ምዕራፍ 8
ይሖዋ ሕዝቡ ንጹሕ እንዲሆኑ ይፈልጋል
“ከንጹሕ ሰው ጋር ንጹሕ ሆነህ ትገኛለህ።”—መዝሙር 18:26
1-3. (ሀ) አንዲት እናት የልጇን ንጽሕና ለመጠበቅ ጥረት የምታደርገው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ሕዝቡ ንጹሕ እንዲሆኑ የሚፈልገው ለምንድን ነው?
አንዲት እናት ልጇን ትምህርት ቤት ለመውሰድ እያዘጋጀችው ነው። ገላውን አጥባ ንጹሕ ልብስ አልብሳዋለች። ንጽሕና ለልጇ ጤንነት በጣም አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም ልጁ ንጹሕ መሆኑ ወላጆቹ በሚገባ እንደሚንከባከቡት ያሳያል።
2 አባታችን ይሖዋ ንጹሕ እንድንሆን ይፈልጋል። (መዝሙር 18:26) ንጽሕናችንን መጠበቃችን እንደሚጠቅመን ያውቃል። ከዚህም ሌላ፣ ንጹሕ መሆናችን ለይሖዋ ክብር ያመጣል።—ሕዝቅኤል 36:22፤ 1 ጴጥሮስ 2:12ን አንብብ።
3 ንጹሕ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው? ንጹሕ መሆናችን የሚጠቅመንስ እንዴት ነው? እስቲ የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ እንመርምር። ይህም በሕይወታችን ውስጥ በአንዳንድ ነገሮች ረገድ ማሻሻያ ማድረግ ያስፈልገን እንደሆነ ለማስተዋል ይረዳናል።
ንጹሕ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?
4, 5. (ሀ) ንጹሕ መሆን ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ለንጽሕና ምን አመለካከት እንዳለው ከፈጠራቸው ነገሮች መረዳት የምንችለው እንዴት ነው?
4 በንጽሕና ረገድ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ የሚሆነን ይሖዋ ራሱ ነው። (ዘሌዋውያን 11:44, 45) ስለዚህ ንጹሕ ለመሆን የሚያነሳሳን ዋነኛው ምክንያት ‘አምላክን ለመምሰል’ ያለን ፍላጎት ነው።—ኤፌሶን 5:1
5 ይሖዋ ለንጽሕና ምን አመለካከት እንዳለው ከፈጠራቸው ነገሮች መረዳት እንችላለን። ይሖዋ በምድራችን ላይ ያለው አየርና ውኃ ምንጊዜም ንጹሕ እንዲሆን ለማድረግ ሲል የተለያዩ ዑደቶችን አዘጋጅቷል። (ኤርምያስ 10:12) የሰው ልጆች ምድርን የሚበክሉ ብዙ ነገሮች ቢያደርጉም ምድር በተለያዩ መንገዶች ራሷን ታጸዳለች። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ በአጉሊ መነፅር ብቻ የሚታዩ ረቂቅ ተሕዋስያንን ፈጥሯል። እነዚህ ተሕዋስያን፣ መርዛማ የሆነውን ቆሻሻ ምንም ጉዳት ወደማያስከትል ነገር የመቀየር አስደናቂ ችሎታ አላቸው። እንዲያውም የሳይንስ ሊቃውንት የአካባቢ ብክለት ያስከተለውን ጉዳት ለማስተካከል በእነዚህ ተሕዋስያን ይጠቀማሉ።—ሮም 1:20
6, 7. ይሖዋ አገልጋዮቹ ንጹሕ እንዲሆኑ እንደሚፈልግ የሙሴ ሕግ የሚያሳየው እንዴት ነው?
