫር’ ብለው በመጥራት ያላግጡ የነበረ ሲሆን እነዚህን ቋንቋዎች የሚናገርን ማንኛውንም ሰው ቫርቫሮስ ብለው ይጠሩት ነበር።