ምሥራቹ አስቀድሞ መሰበክ አለበት
“አስቀድሞም ወንጌል ለአሕዛብ ሁሉ ይሰበክ ዘንድ ይገባል።”—ማርቆስ 13:10
1, 2. የምሥክሮቹ መለያ ምልክት ምንድን ነው? ለምንስ?
የይሖዋ ምሥክሮች ያለመታከት የሚሰብኩት ለምንድን ነው? ከቤት ወደ ቤት፣ ከመንገድ ወደ መንገድም ይሁን መደበኛ ባልሆነ መንገድ የምናገኛቸውን ሰዎች በማነጋገር በምናከናውነው ሕዝባዊ አገልግሎት በዓለም ዙሪያ የምንታወቅ መሆናችን አሌ የማይባል ሐቅ ነው። አመቺ በሆነ አጋጣሚ ሁሉ ምሥክሮች መሆናችንን እናሳውቃለን፤ እንዲሁም እንደ ውድ ሀብት የምንመለከተውን ምሥራች በዘዴ ለሰዎች ለመናገር እንጥራለን። እንዲያውም ይህ አገልግሎት መለያ ምልክታችን ነው ብንል ማጋነን አይሆንም!—ቆላስይስ 4:6
2 እስቲ አስበው፤ ሰዎች በአካባቢያቸው ጥሩ ልብስ የለበሱና ቦርሳዎችን የያዙ ወንዶችን፣ ሴቶችንና ልጆችን ሲመለከቱ ብዙውን ጊዜ በመጀመሪያ ወደ አእምሮአቸው የሚመጣው ነገር ምንድን ነው? ‘እነዚያ ካቶሊኮች (ወይም ኦርቶዶክሶች) ደግሞ መጡ!’ ወይም ‘እነዚያ ጴንጤዎች (ወይም መጥምቃውያን) ደግሞ መጡ!’ ይላሉን? አይሉም። ሰዎች እንዲህ ዓይነቶቹ ሃይማኖቶች አንድ ላይ ሆነው ከቤት ወደ ቤት የሚያገለግሉ ቤተሰቦች እንደሌሏቸው ያውቃሉ። ምናልባት አንዳንድ ሃይማኖታዊ ቡድኖች ጥቂት ሚስዮናውያን ተብዬዎችን ለሁለት ዓመት እንዲያገለግሉ ወደ ተወሰኑ ቦታዎች ይልኩ ይሆናል። የድርጅቱ አካል አባላት ግን ይህን በመሰለው በማንኛውም አገልግሎት አይሳተፉም። አመቺ በሆኑት አጋጣሚዎች ሁሉ መልዕክታቸውን ለሌሎች ሰዎች ለመናገር ባላቸው ቅንዓት በዓለም ዙሪያ ተለይተው የሚታወቁት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ናቸው። መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! በተባሉት መጽሔቶቻቸውም ይታወቃሉ።—ኢሳይያስ 43:10–12፤ ሥራ 1:8
ከሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ጋር ሲነጻጸሩ
3, 4. የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ብዙውን ጊዜ በመገናኛ ብዙሃን የሚገለጹት እንዴት ሆነው ነው?
