ቡጢያችሁን በጥበብ ሰንዝሩ
1. በ1 ቆሮንቶስ 9:26 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ለአገልግሎታችን የሚሠራው እንዴት ነው?
1 ሐዋርያው ጳውሎስ “እኔ መድረሻውን እንደማያውቅ ሰው አልሮጥም፤ ቡጢዬን የምሰነዝረውም አየር ለመምታት አይደለም” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮ. 9:26) ጳውሎስ ይህን ያለው ትኩረቱ ሙሉ በሙሉ ያረፈው አንድ ነገር ላይ ይኸውም መንፈሳዊ ግቦችን በመከታተል ላይ ብቻ እንደሆነ ለመጥቀስ ነው። ሆኖም እዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘው መሠረታዊ ሥርዓት ለአገልግሎታችንም ይሠራል። የምንሰነዝረው ‘ቡጢ’ ወይም የምናደርገው ጥረት ስኬታማ እንዲሆን ጥበብ መጠቀም ይኖርብናል። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
2. የምንሰብክበትን ጊዜና ቦታ በመምረጥ ረገድ የጳውሎስንና በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ የሌሎች ወንጌላውያንን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?
2 ሰዎች ወደሚገኙባቸው ቦታዎች ሂዱ፦ ጳውሎስና በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ሌሎች ወንጌላውያን፣ ሰዎች ይገኛሉ ብለው ወዳሰቡባቸው ቦታዎች ሁሉ እየሄዱ ይሰብኩ ነበር። (ሥራ 5:42፤ 16:13፤ 17:17) በመሆኑም በክልላችን ያሉት አብዛኞቹ ሰዎች በቤታቸው የሚገኙት ምሽት ላይ ከሆነ በዚህ ሰዓት ከቤት ወደ ቤት ማገልገላችን የተሻለ ነው። በአውቶብስ ማቆሚያ ቦታዎች፣ ጠዋትና አመሻሹ ላይ ወደ ሥራ የሚሄዱና ከሥራ የሚመለሱ ሰዎችን በብዛት ማግኘት ይቻል ይሆን? በክልላችሁ በሚገኙ የገበያ ቦታዎች ሰው በብዛት የሚገኘው መቼ መቼ ነው? በእነዚህ ጊዜያት መንገድ ላይ ማገልገላችን ውጤት ሊያስገኝልን ይችላል። መንገድ ላይ ስንመሠክር ሁለታችንም አንድ ሰው ከማስቆም ይልቅ አብዛኛውን ጊዜ በተናጠል ማገልገላችን የተሻለ ነው። እንዲሁም ሶስት ሆኖ ማገልገል ውጤታማ ላይሆን ይችላል። በተጨማሪም የግል ጭውውት በማድረግ ትኩረታችን እንዲከፋፈል ከማድረግ ይልቅ ለሚቀጥለው ሰው ስለምንመሠክርበት መንገድ ማሰባችን የተሻለ ነው።
3. ክልላችንን በምንሸፍንበት ወቅት ቡጢያችንን በጥበብ መሰንዘር የምንችለው እንዴት ነው?
3 ክልላችሁን በጥበብ ሸፍኑ፦ ክልላችንን በምንሸፍንበት ጊዜም ቢሆን ቡጢያችንን በጥበብ ለመሰንዘር እንድንችል አንዳንድ ጥንቃቄዎች ማድረግ አለብን። ለምሳሌ ያህል፣ በርካታ አስፋፊዎችን በአንድ አካባቢ ይዞ ከመሄድ ይልቅ ተከፋፍሎ መሥራት፣ ብዙ ሰዎችን ለማደራጀት የሚጠይቀውን ጊዜና ጥረት ይቀንሳል። በተመሳሳይም በገጠራማ አካባቢ በምናገለግልበት ጊዜ በመኪና ወደዚያ የሚሄዱት ቡድኖች ቁጥር አነስተኛ መሆኑ ክልሉን በፍጥነት ለመሸፈንና ብዙ ሰዎችን ለማነጋገር የሚያስችል አጋጣሚ ይፈጥራል። ወደ ክልላችን ለመድረስ የሚፈጅብንን ጊዜ ለመቀነስ በመኖሪያ ቤታችን አካባቢ የሚገኝ ክልል መውሰድ እንችል ይሆን?
4. ‘ሰው በማጥመዱ’ ሥራ ስኬታማ ለመሆን ምን ሊረዳን ይችላል?
4 ኢየሱስ የምሥራቹን ሰባኪዎች ‘ከሰው አጥማጆች’ ጋር አመሳስሏቸዋል። (ማር. 1:17) የአንድ ዓሣ አጥማጅ ግብ፣ መረቡን ወደ ውኃው መጣል ብቻ ሳይሆን ዓሣ መያዝ ጭምር ነው። ስለሆነም ጎበዝ ዓሣ አጥማጆች፣ ዓሣ ይገኛል ብለው ወደሚያስቡበት ቦታ በትክክለኛው ሰዓት በመሄድ በፍጥነት ዓሣ ማጥመድ ይጀምራሉ። በዚህ መንገድ ሥራቸውን በጥበብ ያከናውናሉ። እኛም በአገልግሎታችን ተመሳሳይ ትጋት እናሳይ።—ዕብ. 6:11