የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው
ኢሳይያስ 26:3—“በአንተ ለምትደገፍ ነፍስ ፈጽመህ በሰላም ትጠብቃታለህ”
“ሙሉ በሙሉ በአንተ የሚመኩትን ትጠብቃለህ፤ በአንተ ስለሚታመኑ ዘላቂ ሰላም ትሰጣቸዋለህ።”—ኢሳይያስ 26:3 አዲስ ዓለም ትርጉም
“በአንተ ላይ ታምናለችና በአንተ ለምትደገፍ ነፍስ ፈጽመህ በሰላም ትጠብቃታለህ።”—ኢሳይያስ 26:3 የ1954 ትርጉም
የኢሳይያስ 26:3 ትርጉም
ነቢዩ ኢሳይያስ እነዚህን የሚያጽናኑ ቃላት በመጠቀም አምላክ በእሱ ላይ ሙሉ በሙሉ ለሚታመኑ ሰዎች ጥበቃ እንደሚያደርግ ገልጿል። አምላክ ይህን የሚያደርገው እንዲህ ያሉ ሰዎች የደህንነት ስሜት እንዲሰማቸውና ውስጣዊ ሰላም እንዲያገኙ በማድረግ ነው።
“ሙሉ በሙሉ በአንተ የሚመኩትን ትጠብቃለህ።” ይህ የጥቅሱ ክፍል የሚናገረው በማንኛውም ጊዜ በይሖዋa አምላክ ለመታመን በልባቸው ቁርጥ ውሳኔ ስላደረጉ ሰዎች ነው። በአምላክ የሚታመኑ ሰዎች በእሱ መመካት እንደሚያስፈልጋቸው ይገነዘባሉ። ለምሳሌ አስፈላጊ ውሳኔዎችን በሚያደርጉበት ጊዜ በራሳቸው አስተሳሰብ አይመኩም። ከዚህ ይልቅ በሚያደርጉት ነገር ሁሉ የአምላክን አስተሳሰብ ግምት ውስጥ ያስገባሉ። (ምሳሌ 3:5, 6) የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ በማንበብና ባነበቡት ነገር ላይ በጥልቀት በማሰላሰል አምላክ ስለ ጉዳዩ ያለውን አመለካከት ለመረዳት ጥረት ያደርጋሉ። (መዝሙር 1:2፤ 119:15) ተፈታታኝ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው ወደ አምላክ ልባዊ ጸሎት በማቅረብ የእሱን እርዳታ ይጠይቃሉ። (መዝሙር 37:5፤ 55:22) እንዲህ በማድረግ በአምላክ ላይ ያላቸውን እምነት ያሳያሉ፤ እሱም በምላሹ ሰላም ይሰጣቸዋል።
“ዘላቂ ሰላም ትሰጣቸዋለህ።” ጥቅሱ መጀመሪያ ላይ በተጻፈበት የዕብራይስጥ ቋንቋ “ሰላም” የሚለው ቃል ለአጽንኦት ሲባል ሁለቴ ተጠቅሶ ይገኛል፤ በበኩረ ጽሑፉ ላይ ያለውን አጽንኦት ለማስተላለፍ ይህ አገላለጽ “ዘላቂ ሰላም፣” “ፍጹም ሰላም” ወይም “ሙሉ ሰላም” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። በሌላ አባባል በይሖዋ ሙሉ በሙሉ የሚታመኑ ሰዎች በሁኔታዎች ላይ ያልተመካ ውስጣዊ ሰላም ወይም የመረጋጋት ስሜት ያገኛሉ። (መዝሙር 112:7፤ 119:165) ይህ ዓይነቱ ሰላም የሚገኘው በግለሰብ ደረጃ ከአምላክ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት በመመሥረትና በእሱ ዘንድ ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ በመጣር ነው።—ምሳሌ 3:32፤ ኢሳይያስ 48:18
“ዘላቂ ሰላም” የሚለው አገላለጽ አምላክ ማንኛውም ዓይነት ችግር እንዳያጋጥማቸው በመከለል አገልጋዮቹን ከጭንቀት ነፃ እንደሚያደርጋቸው የሚያመለክት አይደለም። (1 ሳሙኤል 1:6, 7፤ ኢዮብ 6:1, 2፤ መዝሙር 31:9) ከዚህ ይልቅ የሚያጋጥማቸውን ችግር ለመቋቋም እንደሚረዳቸው የሚያሳይ ነው። (ኢሳይያስ 41:10, 13) ጥበብ፣ ብርታትና መጽናኛ በመስጠት ጸሎታቸውን ይመልስላቸዋል። (መዝሙር 94:19፤ ምሳሌ 2:6፤ ኢሳይያስ 40:29) በመሆኑም ከባድ ችግር በሚያጋጥማቸው ጊዜም እንኳ ተረጋግተው መኖር ይችላሉ።—ፊልጵስዩስ 4:6, 7
የኢሳይያስ 26:3 አውድ
ነቢዩ ኢሳይያስ የኖረው በስምንተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ነው። በዚያ ወቅትም ሆነ ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት በይሁዳ የኖሩ በርካታ ሰዎች ለይሖዋ አምላክ ታማኝ አልነበሩም። በዚህም የተነሳ ይሖዋ በ607 ዓ.ዓ. ዋና ከተማቸው ኢየሩሳሌም እንድትጠፋ ፈቀደ።
ሆኖም ኢሳይያስ ይህ ጥፋት ከመከሰቱ ከመቶ ዓመት በፊት በምዕራፍ 26 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ለይሖዋ የቀረበ ትንቢታዊ የውዳሴ መዝሙር ጽፏል። (ኢሳይያስ 26:1-6) ይህ መዝሙር በይሁዳ ያለች አንዲት ከተማ መልሳ ስለምትቋቋምበት ጊዜ ይናገራል፤ ከሁኔታዎች መረዳት እንደምንችለው ይህች ከተማ ኢየሩሳሌም ናት።
ከ537 ዓ.ዓ. በኋላ ባሉት ዓመታት ኢየሩሳሌም መልሳ ተቋቋመች። ከዚያ በኋላ፣ ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱ ታማኝ አይሁዳውያን “ጠንካራ ከተማ አለችን” ብለው በሙሉ ልብ መናገር ይችላሉ። (ኢሳይያስ 26:1) ሆኖም ከተማዋን ጠንካራ ያደረጋት በቅጥር የተከበበች መሆኗ አይደለም። ከዚህ ይልቅ የከተማዋ ደህንነት የተመካው በይሖዋ በረከትና ጥበቃ ላይ ነው።—ኢሳይያስ 26:2
ዛሬም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። በይሖዋ ሙሉ በሙሉ የሚታመኑ ሰዎች ይሖዋን እንደ “ዓለት” ወይም መጠጊያ አድርገው ስለሚመለከቱት የደህንነት ስሜት ይሰማቸዋል።—ኢሳይያስ 26:4
የኢሳይያስ መጽሐፍን አጠቃላይ ይዘት ለማየት ይህን አጭር ቪዲዮ ተመልከት።
a ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው። (መዝሙር 83:18) “ይሖዋ ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።