ክርስቲያኖች በማገልገል ደስታ ያገኛሉ
“ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ [“ደስተኛ፣” NW ] ነው።”—ሥራ 20:35
1. በዛሬው ጊዜ ምን ዓይነት መጥፎ ዝንባሌ ተስፋፍቶ ይገኛል? ጎጂ የሆነውስ ለምንድን ነው?
በ1900ዎቹ የመጨረሻ አሥርተ ዓመታት “ሚኢዝም” የሚለው ቃል በተደጋጋሚ ይሰማ ነበር። “ሚኢዝም” “እኔ ልቅደም” የሚል ትርጉም ያዘለ ሲሆን ራስ ወዳድነትንና ስግብግብነትን አጣምሮ የያዘ ለሌሎች አሳቢ ካለመሆን የሚመነጭ ዝንባሌ ነው። በ2000ም ቢሆን ይህ ባሕርይ ይጠፋል ብለን ፈጽሞ አንጠብቅም። “ለመሆኑ ለእኔ የሚጠቅም ምን ነገር አለው?” ወይም “ምን ነገር አገኝበታለሁ?” እንደሚሉት ያሉ ጥያቄዎች ሲቀርቡ ምን ያህል ጊዜ ትሰማለህ? እንዲህ ዓይነቱ የራስ ወዳድነት ዝንባሌ ለደስታ ጠንቅ ነው። ኢየሱስ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ [“ደስተኛ፣” NW ] ነው” ሲል ከገለጸው መሠረታዊ ሥርዓት ፍጹም ተቃራኒ ነው።—ሥራ 20:35
2. መስጠት ደስታ እንደሚያስገኝ የታየው እንዴት ነው?
2 በእርግጥ ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል? አዎን። እስቲ ለአንድ አፍታ ስለ ይሖዋ አምላክ አስብ። ‘የሕይወት ምንጭ’ እርሱ ነው። (መዝሙር 36:9) ደስታና እርካታ እንድናገኝ የሚያስችሉንን ነገሮች ሁሉ ይሰጠናል። በእርግጥም ‘የበጎ ስጦታ ሁሉ የፍጹምም በረከት ሁሉ’ ምንጭ እርሱ ነው። (ያዕቆብ 1:17) “ደስተኛው አምላክ” ይሖዋ ያለማቋረጥ ይሰጣል። (1 ጢሞቴዎስ 1:11 NW ) ሰብዓዊ ፍጥረታቱን ስለሚወድ ብዙ ነገር ሰጥቷቸዋል። (ዮሐንስ 3:16) እስቲ ስለ ሰብዓዊ ቤተሰብም አስብ። ወላጅ ከሆንህ አንድ ልጅ ለማሳደግ ምን ያህል መሥዋዕትነት መክፈል፣ ምን ያህል መስጠት እንደሚጠይቅ ታውቀዋለህ። ልጁ እየከፈልከው ያለኸውን መሥዋዕት ለብዙ ዓመታት አይገነዘብም። የምትከፍለውን መሥዋዕት ሁሉ ከምንም አይቆጥረውም። ሆኖም ያለ ምንም ራስ ወዳድነት በመስጠትህ ልጅህ በጥሩ ሁኔታ ሲያድግ ስትመለከት ደስ ይልሃል። ለምን? ምክንያቱም ልጅህን ትወደዋለህ።
3. ይሖዋንና የእምነት አጋሮቻችንን ማገልገል አስደሳች የሆነው ለምንድን ነው?
3 በተመሳሳይም በፍቅር ተነሳስቶ መስጠት የእውነተኛ አምልኮ መለያ ነው። ይሖዋንና የእምነት አጋሮቻችንን ስለምንወድ እነሱን ማገልገልና ራሳችንን ለእነሱ መስጠት ያስደስተናል። (ማቴዎስ 22:37-39) በራስ ወዳድነት ተነሳስቶ አምላክን የሚያመልክ ሰው ብዙም ደስታ አይኖረውም። በአጸፌታው የሚያገኙትን በማሰብ ሳይሆን ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ፍላጎት ተነሳስተው የሚያገለግሉ ሰዎች በእርግጥ ደስታ ያገኛሉ። ከአምልኮታችን ጋር ግንኙነት ያላቸው አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ እንዴት እንደተሠራባቸው መመርመራችን ይህን ሐቅ ለመገንዘብ ያስችለናል። በዚህና በሚቀጥለው ርእስ ከእነዚህ ቃላት መካከል ሦስቱን እንመረምራለን።
የኢየሱስ ሕዝባዊ አገልግሎት
4. የሕዝበ ክርስትና “ሕዝባዊ አገልግሎት” ምን ይመስላል?
