የአንባብያን ጥያቄዎች
መጽሐፍ ቅዱስ በወንጀለኞች ላይ ስለሚበየን የሞት ፍርድ ምን ይላል?
ሁላችንም ባሳለፍነው ተሞክሮና የኑሮ ሁኔታ ምክንያት የየራሳችን አስተያየት ሊኖረን ይችላል። ሆኖም የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን በዚህ ጉዳይ ብዙዎች ከሚወስዱት ፖለቲካዊ አቋም ገለልተኞች በመሆን አምላክ ወንጀለኞችን በሞት ስለመቅጣት ካለው አሳብ ጋር ለመስማማት መሞከር ይኖርብናል።
በአጭር አነጋገር አምላክ ወንጀለኞችን በሞት መቅጣት ስህተት ነው የሚል በቃሉ ውስጥ አላሰፈረም።
በዘፍጥረት ምዕራፍ 9 ላይ እንደምናነበው ይሖዋ ገና በሰው ልጆች ታሪክ መጀመሪያ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለውን አመለካከት ገልጿል። ይህ ታሪክ የሚገልጸው የመላው የሰው ዘር ቅድመ አያቶች ስለሆኑት ስለ ኖኅና ቤተሰቡ ነው። ከመርከብ ከወጡ በኋላ አምላክ እንስሳትን ካረዱና ደማቸውን ካፈሰሱ በኋላ ሊመገቧቸው እንደሚችሉ ነገራቸው። ከዚያም ዘፍጥረት 9:5, 6 ላይ አምላክ እንዲህ አላቸው:- “ነፍሳችሁ ያለችበትን ደማችሁን በእርግጥ እሻዋለሁ፤ ከአራዊት ሁሉ እጅ እሻዋለሁ፤ ከሰውም እጅ፣ ከሰው ወንድም እጅ፣ የሰውን ነፍስ እሻለሁ። የሰውን ደም የሚያስስ ሁሉ ደሙ ይፈስሳል፤ ሰውን በእግዚአብሔር መልክ ፈጥሮታልና።” ስለዚህ ነፍሰ ገዳዮች በሞት እንዲቀጡ ይሖዋ ፈቅዷል።
እስራኤላውያን የአምላክ ሕዝቦች በነበሩባቸው ዘመናት መለኮታዊውን ሕግ የሚፃረሩ የተለያዩ ከባድ ወንጀሎች በሞት ያስቀጡ ነበር። በዘኁልቁ 15:30 ላይ የሚከተለውን አጠቃላይ ድንጋጌ እናገኛለን:- “የአገር ልጅ ቢሆን ወይም መጻተኛ ቢሆን፣ አንዳች በትዕቢት የሚያደርግ ሰው እግዚአብሔርን ሰድቦአል፤ ያም ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጠፋል።”
የክርስቲያን ጉባኤ ከተቋቋመ በኋላስ? ይሖዋ ሰብዓዊ መንግሥታት እንዲኖሩና የበላይ ባለ ሥልጣኖችም እንዲሆኑ እንደፈቀደ እናውቃለን። እንዲያውም ክርስቲያኖች እነዚህን መንግሥታዊ ባለ ሥልጣኖች እንዲታዘዙ አጥብቆ ከመከረ በኋላ እንዲህ ይላል:- “ለመልካም ነገር ለአንተ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና። በከንቱ ግን ሰይፍ አይታጠቅምና ክፉ ብታደርግ ፍራ፤ ቊጣውን ለማሳየት ክፉ አድራጊውን የሚበቀል የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና።”— ሮሜ 13:1-4
ታዲያ እንዲህ ሲል መንግሥታት ከባድ በደል የፈጸሙ ወንጀለኞችን ሕይወት ለማጥፋት ሥልጣን አላቸው ማለት ነውን? በ1 ጴጥሮስ 4:15 ላይ ከሰፈሩት ቃላት በመነሳት አዎን ብለን ልንደመድም እንችላለን። በዘገባው ላይ ሐዋርያው ወንድሞቹን እንዲህ ብሎ አጥብቆ መክሯቸዋል:- “ከእናንተ ማንም ነፍሰ ገዳይ ወይም ሌባ ወይም ክፉ አድራጊ እንደሚሆን ወይም በሌሎች ጉዳይ እንደሚገባ ሆኖ መከራን አይቀበል።” “ከእናንተ ማንም ነፍሰ ገዳይ . . . ሆኖ መከራን አይቀበል” የሚለውን ቃል አስተዋላችሁ? ጴጥሮስ መንግሥታት ነፍሰ ገዳይ የሆነን ሰው የመቅጣት ሥልጣን እንደሌላቸው አላመለከተም። ከዚህ ይልቅ ነፍሰ ገዳይ የሆነ ሰው የሚገባውን ቅጣት ማግኘቱ ትክክል መሆኑን አመልክቷል። ታዲያ እንዲህ ዓይነቱ ቅጣት የሞት ቅጣትን ይጨምራልን?
