“እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳል”
ለጋስ በመሆን ረገድ ይሖዋ ፍጹም ምሳሌ ነው። በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ እሱ ‘የበጎ ስጦታ ሁሉ የፍጹምም በረከት ሁሉ’ ምንጭ መሆኑን ይናገራል። (ያዕቆብ 1:17) ለምሳሌ ያህል አምላክ የፈጠራቸውን ነገሮች ተመልከት። ይሖዋ የፈጠራቸው ለምግብነት የሚሆኑ ነገሮች ግሩም ጣዕም ያላቸው ናቸው እንጂ እንዲሁ ጣዕም የለሽ አይደሉም፤ አበቦችን ብንመለከት በኅብረ ቀለማት ያሸበረቁና ታይተው የማይጠገቡ ናቸው እንጂ የሚሰለቹ አይደሉም፤ የፀሐይ መጥለቅ በጣም አስደናቂ ክስተት ነው እንጂ እንዲሁ ምንም ስሜት የማይሰጥ ነገር አይደለም። አዎን፣ እያንዳንዱ የይሖዋ የፍጥረት ሥራ የፍቅሩና የለጋስነቱ ማስረጃ ነው። (መዝሙር 19:1, 2፤ 139:14) ከዚህም በላይ ይሖዋ የሚሰጠው በደስታ ነው። ለአገልጋዮቹ ጥሩ ነገር ማድረግ ያስደስተዋል።—መዝሙር 84:11፤ 149:4
እስራኤላውያን እርስ በርሳቸው ባላቸው ግንኙነት የአምላክን የለጋስነት ባሕርይ እንዲያንጸባርቁ ታዝዘው ነበር። “ልብህን አታጽና፣ በድሀው ወንድምህ ላይ እጅህን አትጨብጥ” ሲል ሙሴ ነግሯቸዋል። “ፈጽመህ ስጠው፣ በሰጠኸውም ጊዜ በልብህ አትጸጸት።” (ዘዳግም 15:7, 10) የመስጠት ፍላጎት የሚመነጨው ከልብ ስለሆነ እስራኤላውያን ለጋስ በመሆን ደስታ ያገኙ ነበር።
ክርስቲያኖችም ተመሳሳይ ምክር ተሰጥቷቸዋል። በእርግጥም ኢየሱስ “የሚሰጥ ብፁዕ ነው” ሲል ተናግሯል። (ሥራ 20:35) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በደስታ በመስጠት ረገድ ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ በኢየሩሳሌም የነበሩ አማኝ የሆኑ ሰዎች “መሬታቸውንና ጥሪታቸውንም እየሸጡ፣ ማንኛውም እንደሚፈልግ ለሁሉ ያካፍሉት ነበር” በማለት ይዘግባል።—ሥራ 2:44, 45
ይሁን እንጂ ለጋስ የነበሩ እነዚህ የይሁዳ ነዋሪዎች ከጊዜ በኋላ ደኸዩ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት ድህነት ላይ ሊወድቁ እንደቻሉ በቀጥታ አይነግረንም። አንዳንድ ምሁራን መንስኤው በሥራ 11:28, 29 ላይ የተጠቀሰው ረሃብ ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ። ያም ሆነ ይህ በይሁዳ ያሉ ክርስቲያኖች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይገኙ የነበረ ሲሆን ሐዋርያው ጳውሎስ ደግሞ የሚያስፈልጓቸው ነገሮች እንዲሟሉላቸው ፈልጓል። ታዲያ ይህን ማድረግ የሚችለው እንዴት ነው?