4 በአዲሲቱ ዓለም ትርጉም “ሕዝባዊ አገልግሎት” ተብሎ የተተረጎመ በመጀመሪያው ግሪክኛ ቋንቋ ከአምልኮ ጋር ተዛማጅነት ያለው ሊቱሪያ የተባለ አንድ ቁልፍ ቃል አለ። በሕዝበ ክርስትና የሚጠቀሙበት “ሊተርጂ” a (የአምልኮ ሥነ ሥርዓት) የሚለው ቃል የመጣው ከዚህ ሊቱሪያ ከተባለው ቃል ነው። ይሁን እንጂ ሕዝበ ክርስትና በተለምዶ የምታከናውናቸው የአምልኮ ሥነ ሥርዓቶች ጠቃሚ ሕዝባዊ አገልግሎቶች አይደሉም።
5, 6. (ሀ) በእስራኤል ምን ሕዝባዊ አገልግሎት ይከናወን ነበር? ምንስ ጥቅም ነበረው? (ለ) በእስራኤል ይከናወን የነበረውን ሕዝባዊ አገልግሎት የተካው የትኛው ታላቅ ሕዝባዊ አገልግሎት ነው? ለምንስ?
5 ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ እስራኤል ካህናት ሲገልጽ ከሊቱሪያ ጋር ተዛማጅነት ያለው አንድ ግሪክኛ ቃል ተጠቅሟል። “እያንዳንዱ ካህን . . . እነዚያኑ መሥዋዕቶች ዘወትር እያቀረበ በየቀኑ ቆሞ ያገለግላል [“ሕዝባዊ አገልግሎት (ሊቱሪያ) ያቀርባል፣” NW ]” ሲል ገልጿል። (ዕብራውያን 10:11 የ1980 ትርጉም ) ሌዋውያን ካህናት በእስራኤል በጣም ጠቃሚ የሆነ ሕዝባዊ አገልግሎት ያቀርቡ ነበር። የአምላክን ሕግ ያስተምራሉ እንዲሁም የሕዝቡን ኃጢአት የሚሸፍኑ መሥዋዕቶችን ያቀርባሉ። (2 ዜና መዋዕል 15:3፤ ሚልክያስ 2:7) ካህናቱም ሆኑ ሕዝቡ የይሖዋን ሕግ ሲከተሉ ብሔሩ በአጠቃላይ ደስተኛ ይሆን ነበር።—ዘዳግም 16:15
6 በሕጉ ሥር ሕዝባዊ አገልግሎት ማቅረብ ለእስራኤላውያን ካህናት ትልቅ መብት ነበር። ሆኖም የእስራኤል ብሔር ታማኝ ሳይሆን በመቅረቱ ምክንያት አምላክ ሲተወው ካህናቱ የሚሰጡት አገልግሎት የሚያስገኘው ጥቅምም አከተመ። (ማቴዎስ 21:43) ይሖዋ ታላቁ ሊቀ ካህን ኢየሱስ ሕዝባዊ አገልግሎት የሚያቀርብበት የላቀ ዝግጅት አደረገ። ስለ እሱ እንዲህ የሚል እናነባለን:- “እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለ ሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል።”—ዕብራውያን 7:24, 25
7. ኢየሱስ የሚያከናውነው ሕዝባዊ አገልግሎት ተወዳዳሪ የማይገኝላቸው ጥቅሞችን የሚያስገኝ የሆነው ለምንድን ነው?
