ስለ መንፈስ ማሰብ ሕይወት ያስገኛል!
“ስለ መንፈስ ማሰብ . . . ሕይወት . . . ነው።”—ሮሜ 8:6
1, 2. መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሥጋንና መንፈስን’ የሚያነጻጽረው እንዴት ነው?
የሥጋ ምኞቶችን ማርካትን ከፍ አድርጎ በሚመለከት ብልሹ በሆነ ኅብረተሰብ ውስጥ እየኖሩ በአምላክ ፊት ንጹሕ የሥነ ምግባር አቋም ይዞ መመላለስ ቀላል አይደለም። ይሁን እንጂ ቅዱሳን ጽሑፎች ራስን ኃጢአተኛ ለሆነው ሥጋ ማስገዛት በሚያስከትለው ከባድ መዘዝና ለአምላክ ቅዱስ መንፈስ ማስገዛት በሚያስገኘው በረከት መካከል ያለውን ልዩነት በግልጽ በማስቀመጥ “ሥጋን” እና “መንፈስን” ያነጻጽራሉ።
2 ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ ክርስቶስ “ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው፤ ሥጋ ምንም አይጠቅምም፤ እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስ ነው ሕይወትም ነው” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 6:63) ሐዋርያው ጳውሎስ ለገላትያ ክርስቲያኖች “ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛልና፣ እነዚህም እርስ በርሳቸው ይቀዋወማሉ” በማለት ጽፏል። (ገላትያ 5:17) በተጨማሪም ጳውሎስ “በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳልና፣ በመንፈስ ግን የሚዘራው ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል” በማለት ተናግሯል።—ገላትያ 6:8
3. ከመጥፎ ምኞቶችና ዝንባሌዎች ለመላቀቅ ምን ማድረግ ያስፈልጋል?
3 የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ማለትም አንቀሳቃሽ ኃይሉ ርኩስ የሆኑ ‘የሥጋ ምኞቶችንና’ ኃጢአተኛው ሥጋችን የሚያሳድርብንን አጥፊ ተጽዕኖ ከሥሩ ነቅሎ ሊያስወግድ ይችላል። (1 ጴጥሮስ 2:11) ጳውሎስ “ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፣ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው” በማለት በተናገረው መሠረት መጥፎ ዝንባሌዎችን አሽቀንጥሮ ለመጣል የአምላክን መንፈስ እርዳታ ማግኘቱ እጅግ አስፈላጊ ነው። (ሮሜ 8:6) ስለ መንፈስ ማሰብ ሲባል ምን ማለት ነው?
“ስለ መንፈስ ማሰብ”
4. “ስለ መንፈስ ማሰብ” ማለት ምን ማለት ነው?
4 ጳውሎስ “ስለ መንፈስ ማሰብ” ብሎ በጻፈ ጊዜ “አስተሳሰብ፣ አእምሮን በአንድ ነገር ላይ ብቻ እንዲያተኩር ማድረግ፣ . . . ግብ፣ ምኞት፣ ጥረት” የሚል መልእክት የሚያስተላልፍ የግሪክኛ ቃል ተጠቅሟል። ከዚህ ጋር የሚዛመደው ግስ “ማውጣት ማውረድ፣ በአንድ በተወሰነ መንገድ ማሰብ” የሚል ትርጉም አለው። ስለዚህ ስለ መንፈስ ማሰብ ማለት በይሖዋ አንቀሳቃሽ ኃይል ሥር መሆን፣ ለእሱ ራስን ማስገዛትና በዚያ መመራት ማለት ነው። ይህም የአምላክ ቅዱስ መንፈስ አስተሳሰባችንን፣ ዝንባሌያችንንና ምኞታችንን ሙሉ በሙሉ እንዲቆጣጠረው መፍቀዳችንን ያመለክታል።
5. መንፈስ ቅዱስ ለሚያሳድረው ተጽዕኖ ተገዥ መሆን ያለብን እስከ ምን ድረስ ነው?