3 ከይሖዋ ምሥክሮች ፍጹም በተለየ ሁኔታ በአንዳንድ አገሮች ብዙዎቹ ቀሳውስት ልጆችን የሚያስነውሩ፣ አጭበርባሪዎችና የገንዘብ ጥቅም ለማግኘት የሚያታልሉ መሆናቸውን የዜና ሪፖርቶች በየጊዜው አጋልጠዋቸዋል። የሥጋ ሥራቸውና የቅንጦት አኗኗራቸው ለማንም በግልጽ የሚታይ ነው። ይህን ሁኔታ አንድ ዝነኛ የዘፈን ደራሲ “ኢየሱስ ዛሬ በምድር ላይ ቢኖር ኖሮ ሮሌክስ የተባለውን [በጣም ውድ የሆነ የወርቅ ሰዓት] አሥሮ በቴሌቪዥን ይታይ ነበርን?” የሚል ርዕስ ባለው ዘፈኑ ላይ በደንብ ገልጾታል። የሚከተሉትን ጥያቄዎች አቅርቧል፦ “ኢየሱስ ወደ ምድር ተመልሶ ቢመጣ ኖሮ ፖለቲከኛ ይሆን ነበርን? በፓልም ስፕሪንግስ [በካሊፎርኒያ የናጠጠ ማኅበረሰብ መካከል] ሁለተኛ ቤቱን ሠርቶ ሀብቱን ለመደበቅ ይሞክር ነበርን?” “በምድር ላይ ተቀማጥላችኋል በሴሰኝነትም ኖራችኋል፤ ለእርድ ቀን እንደሚያወፍር ልባችሁን አወፍራችኋል” የሚሉት የያዕቆብ ቃላት ምንኛ ተስማሚ ናቸው!—ያዕቆብ 5:5፤ ገላትያ 5:19–21
4 ቀሳውስቱ ከፖለቲከኞች ጋር መወዳጀታቸውና አልፎ ተርፎም የፖለቲካዊ ምርጫ ዕጩዎች ሆነው መሳተፋቸው ዘመናዊ ጻፎችና ፈሪሳውያን መሆናቸውን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ከዚሁ ጋር ጎን ለጎን ደግሞ እንደ ዩናይትድ ስቴትስና ካናዳ ባሉ አገሮች ሃይማኖታዊ ቡድኖች ቀሳውስቱ በልጆችና በአዋቂዎች ላይ በሚፈጽሙት ብልሹ የጾታ ብልግና የተነሣ ለፍርድ ቤት ሙግት ከፍተኛ ወጪ ስለሚያወጡና በቀሳውስቱ ላይ የሚበየነውን የገንዘብ ቅጣት ስለሚከፍሉ ገንዘባቸው እየተሟጠጠ ነው።—ማቴዎስ 23:1–3
5. የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት “ታማኝና ልባም ባሪያ” ሆነው ያልተገኙት ለምንድን ነው?
5 ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩትን ቀሳውስት አስመልክቶ እንዲህ በማለት በትክክል መናገር ችሎ ነበር፦ “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፣ በውጭ አምረው የሚታዩ በውስጥ ግን የሙታን አጥንት ርኩሰትም ሁሉ የተሞሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮችን ስለምትመስሉ፣ ወዮላችሁ። እንዲሁ እናንተ ደግሞ በውጭ ለሰው እንደ ጻድቃን ትታያላችሁ፣ በውስጣችሁ ግን ግብዝነትና ዓመፀኝነት ሞልቶባችኋል።” በዚህም ምክንያት አምላክ ምሥራቹን የመስበክን ተልእኮ ለካቶሊክ፣ ለፕሮቴስታንት፣ ለኦርቶዶክስም ሆነ ለሌላ ለማንኛውም የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖት ቀሳውስት አልሰጠም። አስቀድሞ በትንቢት የተነገረለት “ታማኝና ልባም ባሪያ” መሆናቸውን አላስመሠከሩም።—ማቴዎስ 23:27, 28፤ 24:45–47
ምሥራቹ አስቀድሞ መሰበክ ያለበት ለምንድን ነው?
6. በቅርቡ ምን ነገሮች ይከናወናሉ?
6 ኢየሱስ የምሥራቹ ለአሕዛብ ሁሉ እንዲሰበክ የሰጠውን ትዕዛዝ በአጭሩ የገለጸው ማርቆስ “አስቀድሞ” የሚለውን ቃል የተጠቀመው እርሱ ብቻ ነው። (ማርቆስ 13:10፤ ከማቴዎስ 24:14 ጋር አወዳድር።) በጄ ቢ ፊሊፕስ የተዘጋጀው የእንግሊዝኛ ትርጉም እንዲህ ይነበባል፦ “መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት ወንጌል ለአሕዛብ ሁሉ መሰበክ አለበት።” “አስቀድሞ” የሚለው ቃል ተውሳከ ግስ ሆኖ ሲገባ ዓለም አቀፉን የወንጌላዊነት ሥራ ተከትለው የሚመጡ ሌሎች ክስተቶች እንደሚኖሩ ያመለክታል። እነዚህ ክስተቶች ወደፊት የሚመጣውን ታላቅ መከራና በአዲሲቱ ዓለም ላይ በበላይነት የሚያስተዳድረውን የክርስቶስን የጽድቅ አገዛዝ ያካትታሉ።—ማቴዎስ 24:21–31፤ ራእይ 16:14–16፤ 21:1–4
7. አምላክ ምሥራቹ አስቀድሞ እንዲሰበክ የፈለገው ለምንድን ነው?
