የፍቅር መንገድ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል
“የሚበልጠውን የጸጋ ስጦታ በብርቱ ፈልጉ። ደግሞም ከሁሉ የሚበልጥ መንገድ አሳያችኋለሁ።”—1 ቆሮንቶስ 12:31
1-3. (ሀ) ፍቅር ማሳየትን መማር አዲስ ቋንቋ ከመማር ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? (ለ) ፍቅር ማሳየትን መማር ፈታኝ የሚያደርጉት ነገሮች ምንድን ናቸው?
አንድ አዲስ ቋንቋ ለመማር ሞክረህ ታውቃለህ? አስቸጋሪ መሆኑ አሌ አይባልም! እርግጥ አንድ ትንሽ ልጅ በቋንቋው ከሚጠቀሙ ሰዎች ጋር አብሮ በመኖር ብቻ አንድን ቋንቋ መማር ይችላል። አንጎሉ የቃላቱን ድምፆችና ትርጉማቸውን ቀስ በቀስ እየቀሰመ ብዙም ሳይቆይ ራሱን በሚገባ፣ ምናልባትም በተቀላጠፈ መንገድ የመግለጽ ችሎታ ያዳብራል። ለአዋቂዎች ግን ሁኔታው የተለየ ነው። የአንድን ባዕድ ቋንቋ መሠረታዊ የሆኑ ጥቂት ሐረጎች ለማወቅ ስንል ብቻ እንኳ ቋንቋውን የሚፈታ መዝገበ ቃላት በተደጋጋሚ እንመለከታለን። በቂ ልምምድ ካደረግን በኋላ በአዲሱ ቋንቋ ማሰብ እንጀምራለን፤ ቋንቋውን መናገሩም ቀላል ይሆንልናል።
2 ለሌሎች ፍቅር ማሳየትን መማር አንድን አዲስ ቋንቋ ከመማር ጋር በእጅጉ ይመሳሰላል። እርግጥ ሰዎች በተፈጥሯቸው ይህ መለኮታዊ ባሕርይ በተወሰነ መጠን አላቸው። (ዘፍጥረት 1:27፤ ከ1 ዮሐንስ 4:8 ጋር አወዳድር።) ይሁንና፣ በተለይ ተፈጥሯዊ ፍቅር በተመናመነበት በዚህ ዘመን ፍቅር ማሳየትን መማር ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) አንዳንድ ጊዜ ይህ ሁኔታ በቤተሰብ መካከል ይከሰታል። አዎን፣ ብዙዎች የሚያድጉት ፍቅራዊ ቃላት እምብዛም ወይም ጭራሽ በማይሰሙበትና ሸካራ ንግግር በነገሠበት ቤተሰብ ውስጥ ነው። (ኤፌሶን 4:29-31፤ 6:4) እኛ ራሳችን በሕይወታችን ውስጥ ፍቅርን ለማጣጣም እምብዛም አጋጣሚ ያላገኘን ብንሆንም እንኳ ለሌሎች ፍቅር ማሳየትን መማር የምንችለው እንዴት ነው?
3 በዚህ ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ ሊረዳን ይችላል። ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 13:4-8 ላይ የፍቅርን ጥሬ ፍቺ ሳይሆን ይህ የላቀ የፍቅር ዓይነት ተግባራዊ ስለሚሆንበት መንገድ ዝርዝር መግለጫ ሰጥቷል። እነዚህን ጥቅሶች መመርመራችን የዚህን መለኮታዊ ባሕርይ ምንነት በደንብ ለማስተዋልና ለሌሎች ለማሳየት በሚገባ የታጠቅን እንድንሆን ይረዳናል። ጳውሎስ የዘረዘራቸውን አንዳንድ የፍቅር ገጽታዎች እስቲ እንመልከት። እነዚህን የፍቅር ገጽታዎች በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ልንመድባቸው እንችላለን:- አኗኗራችንን በአጠቃላይ፣ ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነት በዝርዝር፣ በመጨረሻም ጽናታችንን የሚመለከቱ ናቸው።
ፍቅር ኩራትን እንድናሸንፍ ይረዳናል
4. መጽሐፍ ቅዱስ ቅናትን በተመለከተ ምን ማስተዋል ይሰጠናል?