7 ኢየሱስ ያለ ምንም ተተኪ ለዘላለም ካህን ሆኖ ይቀጥላል። ስለሆነም ሰዎችን ሙሉ በሙሉ ሊያድን የሚችለው እርሱ ብቻ ነው። ኢየሱስ ይህን ተወዳዳሪ የማይገኝለት ሕዝባዊ አገልግሎት የሚያከናውነው በእጅ በተሠራ ቤተ መቅደስ ውስጥ ሳይሆን በ29 እዘአ ሥራውን በጀመረው ቤተ መቅደስ ማለትም ይሖዋ ባደረገው የላቀ የአምልኮ ዝግጅት ውስጥ ነው። አሁን ኢየሱስ ሰማይ በሚገኘው በዚህ ቤተ መቅደስ ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ በማገልገል ላይ ይገኛል። “እርሱም የመቅደስና የእውነተኛይቱ ድንኳን አገልጋይ [ሊቱርጎስ] ነው፣ እርስዋም በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለች ናት።” (ዕብራውያን 8:2፤ 9:11, 12) ኢየሱስ ከፍ ያለ ቦታ ያለው ቢሆንም እንኳ ‘የሕዝብ አገልጋይ’ ነው። ያለውን ከፍተኛ ሥልጣን የሚጠቀምበት ለመቀበል ሳይሆን ለመስጠት ነው። ይህም ደስታ ያመጣለታል። ምድር ላይ ባሳለፈው ሕይወት እንዲጸና የረዳው ‘በፊቱ ያለ ደስታ’ አንዱ ይህ ነው።—ዕብራውያን 12:1, 2
8. ኢየሱስ የሕጉን ቃል ኪዳን የሚተካ ሕዝባዊ አገልግሎት ያከናወነው እንዴት ነው?
8 የኢየሱስ ሕዝባዊ አገልግሎት ሌላም ዘርፍ አለው። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “አሁን ግን በሚሻል ተስፋ ቃል በተመሠረተ በሚሻል ኪዳን ደግሞ መካከለኛ እንደሚሆን፣ በዚያ ልክ እጅግ የሚሻል አገልግሎት [“ሕዝባዊ አገልግሎት፣” NW ] አግኝቶአል።” (ዕብራውያን 8:6) ሙሴ እስራኤላውያን ከይሖዋ ጋር ለነበራቸው ዝምድና መሠረት ለሆነው ቃል ኪዳን መካከለኛ ነበር። (ዘጸአት 19:4, 5) ኢየሱስ ደግሞ ከተለያየ ብሔር በተውጣጡ በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ለተገነባው አዲስ ብሔር ማለትም ‘ለአምላክ እስራኤል’ መወለድ መሠረት ለሆነው አዲስ ቃል ኪዳን መካከለኛ ሆኖ አገልግሏል። (ገላትያ 6:16፤ ዕብራውያን 8:8, 13፤ ራእይ 5:9, 10) ይህ እንዴት ያለ ድንቅ ሕዝባዊ አገልግሎት ነው! በእርሱ አማካኝነት በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያለው አምልኮ ማቅረብ ከምንችልበት ከኢየሱስ ጋር በመተዋወቃችን ምንኛ ደስተኞች ነን!—ዮሐንስ 14:6
ክርስቲያኖችም ሕዝባዊ አገልግሎት ያቀርባሉ
9, 10. ክርስቲያኖች የሚያቀርቧቸው አንዳንድ የሕዝባዊ አገልግሎት ዓይነቶች ምንድን ናቸው?
