መንፈስ የሚለውን ስሙ
“ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ ብትል ጆሮችህ በኋላህ:- መንገዱ ይህች ናት በእርስዋም ሂድ የሚለውን ቃል ይሰማሉ።”—ኢሳይያስ 30:21
1, 2. ይሖዋ በታሪክ ዘመናት ሁሉ ለሰዎች መልእክት ሲያስተላልፍ የቆየው እንዴት ነበር?
በፖርቶሪኮ ደሴት በዓለም ትልቁና ከፍተኛ ኃይል ያለው የራዲዮ ቴሌስኮፕ ይገኛል። ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ሳይንቲስቶች ይህን ግዙፍ መሣሪያ በመጠቀም ከሌሎች ዓለማት የሚመጡ መልእክቶችን ለመቀበል ሲጠባበቁ ኖረዋል። ይሁን እንጂ ምንም ዓይነት መልእክት አልደረሳቸውም። ሆኖም ሁላችንም የተወሳሰበ መሣሪያ መጠቀም ሳያስፈልገን በማንኛውም ጊዜ ልንቀበላቸው የምንችል ከሰው ልጆች ዓለም ውጭ የሚመጡ ግልጽ መልእክቶች አሉ። እነዚህ መልእክቶች የሚመጡት ማናችንም ልንገምተው ከምንችለው በላይ በጣም ሩቅ ከሆነ ቦታ ነው። እነዚህን መልእክቶች የሚያሰራጨው ማን ነው? መልእክቶቹን የሚቀበሉት እነማን ናቸው? መልእክቶቹ የሚናገሩትስ ስለ ምን ነገር ነው?
2 ሰዎች መለኮታዊ ምንጭ ያላቸው መልእክቶችን የሰሙበት አጋጣሚዎች እንዳሉ የሚገልጹ በርካታ ዘገባዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛሉ። አንዳንዶቹ መልእክቶች የተላኩት የአምላክ መልእክተኞች ሆነው በሚያገለግሉ መንፈሳዊ ፍጡራን አማካኝነት ነው። (ዘፍጥረት 22:11, 15፤ ዘካርያስ 4:4, 5፤ ሉቃስ 1:26-28) በሦስት የተለያዩ ጊዜያት የይሖዋ ድምፅ ተሰምቷል። (ማቴዎስ 3:17፤ 17:5፤ ዮሐንስ 12:28, 29) በተጨማሪም አምላክ በነቢያት በኩል የተናገረ ሲሆን ብዙዎቹም በመንፈስ አነሳሽነት እንዲናገሩ የተሰጧቸውን መልእክቶች በጽሑፍ አስፍረዋቸዋል። ዛሬ መጽሐፍ ቅዱስ በእጃችን የሚገኝ ሲሆን ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹን መልእክቶችም ሆነ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ያስተማሯቸውን ትምህርቶች በውስጡ ይዞልናል። (ዕብራውያን 1:1, 2) በእርግጥም ይሖዋ ለሰብዓዊ ፍጡሮቹ መልእክት ሲያስተላልፍ ቆይቷል።
3. የአምላክ መልእክቶች ዓላማ ምንድን ነው? ከእኛስ የሚጠበቀው ነገር ምንድን ነው?
3 በመንፈስ አነሳሽነት የተነገሩት እነዚህ ከአምላክ የተላኩ መልእክቶች ስለ ግዑዙ ጽንፈ ዓለም ብዙም የሚናገሩት ነገር የለም። ትኩረታቸውን ያደረጉት አሁን ባለንና ወደፊት በሚኖረን ሕይወት ላይ ተጽዕኖ በሚያሳድሩ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮች ላይ ነው። (መዝሙር 19:7-11፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:8) ይሖዋ በእነዚህ መልእክቶች አማካኝነት ፈቃዱን ያስተላልፋል እንዲሁም መመሪያዎቹን ይሰጠናል። ነቢዩ ኢሳይያስ የተናገራቸው ቃላት ፍጻሜያቸውን እያገኙ ያሉበት አንዱ መንገድ ይህ ነው:- “ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ ብትል ጆሮችህ በኋላህ:- መንገዱ ይህች ናት በእርስዋም ሂድ የሚለውን ቃል ይሰማሉ።” (ኢሳይያስ 30:21) ይሖዋ ‘ቃሉን’ እንድንሰማ አያስገድደንም። መመሪያውን መከተልና በመንገዱ መሄድ ለእኛ የተተወ ነገር ነው። በዚህም ምክንያት ቅዱሳን ጽሑፎች ይሖዋ የሚያስተላልፋቸውን መልእክቶች እንድንሰማ አጥብቀው ይመክሩናል። በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ‘መንፈሱ የሚለውን ስሙ’ የሚለው ማበረታቻ ሰባት ጊዜ ሰፍሮ ይገኛል።—ራእይ 2:7, 11, 17, 29፤ 3:6, 13, 22
4. በአሁኑ ጊዜ አምላክ ከሰማይ በቀጥታ ከእኛ ጋር ይነጋገራል ብሎ መጠበቁ ምክንያታዊ ነውን?