7 ታዲያ አምላክ ምሥራቹ አስቀድሞ እንዲሰበክ የፈለገው ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት ይሖዋ የፍቅር፣ የፍትሕ፣ የጥበብና የኃይል አምላክ ስለሆነ ነው። በማቴዎስ 24:14 እና በማርቆስ 13:10 ላይ ተመዝግበው በሚገኙት የኢየሱስ ቃላት አፈጻጸም ላይ እነዚህ የይሖዋ ባሕርያት የተገለጹበትን አስደናቂ ሁኔታ ማግኘት እንችላለን። እስቲ እነዚህን ባሕርያት አንድ በአንድ በአጭሩ እንመርምራቸውና ከምሥራቹ መሰበክ ጋር እንዴት እንደሚዛመዱ እንመልከት።
ምሥራቹና የይሖዋ ፍቅር
8. የምሥራቹ ስብከት የአምላክ ፍቅር መግለጫ የሆነው እንዴት ነው? (1 ዮሐንስ 4:7–16)
8 የምሥራቹ ስብከት የአምላክን ፍቅር የሚያንጸባርቀው እንዴት ነው? አንደኛው ምክንያት ለአንድ ዘር ወይም ወገን ብቻ እንዲነገር የታሰበ መልዕክት ስላልሆነ ነው። “ለአሕዛብ ሁሉ” የሚነገር ምሥራች ነው። አምላክ ሰብዓዊውን ቤተሰብ እጅግ ስለሚያፈቅር አንድያ ልጁ ለአንድ ዘር ብቻ ሳይሆን ለሰው ዘር ኃጢአት በሙሉ ቤዛዊ መሥዋዕት እንዲሆን ወደ ምድር ላከው። ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፣ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና።” (ዮሐንስ 3:16, 17) እውነትም ሰላም፣ ስምምነትና ፍትሕ የሚሰፍንበት አዲስ ዓለም ይመጣል የሚል ተስፋ ያዘለው መልዕክት የአምላክ ፍቅር ማስረጃ ነው።—2 ጴጥሮስ 3:13
ምሥራቹና የይሖዋ ኃይል
9. ይሖዋ ምሥራቹ በሕዝበ ክርስትና ታላላቅ ሃይማኖቶች እንዲሰበክ ያላደረገው ለምንድን ነው?
9 በምሥራቹ ስብከት የይሖዋ ኃይል የታየው እንዴት ነው? እስቲ ቆም በልና ይህን ተልእኮ እንዲፈጽሙ እነማንን እንደተጠቀመ አስብ። እንደ ሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ወይም እንደ ታላላቆቹ የፕሮቴስታንት እምነት ክፍሎች ያሉትን ከሁሉም የላቀ ኃይል ባላቸው የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ ድርጅቶች ተጠቅሟልን? አልተጠቀመም። በፖለቲካ ውስጥ የሚያደርጉት ተሳትፎ በዚህ ሥራ ለመመደብ ብቃት የሌላቸው አድርጓቸዋል። (ዮሐንስ 15:19፤ 17:14፤ ያዕቆብ 4:4) ያካበቱት ከፍተኛ ሀብት፣ ከከፍተኛው የገዢ መደብ ጋር ያላቸው ትስስርና የሚያሳድሩት ተጽዕኖም ሆነ ከወግና ልማድ ጋር ቁርኝት ያለው ሃይማኖታዊ መሠረተ ትምህርታቸው ይሖዋ አምላክን አይስበውም። የአምላክ ፈቃድ እንዲፈጸም ሰብዓዊ ኃይል አላስፈለገም።—ዘካርያስ 4:6
10. አምላክ የስብከቱን ሥራ እንዲያከናውኑ የመረጠው እነማንን ነው?