9 የኢየሱስን ያህል ከፍ ያለ ሕዝባዊ አገልግሎት ማቅረብ የሚችል ማንም ሰው የለም። ሆኖም ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሰማይ ሽልማታቸውን በሚቀበሉበትና ከኢየሱስ ጋር በሚሆኑበት ጊዜ ነገሥታትና ካህናት በመሆን እሱ በሚያቀርበው ሕዝባዊ አገልግሎት ይካፈላሉ። (ራእይ 20:6፤ 22:1-5) ይሁን እንጂ በምድር ላይ ያሉ ክርስቲያኖችም ሕዝባዊ አገልግሎት ያቀርባሉ፤ በዚህም ከፍተኛ ደስታ ያገኛሉ። ለምሳሌ ያህል በጳለስጢና የምግብ እጥረት በተከሰተ ጊዜ ሐዋርያው ጳውሎስ የደረሰውን ችግር ለማስታገስ በአውሮፓ ካሉ ወንድሞች የተገኘውን እርዳታ በይሁዳ ለሚገኙ አይሁድ ክርስቲያኖች አድርሶ ነበር። ይህ አንድ ራሱን የቻለ ሕዝባዊ አገልግሎት ነው። (ሮሜ 15:27፤ 2 ቆሮንቶስ 9:12) ዛሬም ክርስቲያኖች ወንድሞቻቸው ችግር፣ የተፈጥሮ አደጋ ወይም ሌላ ዓይነት መከራ ሲደርስባቸው አፋጣኝ እርዳታ በመለገስ ተመሳሳይ አገልግሎት ያከናውናሉ።—ምሳሌ 14:21
10 ጳውሎስ እንደሚከተለው ብሎ በጻፈ ጊዜ ሌላ ሕዝባዊ አገልግሎት ጠቅሷል:- “ነገር ግን በእምነታችሁ መሥዋዕትና አገልግሎት ተጨምሬ ሕይወቴ እንኳ ቢፈስ፣ ደስ ብሎኛል ከሁላችሁም ጋር አብሬ ደስ ብሎኛል።” (ፊልጵስዩስ 2:17) ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች የደከመላቸው ድካም በፍቅርና በትጋት የተከናወነ ሕዝባዊ አገልግሎት ነበር። ዛሬም በተለይ መንፈሳዊ ምግብ በተገቢው ጊዜ በማቅረብ ረገድ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ሆነው የሚያገለግሉት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ተመሳሳይ ሕዝባዊ አገልግሎት በማቅረብ ላይ ናቸው። (ማቴዎስ 24:45-47) ከዚህም በላይ በቡድን ደረጃ ‘ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት እንዲያቀርቡ’ እና ‘ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራቸውን የእርሱን በጎነት እንዲናገሩ’ ተልዕኮ የተሰጣቸው “ቅዱሳን ካህናት” ናቸው። (1 ጴጥሮስ 2:5, 9) ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ሲጥሩ እንደ ጳውሎስ ‘ሕይወታቸውን ለማፍሰስ’ እንኳ ፈቃደኞች ከመሆናቸውም በላይ እንዲህ ዓይነት መብት በማግኘታቸው ደስተኞች ናቸው። ‘የሌሎች በጎች’ ክፍል የሆኑት ጓደኞቻቸውም ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማዎቹ ለሰዎች በመንገሩ ሥራ ከጎናቸው ሆነው ድጋፍ ይሰጧቸዋል።b (ዮሐንስ 10:16፤ ማቴዎስ 24:14) ይህ እንዴት ያለ ታላቅና አስደሳች ሕዝባዊ አገልግሎት ነው!—መዝሙር 107:21, 22
ቅዱስ አገልግሎት አቅርቡ
11. ነቢይቱ ሐና ለሁሉም ክርስቲያኖች ግሩም ምሳሌ የምትሆነው እንዴት ነው?
11 በአዲሲቱ ዓለም ትርጉም “ቅዱስ አገልግሎት” ተብሎ የተተረጎመው ከአምልኮታችን ጋር ተዛማጅነት ያለው ሌላኛው ግሪክኛ ቃል ላትሪያ የሚለው ቃል ነው። ቅዱስ አገልግሎት ራሱን የቻለ የአምልኮ ተግባር ነው። ለምሳሌ ያህል የ84 ዓመቷ መበለትና ነቢይት ሐና “በጾምና በጸሎትም ሌሊትና ቀን እያገለገለች [“ቅዱስ አገልግሎት እያቀረበች፣” NW ] [ከላትሪያ ጋር ተዛማጅ የሆነ ግሪክኛ ቃል ነው] ከመቅደስ አትለይም ነበር” ተብሎላታል። (ሉቃስ 2:36, 37) ሐና ወለም ዘለም ሳትል ይሖዋን ታመልክ ነበር። ወጣት፣ አረጋዊ፣ ወንድ፣ ሴት ሳይል ለሁላችንም ግሩም ምሳሌ ናት። ሐና አጥብቃ ትጸልይና ይሖዋን ዘወትር በቤተ መቅደሱ ታመልክ እንደነበረ ሁሉ እኛ የምናቀርበው ቅዱስ አገልግሎትም ጸሎትንና በስብሰባ ላይ መገኘትን ይጨምራል።—ሮሜ 12:12፤ ዕብራውያን 10:24, 25
12. የቅዱስ አገልግሎታችን አብይ ገጽታ ምንድን ነው? ይህም ሕዝባዊ አገልግሎት የሆነውስ እንዴት ነው?
