“በንስሮች ምድር” የይሖዋ ቃል ከፍ ከፍ አለ
አልባኒያውያን በቋንቋቸው አገራቸውን “የንስሮች ምድር” ብለው ይጠሯታል። በባልካን ባሕረ ገብ መሬት ላይ በግሪክና በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ መካከል የምትገኘው አልባኒያ በአንድ በኩል የኤድሪያቲክ ባሕር ያዋስናታል። የአልባኒያውያንን አመጣጥ በተመለከተ ብዙ የሚባል ነገር ቢኖርም፣ አብዛኞቹ ታሪክ ጸሐፊዎች አልባኒያውያን የጥንቶቹ እልዋሪቃውያን ዝርያ እንደሆኑና ቋንቋቸውንም የወረሱት ከእነርሱ እንደሚሆን ይናገራሉ፤ ዚ ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንደሚለው እልዋሪቃውያን የኖሩት በ2000 ከክርስቶስ ልደት በፊት ነው።
በስተ ሰሜን ጫፍ የሚገኙት የሾሉ ተራሮቿና በስተ ደቡብ ደግሞ በነጭ አሸዋ የተሸፈኑ ሰፊ የባሕር ዳርቻዎቿ አልባኒያን ተፈጥሯዊ ውበት አላብሰዋታል። ይህችን አገር ይበልጥ ያስዋቧት ግን ሕዝቦቿ ናቸው። ሰው ወዳድ፣ እንግዳ ተቀባዮችና ተግባቢዎች ከመሆናቸውም በላይ ሐሳባቸውን ለመግለጽ ሕያው በሆኑ አካላዊ መግለጫዎች የሚጠቀሙ ፈጣን ተማሪዎች ናቸው።
አንድ የታወቀ ሚስዮናዊ ያደረገው ጉብኝት
የሰዎቹ ተወዳጅ ባሕርይና የአገሪቷ ውብ መልክአ ምድር፣ ከዓመታት በፊት የአንድን የታወቀ ተጓዥ ትኩረት ስበው ነበር። በ56 ከክርስቶስ ልደት በኋላ አካባቢ፣ ብዙ ቦታዎችን የጎበኘው ሐዋርያው ጳውሎስ “እስከ እልዋሪቆን ዙሪያ ድረስ የክርስቶስን ወንጌል ፈጽሜ ሰብኬአለሁ” በማለት ጽፏል። (ሮሜ 15:19) በስተ ደቡብ ያለው የእልዋሪቆን ግዛት የአሁኗ አልባኒያ ሰሜናዊና መካከለኛ ክፍል ነው። ጳውሎስ ደብዳቤውን የጻፈው በደቡባዊ እልዋሪቆን ይኸውም ቆሮንቶስ፣ ግሪክ ውስጥ ሆኖ ነበር። “እስከ እልዋሪቆን ዙሪያ ድረስ” በደንብ መስበኩን መግለጹ ወደ ክልሉ ዘልቆ ገብቶ መስበኩን አሊያም እስከ ድንበሩ ጫፍ ደርሶ እንደነበረ ያሳያል። ያም ሆነ ይህ ጳውሎስ አሁን ደቡባዊ አልባኒያ በሚባለው ክፍል ሰብኮ ነበር። ስለዚህ በአልባኒያ የመንግሥቱን የስብከት ሥራ ለመጀመሪያ ጊዜ ያከናወነው ጳውሎስ ነበር።
ይህ ከሆነ በኋላ ዘመናት አለፉ። የተለያዩ መንግሥታት ሥልጣን ላይ ሲወጡና ሲወርዱ እንዲሁም የውጭ አገር ገዥዎች ይህችን ትንሽ የአውሮፓ አገር ሲፈራረቁባት ከቆዩ በኋላ በ1912 አልባኒያ ራሷን የቻለች አገር ሆነች። ከአሥር ዓመታት ገደማ በኋላ ስለ ይሖዋ መንግሥት የሚነገረው ቃል እንደገና በአልባኒያ ተሰማ።
አስደሳች የሆነ ዘመናዊ አጀማመር
በ1920ዎቹ፣ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተሰደው የነበሩ ጥቂት አልባኒያውያን ዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው ይጠሩ ከነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች የተማሩትን ለሌሎች ለማካፈል ወደ አልባኒያ ተመለሱ። ከእነዚህም መካከል ናሾ ኢድሪዚ ይገኝበታል። አንዳንዶች በጎ ምላሽ የሰጡ ሲሆን ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመሄዱ በ1924 የሩማኒያ ቢሮ በአልባኒያ የሚካሄደውን የስብከት ሥራ እንዲቆጣጠር ተመደበ።