10 ሁኔታው ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ጉባኤ ደብዳቤ ሲጽፍ እንዳለው ነው፦ “ወንድሞች ሆይ፣ መጠራታችሁን ተመልከቱ፤ እንደ ሰው ጥበብ ጥበበኞች የሆኑ ብዙዎች፣ ኀያላን የሆኑ ብዙዎች፣ ባላባቶች የሆኑ ብዙዎች አልተጠሩም። ነገር ግን እግዚአብሔር ጥበበኞችን እንዲያሳፍር የዓለምን ሞኝ ነገር መረጠ፤ ብርቱንም ነገር እንዲያሳፍር እግዚአብሔር የዓለምን ደካማ ነገር መረጠ፤ እግዚአብሔርም የሆነውን ነገር እንዲያጠፋ የዓለምን ምናምንቴ ነገር የተናቀውንም ነገር ያልሆነውንም ነገር መረጠ፣ ሥጋን የለበሰ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እንዳይመካ።”—1 ቆሮንቶስ 1:26–29
11. ምሥክሮቹን ከሌሎች ሁሉ ፈጽሞ ልዩ ያደረጓቸው እውነታዎች ምንድን ናቸው?
11 የይሖዋ ምሥክሮች በድርጅታቸው ውስጥ ያሉት ሀብታሞች በጣም ጥቂት ናቸው። በመካከላቸው ከፍተኛ የፖለቲካ ሥልጣን ያለው አንድም ሰው የለም። በፖለቲካው ጉዳዮች ጥብቅ የገለልተኝነት አቋም መያዛቸው አንዳችም ዓይነት ፖለቲካዊ ተጽዕኖ ማሳደር አይችሉም ማለት ነው። በተቃራኒው በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን በሃይማኖትና በፖለቲካ መሪዎች ቆስቋሽነት ብዙ ጊዜ አሰቃቂ ለሆነ ስደት ሰለባነት ተዳርገዋል። የናዚ፣ የፋሺስት፣ የኮሙኒስት፣ የብሔራዊ ስሜትና የሐሰት ሃይማኖት ደቀ መዝሙሮች በጫሩት ክብሪት ይህ ነው የማይባል ተቃውሞ ቢደርስባቸውም እንኳ ምሥክሮቹ ምሥራቹን በዓለም በሙሉ እየሰበኩ ከመሆናቸውም ሌላ ቁጥራቸውም በሚያስደንቅ ሁኔታ ጨምሯል።—ኢሳይያስ 60:22
12. ምሥክሮቹ ሥራቸው ሊሳካ የቻለው ለምንድን ነው?
12 ምሥክሮቹ ለሥራቸው መሳካት ምክንያት ሆኗል ብለው የሚጠቅሱት ነገር ምንድን ነው? ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ሲል ቃል ገብቶላቸው ነበር፦ “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፣ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ።” ታዲያ ለሥራቸው መሳካት ምክንያት የሆነው ነገር ምንድን ነው? ኢየሱስ “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ” ብሏል። ዛሬም ልክ እንደዚሁ ምሥክሮቹ በዓለም አቀፉ አገልግሎታቸው ስኬታማ እንዲሆኑ ያስቻላቸው ዋናው ነገር የሰው ችሎታ ሳይሆን ከአምላክ የመጣ ኃይል ነው። አምላክ ከሰዎች መካከል በጣም ደካማ የሚመስሉትን በመጠቀም በታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ታላቅ የማስተማር ሥራ እያከናወነ ነው።—ሥራ 1:8፤ ኢሳይያስ 54:13
ምሥራቹና የይሖዋ ጥበብ
13. (ሀ) ምሥክሮቹ በፈቃደኝነትና ያለምንም ክፍያ የሚያገለግሉት ለምንድን ነው? (ለ) ሰይጣን ላመጣበት ነቀፋ ይሖዋ መልስ እየሰጠ ያለው እንዴት ነው?
13 ምሥራቹ የሚሰበከው በፈቃደኛ ሠራተኞች ነው። ኢየሱስ “በነፃ የተቀበላችሁትን በነፃ ስጡ” ብሏል። (ማቴዎስ 10:8 የ1980 ትርጉም) ስለዚህ ማንኛውም የይሖዋ ምሥክር አምላክን በማገልገሉ ደሞዝ አይከፈለውም፤ እንዲከፈለውም አይጠብቅም። እንዲያውም በስብሰባዎቻቸው ላይ እየዞሩ የርዳታ ገንዘብ አይሰበስቡም። ያላንዳች የስስት ጥቅም ፍለጋ ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ ለአምላክ ወስነው በሚሰጡት አገልግሎት አማካኝነት አምላክ ለከሳሹ ለሰይጣን ዲያብሎስ መልስ እንዲሰጥ ለማስቻል ፈቃደኞች ናቸው። ይህ የአምላክ ተቃዋሚ የሆነ መንፈስ ሰዎች ለራሳቸው የስስት ጥቅም አስበው ካልሆነ በቀር አምላክን አያገለግሉትም ብሏል። ይሖዋ በጥበቡ በሚልዮን የሚቆጠሩ በታማኝነት ከጎኑ የቆሙ ክርስቲያን ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት፣ ከመንገድ ወደ መንገድ እየሄዱና መደበኛ ባልሆነ መንገድ በሚያከናውኑት የምሥራቹ ስብከት አማካኝነት ሰይጣን ላስነሳው ክስ የማያወላዳ መልስ ሰጥቷል።—ኢዮብ 1:8–11፤ 2:3–5፤ ምሳሌ 27:11
14. ጳውሎስ የጠቀሰው ‘የተሰወረ ጥበብ’ ምንድን ነው?
