‘በቃሌ ኑሩ’
“እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ።”—ዮሐንስ 8:31
1. (ሀ) ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲያርግ እዚህ ምድር ላይ ትቶ የሄደው ምንድን ነው? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
የክርስትና መሥራች የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ሲያርግ በዚህች ምድር ላይ ትቶ የሄደው ቁሳዊ ሃብትና ንብረት ሳይሆን ደቀ መዛሙርትንና የእርሱ ተከታይ ለመሆን የሚያስፈልጉ ብቃቶችን ነው። እንዲያውም የእርሱ ተከታይ መሆን የሚፈልጉ ሰዎች እንዲያሟሉ የሚጠበቅባቸውን ሦስት አስፈላጊ ብቃቶች በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ እናገኛለን። እነዚህ ብቃቶች ምንድን ናቸው? እነዚህን ብቃቶች ለማሟላት ምን ማድረግ እንችላለን? የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ለመሆን የሚያስፈልጉትን ብቃቶች እናሟላ እንደሆነና እንዳልሆነ እንዴት ማረጋገጥ እንችላለን?a
2. በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘው ደቀ መዝሙር ለመሆን የሚያስፈልገው ብቃት ምንድን ነው?
2 ኢየሱስ ከመሞቱ ከስድስት ወራት በፊት ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ አንድ ሳምንት የሚፈጀውን የዳስ በዓል ለማክበር ለተሰበሰቡት ሰዎች ሰበከላቸው። በዚህም ምክንያት በበዓሉ አጋማሽ ላይ ‘ከሕዝቡ ብዙዎቹ በእርሱ አመኑ።’ ኢየሱስ ስብከቱን በመቀጠሉ በበዓሉ የመጨረሻ ቀን “ብዙዎች በእርሱ አመኑ።” (ዮሐንስ 7:10, 14, 31, 37፤ 8:30) በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ትኩረቱን ወደ አዳዲሶቹ አማኞች በማዞር ደቀ መዝሙር ለመሆን የሚያስፈልገውን አንድ ወሳኝ ብቃት ነገራቸው። ሐዋርያው ዮሐንስ ይህን ብቃት ‘እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ’ በማለት በወንጌሉ ውስጥ መዝግቦታል።—ዮሐንስ 8:31
3. አንድ ሰው ‘በኢየሱስ ቃል ለመኖር’ የትኛውን ባሕርይ ማዳበር ያስፈልገዋል?
3 ኢየሱስ ይህንን ሲል እነዚያ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት እምነት ይጎድላቸዋል ማለቱ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ቃሉን በመጠበቅ ጸንተው እስከኖሩ ድረስ የእርሱ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት የመሆን መብት እንደተከፈተላቸው መናገሩ ነበር። ቃሉን ተቀብለዋል፤ ሆኖም እስከ መጨረሻው በቃሉ ጸንተው መኖር ይጠበቅባቸዋል። (ዮሐንስ 4:34፤ ዕብራውያን 3:14) በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ለመጨረሻ ጊዜ በተነጋገረበት ወቅት ከአንዴም ሁለቴ “ያለማቋረጥ ተከተለኝ” ብሎ መናገሩ ጽናት ተከታዮቹ ሊያሳዩት የሚገባ አስፈላጊ ባሕርይ መሆኑን ያሳያል። (ዮሐንስ 21:19, 22 NW ) አብዛኞቹ የጥንት ክርስቲያኖች በጽናት ተከትለውታል። (2 ዮሐንስ 4) ይሁንና እንዲጸኑ የረዳቸው ምን ነበር?
4. የጥንቶቹ ክርስቲያኖች እንዲጸኑ ያስቻላቸው ምንድን ነው?
