የጥንቷ አቴንስ እምብርት የነበረው የገበያ ስፍራ
በአቴንስ የሚገኘው ምሁሩ ኅብረተሰብ ታውኳል! በዚያች የግሪክ ከተማ የገበያ ስፍራ ሁልጊዜ አዳዲስ ሐሳቦች ይፈልቁ ነበር። ይሁን እንጂ በዚህ ጊዜ ያለው ሁኔታ ፍጹም የተለየ ነበር። በቅርቡ ወደ ከተማዋ የመጣ አንድ አይሁዳዊ ሰው “አዲሶችን አማልክት የሚያወራ ይመስላል።” “ከሚያገኛቸው” ሰዎች ጋር ትኩረት በሚስቡ ነገሮች ላይ ውይይት ያደርግ ነበር። ኩራተኞቹ ኤፊቆሮሳውያንና ኮስታራዎቹ ኢስጦኢኮች “ይህ ለፍላፊ ምን ሊናገር ይወዳል?” እያሉ ይጠይቁ ነበር። በእርግጥም የአቴንስ የገበያ ስፍራ ስፍር ቁጥር በሌላቸው ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ግልጽ ክርክር የሚደረግበት ቦታ ነበር። ሆኖም አዳዲስ አማልክትን ማስተዋወቅ የማይታሰብ ነገር ነበር!—ሥራ 17:17, 18
ሐዋርያው ጳውሎስ በአቴንስ የገበያ ስፍራ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሰብክ የአቴናውያን ጥርጣሬ ይህ ነበር። ጳውሎስ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስና ስለ ትንሣኤ እየተናገረ ነበር። ይሁንና አቴናውያን ለአዳዲስ ሐሳቦች ጆሯቸውን የመስጠት ልማድ የነበራቸው ሆነው ሳለ እንዲህ ዓይነት ጽንሰ ሐሳቦችን በገበያ ሥፍራው ማስተዋወቁ እንግዳ የሚሆነው ምኑ ላይ ነው?
አቴንስ ሕዝባዊ አደባባይ አገኘች
እንደ እውነቱ ከሆነ ድንቅ የነበረው ነገር ራሱ የገበያ ስፍራው እንዲሁም በአቴናውያን ሃይማኖታዊና ሕዝባዊ ሕይወት ውስጥ የተጫወተው ቁልፍ ሚና ነበር። የአቴንሱ የገበያ ሥፍራ ወደ 60 ሄክታር የሚጠጋ ስፋት ያለው በአክሮፖሊስ ሰሜን ምዕራብ የሚገኝ ተዳፋት ቦታ ነው። ይህ ቦታ የከተማው ሕዝባዊ አደባባይ ሆኖ እንዲያገለግል የተወሰነው በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ መጀመሪያ ላይ በአቴናዊው የፖለቲካ ሰውና ሕግ አርቃቂ በሶሎን የሕይወት ዘመን ሳይሆን አይቀርም። በአቴንስ ዲሞክራሲያዊ አሠራር ተግባራዊ መደረጉና ለዜግነት መብት የተሰጠው ልዩ ትኩረት በቀጣዩ ምዕተ ዓመት የመጀመሪያ ዓመታት ላይ በከተማዋ ውስጥ የግንባታ ሥራዎች እንዲስፋፉ አድርጎ ነበር። ይህ የገበያ ሥፍራው ሞቅ ያለ እንቅስቃሴ እንዲኖረውና ይበልጥ ቁልፍ ሚና እንዲጫወት አድርጎታል።
