ምሕረት በማሳየት ረገድ ይሖዋን ምሰሉት
“አባታችሁ መሐሪ እንደሆነ እናንተም እንዲሁ መሐሪዎች ሁኑ።”—ሉቃስ 6:36 የ1980 ትርጉም
1. ፈሪሳውያን ምሕረት የለሾች መሆናቸውን ያሳዩት እንዴት ነበር?
የሰው ልጆች በአምላክ መልክ ቢፈጠሩም እንኳ ብዙውን ጊዜ ምሕረት በማሳየት ረገድ እሱን መምሰል ያቅታቸዋል። (ዘፍጥረት 1:27) ለምሳሌ ያህል ፈሪሳውያንን ተመልከቱ። ኢየሱስ በሰንበት ቀን የአንድን ሰው የሰለለች እጅ በመፈወስ ምሕረት ባሳየ ጊዜ በቡድን ደረጃ ሲታዩ ፈሪሳውያን ደስታቸውን ለመግለጽ አሻፈረን ብለዋል። ከዚያ ይልቅ ኢየሱስን ‘ለማጥፋት’ ተመካከሩ። (ማቴዎስ 12:9–14) በሌላ አጋጣሚ ደግሞ ኢየሱስ ሲወለድ ጀምሮ ዕውር የነበረን ሰው ፈወሰ። አሁንም እንደገና ‘አንዳንድ ፈሪሳውያን’ ኢየሱስ ባሳየው ምሕረት ሊደሰቱ አልቻሉም። ከዚያ ይልቅ “ይህ ሰው ሰንበትን አያከብርምና ከእግዚአብሔር አይደለም” በማለት አጉረመረሙ።—ዮሐንስ 9:1–7, 16
2, 3. ኢየሱስ ‘ከፈሪሳውያን እርሾ ተጠበቁ’ ሲል ምን ማለቱ ነበር?
2 ፈሪሳውያኑ የነበራቸው ምንም አዘኔታ የሌለው አመለካከት በሰው ልጆች ላይ ወንጀል ወደ መፈጸምና በአምላክ ላይ ኃጢአት ወደ መሥራት መርቷል። (ዮሐንስ 9:39–41) ኢየሱስ ሰዱቃውያንን ከመሳሰሉ አደገኛ አናሳ ቡድኖችና ከሌሎች ሃይማኖታውያን ‘እርሾ እንዲጠበቁ’ ደቀ መዛሙርቱን ያስጠነቀቀው ያለ ምክንያት አይደለም። (ማቴዎስ 16:6) እርሾ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኃጢአትን ወይም ምግባረ ብልሹነትን የሚያመለክት ነው። ስለዚህ ኢየሱስ “የጻፎችና ፈሪሳውያን” ትምህርት እውነተኛውን አምልኮ ሊያበላሽ እንደሚችል መናገሩ ነበር። እንዴት? ሰዎች ምሕረትን ጨምሮ “ዋና ነገር” የተባሉትን ችላ በማለት የአምላክን ሕግ ራሳቸው ካወጧቸው ደንቦችና ሥነ ሥርዓቶች አንፃር እንዲመለከቱ ያስተምር ስለነበር ነው። (ማቴዎስ 23:23) በአምልኮ ሥርዓቶች የታጠረው ይህ ሃይማኖት አምላክን ማምለክ ከባድ ሸክም እንዲሆን አድርጎ ነበር።
3 ኢየሱስ ስለ አባካኙ ልጅ በተናገረው ታሪክ ሁለተኛ ክፍል ላይ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ያላቸውን የተበላሸ አስተሳሰብ አጋልጧል። በታሪኩ ላይ ይሖዋን የሚወክለው አባትየው ንስሐ የገባውን ልጁን ይቅር ለማለት ዝግጁ ነበረ። ሆኖም ‘ፈሪሳውያንንና ጻፎችን’ የሚወክለው የልጁ ታላቅ ወንድም በጉዳዩ ላይ ፍጹም የተለየ አስተሳሰብ ነበረው።—ሉቃስ 15:2
የወንድሙ መቆጣት
4, 5. የአባካኙ ልጅ ወንድም ‘ጠፍቶ’ የነበረው በምን መልኩ ነው?
