“ሙታን ይነሣሉ”
“መለከት ይነፋልና ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ እኛም እንለወጣለን።”—1 ቆሮንቶስ 15:52
1, 2. (ሀ) በነቢዩ ሆሴዕ በኩል ምን የሚያጽናና ተስፋ ተሰጥቷል? (ለ) አምላክ ሙታንን ዳግመኛ ሕያው ለማድረግ ፈቃደኛ መሆኑን እንዴት እናውቃለን?
የምትወደውን ሰው በሞት ተነጥቀህ ታውቃለህ? እንግዲያው ሞት የሚያስከትለውን ሐዘን በሚገባ ታውቀዋለህ ማለት ነው። ሆኖም ክርስቲያኖች አምላክ በነቢዩ ሆሴዕ አማካኝነት በሰጠው ተስፋ ይጽናናሉ:- “ከሲኦል እጅ እታደጋቸዋለሁ፣ ከሞትም እቤዣቸዋለሁ፤ ሞት ሆይ፣ ቸነፈርህ ወዴት አለ? ሲኦል ሆይ፣ ማጥፋትህ ወዴት አለ?”—ሆሴዕ 13:14
2 ሙታን ወደ ሕይወት ይመለሳሉ የሚለው አስተሳሰብ ተጠራጣሪ ለሆኑ ሰዎች የማይመስል ነገር ሆኖ ይታያቸዋል። ይሁን እንጂ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ እንዲህ ያለውን ተዓምር የመፈጸም ኃይል እንዳለው ምንም አያጠራጥርም! አጠያያቂው ጉዳይ ይሖዋ ሙታንን ወደ ሕይወት መልሶ ለማምጣት ፈቃደኛ ነው ወይስ አይደለም የሚለው ነው። ጻድቁ ሰው ኢዮብ “በውኑ ሰው ከሞተ ተመልሶ ሕያው ይሆናልን?” ሲል ጠይቋል። ከዚያም የሚከተለውን የሚያጽናና መልስ ሰጥቷል:- “በጠራኸኝና በመለስሁልህ ነበር፤ የእጅህንም ሥራ በተመኘኸው ነበር።” (ኢዮብ 14:14, 15) “በተመኘኸው” የሚለው ቃል ጥልቅ ፍላጎትን ወይም ጉጉትን ያመለክታል። (ከመዝሙር 84:2 ጋር አወዳድር።) አዎን፣ ይሖዋ ትንሣኤን በጉጉት ይጠባበቃል፤ ታማኝነታቸውን ጠብቀው ያለፉ ሰዎችን እንደገና ለማየት ይናፍቃል። እነዚህ ሰዎች በእሱ ፊት ሕያው ናቸው።—ማቴዎስ 22:31, 32
ኢየሱስ በትንሣኤ ተስፋ ላይ የእውቀት ብርሃን ፈንጥቋል
3, 4. (ሀ) ኢየሱስ በትንሣኤ ተስፋ ላይ ምን ብርሃን ፈንጥቋል? (ለ) ኢየሱስ በሥጋ ሳይሆን በመንፈስ የተነሣው ለምንድን ነው?
