ይህ የመዳን ቀን ነው!
“እነሆ፣ የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤ እነሆ፣ የመዳን ቀን አሁን ነው።”—2 ቆሮንቶስ 6:2
1. በአምላክና በክርስቶስ ፊት ሞገስ የሚያሰጥ አቋም ለመያዝ ምን ያስፈልጋል?
ይሖዋ ለሰው ዘር ፍርድ የሚሰጥበት ቀን ቀጥሯል። (ሥራ 17:31) ይህ ቀን የመዳን ቀን እንዲሆንልን ከፈለግን በይሖዋና በተሾመው ፈራጅ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት ሞገስ የሚያሰጠን አቋም ሊኖረን ይገባል። (ዮሐንስ 5:22) እንዲህ ያለው አቋም ከአምላክ ቃል ጋር የሚስማማ አኗኗርና ሌሎች የኢየሱስ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ለመርዳት የሚገፋፋ እምነት እንዲኖረን ይጠይቃል።
2. የሰው ዘር ዓለም ከአምላክ የራቀው ለምንድን ነው?
2 የሰው ዘር ዓለም በወረሰው ኃጢአት ምክንያት ከአምላክ ርቋል። (ሮሜ 5:12፤ ኤፌሶን 4:17, 18) ስለዚህ የምንሰብክላቸው ሰዎች መዳንን ሊያገኙ የሚችሉት ከእሱ ጋር ከታረቁ ብቻ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በቆሮንቶስ ለሚገኙ ክርስቲያኖች ሲጽፍ ይህን ግልጽ አድርጓል። ጳውሎስ ፍርድን፣ ከአምላክ ጋር መታረቅንና መዳንን አስመልክቶ የተናገረውን ለማወቅ እስቲ 2 ቆሮንቶስ 5:10 እስከ 6:10ን እንመርምር።
‘ሰዎችን እናሳምናለን’
3. ጳውሎስ ‘ሰዎችን ያሳምን’ የነበረው እንዴት ነው? እኛስ ዛሬ ይህን ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?
3 ጳውሎስ እንደሚከተለው ብሎ በጻፈ ጊዜ ፍርድን ከስብከት ጋር አዛምዶታል:- “መልካም ቢሆን ወይም ክፉ እንዳደረገ፣ እያንዳንዱ በሥጋው የተሠራውን በብድራት ይቀበል ዘንድ ሁላችን በክርስቶስ በፍርድ ወንበር ፊት ልንገለጥ ይገባናልና። እንግዲህ የጌታን ፍርሃት አውቀን ሰዎችን እናስረዳለን [“እናሳምናለን፣” NW]።” (2 ቆሮንቶስ 5:10, 11) ሐዋርያው ምሥራቹን በመስበክ ‘ሰዎችን ያሳምን’ ነበር። እኛስ? የዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ጥፋት ከፊታችን ስለሚጠብቀን ሌሎች ኢየሱስ እንዲፈርድላቸውና የመዳን ምንጭ በሆነው በይሖዋ አምላክ ዘንድ ሞገስ የሚያሰጧቸው አስፈላጊ እርምጃዎች እንዲወስዱ ለማሳመን የቻልነውን ያህል ጥረት ማድረግ አለብን።
4, 5. (ሀ) በይሖዋ አገልግሎት ስላከናወንነው ነገር መኩራራት የሌለብን ለምንድን ነው? (ለ) ጳውሎስ “ለአምላክ” ሲል በመኩራራት የተናገረው እንዴት ነበር?