4 “ታላቁ ልጁ በእርሻ ነበረ፤ መጥቶም ወደ ቤት በቀረበ ጊዜ የመሰንቆና የዘፈን ድምፅ ሰማ፤ ከብላቴናዎችም አንዱን ጠርቶ:- ይህ ምንድር ነው? ብሎ ጠየቀ። እርሱም:- ወንድምህ መጥቶአልና በደኅና ስላገኘው አባትህ የሰባውን ፊሪዳ አረደለት አለው። ተቈጣም ሊገባም አልወደደም።”—ሉቃስ 15:25-28
5 ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ውስጥ ችግር የነበረበት አባካኙ ልጅ ብቻ እንዳልሆነ በግልጽ ለማየት ይቻላል። አንድ የጥናት ጽሑፍ “አንደኛው እንዲዋረድ ባደረገው የኃጢአት ተግባሩ ሌላኛው ደግሞ እንዳያስተውል ባደረገው ራስን የማመጻደቅ ባሕርዩ ምክንያት እዚህ ላይ የተጠቀሱት ሁለቱም ልጆች ጠፍተው ነበር” ብሏል። የአባካኙ ልጅ ወንድም አለመደሰት ብቻ ሳይሆን ‘እንደተቆጣ’ ልብ በሉ። ‘ቁጣ’ ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል መሠረታዊ ትርጉሙ በንዴት መገንፈልን ብቻ ሳይሆን ዘላቂ የሆነ የአእምሮ ሁኔታን የሚያመለክት ነው። የአባካኙ ልጅ ወንድም ሥር የሰደደ የጥላቻ ስሜት በውስጡ አምቆ ይዞ ስለነበረ ቀድሞውኑም ቢሆን ቤቱን ጥሎ መሄድ ያልነበረበት ሰው አሁን ተመልሶ በመምጣቱ መደሰት ተገቢ አይደለም የሚል ስሜት አድሮበታል።
6. የአባካኙ ልጅ ወንድም የሚወክለው እነማንን ነው? ለምንስ?
6 የአባካኙ ልጅ ወንድም ኢየሱስ ለኃጢአተኞች ያሳየውን ርኅራኄና የሰጠውን ትኩረት የተቃወሙትን ሰዎች ጥሩ አድርጎ የሚወክል ነው። እነዚህ ራሳቸውን የሚያመጻድቁ ሰዎች ኢየሱስ ያሳየው ርኅራኄ ስሜታቸውን አልነካም፤ አንድ ኃጢአተኛ ይቅርታ በሚደረግለት ጊዜ በሰማይ የሚኖረውን ደስታ አላንጸባረቁም። ከዚህ ይልቅ የኢየሱስ ርኅራኄ ቁጣቸውን ቀሰቀሰባቸው፤ በልባቸውም ‘ክፉ ማሰብ’ ጀመሩ። (ማቴዎስ 9:2–4) በአንድ ወቅት አንዳንድ ፈሪሳውያን ቁጣቸው ስለ ነደደ ኢየሱስ የፈወሰውን ሰው ፈልገው ካገኙት በኋላ ከምኩራብ ‘አወጡት’ ወይም አባረሩት! (ዮሐንስ 9:22, 34) የአባካኙ ልጅ ወንድም ‘ለመግባት ፈቃደኛ’ እንዳልነበረ ሁሉ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎችም ‘ደስ ካላቸው ጋር ለመደሰት’ ፈቃደኞች ሳይሆኑ ቀርተዋል። (ሮሜ 12:15) ኢየሱስ ምሳሌውን በመቀጠል የሚያቀርቡትን በክፋት የተሞላ ምክንያት አጋልጧል።
የተሳሳተ ምክንያት
7, 8. (ሀ) የአባካኙ ልጅ ወንድም የልጅነት ትርጉም ያልገባው በምን መንገድ ነው? (ለ) ታላቁ ልጅ ከአባቱ የተለየ የነበረው እንዴት ነው?
