ጳውሎስ ለቅዱሳን የሚሆን እርዳታ አሰባሰበ
እውነተኛ ክርስቲያኖች ቅድሚያ የሚሰጡት ለመንፈሳዊ ነገሮች ነው። ያም ሆኖ የሌሎች ሰብዓዊ ደህንነትም ያሳስባቸዋል። ችግር ላይ ለወደቁት በተደጋጋሚ የእርዳታ እጃቸውን ዘርግተዋል። ለእምነት አጋሮቻቸው ያላቸው የወንድማማች ፍቅር በችግራቸው እንዲደርሱላቸው ይገፋፋቸዋል።—ዮሐንስ 13:34, 35
ሐዋርያው ጳውሎስ ለመንፈሳዊ ወንድሞቹና እህቶቹ ያለው ፍቅር በአካይያ፣ በገላትያ፣ በመቄዶንያና በእስያ ግዛት ከሚገኙ ጉባኤዎች መዋጮ እንዲያሰባስብ አነሳስቶታል። እንዲህ ማድረጉ ለምን አስፈለገ? እርዳታ የማሰባሰቡ ሥራ የተደራጀው እንዴት ነበር? ምንስ ምላሽ ተገኘ? በጊዜው ስለተከናወነው ሁኔታ ለማወቅ መፈለጋችን ምን ይጠቅመናል?
የኢየሩሳሌም ጉባኤ የነበረበት ሁኔታ
በጰንጠቆስጤ ዕለት ደቀ መዛሙርት የሆኑ አይሁዶችና ከየሥፍራው የተሰባሰቡ ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች በ33 እዘአ ከዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት በኋላ ስለ እውነተኛው እምነት ተጨማሪ እውቀት ለመቅሰም ሲሉ በኢየሩሳሌም ቆይተው ነበር። ይህ ሁኔታ ያስከተለውን ሸክም ለማቃለል በዚያ የነበሩ የእምነት አጋሮች አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በደስታ እርዳታ አበርክተዋል። (ሥራ 2:7-11, 41-44፤ 4:32-37) የአይሁድ ብሔረተኞች የቆሰቆሱት ረብሻና የሕዝብ ዓመፅ የፈጠረው አለመረጋጋትም ተጨማሪ ችግር ፈጥሮ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ አንድም የክርስቶስ ተከታይ እንዳይራብ ሲባል ለችግረኛ መበለቶች በየቀኑ እርዳታ ይታደል ነበር። (ሥራ 6:1-6) ሄሮድስ በጉባኤው ላይ ከባድ ስደት በማድረስ ላይ የነበረ ከመሆኑም በተጨማሪ በ40ዎቹ እዘአ ዓመታት አጋማሽ ላይ ይሁዳ በረሃብ ተመትታ ነበር። እነዚህ ሁሉ ነገሮች ጳውሎስ የኢየሱስን ተከታዮች አስመልክቶ ሲጽፍ “መከራ፣” “ጭንቅ፣” እንዲሁም “የገንዘባችሁንም ንጥቂያ” በማለት የገለጻቸውን ሁኔታዎች አስከትለው ሊሆን ይችላል።—ዕብራውያን 10:32-34፤ ሥራ 11:27–12:1
በ49ም እዘአ ቢሆን አስጊ የሆነው ሁኔታ ቀጥሎ ነበር። ስለሆነም በስብከቱ ረገድ ጳውሎስ በአሕዛብ ላይ እንዲያተኩር ከተስማሙም በኋላ ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ‘ድሆችን እንዲያስብ’ ለምነውታል። ጳውሎስም ለማድረግ የጣረው ይህንኑ ነበር።—ገላትያ 2:7-10
እርዳታ የማሰባሰቡን ሥራ ማደራጀት