4 ለሰባት አሥርተ ዓመታት ያህል ታማኝ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ሆኖ የኖረው ሐዋርያው ዮሐንስ አንድ አስፈላጊ ነገር ጠቅሷል። የታመኑ ክርስቲያኖችን “ብርቱዎች ስለ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም ቃል በእናንተ ስለሚኖር ክፉውንም ስለ አሸነፋችሁ” በማለት የምስጋና ቃል ጽፎላቸዋል። እነዚህ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ሊጸኑ ወይም በአምላክ ቃል ሊኖሩ የቻሉት የአምላክ ቃል በውስጣቸው ስለኖረ ነው። ለቃሉ ልባዊ አድናቆት ነበራቸው። (1 ዮሐንስ 2:14, 24) ዛሬም በተመሳሳይ ‘እስከ መጨረሻው ለመጽናት’ የአምላክ ቃል በእኛ እንዲኖር መፍቀድ አለብን። (ማቴዎስ 24:13) ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ የተናገረው አንድ ምሳሌ የዚህን ጥያቄ መልስ ይሰጠናል።
“ቃሉን የሚሰማ”
5. (ሀ) ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ውስጥ የጠቀሳቸው የተለያዩ የአፈር ዓይነቶች የትኞቹ ናቸው? (ለ) ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ውስጥ ዘሩና አፈሩ ምን ያመለክታሉ?
5 ኢየሱስ ዘር ሊዘራ ስለወጣ ሰው ምሳሌ የተናገረ ሲሆን ይህም በማቴዎስ፣ በማርቆስና በሉቃስ ወንጌሎች ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል። (ማቴዎስ 13:1-9, 18-23፤ ማርቆስ 4:1-9, 14-20፤ ሉቃስ 8:4-8, 11-15) ዘገባውን በምታነብበት ጊዜ የታሪኩ ዋና ገጽታ አንድ ዓይነት ዘር በተለያዩ የአፈር ዓይነቶች ላይ ወድቆ የተለያየ ውጤት ማምጣቱ እንደሆነ ትገነዘባለህ። የመጀመሪያው የአፈር ዓይነት ድድር ሲሆን ሁለተኛው ጭንጫ ሦስተኛው ደግሞ እሾህ የወረሰው ነው። አራተኛው የአፈር ዓይነት ከሦስቱ በተለየ “መልካም መሬት” ወይም ጥሩ አፈር ነው። ኢየሱስ ለምሳሌው በሰጠው ፍቺ መሠረት ዘሩ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው የመንግሥቱ መልእክት ሲሆን አፈሩ ደግሞ የተለያየ የልብ ዝንባሌ ያላቸውን ሰዎች ያመለክታል። በተለያዩ የአፈር ዓይነቶች የተገለጹትን ሰዎች የሚያመሳስሏቸው ባሕርያት ቢኖሩም በመልካሙ አፈር የተመሰሉትን ሰዎች ግን ከሌሎቹ የሚለያቸው የተለየ ባሕርይ አላቸው።
6. (ሀ) ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሰው አራተኛው የአፈር ዓይነት ከሦስቱ የሚለየው በምንድን ነው? ይህስ ምን ትርጉም አለው? (ለ) በክርስቶስ ደቀ መዝሙርነት ጸንቶ ለመኖር በጣም የሚያስፈልገው ምንድን ነው?
