ቤዛው አምላክ ጻድቅ መሆኑን ያጎላል
አዳምና ሔዋን ካመጹ በኋላ ይሖዋ አንድ ዘር ለማስነሳት ዓላማ እንዳለው ገለጸ፤ ይህ ዘር ተረከዙ እንደሚቀጠቀጥ ተነግሮ ነበር። (ዘፍጥረት 3:15) የአምላክ ጠላቶች ኢየሱስ ክርስቶስን በመከራ እንጨት ላይ ሰቅለው በገደሉት ጊዜ ይህ ትንቢት ፍጻሜውን አግኝቷል። (ገላትያ 3:13, 16) ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በተአምራዊ ሁኔታ ከአንዲት ድንግል ስለተጸነሰ ኃጢአት አልነበረበትም። በመሆኑም ደሙ፣ ከአዳም ኃጢአትና ሞት የወረሱትን የሰው ልጆች ለመዋጀት ቤዛ ሆኖ መቅረብ ይችላል።—ሮሜ 5:12, 19
ሁሉን ቻይ አምላክ የሆነው ይሖዋ፣ ዓላማውን ከመፈጸም ሊያግደው የሚችል ነገር የለም። በመሆኑም የሰው ልጅ ኃጢአት ውስጥ ከገባ በኋላ ይሖዋ የቤዛው ዋጋ የተከፈለ ያህል አድርጎ ይመለከተው ስለነበር እርሱ በሰጠው ተስፋ ላይ እምነት ከሚያሳድሩ ሰዎች ጋር ወዳጅነት መመሥረት ይችል ነበር። ይህም እንደ ሄኖክ፣ ኖኅና አብርሃም የመሰሉ ፍጽምና የጎደላቸው የአዳም ዘሮች አምላክ ቅድስናውን ሳያረክስ ከእርሱ ጋር እንዲሄዱና እንዲወዳጁ አስችሏቸዋል።—ዘፍጥረት 5:24፤ 6:9፤ ያዕቆብ 2:23
በይሖዋ ላይ እምነት የነበራቸው አንዳንድ ግለሰቦች እንኳ ከባድ ኃጢአት ፈጽመዋል። በዚህ ረገድ ንጉሥ ዳዊት ምሳሌ ይሆነናል። ምናልባትም ‘ንጉሥ ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር ምንዝር ከፈጸመና ባሏ ኦርዮን እንዲሞት ሁኔታዎችን ካመቻቸ በኋላ እንዴት ይሖዋ እርሱን መባረኩን ይቀጥላል?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። የዚህ ዋነኛው ምክንያት ዳዊት ከልብ ንስሐ መግባቱና እምነት ማሳየቱ ነበር። (2 ሳሙኤል 11:1-17፤ 12:1-14) አምላክ ከፍትሕና ከጽድቅ ሥርዓቱ ጋር ተስማሚ የሆነ እርምጃ የወሰደ ቢሆንም ንስሐ የገባውን ዳዊትን ወደፊት በሚከፈለው በኢየሱስ ክርስቶስ መሥዋዕት አማካኝነት ይቅር ብሎታል። (መዝሙር 32:1, 2) መጽሐፍ ቅዱስ ‘አምላክ ቀድሞ የተፈጸመውን ኀጢአት በማለፍ ጽድቁን ለማሳየት ነው’ በማለት የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ስላከናወነው ድንቅ ነገር ይገልጻል። ‘በአሁኑ ዘመንም’ ቢሆን ኢየሱስ የከፈለው ቤዛ ተመሳሳይ ነገር ያከናውናል።—ሮሜ 3:25, 26
አዎን፣ በኢየሱስ የደም ዋጋ አማካኝነት የሰው ልጆች አስደናቂ በረከቶችን ያገኛሉ። ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኛ የሰው ልጆች በቤዛው አማካኝነት ከአምላክ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት ይችላሉ። ከዚህም በተጨማሪ ቤዛው የሞቱ ሰዎች አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ትንሣኤ የማግኘት አጋጣሚ ይከፍትላቸዋል። ይህም ኢየሱስ ቤዛውን ከመክፈሉ በፊት የሞቱ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮችን ጨምሮ ይሖዋን ሳያውቁና ሳያመልኩ የሞቱ በርካታ ሰዎችን ያካትታል። መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቃንና ኀጥአን ከሙታን እንደሚነሡ” ይናገራል። (የሐዋርያት ሥራ 24:15) በዚያን ጊዜ ይሖዋ በቤዛው አማካኝነት ታዛዥ ለሆኑ ሰዎች ዘላለማዊ ሕይወት ይሰጣቸዋል። (ዮሐንስ 3:36) ኢየሱስ ራሱ እንደገለጸው “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአል።” (ዮሐንስ 3:16) ለሰው ልጆች እነዚህ ሁሉ በረከቶች የሚፈስሱላቸው አምላክ ባዘጋጀው ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ነው።
ይሁንና ቤዛው በዋነኝነት የተከፈለው ለእኛ ጥቅም ሲባል አይደለም። የክርስቶስ ቤዛ ያስፈለገበት ከሁሉ የላቀ ምክንያት ከይሖዋ ስም ጋር በተያያዘ ለሚያከናውነው ነገር ነው። ቤዛው ይሖዋ ንጽሕናውንና ቅድስናውን ሳያጎድፍ ከኃጢአተኛ የሰው ዘሮች ጋር ያለውን ግንኙነት ጠብቆ የሚኖር ፍጹም ፍትሐዊ አምላክ መሆኑን ያረጋግጣል። አምላክ ቤዛ የማዘጋጀት ዓላማ ባይኖረው ኖሮ ሄኖክን፣ ኖኅንና አብርሃምን ጨምሮ ማንኛውም የአዳም ዘር ከይሖዋ ጋር መሄድ ወይም ወዳጅ መሆን ባልቻለ ነበር። መዝሙራዊው ይህን ስለተገነዘበ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ኀጢአትን ብትቈጣጠር፣ ጌታ ሆይ፤ ማን ሊቆም ይችላል?” ብሏል። (መዝሙር 130:3) የሚወደውን ልጁን ወደ ምድር የላከውን ይሖዋንም ሆነ በፈቃደኝነት ሕይወቱን ለኛ ቤዛ አድርጎ የሰጠውን ኢየሱስን በጣም ልናመሰግናቸው ይገባል!—ማርቆስ 10:45