5 መንፈስ ቅዱስ ለሚያሳድረው ተጽዕኖ ራሳችንን ምን ያህል ማስገዛት እንዳለብን ጳውሎስ ‘በመንፈስ ስለመገዛት’ በተናገረው ጥቅስ ውስጥ ጠበቅ አድርጎ ገልጾታል። (ሮሜ 7:6) ክርስቲያኖች በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ ባላቸው እምነት መሠረት ከኃጢአት ባርነት ነፃ የወጡ ሲሆን በዚህም የተነሳ ቀደም ሲል እንደ ባሪያ ይገዙለት ለነበረው ለቀድሞ አኗኗራቸው ‘ሞተዋል።’ (ሮሜ 6:2, 11) በዚህ መንገድ በምሳሌያዊ ሁኔታ የሞቱ ሁሉ በአካል ገና ሕያዋን ከመሆናቸውም በላይ ‘ለጽድቅ ባሪያዎች’ ሆነው ክርስቶስን ለመከተል ነፃ ናቸው።—ሮሜ 6:18-20
አስገራሚ ለውጥ
6. ‘ለጽድቅ ባሪያ’ የሆኑ ሰዎች ምን ዓይነት ለውጥ አድርገዋል?
6 ‘ከኃጢአት ባርነት’ ነፃ ወጥቶ ‘የጽድቅ ባሪያ’ በመሆን አምላክን ማገልገል መቻል በእርግጥም አስደናቂ ለውጥ ነው። እንዲህ ያለውን ለውጥ ስላደረጉ ሰዎች ጳውሎስ ሲናገር “በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፣ ተቀድሳችኋል፣ ጸድቃችኋል” በማለት ጽፏል።—ሮሜ 6:17, 18፤ 1 ቆሮንቶስ 6:11
7. ይሖዋ ለነገሮች ያለውን አመለካከት መያዝ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
7 እንዲህ ያለ አስደናቂ ለውጥ ለማድረግ በመጀመሪያ ደረጃ ይሖዋ ለነገሮች ያለውን አመለካከት መማር ይኖርብናል። ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት መዝሙራዊው ዳዊት “አቤቱ፣ መንገድህን አመልክተኝ፣ . . . በእውነትህ ምራኝ፣ አስተምረኝም” በማለት አምላክን ተማጽኗል። (መዝሙር 25:4, 5) ይሖዋ የዳዊትን ልመና እንደሰማ ሁሉ በዛሬው ጊዜ የሚገኙ አገልጋዮቹ ለሚያቀርቡትም ልመና መልስ ይሰጣል። የአምላክ መንገዶችና የእርሱ እውነት ንጹሕና ቅዱስ ስለሆኑ በእነርሱ ላይ ማሰላሰላችን የረከሱ ሥጋዊ ምኞቶችን እንድናረካ በምንፈተንበትም ጊዜ ይረዱናል።
የአምላክ ቃል የሚጫወተው ወሳኝ ሚና
8. መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታችን የግድ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
8 የአምላክ ቃል መጽሐፍ ቅዱስ የእርሱ መንፈስ ውጤት ነው። ስለዚህ ይህ መንፈስ በእኛ ላይ እንዲሠራ ልንፈቅድ የምንችልበት አንዱ ወሳኝ መንገድ ከተቻለ መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበብና ማጥናት ነው። (1 ቆሮንቶስ 2:10, 11፤ ኤፌሶን 5:18) አእምሯችንንና ልባችንን በመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችና መሠረታዊ ሥርዓቶች መሙላታችን በመንፈሳዊነታችን ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን እንድንከላከል ይረዳናል። አዎን፣ ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት እንድንፈጽም ፈተና በሚገጥመን ጊዜ የአምላክ መንፈስ ከአምላክ ፈቃድ ጋር ተስማምተን ለመኖር የወሰድነውን ቁርጥ ውሳኔ ሊያጠናክሩ የሚችሉ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማሳሰቢያዎችንና መመሪያ የሚሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እንድናስታውስ ሊያደርገን ይችላል። (መዝሙር 119:1, 2, 99፤ ዮሐንስ 14:26) ስለዚህም ተታልለን የተሳሳተ ጎዳና አንከተልም።—2 ቆሮንቶስ 11:3
9. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከይሖዋ ጋር የመሠረትነውን ዝምድና ጠብቀን ለማቆየት የወሰድነውን ቁርጥ ውሳኔ የሚያጠነክርልን እንዴት ነው?