4 ሆኖም አምላክ አገልግሎታችንን ቢባርከው እኛ የምንኩራራበት ምክንያት የለም። በቆሮንቶስ የሚገኙ አንዳንዶች በራሳቸው ወይም በሌሎች በመመካት በኩራት ተወጥረው ስለነበር በጉባኤው ውስጥ መከፋፈል ተፈጥሮ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 1:10–13፤ 3:3, 4) ጳውሎስ ስለዚህ ሁኔታ በተዘዋዋሪ በመጥቀስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በመልክ እንጂ በልብ ለማይመኩ የምትመልሱላቸው መልስ እንዲኖራችሁ፣ በእኛ ልትመኩ ምክንያት እንሰጣችኋለን እንጂ ራሳችንን ደግሞ ለእናንተ የምናመሰግን አይደለንም። እብዶች ብንሆን፣ ለእግዚአብሔር ነው፤ ባለ አእምሮዎች ብንሆን፣ ለእናንተ ነው።” (2 ቆሮንቶስ 5:12, 13) ትዕቢተኛ የነበሩ ሰዎች ለጉባኤው አንድነትና መንፈሳዊ ደኅንነት ደንታ አልነበራቸውም። መሰል አማኞች በአምላክ ፊት ጥሩ ልብ እንዲያዳብሩ ከመርዳት ይልቅ በውጫዊ መልክ ለመመካት ይፈልጉ ነበር። በመሆኑም ጳውሎስ ጉባኤውን ከገሠጸ በኋላ ቆየት ብሎ እንዲህ አለ:- “የሚመካ ግን በጌታ ይመካ።”—2 ቆሮንቶስ 10:17
5 ጳውሎስ ራሱ በኩራት የተናገረበት ጊዜ አልነበረምን? ሐዋርያ ስለመሆኑ ከተናገረው ነገር በመነሳት አንዳንዶች እንዲህ ብለው ያስቡ ይሆናል። ሆኖም ‘ለአምላክ’ ሲል በኩራት መናገር ነበረበት። የቆሮንቶስ ሰዎች ይሖዋን እንዳይተዉ ሲል በሐዋርያነቱ ስላገኛቸው ሹመቶች በኩራት ተናግሯል። ጳውሎስ ይህን ያደረገው እነሱን ወደ አምላክ ለመመለስ ሲል ነበር፤ ምክንያቱም ሐሰተኛ ሐዋርያት ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ እየመሯቸው ነበር። (2 ቆሮንቶስ 11:16–21፤ 12:11, 12, 19–21፤ 13:10) ቢሆንም ጳውሎስ ሁልጊዜ ስላገኛቸው ስኬቶች በመናገር የሌሎች ሰዎችን ትኩረት ለመሳብ አልሞከረም።—ምሳሌ 21:4
የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይላችኋልን?
6. የክርስቶስ ፍቅር እንዴት ሊነካን ይገባል?
6 ጳውሎስ እውነተኛ ሐዋርያ እንደመሆኑ መጠን ስለ ኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ሌሎችን ያስተምር ነበር። ቤዛው በጳውሎስ ሕይወት ላይ ትልቅ ተጽእኖ ነበረው፤ በመሆኑም እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ይህን ስለ ቈረጥን የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናልና፤ አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ፤ እንግዲያስ ሁሉ ሞቱ፤ በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ።” (2 ቆሮንቶስ 5:14, 15) ኢየሱስ ለእኛ ሲል ሕይወቱን አሳልፎ በመስጠት እንዴት ያለ ፍቅር አሳይቷል! በእርግጥም ይህ በሕይወታችን ውስጥ የሚገፋፋ ኃይል ሊሆን ይገባል። ኢየሱስ ሕይወቱን ለእኛ ሲል በመስጠቱ ለእሱ ያለን አድናቆት ይሖዋ በሚወደው ልጁ በኩል ስላዘጋጀው መዳን የሚናገረውን ምሥራች በማወጁ እንቅስቃሴ ቀናተኞች እንድንሆን ይገፋፋናል። (ዮሐንስ 3:16፤ ከመዝሙር 96:2 ጋር አወዳድር።) “የክርስቶስ ፍቅር” በመንግሥቱ ስብከትና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በቅንዓት እንድትካፈል እየገፋፋህ ነውን?—ማቴዎስ 28:19, 20
7. ‘ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አለማወቅ’ ምን ማለት ነው?