3 እንደ ኢዮብ ያሉት የጥንት የእምነት ሰዎች ስለ ትንሣኤ የነበራቸው እውቀት ምሉዕ አልነበረም። በዚህ አስደናቂ ተስፋ ላይ ሙሉ የእውቀት ብርሃን የፈነጠቀው ኢየሱስ ክርስቶስ ነበር። “በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው” ብሎ በተናገረ ጊዜ ራሱ የሚጫወተውን ቁልፍ ሚና አሳይቷል። (ዮሐንስ 3:36) ይህ ሕይወት የሚገኘው የት ነው? አብዛኞቹ እምነት ያላቸው ሰዎች ይህን ሕይወት የሚያገኙት በምድር ላይ ይሆናል። (መዝሙር 37:11) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “አንተ ታናሽ መንጋ፣ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ በጎ ፈቃድ ነውና አትፍሩ” ብሏቸው ነበር። (ሉቃስ 12:32) የአምላክ መንግሥት የሚገኘው በሰማይ ነው። በመሆኑም በዚህ ተስፋ መሠረት አንድ “ታናሽ መንጋ” መንፈሳዊ አካል ለብሶ በሰማይ ከኢየሱስ ጋር ይሆናል ማለት ነው። (ዮሐንስ 14:2, 3፤ 1 ጴጥሮስ 1:3, 4) እንዴት ያለ ክብራማ ተስፋ ነው! ከዚህም በላይ ኢየሱስ የዚህ “ታናሽ መንጋ” ቁጥር 144,000 ብቻ እንደሚሆን ለሐዋርያው ዮሐንስ ገልጦለት ነበር።—ራእይ 14:1
4 ይሁንና 144,000ዎቹ ይህን ሰማያዊ ክብር የሚያገኙት እንዴት ነው? ኢየሱስ “በወንጌል ሕይወትንና አለመጥፋትን ወደ ብርሃን አውጥቶአል።” በደሙ አማካኝነት ወደ ሰማይ የሚያደርስ ‘አዲስና ሕያው መንገድ’ ከፍቷል። (2 ጢሞቴዎስ 1:10፤ ዕብራውያን 10:19, 20) መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ በተናገረው መሠረት በመጀመሪያ ሞተ። (ኢሳይያስ 53:12) ከዚያም ሐዋርያው ጴጥሮስ ከጊዜ በኋላ እንደተናገረው “ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው።” (ሥራ 2:32) ይሁንና ኢየሱስ ሰው ሆኖ አልተነሣም። “እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 6:51) ሥጋውን መልሶ መውሰዱ ይህን መሥዋዕት መና ያስቀረዋል። ስለዚህ ኢየሱስ “በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ።” (1 ጴጥሮስ 3:18) ኢየሱስ “ለታናሹ መንጋ” “የዘላለም ደኅንነትን” ያስገኘው በዚህ መንገድ ነው። (ዕብራውያን 9:12 የ1980 ትርጉም) ለኃጢአተኛው የሰው ዘር ቤዛ እንዲሆን የፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን ዋጋ ለአምላክ ያቀረበ ሲሆን የዚህ ዝግጅት የመጀመሪያዎቹ ተጠቃሚዎች 144,000ዎቹ ናቸው።
5. በመጀመሪያ መቶ ዘመን ለነበሩ የኢየሱስ ተከታዮች ምን ተስፋ ተዘርግቶላቸው ነበር?
5 በትንሣኤ አማካኝነት ሰማያዊ ሕይወት የሚያገኘው ኢየሱስ ብቻ አይደለም። ጳውሎስ በሮም የሚገኙ መሰል ክርስቲያኖች የአምላክ ልጆችና ከክርስቶስ ጋር ተባባሪ ገዥዎች እንዲሆኑ በመንፈስ ቅዱስ እንደተቀቡ ነግሯቸዋል። ይህን ለማግኘት ግን እስከ መጨረሻው በመጽናት ቅቡዕነታቸውን ማረጋገጥ አለባቸው። (ሮሜ 8:16, 17) በተጨማሪም ጳውሎስ “ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን” በማለት ተናግሯል።—ሮሜ 6:5
ለትንሣኤ ተስፋ ጥብቅና መቆም
6. የቆሮንቶስ ሰዎች በትንሣኤ እምነት ላይ ትችት የሰነዘሩት ለምን ነበር? ሐዋርያው ጳውሎስስ ምን ምላሽ ሰጠ?
6 ትንሣኤ የክርስትና ‘የመጀመሪያ መሠረተ ትምህርት’ አንዱ ክፍል ነው። (ዕብራውያን 6:1, 2) ሆኖም ይህ መሠረተ ትምህርት በቆሮንቶስ ውስጥ ትችት ተሰንዝሮበት ነበር። ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው የግሪክ ፍልስፍና ባሳደረባቸው ተጽእኖ ምክንያት በጉባኤ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ሰዎች “ትንሣኤ ሙታን የለም” ይሉ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 15:12) ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ጉዳዩ ሲሰማ ለትንሣኤ ተስፋ በተለይም ለቅቡዓን ክርስቲያኖች ተስፋ ጥብቅና ቆሟል። እስቲ በ1 ቆሮንቶስ ምዕራፍ 15 ላይ ተመዝግበው የሚገኙትን የጳውሎስ ቃላት እንመርምር። ከዚህ በፊት ባለው ርዕስ ላይ በተገለጸው መሠረት መላውን ምዕራፍ ማንበባችሁ ጠቃሚ ሆኖ ታገኙታላችሁ።
7. (ሀ) ጳውሎስ ትኩረቱን ያደረገው በየትኛው ቁልፍ ነጥብ ላይ ነበር? (ለ) ከሞት የተነሣውን ኢየሱስ እነማን አይተውታል?
