ይሖዋ—ምሥጢርን የሚገልጥ አምላክ
“ምሥጢር የሚገልጥ አምላክ በሰማይ ውስጥ አለ።”— ዳንኤል 2:28
1, 2. (ሀ) ይሖዋ ከቀንደኛው ባላጋራው የሚለየው እንዴት ነው? (ለ) ሰዎችስ ይህንን ልዩነት የሚያንጸባርቁት እንዴት ነው?
የአጽናፈ ዓለሙ የበላይ ገዥና አፍቃሪ አምላክ እንዲሁም ብቸኛ ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ የጥበብና የፍትሕ አምላክ ነው። ማንነቱን፣ ሥራውን ወይም ዓላማውን መደበቅ አያስፈልገውም። በወሰነው ጊዜና በመረጠው መንገድ ራሱን ይገልጣል። በዚህ መንገድ እውነተኛ ማንነቱንና ዓላማውን ለመሰወር ከሚጥረው ከባላጋራው ከሰይጣን ዲያብሎስ ፈጽሞ የተለየ ነው።
2 ይሖዋና ሰይጣን ተቃራኒ እንደሆኑ ሁሉ አምላኪዎቻቸውም እንዲሁ ተቃራኒ ናቸው። የሰይጣንን አመራር የሚከተሉ ሰዎች በአስመሳይነትና በአታላይነት ባሕርያቸው ተለይተው ይታወቃሉ። የጨለማ ሥራ እየሠሩ ጥሩ ሰዎች መስለው ለመታየት ይጥራሉ። የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ይህ ሊያስደንቃቸው እንደማይገባ ተነግሯቸዋል። “እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን እየለወጡ፣ ውሸተኞች ሐዋርያትና ተንኰለኞች ሠራተኞች ናቸውና። ይህም ድንቅ አይደለም፤ ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና።” (2 ቆሮንቶስ 11:13, 14) በአንጻሩ ደግሞ ክርስቲያኖች እንደ መሪያቸው አድርገው የሚከተሉት ክርስቶስን ነው። ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የአባቱን የይሖዋ አምላክን ባሕርያት ፍጹም በሆነ መንገድ አንጸባርቋል። (ዕብራውያን 1:1-3) በመሆኑም ክርስቲያኖች ክርስቶስን ሲከተሉ የእውነት፣ የግልጥነትና የብርሃን አምላክ የሆነውን ይሖዋን እየመሰሉ ነው ማለት ነው። እነርሱም ቢሆኑ ማንነታቸውን፣ ሥራቸውን ወይም ደግሞ ዓላማቸውን የሚሰውሩበት ምንም ምክንያት የለም።— ኤፌሶን 4:17-19፤ 5:1, 2
3. ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች ሆኑ ማለት “በምሥጢር ከሚንቀሳቀስ ሃይማኖታዊ ቡድን” ጋር በግድ እንዲቀላቀሉ ተደርገዋል ማለት እንዳልሆነ እንዴት ማስረዳት እንችላለን?
3 ይሖዋ ተገቢ ነው ብሎ ባሰበው ጊዜ ዓላማውንና ወደፊት የሚከናወኑትን ነገሮች በተመለከተ ከሰዎች ተሰውረው የነበሩትን ዝርዝር ሁኔታዎች ይገልጻል። ከዚህ አንጻር ሲታይ ይሖዋ ምሥጢርን የሚገልጥ አምላክ ነው። በመሆኑም እርሱን ለማገልገል የሚፈልጉ ሁሉ እርሱ የገለጠውን ይህን እውቀት እንዲማሩ ግብዣ ብቻ ሳይሆን ጠበቅ ያለ ማሳሰቢያም ተሰጥቷቸዋል። በ1994 በአንድ የአውሮፓ አገር ውስጥ ከ145,000 በሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳሳየው ከሆነ እያንዳንዳቸው የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ከመወሰናቸው በፊት በግላቸው በአማካይ ለሦስት ዓመታት ያክል የይሖዋ ምሥክሮችን ትምህርት ሲመረምሩ ቆይተዋል። ይህ ያለ አንዳች አስገዳጅ በገዛ ምርጫቸው ያደረጉት ውሳኔ ነው። ከዚያ በኋላም ቢሆን የምርጫና የድርጊት ነፃነታቸውን አልተነፈጉም። ለምሳሌ ያህል ከጊዜ በኋላ ጥቂቶች ለክርስቲያኖች ከተሰጠው ከፍተኛ የሥነ ምግባር አቋም ደረጃ ጋር ባለመጣጣማቸው የይሖዋ ምሥክር ሆነው ላለመቀጠል ወስነዋል። ይሁንና ደስ የሚለው ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ቀደም ሲል የይሖዋ ምሥክሮች ከነበሩት ከእነዚህ ሰዎች መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ከጊዜ በኋላ እንደገና የይሖዋ ምሥክር ሆነው እንደ በፊቱ ለመመላለስ እርምጃ ወስደዋል።
4. ክርስቲያኖችን የትኛው ጉዳይ ሊያስጨንቃቸው አይገባም? ለምንስ?
