የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—ነሐሴ 2016
ነሐሴ 22-28
it-1 857-858
አስቀድሞ ማወቅ፣ አስቀድሞ መወሰን
አምላክ ያስነገረው ትንቢት እንዲፈጸም ሲል ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ እንዲሰጥ አስቀድሞ ወስኗል?
የአስቆሮቱ ይሁዳ የተከተለው የክህደት ጎዳና መለኮታዊ ትንቢት እንዲፈጸም ከማድረጉም በላይ ይሖዋም ሆነ ልጁ ነገሮችን አስቀድሞ የማወቅ ችሎታ እንዳላቸው አሳይቷል። (መዝ 41:9፤ 55:12, 13፤ 109:8፤ ሥራ 1:16-20) ይሁን እንጂ ይሁዳ እንዲህ ዓይነት አካሄድ እንደሚከተል አምላክ አስቀድሞ ወስኖ ነበር ማለት አይቻልም። ትንቢቶቹ የሚገልጹት የኢየሱስ የቅርብ ወዳጅ የሆነ ሰው አሳልፎ እንደሚሰጠው እንጂ ከሚቀርቡት ሰዎች መካከል ማናቸው አሳልፈው እንደሚሰጡት አይደለም። ከዚህ ሁኔታ ጋር በተያያዘም ቢሆን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች፣ይሁዳ እንዲህ ዓይነት ድርጊት እንዲፈጽም አምላክ አስቀድሞ እንደማይወስን ያረጋግጣሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ መለኮታዊውን መሥፈርት ሲገልጽ “በማንም ሰው ላይ እጅህን ለመጫን አትቸኩል፤ እንዲሁም በሌሎች ኃጢአት ተካፋይ አትሁን፤ ራስህን በንጽሕና ጠብቅ” ብሏል። (1ጢሞ 5:22፤ ከ3:6 ጋር አወዳድር።) ኢየሱስ 12ቱን ሐዋርያት በጥበብና በተገቢው መንገድ የመምረጡ ጉዳይ በጣም ስላሳሰበው ውሳኔውን ከማሳወቁ በፊት ሙሉ ሌሊት ወደ አባቱ ሲጸልይ አድሯል። (ሉቃስ 6:12-16) አምላክ፣ ይሁዳ ከሃዲ እንደሚሆን አስቀድሞ ወስኖ ከነበረ ይህ እሱ ራሱ ከሰጠው መመሪያ ጋር የሚጋጭ ይሆን ነበር፤ ደግሞም ከዚህ መሥፈርት አንጻር አምላክ በይሁዳ ኃጢአት ተካፋይ ይሆን ነበር።
በመሆኑም ይሁዳ፣ ሐዋርያ ሆኖ በተመረጠበት ጊዜ በልቡ ውስጥ ምንም ዓይነት የከዳተኝነት ዝንባሌ የታየበት አይመስልም። በልቡ ውስጥ ‘መርዛማ ሥር እንዲበቅል’ እና እንዲበክለው በመፍቀዱ ከትክክለኛው ጎዳና ወጥቶ የአምላክን ሳይሆን የዲያብሎስን አመራር ተከተለ፤ በመሆኑም ስርቆትና ክህደት ፈጸመ። (ዕብ 12:14, 15፤ ዮሐ 13:2፤ ሥራ 1:24, 25፤ ያዕ 1:14, 15፤ ይሁዳ ቁ. 4ን ተመልከት።) በዚህ አካሄዱ የተወሰነ ከገፋበት በኋላ ግን ኢየሱስ ራሱ በይሁዳ ልብ ውስጥ ያለውን ማወቅና እንደሚከዳው አስቀድሞ መናገር ችሏል።—ዮሐ 13:10, 11
