የጎረቤት ፍቅር ማሣየት ይቻላል
ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሳምራዊው ሰው የሰጠው ምሳሌ እውነተኛ የጎረቤት ፍቅር ምን ማለት እንደሆነ አሳይቷል። (ሉቃስ 10:25–37) ኢየሱስ እንደሚከተለው ሲልም አስተምሯል:- “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ። ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትዕዛዝ ይህች ናት። ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፣ እርስዋም:- ባልንጀራህን [ጎረቤትህን አዓት] እንደ ነፍስህ ውደድ የምትለው ናት።” — ማቴዎስ 22:37–39
እንደ ብዙዎቹ ሰዎች ከአንተ የተለየ ጎሣ ያለውን ጎረቤትህን መውደድ አስቸጋሪ ሆኖ ታገኘዋለህን? ይህ የሆነው ምናልባት ከዚህ በፊት ስለተፈጸመ የዘር መድሎና ግፍ የምታውቀው ነገር ስላለ ወይም በራስህ ላይ ስለደረሰብህ ይሆናል። አንተ ወይም የምታፈቅራቸው ወዳጆችህ በሌላ ወገን ሰዎች የጭካኔ ድርጊት ተፈጽሞባችሁ ይሆናል።
አምላክ ከሰጣቸው ትዕዛዛት አንዱ ጎረቤትን መውደድ እንደሆነ ኢየሱስ ስላስታወቀ እንደዚህ ዓይነት ጠንካራ ስሜቶችን ማሸነፍ የሚቻል ነገር መሆን አለበት። እንዲህ ለማድረግ ቁልፉ አምላክና ክርስቶስ ሰዎችን በሚመለከቱበት መንገድ መመልከት ነው። በዚህ ረገድ የኢየሱስንና የጥንት ክርስቲያኖችን ምሳሌ ልብ እንበል።
የኢየሱስ መልካም ምሳሌ
በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት አይሁዳውያን በይሁዳና በገሊላ መካከል ለሚኖሩት ሳምራውያን ጠንካራ የጥላቻ ስሜት ነበራቸው። በአንድ ወቅት አይሁዳውያን ተቃዋሚዎች ኢየሱስን በንቀት “ሳምራዊ እንደ ሆንህ ጋኔንም እንዳለብህ በማለታችን መልካም እንል የለምን?” ሲሉ ጠየቁት። (ዮሐንስ 8:48) አንዳንድ አይሁድ ለሳምራውያን የነበራቸው የጥላቻ ስሜት በጣም የከረረ ከመሆኑ የተነሳ በምኩራቦቻቸው እንኳ ሳይቀር በግልጽ ይረግሟቸውና ሳምራውያንን የዘላለም ሕይወት እንዳይሰጣቸው በየዕለቱ ይጸልዩ ነበር።
ኢየሱስ በወንበዴዎች የተደበደበውን አይሁዳዊ ሰው በመንከባከብ እውነተኛ ጎረቤት መሆኑን ስላስመሰከረው ሳምራዊ ሰው ምሳሌ እንዲሰጥ የገፋፋው በአይሁዶች ውስጥ የተተከለውን የጥላቻ ስሜት ማወቁ እንደሆነ አያጠራጥርም። የሙሴን ሕግ ጠንቅቆ ያውቅ የነበረው ሰው “ባልንጀራዬስ [ጎረቤቴስ አዓት] ማን ነው?” ብሎ ሲጠይቀው ኢየሱስ ምን ብሎ ሊመልስለት ይችል ነበር? (ሉቃስ 10:29) ኢየሱስ በቀጥታ ‘ጎረቤትህ ማለት መሰል አይሁዳዊ ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ሰዎች እንዲያውም ሳምራውያንንም ጭምር ያጠቃልላል’ ብሎ ሊመልስለት ይችል ነበር። ይሁን እንጂ አይሁዳውያን ይህን ለመቀበል አስቸጋሪ ይሆንባቸው ነበር። ስለዚህ ከአንድ ሳምራዊ ምሕረትን ስላገኘ አይሁዳዊ የሚገልጽ ምሳሌ ተናገረ። በዚህ መንገድ ኢየሱስ አይሁዳውያን አድማጮቹን የእውነተኛ ጎረቤት ፍቅር አይሁዳውያን ያልሆኑትንም ይጨምራል ወደሚል መደምደሚያ እንዲደርሱ ረዳቸው።