7 “አባቱም ወጥቶ ለመነው። እርሱ ግን መልሶ አባቱን:- እነሆ፣ ይህን ያህል ዓመት እንደ ባሪያ ተገዝቼልሃለሁ ከትእዛዝህም ከቶ አልተላለፍሁም፤ ለእኔም ከወዳጆቼ ጋር ደስ እንዲለኝ አንድ ጥቦት ስንኳ አልሰጠኸኝም፤ ነገር ግን ገንዘብህን ከጋለሞቶች ጋር በልቶ ይህ ልጅህ በመጣ ጊዜ፣ የሰባውን ፊሪዳ አረድህለት አለው።”—ሉቃስ 15:28-30
8 በዚህ አነጋገሩ የአባካኙ ልጅ ወንድም የልጅነት እውነተኛ ትርጉም እንዳልገባው አሳይቷል። አባቱን ያገለግል የነበረው አንድ ሠራተኛ አሠሪውን በሚያገለግልበት መንገድ ነበር። ለዚህም ነው አባቱን “እንደ ባሪያ ተገዝቼልሃለሁ” ሲል የተናገረው። እርግጥ ነው ይህ ታላቅ ልጅ ቤቱን ትቶ አልሄደም ወይም የአባቱን ትእዛዝ አልጣሰም። ሆኖም ታዛዥነቱ የመነጨው ከፍቅር ነበርን? አባቱን በማገልገሉ እውነተኛ ደስታን አግኝቶ ነበርን? ወይስ “በእርሻ” የነበረውን ተግባር በማከናወኑ ብቻ ጥሩ ልጅ እንደሆነ ተሰምቶት በራሱ ወደ መደሰት አዘነበለ? በእርግጥ ለአባቱ ያደረ ልጅ ከነበረ የአባቱን አስተሳሰብ ያላንጸባረቀው ለምንድን ነው? ለወንድሙ ምሕረት የሚያሳይበት አጋጣሚ ሲያገኝ ትንሽ እንኳ ልቡ ያልራራው ለምንድን ነው?—ከመዝሙር 50:20–22 ጋር አወዳድር።
9. የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ታላቁን ልጅ የሚመስሉት እንዴት እንደሆነ አብራራ።
9 የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ከዚህ ታላቅ ልጅ ጋር ይመሳሰላሉ። ሕጉን አጥብቀው ስለ ተከተሉ ብቻ ለአምላክ ታማኝ የሆኑ ይመስላቸው ነበር። እርግጥ መታዘዝ አስፈላጊ ነው። (1 ሳሙኤል 15:22) ሆኖም ለተግባር ከሚገባው በላይ ትኩረት መስጠታቸው የአምላክን እውነተኛ አምልኮ ልማዳዊ ወደሆነ ባዶ ድግግሞሽና እውነተኛ መንፈሳዊነት በሌለው ከላይ በሚታይ ለአምላክ የማደር ባሕርይ እንዲሸፈን አድርገውታል። አእምሯቸው በወጎች ታጭቆ ነበር። ልባቸው ፍቅር አልባ ነበር። ተራ ሰዎችን በእግራቸው ሥር እንዳለ ትቢያ አድርገው ይቆጥሯቸው የነበረ ሲሆን ‘ርጉም ሕዝብ’ እያሉም በንቀት ይጠሯቸው ነበር። (ዮሐንስ 7:49) ልባቸው ከእርሱ እጅግ የራቀ ሆኖ ሳለ እንዲህ ያሉ መሪዎች በሚሠሩት ሥራ አምላክ እንዴት ሊደሰት ይችላል?—ማቴዎስ 15:7, 8
10. (ሀ) “ምሕረትን እወዳለሁ መሥዋዕትንም አይደለም” የሚሉት ቃላት ተገቢ ምክር የሆኑት ለምንድን ነበር? (ለ) መሐሪ አለመሆን ምን ያህል ከባድ ጉዳይ ነው?