6 በሉቃስ 8:12-15 ላይ ከሚገኘው ታሪክ መረዳት እንደሚቻለው በአራቱም የአፈር ዓይነቶች የተመሰሉት ሰዎች ‘ቃሉን ሰምተዋል።’ ይሁን እንጂ ‘መልካምና በጎ ልብ’ ያላቸው ሰዎች ‘ቃሉን ከመስማት’ የበለጠ ነገር አድርገዋል። ይኸውም ‘ቃሉን ሰምተው ጠብቀዋል፤ እንዲሁም በመጽናት ፍሬ አፍርተዋል።’ መልካሙና በጎው አፈር የለሰለሰና በቂ አፈር ያለው በመሆኑ ዘሩ እንደልብ ሥር እንዲሰድና አድጎ ፍሬ እንዲያፈራ አስችሎታል። (ሉቃስ 8:8) በተመሳሳይም ጥሩ የልብ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች የአምላክን ቃል ተረድተዋል፣ አድንቀዋል እንዲሁም ከሕይወታቸው ጋር አዋህደዋል። (ሮሜ 10:10፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:7) የአምላክ ቃል በውስጣቸው ያድራል። በዚህም ምክንያት በመጽናት ፍሬ ያፈራሉ። በመሆኑም የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ሆኖ ለመጽናት ለአምላክ ቃል ከልብ የመነጨ ጥልቅ አድናቆት ማዳበር እጅግ አስፈላጊ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 4:15) ታዲያ ለአምላክ ቃል ከልብ የመነጨ አድናቆት ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?
የልብ ዝንባሌ እና የታሰበበት ማሰላሰል
7. ከመልካም ልብ ጋር ተያይዞ የተገለጸው ምንድን ነው?
7 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መልካምና በጎ ልብ ከምን ጋር ተያይዞ እንደተገለጸ ልብ በል። ‘የጻድቅ ልብ መልሱን ያስባል።’ (ምሳሌ 15:28) ‘አቤቱ፣ የአፌ ቃልና የልቤ አሳብ በፊትህ ያማረ ይሁን።’ (መዝሙር 19:14) ‘አፌ ጥበብን ይናገራል፣ የልቤም አሳብ ማስተዋልን።’—መዝሙር 49:3
8. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስን በምናነብበት ጊዜ ምን ዓይነት ልማድ ማስወገድ ይኖርብናል? ምንስ ማድረግ ይኖርብናል? (ለ) ከጸሎት ጋር በአምላክ ቃል ላይ ማሰላሰላችን ምን ጥቅሞች ያስገኝልናል? (‘በእውነት ጽኑ’ የሚለውን ሣጥን ጨምረህ መልስ።)
8 እንደነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ሁሉ እኛም በአምላክ ቃልና በሥራዎቹ ላይ በአድናቆትና በጸሎት ማሰብ ወይም ማሰላሰል ይኖርብናል። መጽሐፍ ቅዱስን ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በምናነብበት ጊዜ፣ ቆም ብሎ ተፈጥሮን በማየት ከመደሰት ይልቅ ፎቶ ግራፍ ለማንሳት ብቻ ከቦታ ቦታ እንደሚሯሯጥ አገር ጎብኚ መሆን የለብንም። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስን በምናጠናበት ጊዜ ቆም ብለን ስለምናነበው ነገር ማሰላሰል ይኖርብናል።b እንዲህ የምናደርግ ከሆነ የአምላክ ቃል ልባችንንና ስሜታችንን ይነካል፤ እንዲሁም አስተሳሰባችንን ይቀርጽልናል። በተጨማሪም ውስጣዊ ስሜታችንን ለአምላክ በጸሎት እንድንገልጽ ይገፋፋናል። በዚህም ምክንያት ከይሖዋ ጋር ያለን ወዳጅነት ይጠናከራል፤ እንዲሁም ለአምላክ ያለን ፍቅር በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር እንኳ ኢየሱስን መከተላችንን እንድንቀጥል ይገፋፋናል። (ማቴዎስ 10:22) በግልጽ እንደተመለከትነው ታማኝ ሆነን እስከ መጨረሻው መጽናት የምንፈልግ ከሆነ በአምላክ ቃል ላይ ማሰላሰላችን በጣም አስፈላጊ ነው።—ሉቃስ 21:19
9. የአምላክ ቃል በልባችን ውስጥ ሥር እንዲሰድ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
9 ኢየሱስ የተናገረው ምሳሌ በዘር የተመሰለው የአምላክ ቃል እድገት እንዳያደርግ እንቅፋት የሚሆኑ የተለያዩ ነገሮች እንዳሉም ይጠቁማል። ስለሆነም የታመንን ደቀ መዛሙርት ሆነን ለመቀጠል (1) በምሳሌው ውስጥ በመጥፎ የአፈር ዓይነቶች የተመሰሉትን ለእድገት እንቅፋት የሚሆኑ ችግሮች ለይተን ማወቅና (2) ችግሮቹን ለመፍታት ወይም ለማስወገድ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ በልባችን ላይ የተዘራው የመንግሥቱ ዘር ሥር እንዲሰድና ፍሬ እንዲያፈራ ማድረግ እንችላለን።
“በመንገድ ዳር”—በኑሮ ውጣ ውረድ መጠመድ
10. ኢየሱስ በምሳሌው ውስጥ የጠቀሰው የመጀመሪያው የአፈር ዓይነት ምንድን ነው? ትርጉሙስ?
