ትዳራችሁን ለመታደግ የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ
“ላገቡት ሰዎች ይህን መመሪያ እሰጣለሁ፤ ይሁንና ይህ መመሪያ የጌታ እንጂ የእኔ አይደለም።”—1 ቆሮ. 7:10
ልታብራራ ትችላለህ?
በትዳር የተሳሰሩ ሰዎችን አምላክ አጣምሯቸዋል ሊባል የሚችለው እንዴት ነው?
ሽማግሌዎች፣ በትዳራቸው ውስጥ ችግር ያለባቸውን ክርስቲያኖች መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?
ጋብቻን እንዴት ልንመለከተው ይገባል?
1. ክርስቲያኖች ጋብቻን እንዴት ሊመለከቱት ይገባል? ለምንስ?
ክርስቲያኖች ትዳር ሲመሠርቱ በአምላክ ፊት ስእለት ወይም ቃል ኪዳን ይገባሉ፤ ይህ ደግሞ ከባድ ኃላፊነት ነው። (መክ. 5:4-6) ይሖዋ የጋብቻ መሥራች በመሆኑ በትዳር የተሳሰሩ ሰዎችን አምላክ ‘አጣምሯቸዋል’ ሊባል ይችላል። (ማር. 10:9) ጋብቻን በተመለከተ የአገሩ ሕግ ምንም ይሁን ምን አምላክ እነዚህን ሰዎች ምንጊዜም የሚመለከታቸው እንደተጣመሩ አድርጎ ነው። በመሆኑም የይሖዋ አገልጋዮች፣ ትዳር የመሠረቱት የእሱ አምላኪዎች ከመሆናቸው በፊትም ይሁን በኋላ ጋብቻን እንደ ዕድሜ ልክ ጥምረት አድርገው መመልከት ይኖርባቸዋል።
2. በዚህ የጥናት ርዕስ ላይ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
2 ስኬታማ የሆነ ትዳር ከፍተኛ ደስታ ያስገኛል። ሆኖም አንድ ባልና ሚስት ትዳራቸው ውጥረት የነገሠበት ቢሆን ምን ማድረግ ይችላሉ? እንዲህ ዓይነቱን ትዳር ማጠናከር ይቻላል? ትዳራቸው አደጋ ላይ የወደቀ ባልና ሚስት ሰላማቸውን ጠብቀው ለመኖር ምን እርዳታ ማግኘት ይችላሉ?
የደስታ ምንጭ ወይስ ለሐዘን የሚዳርግ?
3, 4. አንድ ክርስቲያን የትዳር ጓደኛ ሲመርጥ ጥበብ የጎደለው ውሳኔ ካደረገ ምን ሊፈጠር ይችላል?
3 አንድ ክርስቲያን ጋብቻው ስኬታማ ከሆነ ግለሰቡ ደስተኛ ይሆናል፤ ትዳሩም ለይሖዋ ክብር ያመጣል። በአንጻሩ ደግሞ ከትዳር ጓደኛው ጋር አብሮ መኖር ካቃተው ሁኔታው ከሐዘን ባለፈ የከፋ መዘዝ ማስከተሉ አይቀርም። ትዳር ለመመሥረት የሚያስቡ ያላገቡ ክርስቲያኖች የአምላክን መመሪያ መከተላቸው ጋብቻቸውን በጥሩ መንገድ ለመጀመር ያስችላቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ የትዳር ጓደኛ በመምረጥ ረገድ ጥበብ የጎደለው ውሳኔ የሚያደርጉ ክርስቲያኖች ደስታቸውን ሊያጡ እንዲሁም ለሐዘን ሊዳረጉ ይችላሉ። ለአብነት ያህል፣ አንዳንድ ወጣቶች ትዳር ለሚያስከትለው ኃላፊነት ዝግጁ ሳይሆኑ መጠናናት ይጀምራሉ። አንዳንዶች ደግሞ የትዳር ጓደኛ ሊሆናቸው የሚችለውን ሰው በኢንተርኔት ይፈልጋሉ፤ ከዚያም ከዚህ ሰው ጋር ዘለው ትዳር ውስጥ በመግባት ደስታ የራቀው ሕይወት ሲመሩ ይታያል። ሌሎች ደግሞ በሚጠናኑበት ጊዜ ከባድ ኃጢአት በመፈጸማቸው አንዳቸው ለሌላው ያላቸው አክብሮት ጠፍቷል፤ በመሆኑም ለመጋባት በሚወስኑበት ጊዜ የትዳር ሕይወታቸው በአብዛኛው በጠንካራ መሠረት ላይ የተገነባ አይሆንም።
