የጥናት ርዕስ 10
ለይሖዋ ያለህ ፍቅርና አድናቆት ለመጠመቅ ያነሳሳሃል
“እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምን ነገር አለ?”—ሥራ 8:36
መዝሙር 37 ይሖዋን በሙሉ ነፍስ ማገልገል
ማስተዋወቂያa
1-2. የሐዋርያት ሥራ 8:27-31, 35-38 እንደሚያሳየው ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ለመጠመቅ የተነሳሳው ለምንድን ነው?
ተጠምቀህ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆን ትፈልጋለህ? ብዙዎች ለይሖዋ ያላቸው ፍቅርና አድናቆት ይህን ውሳኔ እንዲያደርጉ አነሳስቷቸዋል። የኢትዮጵያ ንግሥት ባለሥልጣን የነበረን አንድ ሰው እንደ ምሳሌ እንውሰድ።
2 ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ከቅዱሳን መጻሕፍት በተማረው ነገር ላይ ተመሥርቶ አፋጣኝ እርምጃ ወስዷል። (የሐዋርያት ሥራ 8:27-31, 35-38ን አንብብ።) እንዲህ ለማድረግ ያነሳሳው ምንድን ነው? ቀድሞውንም ቢሆን ለአምላክ ቃል አድናቆት እንደነበረው ጥያቄ የለውም፤ ምክንያቱም በሠረገላው ውስጥ ተቀምጦ የኢሳይያስን መጽሐፍ እያነበበ ነበር። ፊልጶስ ካነጋገረው በኋላ ደግሞ ኢየሱስ ላደረገለት ነገር አድናቆት አዳበረ። ይሁንና ይህ ሰው ወደ ኢየሩሳሌም የተጓዘው ለምን ነበር? ለይሖዋ ፍቅር ስለነበረው ነው። ይህን እንዴት እናውቃለን? ወደ ኢየሩሳሌም የሄደው ይሖዋን ለማምለክ ነበር። ከሁኔታዎቹ መረዳት እንደሚቻለው ይህ ሰው የወላጆቹን ሃይማኖት ትቶ ለእውነተኛው አምላክ የተወሰነውን ብቸኛ ብሔር ተቀላቅሏል። ቀጣዩን ወሳኝ እርምጃ እንዲወስድ ማለትም ተጠምቆ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር እንዲሆን ያነሳሳውም ለይሖዋ ያለው ፍቅር ነበር።—ማቴ. 28:19
3. አንድን ሰው ከመጠመቅ ወደኋላ እንዲል የሚያደርገው ምን ሊሆን ይችላል? (“ልብህ ምን ዓይነት ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)
3 ለይሖዋ ያለህ ፍቅር ለመጠመቅ ሊያነሳሳህ ይችላል። ሆኖም ከመጠመቅ ወደኋላ እንድትል ሊያደርግህ የሚችል የፍቅር ዓይነት አለ። እንዲህ ሲባል ምን ማለት ነው? አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት። የይሖዋ ምሥክር ላልሆኑ ቤተሰቦችህና ጓደኞችህ ጥልቅ ፍቅር ሊኖርህ ይችላል፤ ስለዚህ ‘ከተጠመቅኩ ሊጠሉኝ ይችላሉ’ የሚል ስጋት ይኖርህ ይሆናል። (ማቴ. 10:37) ወይም አምላክ የሚጠላቸውን አንዳንድ ልማዶች በመውደድህ ምክንያት ከእነዚህ ልማዶች መላቀቅ ሊከብድህ ይችላል። (መዝ. 97:10) አሊያም ደግሞ ከልጅነትህ ጀምሮ ከሐሰት ሃይማኖት ጋር ግንኙነት ያላቸውን በዓላት ታከብር ይሆናል። ከእነዚህ በዓላት ጋር በተያያዘ ጥሩ ትዝታ ሊኖርህም ይችላል። በዚህም የተነሳ ይሖዋን የሚያሳዝኑ በዓላትን መተው ከባድ ሊሆንብህ ይችላል። (1 ቆሮ. 10:20, 21) በመሆኑም “ከሁሉም አስበልጬ የምወደው ማንን ወይም ምንን ነው?” የሚለውን መወሰን ይኖርብሃል።
ከሁሉም አስበልጠህ መውደድ ያለብህ ማንን ነው?
4. ለመጠመቅ የሚያነሳሳህ ዋነኛ ምክንያት ምንድን ነው?