6 ይሖዋ በሙሴ በኩል ለእስራኤላውያን የሰጠው ሕግም ንጽሕና ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያጎላል። ለምሳሌ ያህል፣ እስራኤላውያን ለይሖዋ የሚያቀርቡት አምልኮ ተቀባይነት እንዲያገኝ ከፈለጉ አካላዊ ንጽሕናቸውን መጠበቅ ነበረባቸው። በስርየት ቀን ሊቀ ካህናቱ ገላውን ሁለት ጊዜ መታጠብ ይጠበቅበት ነበር። (ዘሌዋውያን 16:4, 23, 24) ሌሎቹ ካህናትም ቢሆኑ መሥዋዕት ከማቅረባቸው በፊት እጃቸውንና እግራቸውን መታጠብ ነበረባቸው። (ዘፀአት 30:17-21፤ 2 ዜና መዋዕል 4:6) እንዲያውም ስለ ንጽሕና የተሰጡትን ሕጎች አለመታዘዝ የሞት ቅጣት ሊያስከትል ይችል ነበር።—ዘሌዋውያን 15:31፤ ዘኁልቁ 19:17-20
7 በዛሬው ጊዜስ? ስለ ይሖዋ መሥፈርቶች ከሙሴ ሕግ ብዙ መማር እንችላለን። (ሚልክያስ 3:6) የይሖዋ አገልጋዮች ንጹሕ መሆን እንዳለባቸው ከሙሴ ሕግ በግልጽ ማየት ይቻላል። የይሖዋ መሥፈርቶች በዚህ ዘመንም አልተለወጡም። በዛሬው ጊዜም ይሖዋ አገልጋዮቹን ንጹሕ እንዲሆኑ ይጠብቅባቸዋል።—ያዕቆብ 1:27
ንጹሕ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው?
8. በየትኞቹ የሕይወታችን ዘርፎች ንጹሕ መሆን ይኖርብናል?
8 ይሖዋ ንጹሕ አድርጎ የሚመለከተን የሰውነታችንን፣ የልብሳችንን እንዲሁም የቤታችንን ንጽሕና ስለጠበቅን ብቻ አይደለም። በሁሉም የሕይወታችን ዘርፎች ንጹሕ መሆን አለብን። ይህም አምልኳችንን፣ ምግባራችንንና ሐሳባችንን ይጨምራል። በእርግጥም ይሖዋ ንጹሕ አድርጎ የሚመለከተን በሁሉም የሕይወታችን ዘርፎች ንጹሕ ከሆንን ብቻ ነው።
9, 10. አምልኳችን ንጹሕ እንዲሆን ምን ማድረግ አለብን?
9 ንጹሕ አምልኮ። ከሐሰት ሃይማኖት ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ ሊኖረን አይገባም። እስራኤላውያን በግዞት ወደ ባቢሎን ተወስደው በነበረበት ወቅት፣ በዙሪያቸው የሚኖሩት ሰዎች በጣዖት አምልኮ ይካፈሉ እንዲሁም በአምልኳቸው ወቅት የሥነ ምግባር ብልግና ይፈጽሙ ነበር። እስራኤላውያን ወደ አገራቸው ተመልሰው ንጹሑን አምልኮ እንደገና እንደሚያቋቁሙ ኢሳይያስ ትንቢት ተናግሮ ነበር። ይሖዋ እነዚህን እስራኤላውያን “ከዚያ ውጡ፤ ማንኛውንም ርኩስ ነገር አትንኩ! ከመካከሏ ውጡ፤ ንጽሕናችሁን ጠብቁ” ብሏቸዋል። እስራኤላውያን ለይሖዋ የሚያቀርቡትን አምልኮ፣ በባቢሎን ከነበሩት የሐሰት ሃይማኖት ትምህርቶችና ልማዶች ጋር ፈጽሞ መቀላቀል አልነበረባቸውም።—ኢሳይያስ 52:11
10 በዛሬው ጊዜ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖችም ከሐሰት ሃይማኖት ይርቃሉ። (1 ቆሮንቶስ 10:21ን አንብብ።) በዓለም ዙሪያ ያሉ በርካታ ተወዳጅ ልማዶችና እምነቶች፣ በሐሰት ሃይማኖት ትምህርቶች ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ለምሳሌ ያህል በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ ሰዎች፣ ሰው ከሞተ በኋላ በሕይወት የምትቀጥል ረቂቅ ነገር በውስጡ እንዳለች ያምናሉ፤ እንደ ፍታት፣ ሣልስት፣ ተዝካርና ሙት ዓመት የመሳሰሉት በአንዳንድ ባሕሎች ውስጥ የሚገኙ ልማዶች በዚህ እምነት ላይ የተመሠረቱ ናቸው። (መክብብ 9:5, 6, 10) ክርስቲያኖች እንዲህ ካሉት ልማዶች መራቅ አለባቸው። የቤተሰባችን አባላት በእነዚህ ልማዶች እንድንካፈል ይጫኑን ይሆናል። እኛ ግን በይሖዋ ፊት ንጹሕ መሆን ስለምንፈልግ እንዲህ ባለው ጫና አንሸነፍም።—የሐዋርያት ሥራ 5:29
11. ምግባራችን ንጹሕ እንዲሆን ምን ማድረግ አለብን?
