ባልና ሽማግሌ ኃላፊነቶቹን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መወጣት
‘የበላይ ተመልካቹ የአንዲት ሚስት ባል ሊሆን ይገባዋል።’—1 ጢሞቴዎስ 3:2 አዓት
1, 2. የቄሶች ብሕትውና ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ የሌለው ለምንድን ነው?
በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ታማኝ ክርስቲያኖች ልዩ ልዩ ኃላፊነቶቻቸውን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ይወጡ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ ነጠላ ሆኖ የኖረ ክርስቲያን “የተሻለ አደረገ” ሲል እንዲህ ዓይነቱ ሰው በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በበላይ ተመልካችነት ለማገልገል የተሻለ ብቃት አለው ማለቱ ነበርን? ነጠላነትን ለሽምግልና አንዱ ብቃት ማድረጉ ነበርን? (1 ቆሮንቶስ 7:38) የካቶሊክ ቄሶች ብሕትውና ይፈለግባቸዋል። ይሁን እንጂ የቄሶች ብሕትውና ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ አለውን? የምሥራቅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የደብር ቀሳውስቱ እንዲያገቡ ብትፈቅድም ጳጳሶቿ እንዲያገቡ ግን አትፈቅድም። ይህ ከመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ጋር የሚስማማ ነውን?
2 የክርስቲያን ጉባኤ መሠረት ከሆኑት የክርስቶስ 12 ሐዋርያት መካከል አብዛኞቹ ባለ ትዳሮች ነበሩ። (ማቴዎስ 8:14, 15፤ ኤፌሶን 2:20) ጳውሎስ “እንደ ሌሎቹ ሐዋርያትና እንደ ጌታ ወንድሞች እንደ ኬፋም [ጴጥሮስ]፣ እኅት ሚስታችንን ይዘን ልንዞር መብት የለንምን?” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 9:5) ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ “የብሕትውና ሕግ የመጣው ከቤተ ክርስቲያን ነው” ሲል ከማመኑም በተጨማሪ “የአዲስ ኪዳን አገልጋዮች የብሕትውና ግዴታ አልነበረባቸውም” ብሏል። የይሖዋ ምሥክሮች የሚከተሉት የቤተ ክርስቲያንን ሕግ ሳይሆን የቅዱስ ጽሑፉን ምሳሌ ነው።—1 ጢሞቴዎስ 4:1-3
የሽምግልና ኃላፊነትና ትዳር አብረው ሊሄዱ ይችላሉ
3. ያገቡ ወንዶች ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ሊሆኑ እንደሚችሉ የትኞቹ ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነታዎች ያሳያሉ?
3 ጳውሎስ በበላይ ተመልካችነት የሚሾሙ ወንዶች ያላገቡ መሆን አለባቸው አላለም፤ ከዚህ ይልቅ ለቲቶ እንዲህ ሲል ጽፎለታል፦ “ስለዚህ ምክንያት የቀረውን እንድታደራጅ በየከተማውም፣ እኔ አንተን እንዳዘዝሁ፣ ሽማግሌዎችን [በግሪክኛ፣ ፕሪስባይትሮስ] እንድትሾም በቀርጤስ ተውሁህ፤ የማይነቀፍና ያንዲት ሚስት ባል የሚሆን፣ የሚያምኑም ልጆች ያሉት፣ ስለ መዳራትም ወይም ስለ አለመታዘዝ የማይከሰስ ማንም ቢኖር፣ ሹመው። ኤጲስ ቆጶስ፣ [“የበላይ ተመልካች፣” አዓት] [ግሪክኛ፣ ኤፒስኮፖስ፣ “ጳጳስ” የሚለው ቃል የተገኘበት] እንደ እግዚአብሔር መጋቢ፣ የማይነቀፍ ሊሆን ይገባዋልና።”—ቲቶ 1:5-7
4. (ሀ) ማግባት ለክርስቲያን የበላይ ተመልካችነት አንዱ ብቃት እንዳልሆነ እንዴት እናውቃለን? (ለ) ሽማግሌ የሆነ ነጠላ ወንድም ምን የተሻለ አጋጣሚ አለው?