በእነዚያ ዓመታት በአልባኒያ ስለ ይሖዋ ካወቁት ሰዎች መካከል ታናስ ዱሊ (አታን ዱሊስ) ይገኝበታል። “በ1925 በአልባኒያ ውስጥ ሦስት የተደራጁ ጉባኤዎችና በገለልተኛ አካባቢ የሚኖሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች እንዲሁም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ነበሩ። በአካባቢያቸው ከነበሩት ሰዎች ጋር ሲወዳደር . . . እርስ በርሳቸው የጋለ ፍቅር ነበራቸው!” በማለት ያስታውሳል።a
ምቹ መንገዶች ስላልነበሩ ከቦታ ቦታ መጓጓዝ በጣም አስቸጋሪ ነበር። እንደዛም ሆኖ ቀናተኛ አስፋፊዎች ይህን አስቸጋሪ ሥራ ተያያዙት። ለምሳሌ፣ በቭሎረ ደቡባዊ ጠረፍ አካባቢ የምትገኘው አሬቲ ፒና በ1928 ስትጠመቅ 18 ዓመቷ ነበር። ይህች ወጣት መጽሐፍ ቅዱስ በእጇ በመያዝ አስቸጋሪ የሆነውን ተራራ እየወጣችና እየወረደች ሰብካለች። አሬቲ ፒና በ1930ዎቹ በቭሎረ ጉባኤ ከሚገኙት ቀናተኛ አስፋፊዎች መካከል አንዷ ነበረች።
በ1930፣ በአልባኒያ የሚካሄደውን የስብከት ሥራ የሚመራው በአቴንስ፣ ግሪክ ውስጥ የሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ነበር። በ1932 ከግሪክ አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች በአልባኒያ የሚገኙትን ወንድሞች ለማበረታታትና ለማጠናከር ተላከ። በዚያን ጊዜ ከነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች አብዛኞቹ ወደ ሰማይ የመሄድ ተስፋ ነበራቸው። ንጹሕና መልካም ሥነ ምግባር ያላቸው ሰዎች በመሆናቸው ያተረፉት ጥሩ ስም በየቦታው ጥልቅ አክብሮት አስገኝቶላቸዋል። የእነዚህ ታማኝ ወንድሞች ሥራ ፍሬያማ ነበር። በ1935 እና በ1936 በእያንዳንዱ ዓመት ወደ 6,500 ገደማ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በአልባኒያ ለማሰራጨት ችለዋል።
አንድ ቀን በቭሎረ ከተማ መሃል ወንድም ናሾ ኢድሪዚ የወንድም ራዘርፎርድን ንግግር በሸክላ ማጫወቻ ማሰማት ጀመረ። ሰዎች ሱቃቸውን ዘግተው ወንድም ኢድሪዚ ንግግሩን ወደ አልባኒያ ቋንቋ ሲተረጉም ያዳምጡ ነበር። በዚያን ጊዜ ይኖሩ የነበሩት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ መጽሐፍ ቅዱስን ያስተማሩ ቀናተኛ ወንድሞች ጥረት በረከት አስገኝቷል። በ1940 አልባኒያ ውስጥ 50 የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ።
አምላክ የለሽ አገር
በ1939 የጣሊያን ፋሺስቶች አልባኒያን ተቆጣጠሯት። የይሖዋ ምሥክሮች የነበራቸው ሕጋዊ እውቅና ተሰረዘ፤ እንዲሁም የስብከቱ ሥራ ታገደ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ የጀርመን የጦር ሠራዊት አገሪቷን ወረራት። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እንዳበቃ አንቫር ሆጃ የተባለ ተወዳጅነት ያተረፈ ወታደራዊ መሪ ብቅ አለ። በ1946 በተካሄደው ምርጫ እርሱ የሚመራው የኮሚኒስት ፓርቲ ሲያሸንፍ ይህ ሰው ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነ። ቀጣዮቹ ዓመታት የነጻነት ጊዜ ተብለው የተጠሩ ቢሆንም ለይሖዋ ሕዝቦች ግን ሁኔታው ተቃራኒ ነበር።