10 ኢየሱስ ፈሪሳውያኑን “ሄዳችሁ:- ምሕረትን እወዳለሁ መሥዋዕትንም አይደለም ያለው ምን እንደ ሆነ ተማሩ” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 9:13፤ ሆሴዕ 6:6) ቅድሚያ የሚሰጡት ተገቢ ላልሆኑ ነገሮች ነበር፤ ምክንያቱም ምሕረትን ማንጸባረቅ ካልቻሉ የሚያቀርቧቸው መሥዋዕቶች በሙሉ ከንቱ ይሆናሉ። ይህ ጉዳይ አሳሳቢ ነው፤ ምክንያቱም አምላክ “ሞት የሚገባቸው” አድርጎ ከሚቆጥራቸው ውስጥ ‘ምሕረት የለሾች’ እንደሚገኙበት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ሮሜ 1:31, 32) ስለዚህ ኢየሱስ በቡድን ደረጃ የሃይማኖታዊ መሪዎቹ ዕጣ ፈንታ የዘላለም ጥፋት መሆኑን መናገሩ ምንም አያስደንቅም። በእርግጥም ለዚህ ፍርድ የዳረጋቸው በአብዛኛው ምሕረት የለሽ መሆናቸው ነበር። (ማቴዎስ 23:33) ይሁን እንጂ በዚህ ቡድን ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ግለሰቦች እርዳታ ሊሰጣቸው ይችል ይሆናል። ኢየሱስ ታሪኩን ሲያጠቃልል አባትየው ለትልቁ ልጅ በተናገራቸው ቃላት አማካኝነት እንደዚህ ያሉትን አይሁዶች አስተሳሰብ ለማስተካከል ጥረት አድርጓል። ይህን እንዴት እንዳደረገ እንመልከት።
የአባት ምሕረት
11, 12. በኢየሱስ ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሰው አባት ታላቅ ልጁን ለማግባባት የጣረው እንዴት ነው? አባትየው “ወንድምህ” የሚለውን ቃል መጠቀሙ ምን ቁም ነገር የሚያስተላልፍ ነው?
11 “እርሱ ግን:- ልጄ ሆይ፣ አንተ ሁልጊዜ ከእኔ ጋር ነህ፣ ለእኔም የሆነ ሁሉ የአንተ ነው፤ ዳሩ ግን ይህ ወንድምህ ሞቶ ነበረ ሕያው ስለ ሆነ ጠፍቶም ነበር ስለ ተገኘ ደስ እንዲለን ፍሥሐም እንድናደርግ ይገባናል አለው።”—ሉቃስ 15:31, 32
12 አባትየው “ወንድምህ” የሚለውን ቃል እንደተጠቀመ ልብ በሉ። ለምን? ቀደም ሲል ትልቁ ልጅ ለአባቱ ሲናገር አባካኙን ልጅ “ወንድሜ” ሳይሆን “ልጅህ” ብሎ መጥራቱን አስታውሱ። በእሱና በታናሽ ወንድሙ መካከል ያለውን ቤተሰባዊ ትስስር አምኖ ለመቀበል የፈለገ አይመስልም። ስለዚህ አሁን አባትየው ለታላቅ ልጁ በተዘዋዋሪ እንዲህ እያለው ነበር:- ‘ይህ የእኔ ልጅ ብቻ አይደለም። ወንድምህ ነው፤ ሥጋህ ነው። በመመለሱ ምክንያት ደስ ሊልህ ይገባል!’ የኢየሱስ መልእክት ለአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ግልጽ ሆኖላቸው መሆን አለበት። እነዚያ ይንቋቸው የነበሩ ኃጢአተኞች “ወንድሞቻቸው” ነበሩ። በእርግጥ “በምድር ላይ መልካምን የሚሠራ ኃጢአትንም የማያደርግ ጻድቅ [አይገኝም]።” (መክብብ 7:20) በመሆኑም ኃጢአተኞች ንስሐ በመግባታቸው ታዋቂ የነበሩት አይሁዶች መደሰት ነበረባቸው።
13. ኢየሱስ ታሪኩን ድንገት ማቆሙ የትኛውን አሳሳቢ ጥያቄ እንድንጠይቅ ያደርገናል?
13 ከአባትየው ልመና በኋላ ታሪኩ በድንገት ያበቃል። ኢየሱስ አድማጮቹ ራሳቸው ታሪኩን እንዲጨርሱት የጋበዘ ይመስላል። የትልቁ ልጅ መልስ ምንም ይሁን ምን እያንዳንዱ አድማጭ የሚከተለው ጥያቄ ቀርቦለታል:- ‘አንድ ኃጢአተኛ ንስሐ በሚገባበት ጊዜ በሰማይ ከሚኖረው ደስታ አንተም ተካፋይ ትሆናለህን?’ በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ክርስቲያኖችም ለዚህ ጥያቄ መልስ ለመስጠት የሚችሉበት አጋጣሚ ተዘርግቶላቸዋል። እንዴት?