10 ዘሩ ከወደቀባቸው ቦታዎች መካከል አንዱ ‘መንገድ ዳር’ ነበር፤ በዚህም ምክንያት ዘሩ ‘ተረገጠ።’ (ሉቃስ 8:5) በእርሻ መካከል ባለ መተላለፊያ ላይ የሚገኝ አፈር እግር ስለሚበዛበት ይደድራል። (ማርቆስ 2:23) በተመሳሳይም የዚህ ዓለም ውጣ ውረድ ጊዜያቸውን ያጣበበባቸውና ያባከናቸው ሰዎች ለአምላክ ቃል ከልብ የመነጨ አድናቆት ለማዳበር የሚያስችል ጊዜ ያጣሉ። ቃሉን ይሰማሉ፤ ሆኖም ጊዜ ሰጥተው ስለማያሰላስሉበት በልባቸው ውስጥ ሥር ሳይሰድ ይቀራል። ለቃሉ ፍቅር ከማዳበራቸው በፊት “ዲያብሎስ ይመጣል አምነውም እንዳይድኑ ቃሉን ከልባቸው ይወስዳል።” (ሉቃስ 8:12) ይህን እንዴት መከላከል ይቻላል?
11. ልባችን በመንገድ ዳር እንዳለው አፈር እንዳይደድር መከላከል የምንችለው እንዴት ነው?
11 ልባችን ፍሬ ማፍራት እንዳልቻለው በመንገድ ዳር እንዳለው አፈር እንዳይሆን መከላከል የሚቻልባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ። እግር የበዛበትና የደደረ አፈር በተደጋጋሚ ከታረሰና ከዚያ በኋላ ሰው እንዳይተላለፍበት ከተደረገ ሊለሰልስና ፍሬ ሊያፈራ ይችላል። በተመሳሳይም የአምላክን ቃል ለማጥናትና ለማሰላሰል የሚያስችል ጊዜ መመደብ ልባችንን እንደ ጥሩው አፈር ፍሬያማ ያደርገዋል። ለዚህ ቁልፉ ተራ በሆኑ የሕይወት ውጣ ውረዶች ከመጠን በላይ አለመጠመድ ነው። (ሉቃስ 12:13-15) ከዚህ ይልቅ በሕይወት ውስጥ ‘ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች’ ጊዜ መስጠት ይኖርብናል።—ፊልጵስዩስ 1:9-11
“በዓለት ላይ” —የፍርሃት ስሜት
12. ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ውስጥ በተጠቀሰው ሁለተኛው የአፈር ዓይነት ላይ የበቀለው ቡቃያ የጠወለገው ለምንድን ነው?