የገበያ ስፍራ ተብሎ የተተረጎመው አጎራ የሚለው ግሪክኛ ቃል “መከማቸት፣ መሰብሰብ” የሚል ትርጉም ካለው ግሥ የተገኘ ነው። የገበያ ስፍራው የከተማዋ ዋነኛ የመሰብሰቢያ ቦታ ሆኖ በማገልገሉ ይህ ትርጉሙ ከገበያ ቦታው ሁኔታ ጋር ይስማማል። የገበያ ስፍራው የማኅበራዊና የሕዝባዊ ሕይወት ማዕከል ነበር። የሕዝባዊ አስተዳደርና የፍርድ አካላት መቀመጫ፣ ዋነኛ የመገበያያና የንግድ ስፍራ፣ ግሪካዊ ድራማዎች የሚታዩበት የቲያትር ማሳያ ቦታ፣ የአትሌቲክስ ውድድሮች የሚካሄዱበት ስፍራና ምሁራዊ ውይይት ለማድረግ ተስማሚ የሆነ ቦታ ነበር።
በአቴንስ የገበያ ስፍራ የሚገኙትን ቤተ መቅደሶች፣ ዓምዶች፣ ሐውልቶችና ሕዝባዊ ሕንፃዎች ፍርስራሾች ለመጎብኘት ትፈልጋለህ? የገበያ ስፍራውን የቀድሞ ታሪክ ለመመርመር በምናደርገው ጥረት በጫጫታና በግርግር የተሞላችውን ዘመናዊቷን ከተማ ትተን በጠጠር በተሠሩ መንገዶች፣ ፀጥታ በሰፈነባቸው የእብነ በረድ ፍርስራሾች፣ በውቅር ድንጋዮች እንዲሁም በአረምና በዱር ቅጠላ ቅጠሎች በተሸፈኑና በመፈራረስ ላይ ባሉ ትልልቅ በሮች ውስጥ አልፈን እንጓዝ።
ቤተ መቅደሶች፣ ቅዱስ ስፍራዎችና የበላይ ጠባቂ የሆኑ አማልክት
ጎብኚዎች ብዛት ያላቸው ቤተ መቅደሶች፣ ቅዱስ ስፍራዎችና ለተለያዩ አማልክት የተወሰኑ የአምልኮ ስፍራዎች መኖራቸውን ሲመለከቱ ይገረማሉ። እነዚህ ሁሉ ነገሮች የገበያ ስፍራውን ከአክሮፖሊስ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ የሚገኝ ዋነኛ የአምልኮ ማዕከል አድርገውታል። በጥንቷ አቴንስ ወርቃማ ዘመን ወቅት ሃይማኖት በእያንዳንዱ ሕዝባዊ ኑሮ ውስጥ ሰርጎ ገብቶ ነበር። ስለዚህም ለመንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶችና ለአስተዳደራዊ አገልግሎት ሰጪዎች የቆሙ የተለያዩ “የበላይ ጠባቂ አማልክት” በዚህ የገበያ ስፍራ ቤተ መቅደስ ነበራቸው ማለት ነው።
ከእነዚህ ሕንፃዎች መካከል ታዋቂ የነበረው የሂፌስቶስ ቤተ መቅደስ ይገኝበታል። አቴና የምትባለው እንስት አምላክ ከሂፌስቶስ ጋር የተጎዳኘች ነበረች። ሁለቱም የኪነ ጥበብና የእጅ ሙያ የበላይ ጠባቂ አማልክት ተደርገው በዚህ ቤተ መቅደስ ይመለኩ ነበር። በዚህ ቤተ መቅደስ ዙሪያ በከርሰ ምድር ጥናት የተገኙ የብረትና የሸክላ ዕቃ መሥሪያዎች ቤተ መቅደሱ በእሳት መጠቀምን ይጠይቅ የነበረው የግሪኩ የኪነ ጥበብ አምላክ የሂፌስቶስ መሆኑን አረጋግጠዋል። ይህ በጥሩ ሁኔታ ተጠብቆ የቆየ ቤተ መቅደስ በሰባተኛው መቶ ዘመን እዘአ የግሪክ ኦርቶዶክስ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሆኖ እንዲያገለግል ሳይደረግ አይቀርም። ሆኖም በአሁኑ ጊዜ በዚህ መልኩ ማገልገሉን አቁሟል።
