ሳውል ለጌታ የተመረጠ ዕቃ
የጠርሴሱ ሳውል የክርስቶስ ተከታዮችን እያሳደደ የሚገድል ተቃዋሚ ነበር። ይሁን እንጂ ጌታ ለአንድ የተለየ ዓላማ አጭቶት ነበር። ሳውል አጥብቆ ይቃወመው ለነበረው ነገር እሱ ራሱ ጥብቅና ሊቆም ነው። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “ይህ [ሳውል] በአሕዛብም በነገሥታትም በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና።”—ሥራ 9:15
ምሕረት ተደርጎለት የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ “የተመረጠ ዕቃ” ሲሆን ‘አሳዳጅ’ የነበረው የሳውል ሕይወት ሙሉ በሙሉ ተለወጠ። (1 ጢሞቴዎስ 1:12, 13) ሳውል ክርስትናን ተቀብሎ ሐዋርያው ጳውሎስ ተብሎ መጠራት ሲጀምር ቀደም ሲል እስጢፋኖስ በድንጋይ ሲወገር ተባባሪ እንዲሆንና በሌሎች የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ላይ ጥቃት እንዲሰነዝር ያነሳሳው የነበረው ኃይል አቅጣጫውን ቀይሮ ፍጹም ለተለየ ዓላማ ይውል ጀመር። ኢየሱስ በሳውል ውስጥ ተፈላጊ የሆኑ ባሕርያትን እንደ ተመለከተ የተረጋገጠ ነው። ምን ባሕርያት? ሳውል ማን ነበር? ያደገበት ሁኔታ እውነተኛውን አምልኮ ለማራመድ ተስማሚ ሆኖ እንዲገኝ ያደረገው እንዴት ነበር? ከእሱ ተሞክሮ ልንማረው የምንችለው ነገር ይኖር ይሆን?
የሳውል ቤተሰብ ታሪክ
በ33 እዘአ ከዋለው የጰንጠቆስጤ በዓል በኋላ ብዙም ሳይቆይ እስጢፋኖስ በተገደለ ጊዜ ሳውል ገና “ጎልማሳ” ነበር። በ60-61 እዘአ ገደማ ለፊልሞና ሲጽፍለት ግን ‘ሸምግሎ’ ነበር። (ሥራ 7:58 የ1980 ትርጉም፤ ፊልሞና 9) ምሁራን እንደሚሉት በጥንቱ የእድሜ አቆጣጠር መሠረት “ጎልማሳ” የሚባለው በአብዛኛው ከ24 እስከ 40 ባለው የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ‘ሽማግሌ’ የሚባለው ደግሞ ከ50 እስከ 56 ዓመት የሆነው ሰው ነበር። ስለዚህ ሳውል የተወለደው ኢየሱስ ከተወለደ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ሳይሆን አይቀርም።
በዚያን ጊዜ አይሁዶች በብዙ የዓለም ክፍሎች ውስጥ ይኖሩ ነበር። በሌሎች አገሮች ድል መደረግ፣ ባርነት፣ ከአገር መባረር፣ ንግድና በገዛ ፈቃድ ከቦታ ወደ ቦታ መዘዋወር ከይሁዳ ውጪ በየአገሩ እንዲበታተኑ ካደረጓቸው ምክንያቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። ሳውል ቤተሰቡ ከተበተኑት አይሁዶች መካከል ቢሆንም እንኳ ቤተሰቡ ሕጉን በጥብቅ ይከተል እንደነበር ጎላ አድርጎ ለመግለጽ ሲል “በስምንተኛው ቀን የተገረዝሁ፣ ከእስራኤል ትውልድ፣ ከብንያም ወገን፣ ከዕብራውያን ዕብራዊ ነኝ፤ ስለ ሕግ ብትጠይቁ፣ ፈሪሳዊ ነበርሁ” በማለት ተናግሯል። ሳውል በብዙዎች ዘንድ ከሚታወቀው የነገዱ አባል ማለትም ከመጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ ጋር የሚመሳሰል ስም አለው። የጠርሴሱ ሳውል በውልደት ሮማዊ በመሆኑ ፓውሉስ የሚባል የላቲን ስምም ነበረው።—ፊልጵስዩስ 3:5፤ ሥራ 13:21፤ 22:25-29