4 ጳውሎስ ፍቅርን በተመለከተ የመግቢያ ሐሳብ ካቀረበ በኋላ “ፍቅር አይቀናም” ሲል ለቆሮንቶስ ሰዎች ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 13:4) ቅናት ሌሎች ባገኙት ብልጽግና ወይም ስኬት ቅር በመሰኘት ሊገለጽ ይችላል። ይህ ዓይነቱ ቅናት አካልን፣ ስሜትንና መንፈስን ይጎዳል።—ምሳሌ 14:30፤ ሮሜ 13:13፤ ያዕቆብ 3:14-16
5. በአንዳንድ ቲኦክራሲያዊ መብቶች ረገድ ቸል እንደተባልን ሆኖ ሲሰማን የሚያድርብንን የቅናት ስሜት ለማሸነፍ ፍቅር እንዴት ሊረዳን ይችላል?
5 ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ:- ‘በአንዳንድ ቲኦክራሲያዊ መብቶች ረገድ ቸል እንደተባልኩ ሆኖ ሲሰማኝ ቅናት ያድርብኛልን?’ መልስህ አዎን፣ ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ያዕቆብ ‘የቅናት ዝንባሌ’ ፍጽምና በሌላቸው ሰዎች ሁሉ ውስጥ ያለ ነገር መሆኑን እንድናስታውስ ያደርገናል። (ያዕቆብ 4:5) ለወንድምህ ያለህ ፍቅር ሚዛንህን እንድትጠብቅ ሊረዳህ ይችላል። አንድ ሰው በረከት በሚያገኝበት ወይም በሚመሰገንበት ጊዜ አንተ እንድትቀየም ሆን ተብሎ የተደረገ ነገር እንደሆነ አድርገህ ከመመልከት ይልቅ ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ እንዲልህ ፍቅር ሊረዳህ ይችላል።—ከ1 ሳሙኤል 18:7-9 ጋር አወዳድር።
6. በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበረው የቆሮንቶስ ጉባኤ ውስጥ ምን አስቸጋሪ ሁኔታ ተከስቶ ነበር?
6 ጳውሎስ ፍቅር “አይመካም፣ አይታበይም” በማለት አክሎ ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 13:4) አንድ ዓይነት ተሰጥዎ ወይም ችሎታ ካለን በሌሎች ዘንድ ጉራ መንዛት የለብንም። ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው ወደ ጥንቱ የቆሮንቶስ ጉባኤ ሾልከው የገቡ አንዳንድ ትዕቢተኛ ሰዎች እንዲህ ያለ ችግር ነበራቸው። ምናልባት ሐሳቦችን የማብራራት ወይም ነገሮችን በጥሩ ሁኔታ የማከናወን የላቀ ችሎታ ይኖራቸው ይሆናል። በጉባኤው መካከል መከፋፈል እንዲኖር አስተዋጽኦ ያደረገው የሌሎችን ትኩረት ወደ ራሳቸው ለመሳብ ያደረጉት ጥረት ሳይሆን አይቀርም። (1 ቆሮንቶስ 3:3, 4፤ 2 ቆሮንቶስ 12:20) ይህ ጉዳይ አደገኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ስለነበር ‘ዋነኞቹ ሐዋርያት’ በማለት የተቻቸውን ‘ሞኞች በመታገሣቸው’ ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን መውቀስ ግድ ሆኖበታል።—2 ቆሮንቶስ 11:5, 19, 20
7, 8. ያለንን ተሰጥዎ አንድነትን ለማጎልበት እንዴት ልንጠቀምበት እንደምንችል ከመጽሐፍ ቅዱስ አስረዳ።
7 ዛሬም ተመሳሳይ ሁኔታ ሊከሰት ይችላል። ለምሳሌ አንዳንዶች በአገልግሎት ስላገኙት ስኬት ወይም በአምላክ ድርጅት ውስጥ ስላሏቸው መብቶች በጉራ የመናገር አዝማሚያ ሊታይባቸው ይችላል። በጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ሰዎች የሌላቸው የተለየ ተሰጥኦ ወይም ችሎታ ቢኖረን እንኳ ትዕቢት እንዲያድርብን ምክንያት ይሆነናልን? ከዚህ ይልቅ ያለንን ማንኛውንም ዓይነት ተፈጥሯዊ ችሎታ ራሳችንን ከፍ ከፍ ለማድረግ ሳይሆን አንድነትን ለማጎልበት ልንጠቀምበት ይገባል።—ማቴዎስ 23:12፤ 1 ጴጥሮስ 5:6