4 ዛሬ ይሖዋ ከሰማይ በቀጥታ አያነጋግረንም። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን እንኳን ሳይቀር በዚህ መልኩ ከሰማይ መልእክቶች ይመጡ የነበረው አልፎ አልፎ ሲሆን አንዳንዶቹም በመቶ ዘመናት በሚቆጠር የጊዜ ልዩነት ውስጥ የተነገሩ ናቸው። ባለፉት የታሪክ ዘመናት ሁሉ ይሖዋ ለሕዝቡ መልእክቱን ያስተላልፍ የነበረው አብዛኛውን ጊዜ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ነው። በእኛ ጊዜም ቢሆን ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። በዛሬው ጊዜ ይሖዋ መልእክቱን ለእኛ የሚያስተላልፍባቸውን ሦስት መንገዶች እንመልከት።
“ቅዱስ ጽሑፉ ሁሉ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ነው”
5. አምላክ በዛሬው ጊዜ መልእክቱን የሚያስተላልፍበት ዋነኛው መሣሪያ ምንድን ነው? እኛስ ከዚህ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
5 በአምላክና በሰዎች መካከል ዋነኛ የመገናኛ መስመር ሆኖ የሚያገለግለው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ሲሆን በውስጡ የሠፈሩት ሁሉ የሚጠቅሙን ናቸው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) መጽሐፍ ቅዱስ ነፃ ምርጫቸውን ተጠቅመው የይሖዋን ድምፅ ለመስማት ፈቃደኛ ስለሆኑና ስላልሆኑ ሰዎች የሚገልጹ በርካታ ምሳሌዎችን በውስጡ ይዞልናል። እነዚህ ምሳሌዎች የአምላክ መንፈስ የሚናገረውን መስማት ጠቃሚ የሆነበትን ምክንያት እንድናስተውል ይረዱናል። (1 ቆሮንቶስ 10:11) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ በሕይወታችን ውስጥ ውሳኔ ከሚጠይቁ ነገሮች ጋር በምንፋጠጥበት ጊዜ ጥሩ ምክር ልናገኝበት የምንችል ተግባራዊ ጥበብ ይዟል። ልክ አምላክ ከኋላችን ሆኖ በጆሯችን “መንገዱ ይህች ናት በእርስዋም ሂድ” ብሎ የሚናገረን ያህል ነው።
6. መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎች ጽሑፎች ሁሉ የላቀ እንዲሆን ያደረገው ነገር ምንድን ነው?
6 በመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች አማካኝነት መንፈሱ የሚናገረውን መስማት እንድንችል መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረን ልናነበው ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ በአሁኑ ጊዜ በብዛት ከሚገኙት ማራኪና ተወዳጅ መጻሕፍት አንዱ እንደሆነ ብቻ አድርገን ልንመለከተው አይገባም። መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት የተጻፈና የአምላክን አሳብ የያዘ መጽሐፍ ነው። ዕብራውያን 4:12 እንዲህ ይላል:- “የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፣ የሚሠራም፣ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፣ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ይወጋል፣ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል።” መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ በውስጡ የሰፈረው መልእክት እንደ ሰይፍ ውስጣዊ አሳባችንንና ስሜታችንን ዘልቆ በመንካት አኗኗራችን ከአምላክ ፈቃድ ጋር ምን ያህል የተስማማ መሆኑን ግልጽ አድርጎ ያሳየናል።
7. መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ይህንንስ ምን ያህል አዘውትረን እንድናደርግ ተመክረናል?