7 ክርስቶስ ለእነሱ ሲል ያደረገውን ነገር እንደሚያደንቁ በሚያሳይ መንገድ ሕይወታቸውን በመጠቀም ቅቡዓኑ ‘ለራሳቸው ሳይሆን ለእሱ ይኖራሉ።’ ጳውሎስ “ስለዚህ እኛ ከአሁን ጀምሮ ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አናውቅም፤ ክርስቶስንም በሥጋ እንደ ሆነ ያወቅነው ብንሆን እንኳ፣ አሁን ግን ከእንግዲህ ወዲህ እንደዚህ አናውቀውም” ብሏል። (2 ቆሮንቶስ 5:16) ክርስቲያኖች ከአሕዛብ ይልቅ ለአይሁዳውያን ወይም ከድሆች ይልቅ ለሀብታሞች በማዳላት ሰዎችን በሥጋዊ ዓይን መመልከት የለባቸውም። ቅቡዓኑ ይበልጥ የሚያሳስባቸው ከመሰል አማኞች ጋር ያላቸው መንፈሳዊ ዝምድና ስለሆነ ‘ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አያውቁም።’ እነዚያ ‘ክርስቶስን በሥጋ እንደ ሆነ የሚያውቁት’ ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ያዩት ሰዎች ብቻ አይደሉም። ምንም እንኳ በመሲሑ ተስፋ ያደርጉ የነበሩ አንዳንዶች በአንድ ወቅት ክርስቶስን ሰብዓዊ ሰው አድርገው ይመለከቱት የነበረ ቢሆንም ይህን አመለካከታቸውን መለወጥ አስፈልጓቸው ነበር። አካሉን ቤዛ አድርጎ ከሰጠ በኋላ ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆኖ ከሞት ተነሥቷል። ሥጋዊ አካላቸውን በመተው ለሰማያዊ ሕይወት የሚነሱት ሌሎች ቅቡዓን ኢየሱስ ክርስቶስን ፈጽሞ በሥጋ አይተውት አያውቁም።—1 ቆሮንቶስ 15:45, 50፤ 2 ቆሮንቶስ 5:1–5
8. ግለሰቦች ‘ከክርስቶስ ጋር አንድ የሚሆኑት’ እንዴት ነው?
8 ጳውሎስ አሁንም ለቅቡዓኑ መናገሩን በመቀጠል እንዲህ በማለት አክሏል:- “ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፣ ሁሉም አዲስ ሆኖአል።” (2 ቆሮንቶስ 5:17) ‘በክርስቶስ መሆን’ ማለት ከእርሱ ጋር አንድ መሆን ማለት ነው። (ዮሐንስ 17:21) ይህ ግንኙነት ለአንድ ሰው እውን የሚሆነው ይሖዋ ወደ ልጁ ሲስበውና ከመንፈስ ቅዱስ እንዲወለድ ሲያደርገው ነው። ከመንፈስ የተወለደ የአምላክ ልጅ በመሆኑ ከክርስቶስ ጋር በሰማያዊው መንግሥት ተካፋይ የመሆን ተስፋ ያለው “አዲስ ፍጥረት” ሆኗል። (ዮሐንስ 3:3–8፤ 6:44፤ ገላትያ 4:6, 7) እነዚህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ላቅ ያለ የአገልግሎት መብት ተሰጥቷቸዋል።
“ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ”
9. አምላክ ሰዎች ከእሱ ጋር መታረቅ እንዲችሉ ሲል ምን አድርጓል?