12 ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው ብሎ በጻፈ ጊዜ የቅዱስ አገልግሎታችንን አንዱን አብይ ገጽታ ገልጿል:- “በልጁ ወንጌል በመንፈሴ የማገለግለው [“ቅዱስ አገልግሎት የማቀርበው፣” NW ] እግዚአብሔር ምስክሬ ነውና፤ ምናልባት ብዙ ቆይቼ ወደ እናንተ አሁን እንድመጣ በእግዚአብሔር ፈቃድ መንገዴን እንዲያቀናልኝ እየለመንሁ ሁልጊዜ ስጸልይ ስለ እናንተ ሳላቋርጥ አሳስባለሁ።” (ሮሜ 1:9) አዎን፣ የምሥራቹ ስብከት ይህን ምሥራች ለሚያዳምጡ ሰዎች የሚቀርብ ሕዝባዊ አገልግሎት ብቻ ሳይሆን ለይሖዋ የሚቀርብ አምልኮም ጭምር ነው። ሰሚ ጆሮ አገኘንም አላገኘን የስብከቱ ሥራ ለይሖዋ የሚቀርብ ቅዱስ አገልግሎት ነው። ተወዳጅ ስለሆነው የሰማይ አባታችን ግሩም ባሕርያትና ጠቃሚ ስለሆኑት ዓላማዎቹ ለሌሎች ለመንገር የምናደርገው ጥረት ታላቅ ደስታ እንደሚያመጣልን ምንም ጥርጥር የለውም።—መዝሙር 71:23
ቅዱስ አገልግሎት የምናቀርበው የት ነው?
13. በይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ውስጠኛ አደባባይ ቅዱስ አገልግሎት የሚያቀርቡት ክርስቲያኖች ተስፋቸው ምንድን ነው? እነማን አብረዋቸው ይደሰታሉ?
13 ጳውሎስ ለቅቡዓን ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፎ ነበር:- “የማይናወጥን መንግሥት ስለምንቀበል በማክበርና በፍርሃት እግዚአብሔርን ደስ እያሰኘን የምናመልክበትን [“ቅዱስ አገልግሎት የምናቀርብበትን፣” NW ] ጸጋ እንያዝ።” (ዕብራውያን 12:28) ቅቡዓን ክርስቲያኖች መንግሥቱን እንደሚወርሱ እርግጠኞች ስለሆኑ የማይናወጥ እምነት በመያዝ ልዑሉን አምላክ ያመልካሉ። በመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ቅድስትና በውስጠኛው አደባባይ ሆነው ለይሖዋ ቅዱስ አገልግሎት የሚያቀርቡት እነርሱ ብቻ ሲሆኑ ወደፊት ደግሞ በቅድስተ ቅዱሳኑ ማለትም በሰማይ ከኢየሱስ ጋር ሆነው የሚያገለግሉበትን ጊዜ በናፍቆት ይጠባበቃሉ። የሌሎች በጎች ክፍል የሆኑት ጓደኞቻቸው እነሱ ባላቸው አስደናቂ ተስፋ አብረዋቸው ይደሰታሉ።—ዕብራውያን 6:19, 20፤ 10:19-22
14. እጅግ ብዙ ሰዎች ኢየሱስ ከሚያቀርበው ሕዝባዊ አገልግሎት ተጠቃሚ የሚሆኑት እንዴት ነው?
