የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች-ታኅሣሥ 2019
ከታኅሣሥ 2-8
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ራእይ 7–9
“አንድም ሰው ሊቆጥራቸው የማይችል እጅግ ብዙ ሕዝብ የይሖዋን በረከት አገኙ”
(ራእይ 7:9) ከዚህ በኋላ አየሁ፤ እነሆም፣ ከሁሉም ብሔራት፣ ነገዶች፣ ሕዝቦችና ቋንቋዎች የተውጣጡ አንድም ሰው ሊቆጥራቸው የማይችል እጅግ ብዙ ሕዝብ ነጭ ልብስ ለብሰው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆመው ነበር፤ የዘንባባ ዝንጣፊዎችንም በእጆቻቸው ይዘው ነበር።
it-1 997 አን. 1
እጅግ ብዙ ሕዝብ
ይህ አንድ ጥያቄ ያስነሳል፦ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” የሚለው አገላለጽ መዳን አግኝተው በምድር ላይ የሚኖሩትን ሰዎች የሚያመለክት ከሆነ እነዚህ ሰዎች “በዙፋኑና በበጉ ፊት [ቆመዋል]” ሊባል የሚችለው እንዴት ነው? (ራእይ 7:9) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድ ግለሰብ ወይም ቡድን በአንድ አካል ፊት ‘ቆሟል’ ሲባል ግለሰቡ ወይም ቡድኑ በዚያ አካል ፊት ተቀባይነት ወይም ሞገስ አግኝቷል ማለት ሊሆን ይችላል። (መዝ 1:5፤ 5:5፤ ምሳሌ 22:29፤ ሉቃስ 1:19) እንዲያውም በራእይ ምዕራፍ 6 ላይ “የምድር ነገሥታት፣ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ የጦር አዛዦች፣ ሀብታሞች፣ ብርቱዎች፣ ባሪያዎች ሁሉና ነፃ ሰዎች ሁሉ . . . በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው ፊትና ከበጉ ቁጣ” ለመሰወር እንደሚሞክሩ ተገልጿል። “ምክንያቱም [በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውና በጉ] ቁጣቸውን የሚገልጹበት ታላቁ ቀን መጥቷል፤ ማንስ ሊቆም ይችላል?” (ራእይ 6:15-17፤ ከሉቃስ 21:36 ጋር አወዳድር።) በመሆኑም ‘የእጅግ ብዙ ሕዝብ’ አባላት፣ ከዚህ ቁጣ በመትረፍ እንዲሁም የአምላክንና የበጉን ሞገስ በማግኘት በዙፋኑና በበጉ ፊት ‘እንደሚቆሙ’ መረዳት ይቻላል።
(ራእይ 7:14) እኔም ወዲያውኑ “ጌታዬ፣ የምታውቀው አንተ ነህ” አልኩት። እሱም እንዲህ አለኝ፦ “እነዚህ ታላቁን መከራ አልፈው የመጡ ናቸው፤ ልብሳቸውንም በበጉ ደም አጥበው ነጭ አድርገውታል።
it-2 1127 አን. 4
መከራ
ኢየሩሳሌም ከጠፋች ከሦስት አሥርተ ዓመታት ገደማ በኋላ ሐዋርያው ዮሐንስ ከብሔራት፣ ከነገዶችና ከሕዝቦች የተውጣጣውን እጅግ ብዙ ሕዝብ አስመልክቶ “እነዚህ ታላቁን መከራ አልፈው የመጡ ናቸው” ተብሎ ተነግሮታል። (ራእይ 7:13, 14) እጅግ ብዙ ሕዝብ ‘ታላቁን መከራ አልፈው እንደመጡ’ መገለጹ እነዚህ ሰዎች ከታላቁ መከራ በሕይወት እንደሚተርፉ ያሳያል። በሥራ 7:9, 10 ላይ የሚገኘው “አምላክ [ከዮሴፍ] ጋር ነበር፤ ከመከራውም ሁሉ ታደገው [ወይም “አሳለፈው”]” የሚለው ተመሳሳይ አገላለጽም ይህን ሐቅ ያረጋግጣል። አምላክ ዮሴፍን ከመከራው እንደታደገው ወይም እንዳሳለፈው መገለጹ፣ ዮሴፍን እንዲጸና ብቻ ሳይሆን መከራውን ተቋቁሞ በሕይወት እንዲተርፍ ጭምር እንደረዳው ያሳያል።
(ራእይ 7:15-17) በአምላክ ዙፋን ፊት ያሉትም ለዚህ ነው፤ በቤተ መቅደሱም ቀንና ሌሊት ቅዱስ አገልግሎት እያቀረቡለት ነው፤ በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውም ድንኳኑን በላያቸው ይዘረጋል። 16 ከእንግዲህ ወዲህ አይራቡም እንዲሁም አይጠሙም፤ ፀሐይ አይመታቸውም፤ ሐሩሩም አያቃጥላቸውም፤ 17 ምክንያቱም በዙፋኑ መካከል ያለው በጉ እረኛቸው ይሆናል፤ ወደ ሕይወት ውኃ ምንጭም ይመራቸዋል። አምላክም እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል።”
it-1 996-997
እጅግ ብዙ ሕዝብ
ማንነታቸውን ማወቅ። በራእይ ምዕራፍ 7 ላይ ስለ ‘እጅግ ብዙ ሕዝብ’ የተሰጠው መግለጫና ከዚህ ዘገባ ጋር ግልጽ ተያያዥነት ያላቸው ሌሎች ዘገባዎች ‘የእጅግ ብዙ ሕዝብን’ ማንነት ለማወቅ የሚያስችል ፍንጭ ይሰጡናል። በራእይ 7:15-17 ላይ አምላክ ‘ድንኳኑን በላያቸው እንደሚዘረጋ፣’ ‘በጉ ወደ ሕይወት ውኃ ምንጭ እንደሚመራቸው’ እንዲሁም ‘አምላክ እንባን ሁሉ ከዓይናቸው እንደሚያብስ’ ተገልጿል። በራእይ 21:2-4 ላይም ተመሳሳይ አገላለጾችን እናገኛለን፤ ጥቅሱ ‘የአምላክ ድንኳን ከሰዎች ጋር እንደሆነ፣’ ‘እንባን ሁሉ ከዓይናቸው እንደሚያብስ’ እንዲሁም ‘ከእንግዲህ ወዲህ ሞት እንደማይኖር’ ይናገራል። ይህ ራእይ ‘አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ከዚያ እንደምትወርድ’ በተገለጸበት በሰማይ ያሉ ሰዎችን ሳይሆን በምድር ላይ ያሉ ሰዎችን የሚመለከት ነው።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ራእይ 7:1) ከዚህ በኋላ አራት መላእክት በአራቱ የምድር ማዕዘናት ቆመው አየሁ፤ እነሱም በምድር ወይም በባሕር ወይም በማንኛውም ዛፍ ላይ ምንም ነፋስ እንዳይነፍስ አራቱን የምድር ነፋሳት አጥብቀው ይዘው ነበር።
የአምላክ እስራኤሎችን ማተም
4 እነዚህ አራት መላእክት የጥፋቱን ፍርድ እስከተወሰነው ጊዜ ድረስ አግደው እንዲያቆዩ ይሖዋ የሚጠቀምባቸውን አራት የመላእክት ክፍሎች የሚወክሉ መሆናቸው ምንም አያጠራጥርም። መላእክቱ አግደውት የነበረውን የመለኮታዊ ቁጣ ነፋስ በአንድ ጊዜ ከሰሜን፣ ከደቡብ፣ ከምሥራቅና ከምዕራብ ሲለቁ በጣም ከፍተኛ የሆነ ጥፋት ይደርሳል። ይሖዋ በአራቱ ነፋሳት አማካኝነት የኤላም ሰዎችን በበታተነበት ጊዜ የደረሰውን ሁኔታ የሚመስል ቢሆንም ከዚያ በጣም የበለጠና የከፋ ይሆናል። (ኤርምያስ 49:36-38) ይሖዋ አሞናውያንን ካጠፋበት “አውሎ ነፋስ” የበለጠ ከፍተኛ ጥፋት የሚያስከትል ይሆናል። (አሞጽ 1:13-15) ይሖዋ ሉዓላዊነቱን ለዘላለም በሚያረጋግጥበት የቁጣ ቀን ጸንቶ ለመቆም የሚችል አንድም የሰይጣን ድርጅት ክፍል አይኖርም።—መዝሙር 83:15, 18፤ ኢሳይያስ 29:5, 6
(ራእይ 9:11) በእነሱ ላይ የተሾመ ንጉሥ አላቸው፤ እሱም የጥልቁ መልአክ ነው። በዕብራይስጥ ስሙ አባዶን ሲሆን በግሪክኛ ደግሞ ስሙ አጶልዮን ነው።
it-1 12
አባዶን
የጥልቁ መልአክ አባዶን ማን ነው?