9 ይሖዋ ለዚህ “አዲስ ፍጥረት” ከፍተኛ ሞገሱን አሳይቷል! ጳውሎስ እንዲህ ይላል:- “ነገር ግን የሆነው ሁሉ፣ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን፣ ከእግዚአብሔር ነው፤ እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፣ በደላቸውን አይቈጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ።” (2 ቆሮንቶስ 5:18, 19) አዳም ኃጢአት ከሠራበት ጊዜ አንስቶ የሰው ልጅ ከአምላክ ርቆ ቆይቷል። ሆኖም ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ ቅድሚያውን በመውሰድ ለመታረቅ የሚያስችል መንገድ በኢየሱስ መሥዋዕት አማካኝነት አዘጋጀ።—ሮሜ 5:6–12
10. ይሖዋ የማስታረቅ አገልግሎትን የሰጠው ለእነማን ነው? ይህንን ለመፈጸምስ ምን አድርገዋል?
10 ይሖዋ የማስታረቁን አገልግሎት ለቅቡዓኑ በመስጠቱ ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ለመናገር ችሏል:- “እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች [“አምባሳደሮች፣” የ1980 ትርጉም] ነን፤ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን።” (2 ቆሮንቶስ 5:20) በጥንት ዘመን አብዛኛውን ጊዜ አምባሳደሮች ይላኩ የነበረው ግጭት በሚፈጠርባቸው ወቅቶች ሲሆን በግጭቱ ምክንያት ጦርነት እንዳይነሳ ማድረግ በሚቻልበት መንገድ ላይ ይደራደሩ ነበር። (ሉቃስ 14:31, 32) ኃጢአተኛው የሰው ዘር ዓለም ከአምላክ የራቀ በመሆኑ አምላክ ያቀረበውን የማስታረቂያ ሐሳብ ለሰዎች እንዲያስታውቁ የተቀቡ አምባሳደሮቹን ልኳል። ቅቡዓኑ የክርስቶስ ተተኪዎች እንደመሆናቸው መጠን “ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ” ብለው ይለምናሉ። ይህ ልመና ሰዎች ከአምላክ ጋር ሰላም እንዲፈጥሩና በክርስቶስ በኩል የሚሰጠውን መዳን እንዲቀበሉ የሚቀርብ የምሕረት ማሳሰቢያ ነው።
11. በቤዛው በማመን በመጨረሻ በአምላክ ፊት የጽድቅ አቋም የሚያገኙት እነማን ናቸው?
11 በቤዛው የሚያምኑ ሰዎች በሙሉ ከአምላክ ጋር ሊታረቁ ይችላሉ። (ዮሐንስ 3:36) ጳውሎስ “እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ [ይሖዋ] ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን [ኢየሱስን] ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው” ብሏል። (2 ቆሮንቶስ 5:21) ፍጹም ሰው የነበረው ኢየሱስ ከውርስ ኃጢአት ነፃ ለወጡት ለሁሉም የአዳም ዘሮች የቀረበ የኃጢአት መሥዋዕት ነበር። በኢየሱስ አማካኝነት “የእግዚአብሔር ጽድቅ” ሆነዋል። ይህ ጽድቅ ወይም በአምላክ ፊት የጽድቅ አቋም መያዝ በመጀመሪያ የመጣው ለ144,000ዎቹ የክርስቶስ ተባባሪ ወራሾች ነው። በሺህ ዓመት የግዛት ዘመኑ የዘላለማዊው አባት የኢየሱስ ክርስቶስ ምድራዊ ልጆች ፍጹም ሰዎች በመሆን የጽድቅ አቋም ያገኛሉ። ለአምላክ የታመኑ መሆናቸውን እንዲያስመሰክሩና የዘላለም ሕይወት ሽልማት እንዲቀበሉ ፍጹም ወደሆነ የጽድቅ አቋም ከፍ ከፍ ያደርጋቸዋል።—ኢሳይያስ 9:6፤ ራእይ 14:1፤ 20:4–6, 11–15
“የተወደደው ሰዓት”
12. የይሖዋ አምባሳደሮችና መልእክተኞች የትኛውን አስፈላጊ የሆነ አገልግሎት በማከናወን ላይ ይገኛሉ?
