የጥናት ርዕስ 17
በይሖዋ እርዳታ ክፉ መናፍስትን ተቃወሙ
“የምንታገለው . . . በሰማያዊ ስፍራ ካሉ ከክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች ጋር ነው።”—ኤፌ. 6:12
መዝሙር 55 አትፍሯቸው!
የትምህርቱ ዓላማa
1. በኤፌሶን 6:10-13 ላይ እንደተገለጸው ይሖዋ በጥልቅ እንደሚያስብልን ከሚያሳይባቸው መንገዶች መካከል አንዱ ምንድን ነው? አብራራ።
ይሖዋ ለአገልጋዮቹ በጥልቅ እንደሚያስብ ከሚያሳይባቸው መንገዶች መካከል አንዱ ጠላቶቻቸውን እንዲቃወሙ የሚረዳቸው መሆኑ ነው። ቀንደኛ ጠላቶቻችን ደግሞ ሰይጣንና አጋንንቱ ናቸው። ይሖዋ እነዚህን ጠላቶች በተመለከተ ያስጠነቀቀን ከመሆኑም ሌላ እነሱን ለመቋቋም እርዳታ እየሰጠን ነው። (ኤፌሶን 6:10-13ን አንብብ።) የይሖዋን እርዳታ የምንቀበልና ሙሉ በሙሉ በእሱ የምንታመን ከሆነ ዲያብሎስን በመቃወም ረገድ ሊሳካልን ይችላል። እኛም ልክ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ “አምላክ ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ሊቃወመን ይችላል?” ብለን በልበ ሙሉነት መናገር እንችላለን።—ሮም 8:31
2. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?
2 እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ስለ ሰይጣንና ስለ አጋንንቱ ለማወቅ አንጓጓም። በዋነኝነት ትኩረት የምናደርገው ስለ ይሖዋ በመማርና እሱን በማገልገል ላይ ነው። (መዝ. 25:5) ያም ቢሆን ሰይጣን ስለሚያደርጋቸው ነገሮች መሠረታዊ እውቀት ማግኘታችን አስፈላጊ ነው። ለምን? እንዲህ ያለው እውቀት በሰይጣን እንዳንታለል ስለሚረዳን ነው። (2 ቆሮ. 2:11 ግርጌ) ሰይጣንና አጋንንቱ ሰዎችን ለማታለል የሚሞክሩበትን ዋነኛ መንገድ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመረምራለን። በተጨማሪም እነዚህን ጠላቶቻችንን በተሳካ ሁኔታ መቃወም የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።
ክፉ መናፍስት ሰዎችን የሚያሳስቱት እንዴት ነው?
3-4. (ሀ) መናፍስታዊ ድርጊት ምንድን ነው? (ለ) በመናፍስታዊ ድርጊቶች የሚያምኑት ምን ያህል ሰዎች ናቸው?
3 ሰይጣንና አጋንንቱ ሰዎችን ለማታለል የሚሞክሩበት ዋነኛው መንገድ መናፍስታዊ ድርጊት ነው። በመናፍስታዊ ድርጊቶች የሚካፈሉ ግለሰቦች፣ የሰው ልጆች ሊያውቋቸው ወይም ሊቆጣጠሯቸው የማይችሉ ነገሮችን የማወቅ ወይም የመቆጣጠር ችሎታ እንዳላቸው ይናገራሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንዶች በጥንቆላ አሊያም በኮከብ ቆጠራ አማካኝነት ስለ ወደፊቱ ጊዜ ማወቅ እንደሚችሉ ይገልጻሉ። ሌሎች ደግሞ ከሞቱ ሰዎች ጋር መነጋገር የሚችሉ ያስመስላሉ። የአስማት ድርጊቶች የሚፈጽሙና በሌሎች ላይ ድግምት የሚያደርጉ ሰዎችም አሉ።b
4 ለመሆኑ በመናፍስታዊ ድርጊቶች የሚያምኑት ምን ያህል ሰዎች ናቸው? በላቲን አሜሪካና በካሪቢያን ደሴቶች ባሉ 18 አገሮች ላይ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው በጥናቱ ከተካፈሉት መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት በአስማት፣ በጥንቆላ ወይም በመተት ያምናሉ፤ ከዚህ ጋር ተቀራራቢ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ደግሞ ከመናፍስት ጋር መነጋገር እንደሚቻል ያምናሉ። በአፍሪካ ውስጥ በሚገኙ 18 አገሮች ላይም ጥናት ተካሂዶ ነበር። በጥናቱ ከተሳተፉት ሰዎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በጥንቆላ እንደሚያምኑ ተናግረዋል። እርግጥ ነው፣ የምንኖረው የትም ሆነ የት ከመናፍስታዊ ድርጊቶች ለመራቅ ጥረት ማድረግ አለብን። ምክንያቱም ሰይጣን “መላውን ዓለም” ለማሳሳት ቆርጦ ተነስቷል።—ራእይ 12:9
5. ይሖዋ ስለ መናፍስታዊ ድርጊቶች ምን አመለካከት አለው?
