ነጠላነት አሳብ ሳይከፋፈል ለማገልገል የሚያስችል አጋጣሚ
“[ይህም] ሳትባክኑም [“አሳባችሁ ሳይከፋፈል፣” አዓት] በጌታ እንድትጸኑ ነው።”—1 ቆሮንቶስ 7:35
1. ጳውሎስ በቆሮንቶስ ውስጥ የሚገኙ ክርስቲያኖችን በተመለከተ ምን የሚረብሽ ወሬ ሰምቶ ነበር?
ሐዋርያው ጳውሎስ ግሪክ ውስጥ በቆሮንቶስ ይገኙ የነበሩ ክርስቲያን ወንድሞቹ ሁኔታ አሳስቦት ነበር። ከአምስት ዓመታት በፊት በዚህ በመጥፎ ሥነ ምግባር በታወቀ የበለጸገ ከተማ ውስጥ ጉባኤ አቋቁሞ ነበር። በ55 እዘአ በትንሿ እስያ በምትገኘው በኤፌሶን ከተማ ሳለ የቆሮንቶስ ጉባኤ ስለ መከፋፈሉና በዚህ ጉባኤ ውስጥ ከባድ የጾታ ብልግና በዝምታ ስለ መታለፉ የሚገልጽ የሚረብሽ ወሬ ሰማ። ከዚህም በተጨማሪ ጳውሎስ የጾታ ግንኙነትን፣ ሳያገቡ መኖርን፣ ትዳርን፣ መለያየትንና እንደገና ማግባትን በተመለከተ መመሪያ እንዲሰጣቸው ለመጠየቅ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የላኩት ደብዳቤ ደርሶት ነበር።
2. በቆሮንቶስ ውስጥ ተስፋፍቶ የነበረው የሥነ ምግባር ብልግና ክርስቲያኖችን የነካቸው እንዴት ነው?
2 በቆሮንቶስ ውስጥ ተስፋፍቶ የነበረው ከባድ የሥነ ምግባር ብልግና በዚያ ይገኝ የነበረውን ጉባኤ በሁለት መንገዶች የነካው ይመስላል። አንዳንድ ክርስቲያኖች በወቅቱ በነበረው ልቅ ሥነ ምግባር ከመሸነፋቸውም በላይ የጾታ ብልግናን በቸልታ ተመልክተው ነበር። (1 ቆሮንቶስ 5:1፤ 6:15-17) ሌሎች ደግሞ በከተማዋ ውስጥ በጣም ተስፋፍቶ የነበረውን የጾታ ስሜት የማርካት ፍላጎት በመቃወም በተጋቡ ባልና ሚስት መካከል የሚደረገውን የግብረ ሥጋ ግንኙነት ጨምሮ ከማንኛውም የጾታ ግንኙነት መቆጠብ ያስፈልጋል የሚል የከረረ አቋም ነበራቸው።—1 ቆሮንቶስ 7:5
3. ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው የመጀመሪያ መልእክቱ ላይ በቅድሚያ የገለጻቸው ነገሮች ምን ነበሩ?
3 ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው ረጅም ደብዳቤ በመጀመሪያ የጠቀሰው በመካከላቸው ተነሥቶ የነበረውን የመከፋፈል ችግር ነው። (1 ቆሮንቶስ ምዕራፍ 1-4) ጎጂ የሆነ መከፋፈል ሊያስከትል ከሚችለው ሰዎችን የመከተል ዝንባሌ እንዲርቁ መክሯቸዋል። ከአምላክ ጋር ‘አብረው የሚሠሩ’ እንደ መሆናቸው መጠን አንድ መሆን ነበረባቸው። ከዚያ ጉባኤውን በንጽሕና ስለ መጠበቅ ግልጽ የሆኑ መመሪያዎችን ሰጣቸው። (ምዕራፍ 5, 6) ቀጥሎ ሐዋርያው ለደብዳቤያቸው ምላሽ ሰጠ።
ስለ ነጠላነት የተሰጠ ምክር
4. ጳውሎስ “ከሴት ጋር አለመገናኘት ለሰው መልካም ነው” ሲል ምን ማለቱ ነበር?
