ኃጢአትን መግለጥ ለምን አስፈለገ?
በምዕራብ አፍሪካ የሚኖሩ አንዳንድ ሰዎች “ነገርን የሚገልጥ የሕዝብ ጠላት ይሆናል” የሚል አባባል አላቸው። ኦሉ ታላቅ ወንድሙ ከእህቱ ጋር የጾታ ግንኙነት እንደፈጸመ በተናገረ ጊዜ የደረሰበት ሁኔታ ከዚህ አባባል ጋር ይስማማል። ወንድሙ “አንተ ውሸታም!” ብሎ ጮኸበት። ከዚያም ኦሉን ክፉኛ ደብድቦ ቤተሰባቸው ከሚኖርበት ቤት ካባረረው በኋላ ልብሱን ሁሉ አቃጠለበት። የመንደሩ ነዋሪዎች ታላቅየውን ወንድም ደገፉ። ኦሉ የመንደሩ ነዋሪዎች ዓይንህን ላፈር ስላሉት አካባቢውን ለቅቆ ለመሄድ ተገደደ። ኦሉ የተናገረው ነገር እውነት እንደሆነ ሰዎቹ የተረዱት ልጅቷ መጸነሷን ከተመለከቱ በኋላ ነበር። ወንድምየው ድርጊቱን መፈጸሙን አመነ፤ ኦሉም ቀድሞ የነበረውን ሞገስ መልሶ አገኘ። ሆኖም ሁኔታዎቹ ከዚህ የተለየ መልክ ሊይዙ ይችሉ ነበር። ኦሉ ተገድሎም ሊሆን ይችል ነበር።
ለይሖዋ ፍቅር የሌላቸው ሰዎች የፈጸሙት ስህተት ወደ ብርሃን መውጣቱ እንደማያስደስታቸው የታወቀ ነው። የሰው ልጅ ያለበት የኃጢአት ዝንባሌ ተግሳጽን እንዳይቀበልና ተግሳጽ ሰጪውን እንዲጠላ ያደርገዋል። (ከዮሐንስ 7:7 ጋር አወዳድር።) ብዙ ሰዎች ሌሎች የፈጸሙትን ስህተት ተገቢውን እርማት የመስጠት ኃላፊነት ላለው አካል ከማሳወቅ ይልቅ እንደ ድንጋይ ዝምታን መምረጣቸው አያስደንቅም።
የተግሳጽን ጥቅም መገንዘብ
ይሁን እንጂ የይሖዋ ሕዝቦች ለተግሳጽ ያላቸው አመለካከት የተለየ ነው። ለአምላክ ያደሩ ወንዶችና ሴቶች ይሖዋ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ ስህተት የፈጸሙ ሰዎችን ለመርዳት ያዘጋጀውን ዝግጅት ከልብ ያደንቃሉ። እንዲህ ያለው ዲስፕሊን የፍቅራዊ ደግነቱ መግለጫ እንደሆነ ይገነዘባሉ።—ዕብራውያን 12:6-11
ይህን ሁኔታ በምሳሌ ለማስረዳት በንጉሥ ዳዊት ሕይወት ውስጥ የተከሰተ አንድ ገጠመኝ መጥቀስ ይቻል ይሆናል። ዳዊት ከወጣትነቱ ጀምሮ ጻድቅ ሰው የነበረ ቢሆንም እንኳ ከባድ ኃጢአት የሠራበት ጊዜ ነበር። መጀመሪያ ምንዝር ፈጸመ። ከዚያም የሴትዮዋ ባል እንዲገደል በማድረግ የሠራው ጥፋት እንዲሸፈን ለማድረግ ሞከረ። ሆኖም ይሖዋ የዳዊትን ኃጢአት ለነቢዩ ናታን በመግለጡ ናታን በድፍረት ፊት ለፊት ዳዊትን ስለ ጉዳዩ አነጋገረው። ናታን ብዙ በጎች የነበሩት አንድ ሀብታም ሰው ወዳጁን ለመጋበዝ ሲል የአንድን ድሃ ሰው ብቸኛና ብርቅዬ በግ ወስዶ እንዳረደ የሚገልጽ አንድ ኃይለኛ ምሳሌ በመጠቀም ሀብታሙ ሰው ምን ሊደረግበት እንደሚገባ ዳዊትን ጠየቀው። ቀደም ሲል እረኛ የነበረው ዳዊት ቁጣውና ንዴቱ ተቀሰቀሰ። “ይህን ያደረገ ሰው የሞት ልጅ ነው” ሲል ተናገረ። በዚህ ጊዜ ናታን “ያ ሰው አንተ ነህ” በማለት ምሳሌው እሱን የሚመለከት እንደሆነ ገለጸለት።—2 ሳሙኤል 12:1-7
ዳዊት በናታን ድርጊት አልተናደደም፤ በተጨማሪም ራሱን ከክስ ነፃ ለማድረግም ሆነ ናታንን መልሶ ለመወንጀል አልሞከረም። ከዚህ ይልቅ የናታን ወቀሳ ሕሊናውን በጣም ነካው። ዳዊት ከልቡ ተጸጽቶ “እግዚአብሔርን በድያለሁ” በማለት ተናዘዘ።—2 ሳሙኤል 12:13