14 ምሥራቹ እንዲሰበክ በማድረግ ረገድ የአምላክ ጥበብ የታየበት ሌላው ማስረጃ የመንግሥቱ ተስፋ ራሱ የአምላክ ጥበብ መግለጫ መሆኑ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በበሰሉት መካከል ግን ጥበብን እንናገራለን፣ ነገር ግን የዚችን ዓለም ጥበብ አይደለም የሚሻሩትንም የዚችን ዓለም ገዦች ጥበብ አይደለም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን የወሰነውን፣ ተሰውሮም የነበረውን የእግዚአብሔርን ጥበብ በምሥጢር እንናገራለን።” ይህ ‘የተሰወረ ጥበብ’ አምላክ በኤደን የተጀመረውን ዓመፅ የሚያስቆምበትን ጥበብ የሚያመለክት ነው። የዚያ ቅዱስ ምስጢር ጥበብ የአምላክ መንግሥት ምሥራች አስኳል በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ተገልጧል።a—1 ቆሮንቶስ 2:6, 7፤ ቆላስይስ 1:26–28
ምሥራቹና የአምላክ ፍትሕ
15. ይሖዋ የፍትሕ አምላክ መሆኑን እንዴት እናውቃለን? (ዘዳግም 32:4፤ መዝሙር 33:5)
15 በማርቆስ 13:10 ላይ ያለውን “አስቀድሞ” የሚለውን ቃል አስፈላጊነት ይበልጥ የምንመለከተው ከፍትሕ ጋር በተያያዘ ሁኔታ ነው። ይሖዋ በፍቅራዊ ደግነት የለዘበ ፍትሕ የሚያሳይ አምላክ ነው። በነቢዩ በኤርምያስ በኩል እንዲህ ብሏል፦ “የሚመካው፦ ምሕረትንና [ፍቅራዊ ደግነትንና አዓት] ፍርድን [ፍትሕን አዓት] ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ፤ ደስ የሚያሰኙኝ እነዚህ ናቸውና፣ ይላል እግዚአብሔር።”—ኤርምያስ 9:24
16. ፍትሕ አስቀድሞ ማስጠንቀቂያ መስጠትን የሚጠይቅ መሆኑን በምሳሌ ማስረዳት የሚቻለው እንዴት ነው?
16 የይሖዋ ፍትሕ በምሥራቹ ስብከት ረገድ የታየው እንዴት ነው? ይህን ለማስረዳት እንግዶች ሲመጡ የሚቀርብላቸውን በጣም ጣፋጭ የሆነ የቸኮላት ኬክ የሠራችን አንዲት እናት ምሳሌ እንጠቀም። ኬኩ የሚበላው መቼ እንደሆነ ለልጆቿ ምንም ሳትነግር በወጥ ቤቱ ጠረጴዛ ላይ ብትተወው ልጆቹ ምን ያደርጋሉ ብላችሁ ትጠብቃላችሁ? ሁላችንም በአንድ ወቅት ልጆች ነበርን! አንዲት ትንሽ ጣት ኬኩን ለመቅመስ መነካካቷ አይቀርም። እናቲቱ መጀመሪያውኑ ተገቢውን ማስጠንቀቂያ ሳትሰጥ ከቀረች ተግሣጽ ለመስጠት በቂ ምክንያት አይኖራትም። በሌላ በኩል ግን ኬኩ የሚበላው ቆየት ብሎ እንግዶቹ ሲመጡ እንደሆነና መንካት እንደሌለባቸው በደንብ ገልጻ ከነገረቻቸው ማስጠንቀቂያውን ሰጥታለች ማለት ነው። ትእዛዙን ከጣሱ ጥብቅና ፍትሐዊ እርምጃ መውሰድ ትችላለች።—ምሳሌ 29:15
17. ይሖዋ ከ1919 ጀምሮ ፍትሑን ልዩ በሆነ መንገድ የገለጸው እንዴት ነው?