እርግጥ፣ በዮሐንስ 6:64 ላይ በሚገኘውና አንዳንድ ደቀ መዛሙርት በኢየሱስ ትምህርቶች እንደተደናቀፉ በሚገልጸው ዘገባ ላይ ኢየሱስ “የማያምኑት እነማን እንደሆኑና ማን አሳልፎ እንደሚሰጠው ከመጀመሪያው ያውቅ” እንደነበር እናነባለን። “መጀመሪያ” የሚለው ቃል (በግሪክኛ አርኪ) በ2 ጴጥሮስ 3:4 ላይ የፍጥረትን መጀመሪያ ለማመልከት ቢሠራበትም ሌሎች ወቅቶችንም ሊያመለክት ይችላል። (ሉቃስ 1:2፤ ዮሐ 15:27) ለምሳሌ፣ ሐዋርያው ጴጥሮስ መንፈስ ቅዱስ በአሕዛብ ላይ ስለ መውረዱ ሲናገር “በመጀመሪያ በእኛ ላይ እንደወረደው ሁሉ በእነሱም ላይ ወረደ” ብሏል፤ ይህን ሲል ደቀ መዝሙር ወይም ሐዋርያ የሆነበትን ጊዜ ማመልከቱ እንዳልነበረ ግልጽ ነው፤ ከዚህ ይልቅ በአገልግሎቱ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውን አንድ ወቅት ማለትም መንፈስ ቅዱስ ለተለየ ዓላማ በእነሱ ላይ መውረድ ‘የጀመረበትን’ በ33 ዓ.ም. የዋለውን የጴንጤቆስጤ ዕለት መጥቀሱ ነበር። (ሥራ 11:15፤ 2:1-4) በመሆኑም ላንገ ያዘጋጀው ኮሜንታሪ ኦን ዘ ሆሊ ስክሪፕቸርስ (ገጽ 227) ስለ ዮሐንስ 6:64 የሰጠው ሐሳብ ትኩረት የሚስብ ነው፦ “መጀመሪያ . . . የሚለው ቃል፣ ማንኛውም ነገር የጀመረበትን . . . ወይም እሱ [ኢየሱስ] ከእያንዳንዳቸው ጋር መተዋወቅ የጀመረበትን . . . አሊያም ደቀ መዛሙርቱን መሰብሰብ የጀመረበትን ወይም መሲሐዊ አገልግሎቱን የጀመረበትን ጊዜ አያመለክትም፤ . . . ከዚህ ይልቅ ቃሉ የሚያመለክተው [አንዳንድ ደቀ መዛሙርት እንዲሰናከሉ ያደረገው] የጥርጣሬ ዘር ማቆጥቆጥ የጀመረበትን ጊዜ ነው። በተመሳሳይም አሳልፎ የሚሰጠውን ሰው ከመጀመሪያ አውቆታል ሊባል ይችላል።”—በፊሊፕ ሻፍ ተተርጉሞ የተዘጋጀ፣ 1976፤ ከ1ዮሐ 3:8, 11, 12 ጋር አወዳድር።
ነሐሴ 29-መስከረም 4
w87 3/15 24 አን. 5
ደስተኛ አምላክ፣ ደስተኛ ሕዝብ!
116:3—“የሞት ገመዶች” የተባሉት ምንድን ናቸው?
መዝሙራዊው፣ ሞት በማይበጠሱ ገመዶች ተብትቦ የያዘው ያህል ስለተሰማው ጨርሶ ማምለጥ የሚችል አይመስልም ነበር። አንድ ሰው እጁ ወይም እግሩ በገመድ ጥፍር ተደርጎ ከታሰረ ኃይለኛ ሥቃይ ይሰማዋል፤ የግሪኩ የሰብዓ ሊቃናት ትርጉምም “ገመዶች” የሚለውን የዕብራይስጥ ቃል “ጣር” ብሎ ፈትቶታል። ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሞት በማያፈናፍነው የሞት ጣር ተይዞ ነበር። ይሖዋ ኢየሱስን ከሞት እንዳስነሳው ሲገለጽ “ከሞት ጣር አላቆ አስነሳው” የተባለው ለዚህ ነው።—ሥራ 2:24