7 ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ ምዕራፍ 15 የመጀመሪያ ሁለት ቁጥሮች ላይ የንግግሩን ጭብጥ ገልጿል:- “ወንድሞች ሆይ፣ የሰበክሁላችሁን ደግሞም የተቀበላችሁትን በእርሱም ደግሞ የቆማችሁበትን በእርሱም ደግሞ የምትድኑበትን ወንጌል አሳስባችኋለሁ፤ በከንቱ ካላመናችሁ በቀር።” የቆሮንቶስ ሰዎች በምሥራቹ ጸንተው ካልቆሙ እውነትን የተቀበሉት በከንቱ ነው። ጳውሎስ በመቀጠል እንዲህ አለ:- “እኔ ደግሞ የተቀበልሁትን ከሁሉ በፊት አሳልፌ ሰጠኋችሁ እንዲህ ብዬ:- መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፣ ተቀበረም፣ መጽሐፍም እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነሣ፣ ለኬፋም ታየ በኋላም ለአሥራ ሁለቱ፤ ከዚያም በኋላ ከአምስት መቶ ለሚበዙ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ፤ ከእነርሱም የሚበዙቱ እስከ አሁን አሉ አንዳንዶች ግን አንቀላፍተዋል፤ ከዚያም በኋላ ለያዕቆብ ኋላም ለሐዋርያት ሁሉ ታየ፤ ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ደግሞ ታየኝ።”—1 ቆሮንቶስ 15:3-8
8, 9. (ሀ) በትንሣኤ ማመን ምን ያህል አስፈላጊ ነው? (ለ) ኢየሱስ “ከአምስት መቶ ለሚበዙ ወንድሞች” የታየው በየትኛው አጋጣሚ ሳይሆን አይቀርም?
8 ምሥራቹን የተቀበሉ ሰዎች በኢየሱስ ትንሣኤ ያለማወላወል ያምኑ ነበር። ‘ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሲል መሞቱንና’ በኋላም መነሣቱን የሚያረጋግጡ ብዙ የዓይን ምሥክሮች ነበሩ። ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ጴጥሮስ በሚለው ስሙ በሰፊው የሚታወቀው ኬፋ ነበር። ኢየሱስ አልፎ በተሰጠበትና በታሰረበት ምሽት ጴጥሮስ ኢየሱስን ከካደው በኋላ ኢየሱስ ለእሱ መገለጡ እጅግ አጽናንቶት መሆን አለበት። ከሞት የተነሳው ኢየሱስ “ለአሥራ ሁለቱ” ማለትም በቡድን ደረጃ ለሐዋርያት መገለጡ ፍርሃታቸውን እንዲያሸንፉና ኢየሱስ ከሞት መነሣቱን በድፍረት እንዲመሠክሩ እንደረዳቸው ምንም አያጠራጥርም።—ዮሐንስ 20:19-23፤ ሥራ 2:32
9 በተጨማሪም ክርስቶስ ብዙ ሰዎችን ላቀፈ ቡድን ማለትም “ከአምስት መቶ ለሚበዙ ወንድሞች” ታይቷል። ኢየሱስ ይህን ያህል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተከታዮች የነበሩት በገሊላ ስለነበር ድርጊቱ የተፈጸመው በማቴዎስ 28:16-20 ላይ ተዘግቦ በሚገኘው መሠረት ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አድርጉ የሚለውን ትእዛዝ በሰጠበት ወቅት መሆን አለበት። እነዚህ ግለሰቦች የሚሰጡት የምሥክርነት ቃል ምንኛ አሳማኝ ይሆን! ጳውሎስ ይህን የመጀመሪያ ደብዳቤ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈበት በ55 እዘአ ላይም አንዳንዶቹ በሕይወት ነበሩ። እነዚያ የሞቱት ግን “አንቀላፍተዋል” እንደተባለላቸው ልብ በል። ሰማያዊ ሽልማታቸውን ለመቀበል ገና አልተነሡም ነበር።
10. (ሀ) ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ካደረገው የመጨረሻ ስብሰባ ምን ውጤት ተገኝቷል? (ለ) ኢየሱስ ‘እንደ ጭንጋፍ ለሆነው’ ለጳውሎስ የተገለጠለት እንዴት ነበር?