ውሎ አድሮ መንግሥት ለሃይማኖት ያለው ጥላቻ እየጨመረ መጣ። በክርስቲያናዊ ገለልተኝነታቸው ምክንያት በአልባኒያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በጦርነት ከመሳተፍና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ ከመግባት ታቅበዋል። (ኢሳይያስ 2:2-4፤ ዮሐንስ 15:17-19) በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ወኅኒ የወረዱ ሲሆን ምግብም ሆነ መሠረታዊ የሆኑ ነገሮች አይሰጧቸውም ነበር። አብዛኛውን ጊዜ ከእስር ቤት ውጭ ያሉ መንፈሳዊ እህቶቻቸው ልብሳቸውን ያጥቡላቸውና ምግብ ያቀርቡላቸው ነበር።
ስደት ቢደርስባቸውም ደፋሮች ነበሩ
በ1940ዎቹ መጀመሪያ ላይ በፐርሜት መንደር አጠገብ ትኖር የነበረች ፍሮሲና ጀካ የተባለች ወጣት ታላላቅ ወንድሞቿ ናሾ ዶሪ ከተባለ ጫማ ሰፊ ይማሩ የነበረውን ነገር ሰማች።b ባለ ሥልጣኖቹ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ያደርጉ ነበር፤ ወላጆቿ በድርጊቷ ደስ ባይሰኙም ፍሮሲና በእምነቷ እየበረታች መጣች። “ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ከሄድኩ ጫማዎቼን ይደብቁብኝ እንዲሁም ይመቱኝ ነበር። የማያምን ሰው እንዳገባ ለማድረግ ሞክረው ነበር። እንደማላገባ ስነግራቸው ከቤት አባረሩኝ። ያን ቀን ደግሞ በረዶ ይጥል ነበር። ናሾ ዶሪ፣ በጂሮካስተር የሚገኝ ጎሌ ፍሎኮ የተባለ ወንድም እንዲረዳኝ ጠየቀው። ከዚያም ከቤተሰቡ ጋር እንድኖር ዝግጅት አደረጉልኝ። ወንድሞቼ በገለልተኝነታቸው ምክንያት ለሁለት ዓመት የታሰሩ ሲሆን ከተለቀቁ በኋላ ወደ ቭሎረ ሄጄ ከእነሱ ጋር መኖር ጀመርኩ።
“ፖሊሶች በፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች እንድካፈል ሊያስገድዱኝ ቢሞክሩም ፈቃደኛ አልነበርኩም። ካሰሩኝ በኋላ አንድ ክፍል ውስጥ አስገቡኝና ዙሪያዬን ከበቡኝ። ከእነርሱ መካከል አንዱ ‘ምን ልናደርግሽ እንደምንችል ታውቂያለሽ?’ በማለት ሊያስፈራራኝ ሞከረ። እኔም ‘ይሖዋ ካልፈቀደ ምንም ልታደርጉኝ አትችሉም’ በማለት መለስኩለት። ‘እብድ መሆን አለብሽ! ውጪ ከዚህ!’ በማለት በንዴት ደነፋ።”
በእነዚህ ሁሉ ዓመታት የአልባኒያ ወንድሞች እንደዚህች ወጣት ያለ የታማኝነት መንፈስ አሳይተዋል። በ1957 ከፍተኛ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ቁጥር 75 ደርሶ ነበር። በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት፣ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተሰዶ የነበረውን የአልባኒያ ተወላጅ የሆነ ጆን ማርክስ የተባለ ወንድም ክርስቲያናዊውን ሥራ እንዲያደራጅ ወደ ቲራኔ ላከው።c ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ ሉቺ ጄካ፣ ሚሃል ስቬዚ፣ ሌኦኒታ ፖፔ እና ሌሎች በኃላፊነት ቦታ ያሉ ወንድሞች የጉልበት ሥራ ወደሚሠራባቸው ካምፖች ተላኩ።
በአስቸጋሪ ወቅት የተስፋ ጭላንጭል ታየ