5 ይሖዋ “የእውነት አምላክ” ነው። (መዝ. 31:5) በመሆኑም መናፍስታዊ ድርጊቶችን አጥብቆ ይጠላል! እስራኤላውያንን እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን በእሳት የሚያሳልፍ፣ ሟርተኛ፣ አስማተኛ፣ ሞራ ገላጭ፣ ምትሃተኛ፣ ድግምተኛ፣ መናፍስት ጠሪ፣ ጠንቋይ ወይም ሙታን አነጋጋሪ በመካከልህ አይገኝ። ምክንያቱም እነዚህን ነገሮች የሚያደርግ ሰው ሁሉ በይሖዋ ፊት አስጸያፊ ነው።” (ዘዳ. 18:10-12) ክርስቲያኖች ይሖዋ ለእስራኤላውያን የሰጣቸውን ሕጎች እንዲከተሉ አይጠበቅባቸውም። ያም ቢሆን ይሖዋ ስለ መናፍስታዊ ድርጊቶች ያለው አመለካከት እንዳልተቀየረ እናውቃለን።—ሚል. 3:6
6. (ሀ) ሰይጣን በመናፍስታዊ ድርጊቶች አማካኝነት ሰዎችን ለመጉዳት የሚሞክረው እንዴት ነው? (ለ) መክብብ 9:5 እንደሚጠቁመው ሙታንን በተመለከተ እውነታው ምንድን ነው?
6 ይሖዋ ከመናፍስታዊ ድርጊቶች እንድንርቅ ያስጠነቀቀን፣ ሰይጣን በዚህ ዘዴ አማካኝነት ሰዎችን ለመጉዳት እንደሚሞክር ስለሚያውቅ ነው። ሰይጣን በመናፍስታዊ ድርጊቶች ተጠቅሞ፣ ‘የሞቱ ሰዎች በሌላ ዓለም ይኖራሉ’ እንደሚሉት ያሉ ውሸቶችን ያስፋፋል። (መክብብ 9:5ን አንብብ።) በተጨማሪም ሰዎች በፍርሃት እንዲዋጡና ከይሖዋ እንዲርቁ ለማድረግ ይሞክራል። ዓላማው በእነዚህ ድርጊቶች የሚካፈሉ ሰዎች ከይሖዋ ይልቅ በክፉ መናፍስት እንዲታመኑ ማድረግ ነው።
ክፉ መናፍስትን መቃወም የምንችለው እንዴት ነው?
7. ይሖዋ ምን መረጃ ይሰጠናል?
7 ቀደም ሲል እንደተገለጸው ይሖዋ በሰይጣንና በአጋንንቱ እንዳንታለል የሚያስፈልገንን መረጃ ይሰጠናል። ከሰይጣንና ከአጋንንቱ ጋር በምናደርገው ውጊያ አሸናፊ ለመሆን ልንወስዳቸው የምንችላቸውን አንዳንድ እርምጃዎች እስቲ እንመልከት።
8. (ሀ) ክፉ መናፍስት የሚያስፋፏቸውን ውሸቶች መቃወም የምንችልበት ዋነኛው መንገድ ምንድን ነው? (ለ) መዝሙር 146:4 ሰይጣን ስለ ሞቱ ሰዎች የሚናገረውን ውሸት የሚያጋልጠው እንዴት ነው?