4 አንዳንድ ክርስቲያኖች ደግሞ “በጌታ ብቻ” እንድናገባ የተሰጠውን ትእዛዝ በመጣሳቸው በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ መኖር የሚያስከትለውን መዘዝ ለማጨድ ይገደዳሉ። (1 ቆሮ. 7:39) የአንተም ሁኔታ እንደዚህ ከሆነ አምላክ ይቅር እንዲልህና እንዲረዳህ በጸሎት ጠይቀው። ይሖዋ፣ አንድ ሰው ቀደም ሲል ስህተት በመሥራቱ የተነሳ የሚደርስበትን መጥፎ ውጤት ባያስወግድለትም ንስሐ ከገባ ግን የሚያጋጥሙትን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመቋቋም የሚያስችለውን እርዳታ ይሰጠዋል። (መዝ. 130:1-4) ዛሬም ሆነ ለዘላለም አምላክን ለማስደሰት ጥረት የምታደርግ ከሆነ የይሖዋ ‘ደስታ ብርታትህ’ ይሆናል።—ነህ. 8:10
ትዳሩ አደጋ ሲደቀንበት
5. ክርስቲያኖች ትዳራቸው ደስታ የራቀው በሚሆንበት ጊዜ ምን ነገሮችን ማሰብ አይገባቸውም?
5 በትዳራቸው ችግር የገጠማቸው ሰዎች እንዲህ ብለው ያስቡ ይሆናል፦ ‘ደስታ የራቀውን ትዳሬን ለመታደግ ጥረት ማድረጌ ምን ጥቅም አለው? ጊዜውን ወደኋላ መመለስ ቢቻል ኖሮ ሌላ ሰው አገባ ነበር!’ በተጨማሪም እንዲህ እያሉ ትዳራቸውን ስለማፍረስ ማውጠንጠን ሊጀምሩ ይችላሉ፦ ‘ነፃነትን መልሶ ማግኘት የመሰለ ምን ነገር አለ! ለምን ተፋትቼ አልገላገልም? ለፍቺ የሚያበቃ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያት ባይኖረኝም እንኳ ተለያይቼ በመኖር ሕይወቴን በአዲስ መልክ ማጣጣም እችላለሁ።’ እንዲህ ያሉ ሐሳቦችን ከማብሰልሰል ወይም በወሰድናቸው እርምጃዎች ከመቆጨት ይልቅ የአምላክን መመሪያ በመፈለግና ተግባር ላይ በማዋል ያለንበትን ሁኔታ ለማሻሻል ጥረት ማድረግ ይኖርብናል።
6. ኢየሱስ በማቴዎስ 19:9 ላይ ያለውን ሐሳብ ሲናገር ምን ማለቱ ነው?
6 ፍቺ የፈጸመ አንድ ክርስቲያን እንደገና ለማግባት ቅዱስ ጽሑፋዊ ነፃነት ሊኖረውም ላይኖረውም ይችላል። ኢየሱስ “በዝሙት ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ሚስቱን ፈቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ ምንዝር ይፈጽማል” ብሏል። (ማቴ. 19:9) “ዝሙት” የሚለው ቃል ምንዝርንና ከፆታ ግንኙነት ጋር የተያያዙ ሌሎች ከባድ ኃጢአቶችን ያመለክታል። አንድ ሰው ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ ሳይኖረው የመፋታት ሐሳብ ቢመጣበት ስለ ጉዳዩ የይሖዋን መመሪያ ለማግኘት መጸለዩ በጣም አስፈላጊ ነው።
7. የአንድ ክርስቲያን ትዳር ቢፈርስ ሌሎች ሰዎች ምን ሊያስቡ ይችላሉ?
7 አንድ ባልና ሚስት መፋታታቸው ወይም መለያየታቸው በመንፈሳዊ ችግር እንዳለባቸው ሊጠቁም ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ የሚከተለውን ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጥያቄ አንስቶ ነበር፦ “ደግሞስ አንድ ሰው የራሱን ቤተሰብ እንዴት እንደሚያስተዳድር ካላወቀ የአምላክን ጉባኤ እንዴት ሊንከባከብ ይችላል?” (1 ጢሞ. 3:5) እንዲያውም አንድ ባልና ሚስት ክርስቲያን ነን እያሉ ትዳራቸውን የሚያፈርሱ ከሆነ ሰዎች፣ የሚሰብኩትን ነገር ተግባራዊ እንደማያደርጉ ሊሰማቸው ይችላል።—ሮም 2:21-24
8. ባለትዳር የሆኑ ክርስቲያኖች ጋብቻቸውን ለማፍረስ መወሰናቸው ምን ችግር እንዳለባቸው ይጠቁማል?