11 ንጹሕ ምግባር። ይሖዋ ንጹሕ አድርጎ እንዲመለከተን ከፈለግን ከማንኛውም ዓይነት የፆታ ብልግና መራቅ ይኖርብናል። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10ን አንብብ።) ይሖዋ “ከፆታ ብልግና ሽሹ” የሚል ትእዛዝ ሰጥቶናል። (1 ቆሮንቶስ 6:18) በተጨማሪም የፆታ ብልግና የሚፈጽሙ ሰዎች ንስሐ ካልገቡ ‘በአምላክ መንግሥት ምንም ውርሻ እንደሌላቸው’ በግልጽ ነግሮናል።—ኤፌሶን 5:5፤ ተጨማሪ ሐሳብ 22ን ተመልከት።
12, 13. ሐሳባችን ንጹሕ እንዲሆን ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?
12 ንጹሕ ሐሳብ። የምናስበው ነገር ብዙውን ጊዜ በድርጊታችን ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። (ማቴዎስ 5:28፤ 15:18, 19) ሐሳባችን ንጹሕ ከሆነ ድርጊታችንም ንጹሕ ይሆናል። እርግጥ ነው፣ ፍጹማን ስላልሆንን አልፎ አልፎ መጥፎ ሐሳቦች ወደ አእምሯችን ይመጡብናል። በዚህ ጊዜ እነዚህን ሐሳቦች ከአእምሯችን ወዲያውኑ ማውጣት አለብን። እንዲህ የማናደርግ ከሆነ ውሎ አድሮ አእምሯችን ሊበከል ይችላል። በአእምሯችን ውስጥ የሚመላለሱትን ነገሮች ለመፈጸም ልንፈተንም እንችላለን። ይህ እንዳይሆን ከፈለግን አእምሯችንን ንጹሕ በሆኑ ሐሳቦች መሙላት አለብን። (ፊልጵስዩስ 4:8ን አንብብ።) በመሆኑም የሥነ ምግባር ብልግና እንዲሁም ዓመፅ ከሚንጸባረቅባቸው መዝናኛዎች እንርቃለን። ከምናነባቸው፣ ከምንመለከታቸውና ከምናወራቸው ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ጥንቃቄ የተሞላበት ምርጫ እናደርጋለን።—መዝሙር 19:8, 9
13 ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ መኖር ከፈለግን አምልኳችን፣ ምግባራችንና ሐሳባችን ንጹሕ መሆን ይኖርበታል። እርግጥ ነው፣ ይሖዋ አካላዊ ንጽሕናችንን እንድንጠብቅም ይፈልጋል።
አካላዊ ንጽሕናችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?