8 ጳውሎስ አንድ ጉባኤ ብዙ ብልቶች ቢኖሩትም ‘አካሉን ያገጣጠመው አምላክ’ እንደሆነ ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 12:19-26) “አገጣጠመ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ቀለም በሚቀላቀልበት ጊዜ እንደሚዋሃደው እርስ በርስ ስምም ሆኖ መዋሃድን ያመለክታል። ስለዚህ በጉባኤው ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም ሰው ስለ ችሎታዎቹ ጉራውን መንዛትና ሌሎችን ለመጫን መሞከር የለበትም። ኩራትና የሥልጣን ጥማት በአምላክ ድርጅት ውስጥ ቦታ የላቸውም።—ምሳሌ 16:19፤ 1 ቆሮንቶስ 14:12፤ 1 ጴጥሮስ 5:2, 3
9. መጽሐፍ ቅዱስ የራሳቸውን ፍላጎት ለማሟላት ይጥሩ ስለነበሩ ግለሰቦች የሚገልጹ ምን የማስጠንቀቂያ ምሳሌዎች ይዟል?
9 ፍቅር “የራሱን ጥቅም ብቻ ፈላጊ አይደለም።” (1 ቆሮንቶስ 13:5 የ1980 ትርጉም) አፍቃሪ የሆነ ሰው የራሱን ጥቅም ለማስፈጸም ሲል ሌሎችን በተንኮል ለማግባባት አይሞክርም። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ የሚናገሩ የማስጠንቀቂያ ምሳሌዎችን ይዟል። በምሳሌ ለማስረዳት:- የራስ ወዳድነት ፍላጎታቸውን ለማሟላት ሲሉ ሌሎችን በተንኮል ለማግባባት ስለ ሞከሩ እንደ ደሊላ፣ ኤልዛቤልና ጎቶልያ ስላሉ ሴቶች እናነባለን። (መሳፍንት 16:16፤ 1 ነገሥት 20:25፤ 2 ዜና መዋዕል 22:10-12) የንጉሥ ዳዊት ልጅ የሆነው አቤሴሎምም አለ። ወደ ኢየሩሳሌም ለፍርድ የሚመጡትን ሰዎች ቀርቦ በማነጋገር የንጉሡ ፍርድ ቤት ለችግሮቻቸው ተገቢውን ትኩረት እንደማይሰጥ በለሰለሰ አንደበት ይነግራቸው ነበር። ከዚያም ፍርድ ቤቱ እንደ እሱ ያለ ከልብ የሚያስብ ሰው እንደሚያስፈልገው ፊት ለፊት ይናገር ነበር! (2 ሳሙኤል 15:2-4) አቤሴሎም በእርግጥ ለተገፉት ሰዎች አዝኖ ሳይሆን የራሱን ፍላጎት ለማሟላት ነበር። ራሱን በራሱ ንጉሥ አድርጎ በመሾም የብዙዎችን ልብ አሸፈተ። ሆኖም ከጊዜ በኋላ አቤሴሎም አሳዛኝ ሽንፈት ገጥሞታል። በሚሞትበት ጊዜ ተገቢ የሆነ የቀብር ሥነ ሥርዓት እንኳ አልተከናወነለትም።—2 ሳሙኤል 18:6-17
10. የሌሎች ሰዎችን ፍላጎት ግምት ውስጥ እንደምናስገባ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
10 ይህ በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ ክርስቲያኖች ማስጠንቀቂያ ነው። ወንዶችም ሆንን ሴቶች ሌሎችን አግባብቶ የማሳመን ተፈጥሯዊ ችሎታ ሊኖረን ይችላል። በአንድ ውይይት ላይ የበላይነቱን በመያዝ ወይም የተለየ አመለካከት ያላቸውን ሰዎች በመጫን ነገሮች እኛ ወደፈለግነው አቅጣጫ እንዲያመሩ የማድረግ ችሎታ ሊኖረን ይችላል። ይሁን እንጂ በእርግጥ ፍቅር ካለን የሌሎች ሰዎችን ፍላጎትም ግምት ውስጥ እናስገባለን። (ፊልጵስዩስ 2:2-4) ተሰሚነት ያላቸው እኛ የምንሰጣቸው አመለካከቶች ብቻ የሆኑ ይመስል በአምላክ ድርጅት ውስጥ ባካበትነው ተሞክሮ ወይም ባለን የኃላፊነት ቦታ አማካኝነት ሌሎችን መጠቀሚያ አናደርግም ወይም አጠያያቂ የሆኑ አስተሳሰቦችን አናስፋፋም። ከዚህ ይልቅ “ትዕቢት ጥፋትን፣ ኩሩ መንፈስም ውድቀትን ይቀድማል” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ እናስታውሳለን።—ምሳሌ 16:18
ፍቅር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖር ያደርጋል
11. (ሀ) በደግነት ላይ የተመሠረተና ተገቢ የሆነ ፍቅር ማሳየት የምንችለው በምን መንገዶች ነው? (ለ) ክፉ በሆነ ነገር እንደማንደሰት እንዴት ልናሳይ እንችላለን?