የገበያ ስፍራው የራሱ የሆነ የበላይ ጠባቂ አምላክ እንደሚኖረው የተረጋገጠ ነው። ይህ አምላክ የንግግር ችሎታን የሚሰጥ ነው ተብሎ የሚታመነው ዚየስ አጎሬኦስ ሲሆን ውድ ከሆነ እብነ በረድ ተጠርቦ የተሠራ ውብ መሠዊያ ነበረው። (ከሥራ 14:11, 12 ጋር አወዳድር።) በአቅራቢያው ደግሞ ለጀግኖች በቆሙ ድንቅ ሐውልቶች የተከበበ አንድ የአማልክት እናት መሠዊያ ይገኝ ነበር።
ጥቂት ራቅ ብሎ ደግሞ አንድ ትንሽ የአዮናውያን ቤተ መቅደስ እናገኛለን። የጂኦግራፊ አጥኚ የሆኑት ፖሴኒያስ ቤተ መቅደሱ የአባ አፖሎ እንደሆነ ገልጸዋል። ለምን? ምክንያቱም እንደ አንድ ጥንታዊ የግሪክ አፈ ታሪክ አባባል አፖሎ የአዮን አባትና አቴናውያንን ጭምር የሚያቅፈው የአዮናውያን ዘር መሥራች ነበር።a አፖሎ የአዮናውያን አባት እንደመሆኑ መጠን በተለይ በከተማው ውስጥ ከሚገኙ የተለያዩ የወንድማማች ማኅበራት ጋር በተያያዘ መንገድ ለመንግሥት አስተዳደር ድርጅቶች የበላይ ጠባቂ አምላክ ሆነ።
ፊታችንን ወደ ሰሜን ስናቀና በአራተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ አጋማሽ ላይ የተገነባን የአንድ አነስተኛ ቤተ መቅደስ የኖራ ድንጋይ ቅሪት እንመለከታለን። እዚህ ይመለኩ የነበሩት የቀድሞዎቹ ሃይማኖታዊ ወንድማማቾች ማኅበራት ዋነኛ አማልክት ዚየስና አቴና ፋትሪዎስ ነበሩ። የአቴናን ዜግነት ለማግኘት የእነዚህ ወንድማማች ማኅበራት አባል መሆን የግድ ነበር። መንገዱን ተሻግሮ የአሥራ ሁለቱን አማልክት መሠዊያ ቀሪ ፍርስራሽ እናገኛለን።
በአቅራቢያው በሚገኘው የዚየስ ኤለቴሮስ በረንዳ ደግሞ ዋነኛው የግሪክ አምላክ የነፃነት እንዲሁም ከመከራ የሚያድን አምላክ እንደሆነ ተደርጎ ይከበር ነበር። ይህ በረንዳ ተወዳጅ የመንሸራሸሪያና የመሰብሰቢያ ቦታ ነበር። በዚህ በረንዳ ላይ ታዋቂው ፈላስፋ ሶቅራጥስ ከጓደኞቹ ጋር ይገናኝ እንደነበር ይነገራል። በበረንዳው ላይ ተቀምጠው ሊያወሩ ወይም ሊንሸራሸሩ ይችሉ ነበር። ይህን በረንዳ ለማስዋብ የተበረከቱት አቴንስን ለመከላከል ሲሉ በውጊያ ላይ የወደቁ ተዋጊዎች ይይዟቸው የነበሩ ጋሻዎችን የመሳሰሉ ስጦታዎች ከተማዋን ከጠላት እጅ ነፃ ከማውጣት ወይም ነፃነቷን ጠብቆ ከማቆየት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ነበሩ።
የፓናቴናውያን መንገድ