14. አካላዊ ንጽሕናችንን መጠበቃችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
14 የሰውነታችንንና የአካባቢያችንን ንጽሕና ስንጠብቅ ራሳችንንም ሆነ በዙሪያችን ያሉትን ሰዎች እንጠቅማለን። ለራሳችን ጥሩ ስሜት ይኖረናል፤ ሌሎችም ከእኛ ጋር መሆን ያስደስታቸዋል። ይሁንና አካላዊ ንጽሕናችንን ለመጠበቅ የሚያነሳሳን ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ ምክንያት አለ። ንጹሕ መሆናችን ይሖዋን ያስከብረዋል። አንድን ልጅ ባገኘኸው ቁጥር ቆሽሾ የምታየው ቢሆን ‘ምን ዓይነት ወላጆች ቢኖሩት ነው?’ ብለህ ማሰብህ አይቀርም። በተመሳሳይ እኛም ንጽሕናችንን የማንጠብቅና የምንዝረከረክ ከሆነ ይሖዋን አናስከብርም። ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “አገልግሎታችን እንከን እንዳይገኝበት በምንም መንገድ ማሰናከያ እንዲኖር አናደርግም፤ ከዚህ ይልቅ በሁሉም ነገር ራሳችንን ብቁ የአምላክ አገልጋዮች አድርገን እናቀርባለን።”—2 ቆሮንቶስ 6:3, 4
15, 16. አካላዊ ንጽሕናችንን ለመጠበቅ ምን ማድረግ እንችላለን?
15 አካላችንና ልብሳችን። ንጽሕናችንን መጠበቅ በየዕለቱ ከምናከናውናቸው ነገሮች አንዱ መሆን አለበት። ለምሳሌ ያህል፣ አዘውትረን ከተቻለም በየቀኑ ሰውነታችንን እንታጠባለን። በተለይ ደግሞ ምግብ ከማብሰላችን ወይም ከመመገባችን በፊት እጃችንን በሳሙናና በውኃ መታጠብ አለብን፤ መጸዳጃ ቤት ከተጠቀምን ወይም ቆሻሻ ነገር ከነካንም እጃችንን የግድ መታጠብ ይኖርብናል። እጅን መታጠብ ትልቅ ነገር ላይመስል ይችላል፤ ሆኖም ባክቴሪያና በሽታ እንዳይዛመት ለማድረግ የሚረዳ ወሳኝ መንገድ ነው። እጅን መታጠብ ሕይወታችንንም ሊያድንልን ይችላል። መጸዳጃ ቤት ወይም የፍሳሽ ማስወገጃ ባይኖረን እንኳ ቆሻሻ የምናስወግድባቸው ሌሎች መንገዶች መፈለግ እንችላለን። የጥንቶቹ እስራኤላውያን የቆሻሻ ማስወገጃ መስመር አልነበራቸውም፤ በመሆኑም ከሰዎች መኖሪያና ከውኃ ምንጮች ርቀው ከተጸዳዱ በኋላ ቆሻሻውን ይቀብሩት ነበር።—ዘዳግም 23:12, 13
16 ልብሶቻችንም ቢሆን ውድ፣ በጣም ያጌጡ ወይም የዘመኑን ፋሽን የተከተሉ መሆን አለባቸው ማለት አይደለም። ሆኖም ሥርዓታማና ንጹሕ ሊሆኑ ይገባል። (1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10ን አንብብ።) አለባበሳችን ምንጊዜም ይሖዋን የሚያስከብር እንዲሆን እንፈልጋለን።—ቲቶ 2:10
17. ቤታችንንና አካባቢያችንን በንጽሕና መያዝ ያለብን ለምንድን ነው?
17 ቤታችንና አካባቢያችን። የምንኖረው የትም ይሁን የት ቤታችን ምንጊዜም ንጹሕ መሆን አለበት። በተጨማሪም መኪና፣ ብስክሌት ወይም ሌላ ተሽከርካሪ ካለን በንጽሕና ልንይዘው ይገባል፤ በተለይ ደግሞ ወደ ስብሰባዎች ስንሄድ ወይም አገልግሎት ስንወጣ ተሽከርካሪያችን ንጹሕ መሆኑን ማረጋገጣችን አስፈላጊ ነው። ደግሞም ለሰዎች የምንሰብከው ወደፊት ንጹሕ በሆነች ገነት ውስጥ የመኖር ተስፋ እንዳለን ነው። (ሉቃስ 23:43፤ ራእይ 11:18) ቤታችንንና አካባቢያችንን የምንይዝበት መንገድ፣ ንጹሕ በሆነ አዲስ ዓለም ውስጥ ለመኖር ከአሁኑ እየተዘጋጀን መሆኑን ያሳያል።
18. የአምልኮ ቦታችን ንጹሕ እንዲሆን ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?