7 ጊዜ እያለፈ ሲሄድና በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙን ክፉና ደግ የሆኑ ነገሮች ተጽዕኖ እያሳደሩብን ሲሄዱ ‘የልባችን ስሜትና አሳብ’ ሊለወጥ ይችላል። የአምላክን ቃል አዘውትረን የማናጠና ከሆነ አስተሳሰባችን፣ ዝንባሌያችንና ስሜታችን አምላክ ካወጣቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ተስማምቶ ሊቀጥል አይችልም። በዚህም የተነሳ መጽሐፍ ቅዱስ “በሃይማኖት ብትኖሩ [“ያለ ማቋረጥ፣” NW ] ራሳችሁን መርምሩ፤ [“ያለ ማቋረጥ፣” NW ] ራሳችሁን ፈትኑ” በማለት ይመክረናል። (2 ቆሮንቶስ 13:5) መንፈሱ የሚለውን መስማታችንን ለመቀጠል የአምላክን ቃል በየዕለቱ እንድናነብ የተሰጠንን ምክር መከተል ይኖርብናል።—መዝሙር 1:2
8. መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ በተመለከተ ራሳችንን ለመመርመር የትኞቹ ሐዋርያው ጳውሎስ የተናገራቸው ቃላት ይረዱናል?
8 መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡ ሁሉ የሚከተለውን ማሳሰቢያ ማስታወሳቸው አስፈላጊ ነው። ያነበባችኋቸው ነገሮች ወደ ውስጥ ዘልቀው እንዲገቡ በቂ ጊዜ መድቡ! መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ እንድናነብ የተሰጠንን ምክር ለመታዘዝ ስንል ብቻ ምንም ሳይገባን በርካታ ምዕራፎችን በችኮላ መሸፈን አይኖርብንም። መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትሮ ማንበቡ ጠቃሚ ቢሆንም ለንባብ ከወጣው ፕሮግራም ወደኋላ ላለመቅረት ብለን ብቻ የምናደርገው ነገር መሆን የለበትም። ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማዎቹ የማወቅ ልባዊ ፍላጎት ሊኖረን ይገባል። በዚህ ረገድ ራሳችንን ለመመርመር የሚከተሉትን ሐዋርያው ጳውሎስ የተናገራቸውን ቃላት ልንጠቀምባቸው እንችላለን። ለክርስቲያን ባልደረቦቹ ሲጽፍ እንዲህ አለ:- “ከአብ ፊት እንበረከካለሁ፤ . . . ክርስቶስም በልባችሁ በእምነት እንዲኖር . . . የእናንተ ሥርና መሠረት በፍቅር ይጸና ዘንድ፣ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ስፋቱና ርዝመቱ ከፍታውም ጥልቅነቱም ምን ያህል መሆኑን ለማስተዋል፣ ከመታወቅም የሚያልፈውን የክርስቶስን ፍቅር ለማወቅ ትበረቱ ዘንድ፣ እስከ እግዚአብሔርም ፍጹም ሙላት ደርሳችሁ ትሞሉ ዘንድ።”—ኤፌሶን 3:14, 16-19
9. ከይሖዋ ለመማር ያለንን ፍላጎት ማዳበርና ማሳደግ የምንችለው እንዴት ነው?