12 በሁለተኛው የአፈር ዓይነት ላይ የወደቀው ዘር በመጀመሪያው አፈር ላይ እንደወደቀው ዘር ከላይ እንደተቀመጠ አይቀርም። ከዚህ ይልቅ ሥር አውጥቶ ያድጋል። ፀሐይ ስትወጣ ግን ቡቃያው ከፀሐዩ ትኩሳት የተነሳ ይጠወልጋል። ይሁን እንጂ ለቡቃያው መጠውለግ ዋነኛው መንስኤ ሙቀቱ እንዳልሆነ ልብ ማለት ይገባል። በመልካሙ መሬት ላይ የበቀለውም ቢሆን ለፀሐይ ከመጋለጥ አላመለጠም። ሆኖም በጥሩ ሁኔታ አደገ እንጂ አልጠወለገም። ታዲያ በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? ኢየሱስ እንደተናገረው ቡቃያው ሊጠወልግ የቻለው ‘አፈሩ ጥልቀት’ እና “እርጥበት ስላልነበረው” ነው። (ማቴዎስ 13:5, 6፤ ሉቃስ 8:6) ከላይኛው አፈር ሥር ያለው “ዓለት” ወይም ጭንጫ ስለሆነ ዘሩ ሥር ሰድዶ እርጥበት በማግኘት ተደላድሎ እንዳይቆም አግዶታል። ቡቃያው የጠወለገው አፈሩ ጥልቀት ስለሌለው ነው።
13. ጥልቀት በሌለው አፈር የተመሰሉት ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው? እንዲህ እንዲሆኑ ያደረጋቸው ዋነኛው ምክንያት ምንድን ነው?
13 ስለ ሁለተኛው የአፈር ዓይነት የሚናገረው ይህ ምሳሌ ‘ቃሉን በደስታ ተቀብለው’ ኢየሱስን “ለጊዜው ብቻ” በቅንዓት የሚከተሉ ሰዎችን ያመለክታል። (ሉቃስ 8:13) እነዚህ ሰዎች በጠራራ ፀሐይ የተመሰለው “መከራ ወይም ስደት” በሚያጋጥማቸው ጊዜ በጣም ከመፍራታቸው የተነሳ ቃሉን ሲሰሙ ያገኙት ደስታና ብርታት ከስሞ ክርስቶስን መከተላቸውን ያቆማሉ። (ማቴዎስ 13:21) ይሁን እንጂ ለፍርሃታቸው ዋነኛው መንስኤ ተቃውሞ አይደለም። ደግሞስ በሚልዮን የሚቆጠሩ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የተለያዩ መከራዎች ቢፈራረቁባቸውም ታማኝነታቸውን ጠብቀው እየኖሩ አይደለም? (2 ቆሮንቶስ 2:4፤ 7:5) አንዳንድ ግለሰቦች ፈርተው እውነትን የሚተዉበት ዋነኛው ምክንያት በዓለት የተመሰለው ልባቸው አዎንታዊና መንፈሳዊ በሆኑ ነገሮች ላይ በጥልቀት እንዳያሰላስሉ ስለሚያግዳቸው ነው። በዚህም ምክንያት ለይሖዋና ለቃሉ ጥልቅ አድናቆት ስላላዳበሩ የሚያጋጥማቸውን ተቃውሞ መቋቋም ሳይችሉ ቀርተዋል። አንድ ሰው እንዲህ ያለ ውድቀት እንዳይደርስበት መከላከል የሚችለው እንዴት ነው?
14. አንድ ሰው የልቡ ሁኔታ ጥልቀት እንደሌለው አፈር እንዳይሆን ለመከላከል ምን እርምጃዎችን መውሰድ ይኖርበታል?
