የማርቆስ ወንጌል
13 ከቤተ መቅደስ እየወጣ ሳለ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ “መምህር፣ እንዴት ያሉ ግሩም ድንጋዮችና ሕንጻዎች እንደሆኑ ተመልከት!” አለው።+ 2 ኢየሱስ ግን “እነዚህን ታላላቅ ሕንጻዎች ታያለህ? ይህ ሁሉ ሳይፈርስ እንዲህ ድንጋይ በድንጋይ ላይ እንደተነባበረ ከቶ አይኖርም” አለው።+
3 በቤተ መቅደሱ ትይዩ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ሳለ ጴጥሮስ፣ ያዕቆብ፣ ዮሐንስና እንድርያስ ብቻቸውን ሆነው እንዲህ በማለት ጠየቁት፦ 4 “እስቲ ንገረን፣ እነዚህ ነገሮች የሚፈጸሙት መቼ ነው? የእነዚህ ነገሮች ሁሉ መደምደሚያ መቅረቡን የሚያሳየው ምልክትስ ምንድን ነው?”+ 5 ኢየሱስም እንዲህ ይላቸው ጀመር፦ “ማንም እንዳያሳስታችሁ ተጠንቀቁ።+ 6 ብዙዎች ‘እኔ እሱ ነኝ’ እያሉ በስሜ ይመጣሉ፤ ብዙዎችንም ያሳስታሉ። 7 ከዚህም ሌላ ጦርነትና የጦርነት ወሬ ስትሰሙ አትደናገጡ፤ እነዚህ ነገሮች መፈጸማቸው የግድ ነው፤ ሆኖም ፍጻሜው ገና ነው።+
8 “ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሳልና፤+ በተለያየ ስፍራ የምድር ነውጥ ይከሰታል፤ በተጨማሪም የምግብ እጥረት ይኖራል።+ እነዚህ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው።+
9 “እናንተ ግን ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ሰዎች ለፍርድ ሸንጎዎች አሳልፈው ይሰጧችኋል፤+ በምኩራብም ትገረፋላችሁ፤+ በእኔ ምክንያት በገዢዎችና በነገሥታት ፊት ያቀርቧችኋል፤ በዚያ ጊዜ ለእነሱ መመሥከር ትችላላችሁ።+ 10 አስቀድሞም ምሥራቹ ለብሔራት ሁሉ መሰበክ አለበት።+ 11 አሳልፈው ለመስጠት በሚወስዷችሁ ጊዜም ምን እንላለን በማለት አስቀድማችሁ አትጨነቁ፤ ከዚህ ይልቅ በዚያች ሰዓት የሚሰጣችሁን ተናገሩ፤ የሚናገረው መንፈስ ቅዱስ እንጂ እናንተ አይደላችሁምና።+ 12 በተጨማሪም ወንድም ወንድሙን፣ አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፤ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ይነሳሉ፤ ደግሞም ያስገድሏቸዋል።+ 13 በስሜ የተነሳም ሰዎች ሁሉ ይጠሏችኋል።+ እስከ መጨረሻው የጸና+ ግን* ይድናል።+
14 “ይሁንና ጥፋት የሚያመጣው ‘ርኩስ ነገር’+ በማይገባው ስፍራ ቆሞ ስታዩ አንባቢው ያስተውል፤ በዚህ ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ።+ 15 በጣሪያ* ላይ ያለ ሰው አይውረድ፤ አንዳችም ነገር ለመውሰድ ወደ ቤቱ አይግባ፤ 16 በእርሻም ያለ መደረቢያውን ለመውሰድ ወደ ኋላ አይመለስ። 17 በእነዚያ ቀናት ለነፍሰ ጡሮችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው!+ 18 ይህ በክረምት እንዳይሆን ዘወትር ጸልዩ፤ 19 ምክንያቱም በእነዚያ ቀናት ከአምላክ የፍጥረት ሥራ መጀመሪያ አንስቶ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ሆኖ የማያውቅ ዳግመኛም የማይሆን+ መከራ+ ይከሰታል። 20 እንዲያውም ይሖዋ* ቀኖቹን ባያሳጥራቸው ኖሮ ሥጋ ሁሉ ባልዳነ ነበር። ሆኖም እሱ ለመረጣቸው ምርጦች ሲል ቀኖቹን አሳጥሯል።+
21 “በዚያን ጊዜም ማንም ‘እነሆ፣ ክርስቶስ ይኸውላችሁ’ ወይም ‘እነሆ፣ ያውላችሁ’ ቢላችሁ አትመኑ።+ 22 ምክንያቱም ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ሐሰተኛ ነቢያት ይነሳሉ፤+ ቢቻላቸው የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ምልክቶችና አስደናቂ ነገሮች ያደርጋሉ። 23 ስለዚህ ተጠንቀቁ።+ ሁሉን ነገር አስቀድሜ ነግሬአችኋለሁ።
24 “ሆኖም በእነዚያ ቀናት፣ ከዚያ መከራ በኋላ ፀሐይ ትጨልማለች፤ ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም፤+ 25 ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፤ በሰማያት ያሉ ኃይላትም ይናወጣሉ። 26 ከዚያም የሰው ልጅ+ በታላቅ ኃይልና ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል።+ 27 እሱም መላእክቱን ልኮ ከአራቱ ነፋሳት፣ ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ ለእሱ የተመረጡትን ይሰበስባል።+
28 “እንግዲያው ይህን ምሳሌ ከበለስ ዛፍ ተማሩ፦ ቅርንጫፎቿ ሲለመልሙና ቅጠሎቿ ሲያቆጠቁጡ በጋ* እንደቀረበ ታውቃላችሁ።+ 29 በተመሳሳይ እናንተም እነዚህ ነገሮች ሲፈጸሙ ስታዩ የሰው ልጅ ደጃፍ ላይ እንደደረሰ እርግጠኞች ሁኑ።+ 30 እውነት እላችኋለሁ፣ እነዚህ ነገሮች ሁሉ እስኪፈጸሙ ድረስ ይህ ትውልድ ፈጽሞ አያልፍም።+ 31 ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤+ ቃሌ ግን ፈጽሞ አያልፍም።+
32 “ስለዚያ ቀን ወይም ሰዓት ከአብ በቀር በሰማይ ያሉ መላእክትም ሆኑ ወልድ፣ ማንም አያውቅም።+ 33 ስለዚህ የተወሰነው ጊዜ መቼ እንደሆነ ስለማታውቁ+ ምንጊዜም በንቃት ተከታተሉ፤ ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ።+ 34 ይህም ለባሪያዎቹ ሥልጣን ከሰጠና ለእያንዳንዱ የሥራ ድርሻውን ከመደበ በኋላ በር ጠባቂውን ነቅቶ እንዲጠብቅ በማዘዝ+ ቤቱን ትቶ ወደ ሌላ አገር እንደሄደ ሰው ነው።+ 35 ስለዚህ የቤቱ ጌታ፣ በምሽት* ይሁን በእኩለ ሌሊት* ወይም ዶሮ ሲጮኽ* ይሁን ከመንጋቱ* በፊት፣ መቼ እንደሚመጣ ስለማታውቁ ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ፤+ 36 አለዚያ ድንገት ሲመጣ ተኝታችሁ ያገኛችኋል።+ 37 ይሁንና ለእናንተ የምነግራችሁን ለሁሉም እናገራለሁ፤ ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ።”+