9 እርግጥ ነው፣ አንዳንዶቻችን በተፈጥሯችን ማንበብ አንወድ ይሆናል፤ ሌሎቻችን ደግሞ ጥሩ አንባቢዎች ልንሆን እንችላለን። ባሕርያችን ምንም ይሁን ምን ከይሖዋ የመማር ፍላጎት ልንኮተኩትና ልናሳድግ እንችላለን። ሐዋርያው ጴጥሮስ ለመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ጉጉት ሊኖረን እንደሚገባ የገለጸ ሲሆን ይህ ፍላጎት መዳበር ሊያስፈልገው እንደሚችልም ተገንዝቦ ነበር። እንዲህ ሲል ጻፈ:- “በቃሉ ወደ መዳን እንድታድጉ አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ላልተበረዘው የቃሉ ወተት ጉጉት አዳብሩ።” (1 ጴጥሮስ 2:2 NW ) ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ‘ጉጉት ለማዳበር’ ከፈለግን ራስን መገሠጽ እጅግ አስፈላጊ ነው። አንድን አዲስ ምግብ በተደጋጋሚ ከቀመስነው በኋላ ልንወደው እንደምንችል ሁሉ ንባብንና ጥናትን ሥራዬ ብለን ለመያዝ ራሳችንን ከገሰጽን ለንባብና ለጥናት የሚኖረን አመለካከት ሊሻሻል ይችላል።
‘በተገቢው ጊዜ የሚቀርብ ምግብ’
10. “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሆኑት እነማን ናቸው? ይሖዋ በዛሬው ጊዜ እየተጠቀመባቸው ያለው እንዴት ነው?
10 ኢየሱስ በማቴዎስ 24:45-47 ላይ ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ለእኛ የሚናገርበትን ሌላ መንገድ ለይቶ ገልጿል። እዚህ ጥቅስ ላይ ‘በተገቢው ጊዜ’ መንፈሳዊ ‘ምግብ’ እንዲያቀርብ ስለተሾመው በመንፈስ ቅዱስ ስለተቀባው የክርስቲያን ጉባኤ ማለትም ስለ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ተናግሯል። የዚህ ቡድን አባላት በግለሰብ ደረጃ የኢየሱስ ‘ቤተሰቦች’ ናቸው። ‘የሌሎች በጎች’ ክፍል የሆኑትን “እጅግ ብዙ ሰዎች” ጨምሮ እነዚህ ቤተሰቦች ማበረታቻና መመሪያ ያገኛሉ። (ራእይ 7:9፤ ዮሐንስ 10:16) ይህ ምግብ በተገቢው ጊዜ የሚመጣው ባብዛኛው እንደ መጠበቂያ ግንብ እና እንደ ንቁ! ባሉና ታትመው በሚወጡ ሌሎች ጽሑፎች አማካኝነት ነው። ተጨማሪ መንፈሳዊ ምግብ በአውራጃ ስብሰባዎች፣ በወረዳና በልዩ ስብሰባዎች እንዲሁም በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በሚቀርቡ ንግግሮችና በሠርቶ ማሣያዎች መልክ ይቀርባል።
11. መንፈሱ “በታማኝና ልባም ባሪያ” በኩል የሚናገረውን የምንቀበል መሆናችንን እንዴት ልናሳይ እንችላለን?
11 “ታማኝና ልባም ባሪያ” እምነታችንንና የማስተዋል ችሎታችንን ለማጎልበት የታቀዱ ትምህርቶችን ያወጣል። (ዕብራውያን 5:14) ሁላችንም እንደየሁኔታዎቻችን መተግበር እንችል ዘንድ እነዚህ ምክሮች ብዙውን ጊዜ የሚቀርቡት ጠቅለል ባለ መንገድ ነው። አልፎ አልፎም የአኗኗራችንን የተለያዩ ገጽታዎች በቀጥታ የሚመለከት ምክርም ይሰጠናል። መንፈሱ በባሪያው ክፍል አማካኝነት በሚናገርበት ጊዜ የምናዳምጥ ከሆነ ምን ዓይነት ዝንባሌ ሊኖረን ይገባል? ሐዋርያው ጳውሎስ “ለዋኖቻችሁ ታዘዙና ተገዙ” በማለት መልሱን ይሰጣል። (ዕብራውያን 13:17) በዚህ ዝግጅት ውስጥ የታቀፉት ሰዎች ፍጹማን እንዳልሆኑ የታወቀ ነው። ሆኖም ይሖዋ በዚህ የመጨረሻ ዘመን እኛን ለመምራት ፍጹማን ባይሆኑም እንኳን ሰብዓዊ በሆኑ አገልጋዮቹ መጠቀም ያስደስተዋል።
ሕሊናችን የሚሰጠን መመሪያ
12, 13. (ሀ) ይሖዋ መመሪያ የምናገኝበት ምን ሌላ ምንጭ ሰጥቶናል? (ለ) ሕሊና የአምላክን ቃል ትክክለኛ እውቀት በማያውቁ ሰዎች ላይ እንኳ ሳይቀር ምን አዎንታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል?