የገበያ ስፍራውን በሰያፍ ሰንጥቆ የሚያልፈው ሰፊ የኮሮኮንች መንገድ የፓናቴናውያን መንገድ በመባል ይታወቃል። ስሙና ለየት የሚያደርገው ባሕርዩ ፓናቴናያ ከሚባለው የአቴናውያን ብሔራዊ በዓል የተገኘ ነው። በዚህ በዓል ወቅት ሰዎች አቴና የምትባለውን እንስት አምላክ መከናነቢያ ተሸክመው የበዓሉ ሥነ ሥርዓት ከሚጀምርበት ቤት (ከከተማዋ በር ቀጥሎ ከሚገኘው) በመነሣት ወደ አክሮፖሊስ ይሄዱ የነበሩት በዚህ መንገድ ላይ ነበር። በአንድ የአቴና ቤተ መቅደስ ግድግዳ ላይ የተቀረጸው ምስል የበዓሉን ሥነ ሥርዓት ታላቅነትና ድምቀት በዓይነ ኅሊናችን ለማየት ይረዳናል። በሰልፉ ውስጥ ፈረሰኞች፣ የውድድር ሠረገሎች፣ ለመሥዋዕት የሚሆኑ ላሞችና በጎች እንዲሁም ለመሥዋዕቱ የሚያገለግሉ እቃዎችን የተሸከሙ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ይገኙበት ነበር። የገበያ ስፍራውን ንድፍ ያወጡት መሐንዲሶች ብዙ ሕዝብ ለመያዝ የሚያስችል ሰፊ ቦታ እንዲኖረው በማድረጋቸው የአቴንስ ዜጎችና እንግዶቻቸው ሥነ ሥርዓቱን ለመመልከት ይችሉ ነበር። ለምሳሌ ያህል በተወሰነ ርቀት የተደረደሩት ዓምዶች ፊት ለፊታቸው ካሉት ከታራዎችና ደረጃዎች ጋር ለሥነ ሥርዓቱ በሚያመች መንገድ በጥንቃቄ ተስተካክለው የተሠሩ ነበሩ። ከፊት ለፊታቸው ተቀርጸው የተሠሩት ስፍር ቁጥር የሌላቸው ደረጃዎች ብዙ ተመልካቾችን ለመያዝ ይችሉ ነበር።
‘በጣዖት የተሞላ’
ብዙ ቤተ መቅደሶች፣ ሐውልቶችና ታሪካዊ ሕንፃዎች አንድ ላይ ተከማችተው የሚገኙ በመሆናቸው ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ከተማው በጣዖት የተሞላ መሆኑን ሲመለከት በመንፈሱ መበሳጨቱ’ ምንም አያስደንቅም። (ሥራ 17:16) ጳውሎስ በገበያ ስፍራው የተመለከተው ነገር ሳያስደነግጠው አይቀርም። ሄርመስ የተባለው አምላክ የወንድ ብልት ቅርጽ ያላቸው ሐውልቶች በጣም ብዙ በመሆናቸው የሄርመስ በረንዳ እየተባለ በሚጠራው ቦታ እንዲከማቹ ተደርጓል። በሌሎቹ የሄርመስ ቅብ ምስሎች ላይ የሚታዩት ልብሶች የመራባትና የሕይወት ምልክት የሆኑ የስዋስቲካ ምስሎች አሉባቸው። የፆታ ፍቅር እንስት አምላክ የሆነችው የቬኑስ ጄንትሪክስና በወንድ ብልት መልክ የተሠሩ በርካታ መስቀሎችን የያዘው የዳዮኒሰስ ሐውልቶች ይገኙ ነበር። የገበያ ስፍራው “የተቀደሰ” መሆኑን ለማመልከት ወደዚያ የሚገቡ ሁሉ የመንጻት ሥርዓት የሚያከናውኑበት “ቅዱስ” ውኃ የያዘ ሰሃን በወሰኑ ላይ በተተከለ ድንጋይ ላይ ተቀምጦ ይገኝ ነበር።