4 “ስለ ጻፋችሁልኝስ ነገር፣ ከሴት ጋር አለመገናኘት ለሰው መልካም ነው” በማለት ጀመረ። (1 ቆሮንቶስ 7:1) እዚህ ላይ “ከሴት ጋር አለመገናኘት” የሚለው አገላለጽ የጾታ ስሜትን ለማርካት ከአንዲት ሴት ጋር ከሚደረገው አካላዊ ግንኙነት መቆጠብ ማለት ነው። ጳውሎስ ቀደም ሲል ዝሙትን ስላወገዘ አሁን እየተናገረ ያለው የተጋቡ ሰዎች ስለሚያደርጉት የጾታ ግንኙነት ነው። ስለዚህ ጳውሎስ አሁን ነጠላነትን አስመልክቶ ምክር እየሰጠ ነው። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 16, 18፤ ከዘፍጥረት 20:6 እና ከምሳሌ 6:29 ጋር አወዳድር።) በዚህ ላይ ጥቂት አክሎ ሲጽፍ “ላላገቡና ለመበለቶች ግን እላለሁ፦ እንደ እኔ ቢኖሩ ለእነርሱ መልካም ነው” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 7:8) ጳውሎስ በዚህ ወቅት ያላገባ ነበር፤ ምናልባትም ሚስቱ ሞታበት ይሆናል።—1 ቆሮንቶስ 9:5
5, 6. (ሀ) ጳውሎስ በምንኩስና ስለ መኖር ምክር እንዳልሰጠ ግልጽ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ጳውሎስ ነጠላነትን ያበረታታው ለምንድን ነው?
5 የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ስለ ግሪኮች ፍልስፍና በመጠኑም ቢሆን ሳያውቁ አይቀርም። የዚህ ፍልስፍና ተከታዮች ባሕታዊ መሆንን ወይም ራስን መጨቆንን ያወድሱ ነበር። የቆሮንቶስ ወንድሞች ክርስቲያኖች ከማንኛውም የጾታ ግንኙነት ቢቆጠቡ “የተሻለ” ነው ወይ? ብለው ለጳውሎስ ጥያቄ ያቀረቡለት ለዚህ ሊሆን ይችላልን? የጳውሎስ መልስ የግሪኮችን ፍልስፍና አያንጸባርቅም። (ቆላስይስ 2:8) ነጠላ ሰዎች ከሌሎች ይልቅ ቅዱሳን የሆኑ ይመስል በአኗኗራቸውና በጸሎታቸው ለራሳቸው መዳን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ በማለት በጽሑፎቹ ውስጥ በየትኛውም ቦታ ቢሆን እንደ ካቶሊክ የሃይማኖት ምሁራን በወንዶች ወይም በሴቶች ገዳም ድንግል ሆኖ በባሕታዊነት ሳያገቡ ስለ መኖር ምክር አልሰጠም።
6 ጳውሎስ ነጠላነትን በተመለከተ ምክር የሰጠው ‘በወቅቱ በነበረው ችግር ምክንያት’ ነው። (1 ቆሮንቶስ 7:26) ጳውሎስ በትዳር ምክንያት በክርስቲያኖች ላይ ሊጨምሩ የሚችሉትን አስቸጋሪ ሁኔታዎች መጥቀሱ ሊሆን ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 7:28) ላላገቡ ክርስቲያኖች “እንደ እኔ ቢኖሩ ለእነርሱ መልካም ነው” የሚል ምክር ሰጥቶ ነበር። ሚስቶቻቸው ለሞቱባቸው ደግሞ “በሚስት አልታሰርህ እንደ ሆንህ ሚስትን አትሻ” ብሏል። ክርስቲያን የሆነች መበለትን አስመልክቶም እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “እንደ ምክሬ ግን እንዳለች ብትኖር ደስተኛ ናት፤ እኔም ደግሞ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ያለ ይመስለኛል።”—1 ቆሮንቶስ 7:8, 27, 40
ነጠላ ሆኖ መኖር ግዴታ አይደለም
7, 8. ጳውሎስ ማንኛውም ክርስቲያን ነጠላ ሆኖ እንዲኖር እንዳላስገደደ የሚያሳየው ምንድን ነው?