4 በሌላ በኩል ደግሞ ማግባት ለሽምግልና አንዱ ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃት አይደለም። ኢየሱስ ነጠላ ነበር። (ኤፌሶን 1:22) በመጀመሪያው መቶ ዘመን በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የታወቀ የበላይ ተመልካች የነበረው ጳውሎስ በወቅቱ ትዳር አልነበረውም። (1 ቆሮንቶስ 7:7-9) በዛሬው ጊዜ ሽማግሌዎች ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙ ብዙ ነጠላ ክርስቲያኖች አሉ። የነጠላነት ሁኔታቸው በበላይ ተመልካችነት ያሉባቸውን ኃላፊነቶች ለመወጣት የሚያስችል ብዙ ጊዜ እንዲያገኙ አጋጣሚ ሊፈጥርላቸው ይችላል።
‘ያገባ ሰው ልቡ ተከፋፍሏል’
5. ያገቡ ወንድሞች የትኛውን ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነታ መገንዘብ ይኖርባቸዋል?
5 አንድ ክርስቲያን ወንድ ትዳር ሲይዝ ጊዜውንና ትኩረቱን የሚሹ አዳዲስ ኃላፊነቶችን እንደተቀበለ መገንዘብ ይኖርበታል። መጽሐፍ ቅዱስ “ያላገባው ጌታን እንዴት ደስ እንዲያሰኘው የጌታን ነገር ያስባል፤ ያገባው ግን ሚስቱን እንዴት ደስ እንዲያሰኛት የዓለምን ነገር ያስባል፣ ልቡም ተከፍሎአል” በማለት ይገልጻል። (1 ቆሮንቶስ 7:32-34) ልቡ የተከፋፈለው በምን መንገድ ነው?
6, 7. (ሀ) ያገባ ሰው ‘አሳቡ ሊከፋፈል’ የሚችልበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው? (ለ) ጳውሎስ ላገቡ ክርስቲያኖች ምን ምክር ሰጥቷል? (ሐ) ይህ ሁኔታ አንድ ሰው አንድን የሥራ ምድብ ለመቀበል የሚያደርገውን ውሳኔ ሊነካበት የሚችለው እንዴት ነው?
6 በመጀመሪያ ደረጃ፣ ትዳር የያዘ ሰው በራሱ አካል ላይ ሥልጣን አይኖረውም። ጳውሎስ እንዲህ በማለት ሲናገር ይህን ጉዳይ ግልጽ አድርጎታል፦ “ሚስት በገዛ ሥጋዋ ላይ ሥልጣን የላትም፣ ሥልጣን ለባልዋ ነው እንጂ፤ እንዲሁም ደግሞ ባል በገዛ ሥጋው ላይ ሥልጣን የለውም፣ ሥልጣን ለሚስቱ ነው እንጂ።” (1 ቆሮንቶስ 7:4) ለማግባት የሚያስቡ አንዳንድ ሰዎች በጋብቻችን ውስጥ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ትልቅ ቦታ ስለማይኖረው ይህ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ለእኛ እምብዛም ለውጥ አያመጣም ብለው ያስቡ ይሆናል። ሆኖም ከጋብቻ በፊት ንጽሕናን መጠበቅ ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃት በመሆኑ ክርስቲያኖች የወደፊት የትዳር ጓደኛቸውን የጾታ ፍላጎት በትክክል ሊያውቁ አይችሉም።
7 ጳውሎስ ሌላው ቀርቶ ‘የመንፈስን ነገር የሚያስቡ’ ባልና ሚስቶች እንኳ አንዳቸው ስለ ሌላው የጾታ ፍላጎት ማሰብ እንዳለባቸው ገልጿል። በቆሮንቶስ ይኖሩ የነበሩትን ክርስቲያኖች እንዲህ በማለት መክሯቸዋል፦ “ባል ለሚስቱ የሚገባትን ያድርግላት፣ እንደዚሁም ደግሞ ሚስቲቱ ለባልዋ። ለጸሎት ትተጉ ዘንድ ተስማምታችሁ ለጊዜው ካልሆነ በቀር፣ እርስ በርሳችሁ አትከላከሉ፤ ራሳችሁን ስለ አለመግዛት ሰይጣን እንዳይፈታተናችሁ ደግሞ አብራችሁ ሁኑ።” (ሮሜ 8:5፤ 1 ቆሮንቶስ 7:3, 5) የሚያሳዝነው ይህ ምክር በሥራ ላይ ሳይውል ሲቀር ምንዝር የተፈጸሙባቸው ጊዜያት አሉ። በመሆኑም አንድ ያገባ ክርስቲያን ለረጅም ጊዜ ከሚስቱ የሚለየውን አንድ የሥራ ምድብ ከመቀበሉ በፊት ጉዳዩን በጥንቃቄ ማመዛዘን ይኖርበታል። ነጠላ በነበረበት ወቅት የነበረውን ዓይነት ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የመንቀሳቀስ ነፃነት የለውም።
8, 9. (ሀ) ጳውሎስ ባለ ትዳር የሆኑ ክርስቲያኖች “የዓለምን ነገር ያስባሉ” ሲል ምን ማለቱ ነበር? (ለ) ባለ ትዳር ክርስቲያኖች ስለ ምን ነገር ማሰብ አለባቸው?