ሆኖም በራእይ 9:11 ላይ “አባዶን” የሚለው ቃል “የጥልቁ መልአክ” ስም ተደርጎ ተሠርቶበታል። የዚህ ቃል አቻ የሆነው “አጶልዮን” የሚለው የግሪክኛ ስም “አጥፊ” የሚል ትርጉም አለው። በ19ኛው መቶ ዘመን አንዳንዶች ይህ ጥቅስ ንጉሠ ነገሥት ቨስፔዥያንን፣ መሐመድን አልፎ ተርፎም ናፖሊዮንን የሚያመለክት ትንቢታዊ ጥላነት ያለው ሐሳብ እንደሆነ ለማሳየት የሞከሩ ሲሆን ይህ መልአክ በአብዛኛው “ሰይጣናዊ” እንደሆነ ይታሰብ ነበር። ይሁን እንጂ በራእይ 20:1-3 ላይ “የጥልቁን ቁልፍ” የያዘው መልአክ ከሰማይ የተላከ የአምላክ ወኪል እንደሆነ እንዲሁም “ሰይጣናዊ” ከመሆን ይልቅ ሰይጣንን እንደሚያስረውና ወደ ጥልቁ እንደሚወረውረው እንደተገለጸ ልብ ማለት ያስፈልጋል። ዚ ኢንተርፕሬተርስ ባይብል ራእይ 9:11ን በተመለከተ የሚከተለውን ማብራሪያ ሰጥቷል፦ “አባዶን የሰይጣን መልአክ ሳይሆን የአምላክን ትእዛዝ ተቀብሎ የእሱን ፍርድ የሚያስፈጽም የአምላክ መልአክ ነው።”
ቀደም ሲል በተጠቀሱት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ጥቅሶች ላይ አቫዶን ከሲኦልና ከሞት ጋር ተያይዞ ተሠርቶበታል። በራእይ 1:18 ላይ ክርስቶስ ኢየሱስ “ለዘላለም እኖራለሁ፤ የሞትና የመቃብር ቁልፎችም አሉኝ” ብሎ እንደተናገረ ተገልጿል። ሉቃስ 8:31 ኢየሱስ በጥልቁ ላይ ሥልጣን እንዳለው ያሳያል። ዕብራውያን 2:14 ደግሞ ሰይጣንን ጨምሮ የአምላክን ጠላቶች የማጥፋት ሥልጣን እንዳለው ይገልጻል፤ ጥቅሱ ኢየሱስ “ለሞት የመዳረግ አቅም ያለውን ዲያብሎስን በሞቱ አማካኝነት እንዳልነበረ ያደርገው ዘንድ” ሥጋና ደም እንደሆነ ይናገራል። በራእይ 19:11-16 ላይ ኢየሱስ በአምላክ የተሾመ አጥፊ ወይም የሞት ፍርድ አስፈጻሚ እንደሆነ በማያሻማ መልኩ ተገልጿል።—አጶልዮን የሚለውን ተመልከት።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
ከታኅሣሥ 9-15
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ራእይ 10–12
“‘ሁለቱ ምሥክሮች’ ተገደሉ፤ ከዚያም እንደገና ሕያው ሆኑ”
(ራእይ 11:3) እኔም ሁለቱ ምሥክሮቼ ማቅ ለብሰው ለ1,260 ቀናት ትንቢት እንዲናገሩ አደርጋለሁ።”
የአንባቢያን ጥያቄዎች
በራእይ ምዕራፍ 11 ላይ የተጠቀሱት ሁለት ምሥክሮች እነማን ናቸው?
ራእይ 11:3 ለ1,260 ቀናት ትንቢት ስለሚናገሩ ሁለት ምሥክሮች ይገልጻል። ከዚያም ዘገባው፣ አውሬው ‘ድል እንደሚነሳቸውና እንደሚገድላቸው’ ይናገራል። ይሁን እንጂ እነዚህ ሁለት ምሥክሮች “ከሦስት ቀን ተኩል” በኋላ ወደ ሕልውና የሚመለሱ ሲሆን በዚህ ጊዜ እያዩዋቸው የነበሩት ሰዎች ሁሉ ይገረማሉ።—ራእይ 11:7, 11
ሁለቱ ምሥክሮች እነማን ናቸው? በዘገባው ውስጥ ያለው ዝርዝር መግለጫ ማንነታቸውን ለይተን እንድናውቅ ይረዳናል። አንደኛ እነዚህ ሁለት ምሥክሮች “በሁለቱ የወይራ ዛፎችና በሁለቱ መቅረዞች የተመሰሉ” እንደሆኑ እናነብባለን። (ራእይ 11:4) ይህም በዘካርያስ ትንቢት ውስጥ የተገለጸውን መቅረዝና ሁለት የወይራ ዛፎች ያስታውሰናል። እነዚህ የወይራ ዛፎች “በምድር ሁሉ ጌታ አጠገብ የቆሙ” እንደሆኑ የተገለጹትን ‘ሁለት ቅቡዓን’ ማለትም ገዢው ዘሩባቤልንና ሊቀ ካህናቱ ኢያሱን እንደሚያመለክቱ ተገልጿል። (ዘካ. 4:1-3, 14 የ1954 ትርጉም) ሁለተኛ፣ ሁለቱ ምሥክሮች ሙሴና ኤልያስ ከፈጸሟቸው ጋር የሚመሳሰሉ ምልክቶችን እንደሚፈጽሙ ተገልጿል።—ራእይ 11:5, 6ን ከዘኍልቍ 16:1-7, 28-35 እና ከ1 ነገሥት 17:1፤ 1 ነገሥት 18:41-45 ጋር አወዳድር።
በራእይና በዘካርያስ መጻሕፍት ላይ የሚገኙትን ዘገባዎች የሚያመሳስላቸው ምንድን ነው? በሁሉም ዘገባዎች ላይ፣ በከባድ የፈተና ወቅት አመራር የሚሰጡ የአምላክ ቅቡዕ አገልጋዮች ተጠቅሰዋል። በመሆኑም በራእይ ምዕራፍ 11 ፍጻሜ መሠረት የአምላክ መንግሥት በ1914 በሰማይ በተቋቋመበት ጊዜ አመራር የሚሰጡ ቅቡዓን ወንድሞች ለሦስት ዓመት ተኩል “ማቅ ለብሰው” ሰብከዋል።
እነዚህ ቅቡዓን ማቅ ለብሰው የሚሰብኩበት ጊዜ ሲያበቃ በአንጻራዊ ሁኔታ ለአጭር ጊዜ፣ ማለትም ለሦስት ቀን ተኩል እስር ቤት መግባታቸው በምሳሌያዊ ሁኔታ እንደተገደሉ ያሳያል። በአምላክ ሕዝብ ጠላቶች ዓይን ሲታይ የቅቡዓኑ ሥራ የሞተ ያህል ስለሆነ ለተቃዋሚዎች ታላቅ ደስታ አምጥቶላቸዋል።—ራእይ 11:8-10
ይሁን እንጂ ልክ በትንቢት በተነገረው መሠረት ሦስት ቀን ተኩሉ ሲያበቃ ሁለቱ ምሥክሮች ወደ ሕልውና ተመልሰዋል። እነዚህ ቅቡዓን ከእስር የተፈቱ ከመሆኑም በላይ ታማኝነታቸውን ለጠበቁት ቅቡዓን፣ አምላክ በጌታቸው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ልዩ ሹመት ሰጥቷቸዋል። በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት የአምላክን ሕዝቦች መንፈሳዊ ፍላጎት እንዲያሟሉ ሲባል ከእነዚህ ቅቡዓን መካከል የተወሰኑት በ1919 “ታማኝና ልባም ባሪያ” ሆነው ተሹመዋል።—ማቴ. 24:45-47፤ ራእይ 11:11, 12
የሚገርመው ነገር ራእይ 11:1, 2 እነዚህን ክስተቶች መንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ከሚለካበት ወይም ከሚመረመርበት ጊዜ ጋር አያይዞ ይጠቅሳቸዋል። ሚልክያስ ምዕራፍ 3 መንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ተመሳሳይ ምርመራ እንደሚካሄድበትና ከዚያም ቤተ መቅደሱ እንደሚነጻ ይገልጻል። (ሚል. 3:1-4) ይህ የምርመራና የማንጻት ሥራ ምን ያህል ጊዜ ወስዷል? ከ1914 ጀምሮ እስከ 1919 መጀመሪያ ድረስ የዘለቀ ነበር። ይህ ወቅት 1,260 ቀናትን (42 ወራት) እና በራእይ ምዕራፍ 11 ላይ የተጠቀሰውን ምሳሌያዊ ሦስት ቀን ተኩል ያጠቃልላል።
ይሖዋ ሕዝቡን አጥርቶ ለመልካም ሥራ የሚቀና ልዩ ሕዝብ ለማድረግ ይህን መንፈሳዊ የማንጻት ሥራ በማዘጋጀቱ ምንኛ ደስተኞች ነን! (ቲቶ 2:14) በተጨማሪም በዚያ የፈተና ወቅት አመራር በመስጠት ምሳሌያዊ ሁለት ምሥክሮች በመሆን ያገለገሉ ታማኝ ቅቡዓን የተዉትን ምሳሌ እናደንቃለን።