9 መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች በሚሰጡት እርዳታ በመታገዝ ቅዱሳን ጽሑፎችን ከልብ በትጋት ማጥናታችንን በቀጠልን መጠን የአምላክ መንፈስ በአእምሯችንና በልባችን ላይ ተጽእኖ ስለሚያሳድር ይሖዋ ላወጣቸው የአቋም ደረጃዎች ያለን አክብሮት እንዲያድግ ያደርጋል። በሕይወታችን ውስጥ የላቀውን ቦታ የሚይዘው ከአምላክ ጋር የመሠረትነው ዝምድና ይሆናል። ፈተና በሚገጥመን ጊዜ በመጥፎ ድርጊት መካፈል ሊያስገኝ ስለሚችለው ደስታ በአእምሯችን ውስጥ አናብሰለስልም። ከዚያ ይልቅ ወዲያው ወደ አእምሯችን ሊመጣ የሚገባው ጉዳይ ለይሖዋ የጸና አቋም መያዝ መሆን ይኖርበታል። ከእርሱ ጋር ለመሠረትነው ዝምድና ያለን ከፍተኛ አድናቆት ይህንን ዝምድና ሊያበላሽ ወይም ሊበጥስ የሚችል ማንኛውንም ዝንባሌ እንድንዋጋ ያነሳሳናል።
“ሕግህን እንደ ምን እጅግ ወደድሁ!”
10. ስለ መንፈስ ለማሰብ የይሖዋን ሕግ መታዘዝ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
10 ስለ መንፈስ ለማሰብ የአምላክ ቃል እውቀት ብቻውን በቂ አይደለም። ንጉሥ ሰሎሞን ስለ ይሖዋ የአቋም ደረጃዎች ጠንቅቆ ያውቅ የነበረ ቢሆንም በሕይወቱ መገባደጃ ላይ ራሱን ከዚያ ጋር አስማምቶ መምራት ሳይችል ቀርቷል። (1 ነገሥት 4:29, 30፤ 11:1-6) እኛም መንፈሳዊ አስተሳሰብ ካለን መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ማወቅ ብቻ ሳይሆን የአምላክን ሕግ በሙሉ ልብ መታዘዝ አስፈላጊ መሆኑንም እንገነዘባለን። ይህም የይሖዋን የአቋም ደረጃዎች በጥንቃቄ መመርመርና እነርሱንም ለመከተል ትጋት የተሞላበት ጥረት ማድረግ ማለት ነው። መዝሙራዊው ይህ ዓይነት ዝንባሌ ነበረው። “ሕግህን እንደ ምን እጅግ ወደድሁ! ቀኑን ሁሉ እርሱ ትዝታዬ ነው” በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 119:97) የአምላክን ሕግ ለመከተል ከልብ የምንጨነቅ ከሆነ አምላካዊ ባሕርያትን ለማንጸባረቅ እንገፋፋለን። (ኤፌሶን 5:1, 2) ለመጥፎ ድርጊት እጃችንን በቀላሉ የምንሰጥ ከመሆን ይልቅ የመንፈስ ፍሬዎችን እናፈራለን እንዲሁም ይሖዋን ለማስደሰት ያለን ምኞት ወራዳ ከሆኑ ‘የሥጋ ሥራዎች’ እንድንርቅ ያደርገናል።—ገላትያ 5:16, 19-23፤ መዝሙር 15:1, 2
11. ዝሙትን የሚከለክለው የይሖዋ ሕግ ለእኛ ጥበቃ መሆኑን እንዴት ልታብራራ ትችላለህ?
