ለሥራ ሚዛናዊ አመለካከት ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?
ከፍተኛ ፉክክር የነገሠበት የንግዱ ዓለም ከሚያሳድረው ጫና የተነሳ በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ወደ ሥራ መሄድ ያስጠላቸዋል። ይሁን እንጂ በሥራችን ልንደሰት ይገባናል። ለምን? በሥራው በሚደሰተው አምላክ አምሳል የተፈጠርን በመሆናችን ነው። ለምሳሌ ያህል ረጅም ዘመናት በፈጁት በስድስቱ የፍጥረት ‘ቀናት’ ማብቂያ ላይ “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፣ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ” በማለት ዘፍጥረት 1:31 ይናገራል።
ይሖዋን “ደስተኛ አምላክ” ለመባል ያበቃው አንዱ ምክንያት ሥራ ወዳድ መሆኑ እንደሆነ አያጠራጥርም። (1 ጢሞቴዎስ 1:11 NW ) ታዲያ እርሱን ይበልጥ በመሰልን መጠን ደስታችን ይጨምራል ቢባል አሳማኝ አይሆንም? ይህን በተመለከተ የላቀ የግንባታና የማደራጀት ችሎታ የነበረው የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን “ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ በድካሙም ሁሉ ደስ ይለው ዘንድ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው” ሲል ጽፏል።—መክብብ 3:13
ዛሬ በፍጥነት እየተለወጠ ባለው የሥራው ዓለም ለሥራ ሚዛናዊና ገንቢ አመለካከት መያዝ ፈታኝ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ይሖዋ አምላክ ፍቅራዊ መመሪያውን የሚከተሉ ሰዎችን ይባርካቸዋል። (መዝሙር 119:99, 100) እነዚህ ሰዎች ተፈላጊና እምነት የሚጣልባቸው ሠራተኞች ስለሚሆኑ በሥራ ገበታቸው ላይ የመቆየት አጋጣሚያቸው ሰፊ ነው። በተጨማሪም ሕይወታቸውንና ሥራቸውን የሚመለከቱት ከገንዘብ አንጻር ሳይሆን ከመንፈሳዊ ጉዳዮችም አንጻር ነው። ይህም በሕይወታቸው ውስጥ ማስተዋል የተሞላበት ውሳኔ እንዲያደርጉና ደስታቸውም ሆነ ደኅንነታቸው የተመካው በሥራቸው ወይም ተለዋዋጭ በሆነው የገበያ ሥርዓት ላይ አለመሆኑን እንዲገነዘቡ ያስችላቸዋል። (ማቴዎስ 6:31-33፤ 1 ቆሮንቶስ 2:14, 15) እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ለሥራ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል።
ለሥራ ያላችሁ አመለካከት አምላክን የሚያስደስት ይሁን
አንዳንድ ሰዎች ሥራቸውን ከምንም ነገር በላይ ስለሚያስቀድሙ የሥራ ሱሰኞች ይሆናሉ። ሌሎች ደግሞ የሥራ መውጫ ሰዓት ደርሶ ወደ ቤት የሚመለሱበት ጊዜ እስኪደርስ ድረስ ይቸኩላሉ። ለሥራ ሊኖረን የሚገባው ሚዛናዊ አመለካከት ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “በድካምና ነፋስን በመከተል ከሁለት እጅ ሙሉ ይልቅ አንድ እጅ ሙሉ በዕረፍት ይሻላል” የሚል መልስ ይሰጣል። (መክብብ 4:6) እንደ እውነቱ ከሆነ ከሚገባው በላይ ወይም ለረጅም ሰዓት መሥራት ከጥቅሙ ጉዳቱ ስለሚያመዝን ‘ነፋስን እንደመከተል’ ነው። እንዴት? ለደስታችን ምክንያት የሚሆኑትን ነገሮች ሊያሳጣን ስለሚችል ነው። እነዚህም ከቤተሰባችንና ከወዳጆቻችን ጋር ያለንን ግንኙነት፣ መንፈሳዊነታችንን፣ አካላዊ ጤንነታችንን አልፎ ተርፎም በሕይወት የመቆየት አጋጣሚያችንን ይጨምራሉ። (1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10) ብዙ ሥራ በመሥራት በራሳችን ላይ ሸክም አብዝተን ለድካምና ለስቃይ ከመዳረግ ይልቅ ሰላማችንን ጠብቀን በጥቂት ቁሳዊ ነገሮች ረክተን መኖር መቻላችን ሚዛናዊ አመለካከት እንዳለን ያሳያል።