ይህን የመሰለውን ሥር የሰደደ ሃይማኖታዊ መንፈስ ስንመለከት ጳውሎስ በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ የነበረ መሆኑን በቀላሉ ለመገንዘብ እንችላለን። ‘አዲሶችን አማልክት ያወራል’ ተብሎ ተጠርጥሯል፤ በዚያን ጊዜ የነበረው ሕግ ‘ማንም ሰው የተለዩ ወይም አዲስ አማልክት ሊኖሩት ወይም በሕግ እስካልተፈቀደ ድረስ የተለየ አምላክ በግሉ ሊያመልክ አይችልም’ ይል ነበር። በመሆኑም ሐዋርያው ለጥያቄ ወደ አርዮስፋጎስ መወሰዱ ምንም አያስገርምም።—ሥራ 17:18, 19
የአስተዳደር ማዕከል
ቶሎስ የሚባለው ክብ ሕንፃ የአቴና መንግሥት ዋና መሥሪያ ቤት ነበር። ኃላፊነት ያላቸውን ባለ ሥልጣናት ሁልጊዜ ማግኘት እንዲቻል ሲባል ብዙዎቹ የከተማዋ ሊቃነ መናብርት በዚህ ሕንፃ ውስጥ ያድሩ ነበር። በቶሎስ ውስጥ ደረጃቸው የተወሰነ የክብደት መመዘኛዎችና መለኪያዎች ይገኙ ነበር። የአስተዳደሩ የተለያዩ ክፍሎች የሚሠሩባቸው ሕንፃዎች በአቅራቢያው ይገኙ ነበር። ምክር ቤቱ በቶሎስ በስተ ሰሜን ምዕራብ በሚገኝ ተዳፋት ላይ የተሠራ ነበር። በዚያ ሥፍራ 500 የምክር ቤት አባላት የኮሚቴ ሥራዎችን ለመሥራትና ለሸንጎው የሚቀርቡ ሕግጋትን ለማውጣት ስብሰባዎችን ያደርጋሉ።
በከተማው ውስጥ የሚገኘው ሌላው ዋነኛ ሕንፃ ደግሞ ንጉሣዊው በረንዳ ነው። በዚያም ከከተማዋ ሦስት ዋና ዋና የሕግ ባለ ሥልጣናት አንዱ የሆነው የአቴናው ሰብሳቢ የሕግ ባለ ሥልጣን መቀመጫ ይገኛል። በዚህ ቦታ ሆኖ ሃይማኖታዊና ሕጋዊ ጉዳዮችን የሚመለከቱ በርካታ አስተዳደራዊ ኃላፊነቶችን ያከናውናል። ሶቅራጥስ ለአምላክ ክብር አልሰጠህም ተብሎ በተከሰሰ ጊዜ የተወሰደው ወደዚህ ቦታ ሳይሆን አይቀርም። ከዚህ ሕንፃ ፊት ለፊት በሚገኝ ሌላ ሕንፃ ግድግዳ ላይ ሲወርድ ሲዋረድ የቆየው የአቴንስ ሕግ ተቀርጾ ይገኛል። ዋና ዋናዎቹ የሕግ ባለ ሥልጣናት በየዓመቱ በዚሁ ሕንፃ ፊት ለፊት በሚገኝ አንድ ድንጋይ ላይ ይቆሙና የሥራ ኃላፊነታቸውን በመሀላ ይረከቡ ነበር።
የአትለስ በረንዳ
በገበያ ስፍራው ውስጥ ከሚገኙት ሕንፃዎች ሁሉ በጥሩ ሁኔታ ተጠብቆ የቆየው የአትለስ በረንዳ ነው። የፔርጋመም ንጉሥ አትለስ (በሁለተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ) በሜዲትራኒያን አካባቢ ባሉ አገሮች ውስጥ የነበሩ ሌሎች ብዙ የንጉሣዊ ቤተሰቦች ልጆች ያደርጉት እንደነበረው እሱም በወጣትነት ዘመኑ በአቴንስ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተምሯል። በዙፋኑ ላይ ሲቀመጥ ለተማረባት ከተማ ይህንን የአትለስ በረንዳ በመባል የሚታወቀውን ዕጹብ ድንቅ የሆነ ስጦታ አበርክቷል።