(ራእይ 11:7) የምሥክርነት ሥራቸውን ባጠናቀቁ ጊዜ፣ ከጥልቁ የሚወጣው አውሬ ውጊያ ይከፍትባቸዋል፤ ድል ይነሳቸዋል፤ እንዲሁም ይገድላቸዋል።
(ራእይ 11:11) ከሦስት ቀን ተኩል በኋላ ከአምላክ የመጣ የሕይወት መንፈስ ገባባቸው፤ በእግሮቻቸውም ቆሙ፤ ያዩአቸውም ሰዎች በታላቅ ፍርሃት ተዋጡ።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ራእይ 10:9, 10) እኔም ወደ መልአኩ ሄጄ ትንሿን ጥቅልል እንዲሰጠኝ ጠየቅኩት። እሱም “ውሰድና ብላት፤ ሆድህን መራራ ታደርገዋለች፤ አፍህ ላይ ግን እንደ ማር ትጣፍጣለች” አለኝ። 10 ትንሿን ጥቅልል ከመልአኩ እጅ ወስጄ በላኋት፤ በአፌም ውስጥ እንደ ማር ጣፈጠች፤ ከበላኋት በኋላ ግን ሆዴ መራራ ሆነ።
it-2 880-881
ጥቅልል
በምሳሌያዊ መንገድ ሲሠራበት። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ጥቅልል” የሚለው ቃል ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ የተሠራባቸው ብዙ ቦታዎች አሉ። ሕዝቅኤልና ዘካርያስ በሁለቱም በኩል የተጻፈባቸው ጥቅልሎች በራእይ ተመልክተዋል። በአብዛኛው በጥቅልል ላይ የሚጻፈው በአንድ በኩል ብቻ ከመሆኑ አንጻር ጥቅልሎቹ በሁለቱም በኩል የተጻፈባቸው መሆኑ የያዙት የፍርድ መልእክት ከባድና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ እንደሆነ ይጠቁማል። (ሕዝ 2:9–3:3፤ ዘካ 5:1-4) ዮሐንስ በተመለከተው ራእይ ላይ በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው፣ በሰባት ማኅተሞች የታሸገ ጥቅልል በቀኝ እጁ ይዞ ነበር፤ ጥቅልሉ በሰባት ማኅተሞች የታሸገው የአምላክ በግ ጥቅልሉን ከመክፈቱ በፊት ማንም እንዳያነበው ለመከልከል ነው። (ራእይ 5:1, 12፤ 6:1, 12-14) በኋላም በራእዩ ላይ ዮሐንስ ራሱ ጥቅልል የተሰጠው ሲሆን ጥቅልሉን እንዲበላም ታዟል። ጥቅልሉን ሲበላው አፉ ላይ ቢጣፍጠውም ሆዱን መራራ አድርጎታል። ጥቅልሉ የታሸገ ሳይሆን የተከፈተ መሆኑ መልእክቱን ሌሎች እንዲረዱት እንደተፈለገ ያሳያል። ዮሐንስ በጥቅልሉ ላይ ያለውን መልእክት መረዳቱ ጥቅልሉ ‘ጣፋጭ’ እንዲሆንለት ቢያደርግም እንዲያውጅ የተነገረው ትንቢት ይዘት ግን ጥቅልሉ መራራ እንዲሆንበት አድርጓል። (ራእይ 10:1-11) ሕዝቅኤልም ከተሰጠው “የሙሾ፣ የሐዘንና የዋይታ ቃላት [የተጻፉበት]” ጥቅልል ጋር በተያያዘ ተመሳሳይ ነገር አጋጥሞታል።—ሕዝ 2:10
(ራእይ 12:1-5) ከዚያም በሰማይ ታላቅ ምልክት ታየ፦ አንዲት ሴት ፀሐይን ተጎናጽፋ ነበር፤ ጨረቃም ከእግሯ ሥር ነበረች፤ በራሷም ላይ 12 ከዋክብት ያሉት አክሊል ነበር፤ 2 እሷም ነፍሰ ጡር ነበረች። ልትወልድ ስትል ምጥ ይዟት በጭንቅ ትጮኽ ነበር። 3 ሌላ ምልክት በሰማይ ታየ። እነሆ፣ ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶች ያሉት፣ በራሶቹም ላይ ሰባት ዘውዶች የደፋ፣ ደማቅ ቀይ ቀለም ያለው ታላቅ ዘንዶ ታየ፤ 4 ጅራቱም የሰማይን ከዋክብት አንድ ሦስተኛ ጎትቶ ወደ ምድር ወረወረ። ዘንዶውም በምትወልድበት ጊዜ ልጇን ለመዋጥ ፈልጎ ልትወልድ በተቃረበችው ሴት ፊት ቆሞ ይጠብቅ ነበር። 5 እሷም ብሔራትን ሁሉ በብረት በትር የሚገዛውን ልጅ አዎ፣ ወንድ ልጅ ወለደች። ልጇም ወደ አምላክና ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ።
it-2 187 አን. 7-9
ምጥ
ሐዋርያው ዮሐንስ፣ በሰማይ ያለች አንዲት ሴት “ልትወልድ ስትል ምጥ ይዟት በጭንቅ [ስትጮኽ]” በራእይ ተመልክቷል። ይህች ሴት ‘ብሔራትን ሁሉ በብረት በትር የሚገዛ ወንድ ልጅ’ ወልዳለች። ዘንዶው ልጁን ለመዋጥ የሞከረ ቢሆንም ልጁ ግን ‘ወደ አምላክና ወደ ዙፋኑ ተነጥቋል።’ (ራእይ 12:1, 2, 4-6) ልጁ በአምላክ የተነጠቀ መሆኑ አምላክ ልጁን እንደ ራሱ ልጅ አድርጎ እንደተቀበለው ያሳያል፤ በጥንት ዘመንም ልጅ ሲወለድ ልጁን አባትየው ፊት በማቅረብ አባትየው ልጁን እንደ ራሱ ልጅ አድርጎ እንዲቀበለው ማድረግ የተለመደ ነበር። (መውለድ የሚለውን ተመልከት።) የልጁ አባት አምላክ ከሆነ “ሴቲቱ” ደግሞ የአምላክ “ሚስት” ማለትም የክርስቶስና የመንፈሳዊ ወንድሞቹ ‘እናት’ የሆነችው “ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም” ናት ማለት ነው።—ገላ 4:26፤ ዕብ 2:11, 12, 17
በሰማይ ያለችው የአምላክ “ሴት” ፍጹም ስለሆነች በምትወልድበት ጊዜ ቃል በቃል ሥቃይ እንደማይኖራት የታወቀ ነው። በመሆኑም “ሴቲቱ” ምጥ እንደያዛት መገለጹ በቅርቡ ልትወልድ መሆኑን እንደተገነዘበች የሚያሳይ ምሳሌያዊ አገላለጽ ነው።—ራእይ 12:2
ለመሆኑ ይህ “ወንድ ልጅ” ማን ነው? ይህ ልጅ “ብሔራትን ሁሉ በብረት በትር [እንደሚገዛ]” ተገልጿል። በመዝሙር 2:6-9 ላይ የአምላክ መሲሐዊ ንጉሥ እንዲህ እንደሚያደርግ ትንቢት ተነግሮለታል። ሆኖም ዮሐንስ ይህን ራእይ የተመለከተው ክርስቶስ ምድር ላይ ከተወለደ፣ ከሞተና ትንሣኤ ካገኘ ከረጅም ጊዜ በኋላ ነው። በመሆኑም ራእዩ ‘በአምላክ ቀኝ በተቀመጠውና ከዚያን ጊዜ አንስቶ ጠላቶቹ የእግሩ መርገጫ እስኪደረጉ ድረስ በመጠባበቅ ላይ በሚገኘው’ በኢየሱስ ክርስቶስ እጅ ያለው መሲሐዊ መንግሥት መወለዱን የሚያመለክት ይመስላል።—ዕብ 10:12, 13፤ መዝ 110:1፤ ራእይ 12:10
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
ከታኅሣሥ 16-22
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ራእይ 13–16
“አስፈሪ የሆኑትን አውሬዎች አትፍሯቸው”