ጳውሎስ በይሁዳ ለሚገኙት ድሃ ክርስቲያኖች የሚሰበሰበውን እርዳታ በበላይነት ይከታተል ነበር። በ55 እዘአ ገደማ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ሲጽፍ እንደሚከተለው ብሏቸዋል:- “ለቅዱሳንም ገንዘብን ስለ ማዋጣት ለገላትያ አብያተ ክርስቲያናት እንደ ደነገግሁት እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ። . . . ከእናንተ እያንዳንዱ በየሳምንቱ በፊተኛው ቀን እንደ ቀናው መጠን እያስቀረ በቤቱ ያስቀምጥ። . . . [ከዚያም] ማናቸውም ቢሆኑ የታመኑ የሚመስሉአችሁ ሰዎች ቸርነታችሁን ወደ ኢየሩሳሌም ያደርሱ ዘንድ ደብዳቤ ሰጥቼ እልካቸዋለሁ።” (1 ቆሮንቶስ 16:1-3) አንድ ዓመት ካለፈ በኋላ ጳውሎስ የመቄዶንያና የአካይያ ክርስቲያኖች እርዳታ በማሰባሰቡ ሥራ እንደተካፈሉ ገልጾአል። እንዲሁም የተዋጣው ገንዘብ ወደ ኢየሩሳሌም ሲላክ ከእስያ ግዛት የመጡ ተወካዮች መገኘታቸው በእስያ አካባቢ ያሉ ጉባኤዎችም በዚህ ሥራ እንደተካፈሉ የሚያሳይ ነው።—ሥራ 20:4፤ 2 ቆሮንቶስ 8:1-4፤ 9:1, 2
ማንኛውም ሰው ከሚችለው በላይ እንዲሰጥ አይጠበቅበትም ነበር። ከዚህ ይልቅ ማንኛውም ትርፍ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ያሉትን ቅዱሳን ጉድለት እንዲሞላ የማድረግ ጉዳይ ነው። (2 ቆሮንቶስ 8:13-15) ጳውሎስ “እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ፣ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም” ብሏል።—2 ቆሮንቶስ 9:7
ሐዋርያው የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ለጋስ የሚሆኑበት ጥሩ ምክንያት እንዳላቸው ገልጾላቸዋል። ኢየሱስ በመንፈሳዊ ‘ባለጠጎች ይሆኑ ዘንድ ስለ እነርሱ ደሃ’ ሆኗል። (2 ቆሮንቶስ 8:9) እነዚህ ክርስቲያኖች የኢየሱስን የሰጪነት መንፈስ ለመኮረጅ እንደሚፈልጉ ምንም ጥርጥር የለውም። በተጨማሪም አምላክ ስለሚያሳዩት ልግስና “በሁሉ ነገር ባለ ጠጎች” ስላደረጋቸው ቅዱሳን የሚያስፈልጓቸውን ነገር ለማሟላት መዋጮ ማድረጋቸው ተገቢ ነበር።—2 ቆሮንቶስ 9:10-12
በእርዳታው ተግባር የተሳተፉት ሰዎች ዝንባሌ
በመጀመሪያው መቶ ዘመን ቅዱሳንን ለመርዳት ታስቦ በተዘጋጀው የእርዳታ ፕሮግራም ተካፋይ የነበሩትን ሰዎች ዝንባሌ በመመልከት በፈቃደኝነት ስለሚሰጥ መዋጮ ብዙ መማር እንችላለን። መዋጮው በድህነት ስለተያዙ የይሖዋ አምላኪዎች ከማሰብ የበለጠ ነገርም የተንጸባረቀበት ነበር። ይህም ከአሕዛብና ከአይሁድ ወገን በመጡት ክርስቲያኖች መካከል የጠበቀ ወንድማዊ ትስስር እንደነበረ የሚያሳይ ነው። እርዳታ የመስጠቱና የመቀበሉ ሂደት በአሕዛብና በአይሁድ ክርስቲያኖች መካከል አንድነትና ወዳጅነት እንዳለ የሚያሳይ ነበር። አንዳቸው ለሌላው ያካፍሉ የነበረው ሥጋዊ ነገር ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ነገሮችን ጭምር ነበር።—ሮሜ 15:26, 27
ጳውሎስ የመቄዶንያ ክርስቲያኖች በከባድ ድህነት ውስጥ ስለነበሩ በመጀመሪያ መዋጮ እንዲያደርጉ አልጋበዛቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ እነዚህ ክርስቲያኖች የመስጠት መብት ለማግኘት “ብዙ ልመና” አቅርበዋል። እንዲያውም ‘በብዙ መከራ በመፈተን’ ላይ የነበሩ ቢሆንም “ከአቅማቸው የሚያልፍ” እርዳታ በደስታ ሰጥተዋል! (2 ቆሮንቶስ 8:1-4) እነዚህ ክርስቲያኖች የተጋፈጧቸው ከባድ ፈተናዎች በሮማውያን ዘንድ የተከለከለ ሃይማኖት ይዛችኋል በሚል የሚቀርብባቸውን ክስም ይጨምራል። ስለዚህ በተመሳሳይ ፈተና ውስጥ ለሚገኙት በይሁዳ ለሚኖሩ ወንድሞቻቸው ማዘናቸው ምንም አያስደንቅም።—ሥራ 16:20, 21፤ 17:5-9፤ 1 ተሰሎንቄ 2:14