የአትለስ በረንዳ በአብዛኛው ሰዎች ተገናኝተው ሐሳብ የሚለዋወጡበት መጠለያ ያለውና ያሸበረቀ የመንሸራሸሪያ ቦታ ሆኖ ያገለግል ነበር። ወለሎቹና ደረጃዎቹ የበዓል ሥነ ሥርዓቶችን ለመመልከት የሚያስችሉ አመቺ ቦታዎች የነበሯቸው ሲሆን ተወዳጅ የመንሸራሸሪያ ቦታ መሆኑ ደግሞ ሞቅ ያለ ንግድ የሚካሄድበት የገበያ ማዕከል እንዲሆን ያደረገው ይመስላል። መንግሥት ሕንፃውን የገቢ ማግኛ ምንጭ አድርጎ ለመጠቀም ሲል ሱቆቹን ለነጋዴዎቹ ሳያከራይ አይቀርም።
የአትለስ በረንዳ መጀመሪያ የነበረውን መልክ እንዲይዝ ተደርጎ በመታደሱ ድንቅ ለሆነ ጆሜትሪያዊ ንድፍ በአርአያነት የሚጠቀስ ነው። ጠቅላላ መጠኑ፣ ከታችና ከላይ የተሠሩት ዓምዶች ያላቸው ማራኪ ልዩነት፣ ደስ የሚለው የብርሃንና የጥላ ቅንጅት እንዲሁም ሕንፃው የተሠራባቸው ዕቃዎች ጥራትና ውበት ሕንፃውን ዕጹብ ድንቅ አድርገውታል። ሕንፃው አንድ ዓይነት ገጽታ እንዳይኖረው ሲባል የዓምዶቹ ላይኛ ክፍል በሦስት የተለያዩ መንገዶች ማለትም በዶሪያውያን፣ በአዮኒያውያንና በግብጻውያን የአሠራር ስልት ተገንብተዋል።
ባህላዊ እንቅስቃሴዎች የሚደረጉበት ቦታ
በአቴንስ በርካታ ባህላዊ እንቅስቃሴዎች ይካሄዱ የነበሩት በቲያትር አዳራሽ ውስጥ ነበር። ይህ አዳራሽ የሮማው ንጉሠ ነገሥት የአውግስጦስ አማች ከሆነው ከቪፕሳኒየስ አግሪጳ በስጦታነት የተበረከተ ነበር። ከፊት ለፊት ያለው ቦታ የተለያየ ቀለም ባለው እብነ በረድ የተነጠፈ ነበር። አዳራሹ 25 ሜትር ስፋትና 1,000 ሰዎችን የመያዝ አቅም ያለው ሲሆን በመጀመሪያ ሲሠራ ከውስጥ ምንም ድጋፍ በሌለው ጣሪያ የተሸፈነ ነበር። ይህ በጥንቱ ዓለም ከሚታወቁት በድፍረት የተሠሩ ጣሪያዎች ውስጥ አንዱ ነበር! ይሁን እንጂ በዚያ ይቀርብ የነበረው አብዛኛው የመዝናኛ ዓይነት ከፍተኛ የሥነ ምግባር ደረጃ ለነበራቸው እውነተኛ ክርስቲያኖች አጠያያቂ የነበረ ይመስላል።—ኤፌሶን 5:3-5
በጥንት ጊዜያት የነበሩ ተመራማሪ ግለሰቦች የፓንቴኖስን ቤተ መጻሕፍት መጎብኘታቸው አይቀርም። ግድግዳዎቹ በእጅ የተጻፉ የፓፒረስና የብራና ጥቅሎች በሚቀመጡባቸው ቁም ሣጥኖች የተሞሉ ነበሩ። የቤተ መጻሕፍቱ ዋነኛ ክፍል ፊቱ ወደ ምዕራብ ያቀና ሲሆን አንድ ሰው ለመንሸራሸር፣ ለማንበብ ወይም ለማሰላሰል አመቺ የሆነውን መጠለያ በረድፍ በተደረደሩት ዓምዶች በኩል መመልከት ይችላል። የቤተ መጻሕፍቱን ሁለት መመሪያዎች የያዘ አንድ የተቀረጸ ጽሑፍ ተገኝቷል። እነሱም “ምንም መጽሐፍ ይዞ መውጣት አይቻልም” እና “[ቤተ መጻሕፍቱ] ከአንድ ሰዓት እስከ ስድስት ሰዓት ድረስ ክፍት ነው” የሚሉ ነበሩ።