11 ለይሖዋ ሕግ የጠለቀ አክብሮትና ፍቅር ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? አንደኛው መንገድ ስለሚያስገኘው ጥቅም በጥንቃቄ መመርመር ነው። የፆታ ግንኙነት በተጋቡ ሰዎች መካከል ብቻ መወሰን እንዳለበት የሚገልጸውን እንዲሁም ዝሙትንና ምንዝርን የሚከለክለውን የአምላክ ሕግ አስብ። (ዕብራውያን 13:4) ይህን ሕግ በመታዘዛችን የሚቀርብን አንዳች ጥሩ ነገር ይኖራልን? አፍቃሪ የሆነው ሰማያዊ አባታችን ጠቃሚ የሆነ ነገር እንዲቀርብን የሚያደርግ ሕግ ያወጣልን? ፈጽሞ እንዲህ አያደርግም! ይሖዋ ለሥነ ምግባር ካወጣቸው የአቋም ደረጃዎች ጋር ተስማምተው የማይኖሩ ብዙ ሰዎች በሕይወታቸው ላይ ምን እየደረሰ እንዳለ ተመልከት። ብዙውን ጊዜ ውርጃ ወደ መፈጸም የሚመራ ያልተፈለገ እርግዝና ያስከትልባቸዋል ወይም ያለ ጊዜውና ደስታ የሌለው ትዳር እንዲመሠርቱ ያደርጋቸዋል። ብዙዎች ያለ ባል ወይም ያለ ሚስት ልጅ እንዲያሳድጉ ይገደዳሉ። ከዚህም በላይ ዝሙት የሚፈጽሙ ሰዎች በፆታ ግንኙነት ለሚተላለፉ በሽታዎች ራሳቸውን ያጋልጣሉ። (1 ቆሮንቶስ 6:18) አንድ የይሖዋ አገልጋይ ዝሙት ቢፈጽም ከፍተኛ የስሜት ሥቃይ ሊደርስበት ይችላል። የሚያሰቃየውን የሕሊና ወቀሳ በውስጡ አምቆ ለመያዝ የሚያደርገው ጥረት እንቅልፍ ሊያሳጣውና የአእምሮ ጭንቀት ሊፈጥርበት ይችላል። (መዝሙር 32:3, 4፤ 51:3) ታዲያ ይሖዋ ዝሙትን የሚከለክል ሕግ የሰጠው ለእኛ ጥበቃ እንደሆነ ከዚህ ለመገንዘብ አንችልም? አዎን፣ የሥነ ምግባር ንጽሕናን ጠብቆ መኖር በእርግጥም ከፍተኛ ጥቅም አለው!
የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት ጸልዩ
12, 13. ኃጢአተኛ በሆኑ ምኞቶች በምንከበብበት ጊዜ መጸለይ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?
12 ስለ መንፈስ ማሰብ ከልብ የመነጨ ጸሎት ማቅረብን ይጠይቃል። ኢየሱስ “ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ፣ በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸው?” በማለት ስለተናገረ የአምላክን መንፈስ እርዳታ መጠየቅ ተገቢ ነው። (ሉቃስ 11:13) በምንጸልይበት ጊዜ ድክመታችንን ለማሸነፍ የመንፈሱ እርዳታ እንደሚያስፈልገን ልንገልጽ እንችላለን። (ሮሜ 8:26, 27) የኃጢአት ምኞቶች ወይም ዝንባሌዎች ተጽእኖ እያሳደሩብን እንዳሉ ከተገነዘብን ወይም አንድ አፍቃሪ የእምነት ባልደረባችን ይህን ጉዳይ ቢያሳውቀን ችግሩን ለይተን በመጥቀስ መጸለይና እነዚህን ዝንባሌዎች እንድናሸንፍ እንዲረዳን አምላክን መጠየቃችን ጥበብ ይሆናል።
13 ይሖዋ ጽድቅ፣ ንጹሕ፣ በጎና ምስጋና በሞላባቸው ነገሮች ላይ እንድናተኩር ሊረዳን ይችላል። “የእግዚአብሔር ሰላም” ልባችንንና የማሰብ ኃይላችንን ይጠብቅልን ዘንድ መማጸናችን ምንኛ የተገባ ነው! (ፊልጵስዩስ 4:6-8) ስለዚህ ‘ጽድቅን፣ ለአምላክ የማደር ባሕርይን፣ እምነትን፣ ፍቅርን፣ ጽናትን፣ የዋህነትን መከታተል’ እንችል ዘንድ ይሖዋ እንዲረዳን እንጸልይ። (1 ጢሞቴዎስ 6:11-14) የሰማያዊ አባታችን እርዳታ ካለን ጭንቀቶችና ፈተናዎች ከቁጥጥራችን በላይ እስከመሆን ደረጃ አይደርሱም። ከዚያ ይልቅ ሕይወታችን አምላክ በሚሰጠው ሰላም የተሞላ ይሆናል።
መንፈሱን አታሳዝኑ
14. የአምላክ መንፈስ ንጹሕ እንድንሆን የሚገፋፋ ኃይል የሆነው ለምንድን ነው?