8 ራሳቸውን ወስነው የተጠመቁ ክርስቲያኖች ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ ሳይኖራቸው ለመለያየት ወይም ለመፋታት ከወሰኑ ከመንፈሳዊነታቸው ጋር በተያያዘ የሆነ ጉድለት መኖሩ ግልጽ ነው። አንደኛው ወገን ምናልባትም ሁለቱም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኙ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ተግባራዊ ሳያደርጉ ቀርተው ሊሆን ይችላል። እነዚህ ባልና ሚስት ‘በፍጹም ልባቸው’ በይሖዋ ቢታመኑ ኖሮ ትዳራቸውን ከመፍረስ መታደግ የማይችሉበት ምንም ምክንያት የለም።—ምሳሌ 3:5, 6ን አንብብ።
9. አንዳንድ ክርስቲያኖች ከትዳር ጋር በተያያዘ ተስፋ ሳይቆርጡ ጥረት በማድረጋቸው የተባረኩት እንዴት ነው?
9 ሊፈርሱ ተቃርበው የነበሩ በርካታ ትዳሮች ከጊዜ በኋላ ስኬታማ ሆነዋል። ክርስቲያኖች በትዳራቸው ችግር ሲገጥማቸው ቶሎ ተስፋ የማይቆርጡ ከሆነ በአብዛኛው ጥሩ ውጤት ሊያገኙ ይችላሉ። በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ ሊከሰት የሚችለውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል። በዚህ ረገድ ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “እናንተ ሚስቶች፣ ለቃሉ የማይታዘዙ ባሎች ካሉ ያለ ቃል በሚስቶቻቸው ምግባር እንዲማረኩ ለገዛ ባሎቻችሁ ተገዙ፤ ሊማረኩ የሚችሉትም ንጹሕ ምግባራችሁንና የምታሳዩትን ጥልቅ አክብሮት በዓይናቸው ሲመለከቱ ነው።” (1 ጴጥ. 3:1, 2) በእርግጥም፣ አንድ የማያምን ሰው በትዳር ጓደኛው ግሩም ምግባር የተነሳ እውነተኛውን እምነት ሊቀበል ይችላል! በዚህ መንገድ ትዳራቸውን መታደጋቸው አምላክን የሚያስከብር ከመሆኑም ሌላ መላው ቤተሰብ እንዲባረክ ያደርጋል።
10, 11. በትዳር ውስጥ ምን ያልተጠበቁ ነገሮች ሊከሰቱ ይችላሉ? ሆኖም አንድ ክርስቲያን ስለ ምን ነገር እርግጠኛ መሆን ይችላል?
10 ብዙ ክርስቲያኖች ይሖዋን ለማስደሰት ስለሚፈልጉ ለትዳር የሚመርጡት ራሱን የወሰነ ታማኝ የእምነት ባልንጀራቸውን ነው። ያም ሆኖ ያልታሰቡ ነገሮች ሊከሰቱ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንደኛው የትዳር ጓደኛ ከባድ የስሜት ቀውስ ያጋጥመው ይሆናል። ወይም ደግሞ ከተጋቡ በኋላ አንዳቸው በመንፈሳዊ ሊቀዘቅዙ ይችላሉ። ሊንዳa የተባለች እህት ያጋጠማትን ሁኔታ እንደ ምሳሌ መጥቀስ እንችላለን። ሊንዳ ቀናተኛ ክርስቲያን እንዲሁም ታታሪ እናት ብትሆንም የይሖዋ ምሥክር የሆነው ባለቤቷ ከቅዱስ ጽሑፉ የወጣ አኗኗር መከተል ሲጀምር ሁኔታው ከአቅሟ በላይ ሆኖባት ነበር፤ በመጨረሻም ባለቤቷ ንስሐ ባለመግባቱ ከጉባኤ ተወገደ። አንድ ክርስቲያን እንዲህ ያለ ሁኔታ ቢያጋጥመውና ትዳሩን መታደግ እንደማይችል ቢሰማው ምን ማድረግ ይኖርበታል?