11 በተጨማሪም ጳውሎስ ፍቅር “ደግ” እንደሆነና “ሥርዓተ ቢስ” እንዳልሆነ ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 13:4, 5 የ1980 ትርጉም) አዎን፣ ፍቅር ስድ፣ ባለጌ ወይም ግብረገብነት የጎደለን እንድንሆን አይፈቅድልንም። ከዚህ ይልቅ ስለ ሌሎች ስሜት እናስባለን። ለምሳሌ ያህል አፍቃሪ የሆነ ሰው የሌሎችን ሕሊና የሚረብሹ ነገሮችን ከማድረግ ይቆጠባል። (ከ1 ቆሮንቶስ 8:13 ጋር አወዳድር።) ፍቅር “ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ስለ ዓመፃ ደስ አይለውም።” (1 ቆሮንቶስ 13:6) የይሖዋን ሕግ የምንወድ ከሆነ የብልግና ድርጊቶችን በግዴለሽነት አንመለከትም ወይም አምላክ በሚጠላቸው ነገሮች አንዝናናም። (መዝሙር 119:97) ፍቅር በሚያፈርሱ ሳይሆን በሚያንጹ ነገሮች እንድንደሰት ይረዳናል።—ሮሜ 15:2፤ 1 ቆሮንቶስ 10:23, 24፤ 14:26
12, 13. (ሀ) አንድ ሰው በሚያስቀይመን ጊዜ ምላሽ መስጠት ያለብን እንዴት ሊሆን ይገባል? (ለ) የተቆጣነው በበቂ ምክንያት ቢሆንም እንኳ ጥበብ የጎደለው እርምጃ እንድንወስድ ሊያደርገን እንደሚችል የሚያሳዩ ምሳሌዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቀስ።
12 ጳውሎስ ፍቅር “አይበሳጭም” (“አትንኩኝ ባይ አይደለም፣” ፊሊፕስ) ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 13:5) ፍጹማን ስላልሆንን አንድ ሰው ሲያስቀይመን መበሳጨታችን ወይም መቆጣታችን የሚጠበቅ ነገር ነው። ይሁን እንጂ ለረዥም ጊዜ ቅሬታን አምቆ መያዝ ወይም ተቆጥቶ መቆየት ስህተት ነው። (መዝሙር 4:4፤ ኤፌሶን 4:26) የምንቆጣበት በቂ ምክንያት ቢኖርም እንኳ ይህን የመሰለውን ቁጣ ካልተቆጣጠርነው በይሖዋ ፊት ሊያስጠይቀን የሚችል ጥበብ የጎደለው እርምጃ እንድንወስድ ያደርገን ይሆናል።—ዘፍጥረት 34:1-31፤ 49:5-7፤ ዘኁልቁ 12:3፤ 20:10-12፤ መዝሙር 106:32, 33