ናታን የዳዊትን ኃጢአት ማጋለጡና በኋላም አምላካዊ ወቀሳ መስጠቱ ጥሩ ውጤቶች አስገኝቷል። ዳዊት የሠራው ስህተት ካስከተለበት መዘዝ ሊያመልጥ ያልቻለ ቢሆንም እንኳ ንስሐ ገብቶ ከይሖዋ ጋር ዕርቅ ሊፈጥር ችሏል። ዳዊት ለእንዲህ ዓይነቱ ወቀሳ የተሰማው ስሜት ምን ነበር? እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ጻድቅ ሰው ይዝለፈኝ፤ ፍቅራዊ ደግነት ነውና፤ ይገስጸኝም፤ በራስ ላይ እንደሚፈስ ዘይት ነው፤ ራሴም ይቀበለዋል።”—መዝሙር 141:5 NW
በዘመናችንም የይሖዋ አገልጋዮች፣ ለብዙ ዓመታት በታማኝነት ያገለገሉትም እንኳ ሳይቀሩ ከባድ ኃጢአት ሊሠሩ ይችላሉ። አብዛኞቹ የይሖዋ አገልጋዮች ሽማግሌዎች ሊረዷቸው እንደሚችሉ በመገንዘብ ራሳቸው ቅድሚያውን በመውሰድ እርዳታ ለማግኘት ወደ እነሱ ይቀርባሉ። (ያዕቆብ 5:13-16) ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ኃጢአት የፈጸመ ሰው ልክ ንጉሥ ዳዊት እንዳደረገው ኃጢአቱን ለመሸፈን ሊሞክር ይችላል። በጉባኤያችን ውስጥ አንድ ሰው ከባድ ኃጢአት እንደሠራ ብናውቅ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
ኃላፊነቱ የማን ነው?
ሽማግሌዎች ከባድ ኃጢአት እንደተፈጸመ በሚያውቁበት ጊዜ ኃጢአቱን የፈጸመውን ሰው ቀርበው አስፈላጊውን እርዳታና እርማት ይሰጡታል። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ እንዲህ ያሉ ሰዎችን ጉዳይ የመመርመር ኃላፊነት ያላቸው ሽማግሌዎች ናቸው። ጥበብ የጎደለው ወይም የተሳሳተ እርምጃ በመውሰድ ላይ ያለን ግለሰብ መንፈሳዊ ሁኔታ ነቅተው በመከታተል እርዳታና ምክር ይሰጡታል።—1 ቆሮንቶስ 5:12, 13፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:2፤ 1 ጴጥሮስ 5:1, 2
ይሁን እንጂ ሽማግሌ ባትሆንና አንድ ክርስቲያን ከባድ ኃጢአት መሥራቱን ብታውቅስ? ይሖዋ ለእስራኤል ሕዝብ በሰጠው ሕግ ላይ ይህን ጉዳይ የሚመለከቱ መመሪያዎች እናገኛለን። አንድ ሰው የክህደት ድርጊቶች፣ ሕዝብን ለዓመፅ የሚያነሳሱ ሁኔታዎች፣ ነፍስ ግድያ ወይም ደግሞ ሌሎች ከባድ ወንጀሎች ሲፈጸሙ ካየ የመናገርና የሚያውቀውን ነገር የመመስከር ኃላፊነት እንዳለበት ሕጉ ይደነግጋል። ዘሌዋውያን 5:1 እንዲህ ይላል:- “ማንም ሰው የሚያምለውን ቃል ቢሰማ፣ ምስክር ሆኖም አንድ ነገር አይቶ እንደ ሆነ ባይናገር፣ ኃጢአት መሥራቱ ነውና በደሉን ይሸከማል።”—ከዘዳግም 13:6-8፤ ከአስቴር 6:2 እና ከምሳሌ 29:24 ጋር አወዳድር።
በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች ምንም እንኳ በሙሴ ሕግ ሥር ባይሆኑም ከሕጉ በስተጀርባ ባሉት መሠረታዊ ሥርዓቶች ሊመሩ ይችላሉ። (መዝሙር 19:7, 8) ስለዚህ አንድ መሰል ክርስቲያን ከባድ ኃጢአት እንደሠራ ብታውቅ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?