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ዓይነቱን ሚዛናዊ አመለካከት ቢያበረታታም ስንፍናን ይደግፋል ማለት አይደለም። (ምሳሌ 20:4) ስንፍና ለራሳችን ያለንን ግምትና ሌሎች ለእኛ ያላቸውን አክብሮት ያሳጣናል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ከአምላክ ጋር የመሠረትነውን ዝምድና ያበላሽብናል። መጽሐፍ ቅዱስ ሥራ መሥራት የማይወድ ሰው ሌሎች ደክመው ያመጡትን መብላት እንደሌለበት በግልጽ ይናገራል። (2 ተሰሎንቄ 3:10) ከዚህ ይልቅ የአስተሳሰብ ለውጥ አድርጎ ተግቶ በመሥራት ለራሱም ሆነ እጁን ጠብቀው ለሚያድሩት የሚያስፈልገውን ማሟላት ይኖርበታል። ተግቶ በመሥራት ለተቸገሩትም ሊተርፍ ይችላል። ይህም የአምላክ ቃል የሚደግፈው ተግባር ነው።—ምሳሌ 21:25, 26፤ ኤፌሶን 4:28
ልጆች የሥራ ፍቅር እንዲያዳብሩ ማሰልጠን
ጥሩ የሥራ ልማድ እንዲሁ በአጋጣሚ የሚገኝ ሳይሆን ከልጅነት አንስቶ መዳበር ያለበት ባሕርይ ነው። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ለወላጆች “ልጅን በሚሄድበት መንገድ ምራው፣ በሸመገለም ጊዜ ከእርሱ ፈቀቅ አይልም” የሚል ምክር ይሰጣል። (ምሳሌ 22:6) ጥበበኛ የሆኑ ወላጆች ትጉ ሠራተኞች በመሆን ጥሩ ምሳሌ ከመተዋቸውም በተጨማሪ እንደ አቅማቸው ቤት ውስጥ ሊሠሩት የሚችሉትን ሥራ በመስጠት ትንንሽ ልጆቻቸውን ማሰልጠን ይጀምራሉ። ምንም እንኳ ልጆች አንዳንድ የሥራ ዓይነቶችን መሥራት ባያስደስታቸውም ጥሩ አድርገው ላከናወኑት ሥራ በተለይ ከወላጆቻቸው ምስጋና ሲቸራቸው በቤተሰቡ ውስጥ ተፈላጊ እንደሆኑ ይሰማቸዋል። የሚያሳዝነው ግን አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸውን የጠቀሟቸው እየመሰላቸው ምንም ሥራ እንዳይሠሩ በማድረግ ያቀማጥሏቸዋል። እነዚህ ወላጆች “ባሪያውን [ወይም ልጁን] ከሕፃንነቱ ጀምሮ በማቀማጠል የሚያሳድግ የኋላ ኋላ እንደ ጌታ ያደርገዋል” በሚለው በምሳሌ 29:21 ላይ ሊያሰላስሉ ይገባል።
ከዚህ በተጨማሪ ኃላፊነት የሚሰማቸው ወላጆች ለልጆቻቸው ትምህርት ትኩረት የሚሰጡ ከመሆኑም በላይ ትምህርታቸውን በትጋት እንዲከታተሉ ያበረታቷቸዋል። ይህም ወጣቶች ከጊዜ በኋላ ወደ ሥራው ዓለም ሲገቡ ይጠቅማቸዋል።
በሥራ ምርጫችሁ ጥበበኛ ሁኑ
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ዓይነት ሥራ መሥራት እንዳለብን ባይናገርም መንፈሳዊ እድገታችን፣ ለአምላክ የምናቀርበው አገልግሎትና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ኃላፊነቶቻችን ቸል እንዳይባሉ የሚረዱ ግሩም መመሪያዎችን ይዟል። ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ዘመኑ አጭር ሆኖአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ . . . በዚችም ዓለም የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙባት ይሁኑ፤ የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነውና።” (1 ቆሮንቶስ 7:29-31) ባለንበት ሥርዓት ውስጥ ቋሚ የሆነ ወይም ፈጽሞ የማይለወጥ ነገር የለም። ጊዜያችንንና ጉልበታችንን ሙሉ በሙሉ በዚህ ሥርዓት ላይ ማዋል ማለት ዕድሜ ልካችንን ለፍተን ባጠራቀምነው ገንዘብ ጎርፍ በሚያጠቃው አካባቢ ቤት ከመግዛት ተለይቶ አይታይም። እንዴት ያለ የቂልነት ውሳኔ ነው!
ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች “እንደማይጠቀሙባት ይሁኑ” የሚለውን ሐረግ ‘አይጠላለፉ’ እና “አይጠመዱ” በማለት ተርጉመውታል። (ዘ ጀሩሳሌም ባይብል፤ ቱዴይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን) ጥበበኛ የሆኑ ሰዎች ይህ ሥርዓት የቀረው ዘመን ‘አጭር መሆኑን’ አይዘነጉም። እንዲሁም በዚህ ዓለም ‘ተጠላልፎ መያዝ’ ወይም ‘መጠመድ’ የኋላ ኋላ ለሐዘንና ለቁጭት እንደሚዳርግ ይገነዘባሉ።—1 ዮሐንስ 2:15-17
‘አምላክ ከቶ አይተዋችሁም’
ይሖዋ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ከእኛ በተሻለ ያውቃል። በተጨማሪም ዓላማው ፍጻሜውን በሚያገኝበት የጊዜ ሂደት ውስጥ የት ላይ እንደምንገኝ ያውቃል። ከዚህም የተነሳ “አካሄዳችሁ ገንዘብን ያለ መውደድ ይሁን፣ ያላችሁም ይብቃችሁ፤ እርሱ (አምላክ) ራሱ:- አልለቅህም ከቶም አልተውህም ብሎአልና” ሲል ያሳስበናል። (ዕብራውያን 13:5) ይህ ጥቅስ ምንኛ የሚያጽናና ነው! ኢየሱስ፣ አምላክ ለሕዝቡ የሚያሳየውን ፍቅራዊ አሳቢነት በመኮረጅ ዝነኛ በሆነው የተራራ ስብከቱ ላይ ደቀ መዛሙርቱ ለሥራና ለቁሳዊ ነገሮች ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖራቸው በሰፊው አስተምሯቸዋል።—ማቴዎስ 6:19-33
የይሖዋ ምሥክሮች ኢየሱስ የሰጠውን ትምህርት በሥራ ለማዋል ይጥራሉ። ለምሳሌ ያህል የኤሌክትሪክ ባለሙያ የሆነ አንድ የይሖዋ ምሥክር አለቃው በቋሚነት ትርፍ ሰዓት እንዲሠራ ሐሳብ ሲያቀርብለት በሐሳቡ ሳይስማማ ቀረ። ለምን? ተቀጥሮ የሚሠራው ሥራ ለቤተሰቡና ለመንፈሳዊ ጉዳዮች የመደበውን ጊዜ እንዲሻማበት ስላልፈለገ ነው። ወንድም ትጉህና ታማኝ ሠራተኛ ስለነበር አሠሪው ሊጫነው አልፈለገም። እርግጥ ነው፣ ሁሉም ነገር በዚህ መልክ መፍትሔ ያገኛል ማለት አይደለም። አንድ ክርስቲያን ሕይወቱን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መምራት እንዲችል ሌላ ሥራ ለመፈለግ ይገደድ ይሆናል። ይሁን እንጂ ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ላይ የሚታመኑ ክርስቲያኖች አብዛኛውን ጊዜ መልካም ባሕርያቸውና ታታሪነታቸው የአሠሪዎቻቸውን አድናቆት እንደሚያተርፍላቸው ተገንዝበዋል።—ምሳሌ 3:5, 6
ማንኛውም ሥራ አስደሳች የሚሆንበት ጊዜ
በዚህ ፍጽምና በጎደለው ሥርዓት ውስጥ ተቀጥሮ መሥራትም ሆነ ሥራ ማግኘት ችግሮችና ያልተጠበቁ ሁኔታዎች አያጡትም። እንዲያውም የዓለም መልክ ይበልጥ አለመረጋጋት ሲታይበትና ኢኮኖሚው ሲዋዥቅ አልፎ ተርፎም ሲንኮታኮት ሁኔታዎች ይባስ አስከፊ ሊሆኑ ይችላሉ። ሆኖም ይህ ሁኔታ ጊዜያዊ ነው። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሥራ አጥነት አይኖርም። ከዚህም በላይ ማንኛውም ዓይነት ሥራ በእርግጥ አርኪና አስደሳች ይሆናል። ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? እንዲህ ዓይነት ለውጥ የሚመጣው እንዴት ነው?