4 ልትወዳቸውና ልታደንቃቸው የሚገቡ ብዙ መልካም ነገሮች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት ከመጀመርህ በፊትም ለመጽሐፍ ቅዱስ ከፍተኛ አድናቆት ይኖርህ ይሆናል። ለኢየሱስም ፍቅር አዳብረህ ሊሆን ይችላል። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ከተዋወቅክ በኋላ ደግሞ ከእነሱ ጋር ጊዜ ማሳለፍ ያስደስትህ ይሆናል። ሆኖም እነዚህን መልካም ነገሮች መውደድህ ብቻውን ራስህን ለይሖዋ እንድትወስንና እንድትጠመቅ ያነሳሳሃል ማለት አይደለም። ለመጠመቅ የሚያነሳሳህ ዋነኛ ምክንያት ለይሖዋ አምላክ ያለህ ፍቅር ነው። ከሁሉም አስበልጠህ ይሖዋን የምትወደው ከሆነ ማንኛውም ሰው ወይም የትኛውም ነገር ይሖዋን ከማገልገል እንዲያግድህ አትፈቅድም። ለይሖዋ ያለህ ፍቅር ለመጠመቅ እንድትነሳሳ ብቻ ሳይሆን ከተጠመቅክ በኋላም ለእሱ ታማኝ ሆነህ እንድትጸና ይረዳሃል።
5. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?
5 ኢየሱስ ይሖዋን በሙሉ ልባችን፣ በሙሉ ነፍሳችን፣ በሙሉ አእምሯችንና በሙሉ ኃይላችን መውደድ እንዳለብን ተናግሯል። (ማር. 12:30) ለይሖዋ እንዲህ ያለ ጥልቅ ፍቅርና አክብሮት ማዳበር የምትችለው እንዴት ነው? ይሖዋ ባሳየን ፍቅር ላይ ማሰላሰላችን እኛም በምላሹ እንድንወደው ያነሳሳናል። (1 ዮሐ. 4:19) በዚህ ርዕስ ውስጥ ይህን ለማድረግ የሚረዱ አንዳንድ ጠቃሚ ሐሳቦችን እንመረምራለን። በተጨማሪም ከሁሉም አስበልጠህ ይሖዋን መውደድህ ለየትኞቹ ነገሮች ፍቅርና አድናቆት ለማዳበር ብሎም የትኞቹን እርምጃዎች ለመውሰድ እንደሚረዳህ እንመለከታለን።b
6. ሮም 1:20 እንደሚገልጸው ስለ ይሖዋ መማር የምትችልበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?
6 የፍጥረት ሥራዎችን በመመርመር ስለ ይሖዋ ተማር። (ሮም 1:20ን አንብብ፤ ራእይ 4:11) በዕፀዋትና በእንስሳት ላይ በተንጸባረቀው የይሖዋ ጥበብ ላይ አሰላስል። ድንቅ ስለሆነው የሰውነትህ አሠራር ለመማር ጥረት አድርግ። (መዝ. 139:14) ይሖዋ በፀሐይ ውስጥ ስላኖረው ኃይል ለማሰብ ሞክር፤ ከዚያ ደግሞ ፀሐይ በቢሊዮኖች ከሚቆጠሩ ከዋክብት መካከል አንዷ ብቻ እንደሆነች አስታውስ።c (ኢሳ. 40:26) እንዲህ ስታደርግ ለይሖዋ ያለህ አክብሮት ይጨምራል። ይሁንና ከይሖዋ ጋር ዝምድና ለመመሥረት እሱ ጥበበኛና ኃያል መሆኑን መገንዘብህ ብቻ በቂ አይደለም። ለይሖዋ ጥልቅ ፍቅር ማዳበር ከፈለግክ ስለ እሱ ይበልጥ ማወቅ ይኖርብሃል።
7. ለይሖዋ ጥልቅ ፍቅር ማዳበር ከፈለግክ ስለ ምን ነገር እርግጠኛ ልትሆን ይገባል?
7 ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብልህ እርግጠኛ ልትሆን ይገባል። የሰማይና የምድር ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ እንደሚያውቅህና እንደሚያስብልህ ማመን ይከብድሃል? ከሆነ ይሖዋ ‘ከእያንዳንዳችን የራቀ እንዳልሆነ’ አስታውስ። (ሥራ 17:26-28) ይሖዋ “ልብን ሁሉ ይመረምራል”፤ እንዲሁም ‘ብትፈልገው እንደሚገኝልህ’ ቃል ገብቶልሃል። (1 ዜና 28:9) እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስን እያጠናህ ያለኸው ይሖዋ ‘ወደ ራሱ ስለሳበህ’ ነው። (ኤር. 31:3) ይሖዋ ላደረገልህ ነገር ያለህ አድናቆት በጨመረ መጠን ለእሱ ያለህ ፍቅርም እያደገ ይሄዳል።
8. ለይሖዋ ፍቅር ምላሽ መስጠት የምትችለው እንዴት ነው?