ሳውል ሮማዊ ሆኖ መወለዱ ከወንድ አያቶቹ መካከል አንዳቸው የዜግነት መብት አግኝተው እንደነበር ያሳያል። እንዴት? የዜግነት መብት ማግኘት የሚቻልባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ። የዜግነትን መብት በውርስ ከማግኘት በተጨማሪ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ለሠሩት መልካም ሥራ፣ ተራ ለሆነ ፖለቲካዊ ጥቅም ወይም ላቅ ላለ መንግሥታዊ አገልግሎት በወሮታነት ሊሰጥ ይችል ነበር። ነፃነቱን ከአንድ ሮማዊ የገዛ ባሪያ ወይም አንድ ሮማዊ ዜጋ ነፃ ያወጣው ሰው ሮማዊ ሊሆን ይችል ነበር። ቀደም ሲል በጦር ኃይል ውስጥ ያገለግል የነበረ ሰው ከሮማ ክፍለ ጦር ሲሰናበት የዜግነት መብት ያገኝ ነበር። በሮማ ቅኝ ግዛቶች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የዜግነት መብት ማግኘት ይችሉ ነበር። በአንድ ወቅት የዜግነት መብት ጠቀም ባለ ገንዘብ ይገዛ እንደነበረም ይነገራል። ይሁንና የሳውል ቤተሰብ የዜግነት መብቱን እንዴት እንዳገኘ ምንም የሚታወቅ ነገር የለም።
ሳውል የመጣው በሮማ ከምትገኘው የኪልቅያ ጠቅላይ ግዛት ዋና ከተማ ከሆነችው ከትልቋ የጠርሴስ ከተማ (በአሁኑ ጊዜ በደቡብ ቱርክ ከምትገኝ) መሆኑን እናውቃለን። በርካታ ቁጥር ያለው የአይሁድ ኅብረተሰብ በአካባቢው ይኖር የነበረ ቢሆንም ሳውል ለአሕዛብ ባህል ሳይጋለጥ አልቀረም። ጠርሴስ ትልቅና የበለጸገች ከተማ ስትሆን በሄለናዊነት ወይም በግሪክ ትምህርት ማዕከልነቷ የምትታወቅ ነበረች። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከ300,000 እስከ 500,000 የሚጠጋ የሕዝብ ብዛት እንደነበራት ግምታዊ አኃዞች ይናገራሉ። በትንሿ እስያ፣ በሶርያና በሜሶጶጣሚያ መካከል በሚገኘው አውራ ጎዳና ላይ የምትገኝ የንግድ ማዕከል ነበረች። ጠርሴስ ልትበለጽግ የቻለችው በንግድ እንቅስቃሴዋና በተለይ ጥራጥሬ፣ ወይንና የተልባ እግር ያበቅል በነበረው ለም መሬቷ ምክንያት ነው። በመስፋፋት ላይ ከነበረው የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዋ ድንኳን ለመሥራት የሚያስችል ከፍየል ጸጉር የሚሠራ ጨርቅ ይመረት ነበር።
የሳውል ትምህርት
ሳውል ወይም ጳውሎስ ድንኳን በመስፋት ራሱንም ሆነ ሚስዮናዊ እንቅስቃሴውን በሚገባ ይደግፍ ነበር። (ሥራ 18:2, 3፤ 20:34) ድንኳን እየሰፉ መሸጥ የትውልድ ከተማው በሆነችው በጠርሴስ ታዋቂ ሥራ ነበር። ሳውል ድንኳን መስፋት የተማረው በወጣትነቱ ከአባቱ ሳይሆን አይቀርም።
ሳውል በርካታ ቋንቋዎችን የሚችል መሆኑ በተለይም በሮማውያን ግዛት ውስጥ የመነጋገሪያ ቋንቋ የነበረውን ግሪክኛን አቀላጥፎ መናገር መቻሉ በሚስዮናዊ አገልግሎቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት አስችሎታል። (ሥራ 21:37–22:2) ተንታኞች በጣም ጥሩ የሆነ የግሪክኛ ቋንቋ ችሎታ እንደነበረው ይናገራሉ። የተጠቀመባቸው ቃላት ጥንታዊ ወይም ሥነ ጽሑፋዊ እውቀት የሚንጸባረቅባቸው አልነበሩም። ከዚህ ይልቅ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ይጠቅሰው