12 ለመዳን ከጳውሎስ ቃላት ጋር የሚስማማ ተግባር መፈጸም አለብን:- “[ከይሖዋ ጋር] አብረንም እየሠራን የእግዚአብሔርን ጸጋ በከንቱ እንዳትቀበሉ ደግሞ እንለምናለን፤ በተወደደ ሰዓት ሰማሁህ በመዳንም ቀን ረዳሁህ ይላልና፤ እነሆ፣ የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤ እነሆ፣ የመዳን ቀን አሁን ነው።” (2 ቆሮንቶስ 6:1, 2) የይሖዋ ቅቡዓን አምባሳደሮችና መልእክተኞቹ “ሌሎች በጎች” የሰማያዊ አባታቸውን ይገባናል የማይሉት ደግነት በከንቱ አይቀበሉም። (ዮሐንስ 10:16) በጥሩ ምግባራቸውና ቅንዓት በተሞላው አገልግሎታቸው በዚህ “የተወደደ ሰዓት” መለኮታዊ ተቀባይነት ለማግኘት ይጥራሉ፤ እንዲሁም ለምድር ነዋሪዎች ይህ “የመዳን ቀን” መሆኑን በማሳወቅ ላይ ናቸው።
13. የኢሳይያስ 49:8 ፍሬ ነገር ምንድን ነው? የመጀመሪያ ፍጻሜውን ያገኘውስ እንዴት ነበር?
13 ጳውሎስ እንደሚከተለው የሚነበበውን ኢሳይያስ 49:8ን ጠቅሷል:- “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:- በተወደደ ጊዜ ሰምቼሃለሁ፣ በመድኃኒትም ቀን ረድቼሃለሁ፤ እጠብቅህማለሁ፣ ምድርንም ታቀና ዘንድ፣ ውድማ የሆኑትንም ርስቶች ታወርስ ዘንድ፣ . . . ቃል ኪዳን አድርጌ ለሕዝቡ ሰጥቼሃለሁ።” ይህ ትንቢት በመጀመሪያ የተፈጸመው የእስራኤል ሕዝብ ከባቢሎን ምርኮ ነፃ ከወጡና ባድማ ወደ ሆነው የትውልድ ስፍራቸው በተመለሱ ጊዜ ነበር።—ኢሳይያስ 49:3, 9
14. ኢሳይያስ 49:8 ከኢየሱስ ጋር በተያያዘ ሁኔታ ፍጻሜ ያገኘው እንዴት ነበር?
14 የኢሳይያስ ትንቢት ተጨማሪ ፍጻሜውን ሲያገኝ ይሖዋ ‘አገልጋዩን’ ኢየሱስን “እስከ ምድር ዳር ድረስ መድኃኒት [ይ]ሆን ዘንድ [የአምላክ ማዳን ግልጥ ይሆን ዘንድ] ለአሕዛብ ብርሃን” አድርጎ ሰጥቷል። (ኢሳይያስ 49:6, 8፤ ከኢሳይያስ 42:1–4, 6, 7 እና ማቴዎስ 12:18–21 ጋር አወዳድር።) ‘የተወደደው ጊዜ’ ወይም “የተወደደው ሰዓት” ኢየሱስ በምድር ላይ የነበረበትን ጊዜ እንደሚያመለክት ግልጽ ነው። ኢየሱስ ጸልዮአል፤ አምላክም ‘ሰምቶታል።’ ይህ ፍጹም አቋሙን ለጠበቀው ለኢየሱስ “የመዳን ቀን” ሆኖለት ነበረ፤ ከዚህም የተነሣ “ለሚታዘዙለት ሁሉ የዘላለም መዳን ምክንያት [ሆኗል]።”—ዕብራውያን 5:7, 9፤ ዮሐንስ 12:27, 28
15. መንፈሳዊ እስራኤላውያን ይገባናል ለማይሉት የአምላክ ደግነት ብቁ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ጥረት ያደረጉት ከመቼ ጀምሮ ነበር? ከምንስ ዓላማ ጋር?