14 አንድ ሰው ሥር የሰደደ ምሬት፣ ራስ ወዳድነት ወይም ተዛማጅነት ያላቸው ሌሎች ስውር ዓለት መሰል ስሜቶች ለእድገቱ እንቅፋት እንዳይሆኑበት መጠንቀቅ ይኖርበታል። እንዲህ ያለ ችግር ካለበት የአምላክ ቃል ያለው ኃይል እንቅፋቱን ሊያስወግድለት ይችላል። (ኤርምያስ 23:29፤ ኤፌሶን 4:22፤ ዕብራውያን 4:12) ከዚያ በኋላ ጸሎት የታከለበት ማሰላሰል በግለሰቡ ልብ ውስጥ ‘የተተከለው ቃል’ ሥር እንዲሰድ ሊያደርገው ይችላል። (ያዕቆብ 1:21) እንዲህ ማድረጉ ተስፋ አስቆራጭ ችግሮችን ለመቋቋም የሚያስችል ብርታትና መከራን በታማኝነት ለመወጣት የሚያስችል ድፍረት ያስገኛል።
“በእሾህ መካከል”—የተከፈለ ልብ
15. (ሀ) ኢየሱስ የጠቀሰው ሦስተኛው የአፈር ዓይነት ይበልጥ ትኩረታችንን የሚስበው ለምንድን ነው? (ለ) በሦስተኛው የአፈር ዓይነት ላይ የተዘራው ዘር ውሎ አድሮ ምን ያጋጥመዋል? ለምንስ?
15 እሾህ የወረሰው ሦስተኛው የአፈር ዓይነት ከመልካሙ አፈር ጋር አንዳንድ ተመሳሳይነት ስላለው ይበልጥ ትኩረታችንን የሚስብ ሆኖ እናገኘዋለን። ከጥሩው አፈር ባልተለየ እሾህ የወረሰው አፈርም በላዩ ላይ የተዘራው ዘር ሥር እንዲሰድና እንዲበቅል ያደርገዋል። በሁለቱ የአፈር ዓይነቶች ላይ በተዘሩት ዘሮች አበቃቀል ረገድ መጀመሪያ ላይ ምንም ልዩነት አይታይም። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ግን ቡቃያውን የሚያንቅ አንድ ችግር ይከሰታል። ከጥሩው አፈር በተቃራኒ ይህ አፈር እሾህ ይወርሰዋል። በዚህ አፈር ላይ የበቀለው ቡቃያ ገና ከመሬት ብቅ ሳይል ‘አብሮት የበቀለው እሾህ’ ምግብ፣ የፀሐይ ብርሃንና ቦታ ይሻማዋል። ቡቃያውና እሾሁ በዚህ ሁኔታ ለተወሰነ ጊዜ ከቆዩ በኋላ ውሎ አድሮ እሾሁ ያሸንፍና ተክሉን ‘ያንቀዋል።’—ሉቃስ 8:7
16. (ሀ) እሾህ በወረሰው አፈር የተመሰሉት ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው? (ለ) በሦስቱ የወንጌል ዘገባዎች መሠረት እሾሁ የምን ምሳሌ ነው?—የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።
16 እሾህ በወረሰው አፈር የተመሰሉት ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው? ኢየሱስ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “እነዚህ የሚሰሙት ናቸው፤ መንገዳቸውንም ሄደው በሕይወት ዘመን በአሳብና በባለ ጠግነት ምቾት ይታነቃሉ፣ ሙሉ ፍሬም አያፈሩም።” (ሉቃስ 8:14) ዘሪው የዘራው ዘርና እሾሁ አብረው እንደሚያድጉ ሁሉ አንዳንድ ግለሰቦችም የአምላክን ቃልና የዚህን ዓለም ‘አሳብና የባለ ጠግነት ምቾት’ እኩል ለማስተናገድ ይሞክራሉ። የአምላክ ቃል እውነት በልባቸው ውስጥ ተዘርቷል፤ ሆኖም ትኩረትን የሚከፋፍሉ ሌሎች ጉዳዮች ለእድገት የሚያስፈልገውን ነገር ይሻሙታል። ምሳሌያዊው ልባቸው ተከፍሏል። (ሉቃስ 9:57-62) ይህም ከአምላክ ቃል ባነበቡት ነገር ላይ በጸሎት የሚያሰላስሉበት በቂ ጊዜ እንዳይኖራቸው ያደርጋቸዋል። የአምላክን ቃል በተሟላ ሁኔታ ስለማይረዱ ለመጽናት የሚያስችል ልባዊ አድናቆት ይጎድላቸዋል። ውሎ አድሮ መንፈሳዊ ፍላጎታቸው መንፈሳዊ ባልሆኑ ነገሮች ይሸፈንና በመጨረሻም ‘ሙሉ በሙሉ ይታነቃሉ።’c ይሖዋን በሙሉ ልባቸው የማይወድዱት ሰዎች መጨረሻቸው ምንኛ አሳዛኝ ነው!—ማቴዎስ 6:24፤ 22:37
17. ኢየሱስ በምሳሌው ውስጥ የገለጸው ምሳሌያዊ እሾህ እንዳያንቀን በሕይወታችን ውስጥ ምን ምርጫዎችን ማድረግ ይኖርብናል?