13 አንዳንዶች የሌሎች አለፍጽምና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ እንዳይገኙ ወይም በመስክ አገልግሎት እንዳይካፈሉ እንቅፋት እንዲሆንባቸው ፈቅደዋል። ከእነዚህ ውስጥ ብዙዎቹ ከዚህ ቀደም የቤተሰብ ተቃውሞን፣ የሥራ ባልደረቦቻቸውን ማንጓጠጥና ሌሎች ፈተናዎችን በጽናት በመቋቋም ለእምነታቸው በብርቱ የተጋደሉ ሰዎች ነበሩ። እነዚህን እንቅፋቶች በጽናት የተቋቋሟቸው በንጹህ አቋማቸው ላይ እንደተቃጡ ፈተናዎች አድርገው ስለተመለከቷቸው ነበር፤ ደግሞም ናቸው። ሆኖም አንድ መሰል ክርስቲያን ፍቅር የጎደለው ነገር ቢናገር ወይም ቢያደርግስ? ይህስ ቢሆን በንጹህ አቋም ላይ የመጣ ፈተና ሊሆን አይችልምን? በእርግጥ ነው፤ ምክንያቱም እንደ ተቆጣን ከቆየን ‘ለዲያብሎስ ስፍራ ልንሰጥ’ እንችላለን።—ኤፌሶን 4:27
14, 15. (ሀ) ‘በደልን መቁጠር’ ማለት ምን ማለት ነው? (ለ) ይቅር ባዮች በመሆን ረገድ ይሖዋን ልንመስለው የምንችለው እንዴት ነው?
14 ጳውሎስ፣ ፍቅር “በደልን አይቈጥርም” ብሎ መናገሩ አለምክንያት አልነበረም። (1 ቆሮንቶስ 13:5) እዚህ ላይ ጳውሎስ መቁጠር የሚል ከሒሳብ ጋር የተያያዘ ቃል መጠቀሙ የተሠራው በደል እንዳይረሳ በቋሚ የሒሳብ መዝገብ ላይ ማስፈርን ለማመልከት ነው። የተሠራውን በደል መጥቀስ የሚያስፈልግበት ጊዜ ይመጣ ይመስል ጎጂ የሆነን ቃል ወይም ድርጊት በአእምሮ መዝግቦ መያዙ ፍቅራዊ ነውን? ይሖዋ ይህን በመሰለ ምሕረት የለሽ መንገድ አንድ በአንድ ስለማይመረምረን ምንኛ አመስጋኞች መሆን እንችላለን! (መዝሙር 130:3) አዎን፣ ንስሐ ከገባን የሠራነውን ስህተት ሁሉ ይደመስስልናል።—ሥራ 3:19
15 በዚህ ረገድ ይሖዋን ልንመስለው እንችላለን። አንድ ሰው ትንሽ ቅር የሚያሰኝ ነገር ያደረገብን በመሰለን ቁጥር እንዲያው ለምን ተነካሁ ባዮች መሆን የለብንም። በቀላሉ የምንቀየም ከሆነ ያስቀየመን ሰው ሊያደርስብን ከሚችለው ጉዳት የበለጠ ራሳችንን ልንጎዳ እንችላለን። (መክብብ 7:9, 22) ከዚህ ይልቅ ፍቅር ‘ሁሉን እንደሚያምን’ ማስታወስ ያስፈልገናል። (1 ቆሮንቶስ 13:7) ማናችንም ብንሆን የተነገረንን ሁሉ ማመን አለብን ማለት ባይሆንም የወንድሞቻችንን ሐሳብ ከልክ በላይ የምንጠራጠር መሆን ደግሞ አይገባንም። በተቻለ መጠን አንዳችን ስለ ሌላው አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝ እንጣር።—ቆላስይስ 3:13
ፍቅር እንድንጸና ይረዳናል
16. ፍቅር ታጋሾች እንድንሆን ሊረዳን የሚችለው በየትኞቹ ሁኔታዎች ሥር ነው?
