ቲኪቆስ የታመነው አገልጋይ
ቲኪቆስ በተለያዩ ወቅቶች ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር የተጓዘ ሲሆን የእርሱ መልእክተኛም ሆኖ ሠርቷል። ገንዘብ በአደራ ተሰጥቶትና የበላይ ተመልካችነት ኃላፊነቶችን ተቀብሎ የሚጓዝ መልእክተኛ ነበር። ቅዱሳን ጽሑፎች ሁሉም ክርስቲያኖች ሊኖራቸው የሚገባው ባሕርይ እንደነበረው ማለትም እምነት የሚጣልበት ሰው እንደነበረ ጎላ አድርገው የሚገልጹ በመሆኑ ስለ እርሱ ይበልጥ ማወቅ ሳትፈልግ አትቀርም።
ጳውሎስ “የተወደደ ወንድምና የታመነ አገልጋይ በጌታም አብሮኝ ባሪያ የሆነ” በማለት ስለ ቲኪቆስ ተናግሯል። (ቆላስይስ 4:7) ሐዋርያው፣ ቲኪቆስን በዚህ መንገድ የገለጸው ለምን ነበር?
ለኢየሩሳሌም እርዳታ የማሰባሰብ ተልእኮ
በ55 እዘአ አካባቢ በይሁዳ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች ቁሳዊ እርዳታ መላክ አስፈልጎ ነበር። ጳውሎስ በአውሮፓና በትንሿ እስያ ያሉ ጉባኤዎች የሚለግሱትን እርዳታ ለማሰባሰብ ዝግጅት አደረገ። የእስያ አውራጃ ተወላጅ የሆነው ቲኪቆስ በእርዳታ ተልእኮው ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።
ጳውሎስ ይህ መዋጮ እንዴት መሰብሰብ እንደሚኖርበት መመሪያ ከሰጠ በኋላ የታመኑ ሰዎች የተዋጣውን ገንዘብ ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሄዱ ወይም ከእርሱ ጋር አብረው እንዲሄዱ ሐሳብ አቀረበ። (1 ቆሮንቶስ 16:1-4) ጳውሎስ ከግሪክ ወደ ኢየሩሳሌም የሚወስደውን ረዥም ጉዞ ሲጀምር በርካታ ወንዶች ተከትለውት ነበር። ከእነዚህም መካከል አንዱ ቲኪቆስ ሳይሆን አይቀርም። (ሥራ 20:4) እነዚህ ሰዎች የሚጓዙት ከብዙ ጉባኤዎች በአደራ የተቀበሉትን ገንዘብ ይዘው ስለነበር በዛ ብለው መሄዳቸው እጅግ አስፈላጊ ነበር። ዘራፊዎች በመንገድ ላይ አደጋ ሊጥሉ ስለሚችሉ በዛ ብለው መሄዳቸው ለደህንነታቸው በጣም አስፈላጊ የነበረ ይመስላል።—2 ቆሮንቶስ 11:26
አንዳንዶች ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም ባደረገው ጉዞ አርስጥሮኮስ እና ጥሮፊሞስ አብረውት ስለነበሩ ቲኪቆስና ሌሎች ሰዎችም አብረውት ተጉዘው መሆን አለበት የሚል እምነት አላቸው። (ሥራ 21:29፤ 24:17፤ 27:1, 2) ቲኪቆስ በዚህ የእርዳታ ፕሮግራም ተካፍሎ ስለነበር ግሪክ ውስጥ መዋጮ በማሰባሰቡ ሥራ ከቲቶ ጋር አብሮ የሠራ ‘ወንድም’ ተብሎ ከመጠራቱም በላይ “በዚህ ቸር ሥራ [ከጳውሎስ] ጋር እንዲጓደድ በአብያተ ክርስቲያናት” ተመርጧል። (2 ቆሮንቶስ 8:18, 19፤ 12:18) ቲኪቆስ ያከናወነው የመጀመሪያው ተልእኮ ኃላፊነት የሚጠይቅ ከነበረ ሁለተኛውም ቢሆን ከዚያ ያነሰ እንደማይሆን የተረጋገጠ ነው።