17 ይሖዋ በፍትሑ ምክንያት በመጀመሪያ ተገቢውን ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ በዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ላይ የፍርድ እርምጃ አይወስድም። በዚህም ምክንያት በተለይ አንደኛው የዓለም ጦርነት “የምጥ ጣር” ካመጣ በኋላ ይኸውም ከ1919 ጀምሮ ይሖዋ ምሥክሮቹ በመላዋ ምድር ላይ የምሥራቹን በቅንዓት እንዲሰብኩ አድርጓል። (ማቴዎስ 24:7, 8, 14) አሕዛብ ይህን ልዩ ማስጠንቀቂያ አልሰማንም ሊሉ ከቶ አይችሉም።
ዓለም በስብከቱ ሥራ ምን ያህል ተሸፍኗል?
18. (ሀ) ምሥክሮቹ ራቅ ብለው በሚገኙ ሥፍራዎች የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ? (ለ) ይህን በተመለከተ አንተ የምታውቃቸው ምን ሌሎች ምሳሌዎች አሉ?
18 ላስት ፕሌስስ—ኤ ጆርኒ ኢን ዘ ኖርዝ (የማይደፈሩ ስፍራዎች፣ በስተሰሜን የተደረገ ጉዞ) በተባለው መጽሐፍ ላይ የዚህን ዓለም አቀፍ የማስተማር ሥራ ውጤታማነት የሚጠቁም ነገር ማየት ይቻላል። የመጽሐፉ ደራሲ ከስኮትላንድ በስተሰሜን ከሚገኙት የሼትላንድ ደሴቶች መካከል አንዷ ወደሆነችው ነጠል ብላ ወደምትገኘው የፎላ ደሴት ለመድረስ የተነደፉትን የባሕር መሥመሮች በሚያመለክቱት ካርታዎች ላይ ሲያማትሩ ያዩትን ነገር ገልጸዋል። ካርታዎቹ “በደሴቲቷ ዙሪያ በሙሉ የሰጠሙ መርከቦች ስብርባሪ፣ አለቶች፣ ወደ ባሕሩ ያገጠጡ የተራራ ጠርዝ አለቶችና ወደ ደሴቲቱ ለማለፍ የሚያስቸግሩ እንቅፋት የሆኑ ነገሮች”ን ያሳያሉ። በካርታዎቹ ላይ ያሉት ምልክቶች ወደ ደሴቲቷ ለመግባት ያሰበውን መርከበኛ መንገዱን እንዲቀይር ያደርጉታል። ፎላን የከበበው ውቅያኖስ አስፈሪ በሆኑ ፈንጂዎች የተሞላ ያህል ነው። ይህም በመሆኑ በሞተር ጀልባ የሚቀዝፉ ሰዎች፣ ለመዝናናት የሚሄዱ ሰዎችና አልፎ ተርፎም ለሕዝብ ግልጋሎት የሚውሉ ሥራዎችን የሚያከናውነው የእንግሊዝ ንግሥት ብርጌድም እንኳ ወደ ደሴቲቱ እንዳይጠጉ አድርጓቸዋል። ነገር ግን የይሖዋ ምሥክሮችን እነዚህ እንቅፋቶች እንዳልበገሯቸው በጥቂት ቀናት ውስጥ ማወቅ ችያለሁ” ሲሉ ተናግረዋል። በመቀጠልም እንዲህ አሉ፦ “እምነታቸውን የሚቀበሉ ሰዎችን ፍለጋ በትልልቅ ከተሞች ውስጥ በሚገኙ ችምችም ብለው በተሰሩ ቤቶችና በሦስተኛው ዓለም አገሮች ውስጥ እግራቸው እስከሚነቃ ድረስ እንደሚዞሩ ሁሉ ራቅ ባለ ሥፍራ በምትገኘው በፎላ ያሉ ሰዎች እምነታቸውን እንዲቀበሉ ለማድረግም ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ።” አንድ የደሴቲቷ ነዋሪ የሆነ አንድሪው የተባለ ሰው ከጥቂት ወራት በፊት በቤቱ ደጃፍ ላይ ተቀምጦ ያገኘው አንድ መጠበቂያ ግንብ እንዳለው በአድናቆት ተናግረዋል። አክለውም እንዲህ አሉ፦ “ይህ ከሆነ ከአንድ ሳምንት በኋላ በፌሮ [በስተሰሜን በሚገኘው ውቅያኖስ ላይ ያሉ ደሴቶች] አንድ [በዴንማርክ ቋንቋ የተዘጋጀ ንቁ!] አይቻለሁ፤ እንዲሁም ከሁለት ወራት በኋላ በግሪንላንድ ኑክ ውስጥ አንድ [በዴንማርክ ቋንቋ የተዘጋጀ መጠበቂያ ግንብ] ተመልክቻለሁ።” በእነዚህ በስተሰሜን በሚገኙ ክልሎች ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያከናውኑትን ቅንዓት የተሞላበት ሥራ የሚያረጋግጥ እንዴት ያለ ግሩም ምሥክርነት ነው!