በዛሬው ጊዜ የአምላክን ምሕረት መኮረጅ
14. (ሀ) በኤፌሶን 5:1 ላይ የሚገኘውን የጳውሎስ ምክር ከምሕረት ጋር በተያያዘ መንገድ ተግባራዊ ልናደርገው የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) የአምላክን ምሕረት በተመለከተ ከየትኛው የተሳሳተ ግንዛቤ ልንጠበቅ ይገባል?
14 ጳውሎስ “እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን የምትከተሉ ሁኑ” በማለት የኤፌሶን ሰዎችን አጥብቆ አሳስቧቸዋል። (ኤፌሶን 5:1) ስለዚህም ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን የአምላክን ምሕረት ልናደንቅ፣ ወደ ልባችን ጠልቆ እንዲገባ ልናደርግና ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ይህን ባሕርይ ልናሳይ ይገባል። ይሁን እንጂ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። የአምላክ ምሕረት ኃጢአትን አቅልሎ መመልከት ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም። ለምሳሌ ያህል አንዳንድ ሰዎች ‘ኃጢአት ብሠራ ሁልጊዜ ወደ አምላክ ልጸልይ እችላለሁ፤ እሱም ምሕረት ያደርግልኛል’ በማለት በግዴለሽነት ይናገራሉ። እንዲህ ዓይነት አመለካከት ያላቸው ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ይሁዳ “የአምላካችንን ጸጋ በሴሰኝነት ይለውጣሉ” ብሎ ከጠራቸው ሰዎች ጋር የሚመሳሰሉ ናቸው። (ይሁዳ 4) ይሖዋ መሐሪ ቢሆንም ንስሐ የማይገቡ ክፉ አድራጊዎችን ግን ‘ሳይቀጣ አያልፍም።’—ዘጸአት 34:7፤ ከኢያሱ 24:19፤ 1 ዮሐንስ 5:16 ጋር አወዳድር።
15. (ሀ) በተለይ ሽማግሌዎች ስለ ምሕረት ሚዛኑን የጠበቀ አመለካከት ሊኖራቸው የሚገባው ለምንድን ነው? (ለ) ሽማግሌዎች ሆን ተብሎ የሚሠራ ኃጢአትን ችላ ብለው ሳያልፉ ምን ነገር ለማድረግ መጣር አለባቸው? ለምንስ?
15 በሌላ በኩል ደግሞ እውነተኛ ንስሐ በገቡትና ለሠሩት ኃጢአት አምላካዊ ጸጸት በተሰማቸው ሰዎች ላይ ከሚገባው በላይ ጥብቅና ፈራጅ ወደ መሆን በማዘንበል ወደ ሌላኛው ጽንፍ እንዳንሄድ ልንጠነቀቅ ይገባል። (2 ቆሮንቶስ 7:11) ሽማግሌዎች የይሖዋን በጎች እንዲንከባከቡ አደራ ስለተሰጣቸው በዚህ ረገድ፣ በተለይም ደግሞ የፍርድ ጉዳዮችን በሚመለከቱበት ጊዜ ሚዛናዊ አመለካከት መያዛቸው ተገቢ ነው። የክርስቲያን ጉባኤ ንጹሕ መሆን ያለበት ሲሆን ‘ክፉውን ሰው’ ማስወገድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ ያለው ተገቢ እርምጃ ነው። (1 ቆሮንቶስ 5:11–13) በተመሳሳይ ደግሞ ምሕረት ለማሳየት የሚያበቃ ግልጽ የሆነ መሠረት በሚኖርበት ጊዜ ምሕረት ማሳየት መልካም ነው። ስለዚህ ሽማግሌዎች ክፉ አድራጊዎችን ቸል ባይሉም ከፍትሕ ድንበር ሳይወጡ የፍቅርና የምሕረት መንገድ ለመከተል ይጥራሉ። “ምሕረትን ለማያደርግ ምሕረት የሌለበት ፍርድ ይሆናልና፤ ምሕረትም በፍርድ ላይ ይመካል” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ምንጊዜም ያስታውሳሉ።—ያዕቆብ 2:13፤ ምሳሌ 19:17፤ ማቴዎስ 5:7
16. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስን በመጠቀም ይሖዋ የባዘኑት ወደ እሱ እንዲመለሱ በእርግጥ እንደሚፈልግ አስረዳ። (ለ) እኛም ጭምር ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞችን በደስታ የምንቀበል መሆናችንን እንዴት ልናሳይ እንችላለን?