17 ከቁሳዊ ነገሮች ይልቅ ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ቅድሚያ በመስጠት በዚህ ዓለም አሳብና ምቾት እንዳንታነቅ ጥንቃቄ ማድረግ እንችላለን። (ማቴዎስ 6:31-33፤ ሉቃስ 21:34-36) መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና ባነበብነው ነገር ላይ ማሰላሰል ቸል ሊባል አይገባውም። አኗኗራችንን በተቻለን መጠን ቀላል የምናደርግ ከሆነ አእምሯችንን ሰብሰብ አድርገን እየጸለይን ለማሰላሰል የሚያስችል ተጨማሪ ጊዜ ማግኘት እንችላለን። (1 ጢሞቴዎስ 6:6-8) በልባቸው ላይ የተዘራው ምሳሌያዊ ዘር በቂ ምግብ፣ የፀሐይ ብርሃንና ቦታ አግኝቶ ፍሬ እንዲያፈራ እሾሁን የሚነቅሉ ማለትም አኗኗራቸውን ቀላል የሚያደርጉ የአምላክ አገልጋዮች የይሖዋን በረከት ያገኛሉ። የ26 ዓመቷ ሳንድራ “በእውነት ውስጥ በመኖሬ ስላገኘኋቸው በረከቶች መለስ ብዬ ሳስብ ይህ ዓለም ከዚህ በረከት ጋር የሚተካከል ምንም ነገር ሊሰጠኝ እንደማይችል እገነዘባለሁ!” ብላለች።—መዝሙር 84:11
18. በአምላክ ቃል መኖርና በክርስቲያንነታችን መጽናት የምንችለው እንዴት ነው?
18 በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ወጣት አዛውንት ሳንል ሁላችንም በአምላክ ቃል መኖርና በክርስቶስ ደቀ መዝሙርነታችን መጽናት የምንችለው ቃሉ በውስጣችን ከኖረ ብቻ ነው። እንግዲያው የምሳሌያዊው ልባችን አፈር እንዳይደድር፣ ጭንጫነት እንዳይኖረው ወይም አረም እንዳይወርሰው እንጠንቀቅ። ከዚህ ይልቅ የለሰለሰና ጥልቀት ያለው እንዲሆን ጥረት እናድርግ። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ የአምላክ ቃል ልባችን ውስጥ ሥር እንዲሰድ ማድረግና ‘በመጽናት ፍሬ ማፍራት’ እንችላለን።—ሉቃስ 8:15
[የግርጌ ማስታወሻ ]
a በዚህ ርዕስ ውስጥ ከሦስቱ ብቃቶች መካከል አንዱን እንመለከታለን። የተቀሩትን በሚቀጥሉት ሁለት ርዕሶች ውስጥ እንመረምራለን።
b ባነበብከው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ከጸሎት ጋር ለማሰላሰል እንደሚከተለው እያልህ ራስህን መጠየቅ ትችላለህ:- ‘የትኞቹን የይሖዋ ባሕርያት ይጠቅሳል? ከመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጥ ጋር ምን ዝምድና አለው? በሕይወቴ ወይም ከሌሎች ጋር ባለኝ ግንኙነት እንዴት ልጠቀምበት እችላለሁ?’