ኢየሱስ ጸረ ሳምራውያን አቋም አልነበረውም። በአንድ ወቅት በሰማርያ ሲያልፍ ደቀ መዛሙርቱ በአቅራቢያዋ ወደምትገኝ ከተማ ምግብ ለመግዛት ሄደው በነበረበት ጊዜ ከአንድ የውኃ ጉድጓድ አጠገብ ተቀመጠ። አንዲት ሳምራዊት ውኃ ልትቀዳ ስትመጣ “ውኃ አጠጭኝ” አላት። አይሁዳውያን ከሳምራውያን ጋር ምንም ግንኙነት ስለማያደርጉ “አንተ የይሁዳ ሰው ስትሆን ሳምራዊት ሴት ከምሆን ከእኔ መጠጥ እንዴት ትለምናለህ?” አለችው። ከዚያም ኢየሱስ መሰከረላት፤ መሲህ መሆኑን እንኳ ሳይቀር በግልጽ ነገራት። እርሷም ወደ ከተማ በመሄድና ሌሎች ሰዎች እንዲያደምጡት ጠርታ በመምጣት አጸፋውን ምላሽ ሰጠች። ውጤቱስ ምን ሆነ? “ከዚያችም ከተማ የሰማርያ ሰዎች ብዙ አመኑበት።” ኢየሱስ በዘመኑ በነበሩት አይሁዳውያን ዘንድ ተስፋፍቶ በነበረው አስተሳሰብ ባለመመራቱ ውጤቱ እንዴት ያማረ ነበር! — ዮሐንስ 4:4–42
አምላክ አያዳላም
ኢየሱስ በቅድሚያ ‘ለጠፉት የእሥራኤል በጎች’ ይኸውም ለአይሁዳውያን እንዲሰብክ የአምላክ ዓላማ ነበር። (ማቴዎስ 15:24) ይህም በመሆኑ የመጀመሪያዎቹ ተከታዮቹ አይሁዶች ነበሩ። በ33 እዘአ በጰንጠቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስ ከፈሰሰ ከሦስት ዓመታት በኋላ አይሁዳውያን አማኞች ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ ለአሕዛብም እንዲያስፋፉት እንደሚፈልግ ይሖዋ ግልጽ አደረገው።
ሳምራውያንን እንደ ነፍሳቸው መውደዱ ለአይሁዳውያን አእምሮ ከባድ ነበር። ከአይሁዳውያን ጋር የነበራቸው ግንኙነት ከሳምራውያን ያነሰ ለነበረው ላልተገረዙት አሕዛብ የጎረቤት ፍቅር ማሳየቱ ደግሞ ይበልጥ አስቸጋሪ ነበር። ዘ ኢንተርናሽናል ስታንዳርድ ባይብል ኢንሳይክሎፒዲያ አይሁዳውያን ለአሕዛብ በነበራቸው አመለካከት ላይ አስተያየት ሲሰጥ እንዲህ ይላል “በአዲስ ኪዳን ዘመን ጥላቻና ንቀት ተስፋፍቶ እናገኛለን። አሕዛብ እርኩሳን እንደሆኑ ተደርገው ይታዩ ነበር፤ ከእነርሱ ጋር ማንኛውንም ዓይነት ወዳጃዊ ግንኙነት ማድረግ እንደ ኃጢአት ይቆጠር ነበር። ወደ አይሁዲነት እስካልተለወጡ ድረስ የአምላክ ቃል የተነፈጋቸው የአምላክና የሕዝቦቹ ጠላቶች ተደርገው ይታዩ ነበር፤ ተለውጠውም እንኳ እንደ ጥንቱ ሙሉ በሙሉ ተባባሪዎች እንዲሆኑ አይፈቀድላቸውም ነበር። አይሁዳውያን ለእነርሱ ምንም ዓይነት ምክር እንዳይሰጧቸው ተከልክለው ነበር፤ ስለ መለኮታዊ ነገሮች ጥያቄ ካቀረቡ ይረገሙ ነበር።”