4 እርግጥ ነው ቀደም ሲል የይሖዋ ምሥክሮች የነበሩት ሁሉ ይመለሳሉ ማለት አይደለም። ከእነዚህም መካከል በአንድ ወቅት በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የኃላፊነት ቦታ የነበራቸው ሰዎች ይገኙበታል። ከኢየሱስ የቅርብ ተከታዮች አንዱ የሆነው ሐዋርያው ይሁዳ እንኳ ወደ ኋላ እንደተመለሰ ስለምናውቅ ይህ ሊያስደንቀን አይገባም። (ማቴዎስ 26:14-16, 20-25) ይሁን እንጂ ይህ ስለ ክርስትና ስጋት እንዲያድርብን የሚያደርግ ነው? የይሖዋ ምሥክሮች በማስተማሩ ሥራቸው እያገኙት ያሉትን ውጤት የሚያጨናግፍ ነውን? በፍጹም፤ የአስቆሮቱ ይሁዳ የክህደት ድርጊት የአምላክን ዓላማ እንዳላኮላሸ ሁሉ ይህም ቢሆን ምንም የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም።
ሁሉን ቻይ ቢሆንም አፍቃሪ ነው
5. ይሖዋ እና ኢየሱስ የሰው ልጆችን እንደሚያፈቅሩ እንዴት እናውቃለን? ይህን ፍቅራቸውንስ የገለጹት እንዴት ነው?
5 ይሖዋ የፍቅር አምላክ ነው። ስለ ሰዎች ያስባል። (1 ዮሐንስ 4:7-11) እጅግ ከፍተኛ ቦታ ያለው ቢሆንም ከሰዎች ጋር ወዳጅነት መመሥረት ያስደስተዋል። ከጥንት አገልጋዮቹ መካከል አንዱን በሚመለከት እንዲህ የሚል እናነባለን:- “አብርሃምም እግዚአብሔርን አመነ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት ያለው ተፈጸመ፤ የእግዚአብሔርም ወዳጅ ተባለ።” (ያዕቆብ 2:23፤ 2 ዜና መዋዕል 20:7፤ ኢሳይያስ 41:8) ሰብዓዊ ወዳጆች እርስ በርስ ምሥጢራቸውን እንደሚካፈሉ ይሖዋም ለወዳጆቹ ምሥጢር ያካፍላቸዋል። በዚህ ረገድ ኢየሱስ የአባቱን ምሳሌ በመኮረጅ ደቀ መዛሙርቱን እንደ ጓደኛ አድርጎ በመያዝ ምሥጢር አካፍሏቸዋል። “ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባርያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፤ ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ፣ ከአባቴ የሰማሁትን ሁሉ ለእናንተ አስታውቄአችኋለሁና” ብሏቸዋል። (ዮሐንስ 15:15) ይሖዋ፣ ልጁና ወዳጆቻቸው በጋራ የሚያውቋቸው የግል ጉዳዮች ወይም “ምሥጢሮች” በማይበጠሰው የፍቅር ማሠሪያ አንድ ላይ እንዲተሳሰሩ ያደርጓቸዋል።— ቆላስይስ 3:14
6. ይሖዋ ለማድረግ ያሰበውን ነገር መደበቅ የማያስፈልገው ለምንድን ነው?
