ዘሌዋውያን
23 ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2 “ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘ልታውጇቸው የሚገቡት+ በየወቅቱ የሚከበሩ የይሖዋ በዓላት+ ቅዱስ ጉባኤዎች ናቸው። በየወቅቱ የሚከበሩት የእኔ በዓላት የሚከተሉት ናቸው፦
3 “‘ለስድስት ቀን ሥራ መሥራት ይቻላል፤ ሰባተኛው ቀን ግን ሙሉ በሙሉ የሚታረፍበት ሰንበት+ ይኸውም ቅዱስ ጉባኤ ነው። ምንም ዓይነት ሥራ መሥራት የለባችሁም። በምትኖሩባቸው ቦታዎች ሁሉ ይህ የይሖዋ ሰንበት ነው።+
4 “‘በተወሰነላቸው ጊዜ ላይ ልታውጇቸው የሚገቡት በየወቅቱ የሚከበሩ የይሖዋ በዓላት ማለትም ቅዱስ ጉባኤዎች የሚከተሉት ናቸው፦ 5 በመጀመሪያው ወር ከወሩም በ14ኛው ቀን+ አመሻሹ ላይ* ለይሖዋ ፋሲካ* ይከበራል።+
6 “‘በዚህ ወር 15ኛ ቀን ላይ የቂጣ በዓል ለይሖዋ ይከበራል።+ ለሰባት ቀንም ቂጣ መብላት ይኖርባችኋል።+ 7 በመጀመሪያው ቀን ቅዱስ ጉባኤ ታከብራላችሁ።+ ምንም ዓይነት ከባድ ሥራ መሥራት የለባችሁም። 8 ሆኖም ለሰባት ቀን ያህል ለይሖዋ በእሳት የሚቀርብ መባ ታቀርባላችሁ። በሰባተኛው ቀን ቅዱስ ጉባኤ ይሆናል። ምንም ዓይነት ከባድ ሥራ መሥራት የለባችሁም።’”
9 በመቀጠልም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 10 “ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘እኔ ወደምሰጣችሁ ምድር ገብታችሁ የምድሪቱን አዝመራ በምታጭዱበት ጊዜ ከአዝመራችሁ መጀመሪያ የደረሰውን+ እህል ነዶ ለካህኑ ማምጣት አለባችሁ።+ 11 እሱም ተቀባይነት እንድታገኙ ነዶውን በይሖዋ ፊት ወዲያና ወዲህ ይወዝውዘው። ካህኑ በሰንበት ማግስት ነዶውን ወዲያና ወዲህ ሊወዘውዘው ይገባል። 12 ነዶው ወዲያና ወዲህ እንዲወዘወዝ በምታደርጉበት ቀን አንድ ዓመት ገደማ የሆነው እንከን የሌለበት ጠቦት ለይሖዋ የሚቃጠል መባ አድርጋችሁ ማቅረብ አለባችሁ። 13 ከዚህም ጋር ሁለት አሥረኛ ኢፍ* በዘይት የተለወሰ የላመ ዱቄት የእህል መባ ይኸውም ለይሖዋ በእሳት የሚቀርብ ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ ያለው መባ አድርጋችሁ አቅርቡ። በተጨማሪም አንድ አራተኛ ሂን* የወይን ጠጅ ከዚያ ጋር የመጠጥ መባ አድርጋችሁ አቅርቡ። 14 የአምላካችሁን መባ እስከምታቀርቡበት እስከዚህ ቀን ድረስ ምንም ዓይነት ዳቦም ሆነ ቆሎ ወይም እሸት መብላት የለባችሁም። በምትኖሩበት በየትኛውም ቦታ በትውልዶቻችሁ ሁሉ ይህ ዘላቂ ደንብ ነው።