8 ሽማግሌዎችን ጨምሮ ባለ ትዳር የሆኑ ክርስቲያን ወንዶች “የዓለምን [ኮስሞስ] ነገር ያስባሉ” ሊባል የሚችለው በምን መንገድ ነው? (1 ቆሮንቶስ 7:33) ጳውሎስ ሁሉም ክርስቲያኖች መራቅ ስለሚኖሩባቸው በዓለም ውስጥ ስለሚገኙት መጥፎ ነገሮች እንዳልተናገረ ግልጽ ነው። (2 ጴጥሮስ 1:4፤ 2:18-20፤ 1 ዮሐንስ 2:15-17) የአምላክ ቃል “ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን [ኮስሚኮስ] ምኞት ክደን . . . ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር” ያስተምረናል።—ቲቶ 2:12
9 ስለዚህ ያገቡ ክርስቲያኖች በትዳር ውስጥ ስለሚኖሩት ሥጋዊ ነገሮች መጨነቃቸው ስለማይቀር ‘በዓለም ስላሉት ነገሮች ያስባሉ’ ሊባል ይችላል። ይህም ልጆች ካሉ የሚመጡትን ሌሎች ብዙ አሳሳቢ ጉዳዮች ሳይጨምር እንደ መኖሪያ ቤት፣ ምግብ፣ ልብስና መዝናኛ ያሉትን ነገሮች ማግኘትን ይጨምራል። ይሁን እንጂ ልጆች የሌሏቸው ባልና ሚስቶችም ቢሆኑ ጋብቻቸው የተሳካ እንዲሆንላቸው ከፈለጉ ባልም ሆነ ሚስት የእሱን ወይም የእሷን የትዳር ጓደኛ ‘ደስ ለማሰኘት’ ልባዊ ፍላጎት ሊኖራቸው ይገባል። በተለይ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ኃላፊነቶቻቸውን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ለመወጣት በሚጥሩበት ወቅት ይህን ማድረጋቸው በጣም አስፈላጊ ነው።
ጥሩ ባልና ጥሩ ሽማግሌ መሆን
10. አንድ ክርስቲያን ለሽምግልና እንዲበቃ የእምነት ጓደኞቹም ሆኑ በውጭ ያሉ ሰዎች ምን መመልከት መቻል ይኖርባቸዋል?
10 ምንም እንኳ ማግባት ለሽምግልና ብቃት ባይሆንም አንድ ክርስቲያን በሽማግሌነት እንዲሾም ከመታጨቱ በፊት ትዳር ከያዘ በቤቱ ውስጥ ተገቢውን የራስነት ሥርዓት እያስከበረ አፍቃሪና ጥሩ ባል ለመሆን እንደሚጥር ማስመስከር እንደሚኖርበት አያጠያይቅም። (ኤፌሶን 5:23-25, 28-31) ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ ‘ማንም ሰው የበላይ ተመልካችነት ላይ ለመድረስ እየተጣጣረ ከሆነ መልካም ሥራን ይመኛል የሚለው ቃል የታመነ ነው። እንግዲህ የበላይ ተመልካቹ የማይነቀፍ፣ የአንዲት ሚስት ባል ሊሆን ይገባዋል።’ (1 ጢሞቴዎስ 3:1, 2 አዓት) ሚስቱ የእምነት ጓደኛው ትሁንም አትሁን አንድ ሽማግሌ ጥሩ ባል ለመሆን የተቻለውን ያህል መጣር አለበት። እንዲያውም ከጉባኤ ውጪ ያሉ ሰዎች ጭምር ሚስቱን በጥሩ ሁኔታ እንደሚይዝና ሌሎች ኃላፊነቶቹን እንደሚወጣ መመልከት ይኖርባቸዋል። ጳውሎስ በዚህ ላይ ሲያክል “በዲያብሎስ ነቀፋና ወጥመድም እንዳይወድቅ፣ በውጭ ካሉት ሰዎች ደግሞ መልካም ምስክር ሊኖረው ይገባዋል” ብሏል።—1 ጢሞቴዎስ 3:7
11. “የአንዲት ሚስት ባል” የሚለው ሐረግ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚያመለክተው ምንድን ነው? ስለዚህ ሽማግሌዎች ምን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋቸዋል?