6 “እንዲሆን ያደርጋል” የሚለው የይሖዋ የስሙ ትርጉም ዓላማውን ለመፈጸም ሲል ለመሆን የሚፈልገውን ሁሉ መሆን እንደሚችል ይጠቁማል። ይሖዋ እንደ ሰው አይደለም፤ ሌሎች እንዳያጨናግፉበት በመፍራት ያሰበውን ነገር የሚደብቅበት ምንም ምክንያት የለም። ምንም የሚሳነው ነገር ስለሌለ ለማድረግ የወጠነውን አብዛኛውን ነገር በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲገለጽ አድርጓል። “ቃሌ እንዲሁ ይሆናል፤ የምሻውን ያደርጋል የላክሁትንም ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም” ሲል ቃል ገብቷል።— ኢሳይያስ 55:11
7. (ሀ) ይሖዋ በኤደን ምን ትንቢት ተናግሯል? ሰይጣንስ አምላክ እውነተኛ መሆኑን ያረጋገጠው እንዴት ነው? (ለ) በ2 ቆሮንቶስ 13:8 ላይ የሚገኘው መሠረታዊ ሥርዓት ሁልጊዜ የሚሠራው እንዴት ነው?
7 ይሖዋ በእርሱና በባላጋራው በሰይጣን መካከል የተነሳው ውዝግብ እንዴት እንደሚቋጭ በአጭሩ የገለጸው በኤደን ዓመፅ ከተፈጸመ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ነበር። አምላክ ተስፋ የሰጠበት ዘር በሚሰቀጥጥ ሁኔታ ቢቀጠቀጥም ዘላቂ የሆነ ጉዳት እንደማይደርስበት፣ ሰይጣን ግን ከሕልውና ውጭ እስኪሆን ድረስ እንደሚቀጠቀጥ ተናግሯል። (ዘፍጥረት 3:15) በእርግጥም በ33 እዘአ ክርስቶስ ኢየሱስ እንዲገደል በማድረግ ዲያብሎስ ይህንን ዘር ቀጥቅጧል። በዚህ መንገድ ሰይጣን ቅዱስ ጽሑፉ ፍጻሜውን እንዲያገኝ አድርጓል፤ ከዚህም ሌላ ሰይጣን በዓላማ ያደረገው ነገር ባይሆንም እንኳ ይሖዋ የእውነት አምላክ መሆኑን አረጋግጧል። ለእውነትና ለጽድቅ ያለው ጥላቻ፣ እንዲሁም ኩራቱና ንስሐ ለመግባት አሻፈረኝ ማለቱ አምላክ ስለ እርሱ የተናገረውን ነገር በሙሉ እንዲፈጽም አድርጎታል። አዎን፣ “ለእውነት እንጂ በእውነት ላይ ምንም ለማድረግ አንችልምና” የሚለው መሠረታዊ ሥርዓት በሰይጣንም ሆነ እውነትን በሚቃወሙ ወገኖች ሁሉ ላይ ይሠራል።— 2 ቆሮንቶስ 13:8
8, 9. (ሀ) ሰይጣን ምን ነገር ያውቃል? ይህን ማወቁ የይሖዋ ዓላማ እንዳይፈጸም እንቅፋት ይፈጥርበታልን? (ለ) የይሖዋ ተቃዋሚዎች ችላ የሚሉት የትኛውን ግልጽ ማስጠንቀቂያ ነው? ለምንስ?