18 የአምልኮ ቦታችን። የጉባኤም ሆነ የትላልቅ ስብሰባ አዳራሾቻችንን በንጽሕና በመያዝ ለንጽሕና ትልቅ ቦታ እንደምንሰጥ እናሳያለን። ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ስብሰባ አዳራሾቻችን ሲመጡ ትኩረታቸውን የሚስበው የቦታው ንጽሕና ነው። ይህ ደግሞ ይሖዋን ያስከብረዋል። የጉባኤው አባላት የሆንን በሙሉ የስብሰባ አዳራሹን የማጽዳትና ጥሩ አድርጎ የመያዝ መብት አለን።—2 ዜና መዋዕል 34:10
የሚያረክሱ ልማዶችን ማስወገድ
19. ከየትኞቹ ልማዶች መራቅ አለብን?
19 መጽሐፍ ቅዱስ ልናስወግዳቸው የሚገቡ መጥፎ ልማዶችን ሁሉ በዝርዝር ባያስቀምጥም ይሖዋ ስለ እነዚህ ልማዶች ያለውን አመለካከት ለማወቅ የሚረዱ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ይዟል። ይሖዋ ማጨስን፣ ከመጠን በላይ መጠጣትን እንዲሁም ጫት መቃምንና ሌሎች ዕፆች መውሰድን ይጠላል። የአምላክ ወዳጆች ከሆንን ከእነዚህ ልማዶች እንርቃለን። ለምን? ከአምላክ ላገኘነው የሕይወት ስጦታ ልባዊ አድናቆት ስላለን ነው። እንዲህ ያሉት ልማዶች የራሳችንንም ሆነ የሌሎችን ጤንነት ሊጎዱና ዕድሜያችንን ሊያሳጥሩት ይችላሉ። ብዙ ሰዎች ከመጥፎ ልማዶች ለመራቅ ጥረት የሚያደርጉት ለጤንነታቸው ሲሉ ነው። እኛ ግን የይሖዋ ወዳጆች እንደመሆናችን መጠን ከመጥፎ ልማዶች ለመራቅ የሚያነሳሳን ከሁሉ የላቀ ምክንያት አለን፤ ይህም ለአምላክ ያለን ፍቅር ነው። አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “በይሖዋ እርዳታ ከሱሶቼ ሁሉ ተላቅቄ ንጹሕ ሕይወት መኖር ጀመርኩ። . . . በይሖዋ እርዳታ ባይሆን ኖሮ እነዚህን ለውጦች ማድረግ እንደማልችል ይሰማኛል።” ጎጂ ልማዶችን ለማስወገድ የሚረዱ አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እስቲ እንመልከት።
20, 21. ይሖዋ ከምን ዓይነት ልማዶች እንድንርቅ ይፈልጋል?
20 “የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ እነዚህ ተስፋዎች ስላሉን ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን እናንጻ፤ እንዲሁም አምላክን በመፍራት ቅድስናችንን ፍጹም እናድርግ።” (2 ቆሮንቶስ 7:1) ይሖዋ አእምሯችንንም ሆነ አካላችንን ከሚያረክሱ ጎጂ የሆኑ ልማዶች እንድንርቅ ይፈልጋል።
21 “ከሚያረክስ ነገር ሁሉ” ራሳችንን እንድናነጻ የሚያነሳሳን ዋነኛ ምክንያት በ2 ቆሮንቶስ 6:17, 18 ላይ ተገልጿል። ይሖዋ ‘ርኩስ የሆነውን ነገር አትንኩ’ ብሎናል። ከዚያም “እኔም እቀበላችኋለሁ። እኔ አባት እሆናችኋለሁ፤ እናንተ ደግሞ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ትሆኑኛላችሁ” በማለት ቃል ገብቶልናል። በእርግጥም፣ ከሚያረክሰን ወይም በእሱ ፊት ንጹሕ እንዳንሆን ከሚያደርገን ከማንኛውም ነገር ከራቅን ይሖዋ ልክ እንደ አባት ይወደናል።
22-25. ጎጂ ልማዶችን ለማስወገድ የሚረዱን የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ናቸው?