8 የአምላክን ቃል አንብቡ እንዲሁም አሰላስሉበት። ክፉ መናፍስት የሚያስፋፏቸውን ውሸቶች መቃወም የምንችልበት ዋነኛው መንገድ ይህ ነው። ጠላትን ለማሸነፍ እንደሚያስችል ስለታም ሰይፍ ሁሉ የአምላክ ቃልም የሰይጣንን ውሸቶች በማጋለጥ የጠላታችንን ጥረቶች ውድቅ ያደርጋል። (ኤፌ. 6:17) ለምሳሌ ያህል፣ የአምላክ ቃል ‘የሞቱ ሰዎች በሕይወት ያሉትን ሊያነጋግሩ ይችላሉ’ የሚለው ትምህርት ውሸት መሆኑን ያጋልጣል። (መዝሙር 146:4ን አንብብ።) በተጨማሪም አስተማማኝ በሆነ መንገድ ስለ ወደፊቱ ጊዜ መናገር የሚችለው ይሖዋ ብቻ እንደሆነ ይገልጻል። (ኢሳ. 45:21፤ 46:10) የአምላክን ቃል አዘውትረን የምናነብና የምናሰላስልበት ከሆነ ክፉ መናፍስት በሚያስፋፏቸው ውሸቶች አንታለልም፤ እንዲያውም ለእነዚህ ውሸቶች ጥላቻ እናዳብራለን።
9. ከመናፍስታዊ ድርጊት ጋር ንክኪ ካላቸው ከየትኞቹ ነገሮች እንርቃለን?
9 ከመናፍስታዊ ድርጊት ጋር ንክኪ ካለው ከማንኛውም ነገር ራቁ። እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በማንኛውም ዓይነት መናፍስታዊ ድርጊት አንካፈልም። ለምሳሌ ያህል፣ ወደ መናፍስት ጠሪዎች አንሄድም፤ አሊያም በሌላ በየትኛውም መንገድ ተጠቅመን የሞቱ ሰዎችን ለማነጋገር አንሞክርም። ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተጠቀሰው፣ ‘ሙታን በሌላ ዓለም እየኖሩ ነው’ በሚለው እምነት ላይ ከተመሠረቱ የቀብር ልማዶች እንርቃለን። በተጨማሪም በኮከብ ቆጠራ ወይም በጥንቆላ አማካኝነት ስለ ወደፊቱ ጊዜ ለማወቅ ጥረት አናደርግም። (ኢሳ. 8:19) እንዲህ ያሉት ድርጊቶች በሙሉ በጣም አደገኛ እንደሆኑ ብሎም ከሰይጣንና ከአጋንንቱ ጋር በቀጥታ ሊያነካኩን እንደሚችሉ እናውቃለን።
10-11. (ሀ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩ አንዳንድ ሰዎች እውነትን ሲያውቁ ምን እርምጃ ወሰዱ? (ለ) 1 ቆሮንቶስ 10:21 እንደሚያሳየው የእነዚህን ክርስቲያኖች ምሳሌ መከተል ያለብን ለምንድን ነው? ይህን ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው?
10 ከምትሃታዊ ድርጊቶች ጋር ግንኙነት ያላቸውን ዕቃዎች አስወግዱ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን በኤፌሶን ይኖሩ ከነበሩ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ በመናፍስታዊ ድርጊቶች ይካፈሉ ነበር። እውነትን ሲማሩ ግን ቆራጥ እርምጃ ወሰዱ። “አስማት ይሠሩ ከነበሩት መካከል ብዙዎች መጽሐፎቻቸውን አንድ ላይ ሰብስበው በማምጣት በሰው ሁሉ ፊት አቃጠሉ።” (ሥራ 19:19) እነዚህ ክርስቲያኖች ክፉ መናፍስትን ለመቃወም የሚያስፈልገውን ማንኛውንም እርምጃ ለመውሰድ አላመነቱም። አስማት ለመሥራት ይጠቀሙባቸው የነበሩት መጻሕፍት ውድ ዋጋ የሚያወጡ ነበሩ። ሆኖም መጻሕፍቱን ለሰዎች ከመስጠት ወይም ከመሸጥ ይልቅ አቃጥለዋቸዋል። እነዚህ ሰዎች ይበልጥ ያሳሰባቸው የመጻሕፍቱ ዋጋ ሳይሆን ይሖዋን ማስደሰታቸው ነበር።
11 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩትን የእነዚህን ክርስቲያኖች ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? ከምትሃታዊ ድርጊቶች ጋር ግንኙነት ያለውን ማንኛውንም ነገር ማስወገዳችን የጥበብ እርምጃ ነው። ይህም የቡዳ መድኃኒቶችን፣ ክታቦችን አሊያም ሰዎች ራሳቸውን ከክፉ መናፍስት ለመጠበቅ ብለው የሚያደርጓቸውን ወይም የሚያሠሯቸውን ነገሮች ማስወገድን ይጨምራል።—1 ቆሮንቶስ 10:21ን አንብብ።
12. ከመዝናኛ ምርጫችን ጋር በተያያዘ ራሳችንን የትኞቹን ጥያቄዎች መጠየቅ እንችላለን?