ጉዳዩን በአግባቡ መያዝ
በመጀመሪያ ደረጃ በእርግጥ ከባድ ኃጢአት መፈጸሙን ሊያሳምን የሚችል በቂ ምክንያት መኖር አለበት። “በንጹሕ ሰው ላይ ያለ በቂ ምክንያት አትመስክር፤ ስሙንም አታጥፋ” ሲል ጠቢቡ ሰው ተናግሯል።—ምሳሌ 24:28 የ1980 ትርጉም
በቀጥታ ወደ ሽማግሌዎች ለመሄድ ትወስን ይሆናል። እንዲህ ማድረጉ ስህተት አይደለም። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ ከሁሉ የተሻለው ፍቅራዊ መንገድ ራሱን ግለሰቡን ቀርቦ ማነጋገር ነው። ምናልባትም እውነታዎቹ እኛ እንዳሰብነው ላይሆኑ ይችላሉ። ወይም ደግሞ ጉዳዩ አስቀድሞ በሽማግሌዎች ታይቶ ሊሆን ይችላል። ጉዳዩን በረጋ መንፈስ ከግለሰቡ ጋር ተወያይበት። ከተወያያችሁም በኋላ ከባድ ኃጢአት መፈጸሙን የሚያሳምን ማስረጃ ካለ ግለሰቡ ወደ ሽማግሌዎች ቀርቦ እርዳታ እንዲጠይቅ አበረታታው፤ በተጨማሪም እንዲህ ማድረጉ ጥበብ እንደሆነ ግለጽለት። ጉዳዩን ለሌሎች አትንገር፤ እንዲህ ማድረጉ ሐሜት ይሆናል።
በቂ ጊዜ ከሰጠኸውም በኋላ ለሽማግሌዎች ካልተናገረ አንተ ራስህ መንገር ይኖርብሃል። ከዚያም አንድ ወይም ሁለት ሽማግሌዎች ግለሰቡን ቀርበው ስለ ጉዳዩ ያነጋግሩታል። ሽማግሌዎቹ በእርግጥ ኃጢአት መሠራቱን ለማወቅ ‘መመርመርና በሚገባ መጠየቅ’ ይኖርባቸዋል። በእርግጥ ኃጢአት ተሠርቶ ከሆነ ጉዳዩን በቅዱሳን ጽሑፎች መመሪያ መሠረት እልባት ይሰጡታል።—ዘዳግም 13:12-14
አንድ ኃጢአት መሠራቱን ለማረጋገጥ ቢያንስ ሁለት ምሥክሮች መኖር አለባቸው። (ዮሐንስ 8:17፤ ዕብራውያን 10:28) ግለሰቡ ድርጊቱን ቢክድና ምሥክርነት የሰጠኸው አንተ ብቻ ከሆንክ ጉዳዩ ለይሖዋ ይተዋል። (1 ጢሞቴዎስ 5:19, 24, 25) እንዲህ የሚደረገው ሁሉ ነገር በይሖዋ ፊት “የተገለጠ” እንደሆነና ሰውየው ጥፋተኛ ከሆነ በመጨረሻ ኃጢአቱ ‘እንደሚያገኘው’ በመገንዘብ ነው።—ዕብራውያን 4:13፤ ዘኁልቁ 32:23
ሆኖም ግለሰቡ ድርጊቱን ክዷል፤ ምስክርነቱንም የሰጠኸው አንተ ብቻ ነህ እንበል። የግለሰቡን ስም አጥፍተሃል ተብለህ ልትወነጀል ትችላለህን? በፍጹም፣ ድርጊቱን ለሌሎች በማውራት እስካላማኸው ድረስ ልትወነጀል አትችልም። የተለያዩ ጉዳዮችን በበላይነት የመቆጣጠርና የማረም ሥልጣንና ኃላፊነት ላላቸው ሰዎች ጉባኤውን የሚነኩ ሁኔታዎችን መንገር ስም አጥፊነት አይደለም። እንዲያውም ሁልጊዜ ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግና ታማኞች ሆነን ለመገኘት ካለን ፍላጎት ጋር የሚስማማ ነው።—ከሉቃስ 1:74, 75 ጋር አወዳድር።
የጉባኤውን ቅድስና መጠበቅ