22 “አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ አእምሮህ ውደድ።” (ማቴዎስ 22:37) ይህ ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ ነው። (ማቴዎስ 22:38) ይሖዋን በሙሉ ልባችን፣ ነፍሳችንና አእምሯችን ልንወደው ይገባል። ለአምላክ እንዲህ ዓይነት ፍቅር አለን እያልን ሕይወታችንን የሚያሳጥር ወይም አእምሯችንን የሚጎዳ ነገር ብናደርግ ውሸት ይሆንብናል። ከዚህ በተቃራኒ፣ ከአምላክ ላገኘነው ሕይወት አክብሮት እንዳለን በሚያሳይ መንገድ ለመኖር ጥረት ማድረግ ይኖርብናል።
23 “ሕይወትንና እስትንፋስንም ሆነ ማንኛውንም ነገር ለሰው ሁሉ የሚሰጠው [ይሖዋ ነው]።” (የሐዋርያት ሥራ 17:24, 25) አንድ ጓደኛህ ግሩም ስጦታ ቢሰጥህ ስጦታውን እንደማትጥለው ወይም እንደማታበላሸው የታወቀ ነው። ሕይወት ከይሖዋ ያገኘነው ግሩም ስጦታ ነው። ይህን ስጦታ ከልባችን እናደንቃለን። ስለዚህ ሕይወታችንን እሱን በሚያስከብር መንገድ ልንጠቀምበት እንፈልጋለን።—መዝሙር 36:9
24 “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ።” (ማቴዎስ 22:39) መጥፎ ልማዶች ካሉን የምንጎዳው እኛ ብቻ አይደለንም። የምንወዳቸውን ሰዎች ጨምሮ አብረውን የሚሆኑ ሰዎችም መጎዳታቸው አይቀርም። ለምሳሌ፣ አጫሽ ከሆነ ግለሰብ ጋር የሚኖሩ ሰዎች እነሱ ባያጨሱ እንኳ ለትንባሆ ጭስ በመጋለጣቸው ብቻ ለከባድ የጤና ችግሮች ሊዳረጉ ይችላሉ። እነዚህን መጥፎ ልማዶች ስናስወግድ ግን አብረውን ላሉት ሰዎች ፍቅር እንዳለን እናሳያለን።—1 ዮሐንስ 4:20, 21
25 “ለመንግሥታትና ለባለሥልጣናት እንዲገዙና እንዲታዘዙ . . . አሳስባቸው።” (ቲቶ 3:1) በብዙ አገሮች ውስጥ አንዳንድ ዕፆችን ይዞ መገኘት ወይም መውሰድ በሕግ የተከለከለ ነው። ይሖዋ መንግሥታትን እንድናከብር ስለሚጠብቅብን እነዚህን ሕጎች እንታዘዛለን።—ሮም 13:1
26. (ሀ) አምልኳችን በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ከፈለግን ምን ማድረግ አለብን? (ለ) ንጹሕ ሆነን ለመኖር የቻልነውን ያህል ጥረት የምናደርገው ለምንድን ነው?
26 የይሖዋ ወዳጆች መሆን ከፈለግን በሕይወታችን ውስጥ በአንዳንድ ነገሮች ረገድ ማሻሻያ ማድረግ ያስፈልገን ይሆናል። ይህን ካስተዋልን ወዲያውኑ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። በእርግጥ የሚያረክሱ ልማዶችን ማስወገድ ቀላል ላይሆን ይችላል፤ ሆኖም የማይቻል ነገር አይደለም። ይሖዋ እንደሚረዳን ቃል ገብቷል። “የሚጠቅምህን ነገር የማስተምርህ፣ ልትሄድበትም በሚገባህ መንገድ የምመራህ እኔ ይሖዋ አምላክህ ነኝ” ብሏል። (ኢሳይያስ 48:17) ንጹሕ ሆነን ለመኖር የቻልነውን ያህል ጥረት ካደረግን ለአምላካችን ክብር እናመጣለን።