7 ጳውሎስ ይህን ምክር በሰጠበት ወቅት የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ይመራው እንደነበር አያጠራጥርም። አለማግባትንም ሆነ ጋብቻን በተመለከተ የጻፈው መልእክት በሙሉ ሚዛናዊነትና ቁጥብነት ይታይበታል። ጉዳዩን የታማኝነት ወይም ታማኝ ያለመሆን መለኪያ አላደረገውም። በነጠላነት ንጹሕ ሆነው መኖር የሚችሉትን ነጠላ እንዲሆኑ ምክር የሰጠ ቢሆንም ጉዳዩ በነፃነት የሚደረግ ምርጫ ነበር።
8 ጳውሎስ “ከሴት ጋር አለመገናኘት ለሰው መልካም ነው” በማለት ከገለጸ በኋላ ወዲያውኑ “ነገር ግን ስለ ዝሙት ጠንቅ ለእያንዳንዱ ለራሱ ሚስት ትኑረው ለእያንዳንዲቱ ደግሞ ለራስዋ ባል ይኑራት” ሲል አክሏል። (1 ቆሮንቶስ 7:1, 2) ያላገቡ ሰዎችንና መበለቶችን ‘እንደ እኔ ብትኖሩ መልካም ነው’ ብሎ ከመከራቸው በኋላ ወዲያው “ነገር ግን በምኞት ከመቃጠል መጋባት ይሻላልና ራሳቸውን መግዛት ባይችሉ ያግቡ” በማለት ጨምሮ ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 7:8, 9) ሚስቶቻቸው ለሞቱባቸው ሰዎች በድጋሚ የሰጠው ምክር “ሚስትን አትሻ። ብታገባ ግን ኃጢአት አትሠራም” የሚል ነበር። (1 ቆሮንቶስ 7:27, 28) ይህ ሚዛናዊ የሆነ ምክር የመምረጥ ነፃነት እንዳለ ያሳያል።
9. ኢየሱስና ጳውሎስ በተናገሩት መሠረት ጋብቻም ሆነ ነጠላነት የአምላክ ስጦታ የሆኑት እንዴት ነው?
9 ጳውሎስ ጋብቻም ሆነ ነጠላነት የአምላክ ስጦታዎች እንደሆኑ ገልጿል። “ሰው ሁሉ እንደ እኔ ሊሆን እወዳለሁና፤ ነገር ግን እያንዳንዱ ከእግዚአብሔር ለራሱ የጸጋ ስጦታ አለው፣ አንዱ እንደዚህ ሁለተኛውም እንደዚያ።” (1 ቆሮንቶስ 7:7) ጳውሎስ፣ ኢየሱስ የተናገረውን በአእምሮው ይዞ እንደነበር አያጠራጥርም። ኢየሱስ ጋብቻ ከአምላክ የመጣ መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ የመንግሥቱን ጥቅሞች ለማራመድ በፈቃደኛነት ነጠላ መሆን ልዩ ስጦታ መሆኑን እንደሚከተለው በማለት ገልጿል፦ “ይህ ነገር ለተሰጣቸው ነው እንጂ ለሁሉ አይደለም፤ በእናት ማኅፀን ጃንደረቦች ሆነው የተወለዱ አሉ፣ ሰውም የሰለባቸው ጃንደረቦች አሉ፣ ስለ መንግሥተ ሰማያትም ራሳቸውን የሰለቡ ጃንደረቦች አሉ። ሊቀበለው የሚችል ይቀበለው።”—ማቴዎስ 19:4-6, 11, 12
የነጠላነትን ስጦታ መቀበል
10. አንድ ሰው የነጠላነትን ስጦታ ‘ሊቀበል’ የሚችለው እንዴት ነው?
10 ምንም እንኳ ኢየሱስም ሆነ ጳውሎስ ነጠላነት “ስጦታ” እንደሆነ ቢናገሩም አንዳቸውም ቢሆኑ ነጠላነት ጥቂቶች ብቻ ሊኖራቸው የሚችል ተአምራዊ ስጦታ ነው አላሉም። ኢየሱስ ይህ ስጦታ ‘ለሁሉም አይደለም’ ብሎ ከመናገሩም በተጨማሪ እንዲህ ማድረግ የሚችሉ ‘ይቀበሉት’ የሚል ምክር ሰጥቷል፤ ኢየሱስና ጳውሎስ ነጠላ ነበሩ። እርግጥ፣ ጳውሎስ “በምኞት ከመቃጠል መጋባት ይሻላል” በማለት ጽፏል፤ ቢሆንም ይህን የተናገረው “ራሳቸውን መግዛት” ለማይችሉት ነው። (1 ቆሮንቶስ 7:9) ጳውሎስ ቀደም ሲል በጻፋቸው መልእክቶች ላይ ክርስቲያኖች በምኞት ከመቃጠል መቆጠብ እንደሚችሉ ገልጿል። (ገላትያ 5:16, 22-24) በመንፈስ መመላለስ ማለት እያንዳንዱን እርምጃችንን የይሖዋ መንፈስ እንዲመራው መፍቀድ ማለት ነው። ወጣት ክርስቲያኖች ይህን ማድረግ ይችላሉን? የይሖዋን ቃል አጥብቀው ከተከተሉ ይችላሉ። መዝሙራዊው “ጎልማሳ መንገዱን በምን ያነጻል? ቃልህን በመጠበቅ ነው” በማለት ጽፏል።—መዝሙር 119:9
11. ‘በመንፈስ መመላለስ’ ማለት ምን ማለት ነው?