11 እርግጥ “የአንዲት ሚስት ባል” የሚለው ሐረግ ከአንድ ሚስት በላይ ማግባት መከልከሉን የሚጠቁም ነው፤ ሆኖም በተዘዋዋሪ መንገድ በጋብቻ ውስጥ ታማኝ መሆንን ሊያመለክት ይችላል። (ዕብራውያን 13:4) በተለይ ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ የሚገኙ እህቶችን ሲረዱ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ምክርና ማበረታቻ የሚያስፈልጋትን እህት ብቻቸውን መጎብኘት የለባቸውም። ከሌላ ሽማግሌ፣ የጉባኤ አገልጋይ ወይም ደግሞ እንዲሁ ለማበረታታት ብቻ ከሆነ ከባለቤታቸው ጋር ቢሄዱ የተሻለ ነው።—1 ጢሞቴዎስ 5:1, 2
12. የሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች ሚስቶች የትኛውን መግለጫ ለማሟላት መጣር አለባቸው?
12 በነገራችን ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ የጉባኤ አገልጋዮችንና የሽማግሌዎችን ብቃት ሲዘረዝር እንደዚህ ላሉ መብቶች የታጩት ወንድሞችን ሚስቶች አስመልክቶ ምክር ሰጥቷል። “እንዲሁም ሴቶች ጭምቶች፣ የማያሙ፣ ልከኞች፣ በነገር ሁሉ የታመኑ ሊሆኑ ይገባቸዋል” ሲል ጽፏል። (1 ጢሞቴዎስ 3:11) አንድ ክርስቲያን ባል ሚስቱ ይህን ምክር እንድትሠራበት ለመርዳት ማድረግ የሚችላቸው ብዙ ነገሮች አሉ።
ለሚስት መደረግ ያለባቸው ቅዱስ ጽሑፋዊ ግዴታዎች
13, 14. አንድ ሽማግሌ ሚስቱ የእምነት ጓደኛው ባትሆንም እንኳ አብሯት መኖርና ጥሩ ባል መሆን ያለበት ለምንድን ነው?
13 እርግጥ ይህ ምክር ለሽማግሌዎች ወይም ለጉባኤ አገልጋዮች ሚስቶች የተሰጠው እነዚህ ሚስቶች ራሳቸውን የወሰኑ ክርስቲያኖች እንደሆኑ ግምት ውስጥ በማስገባት ነው። ክርስቲያኖች “በጌታ ብቻ” እንዲያገቡ ስለሚፈለግባቸው አብዛኛውን ጊዜ ሚስቶቻቸው የእምነት ጓደኞቻቸው ናቸው። (1 ቆሮንቶስ 7:39 አዓት) ይሁን እንጂ ራሱን ለይሖዋ ከመወሰኑ በፊት የማታምን ሴት ስላገባ ወይም ያለ እሱ ጥፋት እውነትን የተወች ሚስት ስላለችው ወንድም ምን ለማለት ይቻላል?