ችግር ለደረሰባቸው የሚሆን ገንዘብ ማሰባሰብ
ጳውሎስ እንደ መቄዶንያ ርቀው ለሚገኙ ጉባኤዎች ሳይቀር የእርዳታ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን በይሁዳ ለሚኖሩ ችግር ለደረሰባቸው ክርስቲያኖች የገንዘብ መዋጮ እንዲደረግ ዝግጅት አድርጓል። ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፎላቸዋል:- “ለገላትያ አብያተ ክርስቲያናት እንደ ደነገግሁት እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ። . . . ከእናንተ እያንዳንዱ በየሳምንቱ በፊተኛው ቀን እንደ ቀናው መጠን እያስቀረ በቤቱ ያስቀምጥ።”a—1 ቆሮንቶስ 16:1, 2
ጳውሎስ የተዋጣው ገንዘብ በአፋጣኝ በኢየሩሳሌም ወዳሉት ወንድሞች እንዲላክ አቅዶ ነበር። ሆኖም የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ጳውሎስ ለሰጠው መመሪያ ቶሎ ምላሽ አልሰጡም። ለምን? በይሁዳ በሚገኙ ወንድሞቻቸው ላይ የደረሰባቸው መከራ ምንም ግድ አልሰጣቸውም ማለት ነውን? አይደለም፣ ጳውሎስ የቆሮንቶስ ሰዎች ‘በነገር ሁሉ፣ በእምነትና በቃል በእውቀትም በትጋትም ሁሉ የተትረፈረፉ’ መሆናቸውን ያውቅ ነበር። (2 ቆሮንቶስ 8:7) ምናልባትም ጳውሎስ በመጀመሪያ ደብዳቤው ላይ የጻፈላቸውን አስፈላጊ ነገሮች በሥራ ለማዋል ሲጥሩ ጊዜያቸው በጣም ተጣብቦ ይሆናል። ሆኖም አሁን በኢየሩሳሌም ያለው ሁኔታ ጊዜ የማይሰጥ ነበር። በመሆኑም ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው ሁለተኛ ደብዳቤው ላይ ስለ ጉዳዩ አንስቷል።
ልግስና ማሳየትን በተመለከተ የቀረበ ጥሪ
ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በመጀመሪያ የነገራቸው የመቄዶንያ ሰዎች ለእርዳታ ማሰባሰብ ጥረቱ ስለሰጡት በምሳሌነት የሚጠቀስ አፋጣኝ ምላሽ ነበር። ጳውሎስ “እነርሱ ብዙ መከራና ፈተና ደርሶባቸዋል፤ ይሁን እንጂ ደስታቸው ታላቅ ስለሆነ ምንም እንኳ በጣም ድኾች ቢሆኑ ከፍ ያለ ልግስና አድርገዋል” በማለት ጽፏል። የመቄዶንያ ሰዎች መጎትጎት አላስፈለጋቸውም። ከዚህ ይልቅ ጳውሎስ “የመርዳት ዕድል እንዳይነፈጋቸውም አጥብቀው ለመኑን” ብሏል። የመቄዶንያ ሰዎች በደስታ ልግስና ያሳዩት እነሱ ራሳቸው “በጣም ድኾች” ሆነው እያሉ መሆኑን ማወቃችን ነገሩን ይበልጥ አስገራሚ ያደርገዋል።—2 ቆሮንቶስ 8:2–4 የ1980 ትርጉም
ጳውሎስ የመቄዶንያን ሰዎች በማወደስ በቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ላይ የፉክክር መንፈስ ለማሳደር መሞከሩ ነበርን? በጭራሽ፤ ምክንያቱም እንዲህ ማድረግ ሰዎችን ለማነሳሳት የሚረዳ ትክክለኛው መንገድ አለመሆኑን ያውቃል። (ገላትያ 6:4) ከዚህም በላይ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ትክክለኛውን ነገር እንዲያደርጉ የሚገፋፋቸው ሰው የሚያስፈልጋቸው እንዳልነበሩ ያውቃል። ከዚህ ይልቅ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የይሁዳ ወንድሞቻቸውን ከልብ እንደሚወዷቸውና ለሚሰባሰበው እርዳታ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ትምክህት ነበረው። “ከአምና ጀምራችሁ ለማድረግ ብቻ ያይደለ ነገር ግን ለማሰብ ደግሞ አስቀድማችሁ የጀመራችሁት [እናንተ ነበራችሁ]” ሲል ነግሯቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 8:10) እንዲያውም