8 የአምላክ መንግሥት በ1914 በማይታይ ሁኔታ በመቋቋሙ ራእይ 12:12 ፍጻሜውን አግኝቷል:- “ስለዚህ፣ ሰማይና በውስጡ የምታድሩ ሆይ፣ ደስ ይበላችሁ፤ ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፣ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቊጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና።” ይሁንና ሰይጣን ጥቂት ጊዜ እንዳለው ማወቁ አካሄዱን እንዲለውጥ አድርጎታልን? ሰይጣን እንዲህ አደረገ ማለት ይሖዋ የእውነት አምላክ፣ የሁሉም የበላይ ገዥና አምልኮ የሚገባው ብቸኛ አካል መሆኑን አምኖ ተቀበለ ማለት ይሆናል። ይሁን እንጂ እውነቱ ከእርሱ የተሰወረ ባይሆንም ዲያብሎስ ሽንፈቱን አምኖ ለመቀበል ፈቃደኛ አይደለም።
9 ክርስቶስ በሰይጣን ዓለም ሥርዓት ላይ የፍርድ እርምጃ ለመውሰድ በሚመጣበት ጊዜ ምን ዓይነት ሁኔታዎች እንደሚኖሩ ይሖዋ በግልጽ ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:29-31፤ 25:31-46) በዚህ ረገድ የይሖዋ ቃል የዓለምን ገዥዎች በሚመለከት እንዲህ ይላል:- “ሰላምና ደኅንነት ነው ሲሉ፣ ያን ጊዜ ምጥ እርጉዝን እንደሚይዛት ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል።” (1 ተሰሎንቄ 5:3) የሰይጣንን አርዓያ የሚከተሉ ሰዎች ይህንን ግልጽ ማስጠንቀቂያ ቸል ይላሉ። ልባቸው ክፉ ከመሆኑ የተነሣ ዓይናቸው ታውሯል፤ ይህም ከክፉ መንገዳቸው ተመልሰው ንስሐ እንዳይገቡና የይሖዋን ዓላማ የሚቃረነውን ግባቸውንና ውጥናቸውን እንዳይለውጡ እንቅፋት ይሆንባቸዋል።
10. (ሀ) 1 ተሰሎንቄ 5:3 እስከ ምን ድረስ ፍጻሜውን አግኝቷል ሊባል ይችላል? ይሁን እንጂ የይሖዋ ሕዝቦች ምን ምላሽ ሊሰጡ ይገባል? (ለ) እምነት የሌላቸው ሰዎች ወደፊት የአምላክን ሕዝቦች በመቃወም ረገድ ይበልጥ ልባቸው ሊደነድን የሚችለው ለምን ሊሆን ይችላል?
10 በተለይ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም ዓመት ተብሎ ከተሰየመው ከ1986 አንስቶ ሰላምና ደህንነት ዓለምን የሚያወያይ አቢይ ርዕስ ሆኗል። የዓለምን ሰላም ለማስጠበቅ አንዳንድ እርምጃዎች የተወሰዱ ሲሆን በተወሰነ መጠን ውጤት ያስገኙ ይመስላል። የዚህ ትንቢት ፍጻሜ ይኸው ብቻ ነው ወይስ ወደፊት አንድ ዓይነት አስገራሚ አዋጅ እንደሚነገር ልንጠብቅ እንችላለን? ይህ ይሖዋ እርሱ በወሰነው ጊዜ የሚገልጽልን ይሆናል። እስከዚያው ድረስ ግን ‘የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቅንና እያስቸኮልን’ በመንፈሳዊ ንቁዎች ሆነን እንኑር። (2 ጴጥሮስ 3:12) ስለ ሰላምና ደህንነት እየተወራ ተጨማሪ ዓመታት ባለፉ ቁጥር ይህንን ማስጠንቀቂያ እያወቁ ቸል ለማለት የሚመርጡ አንዳንድ ሰዎች ይሖዋ ቃሉን አይፈጽምም ወይም ሊፈጽም አይችልም ብለው ስለሚያስቡ ልባቸው ይበልጥ ይደነድናል። (ከመክብብ 8:11-13፤ 2 ጴጥሮስ 3:3, 4 ጋር አወዳድር።) ይሁን እንጂ እውነተኛ ክርስቲያኖች ይሖዋ ዓላማውን እንደሚፈጽም ያውቃሉ!
ይሖዋ ለሚጠቀምባቸው ወኪሎች ተገቢውን አክብሮት ማሳየት
11. ዳንኤልና ዮሴፍ ስለ ይሖዋ ምን ተምረዋል?
11 ሦስተኛ የዓለም ኃያል የነበረው የባቢሎን መንግሥት ንጉሥ ናቡከደነፆር አንድ የሚረብሽ ሕልም ዓይቶ ሕልሙን ማስታወስ ስላቃተው እርዳታ ጠይቆ ነበር። የሕልም ተርጓሚዎቹ፣ አስማተኞቹና መተተኞቹ ያየውን ሕልምም ሆነ ፍችውን ሊነግሩት አልቻሉም። ይሁን እንጂ የአምላክ አገልጋይ የነበረው ዳንኤል ይህንን ማድረግ ችሎ ነበር፤ ሆኖም ሕልሙንና ፍቺውን ሊያሳውቀው የቻለው በራሱ ጥበብ እንዳልሆነ ሳይሸሽግ ተናግሯል። ዳንኤል “ምሥጢር የሚገልጥ አምላክ በሰማይ ውስጥ አለ፣ እርሱም በኋለኛው ዘመን የሚሆነውን ነገር አስታውቆሃል” ሲል ተናግሯል። (ዳንኤል 2:1-30) ከበርካታ መቶ ዘመናት ቀደም ብሎም ሌላው የአምላክ ነቢይ የነበረው ሰው ዮሴፍ፣ ይሖዋ ምሥጢርን የሚገልጥ አምላክ መሆኑን አይቷል።— ዘፍጥረት 40:8-22፤ አሞጽ 3:7, 8
12, 13. (ሀ) ከነቢያት ሁሉ የሚበልጠው የአምላክ ነቢይ ማን ነበር? እንደዚህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው? (ለ) ዛሬ ‘የአምላክ ቅዱስ ምሥጢር መጋቢዎች’ ሆነው የሚያገለግሉት እነማን ናቸው? ለእነርሱ ሊኖረን የሚገባው አመለካከትስ ምን መሆን አለበት?