(ራእይ 13:1, 2) እሱም በባሕር አሸዋ ላይ ቆመ። እኔም አሥር ቀንዶችና ሰባት ራሶች ያሉት አንድ አውሬ ከባሕር ሲወጣ አየሁ፤ በቀንዶቹም ላይ አሥር ዘውዶች የነበሩት ሲሆን በራሶቹ ላይ አምላክን የሚሰድቡ ስሞች ነበሩት። 2 ያየሁትም አውሬ ነብር ይመስል ነበር፤ እግሮቹ ግን የድብ እግር፣ አፉ ደግሞ የአንበሳ አፍ ይመስል ነበር። ዘንዶውም ለአውሬው ኃይልና ዙፋን እንዲሁም ታላቅ ሥልጣን ሰጠው።
ይሖዋ ‘ሚስጥር ገላጭ ነው’
6 ከሞት የተነሳው ኢየሱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ አስደናቂ ራእዮችን ለሐዋርያው ዮሐንስ አሳይቶታል። (ራእይ 1:1) በአንደኛው ራእይ ላይ፣ በዘንዶ የተመሰለው ዲያብሎስ በባሕር አሸዋ ላይ እንደቆመ ዮሐንስ ተመልክቶ ነበር። (ራእይ 13:1, 2ን አንብብ።) በተጨማሪም ዮሐንስ፣ ሰባት ራሶች ያሉት አንድ አውሬ ከባሕር ሲወጣና ከዲያብሎስ ከፍተኛ ሥልጣን ሲቀበል ተመልክቷል። በኋላም ዮሐንስ መልኩ ቀይ የሆነና ልክ እንደ መጀመሪያው አውሬ ሰባት ራሶች ያሉት ሌላ አውሬ የተመለከተ ሲሆን ይህ ቀይ አውሬ በራእይ 13:1 ላይ ያለው አውሬ ምስል ነው። የቀዩ አውሬ ሰባት ራሶች ‘ሰባት ነገሥታትን’ ወይም መንግሥታትን እንደሚያመለክቱ አንድ መልአክ ለዮሐንስ ነግሮታል። (ራእይ 13:14, 15፤ 17:3, 9, 10) ዮሐንስ ራእዩን በጻፈበት ወቅት አምስቱ ወድቀው ነበር፤ አንዱ በሥልጣን ላይ የነበረ ሲሆን “ሌላው ደግሞ ገና አልመጣም።” ለመሆኑ እነዚህ የዓለም ኃያላን መንግሥታት እነማን ናቸው? እስቲ በዚህ ራእይ ውስጥ የተጠቀሱትን ራሶች አንድ በአንድ እንመርምር። ከዚህም ሌላ ስለ አብዛኞቹ መንግሥታት ተጨማሪ ማብራሪያ ከዳንኤል መጽሐፍ እንመለከታለን። ዳንኤል ይህን ዝርዝር ሐሳብ የጻፈው እነዚህ መንግሥታት ከመነሳታቸው ከበርካታ መቶ ዓመታት በፊት ነው።
(ራእይ 13:11) ከዚያም ሌላ አውሬ ከምድር ሲወጣ አየሁ፤ እሱም እንደ በግ ሁለት ቀንዶች ነበሩት፤ ሆኖም እንደ ዘንዶ መናገር ጀመረ።
(ራእይ 13:15) እንዲሁም ለአውሬው ምስል እስትንፋስ እንዲሰጠው ተፈቀደለት፤ ይህም የሆነው የአውሬው ምስል መናገር እንዲችልና የአውሬውን ምስል የማያመልኩትን ሁሉ እንዲያስገድል ነው።
ከሁለት አስፈሪ አራዊት ጋር መታገል
26 ታዲያ የትኛው የዓለም ኃያል መንግሥት ሊሆን ይችላል? የአንግሎ አሜሪካን የዓለም ኃያል መንግሥት ነው። በሌላ አነጋገር የመጀመሪያው አውሬ ሰባተኛ ራስ ሲሆን እዚህ ላይ ልዩ ሚና ይኖረዋል። በራእዩ ውስጥ የተለየ አውሬ ሆኖ ተነጥሎ መታየቱ በዓለም መድረክ በተናጠል የሚፈጽማቸውን ነገሮች በግልጽ እንድንመለከት ያስችለናል። ይህ ምሳሌያዊ ባለ ሁለት ቀንድ አውሬ አብረው ከሚኖሩ፣ ነጻና የፖለቲካ ኃይላቸውን ለማስተባበር ፈቃደኛ በሆኑ ሁለት መንግሥታት የተቋቋመ ነው። ሁለቱ ቀንዶቹ “የበግ ቀንዶች የሚመስሉ” መሆናቸው ሰዎችን የማይጋፋና ልዝብ፣ ዓለም በሙሉ በምሳሌነት የሚመለከተው የሰለጠነ መንግሥት እንደሆነ አድርጐ ራሱን ማቅረቡን ያመለክታል። ይሁን እንጂ የአገዛዝ ሥርዓቱ ተቀባይነት ባላገኘባቸው ሥፍራዎች በኃይል፣ በዛቻና በተለያየ ተጽእኖ ስለሚጠቀም “እንደ ዘንዶ” ይናገራል። ሰዎች ሁሉ በአምላክ በግ ለሚተዳደረው የአምላክ መንግሥት እንዲገዙ አይገፋፋም። እንዲያውም የታላቁን ዘንዶ የሰይጣንን ዓላማና ፍላጎት ያስፈጽማል። ብሔራዊ ጥላቻንና መከፋፈልን ያስፋፋል። ይህ ሁሉ ድርጊት የመጀመሪያውን አውሬ አምልኮ የሚያስፋፋ ነው።
ከሁለት አስፈሪ አራዊት ጋር መታገል
30 ከታሪክ ሂደት እንደምንረዳው ይህ ምስል በብሪታንያና በዩናይትድ ስቴትስ አሳሳቢነት፣ ደጋፊነትና ጠባቂነት የተቋቋመው የቀድሞ ስሙ የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር የተባለው ድርጅት ነው። ይህ ምስል በራእይ ምዕራፍ 17 ላይ የራሱ ነፃ ሕልውና ያለው ሕያውና የሚተነፍስ ቀይ አውሬ ሆኖ በሌላ ምሳሌ ይቀርባል። ይህ ዓለም አቀፍ አካል ለሰው ልጅ ሰላምና ደህንነት ለማምጣት የምችለው እኔ ብቻ ነኝ ብሎ በጉራ ስለሚናገር ከመጠን በላይ “ይናገራል።” እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ለአባል ብሔራት የመነታረኪያና የመሰዳደቢያ መድረክ ከመሆን አላለፈም። ለሥልጣኑ በማይገዛ በማንኛውም ሕዝብ ወይም ብሔር ላይ የውግዘት ቃል ያስተላልፋል። እንዲያውም ይህ የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር የእርሱን ርዕዮተ ዓለም ሳይቀበሉ የቀሩ ብሔራትን ከአባልነት አስወግዶአል። ታላቁ መከራ በሚጀምርበት ጊዜ ደግሞ የዚህ የአውሬ ምስል ጦረኛ “ቀንዶች” የአጥፊነት ሥራቸውን ይፈጽማሉ።—ራእይ 7:14፤ 17:8, 16
31 ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጀምሮ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በመሆን የተከሰተው የአውሬ ምስል ቃል በቃል ሰዎችን ገድሎአል። ለምሳሌ ያህል በ1950 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጦር ኃይል በደቡብ ኮሪያና በሰሜን ኮሪያ መካከል በተደረገው ጦርነት ዘምቶ ነበር። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጦር ከደቡብ ኮሪያውያን ጋር ሆኖ በግምት 1, 420, 000 ሰሜን ኮሪያውያንንና ቻይናውያንን ገድሎአል። በተመሳሳይም ከ1960 እስከ 1964 በነበሩት ዓመታት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጦር ሠራዊት በኮንጎ ውስጥ (በአሁኑ ጊዜ ዛይር) ዘመቻ አካሂዶ ነበር። ከዚህም በላይ ፓፓ ፖል ስድስተኛንና ጆን ፖል ዳግማዊን ጨምሮ የዓለም መሪዎች ይህ የአውሬ ምስል ከሁሉ የተሻለውና የመጨረሻው የሰው ልጅ የሰላም ተስፋ እንደሆነ አበክረው መናገራቸውን ቀጥለዋል። የሰው ልጅ ይህን ድርጅት ማገልገሉን ከተወ የሰው ዘር ራሱን በራሱ ያጠፋል ይላሉ። ይህን በማለታቸውም በምሳሌያዊ ሁኔታ ከምስሉ ጋር ለመተባበርና እርሱን ለማምለክ እምቢተኛ የሆኑትን ሰዎች አስገድለዋል።—ዘዳግም 5:8, 9