15 “‘ከሰንበት ማግስት ይኸውም ለሚወዘወዝ መባ የሚሆነውን ነዶ ካመጣችሁበት ቀን ጀምሮ ሰባት ሰንበቶችን ቁጠሩ።+ እነሱም ሙሉ ሳምንታት መሆን አለባቸው። 16 እስከ ሰባተኛው ሰንበት ማግስት ድረስ 50 ቀን+ ቁጠሩ፤ ከዚያም ለይሖዋ አዲስ የእህል መባ አቅርቡ።+ 17 ከምትኖሩባቸው ቦታዎች ሁለት ዳቦዎችን ለሚወዘወዝ መባ ማምጣት ይኖርባችኋል። እነሱም ከሁለት አሥረኛ ኢፍ* የላመ ዱቄት የተዘጋጁ መሆን አለባቸው። ለይሖዋ የሚቀርቡ መጀመሪያ የደረሱ ፍሬዎች+ እንደመሆናቸው መጠን እርሾ ገብቶባቸው+ መጋገር ይኖርባቸዋል። 18 ከዳቦዎቹም ጋር እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸውና እንከን የሌለባቸው ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶች፣ አንድ ወይፈንና ሁለት አውራ በጎች አቅርቡ።+ እነዚህም ከእህል መባቸውና ከመጠጥ መባዎቻቸው ጋር ለይሖዋ የሚቃጠል መባ ማለትም ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ ያለው በእሳት የሚቀርብ መባ ሆነው ይቀርባሉ። 19 እንዲሁም ለኃጢአት መባ እንዲሆን ከፍየሎች መካከል አንድ ግልገል፣+ ለኅብረት መሥዋዕት+ እንዲሆኑ ደግሞ እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸው ሁለት ተባዕት የበግ ጠቦቶችን አቅርቡ። 20 ካህኑም መጀመሪያ ከደረሱ ፍሬዎች ከተዘጋጁት ዳቦዎችና ከሁለቱ ተባዕት ጠቦቶች ጋር በይሖዋ ፊት የሚወዘወዝ መባ አድርጎ ወዲያና ወዲህ ይወዝውዛቸው። እነዚህም ለይሖዋ የተቀደሱ ነገሮች ናቸው፤ የካህኑም ድርሻ ይሆናሉ።+ 21 በዚህ ቀን ለእናንተ ቅዱስ ጉባኤ ታውጃላችሁ።+ ምንም ዓይነት ከባድ ሥራ አትሥሩ። በምትኖሩበት በየትኛውም ቦታ በትውልዶቻችሁ ሁሉ ይህ ዘላቂ ደንብ ነው።
22 “‘የምድራችሁን አዝመራ በምታጭዱበት ጊዜ የእርሻችሁን ዳርና ዳር ሙልጭ አድርጋችሁ አትጨዱት፤ የእርሻችሁን ቃርሚያም አትልቀሙ።+ እነዚህን ለድሃውና*+ ለባዕድ አገሩ ሰው+ ተዉለት። እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።’”
23 ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ 24 “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘በሰባተኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን መለከት በመንፋት የሚታሰብ+ ሙሉ በሙሉ የሚታረፍበት ቅዱስ ጉባኤ ታከብራላችሁ። 25 ምንም ዓይነት ከባድ ሥራ አትሥሩ፤ ለይሖዋ በእሳት የሚቀርብ መባ ታቀርባላችሁ።’”
26 በተጨማሪም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 27 “ሆኖም የዚህ የሰባተኛው ወር አሥረኛ ቀን የስርየት ቀን ነው።+ ቅዱስ ጉባኤ አክብሩ፣ ራሳችሁን አጎሳቁሉ*+ እንዲሁም ለይሖዋ በእሳት የሚቀርብ መባ አቅርቡ። 28 ይህ ቀን በአምላካችሁ በይሖዋ ፊት ለእናንተ ማስተሰረያ+ የሚቀርብበት የስርየት ቀን ስለሆነ በዚህ ቀን ምንም ዓይነት ሥራ መሥራት የለባችሁም። 29 በዚህ ቀን ራሱን የማያጎሳቁል* ማንኛውም ሰው* ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ ይደረጋል።