12 ይሖዋን በምድር ላይ ካገለገሉት ነቢያት ሁሉ ይበልጥ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው ኢየሱስ ነው። (ሥራ 3:19-24) ጳውሎስ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጐዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፣ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን።”— ዕብራውያን 1:1, 2
13 ይሖዋ የጥንቶቹን ክርስቲያኖች መለኮታዊውን ምሥጢር ባስታወቃቸው በልጁ በኢየሱስ በኩል አነጋግሯቸዋል። ኢየሱስ “ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል” ብሏቸዋል። (ሉቃስ 8:10) ከጊዜ በኋላም ጳውሎስ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘የክርስቶስ ሎሌዎችና የእግዚአብሔር ምሥጢር መጋቢዎች’ እንደሆኑ ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 4:1) ዛሬም ቅቡዓን ክርስቲያኖች በአስተዳደር አካሉ አማካኝነት በጊዜው መንፈሳዊ ምግብ የሚያቀርብ ታማኝና ልባም ባሪያ ሆነው በመደራጀት ከዚሁ ጋር በሚመሳሰል መንገድ ማገልገላቸውን ቀጥለዋል። (ማቴዎስ 24:45-47) የአምላክ መንፈስ ለነበራቸው ለጥንቶቹ የአምላክ ነቢያት በተለይም ለአምላክ ልጅ ጥልቅ አክብሮት ካለን ይሖዋ በእነዚህ አስጨናቂ ቀናት ለሕዝቦቹ የሚያስፈልጋቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ለመግለጽ ለሚጠቀምበት ሰብዓዊ ወኪልስ አክብሮት ልናሳይ አይገባንምን?— 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5, 13
ግልጽ መሆን ወይስ ምሥጢር መጠበቅ?
14. ክርስቲያኖች ሥራዎችን በምሥጢር የሚያከናውኑት መቼ ነው? ይህንንስ የሚያደርጉት የማንን ምሳሌ በመከተል ነው?
14 ይሖዋ ነገሮችን በግልጽ የሚያሳውቅ መሆኑ ክርስቲያኖች በማንኛውም ሁኔታ ሥር የሚያውቁትን ነገር ሁሉ መናገር አለባቸው ማለት ነውን? ክርስቲያኖች ኢየሱስ ለሐዋርያቱ የሰጠውን “እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች ሁኑ” የሚለውን ምክር ይከተላሉ። (ማቴዎስ 10:16) ክርስቲያኖች ሕሊናቸው በሚፈልግባቸው መንገድ አምላክን እንዳያመልኩ ቢከለከሉ ማንኛውም ሰብዓዊ ወገን ለይሖዋ የሚቀርበውን አምልኮ የማገድ መብት እንደሌለው ስለሚገነዘቡ ‘አምላክን መታዘዛቸውን’ ይቀጥላሉ። (ሥራ 5:29) ኢየሱስ ራሱ ይህን ማድረግ ተገቢ እንደሚሆን አሳይቷል። እንዲህ እናነባለን:- “ከዚህም በኋላ ኢየሱስ አይሁድ ሊገድሉት ይፈልጉ ስለ ነበር በይሁዳ ሊመላለስ አይወድም ነበርና በገሊላ ይመላለስ ነበር። የአይሁድም የዳስ በዓል ቀርቦ ነበር። ኢየሱስም [ለማያምኑት የሥጋ ወንድሞቹ] እንዲህ አላቸው:- . . . እናንተ ወደዚህ በዓል ውጡ፤ እኔስ ጊዜዬ ገና ስላልተፈጸመ ወደዚህ በዓል ገና አልወጣም። ይህንም አላቸውና በገሊላ ቀረ። ወንድሞቹ ግን ወደ በዓሉ ከወጡ በኋላ በዚያን ጊዜ እርሱ ደግሞ በግልጥ ሳይሆን ተሰውሮ ወጣ።”— ዮሐንስ 7:1, 2, 6, 8-10
መናገር ወይስ አለመናገር?