ይሖዋ በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት እንዲህ ዓይነት ጊዜ እንደሚመጣ ተንብዮ ነበር። ይሖዋ “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እፈጥራለሁና፤ የቀደሙትም አይታሰቡም፣ ወደ ልብም አይገቡም” ብሏል። (ኢሳይያስ 65:17) እንዲህ ሲል አዲስ መንግሥት እንደሚያቋቁም መናገሩ ሲሆን በዚህ መንግሥት ሥር ፍጹም አዲስና ልዩ የሆነ ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ይወለዳል።—ዳንኤል 2:44
በዚያን ጊዜ የሚኖረውን የሰዎች አኗኗርና ሥራ በተመለከተ ትንቢቱ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “ቤቶችንም ይሠራሉ ይቀመጡባቸውማል፤ ወይኑንም ይተክላሉ ፍሬውንም ይበላሉ። ሌላ እንዲቀመጥበት አይሠሩም፣ ሌላም እንዲበላው አይተከሉም፤ የሕዝቤ ዕድሜ እንደ ዛፍ ዕድሜ ይሆናልና፣ እኔም የመረጥኋቸው በእጃቸው ሥራ ረጅም ዘመን ደስ ይላቸዋልና። እነርሱ ከነልጆቻቸው የእግዚአብሔር ብሩካን ዘር ናቸውና በከንቱ አይደክሙም ለጥፋትም አይወልዱም።”—ኢሳይያስ 65:21-23
አምላክ በሚያዘጋጀው በዚያ አዲስ ዓለም ውስጥ እንዴት ያለ ሥር ነቀል ለውጥ ይታያል! ‘በከንቱ በማትደክምበት’ እንዲያውም በሥራህ ‘ፍሬ’ ሙሉ በሙሉ በምትደሰትበት ይህን በመሰለ ዓለም ውስጥ መኖር አትፈልግም? ይሁን እንጂ ይህን የመሰለ በረከት የሚያገኙት ‘የእግዚአብሔር ብሩካን ዘር መሆናቸውን’ ልብ በል። ስለ ይሖዋ በመማርና እርሱ ያወጣቸውን ብቃቶች በማሟላት አንተም ከእነዚህ “ብሩካን” መካከል መሆን ትችላለህ። ኢየሱስ “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:3) የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክን ቃል፣ መጽሐፍ ቅዱስን በማስጠናት ይህን ለሕይወት የሚያበቃ እውቀት እንድታገኝ ለመርዳት ዝግጁ ናቸው።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
“ምንጊዜም ተፈላጊ ናቸው”
መጽሐፍ ቅዱስ “ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉ፣ የምታደርጉትን ሁሉ በትጋት አድርጉት” ይላል። (ቆላስይስ 3:23) ይህን ግሩም መመሪያ በመከተል ሥራውን በትጋት የሚያከናውን ሰው ተፈላጊ ሠራተኛ እንደሚሆን እሙን ነው። ከዚህም የተነሳ ጄ ጄ ሉና የተባሉ አንድ አማካሪ ሃው ቱ ቢ ኢንቪዝብል በተባለ መጽሐፋቸው ላይ ቀጣሪዎች ሃይማኖተኛ ሰዎችን ቢቀጥሩ የተሻለ እንደሚሆን ከተናገሩ በኋላ አክለው “እንደ እውነቱ ከሆነ ግን በአመዛኙ መቅጠር የምንፈልገው [የይሖዋ] ምሥክሮችን ነው” ብለዋል። የመጽሐፉ አዘጋጅ ከሰጧቸው ምክንያቶች መካከል አንደኛው ምሥክሮቹ በሐቀኝነታቸው የሚታወቁ መሆናቸውን ሲሆን ይህ ባሕርይ በተለያዩ የሥራ መስኮች “ምንጊዜም ተፈላጊ” ያደርጋቸዋል።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሥራን ከመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችና ከመዝናኛ ጋር ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ማካሄድ ደስታ ያስገኛል