ከሮም ወደ ቆላስይስ
ከአምስት ወይም ከስድስት ዓመታት በኋላ (60-61 እዘአ) ጳውሎስ በሮም ከነበረበት ከመጀመሪያው እስር እንደሚለቀቅ ተስፋ አድርጎ ነበር። በዚህ ጊዜ ቲኪቆስ ከሚኖርበት ቦታ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቆ ከጳውሎስ ጋር ነበር። አሁን ቲኪቆስ ወደ እስያ ተመልሶ የሚሄድበት ጊዜ ደረሰ። ይህም ጳውሎስ በዚያ አካባቢ ለሚኖሩ ክርስቲያን ጉባኤዎች ደብዳቤ ለመላክና ከፊልሞና ኮብልሎ የነበረውን ባሪያ አናሲሞስን መልሶ ወደ ቆላስይስ ለመላክ አጋጣሚ ከፈተለት። በዚህ ጊዜ ቲኪቆስና አናሲሞስ በአሁኑ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆኑትን ቢያንስ ሦስት የሚሆኑ ደብዳቤዎች ለኤፌሶን ክርስቲያኖች፣ ለቆላስይስ ክርስቲያኖችና ለፊልሞና ይዘው ሄዱ። ከዚህም በተጨማሪ አንድ ደብዳቤ ከቆላስይስ 18 ኪሎ ሜትር ራቅ ብሎ ወደሚገኘው ወደ ሎዶቂያ ጉባኤ ተልኮ ሊሆን ይችላል።—ኤፌሶን 6:21፤ ቆላስይስ 4:7-9, 16፤ ፊልሞና 10-12
ቲኪቆስ ተራ ደብዳቤ አመላላሽ አልነበረም። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ቲኪቆስ ስለ እኔ ጉዳይ ሁሉንም ነገር ይነግራችኋል፤ እርሱ ተወዳጅ ወንድም ታማኝ አገልጋይና ከእኔም ጋር በጌታ ሥራ ተባባሪ ነው። እርሱን ወደ እናንተ የላክሁበት ምክንያት ስለ እኛ ሁኔታ እንዲነግራችሁና ልባችሁንም እንዲያጽናና ነው።” በመሆኑም ቲኪቆስ እምነት የሚጣልበት የግል መልእክተኛ ነበር።—ቆላስይስ 4:7, 8 የ1980 ትርጉም
ኢ ራዶልፍ ሪቻርድስ የተባሉ አንድ ምሁር ሲናገሩ ደብዳቤ የሚያደርሰው ግለሰብ “በጽሑፍ ከሰፈረው መልእክት በተጨማሪ በጸሐፊውና መልእክቱ በተላከላቸው ሰዎች መካከል እንደ ድልድይ ሆኖ ያገለግላል። . . . የታመነ መልእክተኛ ያስፈለገበት [አንዱ ምክንያት] ብዙውን ጊዜ ተጨማሪ መረጃዎችን ይዞ ስለሚሄድ ነው። ብዙውን ጊዜ አንድ ደብዳቤ ጸሐፊው በአእምሮው የያዘውን ጉዳይ በአጭሩ የሚገልጽ በመሆኑ ጽሑፉን የሚያደርሰው መልእክተኛ ዝርዝር ጉዳዮችን ለተቀባዮቹ እንዲያብራራ ይጠበቅበታል።” ምንም እንኳ አንድ ደብዳቤ ትምህርቶችንና አጣዳፊ ጉዳዮችን የሚገልጽ ሊሆን ቢችልም ሌሎች ተጨማሪ መረጃዎች የሚተላለፉት በታመነ መልእክተኛ አማካኝነት በቃል ነበር።