11 ይህም ብዙዎቹ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ ፊልሞች፣ የመጽሔት ርዕሶች፣ መጻሕፍትና የዘፈን ግጥሞች ከሚያስፋፏቸው ልቅ የሆኑ ሐሳቦች መራቅን ይጠይቃል። እንደነዚህ ዓይነቶቹ ሐሳቦች ሥጋዊ ናቸው። ነጠላ ሆነው መኖር የሚፈልጉ ክርስቲያን ወጣት ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ‘እንደ መንፈስ ፈቃድ እንጂ እንደ ሥጋ ፈቃድ መመላለስ’ የለባቸውም። “እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ የሥጋን ነገር ያስባሉና፣ እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን የመንፈስን ነገር ያስባሉ።” (ሮሜ 8:4, 5፤ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) የመንፈስ ነገሮች ጽድቅ፣ ንጽሕና፣ ፍቅር እና መልካም ሥነ ምግባር የሚንጸባረቅባቸው ናቸው። ወጣቶችም ሆኑ አዋቂ ክርስቲያኖች ‘እነዚህን ነገሮች ቢያስቡ’ ጥሩ ነው።—ፊልጵስዩስ 4:8, 9
12. የነጠላነትን ስጦታ መቀበል በአብዛኛው የሚጠይቀው ምንድን ነው?
12 የነጠላነትን ስጦታ መቀበል በአብዛኛው ልብን በዚያ ግብ ላይ የማድረግና ይህን ግብ በመከታተል ረገድ የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት መጸለይ የሚጠይቅ ጉዳይ ነው። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ሳይናወጥ በልቡ የጸና ግን ግድ የለበትም፣ የወደደውን እንዲያደርግ ተፈቅዶለታል፤ ድንግልናውንም በልቡ ይጠብቅ ዘንድ ቢጸና፣ መልካም አደረገ። እንዲሁም ድንግልን ያገባ መልካም አደረገ ያላገባም የተሻለ አደረገ።”—1 ቆሮንቶስ 7:37, 38
በዓላማ ነጠላ መሆን
13, 14. (ሀ)ሐዋርያው ጳውሎስ ያገቡና ያላገቡ ክርስቲያኖችን ያነጻጸረው እንዴት ነው? (ለ) ነጠላ ክርስቲያን ከባለ ትዳሮች ‘የተሻለ ማድረግ’ የሚችለው እንዴት ብቻ ነው?