(ራእይ 13:16, 17) ሰዎች ሁሉ ማለትም ታናናሾችና ታላላቆች፣ ሀብታሞችና ድሆች እንዲሁም ነፃ ሰዎችና ባሪያዎች በቀኝ እጃቸው ወይም በግንባራቸው ላይ ምልክት እንዲደረግባቸው አስገደደ፤ 17 ይህም የሆነው ምልክቱ ይኸውም የአውሬው ስም ወይም የስሙ ቁጥር ካለው ሰው በስተቀር ማንም መግዛት ወይም መሸጥ እንዳይችል ነው።
የራእይ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች—ክፍል 2
13:16, 17፦ እንደ “መግዛት ወይም መሸጥ” ያሉ ዕለታዊ እንቅስቃሴዎችን በምናከናውንበት ጊዜ ችግሮች ሊያጋጥሙን ቢችሉም አውሬው በሚያሳድርብን ተጽዕኖ ተሸንፈን ሕይወታችንን እንዲቆጣጠረው መፍቀድ አይኖርብንም። ‘የአውሬው ምልክት በእጃችን ወይም በግምባራችን ላይ እንዲደረግ’ ፈቃደኛ መሆን አውሬው ተግባራችንንም ሆነ አስተሳሰባችንን እንዲቆጣጠረው የመፍቀድ ያህል ነው።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ራእይ 16:13, 14) እኔም እንቁራሪት የሚመስሉ በመንፈስ የተነገሩ ሦስት ርኩሳን ቃላት ከዘንዶው አፍና ከአውሬው አፍ እንዲሁም ከሐሰተኛው ነቢይ አፍ ሲወጡ አየሁ። 14 እንዲያውም እነዚህ በአጋንንት መንፈስ የተነገሩ ቃላት ናቸው፤ ተአምራዊ ምልክቶችም ይፈጽማሉ፤ እነሱም ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ ታላቅ ቀን ወደሚካሄደው ጦርነት ሊሰበስቧቸው ወደ ዓለም ነገሥታት ሁሉ ይወጣሉ።
የራእይ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች—ክፍል 2
16:13-16፦ “በመንፈስ የተነገሩ . . . ርኩሳን ቃላት” የሚያመለክቱት ዲያብሎሳዊ ፕሮፖጋንዳዎችን ሲሆን እንዲህ ያሉት ፕሮፖጋንዳዎች የሚነዙበት ዓላማ የምድር ነገሥታት፣ የአምላክን ቁጣ የያዙት የሰባቱ ሳህኖች መፍሰስ ተጽዕኖ ሳያሳድርባቸው ይሖዋን ለመቃወም እንዲነሳሱ ማድረግ ነው።—ማቴ. 24:42, 44
(ራእይ 16:21) ከዚያም ታላቅ የበረዶ ድንጋይ ከሰማይ በሰዎች ላይ ወረደ፤ እያንዳንዱ የበረዶ ድንጋይ አንድ ታላንት ይመዝን ነበር፤ መቅሰፍቱ እጅግ ታላቅ ስለነበር ሰዎቹ ከበረዶው መቅሰፍት የተነሳ አምላክን ተሳደቡ።
‘መዳናችሁ እየቀረበ ነው’!
9 ይህ ጊዜ “የመንግሥቱ ምሥራች” የሚሰበክበት አይደለም። በዚህ ወቅት ምሥራቹን የምንሰብክበት ጊዜ አልፏል። “መጨረሻው” በቅርቡ ይመጣል! (ማቴ. 24:14) የአምላክ ሕዝቦች ኃይለኛ የሆነ የፍርድ መልእክት እንደሚያውጁ ምንም ጥርጥር የለውም። ይህ መልእክት የሰይጣን ክፉ ዓለም ሙሉ በሙሉ ሊጠፋ እንደሆነ ማወጅን ይጨምር ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን መልእክት ከበረዶ ድንጋይ ጋር በማመሳሰል እንዲህ ብሏል፦ “ከዚያም ታላቅ የበረዶ ድንጋይ ከሰማይ በሰዎች ላይ ወረደ፤ እያንዳንዱ የበረዶ ድንጋይ አንድ ታላንት ይመዝን ነበር፤ መቅሰፍቱ እጅግ ታላቅ ስለነበር ሰዎቹ ከበረዶው መቅሰፍት የተነሳ አምላክን ተሳደቡ።”—ራእይ 16:21
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
ከታኅሣሥ 23-29
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ራእይ 17–19
“ጦርነቶችን ሁሉ የሚያስወግደው የአምላክ ጦርነት”
(ራእይ 19:11) እኔም ሰማይ ተከፍቶ አየሁ፤ እነሆም፣ ነጭ ፈረስ ነበር። በእሱም ላይ የተቀመጠው “ታማኝና እውነተኛ” ተብሎ ይጠራል፤ እሱም በጽድቅ ይፈርዳል እንዲሁም ይዋጋል።
(ራእይ 19:14-16) በተጨማሪም በሰማይ ያሉት ሠራዊቶች በነጭ ፈረሶች ተቀምጠው ይከተሉት ነበር፤ እነሱም ነጭና ንጹሕ የሆነ ጥሩ በፍታ ለብሰው ነበር። 15 እሱም ብሔራትን ይመታበት ዘንድ ከአፉ ረጅም ስለታም ሰይፍ ይወጣል፤ እንደ እረኛም በብረት በትር ይገዛቸዋል። በተጨማሪም ሁሉን ቻይ የሆነውን የአምላክን የመዓቱን የቁጣ ወይን ጠጅ መጭመቂያ ይረግጣል። 16 በመደረቢያው አዎ፣ በጭኑ ላይ “የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ” የሚል ስም ተጽፏል።
አርማጌዶን—ጦርነቶችን ሁሉ የሚያስቀረው የአምላክ ጦርነት
ክፉ ሰዎች በሥልጣን ላይ እስካሉ ድረስ ጻድቃን ሰላምና ደኅንነት ሊኖራቸው አይችልም። (ምሳሌ 29:2፤ መክብብ 8:9) እንደ እውነቱ ከሆነ ምግባረ ብልሹነትንና ክፋትን፣ ድርጊቱን ከሚፈጽሙት ሰዎች ለይተን ማየት አንችልም። በመሆኑም ዘላቂ ሰላምና ፍትሕ ሊገኝ የሚችለው ክፉ ሰዎች ከተወገዱ ብቻ ነው። ሰሎሞን “ክፉ ሰው ለጻድቅ . . . ወጆ ይሆናል” በማለት ጽፏል።—ምሳሌ 21:18
ዳኛው አምላክ እንደመሆኑ መጠን በክፉዎች ላይ የሚወሰደው እያንዳንዱ እርምጃ ጽድቅ የሚንጸባረቅበት እንደሚሆን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። አብርሃም “የምድር ሁሉ ዳኛ በቅን አይፈርድምን?” ሲል የጠየቀ ሲሆን ይሖዋ ምንጊዜም ትክክለኛውን ነገር እንደሚያደርግ ተገንዝቧል! (ዘፍጥረት 18:25) ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ክፉዎችን በማጥፋት እንደማይደሰትና ይህን እርምጃ እንደ መጨረሻ አማራጭ እንደሚጠቀምበት ይገልጻል።—ሕዝቅኤል 18:32፤ 2 ጴጥሮስ 3:9
it-1 1146 አን. 1
ፈረስ
ሐዋርያው ዮሐንስ፣ ክብር የተጎናጸፈው ኢየሱስ ክርስቶስ ነጭ ፈረስ ሲጋልብ በራእይ ተመልክቷል፤ ብዙ ሠራዊቶችም በነጭ ፈረሶች ላይ ተቀምጠው ይከተሉት ነበር። ዮሐንስ የተመለከተው ይህ ምሳሌያዊ ራእይ፣ ክርስቶስ አምላኩንና አባቱን ይሖዋን ወክሎ በአምላክ ጠላቶች ላይ የሚያውጀው ጦርነት የጽድቅና የፍትሕ ጦርነት እንደሆነ ያሳያል። (ራእይ 19:11, 14) በሌላ ምዕራፍ ላይ፣ ክርስቶስ ንጉሥ ሆኖ ከተሾመ በኋላ የወሰደው እርምጃና ከዚያ በኋላ የተከሰቱት አስከፊ ሁኔታዎች በሌሎች ፈረሶችና ጋላቢዎች ተወክለዋል።—ራእይ 6:2-8
(ራእይ 19:19, 20) ከዚህ በኋላ አውሬው፣ የምድር ነገሥታትና ሠራዊታቸው በፈረሱ ላይ ከተቀመጠውና ከሠራዊቱ ጋር ለመዋጋት ተሰብስበው አየሁ። 20 አውሬውም ተያዘ፤ በፊቱ ተአምራዊ ምልክቶች የፈጸመው ሐሰተኛው ነቢይም ከእሱ ጋር ተያዘ፤ ይህ ነቢይ በእነዚህ ምልክቶች አማካኝነት፣ የአውሬውን ምስል የተቀበሉትንና ለምስሉ የሰገዱትን አስቷል። ሁለቱም በሕይወት እንዳሉ በድኝ ወደሚነደው የእሳት ሐይቅ ተወረወሩ።