10 ለኢየሱስ ትንሣኤ ሌላው ዋነኛ ምሥክር ደግሞ የዮሴፍና የኢየሱስ እናት የማርያም ልጅ የሆነው ያዕቆብ ነበር። ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ኢየሱስ ከሞት ከመነሣቱ በፊት ያዕቆብ በእርሱ አያምንም ነበር። (ዮሐንስ 7:5) ይሁን እንጂ ያዕቆብ፣ ኢየሱስ ከተገለጠለት በኋላ በእሱ ከማመኑም በላይ ሌሎች ወንድሞቹ ወደ ክርስትና እንዲለወጡ የበኩሉን አስተዋጽኦ ሳያደርግ አይቀርም። (ሥራ 1:13, 14) ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሊያርግ ሲል ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ባደረገው የመጨረሻ ስብሰባ ላይ ‘እስከ ምድር ዳር ድረስ ምሥክሮቹ እንዲሆኑ’ አዟቸዋል። (ሥራ 1:6-11) ቆየት ብሎም የክርስቲያኖች አሳዳጅ ለነበረው ለጠርሴሱ ሳውል ታየ። (ሥራ 22:6-8) ኢየሱስ ‘እንደ ጭንጋፍ ለሆነው’ ለሳውል ታይቷል። ሳውል የቅቡዓኑ ትንሣኤ ከመከናወኑ ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት ከሞት ተነስቶና መንፈሳዊ ሕይወት አግኝቶ ክብር የተቀዳጀውን ጌታ ለማየት የቻለ ያህል ነበር። በሳውል ላይ የደረሰው ይህ ሁኔታ የክርስቲያን ጉባኤን መቃወሙንና ወንድሞችን እያሳደደ መግደሉን ከመቅጽበት እንዲያቆምና ጉልህ ለውጥ እንዲያሳይ አድርጎታል። (ሥራ 9:3-9, 17-19) ሳውል ሐዋርያው ጳውሎስ ተብሎ በመጠራት ለክርስቲያን እምነት ጥብቅና በመቆም የላቀ ግምት ከሚሰጣቸው ውስጥ አንዱ ሆኗል።—1 ቆሮንቶስ 15:9, 10
በትንሣኤ ማመን የግድ አስፈላጊ ነው
11. ጳውሎስ ‘ትንሣኤ የለም’ የሚለው አባባል ሐሰት መሆኑን ያጋለጠው እንዴት ነበር?
11 በመሆኑም የኢየሱስ ትንሣኤ አሌ የማይባል ሐቅ ነው። ጳውሎስ “ክርስቶስ ከሙታን እንደ ተነሣ የሚሰበክ ከሆነ ግን ከእናንተ አንዳንዶቹ:- ትንሣኤ ሙታን የለም እንዴት ይላሉ?” ሲል ገልጿል። (1 ቆሮንቶስ 15:12) እነዚህ ሰዎች ትንሣኤን በተመለከተ የነበራቸው የግል ጥርጣሬ ወይም ጥያቄ ብቻ ሳይሆን እንደማያምኑበት ጭምር አፍ አውጥተው ይናገሩ ነበር። ስለዚህ ጳውሎስ አስተሳሰባቸው የተሳሳተ መሆኑን አጋልጧል። ክርስቶስ ካልተነሣ ክርስቲያናዊው መልእክት ውሸት እንደሚሆንና ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ የመሠከሩ ሰዎችም “ሐሰተኞች የእግዚአብሔር ምስክሮች” እንደሚሆኑ ተናግሯል። ክርስቶስ ካልተነሣ ለአምላክ ምንም ቤዛ አልተከፈለም፤ ክርስቲያኖች ‘አሁንም በኃጢአት ውስጥ ናቸው’ ማለት ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:13-19፤ ሮሜ 3:23, 24፤ ዕብራውያን 9:11-14) እንዲሁም ሰማዕት የሆኑትን ጨምሮ ‘በሞት ያንቀላፉ’ ክርስቲያኖች የማይጨበጥ ተስፋ ይዘው ሞተዋል ማለት ነው። ክርስቲያኖች የሚጠባበቁት ሕይወት ይህ ብቻ ቢሆን ኖሮ ምንኛ የሚያሳዝን ይሆን ነበር! ይህን ሁሉ ሥቃይ የተቀበሉት በከንቱ ይሆን ነበር።
12. (ሀ) ክርስቶስ በሞት “ላንቀላፉት በኩራት” ሆኗል መባሉ ምን ያመለክታል? (ለ) ክርስቶስ ትንሣኤ እውን እንዲሆን ያደረገው እንዴት ነው?