በእርዳታ ማሰባሰብ ጥረቱ አንዳንድ ዘርፍ ረገድ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ራሳቸው ጥሩ ምሳሌ ነበሩ። ጳውሎስ “በጎ ፈቃዳችሁን አውቄአለሁና፤ . . . ለመቄዶንያ ሰዎች በእናንተ እመካለሁ” ሲል የነገራቸው ሲሆን አክሎም “ቅንዓታችሁም የሚበዙትን አነሣሥቶአል” ብሎ ነግሯቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 9:2 በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) አሁን ግን የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ፈቃደኝነታቸውንና ቅንዓታቸውን በሥራ መተርጎም አስፈልጓቸዋል።
በዚህ ምክንያት ጳውሎስ እንዲህ ሲል ነግሯቸዋል:- “እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ፣ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም።” (2 ቆሮንቶስ 9:7) አንድ ሰው ግፊት የሚደረግበት ከሆነ በደስታ ሊሰጥ ስለማይችል ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን ሊጫናቸው አልፈለገም። ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው ጳውሎስ እያንዳንዳቸው ለመስጠት አስቀድሞም አስበው እንደነበር ስለተናገረ ድሮውንም ትክክለኛ ግፊት እንዳላቸው ገምቷል። ከዚህም በተጨማሪ ጳውሎስ እንዲህ ብሏቸዋል:- “በጎ ፈቃድ ቢኖር፣ እንዳለው መጠን የተወደደ ይሆናል እንጂ እንደሌለው መጠን አይደለም።” (2 ቆሮንቶስ 8:12) አዎን በጎ ፈቃድ ሲኖር ማለትም አንድ ሰው ለመስጠት የተነሳሳው በፍቅር በሚሆንበት ጊዜ መጠኑ ምንም ያህል ትንሽ መስሎ ቢታይም ስጦታው በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያገኛል።—ከሉቃስ 21:1–4 ጋር አወዳድር።
በዛሬው ጊዜ ያሉ ደስተኛ ሰጪዎች
በይሁዳ ያሉ ክርስቲያኖችን ለመደገፍ የተደረገው እርዳታ የማሰባሰብ እንቅስቃሴ ለዘመናችን የሚሆን ጥሩ ምሳሌ ይዟል። የይሖዋ ምሥክሮች በመንፈሳዊ ለተራቡ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ምግብ በማቅረብ ዓለም አቀፍ የሆነ የስብከት ዘመቻ እያካሄዱ ነው። (ኢሳይያስ 65:13, 14) ይህን የሚያደርጉት የሚከተለውን የኢየሱስ መመሪያ በመታዘዝ ነው:- “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ . . . ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።”—ማቴዎስ 28:19, 20
ይህን ተልዕኮ መወጣት ቀላል ሥራ አይደለም። ይህ ሥራ በዓለም ዙሪያ የሚስዮናውያን ቤቶችን መሥራትና ከአንድ መቶ በላይ ቅርንጫፍ ቢሮዎችን መክፈት የሚጠይቅ ሆኗል። ከዚህም በተጨማሪ የይሖዋ አምላኪዎች ለመሰብሰብና እርስ በርሳቸው ለመተናነጽ የሚችሉባቸውን አመቺ ቦታዎች እንዲያገኙ የመንግሥት አዳራሾችንና የትልልቅ ስብሰባ አዳራሾችን መገንባት ይጨምራል። (ዕብራውያን 10:24, 25) አንዳንድ ጊዜም የይሖዋ ምሥክሮች በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው አካባቢዎች አስቸኳይ እርዳታ ያቀርባሉ።
እንዲሁም ለኅትመት የሚወጣውን ከፍተኛ ወጪ አስብ። በእያንዳንዱ ሳምንት በአማካኝ ከ22,000,000 በላይ የመጠበቂያ ግንብ ቅጂዎች ወይም ወደ 20,000,000 የሚጠጉ የንቁ! መጽሔት ቅጂዎች ይታተማሉ። በቋሚነት ከሚቀርበው ከዚህ መንፈሳዊ ምግብ በተጨማሪ በየዓመቱ በሚልዮን የሚቆጠሩ መጻሕፍት፣ ብሮሹሮች፣ የቴፕና የቪዲዮ ክሮች ይዘጋጃሉ።