ተዋጊው ንጉሥ አርማጌዶን ላይ ድል ይቀዳጃል
24 የሰይጣንን ፖለቲካዊ ድርጅት የሚያመለክተው ከባሕር የወጣ ባለ ሰባት ራስና ባለ አሥር ቀንድ አውሬ ዳግመኛ ሊታይ በማይችልበት ሁኔታ ይጠፋል። ከእርሱም ጋር ሐሰተኛው ነቢይ ማለትም ሰባተኛው የዓለም ኃያል መንግሥት አብሮት ይጠፋል። (ራእይ 13:1, 11-13፤ 16:13) “በሕይወት ሳሉ” ወይም አንድ ሆነው የአምላክን ሕዝቦች ተቃውመው በመንቀሳቀስ ላይ እንዳሉ “ወደ እሳት ባሕር” ይጣላሉ። ይሁን እንጂ ይህ ቃል በቃል የእሳት ባሕር ነውን? አውሬውም ሆነ ሐሰተኛው ነቢይ ቃል በቃል አራዊት እንዳልሆኑ ሁሉ የእሳቱም ባሕር ቃል በቃል የእሳት ባሕር አይደለም። ሙሉ በሙሉ ለመጨረሻ ጊዜ መጥፋትን፣ መመለሻ የሌለበትን ሥፍራ ያመለክታል። በኋላም ሞትና ሔድስ እንዲሁም ዲያብሎስ የሚወረወሩት ወደዚህ ሥፍራ ነው። (ራእይ 20:10, 14) ክፉዎች የዘላለም ሥቃይ የሚቀበሉበት ገሃነመ እሳት እንዳልሆነ የታወቀ ነው። ምክንያቱም እንዲህ ያለ ሥፍራ መኖሩን እንኳን ይሖዋ ይጸየፈዋል።—ኤርምያስ 19:5፤ 32:35፤ 1 ዮሐንስ 4:8, 16
(ራእይ 19:21) የቀሩት ግን በፈረሱ ላይ ከተቀመጠው አፍ በወጣው ረጅም ሰይፍ ተገደሉ። ወፎችም ሁሉ ሥጋቸውን በልተው ጠገቡ።
ተዋጊው ንጉሥ አርማጌዶን ላይ ድል ይቀዳጃል
25 የመንግሥት ክፍል ባይሆኑም ይህን ብልሹ የሰው ልጆች ዓለም የሙጥኝ ያሉ ሁሉ “በፈረስ ላይ ከተቀመጠው ከአፉ በሚወጣው ሰይፍ ተገደሉ።” ኢየሱስ ሞት የሚገባቸው እንደሆኑ አድርጎ ይፈርድባቸዋል። እነዚህ ሰዎች ወደ እሳት ባሕር እንደሚጣሉ አለመነገሩ ትንሣኤ ይኖራቸዋል ብለን እንድናስብ ምክንያት ይሆነናልን? በዚያ ጊዜ በይሖዋ ፈራጅ የሚገደሉት ትንሣኤ እንደሚኖራቸው የተገለጸበት አንድም ቦታ አናገኝም። ኢየሱስ ራሱ እንደተናገረው “በጎች” ያልሆኑት ሁሉ ‘ለዲያብሎስና ለመላእክቱ ወደተዘጋጀው የዘላለም እሳት’ ይጣላሉ። ይህም ማለት ወደ ‘ዘላለም ጥፋት’ ይጣላሉ ማለት ነው። (ማቴዎስ 25:33, 41, 46) ይህ እርምጃ ‘አምላክ የለሽ ሰዎች የሚጠፉበት የፍርድ ቀን’ የመጨረሻ ክንውን ይሆናል።—2 ጴጥሮስ 3:7፤ ናሆም 1:2, 7-9፤ ሚልክያስ 4:1
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ራእይ 17:8) ያየኸው አውሬ ከዚህ በፊት ነበር፤ አሁን ግን የለም፤ ይሁንና በቅርቡ ከጥልቁ ይወጣል፤ ወደ ጥፋትም ይሄዳል። ዓለም ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ጥቅልል ላይ ያልተጻፈው የምድር ነዋሪዎች አውሬው ከዚህ በፊት እንደነበረ፣ አሁን ግን እንደሌለና ወደፊት እንደሚኖር ሲያዩ በአድናቆት ይዋጣሉ።
አንድ አስገራሚ ምሥጢር ተፈታ
5 “ያየኸው አውሬ አስቀድሞ ነበረ።” አዎ፣ ይህ አውሬ ከጥር 10, 1920 ጀምሮ 63 ብሔራትን አሰባስቦ የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር በሚል ስያሜ ሲንቀሳቀስ ቆይቶ ነበር። ይሁን እንጂ ጃፓን፣ ጀርመንና ኢጣልያ ከማኅበሩ ሲወጡ የቀድሞዋ ሶቪዬት ኅብረትም ከማኅበሩ እንድትወጣ ተደረገ። በመስከረም ወር 1939 የጀርመኑ የናዚ አምባገነን መንግሥት ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ቀሰቀሰ። የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር የዓለምን ሰላም ለማስጠበቅ ስላልቻለ ምንም ሊንቀሳቀስ ወደማይችልበት ጥልቅ ወረደ። በ1942 ነበር ብቻ የሚባልለት ድርጅት ሆነ። ይሖዋ የዚህን ራእይ ሙሉ ትርጉም ለሕዝቦቹ ያብራራው በዚህ ወሳኝ ጊዜ ነበር እንጂ ከዚህ በፊት ወይም ከዚህ በኋላ አልነበረም። ወንድም ኤን ኤች ኖር በአዲሲቱ ዓለም ቲኦክራቲካዊ ስብሰባ ላይ በትንቢቱ መሠረት አውሬው “አሁን የለም” ለማለት ችሎ ነበር። ከዚያም በኋላ “ታዲያ ማኅበሩ ጥልቁ ውስጥ እንደወደቀ ይቀራልን?” ሲል ጠየቀ። ለጥያቄው መልስ ሲሰጥ ራእይ 17:8ን ጠቅሶ “የዓለማዊ ብሔራት ማኅበር እንደገና ያንሰራራል” አለ። ልክ እንደተናገረው ስለተፈጸመ የይሖዋ ትንቢታዊ ቃል እውነት መሆኑ ተረጋግጦአል።
ከጥልቁ መውጣት
6 ቀዩ አውሬ በእርግጥም ከጥልቁ ወጣ። ሰኔ 26, 1945 በሳንፍራንሲስኮ ዩ ኤስ ኤ 50 ብሔራት በብዙ ውካታና ፈንጠዝያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ቻርተር ተቀበሉ። ይህ ድርጅት “ዓለም አቀፍ ሰላምና ደህንነት” እንዲያስጠብቅ የተቋቋመ ነበር። የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበርና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚመሳሳሉበት ብዙ መንገድ ነበር። ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒድያ እንዲህ ይላል:- “የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከመጀመሪያው የዓለም ጦርነት በኋላ የተቋቋመውን የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር የሚመስልበት አንዳንድ መንገድ አለ። . . . የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ካቋቋሙት ብሔራት ብዙዎቹ የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበርንም ያቋቋሙ ናቸው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደ መንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር በብሔራት መካከል ሰላም እንዲኖር ለማገዝ የተቋቋመ ድርጅት ነበር። ዋናዎቹ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካላት ከቃል ኪዳኑ ማኅበር አካላት ጋር በብዙ ይመሳሰላሉ።” ስለዚህ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቀዩ አውሬ ከሞት ተቀስቅሶ የተቋቋመ ድርጅት ነው ለማለት ይቻላል። 190 የሚያክሉ አገሮችን በአባልነት የያዘ ስለሆነ 63 ከነበሩት የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር አባል ብሔራት ቁጥር በጣም ይበልጣል። በተጨማሪም ከእርሱ በፊት ከነበረው የቃል ኪዳን ማኅበር ይበልጥ ሰፊ የሆነ የሥራ ኃላፊነት ተሰጥቶታል።