11 ‘የተፈጠረው ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ትዳሬን ለመታደግ ጥረት ማድረግ ይኖርብኛል?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። እርግጥ በዚህ ጉዳይ ላይ ማንም ሰው ውሳኔ ሊያደርግልህ አይችልም፤ ደግሞም እንዲህ ማድረግ ተገቢ አይደለም። ያም ሆኖ ሊፈርስ የተቃረበን ትዳር ለመታደግ የሚያነሳሱ አጥጋቢ ምክንያቶች አሉ። ፈሪሃ አምላክ ያለው አንድ ክርስቲያን ንጹሕ ሕሊና ለመያዝ ሲል በትዳር ውስጥ የሚገጥመውን ችግር ተቋቁሞ ለማለፍ የሚጥር ከሆነ አምላክ ይህን ሰው ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል። (1 ጴጥሮስ 2:19, 20ን አንብብ።) አንድ ሰው ትዳሩን ለመታደግ ልባዊ ጥረት ሲያደርግ ይሖዋ በቃሉና በመንፈሱ አማካኝነት ይረዳዋል።
ሊረዷችሁ ዝግጁዎች ናቸው
12. ሽማግሌዎች እርዳታቸውን የሚሹ ሰዎችን የሚመለከቱት እንዴት ነው?
12 በትዳርህ ውስጥ ችግር ካጋጠመህ የጎለመሱ ክርስቲያኖችን እርዳታ ከመጠየቅ ወደኋላ ማለት የለብህም። ሽማግሌዎች የመንጋው እረኛ እንደመሆናቸው መጠን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ምክር ሊለግሱህ ፈቃደኞች ናቸው። (ሥራ 20:28፤ ያዕ. 5:14, 15) ሽማግሌዎች ለአንተም ሆነ ለትዳር ጓደኛህ ያላቸው ግምት እንደሚቀንስ በማሰብ መንፈሳዊ እርዳታ ለማግኘት እንዲሁም በትዳራችሁ ውስጥ ያጋጠማችሁን ከባድ ችግር ለማወያየት ወደ እነሱ ከመሄድ ወደኋላ አትበል። እንዲያውም አምላክን ለማስደሰት ከልብ ጥረት እንደምታደርግ ሲመለከቱ ለአንተ ያላቸው ፍቅርና አክብሮት ይጨምራል።
13. ሐዋርያው ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 7:10-16 ላይ ምን ምክር ሰጥቷል?
13 በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ክርስቲያኖች እርዳታ በሚሹበት ጊዜ ሽማግሌዎች ጳውሎስ የሰጠውን ዓይነት ምክር መጠቀም ይችላሉ፤ ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ላገቡት ሰዎች ይህን መመሪያ እሰጣለሁ፤ ይሁንና ይህ መመሪያ የጌታ እንጂ የእኔ አይደለም፤ ሚስት ከባሏ አትለይ፤ ብትለይ ግን ሳታገባ ትኑር ወይም ከባሏ ትታረቅ፤ ባልም ሚስቱን መተው የለበትም። . . . አንቺ ሚስት፣ ባልሽን ታድኚው እንደሆነ ምን ታውቂያለሽ? ወይስ አንተ ባል፣ ሚስትህን ታድን እንደሆነ ምን ታውቃለህ?” (1 ቆሮ. 7:10-16) የማያምን የትዳር ጓደኛ እውነተኛውን አምልኮ ሲቀበል ማየት በእርግጥም ትልቅ በረከት ነው።
14, 15. አንድ ክርስቲያን ከትዳር ጓደኛው ለመለያየት ሊመርጥ የሚችለው መቼ ነው? ሆኖም ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ይሖዋን በጸሎት መጠየቅና ራሱን በሐቀኝነት መመርመር ያለበት ለምንድን ነው?