12 ይሁን እንጂ ሁኔታው እንደዚያ አይደለም። ጳውሎስ በመቀጠል “ክርስቶስ . . . ከሙታን ተነሥቶአል” ብሏል። በተጨማሪም “ላንቀላፉት በኩራት” ሆኗል። (1 ቆሮንቶስ 15:20) እስራኤላውያን በታዛዥነት የምርታቸውን በኩራት ለይሖዋ ሲሰጡ ይሖዋ ደግሞ በተራው የተትረፈረፈ ምርት በመስጠት ባርኳቸዋል። (ዘጸአት 22:29, 30፤ 23:19፤ ምሳሌ 3:9, 10) ጳውሎስ ክርስቶስን “በኩራት” ብሎ መጥራቱ ተጨማሪ መከር ማለትም ሰማያዊ ሕይወት ለማግኘት ከሞት የሚነሡ ግለሰቦች እንደሚኖሩ ማመልከቱ ነበር። ጳውሎስ “ሞት በሰው በኩል ስለ መጣ ትንሣኤ ሙታን በሰው በኩል ሆኖአልና ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና” ሲል ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 15:21, 22) ኢየሱስ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ በመስጠት የሰው ዘር ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ነፃ መውጣት የሚችልበትን መንገድ ከፍቷል። በዚህም መንገድ ትንሣኤ እውን እንዲሆን አድርጓል።—ገላትያ 1:4፤ 1 ጴጥሮስ 1:18, 19a
13. (ሀ) ሰማያዊው ትንሣኤ የሚከናወነው መቼ ነው? (ለ) አንዳንድ ቅቡዓን በሞት ‘የማያንቀላፉት’ በምን መንገድ ነው?
13 ጳውሎስ በመቀጠል “ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ ክርስቶስ እንደ በኵራት ነው፣ በኋላም በመምጣቱ ለክርስቶስ የሆኑት ናቸው” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 15:23) ክርስቶስ ከሞት የተነሣው በ33 እዘአ ነበር። ይሁንና “ለክርስቶስ የሆኑት” ቅቡዓን ተከታዮቹ ኢየሱስ በንጉሣዊ ሥልጣኑ እስኪገኝ ድረስ መጠበቅ ነበረባቸው። ይህም የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንደሚያሳየው በ1914 ተፈጽሟል። (1 ተሰሎንቄ 4:14-16፤ ራእይ 11:18) በሥልጣኑ በሚገኝበት ጊዜ በሕይወት ስለሚኖሩትስ ምን ማለት ይቻላል? ጳውሎስ እንዲህ ብሏል:- “እነሆ፣ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ፤ ሁላችን አናንቀላፋም ነገር ግን የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበት ዓይን እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋልና ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ እኛም እንለወጣለን።” (1 ቆሮንቶስ 15:51, 52) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው በመቃብር አንቀላፍተው ትንሣኤን መጠባበቅ የሚያስፈልጋቸው ሁሉም ቅቡዓን አይደሉም። ክርስቶስ በሥልጣኑ ላይ በሚገኝበት ጊዜ የሚሞቱ ወዲያውኑ ይለወጣሉ።—ራእይ 14:13
14. ቅቡዓኑ ‘ስለ ሙታን የሚጠመቁት’ እንዴት ነው?