ምሥክሮቹ በስብከቱ ሥራቸው እንዲገፉበት ያደረጋቸው ምንድን ነው?
19, 20. (ሀ) የይሖዋ ምሥክሮች በስብከቱ ሥራ እንዲገፉበት የሚገፋፋቸው ነገር ምንድን ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ መልስ የሚሰጥባቸው ጥያቄዎች የትኞቹ ናቸው?
19 እርግጥ ነው፣ አንድ ሰው ምሥክር ሆኖ ምንም ያህል ዓመት ቢያሳልፍም እንኳ ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ለማያውቁት ሰው መስበክ ቀላል ነገር አይደለም። ታዲያ እነዚህ ክርስቲያኖች በስብከቱ ሥራቸው እንዲገፉበት ያደረጋቸው ነገር ምንድን ነው? ለአምላክ የሚያደርጉት ክርስቲያናዊ ውስንነታቸውና ኃላፊነት እንዳለባቸው ሆኖ ስለሚሰማቸው ነው። ጳውሎስ “ወንጌልን ብሰብክ እንኳ የምመካበት የለኝም፤ ግድ ደርሶብኝ ነውና፤ ወንጌልንም ባልሰብክ ወዮልኝ” ሲል ጽፏል። እውነተኛ ክርስቲያኖች ሕይወትን የሚያስገኝ መልዕክት አላቸው፤ ታዲያ ይህን መልዕክት እንዴት ከሌሎች ሰዎች ሊደብቁት ይችላሉ? በአደጋ ጊዜ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ የቀረን ሰው በደም ዕዳ ተጠያቂ የሚያደርገው መሠረታዊ ሥርዓት የምሥራቹን የግድ እንድንሰብክ ይገፋፋናል።—1 ቆሮንቶስ 9:16፤ ሕዝቅኤል 3:17–21
20 ታዲያ ምሥራቹ በመሰበክ ላይ ያለው እንዴት ነው? ምሥክሮቹ ላገኙት ስኬታማነት ቁልፉ ምንድን ነው? የእውነተኛ ሃይማኖት ተከታዮች መሆናቸውን ለይተው የሚያሳውቁት የአገልግሎታቸውና የአደረጃጀታቸው ገጽታዎች የትኞቹ ናቸው? የሚቀጥለው ርዕስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ስለ አምላክ ጥበብና ስለ ‘ቅዱሱ ምስጢር’ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ኒውዮርክ በሚገኘው በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ጥራዝ ሁለት ገጽ 1190 ተመልከት።
ታስታውሳለህን?
◻ የይሖዋ ምሥክሮችን ከቀሳውስት ለይቶ የሚያሳውቃቸው ምንድን ነው?
◻ ስብከቱ የአምላክን ፍቅር፣ ኃይልና ጥበብ የሚያንጸባርቀው እንዴት ነው?
◻ የምሥራቹ ስብከት የአምላክን ፍትሕ የሚያንጸባርቀው እንዴት ነው?
◻ የይሖዋ ምሥክሮችን በአገልግሎታቸው እንዲገፉ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሰዎች ምንም ያህል ገለልተኛ በሆነ አካባቢ ርቀው ቢኖሩም እንኳ የይሖዋ ምሥክሮች እነርሱንም አግኘተው ለማነጋገር ይፈልጋሉ