14 የጎለመሱ የይሖዋ አገልጋዮች “መንፈስን አታጥፉ” የሚለውን የጳውሎስን ምክር በሕይወታቸው ላይ ተግባራዊ ያደርጉታል። (1 ተሰሎንቄ 5:19) የአምላክ መንፈስ ‘የቅድስና መንፈስ’ ስለሆነ ንጹሕ፣ የጠራና የተቀደሰ ነው። (ሮሜ 1:3, 4) ይህ መንፈስ በእኛ ላይ በሚሠራበት ጊዜ ቅዱስ ወይም ንጹሕ እንድንሆን ይገፋፋናል። ለአምላክ ታዛዥ በመሆን በንጹሕ የሕይወት ጎዳና መጓዛችንን እንድንቀጥል ይረዳናል። (1 ጴጥሮስ 1:2) ርኩስ የሆነ ማንኛውም ዓይነት ድርጊት መንፈሱን እንዳቃለልን የሚያሳይ ሲሆን ይህም መጥፎ ውጤት ሊያስከትልብን ይችላል። እንዴት?
15, 16. (ሀ) የአምላክን መንፈስ ልናሳዝን የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) የይሖዋን መንፈስ ከማሳዘን መራቅ የምንችለው እንዴት ነው?
15 ጳውሎስ “ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ” በማለት ጽፏል። (ኤፌሶን 4:30) ቅዱሳን ጽሑፎች የአምላክን መንፈስ ለታመኑ ቅቡዓን ክርስቲያኖች እንደ ማሕተም ወይም ‘ወደፊት ለሚያገኙት ነገር እንደ መያዣ’ አድርገው ይገልጹታል። ይህም የማይሞት ሰማያዊ ሕይወት ነው። (2 ቆሮንቶስ 1:22፤ 1 ቆሮንቶስ 15:50-57፤ ራእይ 2:10) የአምላክ መንፈስ ቅቡዓንንም ሆነ ምድራዊ ተስፋ ያላቸውን ጓደኞቻቸውን የታማኝነት ሕይወት እንዲመሩ ሊመራቸውና ኃጢአተኛ ከሆኑ ሥራዎች እንዲርቁ ሊረዳቸው ይችላል።
16 ሐዋርያው ከውሸት፣ ከስርቆት፣ አሳፋሪ ከሆነ ድርጊትና ከመሳሰሉ ዝንባሌዎች እንድንርቅ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። እንደነዚህ ባሉ ዝንባሌዎች ከተሳብን በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት የተጻፈውን የአምላክ ቃል ምክር የሚቃረን ነገር እናደርጋለን። (ኤፌሶን 4:17-29፤ 5:1-5) የአምላክን መንፈስ በተወሰነ ደረጃ ልናሳዝን እንችላለን። እንዲህ ማድረግ ደግሞ አንፈልግም። ማናችንም ብንሆን የአምላክን ቃል ምክር ችላ ማለት ከጀመርን ሆን ብለን ኃጢአት እንድንሠራና መለኮታዊ ሞገስ ሙሉ ሙሉ እንድናጣ የሚያደርጉ ዝንባሌዎችን ወይም ባሕርያትን ማዳበር ልንጀምር እንችላለን። (ዕብራውያን 6:4-6) አሁን ኃጢአት እየሠራን ባንሆንም እንኳ ወደዚያ አቅጣጫ ልናመራ እንችላለን። መንፈስ ቅዱስ ከሚሰጠው አመራር በሚቃረን ጎዳና መሄዳችንን ከቀጠልን ልናሳዝነው እንችላለን። ከዚህም በተጨማሪ የመንፈስ ቅዱስ ምንጭ የሆነውን ይሖዋን ልንቃወመውና ልናሳዝነው እንችላለን። አምላክን የምንወድ እንደመሆናችን መጠን እንዲህ ማድረግ ፈጽሞ አንፈልግም። መንፈሱን የምናሳዝን እንዳንሆን ከዚያ ይልቅ ስለ መንፈስ ማሰባችንን በመቀጠል ለቅዱስ ስሙ ክብር ማምጣት እንችል ዘንድ የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት እንጸልይ።
ስለ መንፈስ ማሰባችሁን ቀጥሉ
17. ልናወጣቸው የምንችላቸው አንዳንድ መንፈሳዊ ግቦች ምንድን ናቸው? እነዚህ ግቦች ላይ ለመድረስ መጣር ጥበብ የሆነውስ ለምንድን ነው?