ምንም እንኳ ጳውሎስ የመቄዶንያ ሰዎች መዋጮ እንዲሰጡ ለማበረታታት መጀመሪያ ላይ የቆሮንቶስ ሰዎች ያሳዩትን ቅንዓት እንደ ምሳሌ አድርጎ ቢጠቀምም በኋላ ላይ ግን የቆሮንቶስ ሰዎች ቅንዓት ቀዝቅዞ ነበር። በዚህ ጊዜ ሐዋርያው የቆሮንቶስን ሰዎች ለማነሳሳት የመቄዶንያ ሰዎች ያሳዩትን ልግስና እንደ ምሳሌ አድርጎ ተጠቅሟል። ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ከዓመት በፊት የጀመሩትን ሥራ አሁን ዳር እንዲያደርሱ ማሳሰቡን አስፈላጊ ሆኖ አግኝቶታል። ያን ጊዜ የተከናወነው ነገር ምን ነበር?—2 ቆሮንቶስ 8:10, 11፤ 9:1-5
ቲቶ እርዳታ የማሰባሰቡን ሥራ በቆሮንቶስ ያስጀምር እንጂ ጥረቱን መና ያስቀሩ የሚመስሉ ችግሮች ተከስተው ነበር። ቲቶ ወደ መቄዶንያ ተጉዞ ከጳውሎስ ጋር ከተመካከረ በኋላ በቆሮንቶስ የሚገኘውን ጉባኤ ለማበረታታትና መዋጮ የማሰባሰቡን ሥራ ለማጠናቀቅ ከሌሎች ሁለት ሰዎች ጋር በመሆን ወደ ቆሮንቶስ ተመለሰ። አንዳንዶች ጳውሎስ የቆሮንቶስን ክርስቲያኖች ለመበዝበዝ ሞክሯል ብለው ሊሆን ይችላል። ምናልባትም ጳውሎስ ሥራውን እንዲያጠናቅቁ የራሱን የድጋፍ ሐሳብ አክሎ ሦስት ሰዎች የላከው ለዚህ ይሆናል። “ስለምናገለግለው ስለዚህ ለጋስ ስጦታ ማንም እንዳይነቅፈን እንጠነቀቃለን” ሲል ጽፏል። “በጌታ ፊት ብቻ ያይደለ ነገር ግን በሰው ፊት ደግሞ መልካም የሆነውን እናስባለን።”—2 ቆሮንቶስ 8:6, 18-23፤ 12:18
መዋጮውን ማድረስ
በ56 እዘአ ፀደይ ላይ የተሰበሰበውን ገንዘብ ወደ ኢየሩሳሌም ለማድረስ ዝግጅቱ ሁሉ ተጠናቅቆ ነበር። ጳውሎስ መዋጮ ያደረጉት ሰዎች ከመረጧቸው ተወካዮች ጋር በመሆን ወደ ኢየሩሳሌም ሊጓዝ ነው። ሐዋርያት ሥራ 20:4 [የ1980 ትርጉም ] እንዲህ ይላል:- “የጳጥሮስ ልጅ ሱሲ ጳጥሮስ ከቤርያ፣ አርስጥሮኮስና ሲኮንዶስ ከተሰሎንቄ፣ ጋይዮስ ከደርቤ፣ ቲኪቆስና ጥሮፊሞስ ከእስያ፣ ጢሞቴዎስም አብረውት ሄዱ።” ሉቃስም በፊልጵስዩስ የሚገኙትን ክርስቲያኖች በመወከል ከእነርሱ ጋር ሄዶ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ በዚህ ጉዞ ቢያንስ ዘጠኝ ሰዎች ተካፍለዋል።
ዲተር ጆርጂ የተባሉ አንድ ምሁር “ለእርዳታ የተሰባሰበው ገንዘብ በጣም ብዙ መሆን አለበት” ሲሉ ተናግረዋል። “ይህ ባይሆን ኖሮ ጉዞው ሐዋርያው ጳውሎስንና ሌሎቹን ልዑካን ከጠየቀባቸው ድካምና ወጪ ጋር የሚመጣጠን አይሆንም ነበር።” የልዑካኑ አብሮ መሄድ ለደህንነቱ ዋስትና ከመሆኑም ሌላ ጳውሎስ ከማንኛውም የእምነት ማጉደል ክስ ነጻ እንዲሆን አድርጓል። ከዚህም በላይ እነዚህ ልዑካን በኢየሩሳሌም ቅዱሳን ፊት የአሕዛብን ጉባኤዎች ወክለው ተገኝተዋል።