14 ይህ ብቻ ሽማግሌ እንዳይሆን አያግደውም። ሚስቱ እምነቱን አለመከተሏ ብቻም ከእሷ እንዲለይ ሰበብ አይሆነውም። ጳውሎስ “በሚስት ታስረህ እንደ ሆንህ መፋታትን አትሻ” የሚል ምክር ሰጥቷል። (1 ቆሮንቶስ 7:27) ከዚህም በተጨማሪ እንዲህ በማለት አብራርቷል፦ “ከወንድሞች ወገን ያላመነች ሚስት ያለችው ቢኖር እርስዋም ከእርሱ ጋር ልትቀመጥ ብትስማማ፣ አይተዋት፤ የማያምን ግን ቢለይ ይለይ፤ ወንድም ቢሆን ወይም እኅት እንዲህ በሚመስል ነገር አይገዙም፤ እግዚአብሔር ግን በሰላም ጠርቶናል። አንቺ ሴት፣ ባልሽን ታድኚ እንደ ሆንሽ ምን ታውቂአለሽ? ወይስ፣ አንተ ሰው፣ ሚስትህን ታድን እንደ ሆንህ ምን ታውቃለህ?” (1 ቆሮንቶስ 7:12, 15, 16) አንድ ሽማግሌ ሚስቱ የይሖዋ ምሥክር ባትሆንም እንኳ ጥሩ ባል መሆን ይኖርበታል።
15. ሐዋርያው ጴጥሮስ ለክርስቲያን ባሎች ምን ምክር ሰጥቷቸዋል? አንድ ሽማግሌ ኃላፊነቱን የማይወጣ ከሆነ ይህ ሁኔታ ምን ሊያስከትልበት ይችላል?
15 አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ ሚስቱ አማኝ ትሁንም አትሁን ፍቅራዊ አሳቢነቱ እንደሚያስፈልጋት መገንዘብ ይኖርበታል። ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “እናንተ ባሎች ሆይ፣ ደካማ ፍጥረት ስለ ሆኑ ከሚስቶቻችሁ ጋር በማስተዋል አብራችሁ ኑሩ፤ ጸሎታችሁ እንዳይከለከል፣ አብረው ደግሞ የሕይወትን ጸጋ እንደሚወርሱ አድርጋችሁ አክብሩአቸው።” (1 ጴጥሮስ 3:7) የሚስቱን ፍላጎቶች ሆን ብሎ ችላ የሚል ባል ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና አደጋ ላይ ይጥላል፤ ይህም ‘ጸሎቱ እንዳያልፍ በደመና የተሸፈነ’ ያህል ወደ ይሖዋ እንዳይቀርብ ሊያግደው ይችላል። (ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:44) ይህም ከክርስቲያን የበላይ ተመልካችነት እስከ መውረድ ሊያደርሰው ይችላል።
16. ጳውሎስ የተናገረው ነገር ዋና ፍሬ ሐሳብ ምንድን ነው? ሽማግሌዎችስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ሊሰማቸው ይገባል?
16 ቀደም ሲል እንደተገለጸው የጳውሎስ ሐሳብ ዋና ፍሬ ነገር አንድ ሰው ትዳር በሚይዝበት ወቅት ‘አሳቡ ሳይከፋፈል በጌታ እንዲጸና’ የሚያስችለውን ነጠላ ሳለ የነበረውን መጠነኛ ነፃነት ያጣል የሚል ነው። (1 ቆሮንቶስ 7:35) ትዳር የያዙ አንዳንድ ሽማግሌዎች ጳውሎስ በመንፈስ አነሣሽነት ለተናገራቸው ቃላት አንዳንድ ጊዜ ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት እንደሚጎድላቸው ሪፖርቶች ይጠቁማሉ። ጥሩ ሽማግሌዎች ማድረግ ይኖርባቸዋል ብለው የሚያስቡትን ነገር ለማድረግ ባላቸው ፍላጎት ምክንያት አንዳንድ የባልነት ኃላፊነቶቻቸውን ችላ ይላሉ። አንድን የጉባኤ ኃላፊነት መቀበላቸው የሚስቶቻቸውን መንፈሳዊነት ሊጎዳ እንደሚችል ቢያውቁም እንኳ መብቱን አልቀበልም ማለቱ ይከብዳቸዋል። ጋብቻ በሚያስገኟቸው መብቶች ይደሰታሉ፤ ይሁን እንጂ ከእሱ ጋር አብረው የሚመጡትን ኃላፊነቶች ለመወጣት ፈቃደኛ ናቸውን?
17. አንዳንድ ሚስቶች ምን ደርሶባቸዋል? ይህ እንዳይከሰት መከላከል የሚቻለው እንዴት ነው?