15. ዮሴፍ፣ አንዳንድ ጊዜ ምሥጢርን መጠበቅ የፍቅር መግለጫ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?
15 አንዳንድ ጊዜ አንድን ጉዳይ በምሥጢር መያዝ የጥበብ እርምጃ ብቻ ሳይሆን የፍቅር መግለጫም ነው። ለምሳሌ ያህል የኢየሱስ አሳዳጊ አባት የሆነው ዮሴፍ እጮኛው ማርያም እንደ ፀነሰች ባወቀ ጊዜ ምን እርምጃ ወሰደ? ታሪኩ “እጮኛዋ ዮሴፍም ጻድቅ ሆኖ ሊገልጣት ስላልወደደ በስውር ሊተዋት አሰበ” ይላል። (ማቴዎስ 1:18, 19፤ ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።) የሕዝብ መሳለቂያ ቢያደርጋት ኖሮ እንዴት ያለ ደግነት የጎደለው አድራጎት ይሆን ነበር!
16. ምሥጢራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ሽማግሌዎችም ሆኑ የቀሩት የጉባኤው አባላት ምን ኃላፊነት አለባቸው?
16 በግለሰቡ ላይ ችግር የሚፈጥሩ ወይም ስሜቱን ሊጎዱ የሚችሉ ምሥጢራዊ ጉዳዮችን ለማይመለከታቸው ሰዎች መናገር አይገባም። ክርስቲያን ሽማግሌዎች ለመሰል ክርስቲያኖች በግል ምክር ወይም ማጽናኛ ሲሰጡ አለዚያም በይሖዋ ላይ ከበድ ያለ ኃጢአት ለፈጸሙት ተግሳጽ በሚሰጡበት ጊዜ ይህንን ነገር አይዘነጉም። እንደነዚህ ዓይነት ጉዳዮችን በቅዱስ ጽሑፋዊ መንገድ መያዝ በጣም አስፈላጊ ነው፤ ምሥጢራዊ ነገሮችን ጉዳዩ ለማይመለከታቸው ሰዎች አሳልፎ መስጠት አላስፈላጊና ፍቅር የጎደለው ድርጊት ነው። የክርስቲያን ጉባኤ አባላትም ከሽማግሌዎች ምሥጢራዊ ጉዳዮችን ለማውጣጣት አይሞክሩም፤ ይልቁንም ሽማግሌዎቹ የተጣለባቸውን ምሥጢር የመጠበቅ ኃላፊነት ያከብሩላቸዋል። ምሳሌ 25:9 “ክርክርህን ከባልንጀራህ ጋር ተከራከር፤ የሌላ ሰው ምሥጢር ግን አትግለጥ” ይላል።
17. ክርስቲያኖች አብዛኛውን ጊዜ ምሥጢራዊ ጉዳዮችን የሚጠብቁት ለምንድን ነው? ይሁን እንጂ ሁልጊዜ እንደዚያ ማድረግ የማይችሉትስ ለምንድን ነው?
17 ይህ መሠረታዊ ሥርዓት ለቤተሰብ አባሎችም ሆነ በጣም ለሚቀራረቡ ጓደኞችም ይሠራል። አለመግባባቶች እንዳይፈጠሩና ግንኙነታችን እንዳይሻክር ለማድረግ አንዳንድ ምሥጢራዊ ጉዳዮችን መጠበቅ የግድ አስፈላጊ ነው። “የሰሜን ንፋስ ወጀብ ያመጣል፤ ሐሜተኛ [“ምሥጢርን የሚገልጥ፣” NW] ምላስም የሰውን ፊት ያስቆጣል።” (ምሳሌ 25:23) እርግጥ ነው ለይሖዋና ለጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶቹ ያለን ታማኝነትና ኃጢአት ለፈጸሙት ሰዎች ያለን ፍቅር አንዳንድ ጊዜ ምሥጢራዊ ጉዳዮችን እንኳ ሳይቀር ለወላጆች፣ ለክርስቲያን ሽማግሌዎች ወይም ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ሌሎች ሰዎች እንድንናገር ያስገድደን ይሆናል።a ይሁን እንጂ በአብዛኛው ክርስቲያኖች የራሳቸውን ምሥጢር እንደሚጠብቁ ሁሉ የሌሎችንም ምሥጢር ይጠብቁላቸዋል።
18. ምን መናገር እንዳለብንና ምን መናገር እንደሌለብን ለመወሰን የሚረዱን ሦስት ክርስቲያናዊ ባሕርያት የትኞቹ ናቸው?