ይህ ሁሉ ሥራ የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኘው እንዴት ነው? በፈቃደኝነት በሚሰጡ መዋጮዎች ነው። እነዚህ መዋጮዎች የሚደረጉት የሰዎችን ትኩረት ለመሳብ ወይም በራስ ወዳድነት ላይ በተመሠረተ ግፊት ሳይሆን እውነተኛውን አምልኮ ለማስፋፋት ነው። ይህም በመሆኑ እንዲህ ዓይነቱ ልግስና ለሰጪው ደስታ ከማምጣቱም በላይ የአምላክን በረከት ያስገኛል። (ሚልክያስ 3:10፤ ማቴዎስ 6:1–4) ሌላው ቀርቶ በይሖዋ ምሥክሮች መካከል የሚገኙ ልጆች ጭምር ለጋስ በመሆን በደስታ የሚሰጡ መሆናቸውን ያሳያሉ። ለምሳሌ ያህል የአራት ዓመቷ አሊሰን በአንድ የዩናይትድ ስቴትስ ክፍል ላይ ከባድ አውሎ ነፋስ ጉዳት ማስከተሉን ስትሰማ 2 ዶላር አስተዋጽኦ አድርጋለች። “ሳንቲሞችን በማጠራቅምበት ሣጥኔ ውስጥ የነበረኝ ገንዘብ በሙሉ ይኸው ነበር” ስትል ጽፋለች። “ልጆቹ የነበሯቸው መጫወቻዎች፣ መጻሕፍትና አሻንጉሊቶች በሙሉ እንደጠፉባቸው ይሰማኛል። ምናልባትም በዚህ ገንዘብ የኔ እኩያ ለምትሆን አንዲት ትንሽ ልጅ መጽሐፍ መግዛት ትችሉ ይሆናል።” የስምንት ዓመቱ ማክሌን ከወንድሞች መካከል በዓውሎ ነፋሱ ሳቢያ ሕይወቱን ያጣ ባለመኖሩ የተሰማውን ደስታ በጽሑፍ ገልጿል። አክሎም “ከአባቴ ጋር ሆኜ የቸርኪዮ ክዳን በመሸጥ 17 የአሜሪካ ዶላር አጠራቅሜ ነበር። በዚህ ገንዘብ አንድ ነገር ለመግዛት አስቤ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን አደጋ ለደረሰባቸው ወንድሞች ብሰጥ የተሻለ እንደሆነ ተሰማኝ።”—በተጨማሪ ከላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት።
በእርግጥም ልጆችም ሆኑ አዋቂዎች ‘እሱን ከሀብታቸው በማክበር’ የመንግሥቱን ጥቅሞች ሲያስቀድሙ ማየቱ የይሖዋን ልብ ያስደስታል። (ምሳሌ 3:9, 10) እርግጥ ነው ሁሉ ነገር የእሱ ስለሆነ ማንም ሰው በመስጠት ይሖዋን ባለጸጋ ሊያደርገው እንደማይችል የታወቀ ነው። (1 ዜና መዋዕል 29:14–17) ሆኖም ሥራውን መደገፍ አንድ የይሖዋ አምላኪ ለእሱ ያለውን ፍቅር መግለጽ የሚያስችለው መብት ነው። በዚህ መንገድ ልቡ አነሳስቶት አስተዋጽኦ ለሚያደርግ ማንኛውም ሰው ልባዊ ምስጋናችንን እንገልጻለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ምንም እንኳ ጳውሎስ “እንደ ደነገግሁት” ብሎ ቢናገርም፣ በራሱ አነሳሽነት የግድ እንዲያዋጡ ደንግጓል ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ በርካታ ጉባኤዎች የሚያደርጉትን መዋጮ በበላይነት ይቆጣጠር ነበር ማለት ነው። ከዚህም በተጨማሪ ጳውሎስ እያንዳንዱ ሰው “በቤቱ” የሚሰጠው “እንደ ቀናው መጠን” እንዲሆን ተናግሯል። በሌላ አነጋገር ማንኛውም መዋጮ የሚደረገው በግል፣ በራስ አነሳሽነት ነበር። ማንም ሰው መዋጮ እንዲያደርግ አይገደድም ነበር።
[በገጽ 26, 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
አንዳንዶች ለዓለም አቀፉ ሥራ መዋጮ የሚያደርጉባቸው መንገዶች
ብዙዎች “ለማኅበሩ ዓለም አቀፍ ሥራ የሚደረግ መዋጮ—ማቴዎስ 24:14” ተብሎ የተለጠፈባቸው ሣጥኖች ውስጥ የሚጨምሩትን የተወሰነ የገንዘብ መጠን ይመድባሉ ወይም ወጪ ያደርጋሉ። ጉባኤዎች ይህን ገንዘብ በየወሩ በብሩክሊን ኒው ዮርክ ወዳለው ዋና መሥሪያ ቤት ወይም በአካባቢው ወደሚገኝ ቅርንጫፍ ቢሮ ይልካሉ።