17 አንድ ሽማግሌ በቅንዓት ማገልገሉ የሚያስመሰግን እንደሆነ ግልጽ ነው። ሆኖም አንድ ክርስቲያን ሚስቱን በተመለከተ ያሉበትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ኃላፊነቶች ችላ ብሎ የጉባኤ ኃላፊነቶቹን የሚወጣ ከሆነ ሚዛናዊ ነው ሊባል ይችላልን? ሚዛናዊ የሆነ አንድ ሽማግሌ በጉባኤው ውስጥ ያሉትን ለመርዳት የሚፈልግ ቢሆንም ስለ ሚስቱ መንፈሳዊነትም ጭምር ያስባል። አንዳንድ የሽማግሌዎች ሚስቶች በመንፈሳዊ የተዳከሙ ሲሆን ሌሎች ደግሞ “መርከብ አለ መሪ እንደሚጠፋ” ለመንፈሳዊ ውድቀት ተዳርገዋል። (1 ጢሞቴዎስ 1:19) አንዲት ሚስት የራሷን መዳን የመፈጸም ኃላፊነት ያለባት ቢሆንም እንኳ አንዳንድ ጊዜ ሽማግሌው “ክርስቶስ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን [“ለጉባኤው፣” አዓት] እንዳደረገላት” ሚስቱን ‘ቢመግብና ቢንከባከብ’ ይህ መንፈሳዊ ችግር እንዳይከሰት መከላከል ይችላል። (ኤፌሶን 5:28, 29) ሽማግሌዎች ‘ለመንጋው ሁሉና ለራሳቸው መጠንቀቅ’ እንዳለባቸው መታወቅ ይኖርበታል። (ሥራ 20:28) ባለ ትዳር ከሆኑ ደግሞ ይህ ሚስቶቻቸውንም የሚጨምር ነው።
‘በሥጋ ላይ የሚደርስ መከራ’
18. ያገቡ ክርስቲያኖች የሚያጋጥማቸው “ችግር” አንዳንድ ገጽታዎች የትኞቹ ናቸው? ይህስ አንድ ሽማግሌ የሚያከናውናቸውን ሥራዎች ሊነካ የሚችለው እንዴት ነው?
18 በተጨማሪም ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ከዚህ በፊት ያላገባ ሰው ቢያገባ ኃጢአት ሠራ ማለት አይደለም። ይሁን እንጂ የሚያገቡ ሰዎች በሥጋቸው ላይ መከራ ይደርስባቸዋል። የእኔ ምኞት ግን ከዚህ መከራ እንድትድኑ ነው።” (1 ቆሮንቶስ 7:28 አዓት) ጳውሎስ እሱ ነጠላ በመሆን ያሳየውን ምሳሌ መከተል የሚችሉ ክርስቲያኖችን ጋብቻ ከሚያስከትላቸው ጭንቀቶች ሊያድናቸው ፈልጎ ነበር። ልጆች የሌሏቸው ባልና ሚስቶችም እንኳ የጤና መታወክን ወይም የገንዘብ ችግርን እንዲሁም የትዳር ጓደኛን አረጋውያን ወላጆች የመጦርን ቅዱስ ጽሑፋዊ ኃላፊነቶች ጨምሮ በርካታ አሳሳቢ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል። (1 ጢሞቴዎስ 5:4, 8) አንድ ሽማግሌ ለሌሎች ምሳሌ በሚሆን መልኩ እነዚህን ኃላፊነቶች መወጣት አለበት፤ ይህም አንዳንድ ጊዜ ክርስቲያን የበላይ ተመልካች ሆኖ የሚያከናውናቸውን ሥራዎች ሊነካበት ይችላል። ደስ የሚለው አብዛኞቹ ሽማግሌዎች የቤተሰባቸውንም ሆነ የጉባኤ ኃላፊነቶቻቸውን በመወጣት መልካም ተግባር በማከናወን ላይ ናቸው።
19. ጳውሎስ “ሚስቶች ያሉአቸው እንደሌላቸው ይሁኑ” ሲል ምን ማለቱ ነበር?