አንድን ኃጢአት መግለጥ አስፈላጊ የሆነበት አንዱ ምክንያት የጉባኤውን ንጽሕና ለመጠበቅ የሚያስችል በመሆኑ ነው። ይሖዋ ንጹሕና ቅዱስ የሆነ አምላክ ነው። እሱን የሚያመልኩ ሁሉ በመንፈሳዊና በሥነ ምግባር ንጹሕ እንዲሆኑ ይፈልጋል። በመንፈሱ አነሳሽነት ያስጻፈው ቃሉ የሚከተለውን ምክር ይሰጣል:- “እንደሚታዘዙ ልጆች ባለማወቃችሁ አስቀድሞ የኖራችሁበትን ምኞት አትከተሉ። ዳሩ ግን:- እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ።” (1 ጴጥሮስ 1:14-16) ርኩስ የሆኑ ድርጊቶችን ወይም ኃጢአትን የሚፈጽሙ ግለሰቦች እንዲታረሙ አለዚያም እንዲወገዱ ካልተደረገ መላውን ጉባኤ ሊያረክሱና የይሖዋን ሞገስ እንዲያጣ ሊያደርጉ ይችላሉ።—ከኢያሱ ምዕራፍ 7 ጋር አወዳድር።
ሐዋርያው ጳውሎስ በቆሮንቶስ ለነበረው የክርስቲያን ጉባኤ የጻፋቸው መልእክቶች የተሠራው ኃጢአት ሪፖርት መደረጉ በዚያ የነበሩትን የአምላክ ሕዝቦች እንዴት ለማንጻት እንዳስቻለ ያመለክታሉ። ጳውሎስ በመጀመሪያው መልእክቱ ላይ እንዲህ ሲል ጽፎ ነበር:- “በአጭር ቃል በእናንተ መካከል ዝሙት እንዳለ ይወራል የዚያም ዓይነት ዝሙት በአሕዛብስ እንኳ የማይገኝ ነው፣ የአባቱን ሚስት ያገባ ሰው ይኖራልና።”—1 ቆሮንቶስ 5:1
ሐዋርያው ጳውሎስ ይህ ሪፖርት ከማን እንደደረሰው መጽሐፍ ቅዱስ አይነግረንም። ጳውሎስ ስለ ሁኔታው የሰማው ከቆሮንቶስ ተነስተው ጳውሎስ ወደ ነበረበት ማለትም ወደ ኤፌሶን ከተጓዙት ከእስጢፋኖስ፣ ከፈርዶናጥስና ከአካይቆስ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም ጳውሎስ ጥያቄ ያዘለ ደብዳቤ በቆሮንቶስ ከሚገኘው ክርስቲያን ጉባኤ ተልኮለት ነበር። ሪፖርቱ የደረሰው ከማንም ይሁን ከማን ጳውሎስ ሁኔታው ተአማኒነት ባላቸው ምሥክሮች እንደተነገረው ወዲያውኑ ጉዳዩን የተመለከተ መመሪያ መስጠት ችሏል። “ክፉውን ከመካከላችሁ አውጡት” ሲል ጽፏል። ሰውየው ከጉባኤው ተወገደ።—1 ቆሮንቶስ 5:13፤ 16:17, 18
ጳውሎስ የሰጠው መመሪያ ጥሩ ውጤት አስገኝቷልን? እንዴታ! ኃጢአተኛው የፈጸመው ድርጊት ስህተት መሆኑን እንደተገነዘበ ግልጽ ነው። ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው ሁለተኛ መልእክቱ ላይ የጉባኤው አባላት ንስሐ የገባውን ሰው ‘በደግነት ይቅር እንዲሉትና እንዲያጽናኑት’ አጥብቆ መክሯቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 2:6-8) ስለዚህ የተሠራው ኃጢአት ሪፖርት በመደረጉ እርምጃ ሊወሰድ ችሏል። የተወሰደው እርምጃ ደግሞ ጉባኤው ንጹሕ እንዲሆንና ከአምላክ ጋር የመሠረተው ዝምድና ተበላሽቶበት የነበረው ግለሰብ በአምላክ ዘንድ የነበረውን ሞገስ መልሶ እንዲያገኝ አስተዋጽኦ አድርጓል።
