የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው
2 ቆሮንቶስ 12:9—“ጸጋዬ ይበቃሃል”
“ጸጋዬ ይበቃሃል፤ ምክንያቱም ኃይሌ ፍጹም የሚሆነው በምትደክምበት ጊዜ ነው።”—2 ቆሮንቶስ 12:9 አዲስ ዓለም ትርጉም
“ጸጋዬ ይበቃሃል፣ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና።”—2 ቆሮንቶስ 12:9 የ1954 ትርጉም
የ2 ቆሮንቶስ 12:9 ትርጉም
አምላክ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ የሚያጋጥሙትን ተፈታታኝ ሁኔታዎችና ያሉበትን የአቅም ገደቦች ለመቋቋም የሚያስፈልገውን ብርታት እንደሚሰጠው ቃል ገብቶለታል።
“ጸጋዬ ይበቃሃል።” ጳውሎስ በተደጋጋሚ ላቀረበው ጸሎት አምላክ የሰጠው ምላሽ “ደግነቴ ይበቃሃል” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። በሌላ አባባል አምላክ ያሳየው አስደናቂ ደግነት፣ ጳውሎስ ያጋጠሙትን ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንዲወጣ ለመርዳት በቂ ነበር። እንዴት? “ይገባናል የማንለው ደግነት” ወይም “ጸጋ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል፣ ተቀባዩ ይገባኛል ብሎ ሊጠይቅ የማይችለውን አምላክ በልግስና ተነሳስቶ በነፃ የሚሰጠውን ስጦታ ያመለክታል። ከጻፋቸው ደብዳቤዎች መረዳት እንደሚቻለው ጳውሎስ ከአምላክ ጸጋ በእጅጉ ተጠቅሟል። ቀደም ሲል ክርስቲያኖችን ያሳድድ የነበረ ቢሆንም አምላክ ብርታት ስለሰጠው ባሕርይውን መቀየርና ሌሎች ሰዎች ክርስቲያን እንዲሆኑ መርዳት ችሏል። (1 ቆሮንቶስ 15:9, 10፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:12-14) ጳውሎስ ያጋጠመውን ማንኛውንም ችግር ወይም ተፈታታኝ ሁኔታ በአምላክ እርዳታ መወጣት እንደሚችል መተማመን ይችላል።
“ምክንያቱም ኃይሌ ፍጹም የሚሆነው በምትደክምበት ጊዜ ነው።” ይሖዋ፣a ኃይሉ ይበልጥ የሚታየው ደካማና ኃጢአተኛ በሆኑ ሰዎች ላይ እንደሆነ ለጳውሎስ አስታውሶታል። (2 ቆሮንቶስ 4:7፤ 12:8) ክርስቲያኖች ድክመታቸውን አምነው በመቀበል የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉ የአምላክ ኃይል ሙሉ በሙሉ በእነሱ ላይ እንዲሠራ ይፈቅዳሉ። (ኤፌሶን 3:16፤ ፊልጵስዩስ 4:13) ከዚህ አንጻር የአምላክ ኃይል የሚገለጠው በድካም ጊዜ ነው ሊባል ይችላል።
የ2 ቆሮንቶስ 12:9 አውድ
ጳውሎስ በ55 ዓ.ም. ገደማ በቆሮንቶስ ላሉ ክርስቲያኖች በመንፈስ መሪነት ደብዳቤ ጽፎላቸው ነበር። በደብዳቤው የመጨረሻ ክፍል ላይ ሐዋርያ የመሆን ሥልጣን እንዳለው አበክሮ ገልጿል። እንዲህ ለማድረግ የተነሳሳው ራሳቸውን የሾሙ አንዳንድ አስተማሪዎች፣ ምናልባትም በውጫዊ ገጽታው ወይም በንግግር ችሎታው የተነሳ ይተቹት ስለነበር ነው።—2 ቆሮንቶስ 10:7-10፤ 11:5, 6, 13፤ 12:11
ጳውሎስ የመከላከያ ሐሳብ ሲያቀርብ፣ በራሱ ጥንካሬ ቢሆን ኖሮ አገልግሎቱን ማከናወንና የተለያዩ ፈተናዎችን መወጣት እንደማይችል ገልጿል። (2 ቆሮንቶስ 6:4፤ 11:23-27፤ 12:12) ምዕራፍ 12 ላይ “ሥጋዬን የሚወጋ እሾህ” የሚል ምሳሌያዊ አገላለጽ ተጠቅሟል፤ ይህም አካላዊ ወይም ስሜታዊ ሥቃይ ያስከተለበትን ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ችግር የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም። (2 ቆሮንቶስ 12:7) ጳውሎስ ይህ ችግር ምን እንደሆነ ባይገልጽም በአምላክ እርዳታ ችግሩን በጽናት ለመቋቋም ቁርጥ ውሳኔ አድርጎ ነበር።
በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖችም ስደትና ሌሎች ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሊያጋጥሟቸው ይችላሉ። አምላክ የሚሰጣቸው ኃይል፣ የሚያጋጥማቸውን ማንኛውንም ችግር ለመወጣት እንደሚረዳቸው ማወቃቸው ያጽናናቸዋል። እነሱም ልክ እንደ ጳውሎስ በሙሉ ልብ “ስደክም ያን ጊዜ ብርቱ ነኝ” ማለት ይችላሉ።—2 ቆሮንቶስ 12:10
የ2 ቆሮንቶስ መጽሐፍን አጠቃላይ ይዘት ለማየት ይህን አጭር ቪዲዮ ተመልከት።
a ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው። (መዝሙር 83:18) “ይሖዋ ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።