14 በአንዳንድ ሁኔታዎች ምክንያት አንዲት ክርስቲያን “ሚስት ከባሏ [ለመለየት]” ልትወስን ትችላለች። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንዶች የትዳር ጓደኛቸው መሠረታዊ ነገሮችን ለማሟላት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ለመለያየት ወስነዋል። ሌሎች ደግሞ ከትዳር ጓደኛቸው በሚደርስባቸው ከባድ አካላዊ ጥቃት ወይም መንፈሳዊነታቸው ሙሉ በሙሉ አደጋ ላይ በመውደቁ የተነሳ መለያየትን መርጠዋል።
15 ከትዳር ጓደኛ ጋር መለያየትን በተመለከተ አንድ ክርስቲያን የራሱን ውሳኔ ማድረግ ይኖርበታል። ሆኖም አንድ የተጠመቀ ክርስቲያን ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ይሖዋን በጸሎት መጠየቁና ራሱን በሐቀኝነት መመርመሩ የተገባ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ መንፈሳዊነቱ አደጋ ላይ ለመውደቁ ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ የሚሆነው የማያምነው የትዳር ጓደኛ ነው? ወይስ እሱ ራሱ የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱን ችላ የማለት እንዲሁም በስብሰባና በአገልግሎት አዘውታሪ ያለመሆን ችግር ይታይበታል?
16. ክርስቲያኖች ፍቺን በተመለከተ የችኮላ እርምጃ ከመውሰድ መራቅ ያለባቸው ለምንድን ነው?
16 ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና ከፍ አድርገን ስለምንመለከትና እሱ ለሰጠን የጋብቻ ስጦታ አመስጋኞች ስለሆንን ፍቺን በተመለከተ የችኮላ እርምጃ ከመውሰድ መራቅ ይኖርብናል። የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን የስሙ መቀደስ ያሳስበናል። በመሆኑም ሌላ ትዳር ለመመሥረት ስንል ትዳራችንን ማፍረስ ስለምንችልበት መንገድ ፈጽሞ ሴራ አንጠነስስም።—ኤር. 17:9፤ ሚል. 2:13-16
17. ያገቡ ክርስቲያኖች ‘አምላክ የጠራቸው ለሰላም’ መሆኑን የሚያሳዩት ምን ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥማቸው ነው?
17 የማያምን የትዳር ጓደኛ ያለው አንድ ክርስቲያን የጋብቻ ጥምረቱ እንዲቀጥል ልባዊ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል። አንድ ክርስቲያን፣ ትዳሩን ለማጠናከር እንዲህ ያለ ጥረት አድርጎም እንኳ የማያምነው የትዳር ጓደኛ አብሮ ለመኖር ፈቃደኛ ባይሆን የጥፋተኝነት ስሜት ሊያድርበት አይገባም። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “አማኝ ያልሆነው ወገን መለየት ከፈለገ ይለይ፤ እንዲህ ያለ ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት ምንም ዓይነት ግዴታ የለባቸውም፤ ይሁን እንጂ አምላክ የጠራችሁ ለሰላም ነው።”—1 ቆሮ. 7:15b
ይሖዋን ተስፋ አድርጉ
18. ትዳራችንን መታደግ ባንችልም እንኳ በዚህ ረገድ ጥረት ማድረጋችን ምን ጥሩ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል?
18 በጋብቻ ውስጥ ማንኛውም ዓይነት ችግር ሲያጋጥማችሁ ይሖዋ ብርታት እንዲሰጣችሁ ጠይቁት፤ እንዲሁም ምንጊዜም እሱን ተስፋ አድርጉ። (መዝሙር 27:14ን አንብብ።) ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሊንዳ ያጋጠማትን ሁኔታ እንመልከት። ሊንዳ ትዳሯን ለመታደግ ለበርካታ ዓመታት ጥረት ብታደርግም ከጊዜ በኋላ ከባለቤትዋ ጋር በፍቺ ተለያየች። ታዲያ ያደረገችው ጥረት ሁሉ ከንቱ እንደሆነ ተሰምቷታል? “በፍጹም” በማለት መልሳለች፤ አክላም እንዲህ ብላለች፦ “ያደረኩት ጥረት ለሌሎች ጥሩ ምሥክርነት ሰጥቷል። ንጹሕ ሕሊና አለኝ። ከሁሉም በላይ ደግሞ እነዚያ ዓመታት ልጃችን በእውነት ውስጥ ጠንካራ መሠረት እንዲኖራት ረድተዋታል። ልጃችን አድጋ ራሷን የወሰነች ቀናተኛ የይሖዋ ምሥክር ሆናለች።”
19. አንድ ሰው ትዳሩን ለመታደግ ጥረት ማድረጉ ምን ውጤት ሊያስገኝ ይችላል?