በፈቃደኛነት የሚደረጉ የገንዘብ እርዳታዎች በቀጥታ Treasurer’s Office, Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania, 25 Columbia Heights, Brooklyn, New York 11201-2483 በሚለው አድራሻ ወይም በአገርህ ወደሚገኝ የማኅበሩ ቅርንጫፍ ቢሮ መላክ ይቻላል። ጌጣጌጦችን ወይም ሌሎች ውድ ዕቃዎችንም በእርዳታ መስጠት ይቻላል። የተላከው ነገር ስጦታ መሆኑን የሚገልጽ አጭር ደብዳቤ አብሮ መላክ ይኖርበታል።
ተመላሽ ሊሆን የሚችል ገንዘብ ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት
አንድ ሰው ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የሰጠውን ገንዘብ ሊጠቀምበት በሚፈልግበት ጊዜ ሊመለስለት የሚያስችል ልዩ ዝግጅት በማድረግ ለማኅበሩ ሊሰጥ ይችላል። ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ከላይ በተገለጸው አድራሻ መጠየቅ ይቻላል።
በእቅድ የሚደረግ ስጦታ
ለማኅበሩ በቀጥታ የገንዘብ ስጦታ ከመለገስና ተመላሽ ሊሆን የሚችል ገንዘብ ከመስጠት በተጨማሪም በመላው ዓለም የሚካሄደውን የመንግሥት አገልግሎት ለመደጎም መስጠት የሚቻልባቸው ሌሎች መንገዶችም አሉ። ከእነዚህ አንዳንዶቹ:-
ኢንሹራንስ:- የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የአንድ የሕይወት ዋስትና ኢንሹራንስ ፖሊሲ ወይም የጡረታ ክፍያ ተጠቃሚ እንዲሆን ስም ሊዛወርለት ይችላል።
የባንክ ሒሳብ:- የአገሩ ባንክ በሚፈቅደው መሠረት የባንክ ሒሳቦች፣ ገንዘብ መቀመጡን የሚገልጽ የምሥክር ወረቀት ወይም የግል ጡረታ ሒሳቦች በአደራ ወይም በሞት ጊዜ የሚከፈል መሆኑ ተገልጾ ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ሊሰጥ ይችላል።
አክሲዮኖችና ቦንዶች:- አክሲዮኖችና ቦንዶች እንዳለ በስጦታ መልክም ሆነ ገቢው ለሰጪው ያለ ማቋረጥ የሚከፈልበት ዝግጅት ተደርጎ ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በእርዳታ መልክ መስጠት ይቻላል።
የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች:- ሊሸጡ የሚችሉ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች እንዳለ በስጦታነት ወይም ሰጪው በሕይወት እስካለ ድረስ በንብረቱ በመተዳደር እንዲቀጥል መብቱን በማስጠበቅ ለማኅበሩ በእርዳታ መስጠት ይቻላል። አንድ ሰው ማንኛውንም የማይንቀሳቀስ ንብረት ለማኅበሩ ከማስተላለፉ በፊት ከማኅበሩ ጋር መገናኘት ይኖርበታል።
ኑዛዜዎችና አደራዎች:- ንብረት ወይም ገንዘብ በሕግ ፊት ተፈጻሚነት ባለው ኑዛዜ አማካኝነት ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በውርሻ ሊሰጥ ወይም ማኅበሩ በአደራ የተሰጠው ንብረት ተጠቃሚ ተደርጎ ስሙ ሊዘዋወር ይችላል። አንድ የሃይማኖት ድርጅት እንዲጠቀምበት በአደራ የተሰጠ ንብረት በቀረጥ ረገድ አንዳንድ ጥቅሞች አሉት።