የነበረውን የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች የግሪክኛ ትርጉም ከሆነው ከሴፕቱጀንት ጋር የሚመሳሰሉ ነበሩ። በዚህ ማስረጃ መሠረት በርካታ ምሁራን ሳውል በአንድ የአይሁድ ትምህርት ቤት ውስጥ ገብቶ ቢያንስ ቢያንስ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በግሪክኛ በሚገባ ተምሯል የሚል ግምት አላቸው። “በጥንት ጊዜ የተሻለ ትምህርት በተለይም ደግሞ የግሪክኛ ትምህርት እንዲያው በነፃ የሚገኝ ነገር አልነበረም፤ አንዳንድ ቁሳዊ ድጋፍን ይጠይቅ ነበር” ሲሉ ምሁሩ ማርቲን ሄንል ተናግረዋል። ስለዚህም ሳውል ይህን የመሰለ ትምህርት ለማግኘት መቻሉ ከደህና ቤተሰብ የመጣ መሆኑን ያሳያል።
ወደ 13 ዓመት እድሜ ሲጠጋው ሳውል ከቤቱ 840 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው በኢየሩሳሌም ትምህርቱን ሳይቀጥል አይቀርም። በታዋቂውና ፈሪሳዊ ወጎችን በማስተማር ሥራው ላቅ ያለ ግምት ይሰጠው በነበረው በገማልያል እግር ሥር ተምሯል። (ሥራ 22:3፤ 23:6) ይህ ትምህርት በዛሬው ጊዜ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ከሚሰጠው ትምህርት ጋር የሚተካከል ሲሆን በአይሁድ እምነት ውስጥ እውቅናን እንዲያገኝ የሚያስችለውን አጋጣሚ ከፍቶለታል።a
ለበጎ ነገር የዋሉ ችሎታዎች
ሄለናዊነት በሰፈነባት ሮማዊ ከተማ ከአይሁዳዊ ቤተሰብ የተወለደው ሳውል የሦስት ዓለማት ሰው ነበር። ሰፊ የእውቀት አድማስ የነበረው መሆኑና በርካታ ቋንቋዎችን መናገር መቻሉ “ከሁሉ ጋር በሁሉ ነገር እንደ እነርሱ” እንዲሆን እንደረዳው ምንም አያጠራጥርም። (1 ቆሮንቶስ 9:19-23) ሮማዊ ዜግነቱ በኋላ ላይ ለአገልግሎቱ ሕጋዊ መከላከያ እንዲያቀርብና በሮማ ግዛት ውስጥ በሚገኘው ከፍተኛ ባለ ሥልጣን ፊት ምሥራቹን እንዲናገር አስችሎታል። (ሥራ 16:37-40፤ 25:11, 12) እርግጥ ከሞት የተነሣው ኢየሱስ የሳውልን አስተዳደግ፣ ትምህርትና ባህርያት በሚገባ ያውቅ ስለነበር ለሐናንያ እንዲህ ብሎት ነበር:- “ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና ሂድ፤ ስለ ስሜ ስንት መከራ ሊቀበል እንዲያስፈልገው እኔ አመለክተዋለሁና።” (ሥራ 9:13-16) የጳውሎስ ቅንዓት ትክክለኛ አቅጣጫ እንዲይዝ ሲደረግ የመንግሥቱን መልእክት ራቅ ወዳሉ ቦታዎች ለማድረስ መሣሪያ ሆኖ እንዲያገለግል አስችሎታል።
ኢየሱስ ለአንድ ልዩ ተልዕኮ ሳውልን የመረጠበት ሁኔታ በክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የታየ ለየት ያለ ክስተት ነው። ሆኖም በአሁኑ ጊዜ የሚገኙ ክርስቲያኖች ምሥራቹን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማስፋፋት የሚያስችሉ በግለሰብ ደረጃ የራሳቸው የሆኑ ችሎታዎችና ባህርያት አሏቸው። ኢየሱስ የሚፈልግበትን ነገር በተገነዘበ ጊዜ ሳውል የሚጠበቅበትን ለማድረግ አላቅማማም። የመንግሥቱን ፍላጎቶች ለማስፋፋት የሚችለውን ሁሉ አድርጓል። አንተስ እንደዚያ ታደርጋለህ?