የገበያ ሥፍራው በዛሬው ጊዜ
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአሜሪካ የጥንታዊ ነገሮች ጥናት ትምህርት ቤት አማካኝነት የገበያ ስፍራው ሙሉ በሙሉ ተቆፍሮ ወጥቷል። በአሁኑ ጊዜ ከፍ ባለ ቦታ ላይ ካለው ከአክሮፖሊስ በታች የሚገኝ ሲሆን ስለ ጥንታዊቷ አቴንስ መጠነኛ ግንዛቤ ለማግኘት የሚፈልጉ አገር ጎብኚዎች የሚያዘወትሩት ቦታ ነው።
ከገበያ ስፍራውና ከአክሮፖሊስ ጥቂት ራቅ ብሎ የሚገኘው ሞናስቲራኪ የሚባለው ግልጽ የሆነ የገበያ ቦታ ድንቅ ወደሆነ ሌላ ዓለም ያሸጋግራል። አንድ ጎብኚ አስደናቂና አስደሳች የሆነ የግሪክ ትውፊት፣ የመካከለኛውን ምሥራቅ የባዛር መልክ ያለው እንቅስቃሴና ሰዎች በዋጋ ሲከራከሩ ሊመለከት ይችላል። እንዲሁም ሐዋርያው ጳውሎስ ከ1,900 ዓመታት በፊት ያደርግ እንደነበረው ሁሉ ዛሬም የይሖዋ ምሥክሮች ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን ምሥራች ‘ለሚያገኟቸው ሰዎች’ በደስታ ሲሰብኩ ማየቱ አይቀርም።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አዮናዊ የሚለው ቃል የኖኅ የልጅ ልጅ ከሆነው ከያፌት ልጅ ከያዋን የመጣ ነው።—ዘፍጥረት 10:1, 2, 4, 5
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በአቴንስ ይካሄድ የነበረው ንግድ
አጎራ የአቴና ምሁራዊና ሕዝባዊ ኑሮ ማዕከል ብቻ ሳይሆን የከተማዋ ዋነኛ የገበያ ስፍራ ነበረ። አቴንስ በውጭ ምንዛሪዋ ጥንካሬና ሁሉም የንግድ ልውውጦች በትክክልና በሥርዓት መከናወናቸውን እንዲቆጣጠሩ ሥልጣን በተሰጣቸው የሕግ ባለ ሥልጣኖቿ ጥብቅነት የምትታወቅ የንግድ ማዕከል ሆና ነበር።
አቴንስ ወይን፣ የወይራ ዘይት፣ ማር፣ እብነ በረድ እንዲሁም እንደ ሴራሚክና ከብረት የተሠሩ ቁሳቁሶች ያሉ የኢንዱስትሪ ውጤቶችን ወደ ሌሎች አገሮች ትልክ ነበር። በምትኩም አብዛኛውን ጊዜ ስንዴ ታስመጣ ነበር። አቲካ (በአቴንስ ዙሪያ የሚገኝ ክልል) ነዋሪዎቹን ለመመገብ የሚያስችለውን በቂ ሸቀጣ ሸቀጥ ስለማያመርት የንግዱ መመሪያ ጥብቅ ነበር። በፓይሬስ (የአቴንስ ወደብ) የሚገኘው ገበያ ከተማዋንም ሆነ ጦር ሠራዊቱን ለመመገብ የሚያስችል በቂ የሆነ ትኩስ ምግብ ሁልጊዜ ሊኖረው ይገባ ነበር። ነጋዴዎች የዕቃዎች እጥረት በሚኖርበት ጊዜ አውጥተው በውድ ዋጋ ለመሸጥ ሲሉ ዕቃዎችን እንዲያጠራቅሙ አይፈቀድላቸውም ነበር።