14 ጳውሎስ “እንዲያማ ካልሆነ፣ ስለ ሙታን የሚጠመቁ ምን ያደርጋሉ? ሙታንስ ከቶ የማይነሡ ከሆነ፣ ስለ እነርሱ የሚጠመቁ ስለ ምንድር ነው? እኛስ ዘወትር በሚያስፈራ ኑሮ የምንኖር ስለ ምንድር ነው?” ሲል ጠይቋል። (1 ቆሮንቶስ 15:29, 30) አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች እንደሚሉት ጳውሎስ ሕያዋን ግለሰቦች ስለ ሙታን ሲሉ ይጠመቃሉ ማለቱ አልነበረም። ጥምቀት ክርስቲያን ደቀ መዝሙር ከመሆን ጋር የተዛመደ ሲሆን የሞቱ ነፍሳት ደግሞ ደቀ መዛሙርት መሆን አይችሉም። (ዮሐንስ 4:1) ከዚህ ይልቅ ጳውሎስ ስለ ሕያው ክርስቲያኖች መናገሩ ነበር፤ ከእነሱም መካከል ብዙዎቹ እንደ እሱ ‘ዘወትር በሚያስፈራ ኑሮ የሚኖሩ’ ነበሩ። ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘ወደ ክርስቶስ ሞት ተጠምቀዋል።’ (ሮሜ 6:3) ከተቀቡበት ጊዜ አንሥቶ የክርስቶስን ወደ መሰለ ሞት ወደሚመራ አካሄድ ‘ተጠምቀዋል’ ለማለት ይቻላል። (ማርቆስ 10:35-40) ክብራማ ሰማያዊ ሕይወት የሚያስገኝ የትንሣኤ ተስፋ ይዘው ይሞታሉ።—1 ቆሮንቶስ 6:14፤ ፊልጵስዩስ 3:10, 11
15. ጳውሎስ እንዴት ያሉ አደጋዎች አጋጥመውት ሊሆን ይችላል? በትንሣኤ ላይ የነበረው እምነት መከራዎቹን ጸንቶ በመቋቋም ረገድ ምን ሚና ተጫውቷል?
15 አሁን ደግሞ ጳውሎስ “በየቀኑ ሞት ያጋጥመኛል” (የ1980 ትርጉም) ብሎ እስኪናገር ድረስ አስፈሪ ሕይወት ውስጥ ማለፉን ገልጿል። አንዳንዶች በጣም አጋኗል ብለው ካልወነጀሉት በስተቀር ጳውሎስ “በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ ባለኝ በእናንተ ትምክህት [እምላለሁ]” ሲል አክሎ ተናግሯል። ዘ ጀሩሳሌም ባይብል ይህን ጥቅስ እንዲህ ሲል ተርጉሞታል:- “ወንድሞች ሆይ፣ ዕለት ዕለት ከሞት ጋር እጋፈጣለሁ፤ በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ በእናንተ ላይ ባለኝ እምነት እምላለሁ።” ጳውሎስ ከተጋፈጣቸው አደጋዎች አንዱን ምሳሌ አድርጎ በመጥቀስ በቁጥር 32 ላይ ‘በኤፌሶን ከአውሬ ጋር መታገሉን’ ገልጿል። አብዛኛውን ጊዜ ሮማውያን ወንጀለኞችን በሞት የሚቀጡት ዙሪያቸውን በታጠሩ የትግል መወዳደሪያ ቦታዎች ውስጥ ለአውሬዎች አሳልፈው በመስጠት ነበር። ጳውሎስ ቃል በቃል ከአውሬ ጋር ታግሎ ከነበረ ሊድን የቻለው በይሖዋ እርዳታ ብቻ መሆን አለበት። የትንሣኤ ተስፋ ሳይኖረው እንዲህ ላለ አደገኛ ሁኔታ የሚያጋልጥ የሕይወት ጎዳና መምረጡ ቂልነት ይሆንበት ነበር። የወደፊት ሕይወት ተስፋ ሳይኖር አምላክን ከማገልገል ጋር ተያይዘው የሚመጡትን ችግሮች ጸንቶ መቋቋምና መሥዋዕቶችን መክፈል ትርጉም የለሽ ይሆናል። ጳውሎስ “ሙታንስ የማይነሡ ከሆነ፣ . . . ነገ እንሞታለንና እንብላና እንጠጣ” ብሏል።—1 ቆሮንቶስ 15:31, 32፤ 2 ቆሮንቶስ 1:8, 9ንና 11:23-27ን ተመልከት።
16. (ሀ) “ነገ እንሞታለንና እንብላና እንጠጣ” የሚለው አባባል የመነጨው ከየት ሳይሆን አይቀርም? (ለ) እንዲህ ያለውን አመለካከት መያዙ ምን አደጋዎች ነበሩት?