ለኤፌሶንና ለቆላስይስ ሰዎች እንዲሁም ለፊልሞና የተጻፉት ደብዳቤዎች ጳውሎስ ስለነበረበት ሁኔታ እምብዛም አይገልጹም። ስለዚህም ቲኪቆስ የግል መልእክቶችን መንገር፣ ጳውሎስ በሮም ስላለበት ሁኔታ መግለጽና ማበረታቻ ለመስጠት ይችል ዘንድ የጉባኤዎቹን ሁኔታ ጠንቅቆ ማወቅ ነበረበት። እንደዚህ ያሉት መልእክቶችና ኃላፊነቶች የሚሰጡት ላኪውን በታማኝነት ሊወክሉ ለሚችሉ ለታመኑ ሰዎች ብቻ ነበር። ቲኪቆስ እንደዚህ ያለ ሰው ነበር።
ራቅ ባሉ ቦታዎች የበላይ ተመልካችነትን ሥራ መፈጸም
ጳውሎስ በሮም ከነበረበት የቁም እስር ከተፈታ በኋላ ከቲኪቆስ ወይም ከአርጢሞን አንዱን በቀርጤስ ደሴት ወደነበረው ወደ ቲቶ ለመላክ አሰበ። (ቲቶ 1:5፤ 3:12) ጳውሎስ ለሁለተኛ ጊዜ በሮም ታስሮ በነበረበት ወቅት (በ65 እዘአ አካባቢ ሳይሆን አይቀርም) ወደ እርሱ የሚመጣውን ጢሞቴዎስን ተክቶ እንዲሠራ ሳይሆን አይቀርም ቲኪቆስን በድጋሚ ወደ ኤፌሶን ላከው።—2 ጢሞቴዎስ 4:9, 12
በዚህ ወቅት ቲኪቆስ ወደ ሁለቱም ቦታዎች ማለትም ወደ ቀርጤስና ወደ ኤፌሶን ይሂድ አይሂድ የሚታወቅ ነገር የለም። ሆኖም እነዚህ መግለጫዎች እስከ ጳውሎስ አገልግሎት ማብቂያ ድረስ ከሐዋርያው የቅርብ ባልደረቦች አንዱ ሆኖ እንደቀጠለ ያሳያሉ። ጳውሎስ በጢሞቴዎስና በቲቶ ምትክ ቲኪቆስን በመላክ ከባድ ኃላፊነት የሚጠይቁና አስቸጋሪ የሆኑ ተልእኮዎች እንዲፈጽም ለማድረግ አስቦ ከነበረ ቲኪቆስ የጎለመሰ ክርስቲያን የበላይ ተመልካች ሆኖ ነበር ማለት ነው። (ከ1 ጢሞቴዎስ 1:3 እና ከቲቶ 1:10-13 ጋር አወዳድር።) ረዥም ጉዞ ለማድረግና ሩቅ ቦታ ሄዶ ለመሥራት ፈቃደኛ መሆኑ ለጳውሎስም ሆነ ለመላው የክርስቲያን ጉባኤ በረከት እንዲሆን አስችሎታል።
በዛሬው ጊዜ ያሉ የራሳቸውን ጥቅም የሚሠዉ ክርስቲያኖች አካባቢያቸው በሚገኝ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ አምላክን በፈቃደኝነት ያገለግላሉ ወይም በሌላ ቦታ የመንግሥቱን ጉዳዮች ለማራመድ ራሳቸውን ያቀርባሉ። በሺህዎች የሚቆጠሩት ደግሞ በሚስዮናዊነትና በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ለማገልገል ወይም በግንባታ ፕሮጄክቶች ውስጥ ዓለም አቀፍ አገልጋይ ሆነው ለመሥራት አለዚያም ደግሞ በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ዋና መሥሪያ ቤት ወይም በቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ ለማገልገል ፈቃደኞች ሆነዋል። ልክ እንደ ቲኪቆስ እነርሱም ጎልተው የማይታዩ ቢሆኑም እምነት የሚጣልባቸው ‘የጌታ አገልጋዮች’ በመሆናቸው በአምላክና በሌሎች ክርስቲያኖች የተወደዱና ‘የታመኑ’ ትጉህ ሠራተኞች ናቸው።