14 ሌሎች በጎችስ ቅዱስ አገልግሎት የሚያቀርቡት የት ነው? ሐዋርያው ዮሐንስ በዚህ በመጨረሻው ቀን እጅግ ብዙ ሰዎች ብቅ እንዳሉና ‘ልብሳቸውንም አጥበው በበጉ ደም እንዳነጹ’ አስቀድሞ በራእይ ተመልክቷል። (ራእይ 7:14) ይህም ማለት እንደ ቅቡዓን የአምልኮ ጓደኞቻቸው ሁሉ እነሱም በኢየሱስ ሕዝባዊ አገልግሎት፣ ለሰው ዘር ሲል ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን በመስጠት በከፈለው ዋጋ ላይ እምነት እንዳላቸው ያሳያሉ። ‘የይሖዋን ቃል ኪዳን የሚይዙ’ ስለሆኑ ሌሎች በጎችም ከኢየሱስ ሕዝባዊ አገልግሎት ተጠቃሚ ናቸው። (ኢሳይያስ 56:6) እርግጥ ነው፣ የአዲሱ ቃል ኪዳን ተካፋዮች አይደሉም፤ ሆኖም ከዚህ ቃል ኪዳን ጋር የተያያዙትን ሕጎች በመታዘዝና ከዝግጅቶቹ ጋር በመተባበር ይህን ቃል ኪዳን ይይዛሉ። ከአንድ ገበታ በመመገብና ከአባላቱ ጋር አብረው በመሥራት ከአምላክ እስራኤል ጋር ይተባበራሉ፣ አምላክን በሕዝብ ፊት ያወድሳሉ እንዲሁም ደስ የሚያሰኘውን መንፈሳዊ መሥዋዕት ያቀርባሉ።—ዕብራውያን 13:15
15. እጅግ ብዙ ሰዎች ቅዱስ አገልግሎት የሚያቀርቡት የት ነው? ይህ በረከት እነሱን የሚነካውስ እንዴት ነው?
15 ‘እጅግ ብዙ ሰዎች ነጭ ልብስ ለብሰው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆመው’ የታዩት ለዚህ ነው። ከዚህም በተጨማሪ “በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት አሉ፣ ሌሊትና ቀንም በመቅደሱ ያመልኩታል [“ቅዱስ አገልግሎት ያቀርቡለታል፣” NW ] በዙፋኑም ላይ የተቀመጠው በእነርሱ ላይ ያድርባቸዋል።” (ራእይ 7:9, 15) ጥንት በእስራኤል ወደ አይሁድ የተለወጡ ሰዎች በሰሎሞን ቤተ መቅደስ ውጨኛ አደባባይ ሆነው ያመልኩ ነበር። ዛሬም በተመሳሳይ እጅግ ብዙ ሰዎች በመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ውጨኛ አደባባይ ሆነው ይሖዋን ያመልካሉ። በዚያ ማገልገላቸው ያስደስታቸዋል። (መዝሙር 122:1) ከቅቡዓን ጓደኞቻቸው መካከል የመጨረሻው ሰማያዊ ውርሻውን ካገኘ በኋላም እንኳ ቢሆን እንደ ሕዝቦቹ በመሆን ለይሖዋ ቅዱስ አገልግሎት ማቅረባቸውን ይቀጥላሉ።—ራእይ 21:3
ተቀባይነት የሌለው ቅዱስ አገልግሎት
16. ቅዱስ አገልግሎትን በተመለከተ ምን ማስጠንቀቂያዎች ተሰጥተዋል?