c ሦስቱ የወንጌል ዘገባዎች ‘የዚህ ዓለም አሳብ፣’ “የባለጠግነት ማታለል፣” “የሌላውም ነገር ምኞት፣” እና ‘ተድላና ደስታ’ በማለት እንደገለጹት ሁሉ ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሰው ዘር የታነቀው በዚህ ዓለም አሳብ እንዲሁም ተድላና ደስታ ነው።—ማርቆስ 4:19፤ ማቴዎስ 13:22፤ ሉቃስ 8:14 አ.መ.ት ፤ ኤርምያስ 4:3, 4
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ‘በኢየሱስ ቃል መኖራችን’ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
• የአምላክ ቃል በልባችን እንዲኖር ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
• ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሱት አራቱ የአፈር ዓይነቶች የሚያመለክቱት ምን ዓይነት ሰዎችን ነው?
• በአምላክ ቃል ላይ ለማሰላሰል ጊዜ ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
‘በእውነት ጽኑ’
ለረጅም ዓመታት የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ሆነው የኖሩ ብዙ ክርስቲያኖች ከዓመት ዓመት ‘በእውነት መጽናታቸውን’ አስመስክረዋል። (2 ጴጥሮስ 1:12) እንዲጸኑ የረዳቸው ምን ይሆን? እስቲ አንዳንዶቹ የተናገሩትን ተመልከት።
“ማታ ከመተኛቴ በፊት መጽሐፍ ቅዱስን አንብቤ እጸልያለሁ። ከዚያም ባነበብኩት ላይ አሰላስላለሁ።”—ጄን፣ በ1939 የተጠመቁ እህት።
“ሁሉን ቻይ አምላክ የሆነው ይሖዋ ከልብ እንደሚወደን ሳሰላስል ውስጣዊ የመረጋጋት ስሜትና ታማኝነቴን ለመጠበቅ የሚያስችል ብርታት አገኛለሁ።”—ፓትሪሻ፣ በ1946 የተጠመቁ እህት።
“ጥሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ልማድ በማዳበርና ‘በአምላክ ጥልቅ ነገሮች’ ላይ በጥልቅ በመመሰጥ እስከ አሁን ይሖዋን ማገልገሌን መቀጠል ችያለሁ።”—1 ቆሮንቶስ 2:10፤ አና፣ በ1939 የተጠመቁ እህት።
“ልቤንና ውስጣዊ ፍላጎቴን ለመመርመር መጽሐፍ ቅዱስንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን አነብባለሁ።”—ዜልዳ፣ በ1943 የተጠመቁ እህት።
“ከቤት ወጣ ብዬ በእግሬ እየተንሸራሸርኩ ለይሖዋ ውስጣዊ ስሜቴን በጸሎት መንገር በጣም የሚያስደስተኝ ነገር ነው።”—ራልፍ፣ በ1947 የተጠመቁ ወንድም።
“ጠዋት ላይ የመጀመሪያው ሥራዬ የዕለቱን ጥቅስ መመርመርና መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ነው። እንዲህ በማድረግ ቀኑን ሙሉ የማሰላስልበትን አዲስ ሐሳብ አገኛለሁ።”—ማሪ፣ በ1935 የተጠመቁ እህት።
“ጥቅስ በጥቅስ የተብራሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን መመርመር በእጅጉ ያስደስተኛል።”—ዳንኤል፣ በ1946 የተጠመቁ ወንድም።
አንተስ በአምላክ ቃል ላይ በጸሎት ለማሰላሰል ጊዜ ትመድባለህን?—ዳንኤል 6:10ለ፤ ማርቆስ 1:35፤ ሥራ 10:9
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ በመስጠት ‘በመጽናት ፍሬ ማፍራት’ እንችላለን