የብዙዎች አመለካከት ይህን ይመስል በነበረበት ጊዜ ይሖዋ ለጴጥሮስ ራእይ አሳየውና ‘አምላክ ያነጻውን እርሱ ርኩስ ነው እንዳይል’ ነገረው። ከዚያም አምላክ አሕዛብ ወደነበረው ወደ ቆርኔሌዎስ ቤት መራው። ጴጥሮስ ለቆርኔሌዎስ፣ ለቤተሰቡና ለሌሎች አሕዛብም ስለ ኢየሱስ ምስክርነቱን ሰጠ። ጴጥሮስ እንዲህ አለ:- “እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደሆነ በእውነት አስተዋልሁ።” ጴጥሮስ ገና እየሰበከላቸው እያለ በአዲሶቹ አማኞች ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ። ከዚያም ተጠመቁና ከአሕዛብ የመጀመሪያዎቹ የክርስቶስ ተከታዮች ሆኑ። — ሥራ ምዕራፍ 10
“እንግዲህ ሂዱ ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን . . . ደቀ መዛሙርት አድርጉ” የሚለው የኢየሱስ ትዕዛዝ በሁሉም ቦታዎች ለሚገኙት አይሁዳውያን ብቻ የተወሰነ ሳይሆን አሕዛብንም እንደሚጨምር በመገንዘብ በአሕዛብ ላይ መንፈስ ቅዱስ መውረዱን አይሁዳውያን የነበሩት የኢየሱስ ተከታዩች ተቀበሉት። (ማቴዎስ 28:19, 20 አዓት፤ ሥራ 11:18) በውስጣቸው ሊኖር ይችል የነበረውን ማንኛውንም ጸረ አሕዛብ ስሜት በማሸነፍ በአሕዛብ መካከል ደቀ መዛሙርት ለማድረግ ቅንዓት የተሞላበት የስብከት ዘመቻ አደራጁ። 30 ከማይሞሉ ዓመታት በኋላ ወንጌሉ “ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ የተሰበከ ነው” ሊባል ተችሎ ነበር። — ቆላስይስ 1:23
ይህንን የስብከት ሥራ በግንባር ቀደምትነት ያካሂድ የነበረው ሐዋርያው ጳውሎስ ራሱ ከአይሁድ የመጣ ክርስቲያን ነበር። የክርስቶስ ተከታይ ከመሆኑም በፊት የፈሪሳውያን ሃይማኖት ቡድን ቀናተኛ አባል ነበር። እነርሱ አሕዛብን ብቻ ሳይሆን በራሳቸው ብሔር ውስጥ ያሉትን ተራ ሰዎችንም ያንቋሽሹ ነበር። (ሉቃስ 18:11, 12) ነገር ግን ሐዋርያው ጳውሎስ እነዚያ አመለካከቶች ለሌሎች የጎረቤት ፍቅር ከማሳየት እንዲያግዱት አልፈቀደላቸውም። ከዚህ ይልቅ “የአሕዛብ ሐዋርያ” በመሆን ሕይወቱን በሜድትራንያን አገሮች ሁሉ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ላይ አውሏል። — ሮሜ 11:13
በአገልግሎቱ ወቅት ጳውሎስ በድንጋይ ተወግሯል፣ ተደብድቧል እንዲሁም ታስሯል። (ሥራ 14:19፤ 16:22, 23) እንዲህ ዓይነቱ አስቸጋሪ ተሞክሮ እንዲመረርና ከተወሰኑ ብሔሮችና ጎሳዎች ጋር ጊዜዬን በከንቱ እያጠፋሁ ነው ብሎ እንዲደመድም አድርጎት ነበርን? በፍጹም አላደረገውም። በዘመኑ በነበሩት ብዙ ጎሳዎች መካከል ተሰበጣጥረው የሚገኙ ልበ ቅን የሆኑ ግለሰቦች እንዳሉ ያውቅ ነበር።