16 በጥንት እስራኤል ቅዱስ አገልግሎት ከይሖዋ ሕግ ጋር በሚስማማ መንገድ መቅረብ ነበረበት። (ዘጸአት 30:9፤ ዘሌዋውያን 10:1, 2) ዛሬም በተመሳሳይ የምናቀርበው ቅዱስ አገልግሎት በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ከፈለግን ልናሟላቸው የሚገቡ ብቃቶች አሉ። ጳውሎስ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች እንደሚከተለው ሲል የጻፈው ለዚህ ነው:- ‘የፈቃዱ ትክክለኛ እውቀት፣ ጥበብና መንፈሳዊ ማስተዋል አእምሮን ሁሉ እንዲሞላባችሁ፣ በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁ በእግዚአብሔር ትክክለኛ እውቀት እንድታድጉ ስለ እናንተ መጸለይንና መለመንን አልተውንም።’ (ቆላስይስ 1:9, 10) አምላክ የሚመለክበትን ትክክለኛ መንገድ መወሰን የእኛ ሥራ አይደለም። ትክክለኛ የሆነ ቅዱስ ጽሑፋዊ እውቀት፣ መንፈሳዊ ማስተዋልና አምላካዊ ጥበብ ወሳኝ ነገሮች ናቸው። አለዚያ ነገሮች ሁሉ ሊበላሹ ይችላሉ።
17. (ሀ) በሙሴ ዘመን ይቀርብ የነበረው ቅዱስ አገልግሎት የተበከለው እንዴት ነው? (ለ) በዛሬው ጊዜ ቅዱስ አገልግሎት በተሳሳተ መንገድ ሊቀርብ የሚችለው እንዴት ነው?
17 በሙሴ ዘመን የነበሩትን እስራኤላውያን አስታውሱ። “እግዚአብሔር ግን ዘወር አለ የሰማይንም ጭፍራ ያመልኩ [“ቅዱስ አገልግሎት ያቀርቡ፣” NW ] ዘንድ አሳልፎ ሰጣቸው” የሚል እናነባለን። (ሥራ 7:42) እነዚህ እስራኤላውያን ይሖዋ ለእነሱ ሲል የፈጸማቸውን ተአምራት አይተዋል። ሆኖም ይበጀናል ብለው በማሰብ ወደ ሌሎች አማልክት ዘወር አሉ። ታማኞች ሆነው አልተገኙም፤ የምናቀርበው ቅዱስ አገልግሎት አምላክን እንዲያስደስት ከተፈለገ ታማኝ ሆኖ መገኘት ወሳኝ ነው። (መዝሙር 18:25) እርግጥ ነው፣ ዛሬ ይሖዋን ትተው ከዋክብትን ወይም የወርቅ ጥጃ ወደማምለክ ዞር የሚሉ አይኖሩ ይሆናል፤ ሆኖም ሌላ ዓይነት ጣዖት አለ። ኢየሱስ “ለገንዘብ” ማደርን በተመለከተ ሲያስጠነቅቅ ጳውሎስ ደግሞ መጎምጀትን ጣዖት ሲል ጠርቶታል። (ማቴዎስ 6:24፤ ቆላስይስ 3:5) ሰይጣን ራሱን አምላክ አድርጎ ያቀርባል። (2 ቆሮንቶስ 4:4) እንዲህ ዓይነት የጣዖት አምልኮቶች በጣም ከመስፋፋታቸውም በላይ ወጥመድ ናቸው። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስን እከተላለሁ እያለ ሀብታም መሆንን የሕይወቱ ዋነኛ ግብ ስላደረገ ወይም በራሱና ባለው እውቀት ስለሚመካ ሰው እስቲ አስብ። ይህ ሰው በእርግጥ እያገለገለ ያለው ማንን ነው? ይህ ሰው በይሖዋ ስም እየማሉ እርሱ ያደረገላቸውን ተአምራት ግን ርኩስ የሆኑ ጣዖታት እንደፈጸሙላቸው አድርገው ከሚናገሩ በኢሳይያስ ዘመን ከነበሩ አይሁዳውያን በምን ይለያል?—ኢሳይያስ 48:1, 5
18. ጥንትም ሆነ ዛሬ ቅዱስ አገልግሎት የተሳሳተ ትርጉም የተሰጠው እንዴት ነው?