+ 30 በዚህ ቀን ምንም ዓይነት ሥራ የሚሠራን ሰው* ሁሉ ከሕዝቡ መካከል ለይቼ አጠፋዋለሁ። 31 ምንም ዓይነት ሥራ መሥራት የለባችሁም። በምትኖሩበት በየትኛውም ቦታ በትውልዶቻችሁ ሁሉ ይህ ዘላቂ ደንብ ነው። 32 ይህ እናንተ ሙሉ በሙሉ የምታርፉበት ሰንበት ነው፤ በወሩም ዘጠነኛ ቀን ምሽት ላይ ራሳችሁን* ታጎሳቁላላችሁ።+ ሰንበታችሁንም ከዚያ ዕለት ምሽት አንስቶ እስከ ቀጣዩ ቀን ምሽት ድረስ አክብሩ።”
33 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 34 “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘በዚህ በሰባተኛው ወር ከ15ኛው ቀን ጀምሮ ለሰባት ቀን ያህል ለይሖዋ የዳስ* በዓል ይከበራል።+ 35 በመጀመሪያው ቀን ላይ ቅዱስ ጉባኤ ይሆናል፤ እናንተም ምንም ዓይነት ከባድ ሥራ መሥራት የለባችሁም። 36 ለሰባት ቀን ለይሖዋ በእሳት የሚቀርብ መባ ማቅረብ ይኖርባችኋል። በስምንተኛው ቀን ቅዱስ ጉባኤ ታከብራላችሁ፤+ ለይሖዋም በእሳት የሚቀርብ መባ ማቅረብ አለባችሁ። ይህ የተቀደሰ ጉባኤ ነው። ምንም ዓይነት ከባድ ሥራ አትሥሩ።
37 “‘ለይሖዋ በእሳት የሚቀርበውን መባ ማለትም የሚቃጠለውን መባ፣+ ከመሥዋዕቱ ጋር የሚቀርበውን የእህል መባና+ በየዕለቱ እንዲቀርቡ የተመደቡትን የመጠጥ መባዎች+ ለማቅረብ ቅዱስ ጉባኤዎች+ እንደሆኑ አድርጋችሁ የምታውጇቸው በየወቅቱ የሚከበሩት የይሖዋ በዓላት+ እነዚህ ናቸው። 38 እነዚህ ለይሖዋ ልትሰጧቸው ከሚገቡት በይሖዋ ሰንበቶች+ ላይ ከሚቀርቡት፣ ከስጦታዎቻችሁ፣+ ስእለት ለመፈጸም ከምታቀርቧቸው መባዎችና+ ከፈቃደኝነት መባዎቻችሁ+ በተጨማሪ የምታቀርቧቸው ናቸው። 39 ይሁን እንጂ የምድራችሁን ፍሬ በምትሰበስቡበት ጊዜ በሰባተኛው ወር ላይ ከ15ኛው ቀን ጀምሮ የይሖዋን በዓል ለሰባት ቀን ታከብራላችሁ።+ የመጀመሪያው ቀን ሙሉ በሙሉ የሚታረፍበት ሰንበት ይሆናል፤ ስምንተኛውም ቀን ሙሉ በሙሉ የሚታረፍበት ሰንበት ይሆናል።+ 40 በመጀመሪያውም ቀን የተንዠረገጉ ዛፎችን ፍሬ፣ የዘንባባ ዝንጣፊዎችን፣+ የለመለሙ ዛፎችን ቅርንጫፎችና በሸለቆ* የሚበቅሉ የአኻያ ዛፎችን ውሰዱ፤ በአምላካችሁም በይሖዋ ፊት ለሰባት ቀን+ ተደሰቱ።+ 41 ይህን በዓል በየዓመቱ ለሰባት ቀን ለይሖዋ የሚከበር በዓል አድርጋችሁ ታከብሩታላችሁ።+ በትውልዶቻችሁም ሁሉ ዘላቂ ደንብ አድርጋችሁ በሰባተኛው ወር አክብሩት። 42 ለሰባት ቀን በዳስ ውስጥ ተቀመጡ።+ በእስራኤል የሚኖሩ የአገሩ ተወላጆች በሙሉ በዳስ ውስጥ ይቀመጡ፤ 43 ይህን የሚያደርጉት እስራኤላውያንን ከግብፅ ምድር ባወጣኋቸው ጊዜ በዳስ ውስጥ እንዲቀመጡ እንዳደረግኩ መጪዎቹ ትውልዶቻችሁ እንዲያውቁ+ ነው።+ እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።’”
44 ስለዚህ ሙሴ በየወቅቱ የሚከበሩትን የይሖዋን በዓላት ለእስራኤላውያን አስታወቀ።