15 ጳውሎስ፣ ኢሳይያስ 49:8 ለቅቡዓን ክርስቲያኖች እንደሚሠራ በማመልከት አምላክ በሰጠው በዚህ “የተወደደ ሰዓት” እና “የመዳን ቀን” መልካም ፈቃዱን ባለመሻት ‘ይገባናል የማይሉትን የአምላክ ደግነት በከንቱ እንዳይቀበሉ’ ተማጽኗቸዋል። ጳውሎስ በማከል:- “እነሆ፣ የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤ እነሆ፣ የመዳን ቀን አሁን ነው።” (2 ቆሮንቶስ 6:2) በ33 እዘአ ከዋለው የጰንጠቆስጤ ቀን ጀምሮ መንፈሳዊ እስራኤላውያን “የተወደደው ሰዓት” “የመዳን ቀን” እንዲሆንላቸው ይገባናል የማይሉትን የአምላክ ደግነት ለመቀበል ብቁ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ጥረት አድርገዋል።
“ራሳችንን የአምላክ አገልጋዮች አድርገን እናቀርባለን”
16. ጳውሎስ ራሱን የአምላክ አገልጋይ አድርጎ ያቀረበው በምን ፈታኝ ሁኔታዎች ሥር ነበር?
16 በቆሮንቶስ ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ሰዎች ይገባናል የማይሉትን የአምላክ ደግነት ለመቀበል ብቃት ያላቸው መሆኑን ማረጋገጥ ተስኗቸው ነበር። ምንም እንኳ ጳውሎስ ‘ማሰናከያ የሚሆን አንዳች ነገር ላለመስጠት’ ቢጥርም ሐዋርያዊ ሥልጣኑን ለማበላሸት ሲሉ የጳውሎስን ስም ያጠፉ ነበር። ራሱን የአምላክ አገልጋይ አድርጎ ማቅረቡን ያረጋገጠው “በብዙ መጽናት፣ በመከራ፣ በችግር፣ በጭንቀት፣ በመገረፍ፣ በወኅኒ፣ በሁከት፣ በድካም፣ እንቅልፍ በማጣት፣ በመጦም” ነበር። (2 ቆሮንቶስ 6:3–5) ከጊዜ በኋላ ጳውሎስ ተቃዋሚዎቹ አገልጋዮች ከተባሉ እሱ ብዙ ጊዜ በመታሰር፣ በመደብደብ፣ በአደጋና በእጦት በመሠቃየቱ ከእነሱ እንደሚበልጥ ተናግሯል።—2 ቆሮንቶስ 11:23–27
17. (ሀ) ራሳችንን የአምላክ አገልጋዮች አድርገን ማቅረብ የምንችለው የትኞቹን ባሕርያት በማሳየት ነው? (ለ) ‘የጽድቅ የጦር ዕቃዎች’ የተባሉት ምንድን ናቸው?
17 እንደ ጳውሎስና አጋሮቹ ራሳችንን የአምላክ አገልጋዮች አድርገን ልናቀርብ እንችላለን። እንዴት? “በንጽሕና” እንዲሁም ትክክለኛ ከሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ጋር በሚስማማ መንገድ በመኖር ነው። “በትዕግሥት፣” ስህተትን ወይም የሚያበሳጭ ነገርን ችሎ በማሳለፍ እንዲሁም ‘በደግነት’ ሌሎችን የሚጠቅሙ ነገሮች በማድረግ ራሳችንን እናቀርባለን። ከዚህም በላይ መንፈሱ እንዲመራን በመፍቀድ፣ ‘ግብዝነት የሌለው ፍቅር’ በማሳየት፣ እውነት በመናገርና አገልግሎቱን ለመፈጸም የሚያስችለንን ኃይል ለማግኘት በእሱ በመመካት ራሳችንን የአምላክ አገልጋዮች አድርገን ልናቀርብ እንችላለን። ደስ የሚለው ነገር ጳውሎስ ጭምር ያለውን የአገልግሎት ቦታ ያረጋገጠው “ለቀኝና ለግራ በሚሆን በጽድቅ የጦር ዕቃ” አማካኝነት ነው። በጥንት ዘመን ውጊያ ሲካሄድ አብዛኛውን ጊዜ ቀኝ እጅ ሰይፍ ሲይዝ ግራ እጅ ደግሞ ጋሻ ይይዝ ነበር። ጳውሎስ ከሐሰተኛ አስተማሪዎች ጋር በገጠመው መንፈሳዊ ውጊያ ላይ የኃጢአተኛ ሥጋ የጦር ዕቃ በሆኑት በውሸት፣ በተንኰልና በማታለል አልተጠቀመም። (2 ቆሮንቶስ 6:6, 7፤ 11:12–14፤ ምሳሌ 3:32) እውነተኛ አምልኮን ለማስፋፋት የጽድቅ “የጦር ዕቃ” ወይም ዘዴ ተጠቅሟል። እኛም እንዲህ ልናደርግ ይገባል።
18. የአምላክ አገልጋዮች ከሆንን ምን ዓይነት ጠባይ እናሳያለን?