12 ይሖዋ መመሪያ ልናገኝ የምንችልበትን ሌላ ምንጭ ሰጥቶናል። ይህም ሕሊናችን ነው። ይሖዋ ሰውን ሲፈጥር ትክክልና ስህተት የሆኑ ነገሮችን ለመለየት የሚያስችል ውስጣዊ ስሜት ሰጥቶታል። ይህ የተፈጥሯችን ክፍል ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች በጻፈ ጊዜ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ሕግ የሌላቸው አሕዛብ ከባሕርያቸው የሕግን ትእዛዝ ሲያደርጉ፣ እነዚያ ሕግ ባይኖራቸው እንኳ ለራሳቸው ሕግ ናቸውና፤ እነርሱም ሕሊናቸው ሲመሰክርላቸው፣ አሳባቸውም እርስ በርሳቸው ሲካሰስ ወይም ሲያመካኝ በልባቸው የተጻፈውን የሕግ ሥራ ያሳያሉ።”—ሮሜ 2:14, 15
13 ይሖዋን የማያውቁ ብዙ ሰዎች በተወሰነ ደረጃ እንኳ ቢሆን አሳባቸውንና ድርጊታቸውን አምላክ ትክክልና ስህተት ስለሆኑ ነገሮች ካወጣቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ማስማማት ይችላሉ። ትክክለኛውን አቅጣጫ ይዘው እንዲሄዱ ከውስጥ በቀስታ የሚናገርን ድምፅ የሚሰሙ ያህል ነው። ውስጣዊው ድምፅ የአምላክን ቃል ትክክለኛ እውቀት በማያውቁ ሰዎች ላይ ይህን ያህል ሊሠራ ከቻለ በእውነተኛ ክርስቲያኖች ላይ ደግሞ ይበልጥ መሥራት እንዳለበት የታወቀ ነው! በእርግጥም፣ በአምላክ ቃል ትክክለኛ እውቀት የጠራና ከይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ጋር ተስማምቶ የሚሠራ የአንድ የክርስቲያን ሕሊና አስተማማኝ መምሪያ ሊሆን ይችላል።—ሮሜ 9:1
14. በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊና የይሖዋ መንፈስ የሚሰጠንን መመሪያ እንድንከተል ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?
14 በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ጥሩ ሕሊና መንፈስ ቅዱስ እንድንሄድበት በሚፈልገው ጎዳና ላይ እንድንጓዝ ማሳሰቢያ ሊሰጠን ይችላል። ቅዱሳን ጽሑፎችም ሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች በቀጥታ ሐሳብ የማይሰጡበት አንድ ጉዳይ ሊገጥመን ይችላል። በዚህም ጊዜ ቢሆን ሕሊናችን ጉዳት ላይ ሊጥል የሚችል ጎዳና እንዳንከተል ለማስጠንቀቅ የማስጠንቀቂያ ድምፅ ሊያሰማ ይችላል። በዚህ ወቅት ሕሊናችን የሚያሰማውን ድምፅ ለማዳመጥ አሻፈረን ብንል የይሖዋ መንፈስ የሚናገረውን ችላ እንዳልን ያህል ሊቆጠር ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ በሠለጠነ ክርስቲያናዊ ሕሊናችን ላይ መታመንን በመማር በጽሑፍ የሰፈረ ቀጥተኛ መመሪያ በማይኖርበት ጊዜም እንኳን ጥበብ ያለበት ምርጫ ልናደርግ እንችላለን። ይሁን እንጂ በግልጽ የተቀመጠ መለኮታዊ መሠረታዊ ሥርዓት፣ ደንብ ወይም ሕግ በማይኖርበት ጊዜ በክርስቲያን ባልደረቦቻችን የግል ጉዳይ ውስጥ በመግባት የራሳችንን ሕሊና አስተያየት መሰንዘር ተገቢ አለመሆኑን ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው።—ሮሜ 14:1-4፤ ገላትያ 6:5
15, 16. ሕሊናችን በትክክል መሥራቱን እንዲያቆም ሊያደርገው የሚችለው ነገር ምንድን ነው? ይህ ሁኔታ እንዳይደርስብን መከላከል የምንችለው እንዴት ነው?