የልዑካን ቡድኑ ከቆሮንቶስ ተነስቶ ወደ ሶርያ በሚያደርገው ጉዞ በማለፍ በዓል ወቅት ኢየሩሳሌም ይደርስ ነበር። ይሁን እንጂ ጳውሎስን ለመግደል ሴራ በመጠንሰሱ የጉዞ ዕቅዱ ተለወጠ። (ሥራ 20:3) ምናልባትም የጳውሎስ ጠላቶች ጳውሎስ በባሕር ላይ እንዳለ ሊገድሉት አስበው ይሆናል።
ጳውሎስ ሌላም የሚያሳስበው ነገር ነበር። ከመሄዱ በፊት ‘በይሁዳ ካሉት ከማይታዘዙ ይድን ዘንድ እንዲሁም በኢየሩሳሌም ያለው አገልግሎቱ ቅዱሳንን ደስ የሚያሰኝ ይሆን ዘንድ’ በሮም የሚገኙት ክርስቲያኖች እንዲጸልዩለት ነግሯቸዋል። (ሮሜ 15:30, 31) ቅዱሳን የተደረገላቸውን መዋጮ ጥልቅ በሆነ የአመስጋኝነት ስሜት እንደሚቀበሉት ባያጠራጥርም የእርሱ መገኘት በጠቅላላ በአይሁዳውያን ላይ ሊያመጣ የሚችለው ችግር አሳስቦት ሊሆን ይችላል።
በእርግጥም ሐዋርያው የድሆችን ጉዳይ በአእምሮው ይዞ ነበር። ቅዱሳን ጽሑፎች መዋጮው መቼ እንደተሰጣቸው ባይገልጹም ይህ መዋጮ አንድነት እንዲኖር ከማድረጉም በተጨማሪ ከአሕዛብ ወገን የመጡት ክርስቲያኖች በይሁዳ ካሉት ክርስቲያን ባልንጀሮቻቸው ላገኙት መንፈሳዊ ሃብት ያላቸውን አመስጋኝነት እንዲገልጹ አስችሏቸዋል። ጳውሎስ ኢየሩሳሌም ከደረሰ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በቤተ መቅደሱ መታየቱ ዓመፅ ከማነሳሳቱም በላይ እንዲታሰር ምክንያት ሆኗል። ይሁን እንጂ ይህ ሁኔታ ጳውሎስ ለገዥዎችና ለነገሥታት እንዲመሠክር ግሩም አጋጣሚ ከፍቶለታል።—ሥራ 9:15፤ 21:17-36፤ 23:11፤ 24:1–26:32
ዛሬ የምናደርገው መዋጮ
ከመጀመሪያው መቶ ዘመን አንስቶ ብዙ ነገሮች ይለወጡ እንጂ መሠረታዊ ሥርዓቶቹ አልተለወጡም። እርዳታ የሚያስፈልግ ከሆነ ሌሎች ክርስቲያኖች እንዲያውቁት ይደረጋል። ክርስቲያኖች እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው የሚያደርጉት ማንኛውም መዋጮ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተና ለአምላክና ለሰዎች ካላቸው ፍቅር ተገፋፍተው የሚያደርጉት መሆን ይኖርበታል።—ማርቆስ 12:28-31
በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለቅዱሳን ከተሰባሰበው እርዳታ መረዳት እንደሚቻለው እንዲህ ዓይነቱ መዋጮ የማሰባሰብ ሥራ በተደራጀ መልኩና በፍጹም ሐቀኝነት የሚከናወን መሆን አለበት። እርግጥ ይሖዋ አገልጋዮቹ ምን እንደሚያስፈልጋቸው ያውቃል። ስለሆነም ችግሮች እያሉም እንኳ የመንግሥቱን ምሥራች ለሌሎች ማካፈላቸውን እንዲቀጥሉ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ይሰጣቸዋል። (ማቴዎስ 6:25-34) ይሁን እንጂ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታችን ምንም ይሁን ምን ሁላችንም የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማድረግ እንችላለን። በዚህ መንገድ ‘ብዙ ያከማቸም አያተርፍም። ጥቂትም ያከማቸ አያጎድልም።’—2 ቆሮንቶስ 8:15