13 እንዲያው ነጠላ ሆኖ መኖር ብቻውን ልዩ ግምት የሚሰጠው ነገር አይደለም። ታዲያ ነጠላነት “የተሻለ” የሚሆነው ከምን አንፃር ነው? ይህ የተመካው አንድ ሰው ነጠላነት የሚያስገኘውን ነፃነት በሚጠቀምበት አኳኋን ላይ ነው። ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ያለ አሳብ ልትኖሩ እወዳለሁ። ያላገባው ጌታን እንዴት ደስ እንዲያሰኘው የጌታን ነገር ያስባል፤ ያገባው ግን ሚስቱን እንዴት ደስ እንዲያሰኛት የዓለምን ነገር ያስባል፣ ልቡም ተከፍሎአል። ያልተጋባች ሴትና ድንግል በሥጋም በነፍስም እንዲቀደሱ የጌታን ነገር ያስባሉ፤ የተጋባች ግን ባልዋን እንዴት ደስ እንድታሰኘው የዓለምን ነገር ታስባለች። ይህንም ለራሳችሁ ጥቅም እላለሁ፤ በአገባብ እንድትኖሩ ሳትባክኑም [“አሳባችሁ ሳይከፋፈል፣” አዓት] በጌታ እንድትጸኑ ነው እንጂ ላጠምዳችሁ ብዬ አይደለም።”—1 ቆሮንቶስ 7:32-35
14 ትዳር ሳይዝ የሚያሳልፈውን ጊዜ የራስ ወዳድነት ግቦችን ለማሳደድ የሚጠቀምበት ነጠላ ክርስቲያን ካገቡ ክርስቲያኖች “የተሻለ” አላደረገም። በነጠላነት የሚኖረው “ስለ መንግሥተ ሰማያት” ሳይሆን ለራሱ ሲል ነው። (ማቴዎስ 19:12) ያላገባ ወንድ ወይም ያላገባች ሴት “የጌታን ነገር” እና ‘ጌታን እንዴት ደስ እንዲያሰኙ’ ማሰብ ያለባቸው ከመሆናቸውም በላይ ‘ሳይባክኑ [“አሳባቸው ሳይከፋፈል፣” አዓት] በጌታ ይጸናሉ።’ ይህ ማለት አሳባቸው ሳይከፋፈል ይሖዋንና ክርስቶስ ኢየሱስን ያገለግላሉ ማለት ነው። ያላገቡ ክርስቲያን ወንዶችና ሴቶች ካገቡ ክርስቲያኖች “የተሻለ” የሚያደርጉት በዚህ መንገድ ብቻ ነው።
አሳብ ሳይከፋፈል ማገልገል
15. ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ ምዕራፍ 7 ላይ ያቀረበው ሐሳብ ዋነኛ ፍሬ ነገር ምንድን ነው?
15 ጳውሎስ በዚህ ምዕራፍ ላይ ያቀረበው አጠቃላይ ሐሳብ የሚከተለው ነው፦ ምንም እንኳ ማግባት ምንም ስሕተት የሌለበትና በአንዳንድ ሁኔታዎችም ለአንዳንዶች ጥሩ ቢሆንም አሳቡ እምብዛም ሳይከፋፈል ይሖዋን ለማገልገል ለሚፈልግ ወይም ለምትፈልግ ሴት ነጠላነት ጠቃሚ እንደሆነ አይካድም። ያገባ ሰው ‘አሳቡ የተከፋፈለ’ ሲሆን ያላገባ ክርስቲያን ግን ‘በጌታ ነገር’ ላይ ትኩረት ለማድረግ ነፃ ነው።
16, 17. ነጠላ የሆነ ክርስቲያን “የጌታን ነገር” በተሻለ መንገድ ትኩረት ሊሰጠው የሚችለው እንዴት ነው?
16 ካገቡ ሰዎች ይልቅ አንድ ያላገባ ክርስቲያን ሊያተኩርባቸው የሚችሉት የጌታ ነገሮች የትኞቹ ናቸው? ኢየሱስ በሌላ ጥቅስ ዙሪያ ክርስቲያኖች ለቄሣር ሊሰጧቸው ስለማይችሏቸው “የአምላክ ነገሮች” ተናግሯል። (ማቴዎስ 22:21 አዓት) እነዚህ ነገሮች ከአንድ ክርስቲያን ሕይወት፣ አምልኮና አገልግሎት ተነጥለው የማይታዩ ናቸው።—ማቴዎስ 4:10፤ ሮሜ 14:8፤ 2 ቆሮንቶስ 2:17፤ 3:5, 6፤ 4:1
17 አብዛኛውን ጊዜ ነጠላ ሰዎች ጊዜያቸውን በይሖዋ አገልግሎት ለማሳለፍ ነፃ ናቸው። ይህም ለመንፈሳዊነታቸውና የአገልግሎታቸውን አድማስ ለማስፋት ጠቃሚ ነው። በግል ጥናትና በማሰላሰል ከሌሎች የበለጠ ጊዜ ሊያሳልፉ ይችላሉ። ብዙውን ጊዜ ነጠላ ክርስቲያኖች ካገቡ ክርስቲያኖች ይልቅ በፕሮግራማቸው መሠረት የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባቸውን በቀላሉ ሊያነቡ ይችላሉ። ለስብሰባዎችና ለመስክ አገልግሎት በተሻለ ሁኔታ ሊዘጋጁ ይችላሉ። ይህ ሁሉ ‘ለራሳቸው ጥቅም’ ነው።—1 ቆሮንቶስ 7:35
18. ብዙ ነጠላ ወንድሞች ‘አሳባቸው ሳይከፋፈል’ ይሖዋን ማገልገል እንደሚፈልጉ ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነ ው?