“በእቅድ የሚደረግ ስጦታ” የሚለው ሐረግ እንደሚያመለክተው እነዚህን የመሳሰሉ መዋጮዎች በሰጪው በኩል በትንሹም ቢሆን እቅድ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ያሳያሉ። ማኅበሩን በእቅድ በሚደረግ ስጦታ ለመደጎም ለሚፈልጉ ግለሰቦች የዓለም አቀፉን የመንግሥት አገልግሎት ለመደጎም በእቅድ የሚደረግ ስጦታ የሚል ብሮሹር አዘጋጅቷል። ይህ ብሮሹር የተዘጋጀው ስጦታዎችን፣ ኑዛዜዎችንና አደራዎችን በተመለከተ ማኅበሩ ለቀረቡለት ብዛት ያላቸው ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ነው። ብሮሹሩ ንብረትን፣ የገንዘብ አጠቃቀምንና የቀረጥ ምጣኔን አስመልክቶ ጠቃሚ የሆኑ ተጨማሪ መረጃዎችን የያዘ ከመሆኑም በተጨማሪ በዩናይትድ ስቴትስ ለሚኖሩና በዓለም ዙሪያ የሚካሄደውን የመንግሥቱን ፍላጎት ለመደጎም ፍላጎት ያላቸውን ግለሰቦች የቤተሰባቸውና የግል ሁኔታቸው የሚፈቅድላቸውን ጠቃሚና ውጤታማ ዘዴ ለመምረጥ እንዲችሉ ታስቦ የተዘጋጀ ነው።
ይህን ብሮሹር በማንበብና በእቅድ የሚደረግ ስጦታ ዴስክ ላይ ከሚሠሩት ወንድሞች ምክር በመጠየቅ ብዙዎች ማኅበሩን ለመርዳት ከመቻላቸውም በላይ ከቀረጥ ቅናሽ የሚገኘውን ጥቅም ከፍ ለማድረግ ችለዋል። በእቅድ የሚደረግ ስጦታ ዴስክ እነዚህን ዝግጅቶች የሚመለከት ማንኛውንም ሰነድ ማግኘትና ስለ ጉዳዩ እንዲነገረው ያስፈልጋል። ብሮሹሩን ለማግኘት ወይም ከእነዚህ በእቅድ የሚደረጉ ስጦታዎች በአንዱ ለመካፈል የሚፈልጉ ከታች ያለውን አድራሻ ተጠቅመው ወይም በአገራችሁ ወዳለው የማኅበሩ ቢሮ በመጻፍ ወይም በመደወል ማሳወቅ አለባቸው።
Planned Giving Desk
Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
100 Watchtower Drive, Patterson, New York 12563-9204
ስልክ:- (914) 878-7000
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ልጆችም ደስተኛ ሰጪዎች ናቸው!
ተጨማሪ መጻሕፍት እንድታዘጋጁልን ይህን ልሰጣችሁ እፈልጋለሁ። አባቴን በሥራ ረድቼ ያጠራቀምኩት ገንዘብ ነው። ብዙ ስለምትደክሙልን ላመሰግናችሁ እወዳለሁ።—የሰባት ዓመቷ ፓሜላ
ተጨማሪ የመንግሥት አዳራሾች እንዲሠሩ ለማገዝ 49 ብር ልኬላችኋለሁ። ገንዘቡን ያገኘሁት ባለፈው ክረምት መንገድ ላይ የሎሚ ጭማቂ ሸጬ ነው።—የስድስት ዓመቷ ሴሌና
አንዲት ዶሮ አሳድግ ነበር። እሷም የፈለፈለቻቸው ጫጩቶች አውራ ዶሮና ሴት ዶሮ ሆኑልኝ። ሴቷን ዶሮ ለይሖዋ ለመስጠት ወሰንኩ። ከሷም ሦስት ዶሮዎች አገኘሁና ሸጥኳቸው። ገንዘቡን ለይሖዋ ሥራ እንዲውል በፖስታ ልኬላችኋለሁ።—የስምንት ዓመቱ ቴሪ
ያለኝ ገንዘብ በሙሉ ይኸው ነው! እባካችሁ በጥበብ ተጠቀሙበት። በቀላሉ ያጠራቀምኩት ገንዘብ አይደለም። 150 ብር ልኬላችኋለሁ።—የአሥር ዓመቷ ሣራ
በትምህርት ቤት በተሰጠን የቤት ሥራ አንደኛ ወጥቼ ተሸለምኩ። በዚህም ምክንያት በወረዳው በሚደረገው ውድድር ለመካፈል ሄድኩ። እዚያም አንደኛ ወጣሁ፤ ከዚያ በመቀጠል በአውራጃው በተደረገው የመጨረሻ ውድድር ላይ ሁለተኛ ወጣሁ። በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ ገንዘብ ተሸልሜያለሁ። ካገኘሁት ገንዘብ ውስጥ የተወሰነውን ለማኅበሩ ለመስጠት እፈልጋለሁ። ለእነዚህ ሽልማቶች ለመብቃት የቻልኩት በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ስልጠና በማግኘቴ እንደሆነ ይሰማኛል። በዳኞቹ ፊት ሪፖርቴን ሳቀርብ ምንም አልተረበሽኩም ነበር።—የስድስተኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው አምበር
ለይሖዋ እንዲሆን ይህን ልሰጣችሁ እፈልጋለሁ። ገንዘቡን ምን ልታደርጉበት እንደምትችሉ ለማወቅ እሱን ጠይቁት። እርሱ ሁሉን ነገር ያውቃል።—የስድስት ዓመቷ ኬረን
[በገጽ 25 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የይሖዋ ምሥክሮች የሚያካሂዱት ሥራ የሚደገፈው በፈቃደኝነት በሚደረጉ መዋጮዎች ነው