15 በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ንጹሕ ሕሊና ከአምላክ የሚገኝ ስጦታ ነው። (ያዕቆብ 1:17) ሆኖም ይህ ስጦታ ከሥነ ምግባር አደጋ የሚጠብቅ መሣሪያ ሆኖ በትክክል እንዲሠራ ከተፈለገ ከሚበክሉ ተጽእኖዎች ልንጠብቀው ይገባል። አምላክ ካወጣቸው የአቋም ደረጃዎች ጋር የሚጋጩ የአካባቢ ባሕሎችንና ልማዶችን የምንከተል ከሆነ ሕሊናችን በትክክል መሥራቱንና ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ ማመልከቱን ሊያቆም ይችላል። የማመዛዘን ችሎታችን ሊዛባና እንዲያውም ራሳችንን በማታለል አንድ መጥፎ ድርጊት ጥሩ እንደሆነ አድርገን እስከማመን ልንደርስ እንችላለን።—ከዮሐንስ 16:2 ጋር አወዳድር።
16 ሕሊናችን የሚያሰማውን የማስጠንቀቂያ ደወል ችላ ብለን ማለፋችንን ከቀጠልን የሚያሰማው ድምፅ ቀስ በቀስ እየተዳከመ ይሄድና በመጨረሻ በሥነ ምግባር የደነደንን ወይም ምንም ዓይነት ምላሽ የማንሰጥ እንሆናለን። መዝሙራዊው ስለ እነዚህ ዓይነት ሰዎች ሲናገር “ልባቸው እንደ ወተት ረጋ” ብሏል። (መዝሙር 119:70) ሕሊናቸው የሚሰጣቸውን ማሳሰቢያ ለማዳመጥ አሻፈረን የሚሉ አንዳንድ ሰዎች በትክክል የማሰብ ችሎታቸውን ያጣሉ። አምላካዊ በሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶች መመራታቸውን ስለሚያቆሙ ትክክለኛ ውሳኔ ማድረግ ይሳናቸዋል። እንዲህ ያለው ሁኔታ እንዳይደርስብን ጉዳዩ አነስተኛ በሚመስልበት ጊዜም እንኳ ክርስቲያናዊ ሕሊናችን የሚሰጠንን መመሪያ ለመቀበል ፈጣኖች መሆን አለብን።—ሉቃስ 16:10
ሰምተው የሚታዘዙ ደስተኞች ናቸው
17. ‘ከኋላችን ያለውን ቃል’ ስንሰማና በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናችንን ስንከተል የምንባረከው እንዴት ነው?
17 በቅዱሳን ጽሑፎችና በታማኝና ልባም ባሪያ በኩል የምንሰማውን ‘ከኋላችን ያለውን ቃል’ የማዳመጥ ልማድ ስናዳብርና በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነው ሕሊናችን የሚሰጠንን ማሳሰቢያ ስንከተል ይሖዋ በመንፈሱ ይባርከናል። በምላሹም መንፈስ ቅዱስ ይሖዋ የሚነግረንን ነገር የመቀበልና የመረዳት ችሎታችንን ያሳድግልናል።
18, 19. ይሖዋ የሚሰጠው መመሪያ በአገልግሎታችንም ሆነ በግል ሕይወታችን እንዴት ሊጠቅመን ይችላል?