12 በመዝናኛ ምርጫችሁ ረገድ ጠንቃቆች ሁኑ። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ከምትሃታዊ ድርጊቶች ጋር የተያያዙ መጻሕፍትን፣ መጽሔቶችን ወይም ኢንተርኔት ላይ የሚወጡ ርዕሶችን አነብባለሁ? የማዳምጣቸው ሙዚቃዎች፣ የምመለከታቸው ፊልሞችና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ወይም የምጫወታቸው የቪዲዮ ጨዋታዎች እንዲህ ያለ ይዘት ያላቸው ናቸው? የምዝናናባቸው ነገሮች ከመናፍስታዊ ድርጊቶች ጋር ንክኪ ያላቸው እንዲሁም ስለ ቫምፓየሮች፣ ዞምቢዎች ወይም እነዚህን ስለመሳሰሉ ነገሮች የሚያወሱ ናቸው? አስማትን፣ ድግምትን ወይም ሟርትን ምንም ጉዳት እንደሌለው መዝናኛ አድርገው ያቀርባሉ?’ እርግጥ ነው፣ ምናባዊ የሆኑ ወይም በገሃዱ ዓለም ላይ የሌሉ ነገሮችን የሚያንጸባርቁ መዝናኛዎች ሁሉ ከመናፍስታዊ ድርጊት ጋር የተያያዙ ናቸው ማለት አይደለም። መዝናኛ ስትመርጥ፣ ይሖዋ ከሚጠላው ከማንኛውም ነገር ለመራቅ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። ማናችንም ብንሆን ‘በአምላክ ፊት ንጹሕ ሕሊና ይዘን ለመኖር’ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ እንፈልጋለን።—ሥራ 24:16c
13. ምን ከማድረግ መቆጠብ ይኖርብናል?
13 ስለ አጋንንት የሚገልጹ ታሪኮችን ከማውራት ተቆጠቡ። በዚህ ረገድ ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ መከተል እንፈልጋለን። (1 ጴጥ. 2:21) ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በሰማይ ስለኖረ ስለ ሰይጣንና ስለ አጋንንቱ ብዙ ነገር ያውቃል። ሆኖም እነዚህ ክፉ መናፍስት ስላከናወኗቸው ነገሮች የማውራት ልማድ አልነበረውም። ኢየሱስ የመጣው ስለ ይሖዋ ለመመሥከር እንጂ ስለ ሰይጣን ለማስተዋወቅ አይደለም። እኛም ስለ አጋንንት የሚገልጹ ታሪኮችን ከማውራት በመቆጠብ ኢየሱስን እንምሰል። ‘ልባችንን የሚያነሳሳው መልካም የሆነ ነገር’ ማለትም እውነት እንደሆነ በንግግራችን ማሳየት እንችላለን።—መዝ. 45:1
14-15. (ሀ) ክፉ መናፍስትን ልንፈራቸው የማይገባው ለምንድን ነው? (ለ) በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ለሕዝቡ ጥበቃ እንደሚያደርግ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?