18 የአምላክ አገልጋዮች ከሆንን ጳውሎስና የሥራ አጋሮቹ እንዳደረጉት ተገቢ ጠባይ እናሳያለን። ሌሎች ቢያከብሩንም ባያከብሩንም በክርስቲያንነታችን የሚጠበቅብንን እናደርጋለን። ስለ እኛ የሚናፈሱ መጥፎ ወሬዎች የስብከት ሥራችንን አያስቆሙትም፤ ስለ እኛ መልካም ቢወራም የምንታበይበት ምክንያት አይኖርም። እውነትን በመናገር በአምላካዊ ሥራዎች ተለይተን የምንታወቅ ልንሆን እንችላለን። አደገኛ በሆነ የጠላት ጥቃት ሥር በምንሆንበት ጊዜ በይሖዋ እንታመናለን። እንዲሁም ተግሣጽ ሲሰጠን በጸጋ እንቀበላለን።—2 ቆሮንቶስ 6:8, 9
19. በመንፈሳዊ ‘ብዙዎችን ባለጠጋ ማድረግ’ የሚቻለው እንዴት ነው?
19 ጳውሎስ ስለ ማስታረቅ አገልግሎት ያቀረበውን ማብራሪያ ሲደመድም “ኀዘንተኞች ስንሆን ዘወትር ደስ ይለናል፤ ድሆች ስንሆን ብዙዎችን ባለ ጠጎች እናደርጋለን፤ አንዳች የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው” በማለት ስለ ራሱና ስለ ባልደረቦቹ ተናግሯል። (2 ቆሮንቶስ 6:10) እነዚያ አገልጋዮች በደረሰባቸው መከራ ምክንያት ቢያዝኑም ውስጣዊ ደስታ ነበራቸው። በቁሳዊ ሁኔታ ሲታይ ድሆች ቢሆኑም ብዙዎችን በመንፈሳዊ ‘ባለ ጠጎች አድርገዋል።’ እምነታቸው በመንፈሳዊ ባለ ጠጎች ስላደረጋቸውና ሌላው ቀርቶ የአምላክ ሰማያዊ ልጆች የመሆን አጋጣሚ ስላስገኘላቸው ‘ሁሉ የእነርሱ ሆኗል።’ እንዲሁም ክርስቲያን አገልጋዮች በመሆን የበለጸገና ደስተኛ ሕይወት አላቸው። (ሥራ 20:35) እኛም እንደ እነሱ በዚህ የመዳን ቀን በማስታረቅ አገልግሎት በመካፈል ‘ብዙዎችን ባለ ጠጎች ማድረግ’ እንችላለን!
በይሖዋ ማዳን ታመኑ
20. (ሀ) የጳውሎስ ልባዊ ፍላጎት ምን ነበር? በከንቱ የሚባክን ጊዜ ያልነበረውስ ለምንድን ነው? (ለ) ይህ የምንኖርበት ዘመን የመዳን ቀን መሆኑን ለይቶ የሚያሳውቀው ምንድን ነው?