8 ለይሖዋ ፍቅር ምላሽ መስጠት የምትችልበት አንዱ መንገድ እሱን በጸሎት ማነጋገር ነው። የሚያሳስብህን ነገር ስትነግረው እንዲሁም ስላደረገልህ ነገር ሁሉ ስታመሰግነው ለአምላክ ያለህ ፍቅር ያድጋል። ለጸሎትህ ምላሽ የሚሰጥበትን መንገድ ስትመለከት ደግሞ በመካከላችሁ ያለው ወዳጅነት ይጠናከራል። (መዝ. 116:1) ስሜትህን እንደሚረዳልህ እርግጠኛ መሆን ትጀምራለህ። ይሁንና ወደ ይሖዋ ይበልጥ መቅረብ ከፈለግክ አንተም የእሱን አስተሳሰብ ልትረዳ ይገባል። እንዲሁም ከአንተ ምን እንደሚጠብቅ ማወቅ ይኖርብሃል። ይህን ማወቅ የምትችልበት ብቸኛው መንገድ ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ነው።
9. ለመጽሐፍ ቅዱስ አድናቆት እንዳለህ ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?
9 የአምላክ ቃል ለሆነው ለመጽሐፍ ቅዱስ አድናቆት አዳብር። ስለ ይሖዋና ለአንተ ስላለው ዓላማ እውነቱን መማር የምትችለው ከመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ በማንበብ፣ ለጥናትህ በመዘጋጀት እንዲሁም የተማርከውን ነገር በሥራ ላይ በማዋል ለመጽሐፍ ቅዱስ አድናቆት እንዳለህ ማሳየት ትችላለህ። (መዝ. 119:97, 99፤ ዮሐ. 17:17) መጽሐፍ ቅዱስን በግልህ የምታነብበት ፕሮግራም አለህ? ፕሮግራምህን ጠብቀህ በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን ታነብባለህ?
10. መጽሐፍ ቅዱስን ልዩ ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ ምንድን ነው?
10 መጽሐፍ ቅዱስን ልዩ ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ ኢየሱስን በተመለከተ የዓይን ምሥክሮችን ዘገባ የያዘ መሆኑ ነው። በመሆኑም ኢየሱስ ስላደረገልህ ነገር ትክክለኛውን መረጃ ማግኘት የምትችለው ከመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። ኢየሱስ የተናገራቸውንና ያደረጋቸውን ነገሮች ስትማር ደግሞ ከእሱ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት መነሳሳትህ አይቀርም።
11. ለይሖዋ ያለህ ፍቅር እንዲያድግ ምን ይረዳሃል?
11 ለኢየሱስ ፍቅር እያዳበርክ ስትሄድ ለይሖዋ ያለህ ፍቅር ያድጋል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ኢየሱስ የአባቱን ባሕርያት ፍጹም በሆነ መንገድ አንጸባርቋል። (ዮሐ. 14:9) ስለዚህ ስለ ኢየሱስ ይበልጥ በተማርክ መጠን ስለ ይሖዋ ያለህ እውቀትና ለእሱ ያለህ አድናቆት እየጨመረ ይሄዳል። ለምሳሌ ኢየሱስ ሌሎች ለሚንቋቸው ሰዎች ማለትም ለድሆች፣ ለሕመምተኞችና ለደካሞች ርኅራኄ ያሳየው እንዴት እንደሆነ ለማሰብ ሞክር። በተጨማሪም ኢየሱስ ስለሰጠህ ጠቃሚ ምክር እንዲሁም ምክሩን በመስማትህ ሕይወትህ እንዴት እንደተሻሻለ አስብ።—ማቴ. 5:1-11፤ 7:24-27
12. ስለ ኢየሱስ መማርህ ምን ለማድረግ ሊያነሳሳህ ይችላል?
12 ኢየሱስ ኃጢአታችን ይቅር እንዲባልልን ሲል ስለከፈለው መሥዋዕት በጥሞና ማሰብህ ለእሱ ያለህ ፍቅር ይበልጥ እንዲጨምር እንደሚያደርግ ጥያቄ የለውም። (ማቴ. 20:28) ኢየሱስ ለአንተ ሲል እንደሞተ መረዳትህ ንስሐ እንድትገባና የይሖዋን ይቅርታ እንድትፈልግ ሊያነሳሳህ ይችላል። (ሥራ 3:19, 20፤ 1 ዮሐ. 1:9) ለይሖዋና ለኢየሱስ ፍቅር ስታዳብር ደግሞ ይሖዋንና ኢየሱስን ከሚወዱ ሰዎች ጋር ለመቀራረብ መነሳሳትህ አይቀርም።
13. ይሖዋ ምን ሰጥቶሃል?