አሕዛብ የአምላክን መንገዶች ለመማር ፈቃደኞች መሆናቸውን ሲያይ ጳውሎስ ወደዳቸው። ለምሳሌ ያህል በተሰሎንቄ ለነበሩት ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ነገር ግን ሞግዚት የራስዋን ልጆች እንደምትከባከብ በመካከላችሁ የዋሆች ሆንን፤ እንዲሁም እያፈቀርናችሁ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለማካፈል ብቻ ሳይሆን የገዛ ነፍሳችንን ደግሞ እናካፍላችሁ . . . ነበርና።” (1 ተሰሎንቄ 2:7, 8) እነዚህ ልብን የሚነኩ ቃላት ጳውሎስ ከአሕዛብ የመጡትን የተሰሎንቄ ክርስቲያኖች ከልብ ይወዳቸው እንደነበረና ከእነርሱም ጋር የነበረው መልካም ግንኙነት ያስገኘለትን ደስታ ምንም ነገር እንዲያበላሽበት እንዳልፈቀደ ያሳያሉ።
የጎረቤት ፍቅር በተግባር ሲገለጽ
እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ሁሉ ዛሬም ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር የተጣበቁ ሰዎች ከሁሉም ዓይነት ዘር ለመጡ ሰዎች የጎረቤት ፍቅር ይኮተኩታሉ። ለሌሎች ሰዎች አምላክ ያለውን ዓይነት አመለካከት በመያዝና የመንግሥቱን ወንጌል ለእነርሱ በማካፈል እውነተኛ ክርስቲያኖች ፈጽሞ ስለማያውቋቸው ሰዎች የነበራቸውን ዕውቀት አስፍተዋል። ለእነርሱ ወንድማዊ ፍቅርም አላቸው። (ዮሐንስ 13:34, 35) ይህ ነገር ባንተም ላይ ደርሶ ልትመለከት ትችላለህ።
ምንም እንኳ የይሖዋ ምስክሮች “ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም” የተውጣጡና በ229 አገሮች የሚገኙ ቢሆኑም በመካከላቸው እንደዚህ ዓይነቱ ፍቅር ይገኛል። (ራእይ 7:9) ምድር አቀፍ የወንድማማች ማኅበር እንደመሆናቸው መጠን ለይሖዋ በሚሰጡት አምልኮ፣ በጎሳ ግጭቶችና ቅራኔዎች ለመግባት እምቢተኞች በመሆናቸው እንዲሁም ለመሰል ሰብዓዊ ፍጡራን ላላቸው የሞቀ ወዳጅነት ዕንቅፋት ሊሆንባቸው የሚችለውን ሰውን ያለ ምክንያት የመጥላትን ስሜት በማስወገዳቸው አንድ ሆነዋል።
ከይሖዋ ምስክሮች ጋር ብትሰበሰብ ከተለያዩ ጎሳዎች የመጡ ሰዎች እንዴት የአምላክን ፈቃድ እንደሚፈጽሙ ታስተውላለህ። የአምላክን መንግሥት ወንጌል በማወጅ የጎረቤትን ፍቅር በተግባር ሲገልጹ ታያለህ። አዎን፤ በጉባኤዎቻቸው ደግና ጎረቤቶቻቸውን መውደድ በእርግጥ የተማሩ ሰዎች መሆናቸውን በሕይወታቸው የሚያሳዩ ቅን ሰዎችን ታገኛለህ።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በይሖዋ ምስክሮች ጉባኤዎች ውስጥ ከሁሉም ዘሮች የመጡ ደስተኛ ሕዝቦች ታገኛለህ
[ምንጭ]
Arrival of the Good Samaritan at the Inn/The Dore Bible Illustrations /Dover Publications, Inc.