20 ጳውሎስ በ55 እዘአ ገደማ ሁለተኛ ደብዳቤውን ለቆሮንቶስ ሰዎች ሲጽፍ የአይሁድ የነገሮች ሥርዓት ሊጠፋ የቀረው ጊዜ ከ15 ዓመታት የማይበልጥ ነበር። ሐዋርያው አይሁዳውያንና አሕዛብ በክርስቶስ አማካኝነት ከአምላክ ጋር እንዲታረቁ ልባዊ ፍላጎት ነበረው። ያ የመዳን ቀን ነበር፤ በከንቱ የሚባክን ጊዜ አልነበረም። እኛም ከ1914 ጀምሮ ተመሳሳይ በሆነ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ ውስጥ እንገኛለን። በአሁኑ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ በመካሄድ ላይ ያለው የመንግሥቱ ስብከት ሥራ ይህ ጊዜ የመዳን ቀን መሆኑን ለይቶ ያሳውቃል።
21. (ሀ) ለ1999 የተመረጠው የዓመት ጥቅስ የትኛው ነው? (ለ) በዚህ የመዳን ቀን ምን ማድረግ አለብን?
21 አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ያዘጋጀውን መዳን በሁሉም ብሔራት ውስጥ የሚገኙ ሕዝቦች መስማት ያስፈልጋቸዋል። ወደ ኋላ የምንልበት ጊዜ የለም። ጳውሎስ “እነሆ፣ የመዳን ቀን አሁን ነው” ሲል ጽፏል። እነዚህ በ2 ቆሮንቶስ 6:2 ላይ የሚገኙት ቃላት የይሖዋ ምሥክሮች የ1999 የዓመት ጥቅስ ይሆናሉ። ከኢየሩሳሌምና ከቤተ መቅደሷ ጥፋት ይበልጥ የከፋ ነገር ከፊታችን ስለሚጠብቀን ጥቅሱ ለጊዜያችን ምንኛ ተስማሚ ነው! በምድር ላይ ያለውን እያንዳንዱን ሰው የሚነካው የዚህ ጠቅላላ የነገሮች ሥርዓት ጥፋት ቀርቧል። እርምጃ መውሰድ ያለብን ነገ ሳይሆን ዛሬውኑ ነው። ማዳን የይሖዋ መሆኑን ካመንን፣ የምንወደውና የዘላለም ሕይወት ለማግኘት የምንፈልግ ከሆነ ይገባናል የማንለውን የአምላክ ደግነት ዓላማ አንስትም። ይሖዋን ለማክበር ባለን ልባዊ ፍላጎት “እነሆ፣ የመዳን ቀን አሁን ነው” ብለን ስንናገር ቃላችንም ሆነ ተግባራችን ከዚህ ጋር የሚስማማ መሆኑን እናረጋግጣለን።
[ምን ብለህ ትመልሳለህ?]
◻ ከአምላክ ጋር መታረቅ እጅግ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
◻ በማስታረቅ አገልግሎት የሚካፈሉት አምባሳደሮችና መልእክተኞች እነማን ናቸው?
◻ ራሳችንን የአምላክ አገልጋዮች አድርገን ማቅረብ የምንችለው እንዴት ነው?
◻ የይሖዋ ምሥክሮች የ1999 የዓመት ጥቅስ ለአንተ ምን ትርጉም ይኖረዋል?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ጳውሎስ እንዳደረገው ሌሎች ከአምላክ ጋር እንዲታረቁ በቅንዓት እየሰበክህና እየረዳህ ነው?
ዩናይትድ ስቴትስ
ፈረንሳይ
ኮት ዲቩዋር
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዚህ የመዳን ቀን ከይሖዋ ጋር ከሚታረቁት ብዙ ሰዎች መካከል ነህን?