17 ስለ መንፈስ ማሰባችንን እንድንቀጥል የሚረዳን አንደኛው መንገድ መንፈሳዊ ግቦችን ማውጣትና እነዚህ ግቦች ላይ ለመድረስ መጣር ነው። የጥናት ልማዳችንን ማሻሻል፣ በስብከቱ ሥራ ያለንን ተሳትፎ ከፍ ማድረግ ወይም የሙሉ ጊዜ የአቅኚነት አገልግሎት፣ የቤቴል አገልግሎት ወይም ሚስዮናዊነት የመሳሰሉ ግቦችን እንደየሁኔታችን ማውጣት እንችላለን። ይህም አእምሯችን በመንፈሳዊ ነገሮች እንዲያዝና ለሰብዓዊ ድክመቶቻችን እንዳንሸነፍ ወይም በዚህ የነገሮች ሥርዓት ተስፋፍተው የሚገኙትን ቁሳዊ ነገሮችንና ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ምኞቶችን ከማሳደድ እንድንቆጠብ ይረዳናል። ኢየሱስ እንደሚከተለው ብሎ ስለተናገረ ይህ በእርግጥም የጥበብ መንገድ ነው:- “ብልና ዝገት በሚያጠፉት ሌቦችም ቈፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ አትሰብስቡ፤ ነገር ግን ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቈፍረው በማይሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ፤ መዝገብህ ባለበት ልብህ ደግሞ በዚያ ይሆናልና።”—ማቴዎስ 6:19-21
18. በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ስለ መንፈስ ማሰብ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
18 መንፈሳዊ ነገሮችን ማሰብና ዓለማዊ ምኞቶችን መቆጣጠር መቻል በዚህ ‘የመጨረሻ ዘመን’ በእርግጥም የጥበብ መንገድ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) እንዲያውም “ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።” (1 ዮሐንስ 2:15-17) ለምሳሌ ያህል አንድ ወጣት የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ግብ አድርጎ ቢከታተል አስቸጋሪ በሆነው የጉርምስና ወይም የወጣትነት ዕድሜው ወቅት እንደ መሪ ሆኖ ሊያገለግለው ይችላል። እንዲህ ያለው ግለሰብ አቋሙን እንዲያላላ የሚያደርጉ ተጽዕኖዎች ቢያጋጥሙት እንኳ በይሖዋ አገልግሎት ምን ነገር ማከናወን እንደሚፈልግ ግልጽ የሆነ እይታ ይኖረዋል። እንዲህ ያለው መንፈሳዊ ሰው ቁሳዊ ነገሮችን ወይም ኃጢአት ያስገኛል የሚባልለትን ማንኛውንም ዓይነት ደስታ ለመከታተል ሲል መንፈሳዊ ግቦችን ገሸሽ ማድረግ ጥበብ የጎደለው እርምጃ ሌላው ቀርቶ ሞኝነት እንደሆነ በሚገባ ያምናል። መንፈሳዊ ዝንባሌ የነበረው ሙሴ “ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን” እንደመረጠ አስታውስ። (ዕብራውያን 11:24, 25) እኛም ወጣትም ሆንን በዕድሜ የገፋን ስለ ኃጢአተኛው ሥጋ ሳይሆን ስለ መንፈስ ማሰባችንን ከቀጠልን ተመሳሳይ ምርጫ እናደርጋለን።
19. ስለ መንፈስ ማሰባችንን ከቀጠልን ምን ጥቅሞችን እናገኛለን?