በአልባኒያ እስከ 1967 ድረስ ሁሉም ሃይማኖቶች ይጠሉ ነበር። በኋላ ላይ ግን ሃይማኖት እስከ ጭራሹ ታገደ። የካቶሊክም ሆነ የኦርቶዶክስ ቀሳውስት ወይም የሙስሊም ሃይማኖታዊ መሪዎች ሃይማኖታዊ ሥርዓት እንዳያካሂዱ ተከለከሉ። አብያተ ክርስቲያናት እና መስጊዶች ይዘጉ ወይም የስፖርት ማዘውተሪያ፣ ሙዚየም አሊያም የገበያ ቦታ ይደረጉ ነበር። ማንም ሰው መጽሐፍ ቅዱስን መያዝም ሆነ በአምላክ ላይ ያለውን እምነት መግለጽ አይችልም ነበር።
መስበክና መሰብሰብ ፈጽሞ የማይታሰብ ነበር ማለት ይቻላል። ወንድሞች ተበታትነው የነበረ ቢሆንም እያንዳንዱ የይሖዋ ምሥክር በግለሰብ ደረጃ አምላክን ለማገልገል የተቻለውን ሁሉ ያደርግ ነበር። ከ1960 እስከ 1980 ባለው ጊዜ ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር በጣም ተመናመነ። እንደዚያም ሆኖ በመንፈሳዊ ጠንካሮች ነበሩ።
በ1980ዎቹ መገባደጃ ላይ በአልባኒያ የፖለቲካው ሁኔታ ቀስ በቀስ መለወጥ ጀመረ። ምግብና ልብስ ማግኘት አስቸጋሪ ነበር። ሰዎች ደስተኞች አልነበሩም። በምሥራቅ አውሮፓ የተካሄደው የለውጥ እንቅስቃሴ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ወደ አልባኒያ ደረሰ። ከ45 ዓመታት በኋላ አምባገነናዊው መንግሥት ተወግዶ የሃይማኖት ነጻነት በሚሰጥ አዲስ መንግሥት ተተካ።
በይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል መመሪያ መሠረት በኦስትሪያና በግሪክ የሚገኙት ቅርንጫፍ ቢሮዎች ከአልባኒያውያን ወንድሞች ጋር ወዲያውኑ ግንኙነት አደረጉ። የአልባኒያን ቋንቋ የሚችሉ የግሪክ ወንድሞች አንዳንድ በቅርብ የተተረጎሙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ወደ ቲራኔ እና ቤራት ይዘው መጡ። ቀደም ሲል ተበታትነው የነበሩት አልባኒያውያን ወንድሞች ከውጭ የመጡትን ምሥክሮች ከረጅም ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያገኟቸው ልባቸው በደስታ ተሞላ።
ቀናተኛ የውጭ አገር አቅኚዎች ግንባር ቀደም ሆነው መሥራት ጀመሩ
በ1992 መጀመሪያ ላይ የበላይ አካሉ የአልባኒያ ዝርያ ያላቸውን ሚካኤልና ሊንዳ ዲግሪጎርዮ የተባሉ ባልና ሚስት ሚስዮናውያን ወደ አልባኒያ ላካቸው። እነዚህ ባልና ሚስት በአልባኒያ የሚገኙ ታማኝ አረጋውያን ወንድሞችን እንደገና ከዓለም አቀፉ መንፈሳዊ ቤተሰብ ጋር እንዲቀላቀሉ ረዷቸው። አሥራ ስድስት የሚሆኑ ጣሊያናውያን ትጉ ልዩ አቅኚዎች ወይም የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ከአራት ግሪካውያን የዘወትር አቅኚዎች ጋር በመሆን በኅዳር ወር ላይ አልባኒያ ገቡ። አቅኚዎቹ የአልባኒያን ቋንቋ እንዲያውቁ ለመርዳት የቋንቋ ትምህርት ተዘጋጀላቸው።
ለእነዚህ የውጭ አገር አቅኚዎች የዕለት ተዕለት ኑሮ አስቸጋሪ ነበር። ቋሚ የሆነ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አልነበረም። ክረምቱ ቀዝቃዛና እርጥበት አዘል ነበር። ምግብም ሆነ ሌሎች መሠረታዊ ነገሮችን ለማግኘት ሰዎች ለረዥም ሰዓታት መሰለፍ ነበረባቸው። ሆኖም ለወንድሞች ከሁሉም በላይ አስቸጋሪ የሆነባቸው፣ ለእውነት ምላሽ የሚሰጡ ሰዎች ብዙ ስለነበሩ እነርሱን መያዝ የሚችሉ ትልልቅ ሕንጻዎች ማግኘት ነበር!