14 ክፉ መናፍስትን አትፍሯቸው። በምንኖርበት ዓለም ውስጥ የተለያዩ መጥፎ ነገሮች ሊደርሱብን ይችላሉ። ድንገተኛ አደጋ፣ ሕመም አልፎ ተርፎም ሞት በሕይወት ውስጥ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ነገሮች ናቸው። ሆኖም እነዚህ ነገሮች እንዲደርሱብን ያደረጉት ክፉ መናፍስት ናቸው ብለን ሁልጊዜ ልንደመድም አይገባም። መጽሐፍ ቅዱስ “መጥፎ ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች” ማንም ሰው ላይ ሊደርሱ እንደሚችሉ ይናገራል። (መክ. 9:11) ደግሞም ይሖዋ ከአጋንንት በላይ ኃይል እንዳለው አሳይቷል። ለምሳሌ፣ ሰይጣን ኢዮብን እንዲገድለው አምላክ አልፈቀደም። (ኢዮብ 2:6) በተጨማሪም በሙሴ ዘመን ይሖዋ በግብፅ ከነበሩት አስማተኛ ካህናት የበለጠ ኃይል እንዳለው አስመሥክሯል። (ዘፀ. 8:18፤ 9:11) ክብር የተላበሰው ኢየሱስም ቢሆን ከይሖዋ ባገኘው ኃይል ተጠቅሞ ሰይጣንንና አጋንንቱን ከሰማይ ወደ ምድር በመወርወር ከእነሱ የላቀ ኃይል እንዳለው አሳይቷል። በቅርቡ ደግሞ እነዚህን ክፉ መናፍስት ወደ ጥልቁ የሚወረውራቸው ሲሆን በዚያ ሳሉ በማንም ላይ ጉዳት ማድረስ አይችሉም።—ራእይ 12:9፤ 20:2, 3
15 በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ለሕዝቡ ጥበቃ እንደሚያደርግ የሚያሳዩ ብዙ ማስረጃዎች አሉ። እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ በመላው ምድር ስለ እውነት እየሰበክንና እያስተማርን ነው። (ማቴ. 28:19, 20) በዚህ መንገድ የዲያብሎስን ክፉ ሥራዎች እናጋልጣለን። ሰይጣን ቢሳካለት ኖሮ፣ የምናደርገውን እንቅስቃሴ በሙሉ ሊያስቆመን እንደሚፈልግ ምንም ጥያቄ የለውም፤ ግን ይህን ማድረግ አይችልም። በመሆኑም ክፉ መናፍስትን ልንፈራቸው አይገባም። “በሙሉ ልባቸው ወደ እሱ ላዘነበሉት ሰዎች ብርታቱን ያሳይ ዘንድ የይሖዋ ዓይኖች በምድር ሁሉ ላይ [እንደሚመላለሱ]” እናውቃለን። (2 ዜና 16:9) ለይሖዋ ታማኝ እስከሆንን ድረስ አጋንንት ዘላቂ የሆነ ጉዳት ሊያደርሱብን አይችሉም።
የይሖዋን እርዳታ የሚቀበሉ የሚያገኙት በረከት
16-17. ክፉ መናፍስትን መቃወም ድፍረት እንደሚጠይቅ የሚያሳይ ተሞክሮ ጥቀስ።
16 ክፉ መናፍስትን መቃወም ድፍረት ይጠይቃል፤ በተለይ ደግሞ አሳቢ የሆኑ ወዳጆቻችንና ዘመዶቻችን የሚቃወሙን ከሆነ ይህን ማድረግ ቀላል አይሆንም። ይሁን እንጂ ይሖዋ እንዲህ ያለ ድፍረት የሚያሳዩትን ሁሉ ይባርካል። በጋና የምትኖረውን ኤሪካ የተባለች እህት ተሞክሮ እንመልከት። ኤሪካ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ስትጀምር የ21 ዓመት ወጣት ነበረች። አባቷ ከመናፍስት ጋር ግንኙነት ባለው አምልኮ ውስጥ ካህን ሆኖ ያገለግላል፤ በመሆኑም ኤሪካ ለአባቷ አማልክት መሥዋዕት ሆኖ የቀረበውን ሥጋ መብላትን በሚያካትት መናፍስታዊ ድርጊት እንድትካፈል ይጠበቅባታል። ኤሪካ እንዲህ ለማድረግ ፈቃደኛ እንዳልሆነች ስትገልጽ ቤተሰቧ አማልክቱን እንደናቀች ሆኖ ተሰማቸው። ቤተሰቧ፣ አማልክቱ ለአእምሯዊና ለአካላዊ ሕመም በመዳረግ ይቀጡናል የሚል ስጋት አድሮባቸው ነበር።
17 በመሆኑም የኤሪካ ቤተሰብ በዚህ ልማድ እንድትካፈል ሊያስገድዷት ሞከሩ፤ እሷ ግን ከቤት መውጣት ቢኖርባትም እንኳ ከአቋሟ ፍንክች አላለችም። ከቤት ስትባረር አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች ከእነሱ ጋር እንድትኖር ዝግጅት አደረጉላት። በዚህ መንገድ ይሖዋ፣ ለኤሪካ አዲስ ቤተሰብ ማለትም እንደ ወንድሞችና እህቶች የሚሆኑላት የእምነት አጋሮች በመስጠት ባርኳታል። (ማር. 10:29, 30) ቤተሰቦቿ ልጃቸው እንዳልሆነች በመግለጽ የካዷትና ንብረቶቿን ያቃጠሉባት ቢሆንም ኤሪካ ለይሖዋ ታማኝ ሆና ተጠመቀች፤ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በዘወትር አቅኚነት እያገለገለች ነው። ኤሪካ የአጋንንት ፍርሃት እንዲያሽመደምዳት አልፈቀደችም። ቤተሰቧን በተመለከተም እንዲህ ብላለች፦ “ቤተሰቤ ይሖዋን ማወቅ የሚያስገኘውን በረከትና አፍቃሪ የሆነውን አምላካችንን ማገልገል የሚሰጠውን ነፃነት እንዲያጣጥሙ በየዕለቱ እጸልያለሁ።”
18. በይሖዋ መታመን ምን በረከቶች ያስገኝልናል?