16 ጳውሎስ በመቀጠል “ፍቅር ይታገሣል” ይለናል። (1 ቆሮንቶስ 13:4) አስቸጋሪ የሆኑ ሁኔታዎችን ምናልባትም ለረዥም ጊዜ ችለን እንድንጸና ሊያደርገን ይችላል። ለምሳሌ ያህል ብዙ ክርስቲያኖች በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ ለዓመታት ኖረዋል። ሌሎች ደግሞ “በጌታ” የሆነ ተስማሚ የትዳር ጓደኛ ባለማግኘታቸው ሳይወዱ ነጠላ ሆነዋል። (1 ቆሮንቶስ 7:39፤ 2 ቆሮንቶስ 6:14) ሌሎቹ ደግሞ ከማይድን በሽታ ጋር እየታገሉ ለመኖር ይገደዳሉ። (ገላትያ 4:13, 14፤ ፊልጵስዩስ 2:25-30) በዚህ ፍጽምና በጎደለው ዓለም ውስጥ በዚህም ሆነ በዚያ ጽናት የማይጠይቅ ሕይወት የሚመራ ሰው እንደሌለ የተረጋገጠ ነው።—ማቴዎስ 10:22፤ ያዕቆብ 1:12
17. በሁሉ ለመጽናት የሚረዳን ምንድን ነው?
17 ጳውሎስ ፍቅር “ሁሉን ይታገሣል፣ . . . ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፣ በሁሉ ይጸናል” የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል። (1 ቆሮንቶስ 13:7) ለይሖዋ ያለን ፍቅር ለጽድቅ ስንል ማንኛውንም ዓይነት ሁኔታ ታግሠን ለማሳለፍ ያስችለናል። (ማቴዎስ 16:24፤ 1 ቆሮንቶስ 10:13) ሰማዕት የመሆን ፍላጎት የለንም። ዓላማችን ሰላማዊና የተረጋጋ ሕይወት መምራት ነው። (ሮሜ 12:18፤ 1 ተሰሎንቄ 4:11, 12) ያም ሆኖ ግን የእምነት ፈተናዎች ሲያጋጥሙን ክርስቲያናዊ ደቀ መዝሙርነት የሚጠይቀው ዋጋ ክፍል መሆናቸውን ተረድተን በደስታ እንጸናለን። (ሉቃስ 14:28-33) በምንጸናበት ጊዜ ፈታኝ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ የተሻለ ነገር እንደሚመጣ ተስፋ በማድረግ አዎንታዊ አመለካከታችንን ጠብቀን ለማቆየት ጥረት እናደርጋለን።
18. በችግር ጊዜ ብቻ ሳይሆን በደህናም ጊዜ ጽናት አስፈላጊ የሆነው እንዴት ነው?
18 ጽናት አስፈላጊ የሚሆነው በመከራ ጊዜ ብቻ አይደለም። አንዳንድ ጊዜ ጽናት ማለት ፈታኝ ሁኔታዎች ኖሩም አልኖሩ በአንድ በተወሰነ መንገድ ላይ መመላለስን መቀጠል ማለት ነው። ጽናት አንድን ጥሩ የሆነ መንፈሳዊ ልማድ እንደያዙ መቀጠልንም ይጨምራል። ለምሳሌ ያህል ከሁኔታህ ጋር በሚስማማ መንገድ በአገልግሎቱ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እያደረግህ ነውን? የአምላክን ቃል አንብበህ ታሰላስልበታለህ? ከሰማያዊው አባትህስ ጋር በጸሎት ትገናኛለህ? በጉባኤ ስብሰባዎች አዘውትረህ ትገኛለህ? ከመሰል አማኞች ጋር ማበረታቻ ትለዋወጣለህ? እንዲያ ከሆነ አሁን ያለህበት ሁኔታ ጥሩም ይሁን አስቸጋሪ እየጸናህ ነው ማለት ነው። “ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና” ተስፋ አትቁረጥ።—ገላትያ 6:9
ፍቅር—“ከሁሉ የሚበልጥ መንገድ”
19. ፍቅር “ከሁሉ የሚበልጥ መንገድ” የሆነው እንዴት ነው?