የአልባኒያን ቋንቋ ለመማር ጥረት ያደርጉ የነበሩት አቅኚዎች፣ ግባቸው ላይ ለመድረስ የግድ አንድን ቋንቋ አጥርቶ መናገር እንደማያስፈልጋቸው ተገነዘቡ። ተሞክሮ ያለው አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ እንዲህ አላቸው:- “ሞቅ ያለ ፈገግታ ለማሳየትም ሆነ ወንድሞችን ዕቅፍ ለማድረግ በሰዋስው ሕግ መሠረት ትክክል የሆነ ዓረፍተ ነገር መናገር አያስፈልገንም። አልባኒያውያን የሚቀበሏችሁ ትክክለኛ የሰዋስው ሕግ ስለተጠቀማችሁ ሳይሆን ልባዊ ፍቅር ስለምታሳይዋቸው ነው። አትጨነቁ፣ ለማለት የፈለጋችሁትን ይረዷችኋል።”
ከመጀመሪያው የቋንቋ ትምህርት በኋላ አቅኚዎቹ ወደ ቤራት፣ ዱሪስ፣ ጂሮካስተር፣ ሽኮደር፣ ቲራኔ እና ቭሎረ ሄደው ሥራቸውን ጀመሩ። ብዙም ሳይቆይ በእነዚህ ከተሞች በርካታ ጉባኤዎች ተቋቋሙ። በ80ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙት እህት አሬቲ ፒና ጥሩ ጤንነት ባይኖራቸውም በቭሎረ ከተማ ይኖሩ ነበር። ሁለት ልዩ አቅኚዎች ከአሬቲ ጋር አብረው እንዲያገለግሉ ተላኩ። ብዙዎች፣ የውጭ አገር ዜጎች በአልባኒያ ቋንቋ ሲናገሩ በመስማታቸው በመገረም እንዲህ ብለዋል:- “የሌሎች ሃይማኖቶች ሚስዮናውያን ቢሆኑ ኖሮ አንድ ነገር ለመማር ከፈለግን እንግሊዝኛ ወይም ጣሊያንኛ እንድንማር ያደርጉ ነበር። እናንተ የአልባኒያ ቋንቋ መማራችሁ በእርግጥ ከልብ እንደምትወዱንና ልትነግሩን የፈለጋችሁት አስፈላጊ መልእክት እንደያዛችሁ ያሳያል!” እህት አሬቲ እስከሞቱበት የመጨረሻ ወር ድረስ በስብከቱ ሥራ የተካፈሉ ሲሆን በጥር 1994 ምድራዊ ሕይወታቸውን በታማኝነት አጠናቀዋል። እሳቸውም ሆኑ አቅኚዎቹ ያሳዩት ቅንዓት በረከት አስገኝቷል። በ1995 በቭሎረ እንደገና ጉባኤ ተቋቋመ። በአሁኑ ወቅት በዚያ ወደብ ላይ ጥሩ እድገት እያደረጉ ያሉ ሦስት ጉባኤዎች ይገኛሉ።
በመላ አገሪቷ ያሉት ሰዎች በመንፈሳዊ የተጠሙ ሲሆኑ ለሃይማኖት ብዙም ጥላቻ አልነበራቸውም። ከምሥክሮቹ የሚያገኙትን ማንኛውንም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፍ በጉጉት ወስደው ያነቡታል። ብዙ ወጣቶች ጥናት የጀመሩ ሲሆን ፈጣን እድገት አድርገዋል።
በመላ አገሪቷ ከ90 በላይ ጉባኤዎችና ቡድኖች “በእምነት እየበረቱና ዕለት ዕለትም በቍጥር እየጨመሩ” ነው። (የሐዋርያት ሥራ 16:5) በአልባኒያ የሚኖሩት 3,513 የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች አሁንም ብዙ የሚሠራ ሥራ አላቸው። በመጋቢት 2005 በተከበረው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ 10,144 የሚሆኑ ሰዎች ተገኝተው ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ካላቸው አልባኒያውያን ጋር ባደረጉት ውይይት ከ6,000 በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ማግኘት ችለዋል። በቅርቡ በአልባኒያ ቋንቋ ከተዘጋጀው የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ጥቅም እንደሚያገኙ ግልጽ ነው። በእርግጥም የይሖዋ ቃል “በንስሮች ምድር” ከፍ ከፍ ማለቱ ለይሖዋ ውዳሴ አምጥቶለታል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a የታናስ ዱሊን የሕይወት ታሪክ ከታኅሣሥ 1, 1968 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ላይ ማንበብ ይቻላል።
b የናሾ ዶሪን የሕይወት ታሪክ ከጥር 1, 1996 መጠበቂያ ግንብ ላይ ማንበብ ይቻላል።
c የጆን ማርክስን ባለቤት የሄለንን የሕይወት ታሪክ ከጥር 1, 2002 መጠበቂያ ግንብ ላይ ማንበብ ይቻላል።
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በኮሶቮ ውስጥ የጎሳ ግጭት ተወገደ!