18 እንዲህ ያለ ከባድ የእምነት ፈተና የሚያጋጥመን ሁላችንም አይደለንም። ያም ቢሆን ሁላችንም ክፉ መናፍስትን መቃወምና በይሖዋ መታመን ይኖርብናል። ይህን ካደረግን ብዙ በረከቶችን እናጭዳለን፤ በሰይጣን ውሸቶችም አንታለልም። በተጨማሪም በአጋንንት ፍርሃት አንርድም። ከሁሉ በላይ ደግሞ ከይሖዋ ጋር ያለንን ወዳጅነት እናጠናክራለን። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ራሳችሁን ለአምላክ አስገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙት፤ እሱም ከእናንተ ይሸሻል። ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል።”—ያዕ. 4:7, 8
መዝሙር 150 ትድኑ ዘንድ አምላክን ፈልጉ
a ይሖዋ ስለ ክፉ መናፍስትና ስለሚያስከትሉት ጉዳት በፍቅር ተነሳስቶ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶናል። ክፉ መናፍስት ሰዎችን የሚያሳስቱት እንዴት ነው? ክፉ መናፍስትን ለመቃወም የትኞቹን እርምጃዎች መውሰድ እንችላለን? ይሖዋ በክፉ መናፍስት እንዳንታለል የሚረዳን እንዴት እንደሆነ በዚህ ርዕስ ላይ እንመረምራለን።
b ተጨማሪ ማብራሪያ፦ መናፍስታዊ ድርጊቶች የሚባሉት ከአጋንንት ጋር ንክኪ ያላቸው ልማዶች ናቸው። እንዲህ ባለው ድርጊት የሚካፈሉ ግለሰቦች፣ የሞቱ ሰዎች መንፈስ በሕይወት መኖሩን እንደሚቀጥልና አብዛኛውን ጊዜ በመናፍስት ጠሪዎች አማካኝነት በሕይወት ካሉት ጋር ለመነጋገር እንደሚሞክር ያምናሉ። መናፍስታዊ ድርጊቶች እንደ ጥንቆላ፣ መተትና ሟርት ያሉትን ነገሮችም ያካትታሉ። አስማት የሚለው ቃል በዚህ ርዕስ ውስጥ የተሠራበት ከምትሃት ጋር ግንኙነት ያላቸውን ድርጊቶች ለማመልከት ነው። በሰዎች ላይ ድግምት ማድረግንና ድግምት ማስፈታትንም ሊያካትት ይችላል። ቃሉ፣ አንዳንዶች ሌሎችን ለማዝናናት ብለው እጃቸውን በፍጥነት በማንቀሳቀስ የሚያሳዩትን ትርዒት አያመለክትም።
c ሽማግሌዎች የመዝናኛ ምርጫን በተመለከተ ሕጎችን የማውጣት ሥልጣን አልተሰጣቸውም። እያንዳንዱ ክርስቲያን ከሚያነባቸውና ከሚመለከታቸው ነገሮች ወይም ከቪዲዮ ጨዋታዎች ጋር በተያያዘ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናውን ተጠቅሞ ውሳኔ ማድረግ አለበት። ጥበበኛ የሆኑ የቤተሰብ ራሶች የቤተሰባቸው መዝናኛ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የማይጋጭ እንዲሆን ጥረት ያደርጋሉ።—jw.org® ላይ የወጣውን “የይሖዋ ምሥክሮች አንዳንድ ፊልሞችን፣ መጻሕፍትን ወይም ዘፈኖችን ይከለክላሉ?” የሚል ርዕስ ተመልከት፤ ስለ እኛ > ብዙ ጊዜ የሚነሱ ጥያቄዎች በሚለው ሥር ይገኛል።
d የሥዕሉ መግለጫ፦ በሰማይ ያለው ኃያሉ ንጉሣችን ኢየሱስ የመላእክትን ሠራዊት ሲመራ።