19 ሜረሊን የተባለች አንዲት ክርስቲያን በአምላክ በመታመን ትዳሯን ለመታደግ ከፍተኛ ጥረት ማድረጓ ደስታ አምጥቶላታል። ሜረሊን እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴ መሠረታዊ ፍላጎቶቼን ለማሟላት ፈቃደኛ እንዳልሆነና መንፈሳዊነቴን ሙሉ በሙሉ አደጋ ላይ እንደጣለው ስለተሰማኝ ከእሱ ጋር ለመለያየት ተፈትኜ ነበር። ባለቤቴ በአንዳንድ የንግድ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ከመጠላለፉ በፊት የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ ያገለግል ነበር። ከዚያ በኋላ ግን ከስብሰባዎች መቅረት የጀመረ ሲሆን የሐሳብ ልውውጥ ማድረግም አቆምን። እኔ ደግሞ በከተማችን የተፈጸመ አንድ የሽብር ጥቃት በጣም ስላስፈራኝ ራሴን ከሌሎች አግልዬ ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን እኔም ጋ ችግር እንደነበር ተገነዘብኩ። በመሆኑም እንደ ቀድሞው የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ የጀመርን ሲሆን የቤተሰብ ጥናት ማድረግም ቀጠልን፤ እንዲሁም በስብሰባዎች ላይ አዘውታሪ ሆንን። የጉባኤያችን ሽማግሌዎች ደግነት ያሳዩን ከመሆኑም በላይ በጣም ረድተውናል። በዚህም የተነሳ ትዳራችን እንደገና ታደሰ። ውሎ አድሮም ባለቤቴ ብቃቱን በማሟላቱ በጉባኤ ውስጥ አንዳንድ መብቶችን ማግኘት ቻለ። የተማርነው ከመከራ ቢሆንም ውጤቱ ግን ያማረ ነበር።”
20, 21. ከጋብቻ ጋር በተያያዘ ቁርጥ አቋማችን ምን መሆን ይኖርበታል?
20 ያገባንም ሆንን ነጠላ ምንጊዜም ደፋሮች መሆን እንዲሁም ይሖዋን ተስፋ ማድረግ ይኖርብናል። በትዳራችን ውስጥ ችግሮች እያጋጠሙን ከሆነ መፍትሔ ለማግኘት ከልብ ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል፤ በተጨማሪ በጋብቻ የተሳሰሩ ሰዎች “አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም” የሚለውን ሐሳብ መዘንጋት አይኖርብንም። (ማቴ. 19:6) በሌላ በኩል ደግሞ በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ የሚያጋጥሙንን ተፈታታኝ ሁኔታዎች በጽናት የምንወጣ ከሆነ የትዳር ጓደኛችን እውነተኛውን አምልኮ ሊቀበል እንደሚችል እናስታውስ፤ ይህም ከፍተኛ ደስታ ያስገኝልናል።
21 ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ከጉባኤ ውጭ ላሉ ሰዎች ጥሩ ምሥክርነት መስጠት እንድንችል በአኗኗራችን ጠንቃቆች ለመሆን ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። ጋብቻችን አደጋ ላይ ከወደቀ አጥብቀን እንጸልይ፣ ራሳችንን በሐቀኝነት እንመርምር፣ በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ጥልቀት ያለው ምርምር እናድርግ እንዲሁም ሽማግሌዎች መንፈሳዊ እርዳታ እንዲሰጡን እንጠይቅ። ከሁሉም በላይ ደግሞ በማንኛውም ነገር ይሖዋን ለማስደሰት ጥረት እናድርግ፤ በተጨማሪም ግሩም ለሆነው የጋብቻ ስጦታ ያለንን ልባዊ አድናቆት እናሳይ።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ስሞቹ ተቀይረዋል።
b ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’ የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 219-221 እንዲሁም የኅዳር 1, 1988 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ከገጽ 26-27 እና የመስከረም 15, 1975 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 575 ተመልከት።
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ክርስቲያኖች ትዳራቸውን ለመታደግ በሚያደርጉት ጥረት ቶሎ ተስፋ የማይቆርጡ ከሆነ በአብዛኛው ጥሩ ውጤት ያገኛሉ
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ምንጊዜም ይሖዋን ተስፋ አድርጉ፤ እንዲሁም ብርታት እንዲሰጣችሁ በጸሎት ጠይቁት
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ ትዳራቸውን ለመታደግ ጥረት የሚያደርጉ ክርስቲያኖችን ይባርካቸዋል
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የክርስቲያን ጉባኤ የመጽናናት ምንጭ ከመሆኑም በላይ መንፈሳዊ እርዳታ የሚገኝበት ቦታ ነው