18 በተጨማሪም ኢየሱስ “የሚገድላችሁ ሁሉ እግዚአብሔርን እንደሚያገለግል [“ቅዱስ አገልግሎት እንደሚያቀርብ፣” NW ] የሚመስልበት ጊዜ ይመጣል” ሲል አስጠንቅቋል። (ዮሐንስ 16:2) በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ የተባለው ሳውል ‘በእስጢፋኖስ መገደል ሲስማማ’ እና ‘የጌታን ደቀ መዛሙርት ለመግደል ሲዝት’ አምላክን እያገለገለ እንዳለ አድርጎ እንዳሰበ ምንም ጥርጥር የለውም። (ሥራ 7:60፤ 9:1) በዛሬው ጊዜ የጎሳ ምንጠራና የዘር ማጥፋት ዘመቻ የሚያካሂዱ አንዳንድ ሰዎችም አምላክን እንደሚያመልኩ ይናገራሉ። ብዙዎች አምላክን እናመልካለን ይበሉ እንጂ የሚያመልኩት የብሔራዊ ስሜት አማልክትን፣ ጎሰኝነትን፣ ሀብትን፣ ራሳቸውን ወይም ሌላ ዓይነት ጣዖትን ነው።
19. (ሀ) ቅዱስ አገልግሎታችንን የምንመለከተው እንዴት ነው? (ለ) ደስታ የሚያስገኝልን ምን ዓይነት ቅዱስ አገልግሎት ነው?
19 ኢየሱስ “ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ [“ለእርሱ ብቻ ቅዱስ አገልግሎት አቅርብ፣” NW ]” ብሏል። (ማቴዎስ 4:10) ይህን የተናገረው ለሰይጣን ቢሆንም ሁላችንም ይህን ምክር ብንከተል ምንኛ ጠቃሚ ነው! ለአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ ቅዱስ አገልግሎት ማቅረብ አስፈሪና ከፍ ያለ መብት ነው። ከአምልኮታችን ጋር በተያያዘ ሕዝባዊ አገልግሎት ስለማቅረብስ ምን ለማለት ይቻላል? እንደ እኛው ያሉ ሰዎችን ለመጥቀም ስንል ይህን አገልግሎት ማከናወናችን ታላቅ እርካታ የሚያስገኝ አስደሳች ሥራ ነው። (መዝሙር 41:1, 2፤ 59:16) ይህ ዓይነቱ አገልግሎት እውነተኛ ደስታ የሚያስገኘው በሙሉ ልብና በትክክለኛው መንገድ ከተከናወነ ብቻ ነው። በእርግጥ አምላክን በተገቢው መንገድ እያመለኩ ያሉት እነማን ናቸው? ይሖዋ የሚቀበለው የእነማንን ቅዱስ አገልግሎት ነው? ከአምልኮታችን ጋር ተዛማጅነት ያለውን ሦስተኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ስንመረምር ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ እናገኛለን። በሚቀጥለው ርእስ ላይ ይህን ቃል እንመረምራለን።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች አንድም ቅዳሴ አሊያም እንደ ሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ቆረባ ያሉ የተወሰኑ ሥነ ሥርዓቶች ናቸው።
b በአንጾኪያ የነበሩ ነቢያትና መምህራን ለይሖዋ “ሕዝባዊ አገልግሎት” (ሊቱሪያ ከተባለው ግሪክኛ ቃል ጋር ዝምድና ያለው ሐረግ ነው) በማቅረብ ላይ እንደነበሩ በሥራ 13:2 ላይ ተገልጿል። ይህ ሕዝባዊ አገልግሎት ለሕዝብ መመስከርንም እንደሚጨምር የታወቀ ነው።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ኢየሱስ የሚያከናውነው ታላቅ ሕዝባዊ አገልግሎት ምንድን ነው?
• ክርስቲያኖች የሚያከናውኑት ሕዝባዊ አገልግሎት ምንድን ነው?
• ክርስቲያናዊ ቅዱስ አገልግሎት ምንድን ነው? የሚከናወነውስ የት ነው?
• ቅዱስ አገልግሎታችን አምላክን እንዲያስደስት ከተፈለገ ምን ማግኘት አለብን?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወላጆች በመስጠት የላቀ ደስታ ያገኛሉ
[በገጽ 12 እና 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያኖች ሌሎችን በሚረዱበትና ምሥራቹን በሚሰብኩበት ጊዜ ቅዱስ አገልግሎት ያቀርባሉ
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የምናቀርበው ቅዱስ አገልግሎት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ከፈለግን ትክክለኛ እውቀትና ማስተዋል ሊኖረን ይገባል