ጳውሎስ በቆሮንቶስ ለነበረው የክርስቲያን ጉባኤ በጻፈው የመጀመሪያው መልእክት ውስጥ ሌላም ምሳሌ ሰፍሮ እናገኛለን። በዚህ ጊዜ ሐዋርያው ጉዳዩን ሪፖርት ያደረጉለትን ምሥክሮች ስም ጠቅሷል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ወንድሞቼ ሆይ፣ በመካከላችሁ ክርክር እንዳለ ስለ እናንተ የቀሎዔ ቤተ ሰዎች አስታውቀውኛልና።” (1 ቆሮንቶስ 1:11) ጳውሎስ በመካከላቸው የተፈጠረው ግጭትና ለሰዎች ተገቢ ያልሆነ ክብር መስጠታቸው የጉባኤውን አንድነት ሊያፈራርስ የሚችል የመከፋፈል ዝንባሌ እንዳስከተለ ተረድቶ ነበር። በመሆኑም ጳውሎስ በዚያ ለሚገኙት መሰል አማኞች መንፈሳዊ ደህንነት በጥልቅ ያስብ ስለነበረ ወዲያውኑ እርምጃ በመውሰድ ለጉባኤው የእርማት ምክር ጽፏል።
በዛሬው ጊዜ በምድር ዙሪያ ባሉ ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ አብዛኞቹ ወንድሞችና እህቶች በግለሰብ ደረጃ በአምላክ ፊት ተቀባይነት ያለው አቋም ይዘው በመኖር የጉባኤውን መንፈሣዊ ንጽሕና ለመጠበቅ ተግተው ይሠራሉ። አንዳንዶች ይህን ለማድረግ ሲሉ መከራ ተቀብለዋል፤ ሌሎች ደግሞ ጽኑ አቋማቸውን ለመጠበቅ ሲሉ ራሳቸውን ለሞት አሳልፈው እስከ መስጠት ደርሰዋል። ስለዚህ ኃጢአትን ችላ ብሎ ማለፍ ወይም ደግሞ መሸፈን ለእነዚህ ጥረቶች አድናቆት እንደጎደለን የሚያሳይ ነው።
ስህተት ለፈጸሙ ሰዎች የሚሆን እርዳታ
ከባድ ኃጢአት የፈጸሙ አንዳንድ ሰዎች የጉባኤ ሽማግሌዎችን ቀርበው ከማነጋገር ወደ ኋላ የሚሉት ለምንድን ነው? ብዙውን ጊዜ ሽማግሌዎችን ቀርቦ ማነጋገር ያለውን ጥቅም ስለማያውቁ ነው። አንዳንዶች ከተናዘዝን ኃጢአታችንን መላው ጉባኤ እንዲያውቀው ይደረጋል የሚል የተሳሳተ እምነት አላቸው። ሌሎች ራሳቸውን በማታለል ነገሩን አቅልለው ይመለከቱታል። ሌሎቹ ደግሞ ያለ ሽማግሌዎች እርዳታ ራሳቸውን ማስተካከል እንደሚችሉ አድርገው ያስባሉ።
ይሁን እንጂ መጥፎ ድርጊት የፈጸሙ እንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች ከጉባኤ ሽማግሌዎች ፍቅራዊ እርዳታ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። ያዕቆብ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተ ክርስቲያንን ሽማግሌዎች ወደ እርሱ ይጥራ፤ በጌታም ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት። የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል ጌታም ያስነሣዋል፤ ኃጢአትንም ሠርቶ እንደ ሆነ ይሰረይለታል።”—ያዕቆብ 5:14, 15