19 “ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነው” “ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው።” (ሮሜ 8:6, 7) ስለ መንፈስ ማሰባችንን ከቀጠልን በዓይነቱ ልዩ የሆነ ሰላም እናገኛለን። ልባችንና የማሰብ ኃይላችን ኃጢአተኛው ዝንባሌያችን ከሚያሳድርብን ተጽዕኖ ሙሉ በሙሉ የተጠበቀ ይሆናል። መጥፎ ድርጊት እንድንፈጽም የሚገፋፉ ፈተናዎችን በተሻለ መንገድ እንድንቋቋም ያስችለናል። እንዲሁም በሥጋና በመንፈስ መካከል የሚደረገውን የማያባራ ውጊያ እንድንቋቋም መለኮታዊ እርዳታ ይኖረናል።
20. ሥጋና መንፈስ እርስ በርስ በሚያደርጉት ውጊያ ማሸነፍ እንደሚቻል እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
20 ስለ መንፈስ ማሰባችንን በመቀጠል የሕይወትና የመንፈስ ቅዱስ ምንጭ ከሆነው ከይሖዋ ጋር የማይበጠስ ዝምድና ልንመሠርት እንችላለን። (መዝሙር 36:9፤ 51:11) ሰይጣንና ወኪሎቹ ከይሖዋ አምላክ ጋር የመሠረትነውን ዝምድና ለማበላሸት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የላቸውም። እጃችንን ከሰጠንላቸው በመጨረሻ የአምላክ ጠላት እንደምንሆንና ይህም ሞት እንደሚያስከትልብን ስለሚያውቁ አስተሳሰባችንን ለመቆጣጠር ይጥራሉ። ይሁን እንጂ ሥጋና መንፈስ እርስ በርሳቸው በሚያደርጉት በዚህ ጦርነት አሸናፊዎች ልንሆን እንችላለን። ጳውሎስም የገጠመው ይኸው ነበር። ራሱ ስላካሄደው ውጊያ ሲናገር “ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል?” የሚል ጥያቄ በመጀመሪያ አቅርቧል። ከዚያም ደህንነት ሊገኝ እንደሚችል ሲያመለክት “በኢየሱስ ክርስቶስ በጌታችን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን” በማለት ተናግሯል። (ሮሜ 7:21-25) ሰብዓዊ ድክመቶችን ለመቋቋምና ድንቅ የሆነውን የዘላለም ሕይወት ተስፋ በመያዝ ስለ መንፈስ ማሰባችንን እንድንቀጥል የሚያስችል ዝግጅት ስላደረገልን እኛም በክርስቶስ አማካኝነት አምላክን ልናመሰግን እንችላለን።—ሮሜ 6:23
ታስታውሳለህን?
• ስለ መንፈስ ማሰብ ማለት ምን ማለት ነው?
• የይሖዋ መንፈስ በእኛ ላይ እንዲሠራ ልንፈቅድ የምንችለው እንዴት ነው?
• ከኃጢአት ጋር በምናደርገው ውጊያ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት፣ የይሖዋን ሕግ መታዘዝና ወደ እርሱ መጸለይ አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነ አብራራ።
• መንፈሳዊ ግቦችን ማውጣት በሕይወት ጎዳና ላይ መጓዛችንን እንድንቀጥል ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በመንፈሳዊነታችን ላይ የሚሰነዘሩትን ጥቃቶች እንድንቋቋም ይረዳናል
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኃጢአተኛ ምኞቶችን ለማሸነፍ የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት መጸለይ ተገቢ ነው
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መንፈሳዊ ግቦችን ማውጣት ስለ መንፈስ ማሰባችንን እንድንቀጥል ሊረዳን ይችላል