በ1990ዎቹ መጨረሻ ላይ በኮሶቮ በተነሳው የድንበር ውዝግብና ሥር የሰደደ የጎሳ ጥላቻ ምክንያት የተካሄደው ጦርነት እንዲሁም የዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ጣልቃ ገብነት ስለዚህ ክልል በተደጋጋሚ እንድንሰማ አድርጎን ነበር።
በባልካን አገሮች ጦርነት በተነሳበት ጊዜ ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ጎረቤት አገሮች ተሰደዋል። ጦርነቱ ጋብ ካለ በኋላ ጥቂት ወንድሞች ምሥራቹን ለመስበክ ወደ ኮሶቮ ተመለሱ። አልባኒያውያንና ጣሊያናውያን የሆኑ ልዩ አቅኚዎች በኮሶቮ የሚገኙትን 2,350,000 ሰዎች ለመርዳት ራሳቸውን አቀረቡ። በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ ወደ 130 የሚጠጉ አስፋፊዎች ያሏቸው አራት ጉባኤዎችና ስድስት ጠንካራ ቡድኖች በዚህ አካባቢ ይሖዋን ያገለግላሉ።
በፕሪስቲና በ2003 የጸደይ ወራት በተደረገው የልዩ ስብሰባ ቀን 252 የሚያክሉ ሰዎች ተገኝተው ነበር። ከተሰብሳቢዎቹ መካከል የሰርብ፣ የአልባኒያ፣ የጀርመን፣ የጂፕሲና የጣሊያን ተወላጆች ነበሩ። ከጥምቀት ንግግሩ በኋላ ተናጋሪው ሁለት ጥያቄዎችን አቀረበ። የአልባኒያ ተወላጅ የሆነ አንድ ሰው፣ አንዲት ጂፕሲ እንዲሁም የሰርብ ዜግነት ያላት ሦስተኛ ሴት አዎንታዊ ምላሻቸውን ለመስጠት ከመቀመጫቸው ተነሱ።
ሦስቱም ተጠማቂዎች በየቋንቋቸው አንድ ላይ “ቫ!” “ዳ!” እና “ፖ!” ብለው እንደመለሱ የተሰብሳቢዎቹ ጭብጨባ እንደ ነጎድጓድ አስተጋባ። ሦስቱም እርስ በርስ ተቃቀፉ። እነዚህ ሰዎች አገራቸውን ሲያምሳት ለቆየው ሥር የሰደደ የጎሳ ችግር መፍትሔ አግኝተውለታል።
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
የሜዲትራንያን ባሕር
ጣሊያን
አልባኒያ
ግሪክ
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወጣት ምሥክሮች የአረጋውያንን ቅንዓት ኮርጀዋል
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አሬቲ ፒና ከ1928 ጀምሮ በ1994 እስከሞቱበት ጊዜ ድረስ በታማኝነት አገልግለዋል
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የቋንቋ ትምህርት የወሰዱት የውጭ አገር አቅኚዎች የመጀመሪያው ቡድን
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ንስር:- © Brian K. Wheeler/VIREO