16 ይሖዋ የባዘኑት ሰዎች ወደ እሱ እንዲመለሱ እንደሚፈልግ የአባካኙ ልጅ ታሪክ በግልጽ ያሳያል። እነሱ ራሳቸው ጨርሶ የመመለስ ተስፋ እንደሌላቸው እስካላረጋገጡ ድረስ ወደ እሱ እንዲመለሱ ያቀረበላቸውን ግብዣ አያጥፍም። (ሕዝቅኤል 33:11፤ ሚልክያስ 3:7፤ ሮሜ 2:4, 5፤ 2 ጴጥሮስ 3:9) የአባካኙ ልጅ አባት እንዳደረገው ይሖዋ ወደ እሱ የሚመለሱትን ሰዎች ሙሉ መብት እንዳላቸው የቤተሰቡ አባላት አድርጎ በመቀበል በክብር ይይዛቸዋል። በዚህ ረገድ ይሖዋን እየመሰላችሁት ነውን? ለተወሰነ ጊዜ ተወግዶ የነበረ መሰል አማኝ ወደ ጉባኤ በሚመለስበት ጊዜ ምን ምላሽ ትሰጣላችሁ? “በሰማይ ደስታ” እንደሚሆን እናውቃለን። (ሉቃስ 15:7) ሆኖም በምድር ላይ፣ በጉባኤያችሁ አልፎ ተርፎም በልባችሁ ውስጥ ደስታ አለ? ወይስ በታሪኩ ላይ እንደተጠቀሰው ታላቅ ልጅ ቀድሞውኑስ ቢሆን ማን የአምላክን መንጋ ትተህ ውጣ አለውና ነው አሁን ደግሞ በደስታ የምቀበለው በማለት ትንሽ ቅሬታ ይሰማን ይሆን?
17. (ሀ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን በቆሮንቶስ ውስጥ ምን ሁኔታ ተከስቶ ነበር? ጳውሎስስ የጉባኤው አባሎች ጉዳዩን እንዴት እንዲመለከቱት መከራቸው? (ለ) የጳውሎስ ማሳሰቢያ ተግባራዊ የነበረው ለምን ነበር? በዛሬው ጊዜ እኛስ እንዴት ተግባራዊ ልናደርገው እንችላለን? (በተጨማሪም በስተቀኝ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።)
17 በዚህ ረገድ ራሳችንን ለመመርመር እንዲረዳን በ55 እዘአ ገደማ በቆሮንቶስ ውስጥ የተከሰተውን ተመልከቱ። በዚያ ከጉባኤው ተወግዶ የነበረ አንድ ሰው ሕይወቱን አስተካክሎ መምራት ጀመረ። ወንድሞች ምን ማድረግ ነበረባቸው? ንስሐ መግባቱን በጥርጣሬ በመመልከት ከእሱ መራቃቸውን መቀጠል ነበረባቸውን? ከዚህ በተቃራኒ ጳውሎስ የቆሮንቶስ ሰዎችን እንዲህ ሲል አሳስቧቸዋል:- “እንደዚህ ያለው ከልክ በሚበዛ ኀዘን እንዳይዋጥ፣ ይልቅ ተመልሳችሁ ይቅር ማለትና ማጽናናት ይገባችኋል። ስለዚህ ከእርሱ ጋር ፍቅርን እንድታጸኑ እለምናችኋለሁ።” (2 ቆሮንቶስ 2:7, 8) አብዛኛውን ጊዜ ክፉ ሠርተው ንስሐ የገቡ ሰዎች በተለይ የኃፍረትና የተስፋ መቁረጥ ስሜት እንደሚሰማቸው የታወቀ ነው። በመሆኑም እነዚህ ሰዎች መሰል አማኞችና ይሖዋ እንደሚወዷቸው የሚያሳይ ማረጋገጫ ማግኘት ይፈልጋሉ። (ኤርምያስ 31:3፤ ሮሜ 1:12) ይህ በጣም አስፈላጊ ነው። ለምን?