19 ጳውሎስ በዚህ ላይ ሲያክል “ዘመኑ አጭር ሆኖአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሚስቶች ያሉአቸው እንደሌላቸው ይሁኑ” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 7:29) እርግጥ በዚህ ምዕራፍ ላይ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ከጻፈላቸው ነገር አንፃር ሲታይ ባለ ትዳር ክርስቲያኖች በአንድ ዓይነት መንገድ ሚስቶቻቸውን ችላ ማለት አለባቸው ማለቱ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። (1 ቆሮንቶስ 7:2, 3, 33) “በዚችም ዓለም የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙባት ይሁኑ፤ የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነውና” በማለት ሲጽፍ ምን ለማለት እንደፈለገ ግልጽ አድርጓል። (1 ቆሮንቶስ 7:31) ከጳውሎስ ዘመን ወይም ከሐዋርያው ዮሐንስ ዘመን ይልቅ በዛሬው ጊዜ ‘ዓለም እያለፈ ነው።’ (1 ዮሐንስ 2:15-17) ስለዚህ በሕይወታቸው ውስጥ የአምላክን መንግሥት ጥቅሞች የሚያስቀድሙ ያገቡ ክርስቲያኖች ጋብቻ ከሚያስገኛቸው ደስታዎችና መብቶች ዘወትር ሙሉ በሙሉ ሊጠቀሙ አይችሉም።—1 ቆሮንቶስ 7:5
የራሳቸውን ጥቅም የሚሠዉ ሚስቶች
20, 21. (ሀ) ብዙ ክርስቲያን ሚስቶች ምን መሥዋዕትነቶች ለመክፈል ፈቃደኞች ሆነዋል? (ለ) አንዲት ሚስት ባሏ ሽማግሌ ቢሆንም እንኳ ከእሱ ምን የመጠበቅ መብት አላት?
20 ሽማግሌዎች ሌሎችን ለመጥቀም ሲሉ መሥዋዕትነቶችን እንደሚከፍሉ ሁሉ ብዙ የሽማግሌዎች ሚስቶችም የትዳር ኃላፊነቶቻቸውንና በጣም አስፈላጊ የሆኑትን የመንግሥቱን ጥቅሞች ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ለመወጣት ጥረት ያደርጋሉ። በሺህ የሚቆጠሩ ክርስቲያን ሴቶች ባሎቻቸው የበላይ ተመልካችነት ኃላፊነቶቻቸውን ለማከናወን እንዲችሉ ለመተባበር ፈቃደኞች ናቸው። ይህን በማድረጋቸው ይሖዋ የሚወዳቸው ከመሆኑም በተጨማሪ የሚያሳዩትን መልካም ዝንባሌ ይባርካል። (ፊልሞና 25) ሆኖም ጳውሎስ የሰጠው ሚዛናዊ ምክር የበላይ ተመልካቾች ሚስቶች ባሎቻቸው መጠነኛ ጊዜና ትኩረት እንዲሰጧቸው ቢጠብቁ ተገቢ እንደሆነ ያሳያል። ባለ ትዳር የሆኑ ሽማግሌዎች ለሚስቶቻቸው በቂ ጊዜ የመመደብ ቅዱስ ጽሑፋዊ ግዴታ ያለባቸው ሲሆን ይህን በማድረጋቸውም የባልነትና የበላይ ተመልካችነት ኃላፊነቶቻቸውን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ሊወጡ ይችላሉ።
21 ይሁን እንጂ አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ ከባልነት በተጨማሪ የአባትነት ኃላፊነት ቢኖርበትስ? በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንደምንመለከተው ይህ ተጨማሪ የበላይ ጥበቃ መስክ እንዲኖረው ያደርጋል።
ለክለሳ ያህል
◻ አንድ ያገባ ክርስቲያን የበላይ ተመልካች ሊሆን እንደሚችል የሚያሳዩት ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነታዎች የትኞቹ ናቸው?
◻ ነጠላ የነበረ አንድ ሽማግሌ ካገባ ለምን ነገር ንቁ መሆን ይኖርበታል?
◻ ያገባ ክርስቲያን ‘የዓለምን ነገር የሚያስበው’ በምን መንገዶች ነው?
◻ ብዙ የበላይ ተመልካቾች ሚስቶች ግሩም የሆነ የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ የሚያሳዩት እንዴት ነው?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንድ ሽማግሌ ቲኦክራሲያዊ ሥራዎች የሚበዙበት ቢሆንም እንኳ ለሚስቱ ፍቅራዊ አሳቢነት ማሳየት ይኖርበታል