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ሳውል ከገማልያል አግኝቷል ተብሎ የሚታሰበውን የትምህርት መጠንና ዓይነት በተመለከተ የሐምሌ 15, 1996 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 26-9ን ተመልከት።
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
የሮማ ዜግነት ምዝገባና ማረጋገጫ
አውግስጦስ በ4 እና በ9 እዘአ በወጡ ሁለት ደንቦች አማካኝነት ከሮማ ዜጎች የሚወለዱ ሕጋዊ ልጆች እንዲመዘገቡ ደንግጎ ነበር። ምዝገባው ከልደት በኋላ ባሉት 30 ቀናት ውስጥ መከናወን ነበረበት። በየጠቅላይ ግዛቱ የሚገኙ ቤተሰቦች ልጁ ሕጋዊና የሮማ ዜጋ መሆኑን በመግለጽ በተገቢው የመመዝገቢያ ቦታ ለሚገኝ ባለ ሥልጣን ያሳውቃሉ። የወላጆቹ ስም፣ የልጁ ፆታና ስም እንዲሁም የተወለደበት ቀን ይመዘገብ ነበር። እነዚህ ሕጎች ከመደንገጋቸውም በፊት እንኳ በጠቅላላው የሮማ ራስ ገዞች፣ ቅኝ ግዛቶችና አውራጃዎች ውስጥ የሚገኙ ዜጎች በሕዝብ ቆጠራ አማካኝነት በየአምስት ዓመቱ እንደ አዲስ ይመዘገቡ ነበር።
በዚህ መንገድ በተገቢ መንገድ የተያዘን መዝገብ በመመልከት የአንድን ሰው ማንነት ለማወቅ ይቻል ነበር። የእነዚህ ሰነዶች ሕጋዊ ግልባጭ ከእንጨት በተሠሩ ለአያያዝ አመቺ በሆኑ ሰሌዳዎች (የሚተጣጠፉ ሰሌዳዎች) ማግኘት ይቻል ነበር። አንዳንድ ምሁራን እንደሚሉት ጳውሎስ የሮማ ዜጋ መሆኑን ሲናገር ለአባባሉ ማስረጃ የሚሆን ሰርተፊኬት ለማሳየት ሳይችል አልቀረም። (ሥራ 16:37፤ 22:25-29፤ 25:11) የሮማ ዜግነት “ቅድስና ያለው” ተደርጎ ስለሚቆጠርና አንድን ሰው ለብዙ መብቶች ብቁ ያደርገው ስለነበር እነዚህን ሰነዶች አስመስሎ መሥራት ከባድ ወንጀል ነበር። ስለ ግል ሁኔታው የተሳሳተ መረጃ የሰጠ ሰው በሞት ይቀጣ ነበር።
[ምንጭ]
Historic Costume in Pictures/Dover Publications, Inc., New York
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ሳውል የነበረው ሮማዊ ስም
የእያንዳንዱ ሮማዊ ዜጋ ስም ቢያንስ ቢያንስ ከሦስት ስሞች የተዋቀረ ነው። የግል ስም፣ የቤተሰብ ስም (ከጎሳው ወይም ከዘር ሐረጉ ጋር የተያያዘ) እና የመጨረሻ ስም ነበረው። ለዚህ አንድ ጥሩ ምሳሌ ጋየስ ጁሊየስ ቄሣር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስም ሲጠቅስ ሙሉ ሮማዊ ስሞችን አያስቀምጥም፤ ሆኖም ሌሎች ምንጮች የአግሪጳ ሙሉ ስም ማርከስ ጁሊየስ አግሪጳ መሆኑን ይናገራሉ። ጋልዮስ ደግሞ ሉሲየስ ጁኒየስ ጋልዮስ ነበር። (ሥራ 18:12፤ 25:13) በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከአንድ ሰው ሦስት ስሞች ውስጥ የመጨረሻዎቹን ሁለት ስሞች የያዙ እንደ ጴንጤናዊው ጲላጦስ (ከታች ተቀርጾ የሚታየው)፣ ሰርግዮስ ጳውሎስ፣ ቀላውዴዎስ ሉስዮስና ጶርቅዮስ ፊስጦስን የመሳሰሉ ምሳሌዎች አሉ።—ሥራ 4:27፤ 13:7፤ 23:26፤ 24:27
ፓውሉስ የሚለው የሳውል ስም የመጀመሪያ ስሙ ይሁን ወይም የመጨረሻ ስሙ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። አንድ ሰው በቤተሰቡ ወይም በወዳጆቹ የሚጠራበትን ስም በግል ስሙ ላይ መጨመር የተለመደ ነበር። ሳውል እንደሚለው ያለው ሮማዊ ያልሆነ ስም እንደ ምትክ ሆኖም ሊያገለግል ይችላል። አንድ ምሁር “[ሳውል] ጨርሶ ሮማዊ ስም ሆኖ ሊያገለግል አይችልም። ሆኖም ሮማዊ ዜግነት ላለው ሰው የተሰጠ ከትውልድ አገሩ የተገኘ ተጨማሪ ስም ሊሆን ይችላል” ብለዋል። በርካታ ቋንቋዎች በሚነገሩባቸው አካባቢዎች አንድ ሰው በየትኛው ስሙ መጠቀም እንዳለበት የሚወስኑት ሁኔታዎቹ ናቸው።
[ምንጭ]
Photograph by Israel Museum, ©Israel Antiquities Authority