18 ከዚህም በተጨማሪ የይሖዋ መንፈስ አስቸጋሪ የሆኑ ሁኔታዎችን በጥበብና በድፍረት እንድንጋፈጣቸው ያነሳሳናል። በሐዋርያት ላይ እንደታየው የአምላክ መንፈስ የማሰብ ችሎታችንን ሊያነቃቃልን ይችላል እንዲሁም የምንናገረውም ሆነ የምናደርገው ነገር ሁልጊዜ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚስማማ እንዲሆን ይረዳናል። (ማቴዎስ 10:18-20፤ ዮሐንስ 14:26፤ ሥራ 4:5-8, 13, 31፤ 15:28) የይሖዋ መንፈስ በግል ከምናደርገው ጥረት ጋር ተዳምሮ በሕይወታችን ውስጥ ትልልቅ ውሳኔዎች ስናደርግ ባደረግነው ውሳኔ ወደፊት እንድንገፋ የሚያስችል ድፍረት በመስጠት ስኬታማ ያደርገናል። ለምሳሌ ያህል የአኗኗር ዘይቤህን በማስተካከል ለመንፈሳዊ ነገሮች ተጨማሪ ጊዜ ለማግኘት ታስብ ይሆናል። ወይም የትዳር ጓደኛ መምረጥን፣ ያገኘኸውን ሥራ በጥንቃቄ መመርመርን ወይም አዲስ ቤት መግዛትን የመሰሉ ከባድና በኑሯችን ላይ ለውጥ ሊያስከትሉ የሚችሉ ምርጫዎች ከፊታችን ይጋረጡብን ይሆናል። ውሳኔ በምናደርግበት ጊዜ ሰብዓዊ ስሜታችን ብቻ እንዲመራን ከመፍቀድ ይልቅ የአምላክ መንፈስ የሚለውን ነገር መስማትና ከአመራሩ ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል።
19 ሽማግሌዎችን ጨምሮ ክርስቲያን ባልደረቦቻችን በደግነት የሚሰጡንን ማሳሰቢያዎችና ምክሮች ከልብ እናደንቃለን። ይሁን እንጂ ሁልጊዜ ሌሎች እስኪነግሩን ድረስ መጠበቅ አይኖርብንም። ልንከተለው የሚገባንን ጥበብ ያለበት ጎዳና አንዴ ካወቅንና አምላክን ለማስደሰት በአመለካከታችንና በአኗኗራችን ላይ ምን ዓይነት ማስተካከያ ማድረግ እንዳለብን ከተገነዘብን እርምጃ እንውሰድ። ኢየሱስ “ይህን ብታውቁ፣ ብታደርጉትም ብፁዓን ናችሁ” በማለት ተናግሯል።—ዮሐንስ 13:17
20. ‘ከኋላቸው ያለውን ቃል’ የሚያዳምጡ ሁሉ ምን በረከት ይጠብቃቸዋል?
20 በግልጽ ለማየት እንደምንችለው ክርስቲያኖች አምላክን እንዴት ማስደሰት እንደሚችሉ ለማወቅ በቀጥታ ከሰማይ የሚመጣ ድምፅ መስማትም ሆነ በመላእክት አማካኝነት ቀጥተኛ መልእክት መቀበል አያስፈልጋቸውም። በጽሑፍ የሰፈረውን የአምላክ ቃልና በምድር ላይ የሚገኘው ቅቡዓን ክፍል የሚሰጠውን ፍቅራዊ አመራር በማግኘት ተባርከዋል። ‘ከኋላቸው ያለውን ይህን ቃል’ በጥንቃቄ ከሰሙና በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነው ሕሊናቸው የሚሰጣቸውን መመሪያ ከተከተሉ የአምላክን ፈቃድ በመፈጸም ረገድ የተሳካላቸው ይሆናሉ። እንደዚያ ከሆነ “የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል” የሚለው ሐዋርያው ዮሐንስ የገለጸው ተስፋ ፍጻሜውን ሲያገኝ ይመለከታሉ።—1 ዮሐንስ 2:17
አጭር ክለሳ
• ይሖዋ ከሰብዓዊ ፍጡሮቹ ጋር የሐሳብ ግንኙነት የሚያደርገው ለምንድን ነው?
• ዘወትር ከሚደረግ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራም ምን ጥቅም ልናገኝ እንችላለን?
• የባሪያው ክፍል ለሚያስተላልፈው መመሪያ ምላሽ መስጠት ያለብን እንዴት ነው?
• በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናችን የሚነግረንን ችላ ብለን ማለፍ የማይኖርብን ለምንድን ነው?
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሰው ልጅ አምላክ የሚሰጠውን መልእክት ለመቀበል ውስብስብ የሆነ መሣሪያ መጠቀም አያስፈልገውም
[ምንጭ]
Courtesy Arecibo Observatory/David Parker/Science Photo Library
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስና በ“ታማኝና ልባም ባሪያ” አማካኝነት ያነጋግረናል