ስህተት የፈጸሙ ሰዎች ቀደም ሲል የነበራቸውን መንፈሳዊነት መልሰው እንዲያገኙ ለመርዳት የሚያስችል እንዴት ያለ ግሩም ዝግጅት ነው! ሽማግሌዎች በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን የሚያጽናና ምክር በመስጠትና በመጸለይ በመንፈሳዊ የታመሙት ሰዎች ከተሳሳተ መንገዳቸው እንዲመለሱ ሊረዷቸው ይችላሉ። ስለዚህ ንስሐ የገቡት ሰዎች ብዙውን ጊዜ አፍቃሪ ከሆኑ ሽማግሌዎች ጋር ሲገናኙ ራሳቸውን ከመውቀስ ይልቅ የመንፈስ ዕረፍትና ብርታት ያገኛሉ። በምዕራብ አፍሪካ የሚኖር አንድ ወጣት ዝሙት ፈጸመና ኃጢአቱን ለተወሰኑ ወራት ደብቆ ቆየ። ኃጢአቱ ከተገለጠ በኋላ ሽማግሌዎቹን እንዲህ አላቸው:- “ከልጅቷ ጋር ስለነበረኝ የተቀራረበ ግንኙነት የሆነ ሰው ጠይቆኝ ቢሆን ኖሮ እንዴት ጥሩ ነበር! ይህን ነገር መግለጥ በመቻሌ ትልቅ እፎይታ አግኝቻለሁ።”—ከመዝሙር 32:3-5 ጋር አወዳድር።
በመሠረታዊ ሥርዓት በሚመራው ፍቅር ላይ የተመሠረተ እርምጃ
የተጠመቁ የአምላክ አገልጋዮች ‘ከሞት ወደ ሕይወት’ ተሻግረዋል። (1 ዮሐንስ 3:14) ከባድ ኃጢአት ሲፈጽሙ ግን ወደ ሞት መንገድ ይመለሳሉ። እርዳታ ካልተሰጣቸው ንስሐ ለመግባትና ወደ እውነተኛው አምላክ አምልኮ ለመመለስ ያላቸው ፍላጎት ሊሞትና ኃጢአትን ልማድ ሊያደርጉት ይችላሉ።—ዕብራውያን 10:26-29
ኃጢአትን መግለጥ ለኃጢአተኛው ያለንን እውነተኛ አሳቢነት የሚያሳይ እርምጃ ነው። ያዕቆብ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ወንድሞቼ ሆይ፣ ከእናንተ ማንም ከእውነት ቢስት አንዱም ቢመልሰው፣ ኃጢአተኛን ከተሳሳተበት መንገድ የሚመልሰው ነፍሱን ከሞት እንዲያድን፣ የኃጢአትንም ብዛት እንዲሸፍን ይወቅ።”—ያዕቆብ 5:19, 20
እንግዲያው ኃጢአትን መግለጥ ለምን አስፈለገ? ጥሩ ውጤት ስለሚያስገኝ ነው። በእርግጥም ኃጢአትን መግለጥ ለአምላክ፣ ለጉባኤውና ኃጢአቱን ለፈጸመው ግለሰብ ያለንን በመሠረታዊ ሥርዓት የሚመራ ክርስቲያናዊ ፍቅር የምናሳይበት እርምጃ ነው። እያንዳንዱ የጉባኤ አባል የአምላክን የጽድቅ መስፈርቶች በታማኝነት በሚደግፍበት ጊዜ ይሖዋ መላውን ጉባኤ አብዝቶ ይባርከዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ “እርሱም [ይሖዋ] ደግሞ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ያለ ነቀፋ እንድትሆኑ እስከ ፍጻሜ ድረስ ያጸናችኋል” ሲል ጽፏል።—1 ቆሮንቶስ 1:8
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኃጢአት የፈጸመ አንድ ምሥክር ሽማግሌዎችን እንዲያነጋግር ማበረታታት ለግለሰቡ ያለንን ፍቅር የሚያሳይ ነው
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኃጢአት የሠሩ ሰዎች የአምላክን ሞገስ መልሰው እንዲያገኙ ሽማግሌዎች ይረዷቸዋል