(ራእይ 17:16, 17) ያየሃቸው አሥሩ ቀንዶችና አውሬውም አመንዝራዋን ይጠሏታል፤ ከዚያም ይበዘብዟታል፤ ራቁቷንም ያስቀሯታል፤ እንዲሁም ሥጋዋን ይበላሉ፤ ሙሉ በሙሉም በእሳት ያቃጥሏታል። 17 አምላክ ቃሉ ፍጻሜውን እስኪያገኝ ድረስ ሐሳቡን ዳር እንዲያደርሱ አዎ፣ መንግሥታቸውን ለአውሬው በመስጠት አንድ የሆነውን የራሳቸውን ሐሳብ እንዲፈጽሙ ይህን በልባቸው አኑሯልና።
ይሖዋ “በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሊፈጸሙ የሚገባቸውን ነገሮች” ይገልጣል
17 የሐሰት ሃይማኖት ግን እንዲህ እንደዋዛ የሚጠፋ አይደለም። አምላክ በመንግሥታት ልብ ውስጥ አንድ ሐሳብ እስኪያኖር ድረስ ጋለሞታይቱ ነገሥታትን እሷ በፈለገችው አቅጣጫ በመምራት በእነሱ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ጥረት ማድረጓን ትቀጥላለች። (ራእይ 17:16, 17ን አንብብ።) በቅርቡ ይሖዋ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተወከሉትንና በሰይጣን ዓለም ውስጥ ያሉትን ፖለቲካዊ ኃይሎች ተጠቅሞ በሐሰት ሃይማኖቶች ላይ ጥቃት ይሰነዝራል። እነዚህ መንግሥታት በጋለሞታይቱ ላይ እርምጃ ስለሚወስዱ ተጽዕኖ ማሳደሯ ያከትማል፤ እንዲሁም ሀብቷ ይጠፋል። ከጥቂት አሥርተ ዓመታት በፊት ይህን ማሰብ የማይመስል ነገር ነበር። አሁን ግን ሁኔታዎች መልካቸውን እየቀየሩ ነው፤ በቀዩ አውሬ ላይ የተቀመጠችው ጋለሞታ ሚዛኗን መጠበቅ ስላቃታት ልትወድቅ እየተንገዳገደች ነው። ያም ሆኖ ከተቀመጠችበት የምትወድቀው ሸርተት ብላ አይደለም። ከዚህ ይልቅ አወዳደቋ ድንገተኛና አስደንጋጭ ይሆናል።—ራእይ 18:7, 8, 15-19
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
ከታኅሣሥ 30–ጥር 5
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ራእይ 20–22
“እነሆ፣ ሁሉንም ነገር አዲስ አደርጋለሁ”
(ራእይ 21:1) እኔም አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር አየሁ፤ የቀድሞው ሰማይና የቀድሞው ምድር አልፈዋልና፤ ባሕሩም ከእንግዲህ ወዲህ የለም።
አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር
2 ዮሐንስ ዘመን በመቶ ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ይሖዋ ለኢሳይያስ እንዲህ ብሎ ነበር:- “እነሆ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እፈጥራለሁና የቀደሙትም አይታሰቡም፣ ወደ ልብም አይገቡም።” (ኢሳይያስ 65:17፤ 66:22) ይህ ትንቢት ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጸመው ታማኝ አይሁዳውያን ከ70 ዓመታት የባቢሎን ግዞት በኋላ በ537 ከዘአበ ወደ ኢየሩሳሌም በተመለሱ ጊዜ ነበር። በዚህ የተሐድሶ ዘመን በ“አዲስ ሰማይ” ማለትም በአዲስ የአገዛዝ ሥርዓት ሥር “አዲስ ምድር” ወይም የጸዳ ማኅበረሰብ አቋቁመው ነበር። ይሁን እንጂ ትንቢቱ ሌላ ተጨማሪ ፍጻሜ እንደሚኖረው ሐዋርያው ጴጥሮስ አመልክቶአል። “ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን።” (2 ጴጥሮስ 3:13) አሁን ደግሞ ዮሐንስ ይህ የተስፋ ቃል በጌታ ቀን ውስጥ እንደሚፈጸም አመለከተ። “የቀደመው ሰማይና የቀደመው ምድር” ማለትም የተደራጀው የሰይጣን ሥርዓት በሰይጣንና በአጋንንቱ ከሚመራው መንግሥታዊ መዋቅር ጋር ያልፋል። የክፉዎችና የዓመፀኞች ሰዎች ተነዋዋጭ “ባሕር” ፈጽሞ አይኖርም። በእርሱ ቦታ “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” ማለትም በአዲሱ የአምላክ መንግሥት ሥር የሚተዳደር አዲስ ሰብዓዊ ማኅበረሰብ ይቋቋማል።—ከራእይ 20:11 ጋር አወዳድር።
(ራእይ 21:3, 4) በዚህ ጊዜ ከዙፋኑ አንድ ታላቅ ድምፅ እንዲህ ሲል ሰማሁ፦ “እነሆ፣ የአምላክ ድንኳን ከሰዎች ጋር ነው፤ እሱም ከእነሱ ጋር ይኖራል፤ እነሱም ሕዝቡ ይሆናሉ። አምላክ ራሱም ከእነሱ ጋር ይሆናል። 4 እሱም እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።”
“እነሆ፣ ሁሉንም ነገር አዲስ አደርጋለሁ”
“[አምላክ] እንባን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ላይ ይጠርጋል።” (ራእይ 21:4) አምላክ የሚጠርገው ምን ዓይነት እንባ ነው? የደስታ እንባን ወይም ደግሞ ዓይናችንን ከጉዳት የሚከላከለውን እንባ አይደለም። እዚህ ተስፋ ላይ የተጠቀሰው በመከራና በሐዘን ምክንያት የሚመጣው እንባ ነው። አምላክ ይህን የሚያደርገው እንዲሁ እንባን በማድረቅ ብቻ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ሳንፈልግ እንድናነባ የሚያደርጉንን ነገሮች ይኸውም መከራንና ሐዘንን ጨርሶ በማስወገድ ነው።
“ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም።” (ራእይ 21:4) ጠላት ከሆነው ሞት የበለጠ የሐዘን እንባ እንድናነባ የሚያደርግ ምን ነገር ይኖራል? ይሖዋ ታዛዥ የሆኑትን የሰው ልጆች ከሞት መዳፍ ያላቅቃቸዋል። እንዴት? የሞትን ዋነኛ መንስኤ ማለትም ከአዳም የወረስነውን ኃጢአት በማጥፋት ነው። (ሮም 5:12) ይሖዋ፣ በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ታዛዥ የሰው ልጆችን ወደ ፍጽምና ደረጃ ያደርሳቸዋል። ከዚያም “የመጨረሻው ጠላት የሆነው ሞት ይደመሰሳል።” (1 ቆሮንቶስ 15:26) ከዚያ በኋላ ታማኝ የሆኑ ሰዎች አምላክ ለእነሱ ባለው ዓላማ መሠረት ማለትም ፍጹም ጤንነት ኖሯቸው ዘላለም ይኖራሉ።
“ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም።” (ራእይ 21:4) ለመሆኑ ምን ዓይነት ሥቃይ ነው የማይኖረው? ኃጢአተኞችና ፍጽምና የጎደለን በመሆናችን ሳቢያ የሚመጣውና በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት መራራ ያደረገው አእምሯዊ፣ ስሜታዊ እንዲሁም አካላዊ ሥቃይ አይኖርም።
(ራእይ 21:5) በዙፋኑም ላይ የተቀመጠው “እነሆ፣ ሁሉንም ነገር አዲስ አደርጋለሁ” አለ። ደግሞም “እነዚህ ቃላት አስተማማኝና እውነት ስለሆኑ ጻፍ” አለኝ።
ይሖዋ የእውነት አምላክ ነው
14 ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት የሚነግረንን በቁም ነገር ልንይዘው ይገባል። ስለ ራሱ የሚነግረን በሙሉ እውነት ነው፤ እንዲሁም አደርጋለሁ ያለውን ሁሉ ያደርጋል። በእርግጥም በአምላክ ለመታመን የሚያስችል በቂ ምክንያት አለን። ‘እግዚአብሔርን የማያውቁትን፣ ለጌታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማይታዘዙትን እበቀላለሁ’ ሲለን ልናምነው ይገባል። (2 ተሰሎንቄ 1:8) ከዚህም በላይ ይሖዋ ጽድቅን የሚሹትን እንደሚወድ፣ እርሱ የሰጣቸውን ተስፋዎች ለሚያምኑ ሰዎች የዘላለም ሕይወት እንደሚሰጣቸው እንዲሁም ሐዘንንና ስቃይን ሌላው ቀርቶ ሞትን እንደሚያስቀር ሲናገር ልናምነው ይገባል። ይሖዋ በተለይ ሐዘንን፣ ስቃይንና ሞትን እንደሚያስቀር የተናገረው ተስፋ አስተማማኝ መሆኑን ለማረጋገጥ ሲል ለሐዋርያው ዮሐንስ “እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸውና ጻፍ” ብሎታል።—ራእይ 21:4, 5፤ ምሳሌ 15:9፤ ዮሐንስ 3:36
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ራእይ 20:5) (የቀሩት ሙታን ይህ 1,000 ዓመት እስኪያበቃ ድረስ ሕያው አልሆኑም።) ይህ የመጀመሪያው ትንሣኤ ነው።
it-2 249 አን. 2
ሕይወት
አምላክ ለአዳም የሰጠው ትእዛዝ፣ አዳም ታዛዥ ከሆነ እንደማይሞት ይጠቁማል። (ዘፍ 2:17) በመሆኑም ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች የመጨረሻው ጠላታቸው ሞት ሲደመሰስ በሰውነታቸው ውስጥ ከሚሠራ ወደ ሞት የሚመራ ኃጢአት ነፃ ይሆናሉ። ስለዚህ ለዘላለም ይኖራሉ። (1ቆሮ 15:26) ሞት የሚደመሰሰው በክርስቶስ ግዛት መጨረሻ ላይ ሲሆን የራእይ መጽሐፍ የክርስቶስ ግዛት የ1,000 ዓመት ርዝማኔ እንዳለው ይናገራል። ራእዩ ከክርስቶስ ጋር ነገሥታትና ካህናት ሆነው የሚገዙት ሰዎች “ሕያው ሆነው ከክርስቶስ ጋር ለ1,000 ዓመት ነገሡ” ይላል። “ይህ 1,000 ዓመት እስኪያበቃ ድረስ ሕያው አልሆኑም” የተባሉት “የቀሩት ሙታን” ሰይጣን ከጥልቁ ተፈትቶ በሰው ዘር ላይ የመጨረሻውን ፈተና ከማምጣቱ በፊት ባለው የሺው ዓመት ግዛት መጨረሻ ላይ በሕይወት ያሉ ሰዎች መሆን አለባቸው። የሺው ዓመት ግዛት ሲያበቃ በምድር ላይ ያሉት ሰዎች አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከመሥራታቸው በፊት የነበራቸው ዓይነት ፍጽምና ላይ ይደርሳሉ። ከዚያን ጊዜ አንስቶ፣ ሙሉ በሙሉ ፍጹም የሆነ ሕይወት ይኖራቸዋል። ከዚያ በኋላ ሰይጣን ለአጭር ጊዜ ከጥልቁ ሲፈታ የሚያቀርበውን ፈተና የሚያልፉ ሰዎች ለዘላለም ይህን ፍጹም ሕይወት የማጣጣም አጋጣሚ ያገኛሉ።—ራእይ 20:4-10
(ራእይ 20:14, 15) ሞትና መቃብርም ወደ እሳቱ ሐይቅ ተወረወሩ። ይህም የእሳት ሐይቅ ሁለተኛውን ሞት ያመለክታል። 15 በተጨማሪም በሕይወት መጽሐፍ ላይ ተጽፎ ያልተገኘ ሁሉ ወደ እሳቱ ሐይቅ ተወረወረ።
it-2 189-190
የእሳት ሐይቅ
ይህ አገላለጽ የሚገኘው በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ብቻ ሲሆን ምሳሌያዊ ትርጉም እንዳለው ግልጽ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ይህም የእሳት ሐይቅ ሁለተኛውን ሞት ያመለክታል” በማለት የዚህን ምሳሌያዊ አገላለጽ ትርጉም ይናገራል።—ራእይ 20:14፤ 21:8
የእሳት ባሕር የሚለው አገላለጽ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተሠራባቸው ሌሎች መንገዶች ይህ አገላለጽ ምሳሌያዊ መሆኑን ይበልጥ ግልጽ ያደርጋሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ሞት ወደዚህ ሐይቅ እንደተወረወረ ተገልጿል። (ራእይ 19:20፤ 20:14) ሞት ቃል በቃል በእሳት ሊቃጠል እንደማይችል የታወቀ ነው። በዓይን የማይታይ መንፈሳዊ ፍጡር የሆነው ዲያብሎስም እዚህ ሐይቅ ውስጥ ተጥሏል። ዲያብሎስ መንፈስ ስለሆነ በእሳት ሊቃጠል አይችልም።—ራእይ 20:10፤ ከዘፀ 3:2 እና መሳ 13:20 ጋር አወዳድር።
የእሳቱ ሐይቅ “ሁለተኛውን ሞት” ስለሚያመለክት እንዲሁም ራእይ 20:14 “ሞትና መቃብር” ወደዚያ እንደተጣሉ ስለሚናገር ይህ ሐይቅ የሰው ልጆች ከአዳም የወረሱትን ሞት (ሮም 5:12) ወይም መቃብርን (ሲኦልን) እንደማያመለክት ግልጽ ነው። በመሆኑም ሊቀለበስ የማይችልን ሌላ ዓይነት ሞት የሚያመለክት መሆን አለበት፤ ምክንያቱም ይህ “ሐይቅ” እንደ አዳማዊ ሞት ወይም ሐዲስ (ሲኦል) በውስጡ ያሉትን ሙታን መልሶ እንደሰጠ የሚናገር ዘገባ አናገኝም። (ራእይ 20:13) ስለዚህ “በሕይወት መጽሐፍ” ላይ ተጽፈው ያልተገኙ ማለትም የአምላክን ሉዓላዊነት የሚቃወሙና ንስሐ የማይገቡ በሙሉ ዘላለማዊ ጥፋትን ወይም ሁለተኛውን ሞት ወደሚያመለክተው የእሳት ሐይቅ ይወረወራሉ።—ራእይ 20:15
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