18 ለማጠቃለል ያክል አንድ ክርስቲያን አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ አንዳንድ ጉዳዮችን በምሥጢር በመያዝና ተገቢ በሚሆንበት ጊዜ ብቻ ምሥጢሩን በመግለጥ የይሖዋን ባሕርይ ይኮርጃል። የትኛውን መናገር እንዳለበትና የትኛውን መናገር እንደሌለበት እንዲወስን የሚረዱት ባሕርያት ትሕትና፣ እምነትና ፍቅር ናቸው። ትሕትና የሚያውቀውን ሁሉ ለሌሎች በመናገር ወይም ለሌሎች የማይነገር ምሥጢር እንደሚያውቅ በመግለጽ በሌሎች ዘንድ ትልቅ ቦታ ያለው ሰው ሆኖ ለመታየት ከመሞከር ይጠብቀዋል። በይሖዋ ቃልና በክርስቲያን ጉባኤ ላይ ያለው እምነት መለኮታዊ ምንጭ ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት እንዲሰብክ ያነሳሳዋል፤ ይሁን እንጂ ገና ከጅምሩ ሰዎችን የሚያስቆጣ ነገር ላለመናገር ይጠነቀቃል። አዎን፣ ፍቅር ለአምላክ ክብር የሚያመጡና ሰዎች ሕይወት እንዲያገኙ የግድ ሊያውቋቸው የሚገቡ ነገሮችን በግልጽ እንዲናገር ይገፋፋዋል። በአንጻሩ ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ የግለሰብ ምሥጢሮችን መግለጥ ፍቅር የጎደለው አድራጎት መሆኑን በመገንዘብ እንዲህ ዓይነት ምሥጢሮችን ይጠብቃል።
19. እውነተኛ ክርስቲያኖች ተለይተው እንዲታወቁ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው? ይህስ ምን ውጤት አለው?
19 እንዲህ ዓይነቱ ሚዛናዊ አቋም እውነተኛ ክርስቲያኖች ተለይተው እንዲታወቁ ያደርጋል። የአምላክን ስም በመደበቅ ወይም ምሥጢራዊና ለመረዳት አስቸጋሪ የሆነውን የሥላሴ ትምህርት እያስተማሩ የአምላክን ማንነት አይሰውሩም። የማይታወቁ አማልክት፣ የሐሰት ሃይማኖት እንጂ የእውነተኛው ሃይማኖት መለያ አይደሉም። (ሥራ 17:22, 23ን ተመልከት።) የይሖዋ ቅቡዓን ምሥክሮች ‘የአምላክ ቅዱስ ምሥጢር መጋቢዎች’ የመሆን መብት በማግኘታቸው ደስተኞች ናቸው። እነዚህን ምሥጢሮች ለሌሎች ገልጠው በመንገር ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች የይሖዋን ወዳጅነት ለማግኘት እንዲጣጣሩ ይረዷቸዋል።— 1 ቆሮንቶስ 4:1፤ 14:22-25፤ ዘካርያስ 8:23፤ ሚልክያስ 3:18
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በመጠበቂያ ግንብ 11-106 ላይ “በሌሎች ኃጢአት አትካፈል” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ይሖዋ ለማድረግ ያሰበውን ነገር መደበቅ የማያስፈልገው ለምንድን ነው?
◻ ይሖዋ ምሥጢሩን የሚገልጠው ለማን ነው?
◻ ይሖዋ ምሥጢሩን የሚገልጠው ለማን ነው?
◻ ክርስቲያኖች ምን መናገር እንዳለባቸውና ምን መናገር እንደሌለባቸው ለማወቅ የሚረዷቸው ሦስት ባሕርያት የትኞቹ ናቸው?
[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ይሖዋ በቃሉ በኩል ምሥጢሩን ይገልጣል