18 በአሁኑ ጊዜ በጉባኤ አገልጋይነት በማገልገል ላይ የሚገኙ ብዙ ነጠላ ወንድሞች ይሖዋን “እነሆኝ፣ እኔን ላከኝ” ለማለት ነፃ ናቸው። (ኢሳይያስ 6:8) አገልጋዮች ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄደው ለማገልገል ነፃ ለሆኑ ነጠላ የጉባኤ አገልጋዮችና ሽማግሌዎች ታስቦ በተቋቋመው የአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ሊካፈሉ ይችላሉ። ሌላው ቀርቶ ባላቸው ኃላፊነት ምክንያት ጉባኤያቸውን ትተው ወደ ሌላ ቦታ መሄድ የማይችሉ ነጠላ ወንድሞች እንኳ በጉባኤ አገልጋይነት ወይም በሽማግሌነት ወንድሞቻቸውን ለማገልገል ራሳቸውን ሊያቀርቡ ይችላሉ።—ፊልጵስዩስ 2:20-23
19. ብዙ ነጠላ እህቶች የተባረኩት እንዴት ነው? ለጉባኤው በረከት መሆን የሚችሉበት አንዱ መንገድስ ምንድን ነው?
19 የሚያማክሩትና ምሥጢራቸውን የሚያካፍሉት ባል የሌላቸው ነጠላ እህቶች በይበልጥ ‘ሸክማቸውን በይሖዋ ላይ ሊጥሉ’ ይችላሉ። (መዝሙር 55:22፤ 1 ቆሮንቶስ 11:3) በተለይ ለይሖዋ ባላቸው ፍቅር ተገፋፍተው ነጠላ ለሆኑ እህቶች ይህ በጣም አስፈላጊ ነው። ከጊዜ በኋላ ካገቡም የሚያገቡት “በጌታ” ማለትም ራሱን ለይሖዋ የወሰነ ሰው ብቻ ይሆናል። (1 ቆሮንቶስ 7:39) ሽማግሌዎች በጉባኤያቸው ውስጥ ያላገቡ እህቶች በመኖራቸው አመስጋኞች ናቸው፤ እነዚህ ነጠላ እህቶች ብዙውን ጊዜ የታመሙትንና አረጋውያንን ይጠይቃሉ። ይህም ለሁሉም ደስታ ያመጣላቸዋል።—ሥራ 20:35
20. ብዙ ክርስቲያኖች ‘አሳባቸው ሳይከፋፈል በጌታ እንደጸኑ’ በማሳየት ላይ ያሉት እንዴት ነው?
20 ብዙ ወጣት ክርስቲያኖች ‘አሳባቸው ሳይከፋፈል ዘወትር ጌታን ለማገልገል’ ጉዳዮቻቸውን አስተካክለዋል። (1 ቆሮንቶስ 7:35) እነዚህ ወጣቶች የሙሉ ጊዜ አቅኚ አገልጋዮችና ሚስዮናውያን ሆነው ወይም ከመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮዎች መካከል በአንዱ ውስጥ ይሖዋን በማገልገል ላይ ናቸው። እንዴት ያሉ ደስተኛ ወጣቶች ናቸው! የእነሱ መኖር ምንኛ መንፈስን የሚያድስ ነው! እንዲያውም በይሖዋና በኢየሱስ ዓይን “እንደ ጤዛ” ናቸው።—መዝሙር 110:3 አዓት
ለዘለቄታው ላለማግባት አይሳሉም
21. (ሀ) ጳውሎስ ጨርሶ ላለማግባት መሳልን እንዳላበረታታ ግልጽ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ጳውሎስ “ማግባት ወደሚገባው ዕድሜ በደረሰ ጊዜ” ሲል ምን ማመልከቱ ነበር?