13 ለይሖዋ ቤተሰብ ፍቅር አዳብር። የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ቤተሰቦችህና የቀድሞ ጓደኞችህ ራስህን ለይሖዋ መወሰን የምትፈልገው ለምን እንደሆነ ላይገባቸው ይችላል። አልፎ ተርፎም ይቃወሙህ ይሆናል። ሆኖም ይሖዋ መንፈሳዊ ቤተሰብ በመስጠት ይረዳሃል። ከዚህ መንፈሳዊ ቤተሰብ ጋር ከተቀራረብክ የሚያስፈልግህን ፍቅርና ድጋፍ ማግኘት ትችላለህ። (ማር. 10:29, 30፤ ዕብ. 10:24, 25) ምናልባትም ውሎ አድሮ ቤተሰቦችህ አብረውህ ይሖዋን ማገልገልና በእሱ መሥፈርቶች መመራት ይጀምሩ ይሆናል።—1 ጴጥ. 2:12
14. በ1 ዮሐንስ 5:3 ላይ እንደተገለጸው የይሖዋን መሥፈርቶች በተመለከተ ምን ተገንዝበሃል?
14 ለይሖዋ መሥፈርቶች አድናቆት አዳብር፤ እንዲሁም በሥራ ላይ አውላቸው። ይሖዋን ከማወቅህ በፊት የምትመራው በራስህ መሥፈርቶች ሊሆን ይችላል፤ አሁን ግን የይሖዋ መሥፈርቶች የተሻሉ እንደሆኑ ተገንዝበሃል። (መዝ. 1:1-3፤ 1 ዮሐንስ 5:3ን አንብብ።) መጽሐፍ ቅዱስ ለባሎች፣ ለሚስቶች፣ ለወላጆችና ለልጆች ስለሚሰጠው ምክር ቆም ብለህ አስብ። (ኤፌ. 5:22 እስከ 6:4) ይህን ምክር ተግባራዊ ስታደርግ ቤተሰብህ ይበልጥ ደስተኛ ሆኗል? ይሖዋ ስለ ጓደኛ ምርጫ የሰጠውን መመሪያ በመከተልህ ሕይወትህ እንደተሻሻለ ይሰማሃል? ከበፊቱ ይበልጥ ደስተኛ ነህ? (ምሳሌ 13:20፤ 1 ቆሮ. 15:33) ለእነዚህ ጥያቄዎች “አዎ” የሚል መልስ እንደምትሰጥ የታወቀ ነው።
15. የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ በማድረግ ረገድ እርዳታ ካስፈለገህ ምን ማድረግ ትችላለህ?
15 ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተማርካቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረግ የምትችለው እንዴት እንደሆነ ማወቅ የሚከብድህ ጊዜ ሊኖር ይችላል። ለዚህም ሲባል ይሖዋ ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንድትችል የሚረዱ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በድርጅቱ አማካኝነት ያቀርብልሃል። (ዕብ. 5:13, 14) እነዚህን ጽሑፎች ስታነብና ስታጠና ምክሩ ጠቃሚና ግልጽ እንደሆነ ማስተዋልህ አይቀርም፤ ይህም ወደ ይሖዋ ድርጅት ይበልጥ ለመቅረብ ያነሳሳሃል።
16. ይሖዋ ሕዝቦቹን ያደራጀው እንዴት ነው?
