የጌታ እራት ይከበር የነበረው እንዴት ነው?
ክርስቲያኑ ሐዋርያው ጳውሎስ የጌታ እራት እንዴት መከበር እንዳለበት ሲናገር እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እኔ ከጌታ የተቀበልሁትን ለእናንተ አስተላልፌአለሁና፤ ጌታ ኢየሱስ አልፎ በተሰጠባት ሌሊት፣ እንጀራን አንሥቶ ከባረከ በኋላ ቈርሶ፣ ‘ይህ ስለ እናንተ የሚሆን ሥጋዬ ነው፤ ለመታሰቢያዬም አድርጉት’ አለ። እንዲሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ፣ ‘ይህ ጽዋ በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው፤ ስለዚህ ከጽዋው በምትጠጡበት ጊዜ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት’ አለ። ይህን እንጀራ በምትበሉበት ጊዜ፣ ይህንም ጽዋ በምትጠጡበት ጊዜ ሁሉ ጌታ እስከሚመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁ።”—1 ቆሮንቶስ 11:23-26
ጳውሎስ እንደተናገረው ኢየሱስ የጌታ እራትን ያቋቋመው የአስቆሮቱ ይሁዳ ክርስቶስን እንዲሰቅሉት በሮማውያን ላይ ግፊት ላሳደሩት የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ‘አሳልፎ በሰጠው ሌሊት’ ነበር። በዓሉ የተከበረው ሐሙስ መጋቢት 31, 33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ሲሆን አርብ ሚያዝያ 1 ከሰዓት በኋላ ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ ተገደለ። አይሁዳውያን አንድ ቀን የሚሉት ከምሽት አንስቶ እስከቀጣዩ ቀን ምሽት ያለውን ጊዜ ስለሆነ የጌታ እራት የተቋቋመውም ሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ የሞተው በአንድ ቀን ማለትም ኒሳን 14, 33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ነበር።
ኢየሱስ “ለመታሰቢያዬም አድርጉት” ብሎ ነበር። ስለዚህ ከቂጣውና ከወይኑ የሚካፈሉ ሰዎች ለኢየሱስ መታሰቢያ እንዲሆን በዓሉን በየጊዜው ማክበር ነበረባቸው። (1 ቆሮንቶስ 11:24) ስለሆነም የጌታ እራት የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ተብሎም ይጠራል።
የኢየሱስ ሞት መታሰብ የሚኖርበት ለምንድን ነው?
የዚህ ጥያቄ መልስ ኢየሱስ ከሞተበት ዓላማ ጋር የተያያዘ ነው። ኢየሱስ የሞተው የይሖዋን ሉዓላዊነት ለማስከበር ነው። በዚህም ሰዎች አምላክን የሚያገለግሉት ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ነው በማለት ሰይጣን ያቀረበው ክስ ሐሰት መሆኑን አረጋግጧል። (ኢዮብ 2:1-5፤ ምሳሌ 27:11) ኢየሱስ ፍጹም ሰው ሆኖ በመሞት ‘ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ሰጥቷል።’ (ማቴዎስ 20:28) አዳም በአምላክ ላይ ባመጸ ጊዜ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱንና ለዘላለም የመኖር መብቱን አጥቷል። ይሁን እንጂ ‘እግዚአብሔር ዓለምን እንዲሁ ስለወደደ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ አንድያ ልጁን ሰጥቷል።’ (ዮሐንስ 3:16) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “የኀጢአት ደመ ወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር ስጦታ ግን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ነው” ይላል።—ሮሜ 6:23
የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ሁለት ታላላቅ የፍቅር መግለጫዎች የታዩበት ሲሆን እነዚህም ይሖዋ ልጁን በመስጠት ለሰው ልጆች ያሳየው ታላቅ ፍቅርና ኢየሱስ ሰብዓዊ ሕይወቱን በፈቃደኝነት አሳልፎ በመስጠት ለመላው የሰው ዘር ያሳየው የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ ፍቅር ናቸው። የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ በዓል እነዚህ የፍቅር መግለጫዎች ጎላ ብለው እንዲታዩ ያደርጋል። ይሖዋና ኢየሱስ ላሳዩን ፍቅር አድናቆታችንን መግለጽ አይኖርብንም? ይህን ማድረግ የምንችልበት አንደኛው መንገድ በጌታ እራት በዓል ላይ በመገኘት ነው።
የቂጣውና የወይን ጠጁ ትርጉም
ኢየሱስ የጌታ እራትን ባቋቋመበት ጊዜ ምሳሌያዊ ትርጉም ያላቸውን ቂጣና ቀይ ወይን ጠጅ ተጠቅሞ ነበር። ኢየሱስ ቂጣውን አንስቶ “ከባረከ በኋላ ቆርሶ፣ ‘ይህ [ቂጣ] ስለ እናንተ የሚሆን ሥጋዬ ነው’” ብሏቸው ነበር። (1 ቆሮንቶስ 11:24) በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ እርሾ ኃጢአትን ስለሚያመለክት ቂጣው ምንም እርሾ ሳይገባበት በውኃ ብቻ ከተቦካ ዱቄት የሚዘጋጅ ሲሆን ለሁሉም እንዲዳረስ መቆራረስ አለበት። (ማቴዎስ 16:11, 12፤ 1 ቆሮንቶስ 5:6, 7) ኢየሱስ ምንም ኃጢአት አልነበረበትም። ስለዚህ ፍጹም ሰብዓዊ አካሉ ለሰው ልጆች ቤዛ ሆኖ መቅረብ ይችል ነበር። (1 ዮሐንስ 2:1, 2) ስለሆነም ኃጢአት የሌለበትን የክርስቶስን ሥጋ የሚወክለው ቂጣ እርሾ ያልገባበት መሆኑ የተገባ ነው።
እንዲሁም ኢየሱስ ምንም ነገር ያልገባበትን ቀይ ወይን ጠጅ የያዘውን ጽዋ አንስቶ ካመሰገነ በኋላ “ይህ ጽዋ በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው” አለ። (1 ቆሮንቶስ 11:25) ቀዩ ወይን ጠጅ የኢየሱስን ደም ይወክላል። በ1513 ከክርስቶስ ልደት በፊት በአምላክና በእስራኤል ብሔር መካከል የተገባው ቃል ኪዳን በኮርማዎችና በፍየሎች ደም እንደጸና ሁሉ አዲሱ ቃል ኪዳንም ኢየሱስ ሲሞት በፈሰሰው ደም አማካኝነት ይጸናል።
ከቂጣውና ከወይን ጠጁ የሚካፈሉት እነማን ናቸው?
በመታሰቢያው በዓል ላይ ከሚቀርቡት ቂጣና የወይን ጠጅ መካፈል የሚገባቸው እነማን እንደሆኑ ለማወቅ አዲሱ ቃል ኪዳን ምን እንደሆነና ቃል ኪዳኑ የተፈጸመው በእነማን መካከል እንደሆነ መረዳት ይኖርብናል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “‘ከእስራኤል ቤትና፣ ከይሁዳ ቤት ጋር’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ጊዜ ይመጣል። . . . ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፤ በልባቸውም እጽፈዋለሁ። እኔ አምላክ እሆናቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ። . . . በደላቸውን ይቅር እላለሁ፤ ኀጢአታቸውንም መልሼ አላስብም።’”—ኤርምያስ 31:31-34
አዲሱ ቃል ኪዳን ከይሖዋ አምላክ ጋር ልዩ ዝምድና ለመፍጠር አስችሏል። በዚህ ቃል ኪዳን አማካኝነት የተወሰኑ ሰዎች የአምላክ ሕዝብ የመሆን መብት ያገኙ ሲሆን እርሱ ደግሞ አምላካቸው ይሆናል። የይሖዋ ሕግ በልባቸው ተጽፏል፤ ከተገረዙት አይሁዳውያን ወገን ያልሆኑ ሰዎች እንኳን በአዲሱ ቃል ኪዳን አማካኝነት ከአምላክ ጋር ዝምድና መመሥረት ይችላሉ። (ሮሜ 2:29) መጽሐፍ ቅዱስን ከጻፉት ሰዎች መካከል አንዱ የነበረው ሉቃስ አምላክ ‘ለእርሱ የሚሆነውን ሕዝብ ለማግኘት አሕዛብን የመጎብኘት’ ዓላማ እንዳለው ጽፎ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 15:14) በ1 ጴጥሮስ 2:10 ላይ እንደተገለጸው እነዚህ አሕዛብ ‘ቀድሞ ወገን ያልነበሩና አሁን ግን የእርሱ ሕዝብ የሆኑ ናቸው።’ መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን ሕዝቦች ‘የአምላክ እስራኤል’ ማለትም መንፈሳዊ እስራኤላውያን በማለት ይጠራቸዋል። (ገላትያ 6:16፤ 2 ቆሮንቶስ 1:21) እንግዲያው አዲሱ ቃል ኪዳን በይሖዋ አምላክና በመንፈሳዊ እስራኤላውያን መካከል የተፈጸመ ቃል ኪዳን ነው።
ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት በግሉ ሌላ ቃል ኪዳን ገብቷል። “አባቴ ከእኔ ጋር የመንግሥት ቃል ኪዳን እንዳደረገ እኔም ከእናንተ ጋር ቃል ኪዳን አደርጋለሁ” ብሏቸው ነበር። (ሉቃስ 22:29 NW) ይህ የመንግሥት ቃል ኪዳን ነው። ፍጹም ካልሆኑ የሰው ልጆች መካከል በዚህ የመንግሥት ቃል ኪዳን የታቀፉት 144,000 ናቸው። ትንሣኤ አግኝተው ወደ ሰማይ ከሄዱ በኋላ ከክርስቶስ ጋር ነገሥታትና ካህናት በመሆን ይገዛሉ። (ራእይ 5:9, 10፤ 14:1-4) ከይሖዋ ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የተጋቡት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋርም የመንግሥት ቃል ኪዳን ገብተዋል። በጌታ እራት ላይ ከሚቀርቡት ቂጣና ወይን ጠጅ የመካፈል መብት ያላቸው እነዚህ ብቻ ናቸው።
ከወይን ጠጁና ከቂጣው የመካፈል መብት ያላቸው ሰዎች ከአምላክ ጋር ልዩ ዝምድና እንዳላቸውና ከክርስቶስ ጋር አብረው የሚወርሱ መሆናቸውን የሚያውቁት እንዴት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሏል:- “የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ሆኖ ይመሰክርልናል። ልጆች ከሆን ወራሾች ደግሞ ነን፤ የክብሩ ተካፋዮች እንሆን ዘንድ በእርግጥ የመከራው ተካፋዮች ብንሆን፣ የእግዚአብሔር ወራሾች፣ ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን።”—ሮሜ 8:16, 17
አምላክ ከክርስቶስ ጋር አብረው የሚወርሱትን በቅዱስ መንፈሱ ወይም በኃይሉ አማካኝነት ቀብቷቸዋል። የመንግሥቱ ወራሾች መሆናቸውን የሚያረጋግጥላቸው ይህ መንፈስ ነው። በቅቡዓን ክርስቲያኖች ልብ ውስጥ ወደ ሰማይ የመሄድ ተስፋ ይፈጥርባቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰማያዊው ሕይወት የሚናገረውን ሁሉ ለእነርሱ እንደተጻፈ አድርገው ይመለከቱታል። ከዚህም በላይ እነዚህ ክርስቲያኖች ምድራዊ ሕይወታቸውንም ሆነ ሰብዓዊ ዝምድናቸውን በሙሉ መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኞች ናቸው። በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ መኖር አስደሳች እንደሚሆን ቢያውቁም የእነርሱ ተስፋ ግን ያ እንዳልሆነ ይገነዘባሉ። (መዝሙር 37:11) ወደ ሰማይ የመሄድ ጽኑ ተስፋ የያዙት በተሳሳተ ሃይማኖታዊ አመለካከት ሳይሆን የአምላክ መንፈስ በሚያሳድርባቸው ግፊት የተነሳ ነው። ከዚህ አንጻር በመታሰቢያው በዓል ላይ ከሚቀርቡት ቂጣና ወይን መካፈላቸው የተገባ ነው።
አንድ ሰው በአዲሱ ቃል ኪዳንና በመንግሥት ቃል ኪዳን የታቀፈ ለመሆኑ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ አይደለም እንበል። ከክርስቶስ ጋር የሚወርስ መሆኑን የአምላክ መንፈስ ባይመሰክርለትስ? እንደዚያ ከሆነ በመታሰቢያው በዓል ላይ ከሚቀርበው ቂጣና ወይን ጠጅ መካፈሉ ተገቢ አይሆንም። አዎን፣ አንድ ሰው ወደ ሰማይ የመሄድ ተስፋ ሳይኖረው ሆነ ብሎ ራሱን ንጉሥና ካህን አድርጎ ቢያቀርብ አምላክ ያዝንበታል።—ሮሜ 9:16፤ ራእይ 22:5
በዓሉ መከበር ያለበት በየስንት ጊዜው ነው?
የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ በዓል መከበር የሚኖርበት በየሳምንቱ ወይም በየቀኑ ነው? ክርስቶስ የጌታን እራት ያቋቋመውና ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ የተገደለው በማለፍ በዓል ዕለት ነበር። ፋሲካ በመባል የሚታወቀው የማለፍ በዓል እስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት ነጻ የወጡበትን ዕለት ለማሰብ በዓመት አንድ ጊዜ ኒሳን 14 ይከበር ነበር። (ዘፀአት 12:6, 14፤ ዘሌዋውያን 23:5) ‘ፋሲካችን የሆነው የክርስቶስ’ ሞት መታሰቢያ በዓል መከበር ያለበት በየሳምንቱ ወይም በየዕለቱ ሳይሆን በየዓመቱ ነው። (1 ቆሮንቶስ 5:7 የ1954 ትርጉም) ክርስቲያኖች የጌታን እራት ሲያከብሩ ኢየሱስ በዓሉን ባቋቋመበት ዕለት ያደረገውን ሥርዓት ይከተላሉ።
ጳውሎስ “ይህን እንጀራ በምትበሉበት ጊዜ፣ ይህንም ጽዋ በምትጠጡበት ጊዜ ሁሉ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁ” ብሎ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 11:26) እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነበር? ቅቡዓን ክርስቲያኖች በመታሰቢያው በዓል ላይ ከሚቀርቡት ቂጣና ወይን በተካፈሉ ጊዜ ሁሉ በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ ያላቸውን እምነት ለሌሎች ያውጃሉ ማለቱ ነበር።
ቅቡዓን ክርስቲያኖች የክርስቶስን ሞት መታሰቢያ በዓል “[እርሱ] እስከሚመጣ ድረስ” ያከብራሉ። ይህ በዓል ኢየሱስ በሰማይ መንፈሳዊ ሕይወት ለመኖር ትንሣኤ የሚያገኙ ቅቡዓን ተከታዮቹን ለመቀበል ንጉሣዊ ሥልጣኑን ይዞ “እስኪመጣ ድረስ” መከበሩን ይቀጥላል። (1 ተሰሎንቄ 4:14-17) ይህ ደግሞ ክርስቶስ “ሄጄም ስፍራ ካዘጋጀሁላችሁ በኋላ፣ እኔ ባለሁበት እናንተም ከእኔ ጋር እንድትሆኑ ልወስዳችሁ ዳግመኛ እመጣለሁ” በማለት ለአሥራ አንዱ ታማኝ ሐዋርያት ከነገራቸው ቃላት ጋር ይስማማል።—ዮሐንስ 14:3
ይህ በዓል ለአንተ ምን ትርጉም አለው?