16 ጳውሎስ በዕድል ያምኑ ስለነበሩት ዓመፀኛ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች የሚገልጸውን ኢሳይያስ 22:13ን መጥቀሱ ሳይሆን አይቀርም። ወይም ደግሞ ከሞት በኋላ የሚኖረውን የትኛውንም ዓይነት የሕይወት ተስፋ የሚያጣጥሉትንና በሕይወት ውስጥ ዋናው ነገር ሥጋዊ ተድላ ነው ብለው የሚያምኑትን ኤፊቆሮሳውያንን በአእምሮው ይዞ ይሆናል። በዚያም ሆነ በዚህ “እንብላና እንጠጣ” የሚለው ፍልስፍና አምላካዊ አልነበረም። በመሆኑም ጳውሎስ “አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል” ሲል አስጠንቅቋል። (1 ቆሮንቶስ 15:33) ትንሣኤን ከካዱ ጋር መወዳጀት አደገኛ ሊሆን ይችላል። በቆሮንቶስ ጉባኤ ውስጥ ተከስተው የነበሩትና ጳውሎስ እንዲስተካከሉ ያደረጋቸው እንደ ጾታ ብልግና፣ መከፋፈል፣ በፍርድ ቤት መካሰስና ለጌታ እራት አክብሮት ማጣት የመሳሰሉት ችግሮች የእንዲህ ያለው ወዳጅነት ውጤት ሳይሆኑ አይቀሩም።—1 ቆሮንቶስ 1:11፤ 5:1፤ 6:1፤ 11:20-22
17. (ሀ) ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች ምን ማሳሰቢያ ሰጥቷል? (ለ) መልስ የሚያሻቸው ቀሪ ጥያቄዎች የትኞቹ ናቸው?
17 ስለዚህም ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የሚከተለውን ገንቢ ማሳሰቢያ ሰጥቷል:- “በጽድቅ ንቁ ኃጢአትንም አትሥሩ፤ እግዚአብሔርን የማያውቁ አሉና፤ አሳፍራችሁ ዘንድ ይህን እላለሁ።” (1 ቆሮንቶስ 15:34) አንዳንዶች ስለ ትንሣኤ አፍራሽ አመለካከት መያዛቸው የሰከሩ ይመስል መንፈሳዊ ድብታ ውስጥ ከቷቸዋል። መንቃት እንዲሁም አስተዋዮች ሆነው መቀጠል አስፈልጓቸው ነበር። ዛሬም በተመሳሳይ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ዓለም ያለው የጥርጣሬ አመለካከት ተጽዕኖ እንዲያሳድርባቸው ከመፍቀድ ይልቅ በመንፈሳዊ ንቁ መሆን ያስፈልጋቸዋል። የሰማያዊ ትንሣኤ ተስፋቸውን የሙጥኝ ማለት አለባቸው። ይሁን እንጂ በዚያን ጊዜ የነበሩት የቆሮንቶስ ሰዎችም ሆኑ እኛ መልስ ልናገኝላቸው የሚገቡ ተጨማሪ ጥያቄዎች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ 144,000ዎቹ ተነስተው ወደ ሰማይ የሚሄዱት በምን ዓይነት መንገድ ነው? አሁንም በመቃብር ውስጥ ያሉና ሰማያዊ ተስፋ የሌላቸው ሌሎች በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችስ? ለእነዚህ ሰዎች ትንሣኤ ምን ማለት ይሆናል? በሚቀጥለው ርዕሳችን ላይ ጳውሎስ ስለ ትንሣኤ የሰጠውን ማብራሪያ ቀሪ ክፍል እንመረምራለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ስለ ቤዛው ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የየካቲት 15, 1991 መጠበቂያ ግንብ እትምን ተመልከት።
[ታስታውሳለህን?]
◻ ኢየሱስ በትንሣኤ ተስፋ ላይ ምን ብርሃን ፈንጥቋል?
◻ ክርስቶስ ከሞት መነሣቱን የመሠከሩ አንዳንድ ሰዎች እነማን ነበሩ?
◻ የትንሣኤ መሠረተ ትምህርት ተቃውሞ የገጠመው ለምን ነበር? ጳውሎስስ ምን ምላሽ ሰጠ?
◻ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በትንሣኤ ማመናቸው በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምን ነበር?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የኢያኢሮስ ልጅ ትንሣኤ ለመኖሩ ማረጋገጫ ሆናለች
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የትንሣኤ ተስፋ ባይኖር ኖሮ የታማኝ ክርስቲያኖች ሰማዕታዊ ሞት ትርጉም የለሽ ይሆን ነበር