ሊጨምር ይችላል። ሥራ ምዕራፍ 25 ላይ የሚገኙት የጳውሎስ ቃላት ይህን በግልጽ ያሳያሉ። አይሁዳውያን ጳውሎስን ሕጋችንን ተላልፏል ብለው ከሰውት ነበር። ወታደራዊው አዛዥ እስረኛው የሆነውን ጳውሎስን ወደ ሮማዊው ገዥ በላከው ጊዜ ሥራ 23:29 ላይ የሚከተለውን ሪፖርት ጨምሮ ልኮ ነበር:- “በሕጋቸውም ስለ መከራከር እንደ ከሰሱት አገኘሁ እንጂ ለሞት ወይም ለእስራት የሚያደርስ ክስ አይደለም።” ከሁለት ዓመት በኋላ ጳውሎስ ፊስጦስ በተባለው አገረ ገዥ ፊት ቀረበ። ሥራ 25:8 ላይ እንዲህ እናነባለን:- “ጳውሎስም ሲምዋገት:- የአይሁድን ሕግ ቢሆን መቅደስንም ቢሆን ቄሣርንም ቢሆን አንዳች ስንኳ አልበደልሁም አለ።” ሆኖም ከዚህ በኋላ የሞት ቅጣትን ጨምሮ ስለ ቅጣት ምን እንደተናገረ ልብ እንበል። ሥራ 25:10, 11 እንዲህ ይላል:-
“ጳውሎስ ግን:- እፋረድበት ዘንድ በሚገባኝ በቄሣር ፍርድ ወንበር ፊት ቆሜአለሁ። አንተው ደግሞ ፈጽመህ እንደምታውቅ አይሁድን ምንም አልበደልሁም። እንግዲህ በድዬ ወይም ሞት የሚገባውን ነገር አድርጌ እንደ ሆነ ከሞት ልዳን አልልም፤ እነዚህ የሚከሱኝ ክስ ከንቱ እንደ ሆነ ግን ለእነርሱ አሳልፎ ይሰጠኝ ዘንድ ማንም አይችልም፤ ወደ ቄሣር ይግባኝ ብዬአለሁ አለ።”
ጳውሎስ በሕግ በተሾመ ባለ ሥልጣን ፊት ቀርቦ ቄሣር ወንጀለኞችን በሞት እንኳን ሳይቀር የመቅጣት ሥልጣን እንዳለው አምኗል። ራሱም ቢሆን በደለኛ ሆኖ ከተገኘ የሚሰጠውን ቅጣት እንደማይቀበል ወይም ቄሣር የሞት ቅጣት መበየን የሚገባው ለነፍሰ ገዳዮች ብቻ እንደሆነ አላመለከተም።
የሮማውያን የፍትሕ ሥርዓት ፍጹም ወይም ምንም ዓይነት እንከን የሌለበት እንዳልነበረ የታወቀ ነው። ዛሬም ቢሆን ሰብዓዊ ፍርድ ቤቶች ፍጹማን አይደሉም። ጥንትም ሆነ ዛሬ ንጹሐን ሰዎች በሐሰት ተወንጅለው ተቀጥተዋል። ጲላጦስ እንኳን ስለ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “ለሞት የሚያደርሰው በደል አላገኘሁበትም፤ ስለዚህ ቀጥቼ እፈታዋለሁ።” አዎን፣ ምንም እንኳን የመንግሥት ባለ ሥልጣኑ ኢየሱስ ምንም በደል ያልፈጸመ መሆኑን ቢያምንም ይህን በደል ያልፈጸመ ሰው አለአግባብ ተገድሏል።— ሉቃስ 23:22-25
ይሁን እንጂ ጳውሎስም ሆነ ጴጥሮስ እንደነዚህ ያሉትን የፍትሕ ጉድለቶች በመመልከት የሞት ቅጣት አግባብ አይደለም ወይም ከሥነ ምግባር ውጭ ነው ብለው አልተከራከሩም። አምላክ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለው አመለካከት የቄሣር የበላይ ባለ ሥልጣኖች እስከኖሩ ድረስ ‘ክፉ አድራጊዎችን ለመቅጣት ሰይፍ ይታጠቃሉ’ የሚል ነው። ይህም የሞት ቅጣት ለማስፈጸም ሰይፍ መጠቀምን ይጨምራል። ይሁን እንጂ በዚህ ዓለም ያለ ማንኛውም መንግሥት የሞት ፍርድ የማስፈጸም መብት ያለው መሆኑን ወይም አለመሆኑን በሚመለከት እውነተኛ ክርስቲያኖች በጥንቃቄ ገለልተኝነታቸውን ይጠብቃሉ። ከሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት በተለየ መንገድ በዚህ ጉዳይ ላይ በሚደረገው ውዝግብ ውስጥ አይገቡም።