18, 19. (ሀ) የቆሮንቶስ ሰዎች ቀደም ሲል በጣም ልል መሆናቸውን ያሳዩት እንዴት ነበር? (ለ) ምሕረት የለሽ አመለካከት የቆሮንቶስ ሰዎች ‘በሰይጣን እንዲታለሉ’ መንገድ ሊከፍት የሚችለው እንዴት ነበር?
18 ጳውሎስ የቆሮንቶስ ሰዎች ይቅር ባይ እንዲሆኑ አጥብቆ ሲያሳስብ የሰጠው አንዱ ምክንያት “በሰይጣን እንዳንታለል፤ የእርሱን አሳብ አንስተውምና” የሚል ነበር። (2 ቆሮንቶስ 2:11) እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነበር? ቀደም ሲል ጳውሎስ የቆሮንቶስ ጉባኤ በጣም ልል በመሆናቸው ወቅሷቸው ነበር። ይኸው ግለሰብ ያለ ምንም ቅጣት በኃጢአት ተግባሩ እንዲቀጥል ፈቅደው ነበር። ይህን በማድረግ ጉባኤው በተለይም ሽማግሌዎቹ ሰይጣንን በሚያስደስት መንገድ ተመላልሰዋል፤ ምክንያቱም ሰይጣን የጉባኤው ስም እንዲጎድፍ ይፈልግ ነበር።—1 ቆሮንቶስ 5:1–5
19 አሁን ደግሞ ንስሐ የገባውን ሰው ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ባለመሆን ወደ ሌላኛው ጽንፍ ከሄዱ ሰይጣን በሌላ አቅጣጫ ሊያስታቸው ነው ማለት ነው። እንዴት? ሰይጣን የእነሱን ጨካኝና ምሕረት የለሽ መሆን እንደ መሣሪያ አድርጎ ሊጠቀም ይችላል። ንስሐ የገባው ኃጢአተኛ “ከልክ በሚበዛ ኀዘን ከተዋጠ” ወይም ቱደይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን እንደሚለው “ሙሉ በሙሉ እጁን እስኪሰጥ ድረስ ካዘነ” ሽማግሌዎች በይሖዋ ፊት በኃላፊነት ይጠየቃሉ! (ከሕዝቅኤል 34:6 እና ከያዕቆብ 3:1 ጋር አወዳድር።) ኢየሱስ ተከታዮቹ “ከእነዚህ ከታናናሾች አንዱን” ከማሰናከል እንዲቆጠቡ ካስጠነቀቀ በኋላ እንዲህ ብሏል:- “ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ወንድምህ ቢበድልህ ገሥጸው፣ ቢጸጸትም ይቅር በለው።”a—ሉቃስ 17:1–4፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።
20. አንድ ኃጢአተኛ ንስሐ በሚገባበት ጊዜ በሰማይም በምድርም ደስታ የሚሆነው በምን መንገድ ነው?
20 በየዓመቱ ወደ ንጹሑ አምልኮ የሚመለሱ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ይሖዋ ለዘረጋላቸው ምሕረት አመስጋኞች ናቸው። አንዲት ክርስቲያን እህት ከውገዳ ስለ መመለሷ ስትናገር “በሕይወት ዘመኔ ውስጥ ከዚህ ይበልጥ ደስታን የሰጠኝ ነገር እንዳለ አላስታውስም” ብላለች። ደስታዋ በመላእክት ዘንድ እንደተስተጋባ የተረጋገጠ ነው። እኛም አንድ ኃጢአተኛ ንስሐ በሚገባበት ጊዜ ‘በሰማይ በሚኖረው ደስታ’ ተካፋዮች እንሁን። (ሉቃስ 15:7) እንዲህ በማድረግ ምሕረት በማሳየት ረገድ ይሖዋን እንመስለዋለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በቆሮንቶስ የሚገኘው ጥፋተኛ ከውገዳ የተመለሰው በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ቢሆንም ይህ ለሁሉም ውገዳዎች እንደ መመሪያ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም። እያንዳንዱ ጉዳይ የተለየ ነው። አንዳንድ ጥፋተኞች እውነተኛ የንስሐ መንፈስ የሚያሳዩት ወዲያው እንደ ተወገዱ ነው። ሌሎቹ ግን ይህን የመሰለ አመለካከት ለማሳየት ጊዜ ይወስድባቸዋል። ይሁን እንጂ ከውገዳ የሚመለሱ ሁሉ አስቀድመው አምላካዊ ጸጸት እንደተሰማቸው የሚያሳይ ማረጋገጫ መስጠትና በተቻለ መጠን ለንስሐ የሚገቡ ሥራዎችን መሥራት አለባቸው።—ሥራ 26:20፤ 2 ቆሮንቶስ 7:11
[ለክለሳ ያህል]
◻ የአባካኙ ልጅ ወንድም የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎችን የሚመስለው በምን መንገድ ነው?