16 ለይሖዋ ድርጅት ፍቅር አዳብር፤ እንዲሁም የበኩልህን ድጋፍ ስጥ። ይሖዋ ሕዝቦቹን በጉባኤ ያደራጃቸው ሲሆን ልጁን ኢየሱስን በሁሉም ጉባኤዎች ላይ ራስ አድርጎ ሾሞታል። (ኤፌ. 1:22፤ 5:23) ኢየሱስ ደግሞ በዛሬው ጊዜ ሥራውን እንዲያደራጅ በመንፈስ የተቀቡ ጥቂት ወንዶችን ያቀፈን አንድ ቡድን ሾሟል። ኢየሱስ ይህን ቡድን “ታማኝና ልባም ባሪያ” በማለት ጠርቶታል፤ ይህ ባሪያ አንተን በመንፈሳዊ የመመገቡንና ለአንተ ጥበቃ የማድረጉን ኃላፊነት በቁም ነገር ይመለከተዋል። (ማቴ. 24:45-47) ታማኙ ባሪያ አንተን የሚንከባከብበት አንዱ መንገድ ጥሩ እረኛ ለመሆን ብቃት ያላቸው ሽማግሌዎች እንዲሾሙ ማድረግ ነው። (ኢሳ. 32:1, 2፤ ዕብ. 13:17፤ 1 ጴጥ. 5:2, 3) ሽማግሌዎች አንተን ለመንከባከብ፣ ለማጽናናትና ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድትቀርብ ለመርዳት አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ያደርጋሉ። ሽማግሌዎች ሊያደርጉልህ ከሚችሏቸው በጣም ወሳኝ ነገሮች አንዱ ሌሎችን ስለ ይሖዋ ማስተማር እንድትችል መርዳት ነው።—ኤፌ. 4:11-13
17. በሮም 10:10, 13, 14 መሠረት ለሌሎች ስለ ይሖዋ የምንናገረው ለምንድን ነው?
17 ሌሎች ለይሖዋ ፍቅር እንዲያዳብሩ እርዳቸው። ኢየሱስ ተከታዮቹ ሌሎችን ስለ ይሖዋ እንዲያስተምሩ አዟቸዋል። (ማቴ. 28:19, 20) ግዴታ እንደሆነ ስለተሰማን ብቻ ይህን መመሪያ እንታዘዝ ይሆናል። ሆኖም ለይሖዋ ያለህ ፍቅር እያደገ ሲሄድ “ስላየነውና ስለሰማነው ነገር ከመናገር ወደኋላ ማለት አንችልም” በማለት እንደተናገሩት እንደ ጴጥሮስና እንደ ዮሐንስ ዓይነት ስሜት ይሰማሃል። (ሥራ 4:20) አንድ ሰው ይሖዋን እንዲወድ የመርዳትን ያህል ደስታ የሚያስገኝ ነገር የለም ማለት ይቻላል። ወንጌላዊው ፊልጶስ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ የቅዱሳን መጻሕፍትን እውነት እንዲያውቅና እንዲጠመቅ መርዳት በመቻሉ ምን ያህል እንደተደሰተ መገመት ትችላለህ። እንደ ፊልጶስ ሁሉ አንተም ኢየሱስ እንድንሰብክ የሰጠንን መመሪያ መታዘዝህ የይሖዋ ምሥክር መሆን እንደምትፈልግ ያሳያል። (ሮም 10:10, 13, 14ን አንብብ።) እዚህ ደረጃ ላይ ስትደርስ አንተም እንደ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ “እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምን ነገር አለ?” ብለህ ለመጠየቅ መነሳሳትህ አይቀርም።—ሥራ 8:36
18. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?
18 ለመጠመቅ ስትወስን በሕይወትህ ውስጥ በጣም ወሳኙን እርምጃ ለመውሰድ ተዘጋጀህ ማለት ነው። ጥምቀት በጣም ትልቅ ውሳኔ ከመሆኑ አንጻር ጥምቀት ምን ትርጉም እንዳለው አስቀድመህ ማሰብህ አስፈላጊ ነው። ታዲያ ስለ ጥምቀት ምን ማወቅ ይኖርብሃል? ደግሞስ ከመጠመቅህ በፊትና በኋላ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመለከታለን።
መዝሙር 2 ስምህ ይሖዋ ነው
a አንዳንድ ሰዎች ይሖዋን ቢወዱትም እንኳ ለመጠመቅና የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ዝግጁ መሆናቸውን ይጠራጠራሉ። አንተም እንደዚህ የሚሰማህ ከሆነ ይህ ርዕስ ለመጠመቅ ዝግጁ እንድትሆን የሚረዱ አንዳንድ ሐሳቦችን እንድታስተውል ይረዳሃል።
b እያንዳንዱ ሰው የተለያየ ስለሆነ አንዳንዶች በዚህ ርዕስ ውስጥ ያሉትን ሐሳቦች ተግባራዊ የሚያደርጉበት ቅደም ተከተል እዚህ ላይ ከተጠቀሰው ሊለይ ይችላል።
c ተጨማሪ ምሳሌዎችን ለማግኘት ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው? እና የሕይወት አመጣጥ—መልስ የሚያሻቸው አምስት ጥያቄዎች የተባሉትን ብሮሹሮች ተመልከት።
d የሥዕሉ መግለጫ፦ አንዲት እህት በገበያ ስፍራ ላገኘቻት ወጣት ትራክት ስታበረክት።