ከኢየሱስ መሥዋዕት ተጠቃሚ ለመሆንና በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት በመታሰቢያው በዓል ላይ ከሚቀርቡት ወይን ጠጅና ቂጣ መካፈል የግድ ያስፈልጋል? በፍጹም። ኖኅን፣ አብርሃምን፣ ሣራን፣ ይስሐቅን፣ ርብቃን፣ ዮሴፍን፣ ሙሴንና ዳዊትን የመሳሰሉ ፈሪሃ አምላክ የነበራቸው ሰዎች በምድር ላይ ለመኖር ትንሣኤ ካገኙ በኋላ በመታሰቢያው በዓል ላይ ከሚቀርበው ቂጣና ወይን ጠጅ እንደሚካፈሉ የሚጠቁም ዘገባ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አናገኝም። ያም ሆኖ ግን እነርሱም ሆኑ በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ማግኘት የሚፈልጉ ሌሎች ሰዎች በሙሉ በአምላክና በክርስቶስ እንዲሁም ይሖዋ በኢየሱስ አማካኝነት ባዘጋጀው የቤዛ ዝግጅት ላይ እምነት ማሳየት ይኖርባቸዋል። (ዮሐንስ 3:36፤ 14:1) አንተም የዘላለም ሕይወት ለማግኘት የምትፈልግ ከሆነ እንዲህ ዓይነት እምነት ሊኖርህ ይገባል። በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ መገኘትህ ይሀን ታላቅ መሥዋዕት እንድታስታውስና ለመሥዋዕቱ ያለህ አድናቆት ከፍ እንዲል ይረዳሃል።
ሐዋርያው ዮሐንስ እንደሚከተለው ብሎ ለቅቡዓን ባልንጀሮቹ በጻፈ ጊዜ የኢየሱስን መሥዋዕት አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ተናግሯል:- “ልጆቼ ሆይ፤ ይህን የምጽፍላችሁ ኀጢአት እንዳትሠሩ ነው፤ ነገር ግን ማንም ኀጢአት ቢሠራ፣ በአብ ዘንድ ጠበቃ አለን፤ እርሱም ጻድቁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱም የኀጢአታችን ማስተስረያ ነው፤ ይኸውም ለዓለም ሁሉ ኀጢአት እንጂ ለእኛ ብቻ አይደለም።” (1 ዮሐንስ 2:1, 2) ቅቡዓን ክርስቲያኖች የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት የኃጢአታቸው ማስተስረያ እንደሆነ መናገራቸው የተገባ ነው። ሆኖም ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ለመላው የሰው ዘርም የቀረበ መሥዋዕት ነው ለማለት ይቻላል!
አንተስ ሚያዝያ 4, 2004 በሚከበረው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ ትገኛለህ? በዓሉ የሚከበረው በዓለም ዙሪያ የይሖዋ ምሥክሮች በሚሰበሰቡባቸው አዳራሾች ውስጥ ነው። በበዓሉ ላይ የምትገኝ ከሆነ ከሚቀርበው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግር ትጠቀማለህ። ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ ምን እንዳደረጉልን መለስ ብለህ ለማሰብ የሚያስችል ግሩም አጋጣሚም ይሆንልሃል። በተጨማሪም ለአምላክና ለክርስቶስ እንዲሁም ለኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ጥልቅ አክብሮት ካላቸው ሰዎች ጋር መሰብሰብህ ታላቅ በረከት ነው። ይህ በዓል የዘላለም ሕይወት ከሚያስገኘው የአምላክ ጸጋ ተጠቃሚ ለመሆን ያለህን ፍላጎት ያጠናክርልሃል። ምንም ነገር እንቅፋት እንዲሆንብህ አትፍቀድ። የሰማዩ አባታችንን ይሖዋ አምላክን በሚያስከብረውና ደስ በሚያሰኘው በዚህ አስደሳች በዓል ላይ ከመገኘት ወደ ኋላ አትበል።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ሁለት ታላላቅ የፍቅር መግለጫዎች የታዩበት ነው
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ያልቦካው ቂጣና ወይን ጠጁ የኢየሱስን ኃጢአት የሌለበት ሥጋና ደሙን የሚወክሉ ተስማሚ ምሳሌዎች ናቸው