◻ የአባካኙ ልጅ ወንድም የልጅነትን ትክክለኛ ትርጉም ሳይረዳ የቀረው በምን መንገድ ነበር?
◻ የአምላክን ምሕረት በምናንጸባርቅበት ጊዜ ከየትኞቹ ሁለት ጽንፎች ልንርቅ ይገባል?
◻ በዛሬው ጊዜ የአምላክን ምሕረት ልንኮርጅ የምንችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
‘ፍቅራችሁን አረጋግጡለት’
ጳውሎስ ተወግዶ የነበረውን ኃጢአተኛ በተመለከተ ለቆሮንቶስ ጉባኤ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ስለዚህ ከእርሱ ጋር ፍቅርን እንድታጸኑ [“ፍቅራችሁን እንድታረጋግጡለት፣” NW] እለምናችኋለሁ።” (2 ቆሮንቶስ 2:8) “ማረጋገጥ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል “እውነት መሆኑን ማሳየት” የሚል ትርጉም ያለው ሕግ ነክ ቃል ነው። አዎን፣ ንስሐ ገብተው የተመለሱ ሰዎች እንደሚወደዱና የጉባኤው አባላት በመሆን እንደገና ተቀባይነት እንዳገኙ ሆኖ ሊሰማቸው ይገባል።
ይሁን እንጂ አብዛኛው የጉባኤው አባል ሰውየው እንዲወገድ ወይም እንዲመለስ ያደረጉት ሁኔታዎች ምን እንደሆኑ ለይቶ እንደማያውቅ መዘንጋት የለብንም። በተጨማሪም ንስሐ የገባው ሰው ቀደም ሲል በሠራው ስህተት ምክንያት በግል የተነኩ ወይም የተጎዱ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ምናልባትም ይህ ሁኔታ ዘላቂ ጉዳት አስከትሎባቸው ይሆናል። ስለዚህ እነዚህን ሁኔታዎች ግምት ውስጥ ስለምናስገባ ከውገዳ መመለስን የሚገልጽ ማስታወቂያ በሚነገርበት ጊዜ ደስታችንን የሚገልጹ ነገሮች ከማድረግ እንቆጠባለን። ከዚህ ይልቅ ለግለሰቡ በግል ስሜታችንን ልንገልጽ እንችላለን።
የክርስቲያን ጉባኤ አባላት በመሆን እንደገና ተቀባይነት ማግኘታቸውን ማወቁ ከውገዳ የተመለሱ ሰዎችን እምነት ምንኛ የሚያጠነክር ነው! ከእነሱ ጋር በመነጋገር እንዲሁም በመንግሥት አዳራሹ፣ በአገልግሎትና በሌሎችም ተገቢ ወቅቶች አብረናቸው በመሆን እነዚህን ንስሐ የገቡ ሰዎች ልናበረታታ እንችላለን። ለምንወዳቸው ለእነዚህ ሰዎች በዚህ መንገድ ፍቅራችንን ብናረጋግጥላቸው ወይም በእውነት እንደምንወዳቸው ብናሳያቸው በምንም ዓይነት መንገድ የሠሩትን ኃጢአት ክብደት አቅልለን መመልከታችን ነው ማለት አይደለም። ከዚያ ይልቅ ኃጢአተኛ አካሄዳቸውን ትተው ወደ ይሖዋ በመመለሳቸው ከሰማይ መላእክት ጋር በመሆን ደስታችንን እንገልጻለን።—ሉቃስ 15:7
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ትልቁ ልጅ በወንድሙ መመለስ ለመደሰት አልፈለገም