21 የጳውሎስ ምክር ዋነኛው ነጥብ ክርስቲያኖች ነጠላነትን ቢቀበሉ “መልካም” ነው የሚል ነው። (1 ቆሮንቶስ 7:1, 8, 26, 37) ሆኖም ጨርሶ ላለማግባት እንዲሳሉ ፈጽሞ አላበረታታቸውም። ከዚህ በተቃራኒ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ዳሩ ግን ማግባት ወደሚገባው ዕድሜ በደረሰ ጊዜ ስለ ድንግልናው ያፈረ ሰው ቢኖር፣ የወደደውን ያድርግ፤ ኃጢአት የለበትም፤ ይጋቡ።” (1 ቆሮንቶስ 7:36) “ማግባት ወደሚገባው ዕድሜ በደረሰ ጊዜ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል (ሃይፕራክሞስ) ቃል በቃል ሲተረጎም “ከከፍተኛ ደረጃ ያለፈ” ማለት ሲሆን የጾታ ስሜት የሚያይልበት ጊዜ ማለፉን ያመለክታል። ስለዚህ በነጠላነት ብዙ ዓመታት ያሳለፉና ከጊዜ በኋላ ማግባት እንዳለባቸው የተሰማቸው ክርስቲያኖች የእምነት ጓደኛቸውን ለማግባት ሙሉ በሙሉ ነፃ ናቸው።—2 ቆሮንቶስ 6:14
22. ከሁሉም አቅጣጫዎች ሲታይ አንድ ክርስቲያን በልጅነቱ አለማግባቱ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
22 አንድ ወጣት ክርስቲያን አሳቡ ሳይከፋፈል ይሖዋን በማገልገል የሚያሳልፋቸው ዓመታት በጥበብ ጥቅም ላይ የዋሉ ናቸው። እነዚህ ዓመታት እሱን ወይም እሷን ተግባራዊ ጥበብ፣ ተሞክሮና ማስተዋል እንዲያገኙ ያስችሏቸዋል። (ምሳሌ 1:3, 4) ለመንግሥቱ ሲል በነጠላነት የኖረ ክርስቲያን የኋላ ኋላ ለማግባት ቢወስን የትዳር ሕይወት ምናልባትም ወላጅነት የሚያስከትላቸውን ኃላፊነቶች ለመሸከም የተሻለ አቋም ይኖረዋል።
23. አንዳንዶች ለማግባት ሲያስቡ በአእምሯቸው ምን ሊይዙ ይችላሉ? ሆኖም በሚቀጥሉት ርዕሶች ላይ ትኩረት የሚደረግበት ጥያቄ የትኛው ነው?
23 በርከት ላሉ ዓመታት በነጠላነት ይሖዋን በሙሉ ጊዜ ሲያገለግሉ የኖሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች በአንድ ዓይነት የሙሉ ጊዜ አገልግሎት የመቀጠል ግብ ይዘው የወደፊት የትዳር ጓደኛቸውን በጥንቃቄ ይመርጣሉ። ይህ በጣም የሚያስመሰግን እንደሆነ አያጠያይቅም። አንዳንዶች ትዳር በማንኛውም መንገድ አገልግሎታችንን እንዳይቀንስብን እናደርጋለን የሚለውን ሐሳብ በአእምሯቸው ይዘው ሊያገቡ ይችላሉ። ይሁን እንጂ አንድ ያገባ ክርስቲያን እሱ ወይም እሷ ነጠላ በነበሩበት ወቅት የነበረውን ያህል በይሖዋ አገልግሎት ላይ ለማተኮር ነፃ እንደሆነ ሊሰማው ይገባልን? ይህ ጥያቄ በሚቀጥሉት ርዕሶች ላይ ይብራራል።
ለክለሳ ያህል
◻ ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ጉባኤ ደብዳቤ መጻፍ አስፈላጊ እንደሆነ የተሰማው ለምን ነበር?
◻ ጳውሎስ በምንኩስና መኖርን እንዳላበረታታ እንዴት እናውቃለን?
◻ አንድ ሰው ነጠላነትን ‘መቀበል’ የሚችለው እንዴት ነው?
◻ ነጠላ እህቶች ከነጠላነታቸው ሊጠቀሙ የሚችሉት እንዴት ነው?
◻ ነጠላ ወንድሞች ነፃነታቸውን ‘አሳባቸው ሳይከፋፈል’ ይሖዋን ለማገልገል ሊጠቀሙበት የሚችሉት በምን በምን መንገዶች ነው?