19 ጳውሎስ ይህን መለኮታዊ ባሕርይ “ከሁሉ የሚበልጥ መንገድ” ብሎ በመጥራት ፍቅር የማሳየትን አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥቶታል። (1 ቆሮንቶስ 12:31) ፍቅር “የሚበልጥ” የሆነው በምን መንገድ ነው? ጳውሎስ ቀደም ብሎ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ዘንድ የተለመዱ የነበሩትን የመንፈስ ስጦታዎች ዘርዝሮ ነበር። አንዳንዶች ትንቢት የመናገር፣ ሌሎች የመፈወስ፣ ብዙዎች ደግሞ በልሳን የመናገር ችሎታ ተሰጥቷቸው ነበር። እነዚህ በእርግጥም ድንቅ ስጦታዎች ናቸው! ቢሆንም ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች እንዲህ ብሏቸዋል:- “በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጸናጽል ሆኜአለሁ። ትንቢትም ቢኖረኝ፣ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፣ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ።” (1 ቆሮንቶስ 13:1, 2) አዎን፣ ጠቃሚ የሆኑ ተግባራት ብናደርግ እንኳ ለአምላክና ለጎረቤት ባለን ፍቅር ተገፋፍተን ካልሆነ ‘የሞቱ ሥራዎች’ ይሆናሉ።—ዕብራውያን 6:1
20. ፍቅርን መኮትኮት ከፈለግን ቀጣይ የሆነ ጥረት ማድረግ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
20 ኢየሱስ መለኮታዊ ባሕርይ የሆነውን ፍቅርን የምንኮተኩትበትን ሌላ ምክንያት ገልጾልናል። “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” ብሏል። (ዮሐንስ 13:35) “ቢኖራችሁ” የሚለው ቃል ለሌሎች ፍቅር ማሳየትን መማር ለእያንዳንዱ ክርስቲያን የተተወ መሆኑን ያሳያል። በአንድ ባዕድ አገር ውስጥ መኖር ብቻውን ቋንቋውን መናገርን እንድንማር ሊያስገድደን አይችልም። በመንግሥት አዳራሽ በሚካሄዱ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ወይም ከመሰል ክርስቲያኖች ጋር አብሮ መሆን ብቻውን ፍቅርን ማሳየትን ያስተምረናል ማለት አይደለም። ይህን “ቋንቋ” መማር ቀጣይ የሆነ ጥረት የሚጠይቅ ነው።
21, 22. (ሀ) ጳውሎስ ካብራራቸው የፍቅር ገጽታዎች መካከል አንዳንዶቹን የማናሟላ ብንሆን እንዴት ሊሰማን ይገባል? (ለ) “ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም” ሊባል የሚችለው በምን መንገድ ነው?
21 አልፎ አልፎ ጳውሎስ የገለጻቸውን አንዳንድ የፍቅር ገጽታዎች አታሟላ ይሆናል። ሆኖም ተስፋ አትቁረጥ። በትዕግሥት ጥረት ማድረግህን ቀጥል። መጽሐፍ ቅዱስን መመርመርህንና በውስጡ ያሉትን መሠረታዊ ሥርዓቶች ከሌሎች ጋር ባለህ ግንኙነት ተግባራዊ ማድረግህን ቀጥል። ይሖዋ የተወልንን ምሳሌ በፍጹም አትዘንጋ። ጳውሎስ የኤፌሶን ሰዎችን “እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፣ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ” በማለት አጥብቆ መክሯቸዋል።—ኤፌሶን 4:32
22 ራስህን በአዲስ ቋንቋ መግለጹ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀለለህ እንደሚመጣ ሁሉ ለሌሎች ፍቅር ማሳየትም ከጊዜ ወደ ጊዜ ቀላል እየሆነልህ ይመጣል። ጳውሎስ “ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (1 ቆሮንቶስ 13:8) ተአምራዊ ከሆኑ የመንፈስ ስጦታዎች በተቃራኒ ፍቅር ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል። ስለዚህ ይህን መለኮታዊ ባሕርይ ማሳየት መማራችሁን ቀጥሉ። ጳውሎስ እንዳለው ፍቅር “ከሁሉ የሚበልጥ መንገድ” ነው።
[ልታብራራ ትችላለህ?]
◻ ፍቅር ኩራትን እንድናሸንፍ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?
◻ ፍቅር በጉባኤ ውስጥ ሰላም እንዲጎለብት ለማድረግ ሊረዳን የሚችለው በምን መንገዶች ነው?
◻ ፍቅር እንድንጸና ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?
◻ ፍቅር “ከሁሉ የሚበልጥ መንገድ” የሆነው እንዴት ነው?
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፍቅር የእምነት ባልንጀሮቻችንን ጉድለቶች ችላ ብለን እንድናልፍ ይረዳናል
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጽናት ቲኦክራሲያዊ ልማዳችንን ጠብቆ መቆየትንም ይጨምራል